>

የኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ምንጭና ፋይዳው፡፡ ፋይዳ ካለው - ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ምንጭና ፋይዳው፡፡ ፋይዳ ካለው

 

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

እንደ መንደርደሪያ

እየዳኀ በነበረው  የ1954ቱ ዓ.ም. መፈንቅለ መንግስት ወቅትም ሆነ ከመፈንቅለ መንግስቱ ጥንስስ ብዙም ሳይርቅ ወይም ‹‹ በ ሐምሌ 1964 ዓ.ም.  ኢትዮጵያ በአምላክ እጆች ያለች ሚስጥራዊ ሀገር ናት ›› በሚል ትንቢታዊ ንግግራቸው የሚታወቁት አጼ ኃይለስላሴ በ1966ቱ ህዝባዊ አመጽ  በኢትዮጵያዊ ወታዳራዊ ባለስልጣናት በአብዛኛው የበታች መኮንኖች በነበሩት ከስልጣናቸው ተገርስሰው ከወደቁ በኋላ በነበረው የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ተዋናይ የነበሩት በርካታ የተማሪው ፖለቲካ ተሳታፊዎችና በርካታ የተማሩ ኢትዮጵያውያን የጎሳ ፖለቲካ ማቀንቀን እንደጀመሩ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ታሪክ እንማራለን፡፡ በአጭሩ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች የተፈጠሩት አጼ ሐይለስላሴ ከመወደቃቸው በፊት ባሉት ጥቂት አመታት ውስጥና በደርግ የመጀመሪያ አመታት ውስጥ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ በነበሩ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች አመኃኝነት እንደነበር ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ እንማራለን፡፡ በነገራችን ላይ ለጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ መፈጠር የአጼ ሀይለስላሴ መንግስት  ዋነኛ ተጠያቂ አልነበረም፡፡ የጎሳ ፖለቲካ የተወለደው በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ተደብቀው በተፈጠሩ አክራሪ ብሔርተኞች ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የአጼ ሐይለስላሴ መንግስት ቀደም ብሎ ከመወደቁ በፊት በኢትዮጵያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር ሁኔታዎችን ቢያመቻች፣ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን ቢባጅ ኖሮ አክራሪ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች የጎሳን ፖለቲካ ባለቀነቀኑ ነበር በሚል የሚከራከሩ ምሁራን ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የአጼ ሀይለስላሴ መንግስት ውድቀት የመደብ ትግል እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

 በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ምንጭ ወይም በመጀመሪያ ማቀንቀን የጀመሩት በዋነኝነት በማርክሲዝም ሌኒንዝም ርእዮት አለም የተጠመቁ ወጣት ተማሪዎች እና ምሁራን ነበሩ ፡፡ ( እነኚህ ወጣት ተማሪዎችና ምሁራን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ መጀመሪያ  ላይ የነበሩ ናቸው፡፡) 

ጎሰኝነትና አክራሪነት ( Ethinicity and Radicalization )

 አንዳንድ ምሁራን፣ በተለይም ከታወቁት የጎሳ ቡድኖች የተገኙት አንዳንድ ምሁራን በደረሱበት ድምዳሜ መሰረት  በኢትዮጵያ የጎሳ ወይም የብሔር ጭቆና  ለአክራሪ የተማሪዎች አንቅስቀስቃሴ መፈጠር ሁነኛ ምክንያት ነበር፡፡ በርካታ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካና የታሪክ አዋቂዎች በደረሱበት ድምዳሜ መሰረት በኢትዮጵያ የአክራሪ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የተፈጠረው በማርክሲስት ሊኒንዝም ርእዮት አለም ስር መስደድ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ ተገን በማድረግ የጎሳ ፖለቲካን ሲያቀነቅኑ የነበሩት የኤርትራ ነጻ አውጪ ድርጅት መሪና አባል የነበሩት፣ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት፣ የኦሮሞና ሶማሊያ ነጻ አውጪ ድርጅት መሪዎችና አባላት ነበሩ፡፡ ዋነኛ አላማና መነሻ ምክንያታቸው ደግሞ  በአማራ አገዛዝ መከራ አይተናል ተጨቁነናል በሚል ምክንያት ነበር፡፡

ሆኖም ግን ይሁንና በርካታ  የፖለቲካ ጠበብቶች ጥናት ውጤት ከሆነ የ1974ቱ ( አንደ ጎርጎሮሲያኑ

 አቆጣጠር) ወይም የ1966ቱ ዓ.ም. አብዮት መሰረታዊ ምክንያቱ  በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ

 እንቅስቃሴው የአማራ የበላይነት ስለ ነበረ አይደለም፡፡ ወይም አክራሪ ብሔርተኛ የጎሳ ፖለቲከኞች እንደሚደሰኩሩት አማራ ብለው የሚጠሩት ብሔር ሌሎች ኢትዮጵያዊ ነገዶችን ስለጨቆነ አልነበረም፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ የእነርሱ ነገር ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ አይነት ይመስላል፡፡ በተለይም ዋለልኝ መኮንን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1968 ‹‹ ታገል›› በሚባል ይታወቅ በነበረው ዝነኛው የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ህብረት መጽሔት ላይ አንድ ዝነኛ ጽሁፍ አቅርቦ ነበር፡፡ ይሄውም የሚከተለው ነበር፡፡ እንደ ተማሪ ዋለልኝ አስተምህሮ ከሆነ ( በግዜው ዋለልወኝ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪ እንደነበር ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ እንማራለን፡፡)  እንደ ዋለልኝ የማርክሲስት ርእዮት አስተምህሮ ከሆነ ‹‹ ኢትዮጵያ አንድ ሀገር አልነበረችም፡፡ ኢትዮጵያ የተሰራችው የራሳቸው ባህል፣ሙዚቃ፣ አለባበስ፣ ታሪክ ወዘተ ካላቸው ብሔር ብሔር ብሔረሰቦች ነው፡፡ ሆኖም ግን እነኚህ ብሔር ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን ማንነት እንዳያወጡ ( ፊትለፊት እንዳያሳዩ) ተከልክለው ቆይተዋል፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያ የተገነባቸው በአማራ እና ትግራይ ባህል፣ ሙዚቃ፣ አለባበስ ፣ ታሪክ ወዘተ ብቻ ነው፡፡ የሚል የሐሰት ማርክሲስት ትርክት ነበር ያቀረበው፡፡ በጣም አስገራሚው ዋለልኝ ወሎ ክፍለሀገር የተወለደ አማርኛ ተናጋሪ መሆኑ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የዋለልኝ ንግግር ወይም ጽሁፍ በርካታ ኢትዮጵያዊ ምሁራንን ያነጋገረና በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎች ያቀረቡበት ጉዳይ ነው፡፡ ገሚሶቹ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ ምሁራን የዋለልኝን ጽፍና ንግግር ዛሬም ድረስ እንደውዳሴ ማሪያም እየደገሙ ትክክል ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅትም በመመስረት ደጋፊዎቻውን ይሰብካሉ፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ እድል የሚያሳስባቸው ምሁራን ዋለልኝ ያረበው የሀሰት ትርክት ስለመሆኑ ይከራከራሉ፡፡ የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ታሪክ በመጥቀስ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብ ይሞግታሉ፡፡ ለማናቸውም  ወይም ግራም ነፈሰቀኝ የዋለልኝ ማርክስሲት ቀኖና ለጎሳ ፖለቲካ ወይም ለነጻ አውጪ ድርጅቶች መፈልፈል የራሱን አዎንታዊ አስተዋጽኦ አብርክቶ አልፏል፡፡ ኢትዮጵያን ግን ለከፋ ችግር ዳርጓት አልፏል፡፡ በእኔ የግል አስተያየት የዋለልኝ ንግግር የዚቺን የብዙ ሺህ አመታት ታሪክ ያላትን ታላቅ ሀገር ታሪክ የካደ ነበር የዋለልኝ ዲስኩርና የሀሰት ትርክት፡፡ የዋለልኝን የሀሰት ትርክት ክፉኛ ከተቹት ኢትዮጵያዊ ምሁር አንዱ ሀጎስ ገብረየሱስ ይጠቀሳሉ፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ‹‹ ይህ ሀገርን እንደመክዳት ይቆጠራል፡፡ ከዚህ ባሻግር ብሔራዊ ስሜት የሌለው ራስን መጥላት ›› ባህሪ የመነጨ ነው ሲሉ ነበር በጥናት ወረቀታቸው ላይ የጠቀሱት፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት በቅዠት አለም የተሞላ፣ ከገሃዱ አለም የወጣ፣ ለራስ ጥቅም ሲባል የአንድን ሀገር አንድነት የሚያናጋና ማህበራዊ ውድቀትን የሚቀፈቅፍ ንግግር ሲሉም  ነበር የዋለልኝ ንግግርን የነቀፉት፡፡ በነገራችን ላይ ከጎሰኞች ወይም ከአክራሪ ብሔርተኞች ጀርባ ምንም ነገር የለም፡፡ ያለው ነገር ብሔራዊ ጥላቻና ቅዠት ብቻ ነው የሚገኘው፡፡ የጎሳ ፖለቲከኞችና ተገንጣዮች የእኔ የሚሉትን ጎሳ ያቀርባሉ፣ ለመጥቀም ይሞክራሉ፣ ሌሎችን ግን የሚያገሉ ናቸው፡፡ እነርሱ ለሌሎች እወክለዋለሁ ከሚሉት ጎሳ ውጪ ላሉት ማህበረሰብ ከሚሉት የሚደማ ልብ የላቸውም፡፡ አንደው ለነገሩ አነሳሁት አንጂ እነርሱ የጎሳ ፖለቲከኞችን ማለቴ ነው የግለሰብ መብትን ማክበር ስለማይሆንላቸው ወክየዋለሁ የሚሉትን ጎሳ ሳይቀር ወደላቀ የእድገት ደረጃ ለማድረስ አይሆንላቸውም፡፡ እነርሱ ከዲሞክራቲክ አስተምህሮ ተጻራሪ አቋምን ነው የሚያራምዱት፡፡ ምንግዜም ቢሆን ህልማቸውና ግባቸው ለእኔ ብቻ የሚል ነው፡፡ ከ27 አመታት በላይ ኢትዮጵያን የገዛው ወያኔ ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል፡፡ ዛሬ ደግሞ ግዜ ያመጣቸው ተረኛ ነን ባዮች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የጎሳ ፖለቲካ ምን ያህል ከእኩልነት እሳቤ ተጻራሪ መሆኑን አስረጂ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋለልኝ ስለ እኩልነት ያነሳው ሃሳብ እውነትነት እንደነበረው የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡ ዋለልኝ አበክሮ እንዳስገነዘበው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጎሳዎች ( በዋለልኝ አባባል ብሔር ብሔረሰቦች) እኩል መብት ሊኖራቸው ይገባል የሚለው ነው፡፡ ዋለልኝ ካለፈ ግማሽ ክፈለዘመን ሊሞላው ነው፡፡ እውን የኢትዮጵያ ህዝብ የእኩለነት መብቱ ተጠብቆለት ይሆን ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡  

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የተጠበቡ የፖለቲካ ተንታኞች እንደደረሱበት ከሆነ የ1966ቱ አብዮት በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ማስመዝገቡ እውነት ቢሆንም በኢትዮጵያ ህዝብም ላይም ሆነ በፊውዳል ገዢዎች አኳያ ውድቀቶች አስከትሎ አልፏል፡፡ እነኚህም፡-

  • በታችኛው ህብረተሰብ ላይ ውድቀትን አስከትሎ ነበር (ይህም ማለት እውነተኛ ነጻነቱን አልተጎናጸፈም ነበር፣ እንደተባለው በከፍተኛ የማህበራዊ እድገት ላይ ለመድረስ አልቻለም ነበር፡፡ ወታደራዊው ስርአት ለበለጠ ጥቃት አጋልጦት ታሪካዊ ሞቱን ተግቶ አልፏል፡፡
  • በፊውዳል ገዢዎች ላይ ውድቀትን አስከትሏል ( ሀገሪቱ መቼም የማትተካቸውን ታላላቅ ሰዎች የፊውዳል ስርአት አገልጋዮች ወይም ፊትአውራሪዎች ነበሩ በሚል የወታደሮች ፈሊጥ በግፍ ተገድለዋል፡፡) በእውነቱ ለመናገር ክቡር አክሊሉ ሀብተወልድን የመሰለ ታላቅ የዲፕሎማቲክ አታሼ ወይም ሰው ኢትዮጵያ ምንግዜም ቢሆን መተካት አይቻላትም፡፡ ዛሬ የደረስንበትን የዲፕሎማቲክ ቁመና ሳስበው ከልብ አዝናለሁ፡፡ አፍራለሁ፡፡ ይህም ብቻ አልነበረም ኢትዮጵያ ሀገራችን የጃፓንን ወይም የታላቋን ብሪታንያ እድል አሳጥቷት አልፏል፡፡ ሀገሬ ኢትዮጵያ በህገመንግስት መሰረት ላይ የቆመ ንጉስ እንዲኖራት ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ይህ ገቢራዊ ቢሆን ስዊዝ ተከማቸ የተባለው ወርቅም ሆነ ብር ለኢትዮጵያ ጥቅም ላይ እንዲውል እድል በሯን ትከፍታለች ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን አልሆነም፡፡ እርግማን ይሆን ?
  • የሐገሪቷን አንድነት አናግቶ አልፏል ( ዛሬ ለደረስንበት ብሔራዊ ውርደት መነሻው የ1966ቱ ዓብዮት በአግባቡ ባለመያዙ ነበር፡፡ ማለትም ስልጣን በወታደሮች ብቻ ተጠቅልሎ በመያዙ ብዙ ኢትዮጵያዊ አርበኞችን አስኮረፈ፡፡ እነ ጄኔራል ነጋ ሀይለስላሴን ጨምሮ ዱር ቤቴ አሉ፣ ኢትዮጵያ መቼም የማትተካቸው የአንድነት ሀይሎች የደርግን ግፈኛና አምባገነን መንግስት በመቃወማቸው፣ ትግል በመጀመራቸው ምክንያት በደርግ የጭካኔ ሰይፍ አለቁ፡፡ ይህ ደግሞ ለተገንጣይ ሀይሎች መጠናከር መልካም አጋጣሚን ፈጠረ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መጠነ ሰፊ እርዳታ ሲጎርፍላቸው የነጻአውጪ ድርጅቶች  የሀገርን አንድነት መገዝገዝ በመጀመራቸው የኢትዮጵያ አንድነት እየላላ መጣ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ወታደራዊው የደርግ መንግስት በእልህና በንዴት፣ በቂም በቀል በመነሳሳት የአንድነት ሀይሎችን አጥፍቷቸዋል፡፡ ለአብነት ያህል ለእናት ኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ የታገሉትን በርካታ የኢህአፓ ታጋይ ወጣቶችን በአደባባይ እረሽኗል፣ ቀደም ብዬ እንደጠቀስለኩት 60ዎቹን የአጼ ሐይለስላሴ ባለስልጣናትን ጨምሮ የሀገር ዋርካዎችን እረሽኗል፡፡ ከገንጣይና አስገንጣይ ወንበዴዎች ጋር ሲፋለሙ የነበሩ የኢትዮጵያ የጦር ጄኔራሎችን በሸፍጥ እና በወሬ አቀባዮች የሀሰት ውንጀላ ተመርቶ እንደ ልጃቸው በሚያዩት መለዮ ለባሽ ፊት ፡፡ ኮሎኔል ታሪኩ አይኔን ፣ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ፣ ጀኔራል ፋንታ በላይ፣ ወዘተ ወዘተ ደርግ በግፍ እንዲረሸኑ በማድረጉ ነበር የሀገሪቱ በር ወለል ብሎ የተከፈተው፡፡ ሌሎች መጠነ ሰፊ ምክንያቶች ቢኖሩም በዋነኝነት የሐገር ዋርካ የነበሩ ፤ በሀገር ፍቅር ስሜት የነደዱ ታላላቅ የጦር ጄኔራሎች በረባ ባልረባው ምክንያት በደርግ አመራሮች ስለተገደሉ ነው ወያኔ የተባለ እባብ ምኒሊክ ቤተመንግስት ዘው ብሎ የገባው ከዚያም ሀገሪቱን ለ27 አመታት ሲነድፋት የነበረው፣ አርቲስቱ የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርዳል ብሎ በዚያም ጥኡም ድምጹ እንዳዜመው  በመጨረሻም ታሪካዊ ሞቱን የተጋተው፡፡) 

የምሁሩ ግጭትና ጎሰኝነት ( Elite conflict and Ethnicization )

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ሊወለድ የቻለው በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ የነበሩ በርካታ ተማሪዎችና ምሁራን በማርከሲስት ሌኒንስት ርእዮት አለም ፍቅር ስለወደቁ ነበር ፡፡ እንደ ብዙ ምሁራን ጥናትና ምርምር ውጤት ከሆነ በማርክሲስት ርእዮት አለም ፍቅር የወደቁት  ደግሞ ፍጹም የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ አሸቀንጥሮ በመጣል ነበር፡፡ እንደ ወያኔ ያሉት ቡድን አባላት በአልባኒያ ሶሻሊስት ፍቅር ሲወድቁ፣ ሌሎች ደግሞ የጆሴፍ ስታሊን ኮሚንስት ፍልስፍና አራማጆች ነበሩ፡፡ የእነ ሆቸሚኒ፣ ቼኩቬራ ወዘተ አድናቂዎችም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም፡፡ በነገራችን ላይ በተማሪው እንቅስቀሴ ላይ የነበሩትን ሁሉንም ( በደምሳሰው) ምሁራን እና ተማሪዎች የጎሳ ፖለቲካ አቃንቃኞች ነበሩ ብሎ መጻፍ የታሪክ ክህደት ይሆናል፡፡ አብዛኛዎች የያ ትውልድ ወጣቶችና  ምሁራን በሀገር ፍቅር ስሜት የነደዱ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሉ ህይወታቸውን ቤዛ አድርገው ያለፉ ናቸው፡፡ ስለሆነም የአሁኑ ትውልድ ሚዛናዊ እንዲሆን ከፈለገ ህሊና በፈጠረባቸው እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ምሁራን  ደክመው ለፍተው ያዘጋጁትን የታሪክ መጽሐፍትን፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክን መጽሐፍት  መመርመር አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡  በነገራችን ላይ የአክራሪ  ምሁራን ጥያቄዎች እጅጉን የተወሳሰቡ ናቸው፡፡ ስለሆነም ጥያቄዎቻቸው በብዙ ምክንያቶች እንደተሞሉ ይከራከራሉ፡፡ ለማናቸውም አብዮት ሊፈነዳ የሚቻልባቸው ምክንያቶችን የፖለቲካ ምሁራን በአምስት የንድፈ ሃሳብ ትምህርት ቤቶች ይመድቧቸዋል፡፡ እነኚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡ የስማቸውን የአማርኛ ቀጥተኛ ትርጉም በአጭሩ ማሰቅመጥ ሰለቸገረኝ የእንግሊዝኛ ስማቸውን ስላሰፈርኩ አንባቢውን ይቅርታ እጠይቃለሁኝ

1 ዘቲዎሪ ኦፍ ዲፕራይቬሽን .(The theory of deprivation )

በአንዲት ሀገር አስከፊ ችጋር ከተከሰተ የሰራተኛው መደብ ስነ ልቦና ይጎዳል፣ ተስፋ ይቆርጣል ይሄና ሌሎች ምክንያቶች ተጨምረው አብዮት ሊፈነዳ ይቻለዋል፡፡

  1. ዘፈንክሽናል ስትራክቸራል አፕሮች (The functional structural approach  )

በአንድ ሀገር የሚኖሩ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች መብት ካልተከበረ፣ የእኩልነት መብት ከተገፈፈ አብዮት ሊቀጣጠል ይቻለዋል፡፡ አንደኛው የበይ ተመልካች ሌላው ብቸኛው የሀብት ተጠቃሚ ከሆነ አብዮት አይቀሬ ይሆናል፡፤

  1. የማርክሲዝም ሌኒንዝም ንድፈ ሀሳብ (The Marxist  Leninist-  theory ) 

በምርት ሀይሎች እና መደብ ትግል እንቅስቃሴ ምክንያት አብዮት  ይነሳል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በሌላ አነጋገር አብዮት የሚጀምረው በወዛደሩ ትግል ነው ብለው ያምናሉ ፡፤ ወይም ወዘወአደሩ ( ላብአደሩ) በካፒታሊስቱ በሚደርስበት ጭቆና ምክንያት አብዮት ይቀሰቀሳል፡፡

4.State Centred approach ( መንገስትን ማእከል ያደረገ)

የአንድ ሀገር መንግስት ሙሉበሙሉ እየተዳከመ ሲመጣ አብዮት ሊፈነዳ ይቻለዋል የሚል ፍልስፍና አላቸው፡፡

5.Poltical conflict theory ( የፖለቲካል ግጭት ንድፈ ሀሳብ)

ይህ ንድፈ ሃሳብ የሚያተኩረው አጉል የሆነ የምሁራን ፉክክር ላይ ነው፡፡ በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ምሁራን በአጉል ፉክክር ውስጥ ከወደቁ፣ ባለፉት ምእተ አመታት ላይ የተከሰቱ ችግሮች ላይ ብቻ ካተኮሩ፣ ወይም ያልነበሩ ችግሮችን እንደነበሩ በማስመሰል አዲስ ትርክት የሚፈጥሩ ከሆነ፣ ለሀገሪቱ ነባራዊ ችግር መፍትሔ መሻት ትተው ርሰበርስ በመናቆር ጊዜያቸውን የሚባክኑ ከሆነ፣ ለብሔራዊ እርቅ ዝግጁ ካልሆኑ፣ ቁጭ ብለው በሰከነ መንፈስ በመነጋገር ወደ መስማማት መድረስ ካቃታቸው፣ በሀገራቸው ታሪክ፣ሰንደቅ አላማ፣ ስም ወዘተ ወዘተ መስማማት ካቃታቸው በዛች ሀገር ላይ ድንገት የሚፈነዳ አብዮት ይከሰታል፡፡

ማስታወሻ፡- ከላይ በተራ ቁጥር አንድ እና ተራ ቁጥር  ሶስት ላይ የሰፈሩት ንድፈ ሀሳቦች ውስጥ በተጠቀሱት ምክንያቶች የሚቀሰቀስ አብዮት አብዛኛውን ማህበረሰብ ማለትም ሰፊውን ህዝብ የሚያሳትፍ ይሆናል፡፡

ለምን ይሆን በርካታ ምሁራን የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኝ ለመሆን የሚፈልጉት ?

ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ብዙዎች የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች እንደሚሉት ተገፍተናል፡፡ ከሀገሪቱ ብሔራዊ ኬክ እኩል ተካፋይ አልበርንም፣ የምንወክለው ጎሳ ብሔራዊ ጭቆና ደርሶበታል ባይ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ለዚህ ክሳቸው በቂ ማስረጃ ማቅረብ አይሆንላቸውም፡፡ እውነቱ ግን ለየቅል ነው ብዙዎች ወደ ስልጣን መወጣጫው ቀላሉ መንገድ ወይም መሰላል የጎሳ ፖለቲካ ነው ብለው አምነዋል፡፡ ባለፉት ሰላሳ አመታትም ያየነው መራር እውነት ይሄው ነው ፡፡ በጎሳ ፖለቲካ የተደራጁት የስልጣን ጥማታቸውን ለማርካት ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ ለስቃይ ዳረጉት እንጂ ተድላና ደስታ አላመጡለትም፡፡ ለአብነት ያህል ለሃያ ስምንት አመታት የሀገሪቱን ማእከላዊ መንግስት የተቆጣጠሩት ወያኔዎች፣ ለሰላሳ አመታት የታገሉት ወያኔዎች ለአጠቃላዩ የትግራይ ተወላጅ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ እናቶቻችን በመጨረሻ ላይ ጥለውት ያለፉት ችጋር፣ መከራና ስደት ነው፡፡ ዛሬ በሰሜናዊት ኢትዮጵያ ትግራይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ የትግራይ ተወላጆች ለረሃብ፣ ለችጋር ተጋልጠዋል፡፡ ይህ ደግሞ በዋነኝነት በጎሰኛውና አምባገነኑ ወያኔ ይከተል በነበረው ተሳሳት የፖለቲካ አካሄድ ነው፡፡ ሀሰት የሚል ካለ መከራከር ይችላል፡፡ እርግጥ ነው ዛሬ ወያኔ የለም ፡፡ ላይመለስ ሄዷል፡፡ እርሱ ዘርቶት የሄደው የጎሳ ፖለቲካ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ዜጎችን ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡ ስለሆነም በትግራይም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች እንደ ምእራብ ወላጋ ሆሮጉዱሩና መተክል ዞን የተከሰቱትን የሰብዓዊ ቀውሶች መታደግ በዋነኝነት ሀላፊነቱ የኢትዮጵያ መንግስትና የኢትዮጵያ ህዝብ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅት አቋቁሞ መደራጀት መብት መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  የጎሳ ፖለቲካን ከዲሞክራቲክ አስተምህሮ  አንጻር ለማስታረቅ ከባድ ይመስለኛል፡፡ ለዲሞክራቲክ አስተምህሮ የሚደማ ልብ ያላቸው በርካታ የፖለቲካ ምሁራን አበክረው እንደሚያቀርቡት ምክረ ሀሳብ  ከሆነ ዜጎች ከጎሳ መሰረት ወጥተው በአስተሳሰብ ወይም በርዮት አኳያ ቢደራጁ ዲሞክራሲ ስር ይሰዳል ፡፡ ለአብነት ያህል የምእራብ አውሮፓ ሀገራት ዜጎች ከጎሳ አስተሳሰብ ከወጡ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በአውሮፓ ምድርም ሆነ በተባበረችው አሜሪካ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ( አብዛኛዎቹ ማለቴ ነው) መሰረታቸው አስተሳሰብ ወይም ርእዮት አለም ነው፡፡ ስለሆነም በተጠቀሱት የአለም ክፍሎች ዲሞክራሲ ስር ሰዷል፡፡ ዜጎቻቸው በየትኛውም የሀገራቸው ክፍል የመዘዋወር፣ የመስራት መብቶቻው ተከብረውላቸዋል፡፡ የጎሳዎች ግጭት የሚባል ዜና ከተሰማ ብዙ አመታት ተቆጠሩ፡፡ በአጭሩ ነጻነታቸው ምሉሄበኩልሄ ነው ባይባልም  የሰውነት ክብራቸውን ማንም ዘሎ ሊገፈው አይቻለውም፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ በተለይም በአፍሪካ ምድር ዛሬም ከጎሳ አስተሳሰብ መውጣት ያልቻለች አሳዛኝ አህጉር ናት፡፡ ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ጊዜ ( ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም.) በመሃከለኛው አፍሪካ የተነሱ አማጽያን ጎሳ ተኮር ጥቃት በመጀመራቸው በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የዛች ሀገር ዜጎች በሀገራቸው ምድር ስደተኛ ሆነዋል፡፡ ወደ ዘጠና ሁለት ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሰደዳቸውን ከአልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሰማሁ፣ ይሄን ተከትሎ የአለሙ ብይነ መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ እየተጣደፈ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ አማጺው ሀይልና የሀገሪቱ መንግስት የሚፋለሙት የአልማዝና ወርቅ ማእድን ሀብትን ለመቀራመት አስበው እንጂ ለምልአተ ህዝቡ አስበው አይደለም፡፡ ከጀርባው ደግሞ የአለም የጥሬ ሀብት ጥማተኞች እጅ አለበት፡፡ የተባበሩት መንግስታት ጦር ባለበት ሀገር ይህን ያህል ቁጥር ያለው አፍሪካዊ መሰደዱ ያሳዝናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ቅዳሜ ጥር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከሚዘግቡ የዜና አውታሮች እንደሰማሁት ከሆነ በምእራብ ወለጋ ጎሳ ተኮር ጥቃት እንደተፈጸመ ሰማሁና በእጅጉ አዘንኩ፡፡ አውሮፓውያኖችም ሆኑ የተባበረችው አሜሪካ ከጎሳ አስተሳሰብ በተለይም መሰረቱን ጎሳ ላይ ካደረገ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅት ከተገላገሉ ከመቶ አመታት በላይ የሆናቸው ቢሆንም፣ በአፍሪካ ምድር ዛሬም የጎሳ ፖለቲካ ስላልተወገደ አፍሪካ ከችግር መውጣት አልቻለችም፡፡ በነገራችን ላይ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በጎሳ ላይ መሰረቱን ያደረገ የፖለቲካ ድርጅት እንዳይመሰረት መከልከላቸው ቢታወቅም፡፡ በአፍሪካ ምድር ቅኝ ገዢዎች ዘርተው የሄዱትን የጎሳ ፖለቲካ አሜኬላ ወይም ግዜውን እየጠበቀ የሚፈነዳውን የጎሳ ፖለቲካ ፈንጂ ማምከን የሆነላቸው አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ ጎሳ ላይ መሰረታቸውን ያደረጉ በማናቸውም የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች አነርሱ ወክለነዋል ከሚሉት ጎሳ ውጪ ያሉትን ማህበረሰብ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ለማክበር አይሆንላቸውም፡፡ የጎሳ ፖለቲካ የግለሰብ መብትን ለማስከበር ተፈጥሮአዊ ባህሪው የሚፈቅድለት አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ለአብነት ያህል በጎሳ አጥር በተከለለ አንድ ክልል አንድ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ግለሰብ የአካባቢውን ቋንቋ መናገር ባለመቻሉ ምክንያት ብቻ ሌላ እኩል ዲግሪ ከጨበጠ የአካባቢውን ቋንቋ መናገር ከሚችል ግለሰብ ወይም ከአካባቢው ተወላጅ ግለሰብ ጋር ስራ ለመቀጠር ተወዳድሮ የቀረበለትን የቃል ፈተና ወይም ቃለ መጠይቅ በአጥጋቢ ውጤት ቢያልፍም  ስራ የማግኘት መብቱ ሊጣስ ይችላል፡፡ ይህ የአንድ የግለሰብ ስራ የማግኘት መብት ስለመጣሱ ማሳያ ነው፡፡ ሌላ ተጨባጭ ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህል በቤንሻጉል ጉሙዝ ክልል መተክል ዞን ኢትዮጵያዊ ዜጎች በግፍ በአረመኔዎች ሲገደሉ በክልሉ የሚነቀሳቀሰው ወይም የክልሉ ገዢ ፓርቲ ድምጹ አልተሰማም፡፡ ወይም ድርጊቱን ለማስቆም ያደረገው ጥረት አጥጋቢ አልነበረም፡፡ ሌሎችም የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ በርእዮት አለም አኳያ የተደራጁ የስም የፖለቲካ ድርጅቶች ልባቸው አልደማም ነበር፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር የጎሳ ፖለቲካ ወይም እውነተኛ ያልሆኑ የስም ፖለቲካ ድርጅቶች ( በርእዮት አለም አኳያ ተደራጀን የሚሉትን ማለቴ ነው) ምንያህል የሰብዓዊ ስሜትን እንኳን ሊያሳሳ እንደሚቻለው ነው፡፡ በአጠቃላይ የጎሳ ፖለቲካ በአንዳንድ ምሁራን አጉል እና ምክንያታዊ ባልሆነ የፖለቲካ ፉክክር የሚፈጠር ነው ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡ እንድነ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ እና ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ የመሳሰሉ ጎምቱ ኢትዮጵያዊ ምሁራን በተለያዩ የጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከሆነ ዛሬ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የጎሳ ፖለቲካን ከማቀንቀን አኳያ መነሻው አንዳንድ ምሁራኖች ቢሆኑም፣ በሰፊው የናኘው ግን የኢትዮጵያን ገበሬ ከጎሳ አኳያ ማደራጀት ሲጀምሩ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል የትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት የነበረው  ወያኔ አብዛኛው ጦሩ ገበሬ ነበር፡፡ ሌሎችም የነጻ አውጪ ድርጅችም ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፡፡

ከአማራ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ነው ብለው በርሃ ከገቡት፣ ኋላም አስመራና አዲስ አበባ ከተማ ላይ መንግስት ለመመስረት ጊዜና ታሪክ የፈቀደላቸው ከትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት እና ኤርትራ ነጻ አውጪ ድርጅት እንደነበሩ ሁላችንም የምናውቀው ይመስለኛል፡፡ ከሰላሳ አመት በፊት አንዲት ሉአላዊት ሀገር ኤርትራን ስለሚመራው አገዛዝ የምለው የለኝም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ወያኔ ስላስገኘው ፋይዳ ወይም ውድቀት ማንሳት ይቻላል፡፡ በአጭሩ ወያኔ ለኢትዮጵያም ሆነ እወክላለው ለሚለው የተግራይ ተወላጆች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻችን እህቶቻችን፣ አባቶቻችን፣ እናቶቻችን ነጻነትን ማጎናጸፍ አልቻለም፡፡ ያሰፈነው ነገር ቢኖር የትግራይ ኤሊቶችና ጥቂት ባለሀብቶችን መፍጠር ነበር፡፡ የራሱን የፖለቲካ ኤሊት መፍጠር ሌሎች ተወዳዳሪ ኤሊቶችን ማጥፋት ነበር ስራው፡፡ በመጨረሻ ራሱ መጥፋቱ ታይቷል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ለዲሞክራሲ ስርአት የተዘጋጀ አይደለም፡፡ የጎሳ ፖለቲካና ዲሞክራሲ ለየቅል ናቸው፡፡ 

እንደ መውጫ 

በየትኛውም አለም ፣ በተለይም በኢትዮጵያ ምድር የጎሳ ፖለቲካ ለህግ የበላይነት ፣ ለዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች መከበር እንደማይረዳ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የጎሳ ፖለቲካ ከግለሰብ መብት አንጻር  ተጻራሪ  ጽንሰ ሃሳብ  እንደሆነ ብዙዎች የፖለቲካ አዋቂዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባለፉት ሰላሳ አመታት ውስጥ በነቢብም ሆነ በገቢር የጎሳ ፖለቲካ ካመጣልን ፋይዳ ይልቅ ያመጣብን መዘዝ መጠነ ሰፊ እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይገነዘቡታል ብዬ አስባለሁ፡፡ የአንድ ሀገር ህዝብ ለአካባቢ ልማት፣ ሙዚቃና ባህላቸውን ለማሳደግ እና ለሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች በጎሳ አንጻር ክፋት የለውም ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን የፖለቲካ ድርጅትን በጎሳ መሰረት ላይ ሆኖ ማቋቋም መብት ቢሆንም መዘዙ ብዙ ይመስለኛል፡፡ ለማናቸውም የዛሬውን ጽሁፌን የምቋጨው አቤቱኪቻው ሰሞኑን በማህበራዊ ድረገጽ ላይ በለጠፋት መራር ስላቅ ይሆናል፡፡ ሰላም

‹‹ በልጅነታችን ከእኩዮቻችን ጋር ስንጣላ ጫማህን አውልቅ እና ይዋጣልን ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ለክርክር መድረክ ላይ የምትወጡ ሰዎች አፈር ስሆን ብሔራችሁን አውልቁ እና ይዋጣልን፡፡

Filed in: Amharic