የህወሃት ሊቀ መንበር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከሁለት ወራት በኋላ ምን አሉ?
ምስጋናው ታደሰ
የህወሃት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከሁለት ወራት ዝምታ በኋላ በትናትናው ዕለት፣ ጥር 22፣ 2013 ዓ.ም በድምፂ ወያነ ትግራይ ፌስቡክ ገፅ በቀጥታ ለትግራይ ህዝብ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በትግራይ ላይ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በተቋረጠውና ከአሜሪካ እየተላለፈ እንደሆነ በተገለፀው ድምፂ ወያነ ትግራይ የፌስቡክ ገፅ በቀጥታ ለ13 ደቂቃዎች በድምፅ ባስተላለፉት መልዕከት ክልሉ ላይ ደርሷል ስለተባሉ ውድመቶች፣ ቀጥሏል ስላሉት ትግል ሁኔታ እንዲሁም ለትግራይ ህዝብና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል።
ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ//ር) በትግራይ ላይ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት አስመልክቶ “ህዝቡ ራሱን በራሱን የማስተዳደር መብቱን በተግባር ለማረጋገጥ በፅናት ስለታገለ የተቃጣበት ጦርነት” ያሉት ሲሆን አራት መንግሥታትና የክልሎች ልዩ ኃይሎች ተሳትፈውበታል ብለዋል።
አራቱ ብለው የጠሯቸው መንግሥታት እነማን እንደሆነ ባይዘረዝሩም “በዚህም ምክንያት የኃይል አለመመጣጠን አጋጥሟል” በማለት አስረድተዋል።
በተለያዩ ሪፖርቶች የኤርትራ ወታደሮች መሳተፋቸው የተጠቀሰ ሲሆን በቅርቡ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በተደጋጋሚ ይህ ህግ የማስከበር ዘመቻ እንደሆነና በትግራዩ ግጭት የኤርትራ ጦር አለመሳተፉን ማሳወቁ የሚታወስ ነው።
በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ያለው ትግል እንደቀጠለና በክልሉ ከነበረው ሰሜን እዝ የተገኘውን ኃይል በመጠቀም እየታገሉ መሆናቸውን አስታውሰው ” በኃይል አለመመጣጠን ምክንያት ጊዜያዊ ወታደራዊ ብልጫ ስላገኙ ይህንን ሚዛን ለመለወጥ የመመከት ትግላችንን አጠናክረን እያስቀጠልን እንገኛለን።” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በአሁኑ ወቅት በትግራይ ውስጥ የሚካሄድ ጦርነት እንደሌለና እየተደረገ ያለው የህወሓት አመራሮችን በማደን በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።
የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሰራዊት ቁጥጥር መግባቱን ተከትሎ ከሰዓታት በኋላ የህወሃት ሊቀ መንበር ከሮይተርስ ጋር በመልዕክት ባደረጉት ንግግር ትግሉ እንደሚቀጥልና “ትግሉ የራስን መብት በራስ የመወሰን እንደሆነ” ተናግረው ነበር።
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ከነዚህም አመራሮች አንዱ የህወሃት ሊቀ መንበር ደብረ ፅዮን ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ያሉበት እንደማይታወቅና ከመንግሥት ኃይሎች ተድብቀው በትግራይ ተራራማ ቦታዎች ተደብቀው እንደሚገኙ ተገልጿል።
ለእስር ማዘዣው ዋነኛ ምክንያቶቹ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል በመፈፀም፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።
ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል በጠቀሱት ትግል “ከፍተኛ ዋጋ ጠይቋል” ያሉ ሲሆን። “የህወሃት መስራች አባላት ከሚባሉት ላለፉት 45 ዓመታት ከያዙት ህዝባዊ መስመር ፈቀቅ ሳይሉ የታገሉና የመሩ፣ ያታገሉና ብዙ ድል ያስመዘገቡ አዛውንት ነባር ታጋዮች በዚህ የወረራ ጦርነት፣ በጠላት እጅ ተጎድተውብናል። ከባድ መስዋዕትነት ከፍለዋል። አሁንም እየከፈሉ ይገኛሉ። የነዚህ ጀግኖቻችን መስዋዕትነት የበለጠ ቁጭትና እልህ ያስንቀናል እንጂ ፈፅሞ ከትግላችን የሚያቆመን አይሆንም።” ብለዋል
ዶ/ር ደብረፅዮን መስዋዕት ሆነዋል ያሏቸውን ግለሰቦች በስም ባይጠቅሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና አምባሳደር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን፣ በተለያዩ የሥልጣን ቦታ ላይ የነበሩት አቶ አባይ ጸሐዬ፣ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊቱ ከድተዋል የተባሉት ኮሎኔል ኪሮስ ሐጎስ በግጭቱ ወቅት እጅ አልሰጥም በማለታቸው መገደላቸው ተገልጿል።
ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል በክልሉ ላይ ደረሱ ስላሏቸው ጥቃቶችና ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመዘርዘር ተናግረዋል።
“የትግራይ ሴቶች በተናጠልና በደቦ ይደፈራሉ። የትግራይ ሰዎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች በከፋ መገለጫና አኳሃን ይጣሳሉ፣ ይገፈፋሉ። የትግራይ መንደሮችና ዓብያተ እምነቶች፣ የትግራይ ሰራዊት ይኑርበት አይኑርበት ሳይገዳቸው የቦምቦችና የመድፎ ዒላማ ይደረጋሉ። ውድና መተኪያ የሌላቸው ቅርሶችም ይወድማሉ፣ ይዘረፋሉ። በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዳለ ከቀየው ወጥቶና ተፈናቅሎ የመከራ ኑሮ ይኖራል።” ብለዋል።
ደብረ ፅዮን ህዝቡ ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉትን ወንጀል በግልፅ እንዲቃወምና እንዲያወግዝ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ተፈፀመ ያሉት ወንጀል በገለልተኛ አካል እንዲጣራና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀው ለዚህ ተጠያቂ ናቸው ብለው የጠሯቸውን የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ወደ አለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጥሪ አድርገዋል።
በቅርቡም የአውሮፓ ሕብረት በከፍተኛ ዲፕሎማቱ ጆሴፕ ቦሬል በኩል ባወጣው መግለጫ “ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ ዘረፋዎች፣ አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶችና ስደተኞችን በግዴታ ወደ አገራቸው መመለስና የጦር ወንጀል ድርጊቶች ሊሆኑ የሚችሉ ክስተቶችን በተመለከተ በተከታታይ መረጃ ይደርሰናል” ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በግጭት ወቅት የሚከሰት ወሲባዊ ጥቃት ላይ አተኩሮ የሚሠራው ቡድን በትግራይ ክልል እየደረሰ ያለው ወሲባዊ ጥቃት እንዲገታ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።
ድርጅቱ “በመቀለ ከተማ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው የመደፈሩ ክስና በአጠቃላይ ከትግራይ ክልል የተሰሙት የወሲባዊ ጥቃት ክሶች እጅግ አሳስበውኛል” ብለዋል።
ስለቀጠለው ትግል
የፌደራል መንግሥቱ መቀለን ከተቆጣጣረ በኋላ ውጊያዎች እንደቆሙና በክልሉ ያለውን የመሰረተ ልማት ግንባታ እንደተጀመረ በተለያዩ ሚዲያዎች ገልጿል።
ደብረ ፅዮን በትናንትናው መልእክታቸው በአሁኑ ወቅት በርካቶች ወደ ትግሉ ሜዳ እየጎረፉ እንደሆነ ገልፀው ህዝቡ ያለ አንዳች ልዩነት “ጠላት” ብለው የጠሩትን ኃይል እንዲታገሉ ጠይቀዋል።
ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ባስተላለፈት መልእክት፣ በጦር ሜዳው፣ መድረኩም ሆነ፣ ድምፅ በማሰማትና በሌሎች መድረኮች ላይ ትግሉ እንደቀጠለ አስታውሰው “ሌሎቻችሁም በፍጥነት የትግሉን ጎራ ተቀላቀሉ።” በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ትግሉ እስከመጨረሻ እንደሚቀጥል ባስተላለፉበት በዚህ መልዕክት “እኛ ከመሬታችን እና ከቀያችን ለቀን የምንሄድበት ሌላ ቦታ የለንምና የተሟላ ድል እስክንቀዳጅ ህዝባዊ ጦርነት ከማፋፋም ወደ ኋላ እንደማንል ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው ይገባል።” በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።
የደብረ ፅዮንን ንግግር በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።