>

በራራ  - ቀዳሚት አዲስ አበባ (ጸሐፊ፡ ሀብታሙ መንግስቴ ተገኘ(ፕ/ር) ምልከታ አቅራቢ፡ አንዳርጋቸው ጽጌ )

መጽሐፍ ምልከታ

የመጽሐፉ ርዕስ፡  በራራ  – ቀዳሚት አዲስ አበባ
                     (1400 – 1887 ዓም)
                     እድገት ውድመት እና ዳግም ልደት
                     ያልተነገረው የኢትዮጵያ ታሪክ
ጸሐፊሀብታሙ መንግስቴ ተገኘ(ፕ/ር)
ምልከታ አቅራቢ አንዳርጋቸው ጽጌ 

በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ በቃለ መጠይቅ፣ በጻፍኳቸው አጫጭር ጽሁፎች፣ ባሳተምኳቸው መጽሐፎች የኔ ትውልድ ከነበረው ቀናነትና የሃገር ፍቅር ባሻገር ከድንቁርና በመጣ ድፍረት የተናገራቸው፣ የጻፋቸውና የሰራቸው ስራዎች ዛሬ ሃገራችን ላለችበት አሳፋሪ ድህነት፣ ደም መፋሰስና አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ጉልህ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል በማለት በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ። ይህ ትወልድ ተምሬያለሁ የምንለውን ትውልድ ብቻ የሚመለከት እንደሆነ ልብ በሉልኝ።
ይህ በሀብታሙ መንግስቴ ተገኘ የተጻፈ መጽሐፍ የኔ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ከኔ ትወልድ በፊት የነበረውንና ከኔ ትውልድ በኋላ የመጣው ትውልድ፣ በተለይ ታሪክን አስመልክቶ የነበረው እይታ ከድንቁርና በመጣ ድፍረት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ግልጥልጥ አድርጎ በመረጃ የሚያሳይ ነው። ትልልቆቹ የሃገራችን ስመጥር የታሪክ ምሁራን ሳይቀሩ የኢትዮጵያን ታሪክ በተለይ የመካከለኛው ዘመን የሚባለውን ከ13ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ እስከ 16 ምዕተ ዓመት መጨረሻ የዘለቀውን ታሪክ አስመልክተው የሰነዱት ታሪክ ስህተት የተሞላበትና ትልቅ ጉድለት የታየበት እንደሆነ ያሳያል። በተለይ ደግሞ ወደ ዘመናችን ስንመጣ ታሪክን የፖለቲካ መሳሪያ ለማድረግ በማሰብ በጽንፈኛ ብሔርተኞች የተጻፉ መጽሐፎችና በምሁራኑ የሚቀርቡ ትርክቶች ከማናችንም በላይ በድንቁርና ላይ በተመሰረተ ድፍረት መጻፋቸው ብቻ ሳይሆን አደገኛነታቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መጽሐፍ ነው።
ይህ የዛሬው ጽሑፌ “በራራ”ን የተመለከተ የመጽሐፍ ግምገማ አይደለም። ይህን መጽሐፍ በደንብ ለመገምገም በቂ ጊዜና ትኩረት ሰጥቶ መሰራት አለበት። አሁን ያለሁበት በወከባ የተሞላ ሁኔታ ይህን ለማድረግ አላመቸኝም። ሆኖም ግን ባለፉት የገና እና የጥምቀት በዓላት ወቅት ባገኘሁት ፋታ ካነበብኳቸው መጽሐፎች መሃል “በራራ” በጣም የወደድኩት፣ ያስገረመኝ እና ብዙ ትምህርት የሰጠኝ መጽሐፍ ነው። መጽሐፉን እንዳነብ ጥቆማ የሰጠኝ ሄኖክ ብዙአየሁ የተባለ የፌስ ቡክ ጓደኛ ነው።በዚህ አጋጣሚ አመሰግነዋለሁ። ይህን መጽሐፍ በዚህ መጣጥፌ ተኮርኩራችሁ የምታነቡ ሁሉ ወደፊት እንደምታመሰግኑት ተስፋ አለኝ።
መጽሐፉ ትኩረቴን የሳበው የሚያስገርምና ትምህርት ሰጪ ስለሆነ ብቻ አይደለም። ከሌሎች የታሪክ መጽሐፍት በተለየ ከፍተኛ የፖለቲካ ትርጉም ያለው መጽሐፍ በመሆኑ ነው።  በሃሰት ትርክት ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን መውጫ ወደሌለው ገሃነም እየጎተተ ያለው የዘር ፖለቲካ የቆመበትን እረግረግ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መጽሐፍ በመሆኑ ነው። የቀደሙ የታሪክ ጸሐፍት በሰፊው የነዙትን የተሣሣቱ ትንታኔዎች የቆሙበትን መሰረት በአሳማኝ አመክንዮና ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ የዋቢ አጀብ ይንዳቸዋል፣ ያፈራርሳቸዋል። በተቃራኒው ደግሞ በማስረጃ አስደግፎ፣ በአመክንዮ አጅቦ አዳዲስ ሀሳቦችንና ሃቆችን ያሳውቃል።
ጸሐፊው ሃብታሙ መንግስቴ በተለያዩ የመጽሐፉ ገጾች ከሰጣቸው አስተያየቶች ተንስቼ የመጽሐፉ አላማ ዝም ብሎ የኢትዮጵያን የታሪክ ሁነቶችን ለመደርደር፣ መዘክሮችን ለመዘርዘር ብቻ ሳይሆን በሃሰት ትርክት ላይ የተመሰረቱ የጽንፈኛ ብሔርተኞችን በተለይ የኦሮሞ ጽንፈኛ ብሔርተኛ ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን የታሪክ ትርክት ባዶነት ጭምር ለማሳየት ነው። መጽሐፉ የታሪክን ከፍ ያለ ዋጋና ጠቀሜታ የሚያስገነዝብ ሰነድ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ታሪክ መጻፍ ያለበት የታሪክን ትርጉም ለማሳየት እንጂ ዝም ብሎ የመዝገብ ቤት ሰራተኞች ኩነቶችን እንደሚመዘግቡት አይነት ተራ የታሪክ ሁነቶች ድርደራ አይደለም የሚል እምነት ስላለኝ የሀብታሙ የታሪክ አጻጻፍ ተመችቶኛል።
በበኩሌ እንደማየው የታሪክ ትርክቶች የሃገራችን የፖለቲካ ሕይወት ቆልፈው ይዘውታል። ፖለቲካ በመሰረቱ የዜጎችና የመንግስታዊ አስተዳደር ጉዳይ መሆኑ ቀርቶ ታሪክ ላይ የተመሰረተ የልሂቃን የስልጣንና የጥቅም መራኮቻ ስፍራ ሆኖ ጤና ካጣ 40 አመታት በላይ አልፎታል። በአሁኑ ዘመን ታሪክ በፖለቲካ ሕይወታችን ላይ ያሳደረውን ትልቅ ተጽእኖ ለመቀነስ እርባና ያላቸውን የታሪክ መጽሐፍት የሚጽፉ እንደ ሃብታሙ መንግስቴ አይነት ጸሐፊዎች የሃገርና የሕዝብ ባለውለታዎች ናቸው የሚል እምነት አለኝ።
የታሪክ ጸሐፊ ሆኖ፣ በስልጣን ላይ የተቀመጡ የፖለቲካ ባለስልጣናት የታሪክን ሳይንስ፣ ፍልስፍና እና የታሪክን ጭብጦች  አስመልክተው ምንም አይነት ምሁራዊ መሰረት የሌለው ቅጥፈት ሲያሰራጩ፣ ቅጥፈቱም የሃገር ህልውና የሚያናጋ፣ የሚሊዮኖችን እልቂትና ስደት ሊያስከትል እንደሚችል እያወቀ ዝም ብሎ የሚመለከት የታሪክ ምሁርና የታሪክ ተመራማሪ ሊኖር አይገባም ባይ ነኝ። ባለፈው 30 አመታት በሃገራችን ዩኒቨርስቲዎች በታሪክ ተመራማሪነት እንሰራለን የሚሉ ትልልቅ ምሁራን ያደረጉት ይህን ነው። ፍራቻ በወለደው ዝምታ ስልጣንና ጉልበት ያላቸውን ሃይሎች የሃሰት ትርክት አጎንብሶ ማሳለፍ።  ይህን በማለቴ የታሪክ ተመራማሪዎች ለምን የፖለቲካ አክቲቪስቶች አልሆኑም የሚል መከራከሪያ እያቀረብኩ እንደሆነ ተደርጎ ተተርጉሟል። ይህ እውነት አይደለም።  የኔ ምልከታ የሚነሳው የታሪክ ተመራማሪ ምሁር ነው። አንድ በየትኛውም የእውቀት ዘርፍ የሚገኝ ምሁር እውነተኛ ለሆነ ነገር የሚወግን ነው። እውቀትና እውነት መለያየት አይችሉም።  የታሪክ ተመራማሪም በምሁሩነቱ ለእውነት መወገን ብቻ ሳይሆን ለታሪክ ሙያ መከበር ሲል መሰየፍም አለበት። እያወራሁ ያለሁት ስለታሪክ ብቻ አይደለም። በሁሉም የእውቀትና የሙያ ዘርፎች ራሳቸውን ምሁር አድርገው ስለሚያቀርቡ ኢትዮጵያወያን ፍጥረቶች ነው። በተለይ በራሱ የሙያ ዘርፍ ማለትም የታሪክ የሙያ ዘርፍ ፖለቲከኞች ሃሰት ሲያሰራጩ አንድ ምሁር ዝም ብሎ ከተመለከተ ምሁር ሊባል አይገባውም። የሃብታሙ መንግስቴን “በራራ” የወደድኩት ከላይ ካስቀመጥኩት ሰንካላ ጸረ_ምሁር አስተሳሰብ የጸዳ፣ ግብዝነት የማይታይበት እውነትን ብቻ ወግኖ የቆመ በመሆኑ ነው።
“በራራ በዋነኛነት ትኩረቱ፣ ከአርስቱ መግለጫ ማንም መረዳት እንደሚችለው፣ ዛሬ አዲስ አበባ የምንላት ከተማ ቀደም ብሎ “በራራ” የሚል ስያሜ የነበራት ትልቅ የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ከተማ ባድማና  ፍርስራሽ ላይ የተመሰረተች ከተማ መሆኗን የሚያሳይ ነው። ጸሐፊ ሃብታሙ መንግስቴ አዲስ አበባ በታላቋ የበረራ ከተማ ባድማና ፍርስራሽ ላይ መመስረቷን እንድንቀበል የሚሞግተን ማሰረጃ የሌላቸውን የወሬ ክሮች እየፈተለ፣ የሃሰት የታሪክ ትርክት ድርሳን በምናቡ ፈጥሮ አይደለም። ህልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ተጨባጭና የማያፈናፍኑ የታሪክ ማስረጃዎች እያቀረበ ነው። ይህ መጽሐፍ ከሚገባው በላይ በጥናትና በምርምር የተደገፈ መጽሐፍ ነው።
ሀብታሙ መንግስቴ በራራ የበርካታ የኢትዮጵያ ነገስታትና ጳጳሳት መኖሪያ፣ የትልልቅ ቤተ መንግስታትና ቤተ ክርስቲያናት መገኛ፣ የንግድና የጥበብ ማእከል፣ በወቅቱ ዝነኛ ከነበሩ የአውሮፓ መንግስታትና ከተሞች የመጡ ሰዎች ይኖሩባት የነበረ፣ እሷም ወደ ትላልቆቹ የአውሮፓ ከተሞች መልእክተኞች፥ የእውቀትና የጥበብ ቃራሚ ዜጎቿን ትልክ እንደነበር በበቂ ማሰረጃ አስደግፎ አቅርቦልናል። ይህ የከተማ ስልጣኔ እንዴትና በማን እንደተደመሰሰ፣ የዚህ ስልጣኔ መደምሰስ ኢትዮጵያን ከአውሮፓ ሃገራት እኩል በዘመናዊ ስልጣኔ መጓዝ የምትችልበትን ትልቅ እድል እንዴት እንዳሳጣት መረዳት የሚያስችል ፍንጭ ይሰጠናል። እኔ በበኩሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከጥቂት ምዕተ አመታት በፊት በአውሮፓ ከሚገኙ ተመሳሳይ የእምነት ተቋምት ውስጥ ይሰጡ ከነበሩ የትምህርት አይነቶች የበለጡ ትምህርቶች ትሰጥ እንደነበር አሳታውሼ እንዴት እነ እንግሊዝ እነዚህን ተቋማት በአለም ላይ ዝናቸው ወደ ገዘፈ ኦክስፈርድና ኬምብሪጅ ወደሚባሉ አለም የሚቀናባቸው ዘመናዊ ዩኒቭርስቲዎች መቀየር ሲችሉ የእኛዎቹ የለቅሶና የእርግማን ማእከሎች ሆነው ቀሩ ለሚለው  የሁል ጊዜ ጥያቄዬ መልሱን ያገኘሁት ከዚህ መጽሐፍ ነው።
ሀብታሙ በመካከለኛው ዘመን ኢትዮጵያን ሲገዛ የነበረው የሸዋ የሰለሞናዊ ስርዎ መንግስት መቀመጫ የነበረው በራራን ዋናው ከተማው ያደረገው ግዛት ውስጥ የትኞቹ “ነገዶች” ይኖሩ ነበር? እነዚህ “ነገዶች” ምን ሆኑ? ይህ ግዛት በታሪክ እጣው ምን ሆነ? በዚህ ግዛት ውስጥ የነበረው በራራ የሚባል ትልቅ ከተማ እንዴት ወደመ? እንዴትስ ዳዋ በልቶት ቀረ? ይህን ከተማ መልሶ ለመቆርቆር በራራ ከወደመ በኋላ የነገሡ የቀደሞ የኢትዮጵያ ነገሥታት ምን አይነት ጥረቶች አደረጉ? በመጨረሻም አዲስ አበባ በጥንቱ የአማራና ሌሎች “ነገዶች” ግዛት ዋና ከተማ በነበረበው በራራ በሚባል የጥንት ከተማ ባድማ ላይ  እንዴት በምኒልክ ዘመን መልሳ መገንባት እንደቻለች ሌሎች የታሪክ ምሁራን በተቃራኒው ተሟግተው ሊያሸነፉት በማይችሉት የታሪክ ዋቢና ማስረጃዎች አጀብ አስደግፎ አቅርቦታል።
ይህ መጽሐፍ በሃገራችን ጤነኛ የሆነ የፖለቲካ ሕይወት እንዲያብብ በጎ ተጽእኖ መፍጠር ይችላል ብዬ አስባለሁ። ታሪክን፣ በተለይ በመረጃ ላይ ያልተመሰረተ ታሪክን የፖለቲካ መሳሪያ ለማድረግ የሚፈልጉ የየትኛውም ዘር/ብሔር ጽንፈኞች እነሱ ከሚያወሩት አፈ ታሪክ በተሻለ መረጃ ላይ  የቆመ ተጻራሪ ትርክት ማቅረብ እንደሚቻል ሲያውቁት የታሪክን ነገር ከፖለቲካው አውጥተው ለሁላችንም የምትመች ሃገር እንዴት በጋራ እንፍጠር ወደሚል ጤነኛ እሳቤ እንዲሄዱ ሊገፋቸው ይችላል የሚል እምነት አለኝ። ወደ እዚህ ጤነኛ አመለካከት መምጣት ከተሳናቸውም፣ ሌላውም ጽንፈኛ ብሔርተኛ የራሱን ሕዝብ ከመበደል፣ ከመገፋት፣ ከመወረር፣ ስሜት መቀስቀስና የራሱን ታላቅነትና ገናናነት በማራገብ ሌላውን ዘረኛ በመረጠው የፍልሚያ ስልት ሊገጥመው የሚችልበትን አቅም በቀላሉ መገንባት የሚያስችል የተሻለ እድል ያለው መሆኑን ከዚህ መጽሐፍ ሊረዱት ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። በብሔርተኝነት ወይም በዘረኝነት ታጥሮ የሚነሳ ፍልሚያ ደግሞ የመኖር ወይም ያለመኖር ፍልሚያ ስለሚሆን በቁጥር ትልልቅ ነን የሚሉት በቁጥር በጣም አነስተኛ የሁኑትን እንኳ ለማንበርከክ እንደማይችሉ የታወቀ ነው። ጽዮናዊነትን መሰረቱ ያደረገው የትንሿ እስራኤል ብሔርተኝነት ግዙፍ አቅምና ሕዝብ ያለውን የአረብ ብሔርተኝነት አደብ ማስገዛት የቻለበት የታሪክ ሃቅ ለሁላችንም ትምህርት መሆን ይገባዋል። የሚሰማ ካለ!
የሀብታሙ መጽሐፍ ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኛ ምሁራንን ሊያስቆጣ ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ ጽንፈኛ የአማራ ብሔርተኛ ምሁራንን ሊያስደስት ይችላል። ምክንያቱም በሃብታሙ መጽሐፍ ደራሲው ያቀረበው የታሪክ ማስረጃ የሚያሳየው፣ የተወረረው፣ ባህሉ፣ እምነቱ፣ ስልጣኔው፣ ማንነቱ የወደመው ከዛም አልፎ በገዛ ርስቱ ባሪያና ገባር የተደረገው፣ ሜዳና ለምለም ከነበረው አጽመ ርስቱ ተፈናቅሎ እንደ ዝንጀሮ በሰሜን ሸዋ ገደላገደሎች ላይ ተንጠልጥሎ ኑሮውን እንዲመሰረት የተገደደው አማራው መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ይህ ሃብታሙ ያቀረበው የታሪክ ሰነድ ፣ በኢትዮጵያ የግራ ፖለቲካ አራማጆችና በኦሮሞ ጽንፈኛ ብሄርተኛ ምሁራን እስከዛሬ ሲቀነቀን የነበረውን መሰረተ ቢስ  ትርክት በጭንቅላቱ የሚያቆመው ስለሆነ ነው በተለይ በብሄርተኞች የማይወደድ ይሆናል ያልኩት።
በሌላ በኩልም “በራራ” የአማራ ሕዝብ፣ በሃገሪቱ ጽንፈኛ ብሄርተኞች የሃሰት ትርክት ያለአግባብ ሲወነጀል፣ ሲጠቃና አበሳውን ሲያይ እንደነበር፤ ሆኖም ግን መሬቱን የተቀማው፣ ባህሉ፣ ቋንቋው፣ ዘሩና ስልጣኔው የጠፋው፣ ገባርና ባሪያ ሆኖ የቀረው አማራው መሆኑን የሚያስረዳ ሰነድ ህኖ መገኘቱ በጽንፈኛ የብሔርትኝነት ጎዳና አማራውን ለመውሰድ ለሚፈልጉ ሃይሎች ትልቅ መሳሪያ እንደሚሆን አያጠራጥም። ይህ ለመሆኑ ምልክቶቹ ታይተዋልና።
በኔ እይታ ግን ሁላችንም በተረጋጋ መንፈስ “በራራ” ካነበብነው፣ ያለምንም አይን ያወጣ ወገንተኛነት ካጤንነው፣ በሃገራችን ዘርን ወይም ብሔርን መሰረት ያደረገ በተለይ በታሪክ ትርክት ላይ በመካሰስ የሚሄድ ፖለቲካ ሁላችንንም መውጫ ወደሌለው መቀመቅ ይዞን ሊወርድ እንደሚችል አይናችንን እንድንገልጥ  ያስችለናል የሚል ተስፋ ሰንቄያለሁ። መጽሐፉ ከአገራቸው መጤ እየተባሉ ለሚሳደዱትና ለሚዘረፉት ግፉአን፣ በዜግነት ፖለቲካ ለሚያምኑ እና በአጠቃላይ ስለኢትዮጵያ ለሚታገሉ አይነተኛ መሳሪያ ሊሆን ይችላል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።
ኢትዮጵያ እጅግ ውስብስ በሆኑ ማንም በቀላሉ እየበለተ ሊያስቀምጣቸው በማይችል የታሪክ ሂደት ያለፈች ሃገር ናት። ለትልልቅ ስልጣኔ መነሻ የሆኑ ትልልቅ ግዛቶች የገነቡ የፕረዥያ፣ የግሪክ፣ የሮም፣ የኦቶማንና ሌሎችም ግዛቶች ሲፈርሱ፣ የሺዎች አመታት እድሜ ያለው የኢትዮጵያ ሃገረ ግዛት ከነብዙ ችግሮች መፍረስ ያልቻለው በዚህ የተወሳሰበ ታሪካችን ምክንያት ነው። የመሬት ባለቤትነት፣ የዘር ቆጠራ፣ የገባርና የአስገባሪ፣ የወራሪና የተወራሪ የታሪክ ፍሰት በአንድ አቅጣጫ ብቻ የፈሰሰበት ሃገር አለመሆኗ ነው ኢትዮጵያን ብቸኛዋ ቀጣይነት ያላት ሃገር አድርጎ ለይቶ ያስቀራት።
ሌሎች ጥንታዊነት የነበራቸው ግዛቶች ወደ ሃገርነት መቀየር አቅቷቸው በግዛቶቹ ውስጥ የነበሩ ህዝቦች ቋንቋቸውና ባህላቸው አንዳንዴም እመነታቸው መሰረት ወደአድረጉ በርካታ ሃገሮች መበታተንና ጨርሶ መጥፋት እጣቸው ሲሆን (ከሮማን ኢምፓየር በርካታ የአውሮፓ ሃገሮች፣ ከኦቶማን ኢምፓየር በርካታ የአረብና አረብ ያልሆኑ ሃገሮች)  ኢትዮጵያ ይህን እጣ ያመለጠችው በታእምር አይደለም። በእርስ በርስ ውጊያ፣ በወረራ፣ በፍልሰት፣ በንግድ፣ በጋብቻ፣ በእምነት፣ ሕዝብና መሬት እየተቀላቀለ እንዳይበተን ሆኖ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምእራብ የተጋመደ ሃገር በመሆኑ ነው።
ይህን እውነታ ለመረዳት ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ ጉዳይ ነበር። ይህን ጥናት ያላደረገ አውሮፓና አሜሪካ ወይም አዲስ አበባ ከተማዎች ላይ ተቀምጦ በድንቁርና ላይ በተመሰረተ ድፍረት በሃገራችን ያለምንም ችግር ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ ራሳቸውን ችለው መንግስትና ሃገር መሆን የሚችሉ ከ80 በላይ የሚጠጉ ብሄር/ብሄረሰቦች ያሉባት ሃገር እንደሆነች በማስላት በ1960ዎቹ የፖለቲካ ፕሮግራም ቀርጾ ወደ ፖለቲካው ብቅ ያለው ትውልድ ዛሬ ሃገሪቱን ምን አይነት ቀውስ ውስጥ እንደጨመራት ገሃድ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ግዛት ከዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በፊት 80ዎቹ ነገዶች እራሳቸውን ችለው በነጻነት የሚተዳደሩበት ምድር ነበረ እንጅ ታላቅ የአገር መንግሥትነት ጥልቅ ታሪክ አልነበረውም የሚለው ትርክት ከአገሪቱ እውነተኛ ታሪክ ጋር ያልሰመረ እንደሆነ በበራራ የተገለጠው ታሪክ ያስረዳል። ምንም እንኳ በተለያየ ጊዜ ከፍተኛ መናወጥ ቢገጥማትም ኢትዮጵያ ከአክሱማውያን ዘመን ጀምሮ የአገረ መንግሥት ስልጣኔ ታሪኳ ሳይቋረጥ የዘለቀች የጥንት አገር እንጅ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በግፍ፣ በሐይል የመሰረቷት በድቡሽት ላይ የቆመች አገር እንዳልሆነች በበራራ ላይ የተመሰረተው ታሪኳ ምስክር ነው።
ይህ ከተሳሳተ የታሪክና የሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ያልተገናዘበ የፖለቲካ ግንዛቤ ከጥቂት ተማሪዎችና ምሁራን በሲጋራ ጭስ ከተሞሉ ክርክር ከሚደረግባቸው ክፍሎች ወጥቶ የሃገረ ኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ለመሆን በቅቷል። የሃገሪቱ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ አደረጃጀት መመስረቻ የተለየ ስልጣን፣ ጥቅምና ባላቤትነት ማደላደያ መነሻ ሃሳብ ሆኗል።  የሕገ መንግስቱ አተገባበር እንጂ ሕገ መንግስቱ ችግር የለበትም ለሚሉ ለሕገ መንግስቱ መቀረጽ መነሻ የሆነው ትልቁ ቁም ነገር ሕገ መንግስቱ የቆመበት የሃስት የኢትዮጵያ የታሪክ ትርክት መሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል። ውሸትን መሰረቱን ያደረገ ሕገ መንግስት እንዴት በሃገራችን ሰላም፣ አንድነትንና ብልጽግና ያመጣል የሚል ጥያቄ መጠየቅ ከአንድ ጤነኛ አይምሮ ካለው ፍጥረት የሚጠበቅ ነው።
በራራን የሚያነብ ሰው በመጽሐፉ ከመደነቅ አለፎ  አንድ መሰረታዊ ጥያቄ መጠየቁ አይቀርም። ይህ ጥያቄ በራራ ላይ በቀረበው የታሪክ ሰነድ መሰረት አዲስ አበባና በዙሪያው ያለው ሃገር ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በፊት ዋናው የአማራ ሕዝብና የሌሎች ነገዶች መኖሪያ መሆኑ በመረጃ ከተረጋገጠ ዛሬ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሰፈሩት ኦሮሞዎችና አዲስ አበባ የተገነባችው በኛ አጽመ ርስት ላይ ነውና ከተማዋ የኛ ናት የሚሉት የኦሮሞ ብሔርተኞች የባለቤትነት ጥያቄ በአማራውና በሌሎች ነገዶች እንዴት ሊታይ ነው የሚለው ጥያቄ ነው። የጽንፈኞቹን ቋንቋ እንጠቀምና የትኞቹ ነባር የትኞቹ መጤ ሊሆኑ ነው? ማነው ማንን  ከአጽመ ርስቴ ልቀቅ የሚለው? በዚህ መንገድ ተሄዶ ሃገራችን የገባችበትን ችግር ማቃለል ይቻላል ወይ? ይህ ዘርን መሰረት ያደረገ የመሬት የባለቤትነት ጥያቄ ወልቃይትና ራያ ላይ ያመጣውን ችግር አይተናል። ይህን ችግር እያየን ይህን ችግር በሽዎች ሊያባዛ የሚችልን ታሪክንና ፖለቲካን የቀላቀለ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ እሳቤና ተግባር ያዋጣናል ወይ?
ከ1966 ዓ.ም. ከፈነዳው አብዮት ጀምሮ በኢትዮጵያ የተከሰቱት የመንግስት ለውጦች እንዲመጡ ምክንያት የሆኑት የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በተሳሳተ የታሪክ አረዳድ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን በ“በራራ – ቀድሚት አዲስ አበባ” የተገለጠው የአገራችን ታሪክ በማያወላዳ ሁኔታ ያስረዳናል። ስለዚህ በአለፉት ግማሽ ምዕት ዓመት ገደማ እንደተከሰቱት ያሉ ለአሳፋሪ ድህነትና ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ በተሳሳተ የታሪክ አረዳድ ላይ የተመሰረቱ አፍራሽና አሉታዊ የፖለቲካ ለውጦችንና እንቅስቃሴዎችን ለመቃወም፣ በማስረጃ የተደገፈ እውነተኛ ታሪክ ያስፈልገናል።
ሃገራችን እና ማህበረሰባችን ማለቂያ ማግኝት ባልተቻለላቸው ፈተናዎችና መከራዎች ተጠምደው ምዕተ ዓመታት አሳልፈዋል።  ሆኖም ግን  ቀደም ባሉት ዘመናት ሃገራችንን የገጠሟት ፈተናዎቻችንና መከራዎቻችን በመላው አለም ከሚገኙ በተመሳሳይ ዘመን ይገኙ ከነበሩ ማህበረሰቦችና ሃገሮች ጋር ተመሳሳይ ስለነበር ለምን እኛ ብቻ ተለይተን ከፈተናና ከመከራ ነጻ አልነበርንም የሚል መማረር ወይም መቆጨት ውስጥ መውደቅ አይገባንም። አንችልም። የሰው ዘር እንደአውሬ እርስ በርሱ ሲባላ፣ አንዱ በአንዱ ላይ  ሲዘምት፣ አንዱ አንዱን በጉልበት አስገብሮ ባሪያና አገልጋይ ሲያደርግ፣ ግዛት ሲያሰፋ፣ የአንዱ እምነት ተከታይ በሌላው እምነት ተከታይ ላይ ሲነሳ፣ በአንድ እምነት ውስጥ ክፍፍሎች ተነስተው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሰዎችን እልቂት ሲያስከትሉ፣ አንድ አይነት እምነት ለማስፈን ሲባል ሰዎች በድንጋይ ሲወገሩ፣  በመስቀል ላይ ተቸንከረው፣ በእሳት ተለብልበልው በጉራዴና በጥይት ተጨፍጭፈው የሰው ልጅ ደም እንደጎርፍ ፈሶ ወንዞችን ሃይቆችን እንዲቀላቀል ባደርገ የጨለማ ዘመን የታሪክ ሂደት የሰው ዘር በሙሉ እንዳለፈ እያወቅን እኛ ብቻችንን ከነዚህ ህጸጾች ነጻ የሆነ ታሪክ ለምን አልነበረንም ብሎ መጸጽት መቆጨትና መነጫነጭ አንችልም።
ይህን የምለው ታሪክ ወደኋላ በሚያማትር ምኞት ሊሰራ ስለማይችል ነው። ታሪክ የሚሰራው በየዘመኑ በነበሩ የሰው ልጆች የእውቀት፣ የብቃትና የአቅም ማእቀፍ ውሰጥ በመሆኑ የዘመናችንን እውቀት፣ ብቃትና አቅም ወስደን ያለፉ ዘመናትን የታሪክ ክንውኖች፣ እንኳን መጥፎውን በጎውን የመለኪያ መስፈርት ማድረግ እንደማንችል ሁላችንም መገንዘብ ስለሚገባን ነው።
እንዳውም እኛ ኢትዮጵያውያን ታሪካችንን በደንብ ከመረመርን ሃገራችን በጥንቱ ዘመን ስልጣኔ ማማ ላይ የደረሰችበት ምክንያት ሌላው የሰው ዘር በአብዛኛው የምድር ክፍል መፍጠር ያልቻለውን፣ ለስልጣኔ ግንባታ የሚሆን የተረጋጋ ሰላም ያለበት ሁኔታ እንዲሰፍን፣ ደንብና ስርአት የማህበራዊ ህይወት መሰረት እንዲሆን ያስቻሉ፣ ሰፊ ማህበረሰብ ያካተተ መንግስትና ግዛት መገንባት የቻሉ ህዝቦች የኖሩባት ምድር ከመሆኗ ጋር የተያያዘ እንደነበር መረዳት አያስቸግረንም።
በጥንት ዘመን የሰው ልጅ መሰረታዊ ማህበረሰባዊ አደረጃጀቱ በትንንሽ የቤተሰብና የዘር ስብስብ ዙሪያ እንደነበር ይታወቃል። ሌላው የሚታወቀው ነገር ይህ የጥንት ዘመን ማህበራዊ አደረጃጀት የሰው ልጅ ለህይወቱ ለንብረቱና ለነጻነቱ ዋስትና የመስጠት አቅም  እንዳልነበረው ነው። በእንዲህ አይነቱ ሁኔታ የሰው ልጅ እንደ አውሬ ከመባላት አልፎ፣ ስለ ጥበብና ስልጣኔ ማሰብና መትጋት ቀርቶ ውሎ ማደር ለመቻሉ ምንም አይነት ዋስትና በሌለው የሰቀቀንና የስጋት ህይወት ይኖር እንደነበር ታሪክ ያስገነዝበናል።  ህይወትም ከየት ሊመጣ እንደሚችል በማይታወቅ ጥቃት ልትቀነጠስ የምትችልበት ሁኔታ ስለነበር “አጭር መጥፎና አስከፊ” እንደነበረች ይነገራል።
የሰው ልጅ ከዚህ ስጋት ወጥቶ ተረጋግቶ እንዲኖር እድሉን ያገኘው እርስ በርሳቸው ሲናቆሩ የነበሩ ትንንሽ ማህበራዊ ስብስቦችን በጉልበት ጨፍልቆ አንድ ትልቅ ማህበረሰብ ማድረግና ለዚህ ማህበረሰብ በሰላም መኖር ደንብና ሰርአት ማውጣት የቻሉ ትልልቅ ግዛቶችና መንግስት የተባለው ተቋም በመመስረቱ እንደሆነ ይታወቃል። ገናና የሚባሉ የቀድሞ ስልጣኔዎች በሙሉ ከግብጽ አንስቶ የፐርዥያ፣ የግሪክ፣ የሮም፣ የኦቶማን ስልጣኔዎች ትልልቅ ግዛቶች ወይም ኢምፓየሮች ከመገንባትና በትንንሽ ማህበረሰቦች አማካይነት ይደረግ የነበረውን የማያቋርጥ ግጭት እልባት ከመስጠት ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑ መረጃዎች ናቸው።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስም የዳማት፣ የአክሱም፣ የላሊበላና በበራራ መጽሐፍ የተሰነደው የመካከለኛው ዘመን ስልጣኔና ገናናነት ከሰፊ ግዛትና ሃገር መንግስት ግንባታ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።  የጥንቱ ብቻ ሳይሆን በአስራ ዘጠነኛው ምዕተ አመት መጨረሻ መላው አፍሪካ በነጮች ቅኝ ሲወድቅ ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ነጻ የሆነች ሃገር ሆና መትረፍ የቻላቸው ሰፊና ትልቅ ማህበረሰብ ያካተተ ሃገረ ግዛት በዳግማዊ ምኒልክ በመገንባቱ ነው። ሌላ ሚስጥር አልነበረውም። ኢትዮጵያ ከአስራ ስድስተኛው ምዕተ አመት መጨረሻ ጀመሮ ወድቃ በነበረበት ህልውናዋን ያናጋ አውዳሚ የእምነትና የጎሳ ጦርነቶች ውስጥና ከዛም ቀጥሎ በመጣው የመሳፍንቶች የርስ በርስ ውጊያ ውስጥ እንዳለች ለወረራ የመጡትን አረቦችን እና ነጮችን ገጥማ ቢሆን ኖሮ እያንዳንዱን የተበጣጠሰ ማህበረሰብ ነጮች ተራ በተራ እያስገበሩ፣ እኛን ብቻ ሳይሆን መላው የጥቁርን ዘር ዘላለማዊ የነጮች ባሪያ በማድረግ ሊጠናቀቅ ከሚችል የአድዋ ጦርነት ሽንፈት እጣ አናመልጣም ነበር። በአድዋ ድል አድራጊነታችን እራሳችንን ብቻ ሳይሆን መላውን የጥቁር ዘር ከዘላለማዊ ባርነት ወይም ጥፋት ማዳናችንን ብዙዎች ያውቁታል።
ሁላችንም ዛሬ በባህላችን በቋንቋችን በትውፊታችን በእምነታችን እንኮራለን የምንል ዜጎችና ማህበረሰቦች የምንኮራበትን ማንነት መዳንና መጠበቅ የቻለው ምኒሊክ በዛ ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ ወቅቱ የሚፈቀደውን ማንኛውንም ስልት ተጠቅሞ ትልቅ ሃገረ ግዛት በመገንባቱ ብቻ እንደሆነ ልንዘነጋው አይገባም።  ምኒሊክ ከሰፊው ግዛቱ ያሰባሰበው የሰው ሃይልና ሃብት ጣሊያኖችን በአድዋ ጦርነት ላይ ድል ለመንሳት ወሳኙ ድርሻ ይወስዳል።
ዛሬም ቢሆን ይህ በሚገርም የታሪክ ሂደት እንዳይለያይ ተደርጎ ተገምዶና ተሰናስኖ የኖረን  ትልቅ ሃገር በትልቅነቱ ከማስቀጠል ውጭ የትንንሽ ግዛቶች ስሜትና ፍላጎት እንዲራገብና እንዲስፋፋ በማድረግ እንደ ሃገርና ሕዝብ፣ ከሰላም እጦት፣ ከድህነት መንሰራፋት  ከመብት አለመከበር ጋር የገጠሙንን ችግሮች መወጣት እንደማንችል ታሪክ ያስጠነቅቀናል። የሀብታሙ መንግስቴ “በራራ” ከእነዚህ ማስጠንቀቂያዎች አንዱ ነው።
ሁሉም በራራን በጥሞና ያንብበው፣ አንብበን ሁላችንም በጥሞና እናሰላስል። በተለይ በራራ ውስጥ የተከተቡት የታሪክ ሁነቶችና ሃቆች የሃገሪቱን ፖለቲከኞች አደብ የሚያስገዙ ናቸውና ራሳቸውንም ሆነ ሕዝብን ከመከራ ማትረፍ እንዲችሉ ይጠቅሟቸዋል ብዬ አምናለሁ። የኢትዮጵያን ህዝብ ወይም የራሴን ብሄር ወይ ዘር ከልብ እወዳለሁ የሚል የፖለቲካ ፍላጎት ያለው ማንኛውም ፖለቲከኛ በራራን በማንበቡ ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም። የተቀረውም ማንበብ የሚችል ዜጋ ሁሉ ሊያነበው ይገባል።
**መጽሐፉ በኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞች፣ በአሜሪካ፣ እንግሊዝና አውስትራሊያ እንደሚሸጥ ተነግሮኛል። ገዝታችሁ አንብቡት ሌሎችም እንዲያነቡት ምከሩ!
አንዳርጋቸው ጽጌ
Filed in: Amharic