>

‹የመጣንበትን የማያውቁ፣ የምንሄድበትን አያውቁም!›› (አሰፋ ሀይሉ))

 

‹‹የመጣንበትን የማያውቁ፣ የምንሄድበትን አያውቁም!››

(አሰፋ ሀይሉ
ሣህለ ሥላሴ — ንጉሠ ሻዋ፣ የጉራጌ፣ የጋላ፣ የሻንቅላ፣ ያዳል፣ የከረዩ፣ የይፋት፣ የወሎ፣ ያረመኔ የክርስትያን የሁሉ ንጉሥ!

ወጣቱ መርዕድ አዝማች ሣህለ ሥላሴ በአባቱ እግር ተተክቶ ወደ መሪነት ወንበሩ ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻና ክፍተት የተወሰነ ግርግር፣ ውንብድናና አመጽ ባገሩ ተከስቶ ነበር፡፡ ብዙ አማሮች የበዙባቸውም፣ ኦሮሞዎች የሚኖሩባቸውም ግዛቶች አመጽ አስነስተዋል፡፡ ስለነዚህ አመጾችና ስለ ሣህለ ሥላሴ ዘመቻዎች በብዙ የታሪክ ድርሳኖች የተባለ ነው፡፡ ብዙ ተብሏል፡፡ ላሁኑ ሙሉ በሙሉ የምጠቅሰው በዶክተር ሥርግው ሀብለሥላሴ መጽሐፍ የሰፈረውን ውብ ትረካ ነው፡፡ በትረካው ግርጌ ጥቂት የራሴን ማስታወሻና ቀጣይ የምመለስበትን የአንድ መሳጭ ታሪክ ዳር-ዳር አስፍሬያለሁ፡፡ አሁን በቀጥታ ወደ ሥርግው ትረካ አሻግራችኋለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡
«በብጥብጡ ጊዜ ከዓመፁት የአማራ አገሮች አንዱ ሞረት ነበረ፡፡ ይህ አገር ቀደም ሲል በወሰን ሰገድ ዘመን ተሸንፎ የገበረ ነው፡፡ ከወሰን ሰገድ ሞት በኋላ በተፈጠረው ብጥብጥ በመጠቀም አፈነገጠ፡፡ የሴራው ቀንደኛ ኃይሉ የተባለው የጥዱ ልጅ ነበረ፡፡ ሣህለ ሥላሴ ለዚህ ዘመቻ ቅድሚያ ሰጥቶት ነበረ፡፡ ምክንያቱም የእዚህ አገር ማመፅ እንደገና ለደብረ ሊባኖስ መመዝበር ምክንያት ስለሆነ፡፡ ሞረት ማመፁ በኦሮሞዎቹ ዘንድ በተሰማ ጊዜ ደብረ ሊባኖስን ወርረው ከመነኮሳቱ ብዙዎችን ገደሉ፡፡ አስፋ ወሰን ያሠራውንም ቤተ ክርስትያን አቃጠሉ፡፡ ያመለጡት ጥቂት መነኮሳት ጽላቱንና ከንዋየ ቅድሳቱ የቻሉትን ያህል ይዘው እንደገና ወደ ቆላው የኦሮሞ ፈረሰኛ ከማይደርስበት ተሰደዱ፡፡ ይህ ሣህለ ሥላሴን ስለ አስቆጣው ዘመቻውን ወደ እዚያ አሠማራ፡፡
«ሣህለ ሥላሴ የአደረገው ይህ ዘመቻ ግቡን መትቶአል፡፡ ሞረትን አንድ አካል አንድ አምሳል ለማድረግና ዳግመኛ ከእንደዚህ ያለ አድራጎት እንዲታቀብ ለማድረግ በጋብቻ መተሳሰሩ ስለሚጠቅም የባላባቱን የኃይሉን ሴት ልጅ ወይዘሮ በዛብሽን አገባ፡፡ እርሷም አራት ሴቶች፣ ሁለት ወንዶችን ወልዳለታለች፡፡ ወንዶቹ ልጆች ኃይለ መለኮትና ሰይፈ ሥላሴ (ሠይፉ) ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው ኃይለ መለኮት ወደፊት እንደምናየው የአባቱን አልጋ ይወርሳል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች አራት ወንዶች ልጆች ኃይለ ሚካኤል፣ ዳርጌ፣ ካሰኝና ባሕርይ የሚባሉ ነበሩት፡፡ የመጨረሻ ሁለቱን ከስማቸው በቀር የምናውቀው የለንም፡፡
«የሞረቱ ዓመፅ ከተወገደ በኋላ ጥቂት ቆይቶ መርሐ ቤቴ ሸፈተ፡፡ አስተዳዳሪው ተገኑ የሚባል ሰው በነበረ ጊዜ አገሩ በሰላም እየገበረ ይኖር ነበረ፡፡ ችግሩ የተፈጠረው አቶ ተገኑ ከሞተ በኋላ ነበር፡፡ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ጸጥታውን በቅርብ የሚቆጣጠሩ ጥቂት ወታደሮች ትቶ ነበረ፡፡ እነሱን ሕዝቡ ገደላቸው፡፡ ከዚያን በኋላ አገር ስለ ተበጠበጠ የተገኑ ማጉደል ይበልጥ ታወቀ፡፡ ይህንኑ በተመለከተ እንዲህ ተብሏል፡-
‹‹የላይ ቤት የታች ቤት ነበርኮ ተገን
ካልሄደ ካልሞተ ሰው አይመሰገን፡፡››
«ሣህለ ሥላሴ በዚህ ነገር ስለተቆጣ የወታደሮቹን ደም ለመበቀል የይፋትንና የሞረትን ሰዎች አዘመተባቸው፡፡ ይፋት በምሥራቅ ሞረት በምዕራብ በኩል ዘምተው አጣድፈው አሸነፉት፡፡ እንደሚባለው የይፋት ሴቶች ወንዱን በጥፊ እያሉ ማረኩት፡፡ ይህን በተመለከተ የሚከተለው ግጥም ተደርሷል፡-
‹‹አወይ መርሐ ቤቴ ሁለት ዕዳ ከፋይ
ይፋቶች በጥፊ ሞረቶች በክፋይ፡፡››
«ይህ እንዲህ ከተከናወነ በኋላ አሁን ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመቻውን በኦሮሞዎች ላይ አሠማራ፡፡ መጀመሪያ የዘመተው በቅርቡ በሚገኘው በገላን ኦሮሞ ላይ ነበረ፡፡ ስለዚሁ እንዲህ ተብሎ ተፎክሯል፡-
‹‹ዲና* ተነሥቶ ካንጎለላ ላይ
ሸኖ ማራኪ ገርማማ ገዳይ፤
ዲና ቢነሣ ከማሀል ማማ
ገብሮ አደረ እስከ ወጨማ፡፡››  /*ዲና የሣህለ ሥላሴ የፈረስ ስም ነበረ፡፡/
«በብዙ ጎን እንደምንረዳው የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ጦር አብዛኛውን በነበረው የመሣሪያ ብልጫ እየተረዳ የበላይነትን አግኝቷል፡፡ ሆኖም በዚህ የተገኘው ድል ፍጹም ፀጥታ ተገኘ ማለት አይደለም፡፡ አመቺ ጊዜ ሲያጋጥመው የገላንና የአብቹ ኦሮሞ መክዳቱንና አደጋ መጣሉን አልተወም፡፡ ይህን በተመለከተ አንድ ጊዜ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ‹‹እርጎ›› የተባለ በገናውን እየደረደረ እንዲህ ሲል አንጎራጎረ ይባላል፡-
‹‹ብርድ አይችልም ጋላ ከቤቱ ከወጣ
እዩት ገላንሥቶ እሳት ሊጭር መጣ፡፡››
«የገላንን መሸፈት የሰማ አንድ የንጉሡ አዝማሪ ደግሞ እንዲህ አለ፡-
‹‹አብቹና ገላን ምን ያጉመተምታል
አሁን የኔ ጌታ በማሌት ይደርሳል፡፡››
« ‹‹ማሌት›› ለገላን የቀረበ የቦታ ስም ነው፡፡ እንደ ተባለውም ሣህለ ሥላሴ ጦሩን ይዞ ዘመተና ማሌትን አልፎ አብቹና ገላንን አስገበረ፡፡ ወዲያው ዘመቻውን ወደ አዳ ቀጥሎ የአገሩን ባላባት ቡኔን አስገበረና ከዚያ አዋሽን ተሻግሮ ሶዶ ደረሰ፡፡ የዚያን ጊዜ ነው ይባላል ‹‹ምነው ገለሌ›› የሚለው ሽለላ የወጣው፡፡ ትርጓሜው ምን ማለት እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ቅርብ ዘመን ይህ ሽለላ አለ፡-
‹‹ምነው ገለሌ ምነው ገለሌ
አዋሽ ማዶ በቁልቁለቱ
ደፋው ባንገቱ›፤
አዋሽ ማዶ ዱብ ዱብ ይላል
ያ ልጅ ይሆናል፤
ምነው ገለሌ ምነው ገለሌ
የዲናው ጌታ ክተት ሣህሌ፡፡››
«የሚቀጥለው ዘመቻ ደግሞ ወደ ምዕራብ ነበረ፡፡ በዚህም ግንባር በለስ ቀንቶታል ሣህለ ሥላሴ፡፡ ሜታ፣ ሜጫ፣ ሙሎ ፈርዳ (ሰላሌ)፣ ወረብና በች ገበሩ፡፡ ከዚያም ወደ ዓባይ አግጣጫ ጉዞውን በመቀጠል ሙገርንና አካባቢውን በቁጥጥሩ ስር አዋላቸው፡፡ በዚህ ዓይነት የግዛቱ ስፋት በሰሜን ወሎ ጫፍን ይነካና በአንዳንድ አግጣጫ ደግሞ የበሸሎና የዓባይ ተፋሳሽ ወንዞች ይገቱታል፡፡ በዚያው አግጣጫ ወደ ደቡብ ሲሔድ እስከ ዓባይ ይጠጋል፡፡ በዚህ ሸዋ ሜዳና መርሐ ቤቴ ይጠቃለላሉ፡፡ በደቡብ-ምዕራብ አዋሽን አልፎ ሶዶንና ጉራጌን ይጨምራል፡፡ በደቡብ-ምሥራቅ ከሰምን ተሻግሮ ከረዩን ይይዛል፡፡ በምሥራቅ እስከ አዳል ይዘልቃል፡፡ በሰሜን-ምሥራቅ ደግሞ ግድምና ይፍራታን አልፎ ወሎ አርጎባን ያጠቃልላል፡፡
«የሣህለ ሥላሴ ግዛት በማይል ሲለካ በግምት ምሥራቅ-ምዕራብ 125፣ በሰሜን-ደቡብ 220 ይሆናል፡፡ የሕዝቡ ብዛት 1,000,000 ይገመታል፡፡ በዚህ ዓይነት ማዕረጉ ‹‹መርዕድ አዝማች›› መሆኑ ቀርቶ ‹‹ንጉሥ›› ተብሎአል፡፡ የመጀመሪያው የሸዋ መሪ ይህን የማዕረግ ስም የተጠቀመ ሣህለ ሥላሴ ነበረ፡፡ ስለዚህ በይፋ፡- ‹‹ሣህለ ሥላሴ ንጉሠ ሻዋ፣ የጉራጌ፣ የጋላ፣ የሻንቅላ፣ ያዳል፣ የከረዩ፣ የይፋት፣ የወሎ፣ ያረመኔ የክርስትያን የሁሉ ንጉሥ›› ተብሎ ይጠራ ነበረ (ሰነድ ተመልከት)፡፡
«ነጥቡ አሸንፎ አገር መያዙ ላይ አልነበረም፡፡ ከዚያ በኋላ ጸጥታን ማስከበሩ ነበረ፡፡ በዚህ ግዛት ሁሉ ሙሉ ትጥቅ ያለው ግብረ ኃይል አስፍሮ ፀጥታውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የነበረው የሰውና የመዋዕለ ንዋይ እጥረት አይፈቅድም ነበረ፡፡ ጥቂት ጥቂት ለምልክት ያህል ጦር ይተዋል፡፡ ግን እርሱ የሚነሣውን ማዕበል ለመቋቋም አይችልም፡፡ ከሁሉ መጥፎ ደግሞ የንጉሡ ወታደሮች የጠበቀ ምሽግ ለጥቂት ጊዜ የሚያከራክር አልነበራቸውም፡፡ አደጋ ሲነሣ ወዲያው ይደመሰሳሉ፡፡ ለዚህ ምሳሌ ብንጠቅስ ማለፊያ ይሆናል፡፡
«ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ በ፲፰፻፴፪ [በ1832] ዓ.ም. ገደማ ወደ ፍንፍኔ የዛሬው አዲስ አበባ ባደረገው ዘመቻ በለስ ቀንቶት ድልን ተቀዳጀ፡፡ ወደፊት በስፍራው እንደምንገልጸው ይህ ስፍራ ለከተማነት የታጨው ያን ጊዜ ስለነበረ ቀራንዮ መድኃኔ ዓለም ታቦት ተተከለበትና አገልጋዮች ካህናት ተሠሩበት፡፡ ጠባቂዎችም ጥቂት ወታደሮች አብረዋቸው ቀሩ፡፡
«ችግሩ ክረምት ሲገባ ነው፡፡ የዚያን ጊዜ ወንዞች ስለሚሞሉ ግንኙነት ይቋረጣል፡፡ የአካባቢው ሰው ይህን የተፈጥሮ ኃይል ተገን በማድረግ በጥቂቶች ላይ ይዘምታል፣ ብሎም ይደመስሳቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ጸንቶ የሚቆየው ላጭር ጊዜ ክረምቱ እስኪወጣ ድረስ ነበረ፡፡ መስከረም ሲጠባ ንጉሡ ዲና ፈረሱን ይጭናል፡፡ በዚያን ጊዜ በፊቱ የሚቆም ኃይል የለም፡፡ እንዲህ ብድሩን ይመልሳል፡፡ ነገሩ ሁሉም ተደጋጋሚ ነበረ፡፡ ለዚህ ዘላቂ መፍትሔ ነው ተብሎ የተገኘው በጋብቻ መተሳሰርና በእምነት መመሳሰል ነበረ፡፡ እንደ ታቀደውም ተሞከረ፡፡ ብዙ ባላባቶችና ዝርያቸው ከአማራ ሴቶች ጋር ተጋብተው ተዋለዱ፡፡ ሌላው ቢቀር ይሄ የዘመቻውን አኃዝ ዝቅ አድርጎታል፡፡
« ‹‹ጫሜ›› የተባለችው የሙሎ ፈርዳ ንግሥት ነኝ የምትል ባሏ ከሞተ በኋላ አገሩን የምታስተዳድር እርሷ ነበረች፡፡ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ የጋብቻ ድርድር አቀረበላት ይባላል፡፡ የእርሷ መልስ ግን ፌዝን የተመላ ነበረ፡-
‹‹ከአንጎለላ እስከ እኔ ቤት ድረስ ሥጋጃ የተነጠፈ እንደሆነ በነገሩ አስብበታለሁ››
«ብላ መልስ ላከች፡፡ በዚህ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ተቆጥቶ ዘመተባት፡፡ ከተሸነፈች በኋላ ለአንድ ኦሮሞ ባላባት ‹‹ጎበና›› ለሚባል ዳራት፡፡ የጫሜን ልጅ ጃራን ክርስትና አንሥቶ ግዛቱን ለእርሱ ሰጠ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጃራ ለንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ፍጹም ታማኝ ሆኖ በሚያስፈልግበት ጊዜ ከንጉሡ ጎን በመሰለፍ ከፍ ያለ አገልግሎት አበርክቷል፡፡
«ሌላው ከስምምነት ላይ የደረሰ የአብቹ ባላባት መረጭ ነበረ፡፡ ከዚህ በፊት አብቹ ብዙ ጊዜ ከሸዋ መሳፍንት ጋራ ሲዋጋ ቆይቷል፡፡ ለዚህ ለቆየ ጠብ እልባት ለመስጠት ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ጽኑ ፍላጎት ነበረው፡፡ ስለዚህ እንደ ምንም ብሎ መረጭን ተወዳጀው፡፡ ሀብትና ሹመትም በገፍ ለገሰው፡፡ ከአሁን ወዲያ መረጭ ታማኝ ሆነ፡፡ በእምነቱም ክርስትናን በመቀበል ከንጉሡ ጋር አንድ ሆነ፡፡ ታማኝነቱም ተፈትኖ የወጣለት ስለነበረ መተኮ ከተገደለ በኋላ በኦሮሞው ክፍል አበጋዝ አድርጎ ሾመው፡፡»
/የዶ/ር ሥርግው ሀብለሥላሴ ትረካ እዚህ ላይ ያበቃል፡፡ አንድ ጥያቄ ግን አንስቼ ጥቂት ብዬ ልሰናበት፡፡ ለመሆኑ መተኮ ማነው? መተኮ በሸዋ ዘውዳዊ ታሪክ ውስጥ ምን የተለየ ታሪክ አለው? ማነው መተኮ?/
ወዳጄ! – መተኮ በግማሽ ልብ እያመፀ፣ በግማሽ ልቡ ለንጉሥ የገበረ ታማኝ የሣህለ ሥላሴ የጦር ጀኔራል (የጦር መሪ) ነበር፡፡ ስለ መተኮ ታሪክ በመጀመሪያ ያነበብኩት ዶ/ር ዶናልድ ሌቪን ምንጭ ጠቅሶ በ‹‹ዋክስ ኤንድ ጎልድ›› በሚል መጽሐፉ በትዕምርት ካሰፈረው በወቅቱ ሸዋን በአካል ከጎበኘ የአንድ አውሮፓዊ ተጓዥ የእማኝነት ማስታወሻ ላይ ነበር፡፡ በመቀጠል ደግሞ የዚሁን የመተኮን ታሪክ ዶ/ር ሥርግው ሀብለሥላሴ ‹‹ዳግማዊ ምንሊክ የአዲሱ ስልጣኔ መስራች›› በሚል ካሳተሙት መጽሐፋቸው ላይ ስለ ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ በሚተርኩበት ምዕራፍ ላይ ሰፊ ቦታ ተሰጥቶት የሰፈረውን ታሪክ አነበብኩት፡፡
የመተኮ ታሪክ እጅግ ይመስጣል፡፡ መተኮ አፍቃሪ ነው፡፡ ኃይለኛና ጉልበታም ተዋጊ ነው፡፡ እና የንጉሡን መንበር ፈንቅሎ ለመንገሥም የሚሻ ‹‹ምኞተ-ብዙ›› (‹‹አምቢሽየስ››) ሰውም ነበር፡፡ መተኮ በውበቷ የታወቀችውን የሣህለ ሥላሴን ሴት ልጅ ለማግባት ይጠይቃል፡፡ በብዛቱ ታይቶ የማይታወቅ ጥሎሽም ለንጉሡ ይልካል፡፡ ሆኖም ከፍቅር አዚሙ፣ ከዝምድና ፍለጋውና፣ ከቱባ ጥሎሹ በስተጀርባ የንጉሡን ወንበርም አጥብቆ መሻቱ ታመነ፡፡ እና ጋብቻውን ተከለከለ፡፡ በንጉሡ ዙፋን ፊትም ሞገስ አጣ፡፡ የመተኮም እቡይ ‹‹የማን አህሎኝ›› ባህርይ ልኩን አጣ፡፡ እና ብዙም ሳይቆይ በመተኮና በሣህለ ሥላሴ መሐል ጦርነት ተቀሰቀሰ፡፡
ዶ/ር ሥርግው ሀብለሥላሴ የመተኮን ጥጋብና ሽንፈት ታሪክ ከመፈንቅለ ሥልጣን ሙከራና በተለይ አንድ ‹‹አሥራት›› ከተባለ ኢያጎን የመሰለ ተንኮለኛ ደብተራ ሸር ጋር በማገናኘት በሰፊው አብራርተው ዘግበውልን እናገኛለን፡፡ ዶ/ር ዶናልድ ሌቪን ደግሞ በበኩሉ ለመተኮ የጋብቻ ጥያቄ ሣህለ ሥላሴ ‹‹ልጄን ለአንድ ሐይማኖት ለሌለው አረመኔ ከምሰጥ በቁሜ ብቀበር እመርጣለሁ!›› የሚል የንቀት መልስ በመስጠታቸው የተቀሰቀሰ እንደሆነ በማተት ከእምነት ጋር የተያያዘ ቀለም ሰጥተውት እናገኛለን፡፡
ለማንኛውም መተኮ ይሸነፋል፡፡ ተማርኮ በእስር ከተቀመጠበት የገደል ጫፍ ከሚገኝ ጥብቅ አምባ በተዓምራዊ ድራማና በማይታመን ጀግንነት በገደል አናት ዘልሎ ተሰባብሮ ያመልጣል፡፡ የአቢቹ ኦሮሞዎችን አሳምፆ ድጋሚ ጦርነት ይመራል፡፡ ይያዛል፡፡ ያኋላ ኋላ በምህረት ይመለሳል፡፡ ጦርን ለፈንቃይ አይሰጡትምና ከጦር አዛዥነቱ አንስተው፣ ሀገረ-ገዢ ያደርጉታል፡፡ በይቅርታ የተመለሰው የንጉሥ ሹም መተኮ የንጉሡን ሴት ልጅ መመኘቱን ቢተውም፣ ከጦሩ ቢርቅም፣ አሁንም የንጉሡን ወንበር መመኘቱን አልተው አለ፡፡ በመጨረሻ መተኮ በንጉሡ እልፍኝ አንዱን የሣህለ ሥላሴ ጭፍራ አናቱን ብሎ በጣለበት፣ አስር የሚሆኑ እልፍኝ አስከልካዮች ደርሰው ተረባርበው ይገድሉታል፡፡ አንዳንዶች ይህንንም ሆነ ተብሎ የተቀነባበረ የግድያ ሴራ ይሉታል፣ ሌሎች መጥፎ አጋጣሚ ይሉታል፣ ሌሎች ደግሞ የመተኮ ያልተገራ ብልግና የፈጠረው የግልፍት ተግባር ይሉታል፡፡
ይህን የሣህለ ሥላሴ አሽከር፣ የአብቹ ኦሮሞውን የጦር ጀኔራል፣ እና እንደ ጥንታዊ ግሪኳ ሔለን ጦርነትን ስላስነሳችው የንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ሴት ልጅ ታሪክ ላወጋ ከሰሞኑ ብቅ እላለሁ፡፡ ለዛሬ አበቃሁ፡፡ መልካም ጊዜ፡፡
Filed in: Amharic