የሱዳን ፖለቲካ የደቀነው ሥጋት….!!!
ዮሐንስ አንበርብር
ለሦስት አሥርት ዓመታት ሱዳንን የመሩት የኦማር አል በሽር መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት በገጠመው የሱዳን ሕዝባዊ አብዮት ከተፍረከረከ በኋላ፣ የሱዳን ጦር ፕሬዚዳንቱን ከመንበራቸው በማውረድ ያደረገውን ጥገናዊ ለውጥ ሕዝባዊ አብዮቱ አልተቀበለውም።
በወታደራዊ አገዛዝ ሥር የመውደቅ አደጋውን የተመለከተው የሱዳን ሕዝባዊ አብዮት በአገሪቱ ሴቶች ጉልህ የመሪነት ድርሻ እየተመራ፣ አብዮታዊ እምቢታውን አጠናክሮ መቀጠሉ የዓለምን ትኩረት እንዲስብ አድርጎታል። በስተመጨረሻም ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አማካይነት ባበረከተችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ የሱዳን ጦር አሳይቶት የነበረው መንበረ መንግሥቱን የመቆጣጠር ፍላጎት እንዲገታና በጦሩና በተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚዋቀር ምክር ቤት ተቋቁሞ፣ በሕዝባዊ ምርጫ መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ የሽግግር መንግሥት ሆኖ አገሪቱን እንዲመራ እስችሏል።
በዚህም መሠረት ከአገሪቱ ጦርና ተራማጅ ከሆኑ በሕዝባዊ አብዮቱ የተሳተፉ የሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጣ የሽግግር ምክር ቤት የተመሠረተ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም በሲቪል አስተዳደርና በአገሪቱ ጦር ተከፍሎ ለሦስት ዓመት የተወሰነውን የሽግግር ጊዜ በመፈራረቅ እንዲመራ የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊ መደረግ በመጀመሩ፣ የሕዝባዊ አብዮቱ ፍላጎት ከመደናቀፍ ተርፏል።
በተደረሰው ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት የጦር ኃይሉ ለ21 ወራት በበላይነት የመምራት ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን፣ የሥራ አስፈጻሚነት ኃላፊነትን ደግሞ በሲቪል አስተዳደር እንዲመራ ተደርጓል።
የአገሪቱ የጦር ኃይል የሽግግር ምክር ቤቱ በመምራት የመጀመሪያዎቹን 21 ወራት አገሪቱን የማስተዳደር ኃላፊነት ሲያጠናቅቅ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ደግሞ ለቀሪዎቹ የሽግግር ወራት ምክር ቤቱን በመምራት ሱዳንን ለማስተዳደር ተስማምተዋል።
በዚህ መሠረት ከውድቀት የተረፈችው ሱዳን ወታደራዊው ኃይል በሚመራው የሽግግር ምክር ቤት እየተመራች ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥራለች።
ይሁን እንጂ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ በተለያዩ የተደራጁ ውሳጣዊ ፍላጎቶች የታመቀ ከመሆኑ ባለፈ፣ ኢኮኖሚዋ ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታትና በላይ ለሆነ ጊዜ በአሜሪካ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕቀብ መድቀቁ ተጨምሮበት፣ ፈተናዋ እንዲበዛና ለውጭ የፖለቲካ ፍላጎቶች በሯን ወለል አድርጋ እንድትከፍት አስገድዷታል።
ይህም በአንድ በኩል የሽግግር መንግሥቱ በተለይም የወታደራዊ ክንፉ ኃይሎች ባለሥልጣናት የሽግግር ወቅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ መንበረ ሥልጣኑ ለመቆጣጠር ባላቸው የግል የተደበቀ ፍላጎት፣ የኃያላን አገሮችን ፖለቲካዊ ይሁንታ ለማግኘት የእነሱን የፖለቲካ ፍላጎቶች የመፈጸም ተልዕኮ የሚገለጽ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የሽግግር መንግሥቱ ሥራ አስፈጻሚ (ሲቪል አስተዳደር) አገሪቱን ከኢኮኖሚ ፈተናዋ ለማውጣት፣ መሠረታዊ ዕርምጃ ብሎ የቀረፀውን በአሜሪካ የተጣለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ የማስነሳት ግብ ለመወጣት የአሜሪካንም ሆነ የሌሎች ኃያላን ምዕራባዊያን የፖለቲካ ፍላጎቶች ለማስተናገድ በሩን የመክፈት ግዴታ ውስጥ ገብቷል።
በዚህም በተሳናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ፍኖተ ካርታ የመቀበል አንዱ ግዴታ ሲሆን፣ በቅርቡም በአሜሪካ የተቀረፀውን ነገር ግን ሱዳን ተወክላ ያልተወያየችበትን ‹‹የአብረሃም ስምምነት›› የሚል መጠሪያ የተሰጠውን፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ተባብሮና ተቻችሎ በሰላም የመኖር ማዕቀፍን እንድትፈርም አስገድዷታል።
በሌላ በኩል ከእስራኤል ጋር ላለፉት በርካታ ዓመታት ያቋረጠችውን ግንኙነት በዕርቅ እንድትፈጽም የተገደደች ሲሆን፣ ይህም የሱዳን የፖለቲካ ልሂቃን ያልመከሩበትና ያለ ፍላጎታቸው የተፈጸመ በመሆኑ ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ አስገድዷል።
ሱዳን እነዚህንና ሌሎች ያልተገለጹ ዓበይት የፖለቲካ ተፅዕኖዎችን ለመቀበል ስትገደድ፣ የአገሪቱ ሽግግር ምክር ቤት በፅኑ እንዳልመከረበት መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚያ ይልቅ የሽግግር ምክር ቤቱን የሚመሩ ወታደራዊ ባለሥልጣናት የአገሪቱን የውጭ ዲፕሎማሲ እንዲመራ በሽግግር ቻርተሩ ኃላፊነት የተሰጠው የሲቪል መንግሥት ሳያውቅ፣ በግል የፖለቲካ ፍላጎታቸው የተቀበሏቸውና በኋላም በአገሪቱ ላይ የወደቁ የውጭ ተፅዕኖዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
አሜሪካና ኃያላኖቹ የአውሮፓ አገሮች በሱዳን ላይ ከጫኑት ተፅዕኖ በተጨማሪ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ኃያላን አገሮች በዋናነትም ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በጋራና በተናጠል ሆነው ፈርጀ ብዙ ፍላጎታቸውን በመጫን በሱዳን የውስጥ ፖለቲካ ውስጥ የሚንቀሳቀስ እጃቸው ይታያል።
ይህም በአንድ በኩል ከቱርክና ከሩሲያ ጋር ከነበራት ወዳጅነት ሸርተት ብላ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ፍላጎትን በማንፀባረቅ የሚገለጽ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በሚዋዥቀው አቋሟ ተንፀባርቋል።
በቅርቡም በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚያዋስናትን ድንበር በወታደራዊ ኃይል በመውረር እስከ መቆጣጠር ደርሳለች።
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገብባቸውን ድንበሮች በኃይል የተቆጣጠረችው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ኃይሉን በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ባደረገበት ወቅት መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በክህደት ስሜት የገለጸው ቢሆንም፣ ሰላማዊ መፍትሔን መሠረታዊ አማራጭ አድርጓል።
ለዚህም መሠረታዊ ምክንያቱ ደግሞ የዚህ የጠብ ድግስ አቀናባሪ የውጭ ኃይል እንደሆነ በመረዳት፣ ሱዳንን ምክንያት አድርጎ ወደ ተዘጋጀው የጠብ ወጥመድ ውስጥ ኢትዮጵያን ይዞ ላለመግባት ይመስላል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ሰሞኑን በሰጡት አስተያየት፣ ሱዳን ወደዚህ የድንበር ወረራ የገባችው በውጭ ኃይል ተገፍታ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን የሚገጥማቸው የውስጥ ችግር ያልበገረው ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳላቸው ያስታወሱት ጄኔራል ብርሃኑ፣ ከአንድ ዓመት በፊት ሱዳን የገጠማት ፖለቲካዊ ችግር ሱዳናውያንን ሳይጎዳ በሰላም ዕልባት እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ያበረከተችውን ሚና አውስተዋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ የገጠመውን ችግር ለመፍታት የሕግ ማስከበር ዕርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት፣ የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሶ መግባቱ ሁለቱ አገሮች ካላቸው ወዳጅነት አንፃር ከሱዳን የማይጠበቅ አሳዛኝ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሶ ከመግባቱ ጀርባ፣ የግድቡን ድርድርና ግንባታ ማስተጓጎልን ያለመ ሦስተኛ አካል መኖሩንም አመልክተዋል።
በስም ያልገጹት ይህ አካል ኢትዮጵያ የሕግ ማስከበር ዕርምጃ ላይ መሆኗን፣ ሱዳን ደግሞ ፖለቲካዊ ሽግግር ላይ መገኘቷን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀሙን ጠቁመዋል።
በሁለቱ አገሮች ድንበር አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮች አዲስ አለመሆናቸውንና በሰላም ሲፈቱ መቆየታቸውን ያስታወሱት ጄኔራል ብርሃኑ፣ የአሁኑ ግን የሦስተኛ ወገን እጅ ስላለበት ችግሩ ጎላ ብሎ መውጣቱን ገልጸዋል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላም መፍታት እንጂ ከወዳጅ አገር ሱዳን ጋር ወደ ጦርነት መግባት እንደማትፈልግ፣ ሱዳንም በሦስተኛ ወገን ከተደገሰላት የጦርነት ወጥመድ ወጥታ ችግሩን በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባትም ጥሪ አቅርበዋል።
ከወጥመዱ ጀርባ ያለው ኃይልና ወጥመዱን የማምከን ጥምረት
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰንባቸው ድንበሮች የግልጽ በመሬት ላይ የተካለለ ባይሆንም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ድንበርን የተመለከተ ጥል ወይም ውጊያ በቅርብ ዘመን ታሪካቸው አይታወቅም። ሆኖም በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ በሚገኙ ሕዝቦች መካከል የእርሻና የተፈጥሮ ሀብትን ለመቆጣጠር አልፍ አልፎ የሚነሱ ግጭቶች ተደጋግመዋል።
በተለይም አሁን የሱዳን ጦር በኃይል የያዘው የድንበር አካባቢ የተከዜ ወንዝ ወደ ሱዳን የሚፈስበትና ለእርሻ ምቹ ከመሆኑ የተነሳ፣ በድንበር አካባቢ ነዋሪዎች መካከል ግጭቶች ይደጋገማሉ። በዚህ ሳቢያ ይህንን ድንበር ለማካላል በሁለቱ አገሮች የጋራ ድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ በርካታ አሥርት ዓመታት ቢቆጠሩም፣ በሁለቱ አገሮች ውስጥ በሚነሱ ፖለቲካዊ ሁነቶች ሳቢያ ሲቋረጡና ዳግም ሲጀመሩ እስከ ዛሬ ዕልባት ማግኘት አልተቻለም።
ይህም የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ቅድሚያ የሚሰጡት አለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል። በስምምነት ድንበሩ እስኪካለል ድረስ የሁለቱ አገሮች አርሶ አደሮች ባሉበት መሬት ላይ እንዲቆዩም መስማማታቸው ይነገራል።
ነገር ግን በ2013 ዓ.ም. ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ሱዳን ጦር ሠራዊቷን አንቀሳቅሳ የድንበር አካባቢዎቹን በኃይል ተቆጣጥራለች። የኢትዮጵያ መንግሥት በወቅቱ ሙሉ የጦር አቅሙን በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ያደረገበት ወቅት በመሆኑ፣ የሱዳን ጦር የጎላ ችግር ሳይገጥመው አካባቢዎቹን ተቆጣጥሯል።
ሱዳን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጥሩ የፖለቲካ መግባባት ላይ ሆና በኃይል አካባቢዎቹን መቆጣጠሯ ለኢትዮጵያ ያልተጠበቀ ቢሆንም፣ የሱዳን መንግሥት የጦር አመራሮችና ባለሥልጣናት ግን በፈጸሙት ተግባር ሆታና ዕልልታ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን መንግሥትና የጦር ኃይል ድርጊት ግራ ቢጋባም፣ ድርጊቱ በሱዳን መንግሥትና ሕዝብ ምሉዕ ፍላጎት የመነጨ ሳይሆን በውጭ ኃይል ጫና የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ፣ ሱዳን የተደገሰላትን ጦርነት ሰከን ብላ እንድትመለከት በመምከር ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ኃይል የሚለውን አካል ማንነት በይፋ ባይጠራውም፣ ከጀርባ ያለው አካል በህዳሴ ግድቡ ላይ ፍላጎት ያለው መሆኑን በማሳወቁ፣ እንዲሁም የሱዳን ወታደራዊ ኃይል አመራሮች ከሚያደርጓቸው ፖለቲካዊ ግንኙነቶች ከጀርባ ያለው ኃይል የግብፅ መንግሥት ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል።
የግብፅ መንግሥት ይህንን የሚያደርገው ኢትዮጵያ የጀመረችው የህዳሴ ግድብ በውስጥና በውጭ ግጭቶች እንዲሰናከል ለማድረግ እንደሆነ የሚናገሩት አንድ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ በተለይ የህዳሴ ግድቡ በዘንድሮ፣ የውኃ ሙሌት ውዝግቡን ሊያመክን የሚችለውን 13 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የሚሞላበት በመሆኑ፣ የግብፅ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና የሱዳን የውስጥ የሥልጣን ሽኩቻ የፈጠረው ዕድል እንዳያመልጣቸው መንቀሳቀሳቸውን ይገልጻሉ።
ግብፅ ይህንን ለማሳካት የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሆነው አገሪቱን እየመሩ የሚገኙት የጦር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተና ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃንን በዋናነት በአስፈጻሚነት መያዟን ይገልጻሉ።
ከእርሳቸው በመቀጠል የሽግግር ምክር ቤቱ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርና ለዘብተኛ መስለው የሚንቀሳቀሱት የሱዳን ልዩ ጦር አዛዥ የሆኑትን የቀድሞ የጃንጃዊድ ሚሊሻ መሪ ሌተና ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ማሠለፏን ይናገራሉ።
ለዚህ የግብፅ ተልዕኮ በዋናነት የታጩት የሽግግር ምክር ቤቱ ሊቀመንበር በቀጣይ የሱዳን መንበረ መንግሥትን በቋሚነት በመቆጣጠር ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት፣ የግብፅን ብሎም የባህረ ሰላጤው ዓረብ አገሮችን ድጋፍ በመሻት ተልዕኮውን የተቀበሉ ሲሆን፣ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ ሌተና ጄኔራል ዳግሎ (በቅጥል ስማቸው ሃማቲም) በተመሳሳይ የሥልጣን ፍላጎት የሱዳን ጦር ድርጊትን ሳይቃወሙ ለዘብተኛ መስለው ከግብፅ ጋር እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
ሁለቱ የጦር ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ጊዜ አልፎ አልፎ ይፋዊ በሆነ መንገድ ከግብፅ የደኅንነት ኃላፊና ከግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር እንደሚገናኙም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን ድብቅ የሚመስል ግልጽ ሴራ ይረዳል ያሉት እኝሁ ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ በሱዳን በኩል ለተሠራው ደባ መልሱ ቀላልና ወደ ወጥመዱ አለመግባት እንደሆነ አቅጣጫ አስቀምጦ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ማለት ግን ነገሩ የትም አይደርስም ብሎ በዝምታ መመልከት እንዳልሆነ የሚናገሩት ባለሥልጣኑ፣ ሱዳን የኢትዮጵያ ድንበርን በኃይል ስትወር ጉዳዩ በኢትዮጵያና በሱዳን ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑን ባለሥልጣኖቿ ዘንግተዋል ብለዋል።
በመሆኑም ሱዳን ስህተቷን እንድታርም በጎረቤት ወዳጅ አገሮች በኩል እንደሚሠራ የገለጹት ኃላፊው፣ ለዚህ ተግባርም የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ኃላፊነት ወስደው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በበኩላቸው በሱዳን በኩል የተቃጣው ወረራ መፍትሔ ካላገኘ፣ አካባቢውን የመረበሽ አደጋ እንደሚፈጠር የሚገነዘቡ ጎረቤት አገሮች ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።
ከእነዚህም መካከል አንዷ ኤርትራ ስትሆን፣ የኤርትራ መንግሥት በመጀመሪያ ካደረጋቸው ተግባራት መካከል አንዱ በአስመራ የሚገኘውን የግብፅ አምባሳደር ከአገሪቱ እንዲወጣ ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኤርትራ የግብፁን አምባሳደር ባለፈው ወር መገባደጃ ላይ ስታስወጣ ግልጽ መልዕክት ለግብፅ ያስተላለፈች መሆኑን የሚናገሩት ዲፕሎማቱ፣ የሱዳን ዕብደት ለእሷም እንደሚተርፍ በመረዳት ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት የከሰላ ድንበር ጦሯን እንዳሠለፈችም ገልጸዋል።
ኤርትራ ከሱዳን ጋር በተምትዋሰንበት የከሰላ ድንበር ተመሳሳይ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ እንዳለ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከሰሞኑም በዚሁ ወሰን ላይ ግጭት መቀስቀሱን የሱዳን የዜና ምንጮች ገልጸዋል።
ኤርትራ የግብፁን አምባሳደር ከአገሯ ያስወጣችበት ምክንያት በተወሰነ ደረጃ ከኢትዮጵያ ጋር መቆሟን የሚያስረዳ ቢሆንም፣ መሠረታዊ መነሻው ግን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ዳግም የጀመረችው ወዳጅነትና በቅርቡም በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻን ደግፋ መቆሟ የግብፅ መንግሥት በመቃወሙ እንደሆነ ገልጸዋል።
በኤርትራ የነበሩት የግብፁ አምባሳደርም በኤርትራ የሚገኙ ሌሎች ዲፕሎማቶችን በተደጋጋሚ በማግኘት፣ በኤርትራ ላይ ጫና ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር በመታወቁ የተወሰደ ዕርምጃ ስለመሆኑ ይገልጻሉ።
ኤርትራ ከሱዳን በምትዋሰንበት የከሰላ ድንበር ጦሯን ማስፈሯን ተከትሎም፣ የሱዳኑ የሽግግር ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ዳጋሎ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ ኤርትራ በመጓዝ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የገባችበትን የድንበር ውዝግብ በድርደር እንዲፈታ ጥሪ ያቀረቡትንና የአደራዳሪነት ሚናውንም የወሰዱትን የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጥሪ መቀበሏ፣ የፈጸመችው ስህተት ቀስ ብሎ እንደተገለጸላት ያሳያል ብለዋል።
ምከንያቱንም ሲያስረዱ ሱዳን በኢትዮጵያ በኩል ከምትወዛገብበት ድንበር ይልቅ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያልጨረሰችው የድንበር ጉዳይ ሰፊ መሆኑን፣ እንደዚህ ዓይነት የድንበር ጉዳዮችን ከዲፕሎማሲያዊ መንገድ ውጪ ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ እንዳደረገችው በኃይል ለመመለስ መሞከር፣ ሌሎች ጥያቄ ያላቸው አገሮችም ተመሳሳይ መንገድ መከተል እንደሚችሉ መንገዱን ማሳየት እንደሆነ ይቆጠራል ብለዋል።
በመሆኑም ኤርትራም ሆነች ደቡብ ሱዳን ይገባናል የሚሉትን ድንበር በኃይል እንዲወስዱ ያበረታታል፣ ይህ ከሆነ ሱዳን በስንት ድንበር ጦሯን ታሠልፋለች የሚሉት ዲፕሎማቱ፣ የተማመነቻት ግብፅም የፖለቲካ ስህተት መፈጸሟ ሳይገለጽላት እንዳልቀረ ይገልጻሉ።
ባለፈው ሳምንት ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ የጀርመን የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር፣ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ሱዳን ተጉዘው ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ከሌሎች ባለሥልጣናት ጋር በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ አስመልክቶ መወያየታቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም በስልክ ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸው ሱዳን በፈጸመችው ስህተት በቀጣናው ሊከሰት የሚችለውን ቀውስ እንደተረዱ ያስገነዝባል ብለዋል።