>

የህወኀት ሥርዓተ-ቀብር የመጠናቀቁ ፊሽካ ከአብይ አህመድ አፍ መሰማቱ አይቀርም… ! (አሰፋ ሀይሉ)

የህወኀት ሥርዓተ-ቀብር የመጠናቀቁ ፊሽካ ከአብይ አህመድ አፍ መሰማቱ አይቀርም… !

አሰፋ ሀይሉ

 

ግን እስከዚያስ? ምን ያህል ሉዓላዊነት ይተርፈናል?
በግሌ የኤርትራ ህዝብ ወዳጅ ነኝ፡፡ ወይም እንደዚያ ነኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡ እስከ ዝንተዓለም ኤርትራን ከሀገሬ ኢትዮጵያ ነጥዬ የማላይ ሰውም ነኝ፡፡ በብዙ ታሪካዊ ምክንያቶችና ሴራዎች ከእናት ሀገራቸው የተነጠሉት የኤርትራ ህዝቦች ከወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር አንድ የሚሆኑበት ቀን፣ እና አንድ የሚያደርጋቸው ትውልድ አንድ ቀን በእርግጠኝነት መምጣቱ እንደማይቀርም አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ወንድማማችነት አብዝተው ከሚጮሁ ቅን ተመኚ ወገኖቼም አንዱ ነኝ ብል እያጋነንኩ አይደለም፡፡ ያውም መቃቃር ብሔራዊ ፖሊሲ ሆኖ በነገሠበት ወቅት ጭምር፡፡
ከላይ ያልኩት ሁሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በቅርቡ የተከናወኑ ብዙ ሀገራዊ ክስተቶችን በማስተዋል – በአሁኑ ወቅት በአብይ አህመድ ፊት መሪነት እየተከናወነ ያለው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር-ዘለል ግንኙነት በህጋዊ ሂደትና በሥርዓት ሊመራ ይገባዋል ከሚሉ የሀገር ተቆርቋሪ ዜጎች መሀል ሆኜ ራሴን አግኝቼዋለሁ፡፡ በሃሳብ፡፡ ይህ ማለት ግን በመግቢያዬ እንዳስቀመጥኩት የኢትዮጵያና የኤርትራን ህዝቦች አዲስ የፍቅርና የትብብር ምዕራፍ እጠላለሁ ማለት እንዳልሆነ በድጋሚ ይሰመርልኝ፡፡
ከብዙ የመረጃ ምንጮችና የዜና አውታሮች ማረጋገጥ እንደሚቻለው በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች ለረዥም ዓመታት ሲያጨቃጭቁን በቆዩ፣ ብሎም የወገኖቻችንን ደም ባፋሰሱ የድንበር ሥፍራዎች ላይ ወደ ኢትዮጵያ ይዞታዎች ተሻግረው በመግባት አካባቢዎቹን በቁጥጥራቸው ሥር ካዋሉት ሰንበትበት ብለዋል፡፡ ከዚህም አልፎ አብይ አህመድና ኢሣያስ አፈወርቂ በሚያውቁት፣ እና እስካሁን ከኢትዮጵያ ህዝብ በተሰወረው ስምምነት መሠረት – የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው በወያኔ ላይ ለመዝመት ከተሰለፉና ከተግባርም ከዘመቱ ሰንበትበት ማለቱም እሙን ነው፡፡
የሁለቱ ሀገሮች የቅርብ ጊዜ ግንኙነት በወታደራዊው መስክና በግዛት-እንካችሁ ብቻ የተወሰነም አይደለም፡፡ በሁለቱ የየሀገራቱ የወቅቱ መሪዎች በኩል የጋራ ኢኮኖሚ ጥቅም ያመጣሉ የተባሉ እና ከፍተኛ የሀገር መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰባቸው ግዙፍ ግንባታዎችና በወደብ አጠቃቀም ዙሪያ የተቃኙ ድንበር-ዘለል የግንኙነት ምዕራፎችም ተከፍተዋል፡፡ ገደብ ያልተበጀላቸው ድንበር-ዘለል የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችም መጀመራቸው በብዙዎች እሠየሁ ያስባለ እውነት ሆኖ አልፏል፡፡
በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባን ጨምሮ በየከተሞቹ ተወላጅነታቸው ወይም ዜግነታቸው የኤርትራ የሆኑ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወገኖች በኢትዮጵያ ውስጥ  እንደልባቸው ኑሮ መስርተው፣ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማናቸውም ዓይነት የሕይወት መስክ ተሰማርተው ለማደር የሚከለክላቸው መደበኛም ሆነ መደበኛ-ያልሆነ ገደብም እንደሌለባቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሁሉ ሂደቶች ለኢትዮጵያውያን መልካም ውጤትን ይዘው ከመጡ፣ ለኤርትራውያንም ጥሩ ቀን ካወጣላቸው ቅር የሚለው ሰው ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ በበኩሌ እንደ አንድ አፍቃሬ-ኤርትራ ኢትዮጵያዊ – እነዚህ ሁሉ የግንኙነት መስኮች ፈጽሞ ሊያስከፉኝ አይገባም ብዬ አስባለሁ፡፡
እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ግን ወዳጅነትን የመጥላት ነገር አይደለም፡፡ ወዳጅነታችን ረዥም ዕድሜ እንዲኖረው፣ መልካም ግንኙነታችን ነገ እንዳይቀለበስ፣ መወሰድ የሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ተወስደዋል ወይ? ወይስ አልተወሰዱም? የሚሉት ጥያቄዎች ማንኛውም የሁለቱን ሕዝቦች ዘላቂ ሠላም በሚወድ ሰው በዚህ ወቅት መጠየቅ ያሉባቸው ተገቢ ጥያቄዎች ይመስሉኛል፡፡
በቅርብ የታዩትና የተሰሙት በአብይ አህመድ (እና ኢሣያስ አፈወርቂ) ይሁንታ፣ በአብይ አህመድ ፈቃድ፣ ፣ በአብይ አህመድ አማላጅነት፣ እና በአብይ አህመድ አድራጊ-ፈጣሪነት የተከናወኑት የሁለቱ ህዝቦች ግንኙነቶችና ሀገር-አቀፍ እንቅስቃሴዎች – ተጠያቂነት በታከለበት፣ እና ግልጽነት ባለው ሁኔታ ተከናውነዋል ወይ? ወይስ በአንድ አብይ አህመድ ግላዊ መልካም ፈቃድና ውሳኔ ብቻ እየተዘወሩ የሚቀሩ ጉዳዮች ናቸው? የሚለው እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ያሳስበኛል፡፡ እነዚህን አሳሳቩ ጥያቄዎች ለምን አነሳህ ብሎ የሚከሰኝ ወቃሽ ካለ ይምጣና እንከራከርበት፡፡ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ በአስተውሎት መጤንም ያለበት ጥያቄ ይመስለኛል፡፡
ህወኀት ገና በሥልጣኗ ጅማሮ ላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት እና ድንበር ለሻዕቢያም ሆነ ለሌላ ኃይል አሳልፋ ስትሰጥ ያለ ምክንያት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቷም ‹‹መጀመሪያ መቀመጫዬን›› እንዳለችው ዝንጀሮ የመሰለ ነበር፡፡ የሥልጣን መንበሯ በሀገሪቱ ላይ ሳይፀና – ከሻዕቢያ ጋር የምትከራከርበት ሞራሉም፣ አቅሙም፣ ድፍረቱም አልነበራትም፡፡ ወያኔ እንደ ኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ፣ እና እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ ወኪል ራሷን ብትቆጥር ኖሮ – የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ሁሉ ለሻዕቢያ ሳትከራከር አትሸጥለትም ነበር የሚል ግምት አለኝ፡፡ ያን ብታደርግ ኖሮ ግን በሥልጣን ወንበሯ ላይ ያለ አንድ ዓመትም የምትነግሥ አይመስለኝም፡፡ ለህወኀት ያን ብታደርግና ሥልጣኗ ቢቀርባት ይሻላት ነበር? ወይስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብትና ብሔራዊ ጥቅም ለ27 ዓመት ሥልጣን ስትል መቀየሯ ብልጥ ያሰኛታል? – በበኩሌ አላውቅም! ፈራጅ ታሪክ ነው! ታሪክ በደማቁ ፍርዱን የሰጠ ይመስለኛል! ከኛ የሚጠበቀው ከዚያ ወያኔያዊ ታሪክ መማር ብቻ ነው!
ወያኔ አንድም ቀን በየትኛውም የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያን ህዝብ አማክራ አታውቅም! በራሷ አምሳል ጠፍጥፋ ከዚህ ከዚያ ለቃቅማ በሰበሰበችው ትያትረኛ ፓርላማዋ ፊት ሀገራዊ ጉዳዮችን አቅርባ እያስወሰነች የምትወጣውን ነገር ከእውነተኛ የህዝብ ተወካዮች ውይይትና ይሁንታ ጋር የሚያምታታው ካለ አሁን ላይ የምረዳው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ አብዝቼ አዝንለታለሁ፡፡
መለስ ዜናዊ ‹‹ሀ›› ብሎ የሀገሪቱን የሥልጣን ጉዞውን ሲጀምር ጀምሮ – ‹‹ሻዕቢያ ኤርትራን የወሰደው እኛ ይሁንና አይሁን ስላልን ሳይሆን፣ በጦርነት አሸንፎ በጉልበቱ ነው የወሰዳት – የተሸነፈ ሀገር፣ እና የተሸነፈ ህዝብ የተባለውን ሁሉ ሳያንገራግር ከመስጠት በቀር አማራጭ የለውም፣ በጦርነት ሀገሬን አስመልሳለሁ የሚል ካለ ደግሞ መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት፣ እኛ በበኩላችን ጦርነት መርሮናል›› በማለት እያፌዘ ነበር ለፈጣሪዎቹና የጦር ጓዶቹ ለእነ ኢሣያስ አፈወርቂ ሀገሪቱን ከነህዝቦቿ ባርኮ ያስረከባቸው፡፡
ኢትዮጵያ እጅ የሰጠችው በእውነትም ተሸንፋ ከሆነ፣ የተሸነፈውን ህዝብና ከሽንፈት የተረፈችውን ሀገር ሊያስተዳድራት የሚገባው፣ ያው የተሸነፈውና እጅ የሰጠው ሀገሩም የተወሰደበት መንግሥት መሆን ነበረበት፡፡ የእኛ ነገር እኮ እንዲያ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ ተሸንፋም፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተሸንፌያለሁ ብሎ ሀዘን የተቀመጠ አካል ሳይሆን ያሳተዳደራት – ‹‹ኢትዮጵያን አሸንፌያለሁ›› እያለ፣ ለኢትዮጵያ የተዋጋላትን ጦርሠራዊትና አናስደፍራትም ብለው የቆሙላትን የቁርጥ ቀን ልጆቿን ‹‹ጠላት›› እያለ፣ በሽሬ ግንባር ጠላትን ደመሰስኩ፣ በደብረ ታቦር ግንባር ጠላትን ደመሰስኩ፣ ወዘተ እያለ በያመቱ ‹‹ጠላቱን›› የደመሰሰበትን ግንቦት 20ውን የዳንኪራ ከበሮ እየደለቀ የሚያከብር አካል እኮ ነው ከምርኮና ከንጥቂያ የተረፈችውን ኢትዮጵያን ያስተዳደራት፡፡ ይሄን የማያውቅ ካለ የሀገሩን ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ ይመርምር፡፡ አሁን ያልደረሰበት አንድ ቀን እውነቱ ላይ መድረሱ አይቀርም፡፡
እና በትክክል የተፈጸመብንን ታሪካችንን የምናውቅ ከሆነ ማለት ያለብን ‹‹ኢትዮጵያን ያሸነፋት ኤርትራን ገነጠለ፣ እንደገናም ኢትዮጵያን ያሸነፋት በቁጥጥሩ ሥር አውሎን ለ27 ዓመታት ሀገሪቱን ገዛት›› ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁንም አላሸነፈችም፡፡ ለኢትዮጵያ የቆሙላትን ‹‹ጠላቶቼ›› እያለ ሲወጋና ሲያደማ በኖረው የኢትዮጵያና የባንዲራዋ ‹‹ጠላት›› በሆነው በወያኔ ግዞት እንደተያዘች ነች፡፡ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብቶች ያለምንም ቅድመሁኔታና ድርድር ለሻዕቢያ አሳልፎ ለመስጠት ሲል ‹‹ጦርነት መሮናል›› ያለው መለስ ዜናዊ፣ እንዲያ ባለበት አፉ ነው አይኑን አፍጥጦ ‹‹መሬት ተወሰደብን፣ ድንበር ተነካብን›› ብሎ ዳግመኛ ሺህዎች ያለቁበትን የባድሜ ጦርነት የመራው፡፡ በእኔ አረዳድ ያም ጦርነት ቢሆን ኢትዮጵያን አሸንፎ በግዞት የያዛት ጠላታችን ወያኔ፣ ጠላት ሆኖ የተነሳበትን ሻዕቢያን ያሸነፈችበት ጦርነት እንጂ፣ ኢትዮጵያ ኤርትራን ያሸነፈችበት ጦርነት አይደለም!
ኢትዮጵያ ዛሬም እንደተሸነፈች ቀርታለች፡፡ አሁንም ሥልጣን ላይ ያሉት ‹‹ኢትዮጵያን ወግተን አሸንፈናል›› የሚሉት ባንዳዎች የኢትዮጵያዊነት ውርጃ ታሪክ ተረካቢዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ባንዲራ እንደ ጠላት ባንዲራ፣ የኢትዮጵያን ወታደር እንደ ጠላት ወታደር የቆጠሩ ተጋዳላዮች ጠላታቸውን ኢትዮጵያን አሸንፈው የመሠረቱት የግዞት መንግሥት ነው አሁንም በኢትዮጵያ ቀጥሎ ያለው፡፡ ኢትዮጵያ የሚያሸንፍላትን ትውልድ ገና አላፈራችም፡፡ ቆንጆዎቹ ያገሬ ልጆች ገና አልተወለዱም፡፡
እኛ የተሸነፍን ኢትዮጵያውያን መራሩን ሽንፈታችንን መቀበላችንና ላለፍንበት የታሪክ ቁልቁለት ዕውቅና መስጠታችን ግን – አንድ ቀን ኢትዮጵያን ጠፍንገው ከያዟት ጠላቶቿ መዳፍ የሚያላቅቃት ትውልድ እስኪመጣ እየሆንብን ያለውን ሁሉ እንደ ግዑዝ ዝም ብለን ተኝተን እናሳልፋለን ማለት አይደለም፡፡ በእንደዚህ ያለ የሥልጣነ መንበር ሽግግር ወቅት ኢትዮጵያችን ከተቦጨቀችው በላይ እንዳትቦጨቅ፣ ከተሸነፈችውም በላይ እንዳትሸነፍ፣ ከጠሏት በላይ የሚጠሏት እንዳይገዙን፣ አስተውሎ ማየትና የቻልነውን ማድረግ ከእኛ የሚጠበቅ እና ለድርድር የማናቀርበው ተግባር ነው፡፡
በአሁን ወቅት አንድ ወሳኝ ጥያቄ ራሳችንን አበክረን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል፡- በ1983 ላይ መለስ ዜናዊ ሥልጣኑን ለማርጋት ሲል የፈጸመውን ታሪካዊ የሀገር ክህደት የሞላበት ምርጫ (ማለትም ለሀገሪቱ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ከምቆምና ዕድሜዬን ከማሳጥር ይልቅ፣ ሥልጣኔን አርግቼ ለነገ መትረፍ ይበልጥብኛል ብሎ የሀገር ክህደትን የመረጠውን ምርጫ) – አሁን በ30 ዓመቱ (ዛሬ በ2013 ላይ) – አብይ አህመድስ እየደገመው እንዳልሆነ ምን ማረጋገጫ አለን?
እነዚያ ያለፉ አንገት አስደፊ ክስተቶች፣ የሀገር መገነጣጠሎች፣ እና በከንቱ የፈሰሰው የብዙ ወገኖቻችን ደም፣ እና በከንቱ የተከሰከሰው የወገን አጥንት የማይቆጨው – እና ከዛ የማይማር ኢትዮጵያዊ ካለ – ያለምንም ጥርጥር ማሰቢያው የተደፈነበት አሊያም ኢትዮጵያን አጥብቆ የሚጠላ መሆን አለበት፡፡ እነዚያ ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጀው ያስተዳደሩ ግለሰባዊና ቡድናዊ የሀገር ቁማርተኞች ትልቅ ሀገራዊ ዋጋ አስከፍለውን ነው ያለፉት፡፡ አሁንም እያስከፈሉን ነው፡፡ አሁን እያደረግናቸው ያሉትም ግለሰባዊና ቡድናዊ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የሚደረጉ ቁማሮች ብዙ ዋጋ እንደማያስከፍሉን እያረጋገጡ መጓዝ ኢትዮጵያ ሀገራችን ከምንል ዜጎች ሁሉ የሚጠበቅ ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው፡፡ ካለፈው አለመረዳት፣ ከስህተት-ያለመማር ትልቅ ደናቁርትነትም ነው፡፡ በጊዜ ማስተዋል ከብዙ ጥፋት ያድናል፡፡
የፈለገው ቢሆን – የኢትዮጵያ ድንበር በህገወጥም ይሁን፣ በህጋዊ መንገድ ለሌላ ሀገር ተላልፎ ሲሰጥ – ከምንም በላይ በኢትዮጵያውያን ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው የሉዓላዊነትና የሀገር ዳር ድንበር ጉዳይ ነውና – ምንም እንኳ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው በወያኔ-ኢህአዴግ ዘመን በተለመደው ኮሮጆ ግልበጣ ተመርጦ የተገጠገጠ የይስሙላ ፓርላማም ቢሆን፣ ምንም እንኳ ተቀናቃኞቹን አባሮ የራሱን የሥልጣን ጊዜ አራዝሞ የተቀመጠ ፓርላማም ቢሆን – ቢያንስ በዚሁም ፓርላማ ፊት – የድንበር አሳልፎ አሰጣጣችን፣ እና በሉዓላዊነት ላይ ያደረግናቸው ድርድሮች (‹ኮምፐሮማይዝስ›) ሁሉ (አንድም ሳይቀር) በዝርዝርና በሙሉ ቀርበው፣ ህጋዊ ሂደቱን ጠብቀው፣ የሕዝብ ተወካዮቹንና የፌዴሬሽን ምክርቤቱን ይሁንታ አግኝተው፣ ቢያንስ ሌላው ቢቀር አሁን ያለው የሥርዓቱ የራሱ አሠራር በሚያዘውና በሚፈቅደው መሠረት ብቻ መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡
ይሄ የሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ነው፡፡ የግል ቤት የአየር በአየር ሽያጭ ውል፣ ወይ ተራ የካርታ ርክክብ አይደለም፡፡ የቀበሌ ቤት ርክክብ እንኳ ሲደረግ መሟላት ያለባቸው የራሱ ህጋዊ መስፈርቶች፣ ሂደቶችና ተግባሮች አሉት፡፡ እንኳን ሀገርን ያህል ነገር!  እንኳን ስንት ሺህ ኢትዮጵያውያን ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ጫፍ ተጠራርተው ባንዲራቸውን እያውለበለቡ የወደቁበትን የደም መሬት – ማንም ግለሰብ – አብይ አህመድም ሆነ ማንም ከፀሐይ በታች ያለ ግለሰብ – ሲነሽጠው እየተነሳ – እንደራሱ አሮጌ ጣሳ ብድግ እያደረገ – የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቀውና ሳይስማማበት – የኢትዮጵያን ዳር ድንበር፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የኢትዮጵያን መሬት፣ በኢትዮጵያ ባንዲራ ሥር የተጠለለን የትኛውንም ሕዝብ – ለሌላ ሀገር የመስጠት አንዳችም መብት የለውም! አንዳችም ስንዝር ታህል እንኳን!!!
አሁን እያየነው እንዳለነው ‹‹በይሁንልህ-ይሁንብኝ›› በግለሰብ መሪዎች መካከል በሚደረግ መሐላም ብድግ ተደርጎ አይሰጥም ሀገር፡፡ ህዝብ ማወቅ አለበት፡፡ ህዝብ መወያየትና መስማማት አለበት፡፡ መንግሥትን የሚመሩት አካሎች ሁሉ ቁጭ ብለው ተወያይተው ገደቦችን ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ ፓርላማው አፈጻጸሙን መከታተልና ማረጋገጥ አለበት፡፡ ሀገር የሚመራው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ቢያንስ ማንም ሆኑ ማን፣ ከፉም ለሙም እነዚህ የታወቁ አካሎች የሚፈጽሙት ተግባር አሁን ላይ ተጠያቂነት ባያስከትል፣ የታሪክ ተጠያቂነት ያለበት ተግባር ነው፡፡ አንድም የህዝብ፣ አንድም የታሪክ ተጠያቂነትን የተቀበለ አካል ነው ስለ ሀገር ሉዓላዊነት ሊወስን የሚችለው፡፡ እንጂ በአየር ባየር በመርካቶ ደላላ እንደሚሸጥ የተበለተ የመኪና አካል ‹‹ሃይ መሃመድ! ሃይ ከቤ!›› እየተባባሉ – ዝም ብሎ በአየር ላይ ሀገር አይሸጥም፣ በአየር ላይ ሀገር አይለወጥም፣ በአየር ላይ ተላልፎ አይሰጥም ሀገር ለሌላ፡፡ ሁሉም ነገር ህግ፣ ደንብና ራሱን የቻለ ሥርዓት አለው፡፡
ስለሆነም የአብይ አህመድ መንግሥት – ዛሬ ሀገር እንዴት እንደምትመራ ጠንቅቆ ባለማወቅም ይሁን፣ አሊያም በችኮላና ግብታዊ ስሜት በመመራት፣ አሊያም ብዙ ጉዳዮችን አርቆ ባለማስተዋል – ወይም አንዳንዶቻችን እንደምናስበው – በማን አህሎኝነትም ይሁን፣ ‹‹ሾርት ሜሞሪ›› እንዳለው በሚታመነው ህዝብ የአዕምሮ ነሆለልነት ተወራርዶ – አሊያም በማናቸውም ምክንያት ይሁን በምን – ይህ በአንድ ግለሰብ መልካም ፈቃድ እንዳሻው እየተጋለበ ያለው የሀገርና የሉዓላዊነት ጉዳይ – ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን የሀገሩን የኢትዮጵያን ህዝብ (እና በነገራችን ላይ የኤርትራንም ህዝብ ጭምር) አሳውቆና የሕዝቡን ይሁንታ አግኝቶ መፈጸም ይኖርበታል፡፡
አብይ አህመድ ዛሬ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሳያሳውቅ፣ ህጋዊ ሂደቶችን ሳይጠብቅ፣ እና ቢያንስ አሁን በሥራ ላይ ባለው የአገዛዙ ሥርዓት መንግሥታዊ አካሎች ሁሉ የበላይ የሆነው ‹‹የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት›› ፊት አቅርቦ አወያይቶ ሳያስፀድቅ፣ ፓርላማው ይህን እንዲያስፈጽም ሳያዘው፣ አፈጻጸሙን ሳይከታተልና ሳይቆጣጠረው – በግሉ ከኢሣያስ አፈወርቂ ጋርም ሆነ ከአብደላ ሀምዶክ፣ ወይም ከአልሲሲና ኢስማኤል ጌዶ ጋር ያደረጋቸውና የሚገባባቸው ማናቸውም ሉዓላዊነትን የሚነኩ፣ ሀገርን አሳልፎ መስጠትን የሚመለከቱ፣ እና በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ላይ ሀገራዊና ዓለማቀፋዊ መብትና ግዴታዎችን የሚጥሉ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚደረጉ ድንበር-ዘለል ስምምነቶች ሁሉ – ነገና ከነገ ወዲያ ህጋዊ ተደርገው የሚቀርቡበት አግባብ የለም፡፡ እስካሁን ባየናቸው መልኩም የኢትዮጵያ ህዝብ ሳያውቃቸው ተዘልሎ የገባባቸው ስምምነቶችና ሉዓላዊነት የሚነኩ ተግባራት ሁሉ ነገ ጥያቄ የሚያስነሱ መሆናቸው አይቀርም፡፡
ዛሬ አብይ አህመድ የገባባቸው ስምምነቶች ነገ አብይ አህመድ በግሉ የሚፈጽማቸው አይደሉም፡፡ አይፈጽማቸውምም፡፡ እነዚህ የሀገሬው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ የሚወድቁ ናቸው፡፡ ማንም ሰው – ማንም ከፀሐይ በታች ያለ አንድ ግለሰብ – አሁን ባለውና በወደፊቱ ትውልድ ላይ ያሻውን እየጫነ የመቀጠል መብት የለውም፡፡ ሊኖረውም አይገባም፡፡ ያገሩ ህዝብ ሳያውቀውና ይሁን ሳይለው እነዚህን ሀገርን አሳልፎ የመስጠት ድርጊቶች መፈጸም – ነገ ግለሰቡን ራሱንም፣ ሀገርንም፣ ህዝብንም ታላቅ ዋጋ የሚያስከፍል እጅግ አደገኛ – እና የወደፊት ግጭቶችን ፈጣሪ ተግባር ነው፡፡ በሌላ በኩልም ይህ ነገር በእሳት እንደ መጫወትም መሆኑ ለአፍታም መረሳት የለበትም፡፡
እነዚህ የአብይ አህመድ ተግባሮች ዛሬ ላይ ህገወጥ መሆናቸው ብቻ አይደለም፡፡ ውሎ አድሮ ነገና ከነገወዲያ የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ሚዛን ሲለዋወጥ፣ እና ከኋላ እየተከተለ የሚያጨበጭብ ደጋፊ ኃይል ሲታጣ – አብይ አህመድን ከፍተኛ በሆነው ‹‹የሀገር ክህደት ወንጀል›› ሊያስጠይቁ የሚችሉ – ብሎም አሁን ባለው ‹‹ህገመንግሥት›› በተሰጠው ቀዳዳ በመጠቀም የሀገር ሉዓላዊነትን እንጠብቃለን በሚል ሰበብ – ከሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ አብይ አህመድን ከሥልጣኑ ለመፈንቀል (መፈንቅለ-መንግሥት ለማድረግ) ለሚነሳ መፃኤ የመፈንቅለ-መንግሥት ሞካሪ አንጃ ትልቅ ‹ሌጂትሜት ኮዝ› የሚሰጥ ጉዳይ መሆኑን አለማወቅ ትልቅ ጅልነት ነው፡፡ ይህ የሉዓላዊነት ጉዳይ በህጋዊ መስመር እንዲከናወን ተደርጎ ከወዲሁ እልባት ካልተበጀለት-  አሁን ሀገርን እየመራ ላለው ወቅታዊ የፖለቲካ ኃይል የሥልጣን ቀጣይነት ታላቅ አደጋን የሚጋብዝ – ታላቅ የታሪካዊ ህፀፅ ነው፡፡
አብይ አህመድና ዛሬ ላይ እርሱን ከቦ ‹‹አሜን አሜን›› የሚለው የሥልጣን ግሪሳ ቆም ብሎ ማሰቢያ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ዛሬ ይህን ጉዳይ ቸል ብሎ ፍፁም ወደ ኋላ መመለስ ወደማይቻልበት የወደፊቱ ምዕራፍ ውስጥ ከመገባቱ በፊት – በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ አብይ አህመድ ያደረጋቸውንና እያደረጋቸው ያሉትን ስምምነቶችና ተግባሮች ቆም ብሎ የመፈተሻውና ስህተቶችን በፍጥነት የማረሚያው ጊዜ አሁን ነው፡፡
ይህን ሁሉ ስል አሌክስ ደ ዋል ከሃሳቤ አልጠፋ እንዳለኝ ነው፡፡ አሌክስ ደ ዋል በተፍትስ ዩኒቨርሲቲ የWorld Peace Foundation ዋና ዳይሬክተር ሲሆን፣ በተለይ በአፍሪካ ምሁራን ሲራገቡ የቆዩ ዘርፈ ብዙ የጥላቻና የግጭት ፖለቲካዎችን ከሥር ከመሠረታቸው አብላልቶ ያጠና በሳል ምሁርም ነው፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የኃይል አሰላለፍና የጎሳና ሐይማኖት አክራሪነት በወለዳቸው ግጭቶች ዙሪያ በዓለማቀፍ ደረጃ ታላቅ አክብሮት የተቸራቸውን (በግሌ እጅግ የማደንቃቸውንም) ምሁራዊ ድርሳኖች በማሳተምም የሚታወቅ እንግሊዛዊ የፖለቲካ ተንታኝ ነው፡፡
ታዲያ ይህ አሌክስ ደ ዋል ሰሞኑን ፊት ለፊት ማስረጃ እያጣቀሰ ካጋለጣቸው የአፍሪካ ቀንድ እውነቶች መካከል – ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር፣ ከሱዳን ጋር፣ እና ከኤርትራ ጋር ያደረገቻቸው ወቅታዊ ስምምነቶችና ዓለማቀፋዊ ትኩረትን የሳቡ ክንውኖች ይገኙበታል፡፡ አሌክስ ደ ዋል ኢትዮጵያ አሜሪካን በአሸማጋይነት ጨምራ በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ለመደራደር የተስማማችው አብይ አህመድ ሩሲያ በጠራችው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ ትብብር ሰሚት (ጉባዔ) ላይ ሊሳተፍ በሄደበት የግብጹን ፕሬዚደንት ጀኔራል አልሲሲን አግኝቶ ስለ አባይ ጉዳይ በግል ባናገረበት ወቅት በአልሲሲ የቀረበለትን በአሜሪካ አሸማጋይነት የሚደረግን የኢትዮ-ኢጅይፕት ስምምነት ተቀብሎ በመምጣቱ እንደሆነ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ በማይታበል አነጋገር አስረግጦ አጋልጧል፡፡
እዚህ ላይ ዋናው ነጥብ የእውነቱ መገለጥ ብቻ አይመስለኝም፡፡ እውነቱ ተገለጠ፡፡ ግን ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ ስንት እሰጥ-አገባ ውስጥ ነው የገባችው? ግብጾች አሰላስለው ጦር አልመዘዙም እንጂኮ በዚህ የአብይ አህመድ ግላዊ ውሳኔ የትራምፗ አሜሪካ ሙሉ ድጋፍ ያልተለየው የሚሳይል ጥቃት ሊሰነዘርብን ይችል እኮ ነበር፡፡ በዚህ አብይ አህመድ ዘው ብሎ በገባበት ስምምነት መሰረት ሀገርን የጎዱ ዘርፈ-ብዙ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ክሽፈቶችንም ጨምረን እናስብ፡፡ ዛሬ የገጠመን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በአብይ አህመድ በግብታዊነት የተሞሉ ሺህ ዓይነት የአየር-በአየር የድለላ ጨዋታ የሚመስሉ ብዙ አደገና ስምምነቶች ተከበናል በያቅጣጫው ዛሬ፡፡ ሀገር በግለሰብ እጅ ዛሬ-በዚህ ነገ-በዚያ እየተላጋች ስትዘወር የሚጠብቃትን አስከፊ ዕጣ-ፈንታ ለማየት ይሄ በትንሹ ጥሩ አብነት ሆኖ በሠላም ያለፈ (ጦሱ ገና ያላለፈም ቢሆን) ክስተት ነው – ብሎ እወነቱን መቀበልና ማስተውል ትምህርትም መውሰድ ትልቅነት ነው፡፡
በነገራችን ላይ አሌክስ ደ ዋል በቢቢሲ ባሰራጨው የሆርን ኦፍ አፍሪካ ትንተና በማስረጃና በመረጃ እያስደገፈ የገለጠው እውነት ይሄን ብቻ አይደለም፡፡ በመተማ በኩልም ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የሚያጨቃጭቃትን ድንበር በ2008 (በፈረንጆች አቆጣጠር – በእኛ 2001 ዓ.ም.) ለሱዳን ተላልፎ እንዲሰጥ ተስማምቶ የመጣው የወያኔው አባይ ፀሐዬ መሆኑንም ስምምነቱን ጭምር ጠቅሶ አጋልጧል የምስራቅ አፍሪካው ጉምቱ ሪሰርቸር አሌክስ ደ ዋል፡፡ በህወኀቱ አባይ ፀሐዬ የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ነው በ2008 እ.ኤ.አ. (ለፓርላማው ሳያሳውቅ) ወደ ሱዳን አምርቶ – ከሱዳን መንግሥት ጋር በመተማ በኩል ያለውን ኢትዮጵያኖች ሲያርሱት የኖሩትንና በኢትዮጵያ ይዞታ ሥር ያለውን ሰፊ የሰሊጥ እርሻና የግጦሽ መሬት – ከነነዋሪዎቹ ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት የተስማማው፡፡ ስምምነቱ ወያኔዎች የለመዱትን የፌዝ አንቀጽም ያጠቃለለ መሆኑ ተጋልጧል፡፡ በመሬቱ ላይ የሚያርሱ ኢትዮጵያውያንን መብት ሱዳን እንድታከብር በማለት ያትታል አባይ ፀሐዬ መራሹ የሀገር ሉዓላዊነትን ለሱዳን ያስተላለፈው ‹‹ስምምነት››!
ይህ ብቻም አይደለም፡፡ አብይ አህመድም በዚያው መሰረት ስለሚፈጸመው የሱዳን ‹‹ድንበሯን›› (በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ ይሰመርበት!) የማረጋገጥ እንቅስቃሴ ምንም ተቃውሞ ሳያነሳ እንደተቀበለና፣ የወያኔ ጥቃት እንደተሰነዘረበት በችኮላ ሮጦ ከአብደላ ሀምዶክ ጋር የሱዳን ጦር በመተማ በኩል ስለሚሰፍርበት ሁኔታ እንደተስማማ – ይገልጽልናል፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ አሁን ፀሐይ የሞቀው እውነት ሆኗል፡፡ /በዚህ ጉዳይ የአሌክስ ደ ዋልን ትንታኔ ይመለከቷል፡፡/
ይህ ነገር አንድን ጥርጣሬን ደጋግሞ የሚዘራብን ጉዳይ ነው፡፡ ብዙዎች ደጋግመው ሲሉት የቆዩት – እና ብዙ ጊዜ እጄ የለበትም እያለ ሲያስተባብል የቆየው – የአብይ ምክትል የደመቀ መኮንን ሐሰን ተሳትፎ ጉዳይ፡፡ ተግባራዊ ይደረግም አይደረግም – የስምምነቱ ቅጂ በሁለቱም ሀገሮች እጅ እንደተቀመጠ ለዓለም ግልጽ በሆነበት በዚህ ወቅት ላይ – የሰነዱ ይዘት ከኢትዮጵያ ህዝብና ፓርላማ እስካሁንም መሰወሩ – እና በአሌክስ ደ ዋል የስምምነቱ አንቀጾች ሁሉ እየተጠቀሱ ከመቅረባቸው ጋር – እና ከአባይ ጸሐዬ ሌላ በኢትዮጵያ በኩል በሰነዱ እጃቸውን ያሳረፉ ፈራሚዎች ተዘርዝረው ያለመገለጻቸው ሁሉ – የሚጠቁመን አሁንም በጅምላ የተካደና ሙሉ በሙሉ ያላወቅነው አንዳች እውነት መኖሩን ነው፡፡
ይህ ሁሉ የሚያሳየን – የአጠቃላዩን የኢትዮጵያን ህዝብ ዕውቅናና ስምምነት የሚጠይቁ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም የሚመለከቱ ጉዳዮች – በታሪካዊ አጋጣሚ በሥልጣን ላይ ፊጥ ብለው በተገኙ ጎጠኛ ግለሰቦችና የወያኔ-ኢህአዴግ ሹማምንት በህቡዕ ሲወሰኑ፣ በግለሰቦች ይሁንታ ሀገር ሲሸጥና ሲለወጥ የመክረሙን የመረረ እውነታ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ያ ወያኔያዊ የሀገር ሽያጭና ክህደት በወያኔዎቹ አለማብቃቱ ነው፡፡ የሚያሳዝነው የድሮውን እያነሳን ለመጻፍ የምንገደድባቸው እነዚያው ኢህአዴጋዊ ሸፍጦች አሁንም ተባብሰው የመቀጠላቸው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡
አብይ አህመድም በበኩሉ – ወያኔዎቹ ወደ ትውልድ መንደሮቻቸው አፈግፍገው በተቀመጡባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ – ማንንም ሳያማክርና ፓርላማውን ሳይጠራ፣ በራሱና በራሱ ውሳኔ በባድመ፣ ሽራሮ፣ ዛላንበሳ፣ ፆረና፣ ኢሮብና በመሳሰሉት የድንበር ጦርነት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሠፍሮ የቆየውን የኢትዮጵያ ጦርሠራዊት ከሥፍራዎቹ ማንሳቱ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ ነገሩ በዚያ ብቻ ቢያበቃም ምንም ባልነበር፡፡
አሁን ግን በወያኔ ላይ የተከፈተውን ጦርነት ተከትሎ (አሌክስ ደ ዋልን ጨምሮ እንደ ብዙዎች ዘገባ በወያኔ ላይ ጦርነት ባወጀ በዚያው ዕለት) – በተጠንቀቅ ዝግጁ ሆነው ይጠባበቁ የነበሩት የኤርትራ ወታደሮች – በኢትዮጵያ ይዞታ ሥር የነበሩትን ግዛቶች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል፡፡ በአካባቢው በአካል የሄዱ ዘጋቢዎች እንደመሰከሩት የኤርትራውያኑም ሠራዊት የሆነውን አልሸሸገም፡፡ ‹‹የድንበር ኮሚሽኑ የወሰነልንን ግዛታችንን ከአብይ አህመድ ጋር ባድግነው ስምምነት መሠረት መልሰን ተቆጣጥረናል›› ብለው ነው ለህዝቡም ለዓለማቀፉም ጠያቂ አካል ምላሽ የሰጡት፡፡ ይህ ከታወቀ ውሎ ያደረ፣ ግን ለእኛ እስካሁን በይፋ ያልተነገረም፣ በይፋ ስምምነት ያልተሰጠበትም፣ የአብይ አህመድ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ለመሆኑ እነዚህን በቀጥታ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚመለከቱ ድንበር-ዘለል ድርጊቶች አሁን በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፓርላማ የመከረባቸው ናቸው ወይ? ይሁን ብሎ አፅድቋቸዋል ወይ? ወይስ አብይ አህመድ በራሱ ተነሳሽነትና ውሳኔ ከኤርትራው አቻው ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በምስጢር እየመከረ እንዳሻው የሚሰጣቸው – የሚለውጣቸው – በኢትዮጵያውያን ደም የረጠቡ ለጉድ የፈጠራቸው መሬቶቻችን ናቸው?
የኛ ነገር የሚያሳዝነው ሁሌም የሚሆንብን ነገር ያው መሆኑ ነው፡፡ ከታሪክ አንማርም፡፡ ከስህተታችን አንታረምም፡፡ እና ክፉው ነገር ደግሞ ደጋግሞ ይጎበኘናል፡፡ ትናንት መለስ ዜናዊና የወያኔ ከሃዲያን የአሰብን ወደብ ለሻዕቢያ (ያኔ ገና የኤርትራ መንግሥት የሆነች አይመስለኝም) አሳልፎ ሲሰጥ – የኢትዮጵያን ህዝብ አማክሮና ይሁንልኝ ብሎ እንዳልሆነ የዓለም ህዝብ የሚያውቀው እውነት ነው፡፡ መለስ ዜናዊ ያንንም ስምምነት ከኢሳያስ ጋር ሲፈራረም – ልክ አሁን በአባይ ፀሐዬ ፊታውራሪነት ተፈርሞ ተገኘ እንደተባለው ስምምነት ሁሉ – ኢትዮጵያውያን የአሰብን ወደብ የመጠቀም መብት አላቸው የሚል ‹‹የለበጣና የፌዝ›› ስምምነት ጨምሮበት ነበር የተፈራረመው፡፡ በተግባር የሆነውን ያየነውና የምናውቀው ነው፡፡
አሁንም አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና የማይገሰስ ብሔራዊ መብት ምን እና እስከምን እንደሆነ በቅጡ ያውቀዋል ወይ? ወይስ ታሪካችንንና የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅሞች ሳያውቅና ሳይረዳ፣ ውክልናም ሳይሰጠው፣ የስሙ ፓርላማ እንኳ ሳይፈቅድለትና ሳያፀድቅለት – ልክ እንደ እብሪተኛው መለስ ሁሉ – የአሰብን ጉዳይ በተመለከተ ከኢሳያስ ጋር ቁጭ ብሎ የግሉን ስምምነት ፈቃጅና አስፈጻሚ ሆኖ ራሱን ቀብቷል? እንዴ? ለመሆኑ ይህን ዓይነቱን ማን-አህሎኝነት ከመቼውና ከየት ተማረው? ከየትስ መነጨ ይህን የሚያህለው ድፍረት? ወይስ የሀገርን ጉዳይና ብሔራዊ ጥቅም እንዳሻው እንደሚያደርገው የአባት-የእናቱ የቡና ማሳ ቆጥሮት ይሆን ይሄ ሰውዬ? (ለአነጋገሬ ይቅርታ) – የምሬን እኮ ነው የምጠይቀው! ሰውየው እንደ ቀልድና ያለምንም ድንጋጤ ተረጋግቶ እያደረገ ያለው ነገር እኮ ህጋዊና ሥርዓታዊ ሂደቱን ጠብቆ ሊደረግ የሚገባው ሀገራዊና ሉዓላዊ ጉዳይ እኮ ነው! ይሄ ሰውዬ የሚመክረው፣ ተው ፣ ረጋ በል የሚለው፣ ለነገ ለዘለቄታው የሚሆንን ህጋዊውን ሥርዓትና መስመር የሚያስይዘው ሰው የለውም ወይ ባገሩ? ማመን ያቅተኛል፡፡
ስለ አሌክስ ደ ዋል አንድ በጣም የገረመኝን ነገር ተናግሬ ላብቃ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ ምሁሩ አሌክስ ደ ዋል በቅርቡ ባሰፈረው ትንተናው በአብይ አህመድ፣ እንዲሁም ወደ መቃብር በላካቸው የቀድሞ ወያኔ ባልደረቦቹ (እነ አባይ ፀሐዬ) አማካይነት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ከኤርትራ፣ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር ስለፈጸመቻቸው ስምምነቶችና ተግባራት ሁሉ አንድም ሳያስቀር – በሚገርም ‹ፕሪሲዥን› እና ነጥብ-በነጥብ ተከታትሎ በገለልተኝነት የወረዛ ትንተናውን በቢቢሲ አማካይነት ለዓለም አሰራጨ፡፡ እነ አብይ አህመድስ ከአሌክስ ደ ዋል ማጋለጥ በኋላ ምን ምላሽ ሰጡ? የምንገምተው ‹‹ደብቁኝ-ደብቁኝ›› ይላሉ ብለን ነው አይደል? የአሌክስ ደ ዋል ትንተና ለዓለም ይፋ በሆነ ማግስት ግን እነ አብይ አህመድ ያደረጉት ያንን አይደለም፡፡ ‹‹የሶማሌ ክልሉ›› ርዕሰ-መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በትዊተር ገጹ ብቅ አለና – አሌክስ ደ ዋል ላይ የውግዘት ውርጅብኝ አዘነበበት! ምላሹ ይህ ነበር የአብይ አህመድ!
እጅግ ገረመኝ በእውነቱ ይህ ሰው! በዓለም አደባባይ የሚታወቅን እውነት ለማበል፣ ባህር ተሻግሮ ሀገር ያወቀውን የአፍሪካ ቀንድ ምሁር ስም እየጠራ በካድሬ የቃላት ጅራፍ ለመግረፍ የተላበሰው አሰቃቂ ወኔ አሳቀቀኝ፡፡ አሸማቃቂ ልሽቀት! በ1930ዎቹ ኦሮሞዎችን ‹‹የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ሃዲድን እየነቀሉ ለጦር መሥሪያ የሚያውሉ ያልሰለጠኑ ጋሎች›› ብሎ በጉዞ ማስታወሻ መጽሐፉ ላይ አስፍሮ የተገኘውን ኤቭሊን ቮግን ሰውየው ከሞተ በስንትና ስንት ዓመቱ፣ እና መጽሐፉ ከታተመ በ90 ዓመቱ ሰውየውን ፋሺስት፣ ናዚ፣ ሰላይ፣ ደንቆሮ በማለት የስም-ማጥፋት ጅራፍ ያወረደበት አንድ የኦሮሞ ገራፊም (የብዕር ገራፊ) – በአሌክስ ደ ዋል ከደረሰበት የቃላት ውርጅብኝ ጋር አብሮ ትዝ አለኝ፡፡
አመንንም አላመንንም ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው የአብይ አህመድ ሥርዓት ባለ ገጀራ ደም አፍሳሾችን ብቻ ሳይሆን፣ ባለ ብዕር አብዮት-ጠባቂ ካድሬዎችንም ያሰማራ ሥርዓት መሆኑ ባደባባይ እየተገለጠ ነው! የገባንበት አገዛዝ – በሥልጣኑና በወከለው የዘር ከረጢት የመጡበትን ምሁራንና ፀሐፊያን – እንዲህ ከሩቅ እያነፈነፈ የነገር አዳፍኔ መልቀቁን ተያይዞታል፡፡ ሥርዓቱን ተችተህ፣ እውነቱን ተጋፍጠህ አደባባይ ብትወጣ – ሥርዓቱ አይምሬ ነው፡፡ ሀገር ውስጥ ካለህ ይገድልሃል፣ ይግባኝ ወደማትልበት እስርቤት ይጨምርሃል፡፡ የትም ግባ፣ ማንም ሁን – ረዥም ያነጣጠረ አፀፋዊ የዘለፋ ስከድ ሚሳይሉን ይተኩስብሃል! ከረቀቀውና ሤረኛው የወያኔ የባንዶች ሥርዓት ወጣን ብለን ሳናበቃ፣ ለመሻሻል፣ ምክር ለመስማት፣ ለመተቸት ዕድል ወደማይሰጥና በባንዳዊ ስሌት ሥልጣኑ ላይ አተኩሮ ወደሚሠራ ይሉኝታ-ቢስ አገዛዝ ተሸጋግረናል!
ጽሑፌን ሳጠቃልል – የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በእነዚህ ዓይነት ፀረ-እውነትና ፀረ-ይሉኝታ ሰዎች እጅ ገብቶ እየተዘወረ ነው፡፡ የሀገሪቱ ህዝብ መጻዔ ዕጣ-ፈንታ፣ ብሔራዊ ጥቅምና የሀገሪቱ ሉዓላዊነት ሁሉ ተጠቃልለው በአንድ ግለሰብ እጅ ወድቀው – በዚህም በዚያም አቅጣጫ ለጊዜያዊ ሥልጣን ማስጠበቂያነት ግልጋሎት – በቅያሬነት እየተመፀወቱ ነው፡፡
ለመሆኑ ሥርዓቱ ወደየት እየወሰደን ነው? አብይ አህመድ ዛሬ በሁሉም ዋጋ (‹‹አት ኦል ኮስትስ!››) ሊያስጠብቀው ቆርጦ የተነሳለት ሥልጣን፣ ለነገ በያቅጣጫው ምን ዓይነት ግጭትን ነው ደግሶልን እያለፈ ያለው? ከዚህ የኢትዮጵያችን የዳግም ‹‹አብሶሉት ዲክታተርሺፕ›› ጅማሮ መሐል – ለነገ የሚተርፍ የዲሞክራሲ ተስፋ ማድረግ ይታሰባል ወይ ለመሆኑ? አንድ ግለሰብ እንዳሻው እንዲያንቦጫርቀው የፈቀድንለትን ሀገርን አሳልፎ የመስጠት፣ የሉዓላዊነት፣ እና የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይስ በህግ ማስኬድ፣ በሥርዓት ማስገዛት፣ በአግባቡ እንዲመራ ማድረግና ልጓም ማበጀትስ ይቻላል ወይስ አይቻልም?
አሁን ለሁሉም ነገር ሽፋን እየሆነ ያለው የወያኔዎች ሽኝት ጉዳይ ይመስላል፡፡ እንደኔ እንደኔ ያ የወያኔ ሥርዓተ-ቀብር የመጠናቀቁ ፊሽካ በቅርቡ ከአብይ አህመድ አፍ መሰማቱ አይቀርም፡፡ እስከዚያው ድረስስ ግን – ምን ያህሉ ሉዓላዊ ግዛታችን፣ ምን ያህሉስ ብሔራዊ ጥቅማችን፣ ምን ያህሉስ የመጪው ትውልድ ሀብትና ቅርሶች ተሸቅለው፣ ተዘክረው፣ ተለቅተው ይጠብቁን ይሆን? አንድዬ ይወቅ! አንድዬ ይሁነን! የአባቶቻችን አምላክ ሳናውቀው ከመወሰድ ይጠብቀን፡፡ ለጊዜው አበቃሁ! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic