>

ብሔራዊ ጥቅም ሲባል????  (ሔቨን ዮሐንስ)

ብሔራዊ ጥቅም ሲባል???? 

ሔቨን ዮሐንስ

ብሔራዊ ጥቅም በጀኔራል ቻርለስ ደጎል አንደበት
አገራት የየራሳቸው አንፀብረቅራቂ ታሪክ ያላቸው ጀግኖች አላቸው! ለዛሬው የፍቅር አድባር መሆኗ የሚመሰከርላት ፈረንሳይን እንቃኝ። ፈረንሳይ በዘመና ብዙ የጦርነት ታሪክ አስተናግዳለች፤ ስትወር ስትወረር መሆኑ ነው። የሆነው ሆኖ በመውረርም ይሁን በመወረራ ጊዜ ስለ አገራቸው ክብር የተዋጉ ብዙ ጀግኖችም ነበሯት! ከእነዚህም አንዱ የፈረንሳይ ጀግና #ጀነራል_ቻርለስ_ደጎል ነው። በአርግጥ ለፈረንሳዮች እኚህ ሰው ታላቅ ጀግና ናቸው።
ጀኔራል ደጎል ለፓሪስ ያልሆኑላት የለም። ደራሲም ወታደርም መሪም አዋጊ ጀኔራልም ሆነው አገልግለዋታል። ቻርለስ ደጎል ስለ ብሄራዊ ጥቅም በሕይወታቸው ማምሻ አካባቢ ሲናገሩ ያስቅደሙት በአውሮፓዊያኑ ሰኔ 18 ቀን 1940 ለንደን ውስጥ ቢቢሲ ራዲዮ 4 ላይ ቀርበው ያደረጉትን ታሪካዊ ንግግር ነው። ያ ታሪካዊ ንግግራቸው የሚያተኩረው በወቅቱ ሂትለር መራሽ መስፋፋቱ ፓሪስ ዘልቆ በፈረንሳይ የሂትለር አሻንጉሊት መንግስት መመስረቱን ተከትሎ ነው።
“ፓሪስ አልተንበረከከችም”!
“ያኔ” ይላሉ ጀኔራል ደጎል “እጅግ የተበሳጨሁት ለአገሬ ሰዎች ከሂትለር በፊት ያደረኩትን የማንቂያ ደዎል ሳስብ ነው። ቀድሜ ለአገሬ ሰዎች የማዚኖ አጥር ድንጋይ ነው የሚል ጭብጥ ያለው መጽሐፍ ደርሼ አሰራጭቼ ነበር። የአገሬ ህዝብ ግን ልብ ብሎ አላነበበውም።
የመጽሐፉ ቁም ነገር ሲፈተሽ ፈረንሳይ ጀርመን እና ሌሎች አገራት ድጋሚ ጥቃት እንዳይፈፅሙ በሚል ድንበሯን በረዥም የድንጋይ አጥር ከልላ ነበር። #የማዚኖ_አጥር የሚባለው።”
ታላቁ ደራሲ እና የጦር መኮንን ጀኔራል ቻርለስ ደጎል ግን የማዚኖ አጥር ድንጋይ ነው። ፈረንሳይ ዘመናዊ ጦር መገንባት አለባት፤ ዘመናዊ ታንኮች ሊፈበረኩ ይገባል ነበር ጉትጎታው። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ማግስት ፓሪሶች ለእኚህ ጀኔራል ጆሮ ነፍገዋቸው ነበር። እርሳቸውም ፓሪስ ስትጠራኝ እመለሳለሁ ብለው ወደ ሚወዱት የድርሰት ስራ ተመለሱ ፓሪስን የኋሊት ትተዋት ወደ ገጠራማው አካባቢ ተጓዙ።
ሂትለር ስልጣን ሲጨብጥ ደግም መስፋፋቱን ሲጀምር ቻርለስ እንዳሉት የማዚኖ አጥር ድንጋይ ሆኖ በሂትለር ዘመናዊ ታንክ በደቂቃዎች ውስጥ ተደርምሶ ፈረንሳይ በሂትለር ብረት መዳፍ ስር ወደቀች። አሁን ፓሪስ የገፋችውን ጀኔራል መልሳለ ጠራች ጀኔራል ቻርልስ ደጎል የት አለ ስትል ድምፃን ከፍ አድርጋ ተጣራች
ጀኔራሉም ፓሪስ ስትጠራኝ እመጣለሁ አይደል ያሉት ከተፍ አሉ፤ ፓሪስ ሳይህን ለንደን።
የመረጃውን ጦርነት ቀድመው ከፈቱት፤ ቢቢሲ ላይ ቀርበው “ፓሪስ አልተንበረከከችም” የሂትለር አሻንጉለቲ መንግስት ሳይሆን እኛ ነን የፓሪስ የቁርጥ ቀን ልጆች መሪዎች አሉ። ይህን ንግግራቸው እና ድርጊታቸውን በረዥሙ ካስታወሱ በኋላ ለብሄራዊ ጥቅም ዘብ መቆም ማለት አገር አደጋ ውስጥ በገባች ጊዜ እንጂ በሰላም ጊዜ አርበኛ መሆን አይደለም ይላሉ።
አገር በአራቱም አቅጣጫዎች ከውስጥም ከውጭም ስጋት ከተጋረጠባት እነዚያን መንታ ስጋቶች ለማክሸፍ በሞራል ከፍታ የተግባር ሰው መሆን ነው ይላሉ። እኔም ያደረግኩት ይህን ወርቃማ እድል ነው ባይ ናቸው። አይ ታላቁ ደጎል ወርቃማ እድል አሉት አይደል።
ለቻርልስ ደጎል ብሄራዊ ጥቅም ማለት
አገር ክንደ ፈጣማ እንድትሆን በሁሉም ዘርፍ መትጋት
በአስችጋሪ ጊዜ ሲጠሩ አቤት ወደዬት ማለት
ጥላትን ፊት ለፊት በጦር በጎራዴ ብቻ ሳይሆን በመረጃ ጦርነትም መፋለም ከሁለም በላይ ግን አገሬ አልተንበረከከችም ብሎ የሞራል ከፍታን አንስቶ ለሰንደቅ ዓላማዋ መፋለም ቀዳሚው ነው ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅም በኮንዶሊዛ ራይስ አንደበት
ከዝነኞቹ የአሜሪካ የፖሊሲ ጉዳይ የጥናት ማዕከላት መካከል አንዱ የሆነው ሁቨር ኢንስቲቲዩት ትልቁ አዳራሽ በታላላቅ እንግዶች እና በጀማሪ ዲፕሎማቶች ፣በአለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ተከታታዮች እና መምህራን እንዲሁም የዋሽንግተን ባለስልጣናት ታድመውበታል።
ጊዜው ሰኔ 14 2000 ዓመት ምህረት በአውሮፓዊያኑ ነበር። የቴክሳሱ አገረ ገዥ በዚያ አዳራሽ የመገኘታቸው ሁኔታ ታላላቅ ባለስልጣናትን ለታናሹ ቡሽ የምርጫ ቅሰቀሳ ድጋፍ የሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫዎች ላይ ሀሳብ እንዲሰጡ ይጋብዛሉ የሚል ጭምጭምታ ተሰምቶ ነበር።
የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቁ ሄነሪ ኪሲንጀር እና የያኔው ሹም ኮሊን ፖል ከሁለት አንዳቸው ወደ ሆቨር አዳራሽ ወደ መድረክ ይወጣሉ በሚል እተጠበቀ ነበር።
የሆነው ግን ተቃራኒው ነው።
ኒዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሁነቱን ባሰፈረበት አምድ ላይ እንዳብራራው ያኔ 45 ዓመት የሞላቸው የስታንፎርድ ዩኒቨርሲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሯ ኮንዶሊዛ ራይስ ነበሩ የተጋበዙት።
የኮንዶሊዛ ራስ የንግግር አጀንዳ ደግሞ ለብሄራዊ ጥቅም መታገል(Promoting national interest ) የሚል ነበር። ለስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ ራይስ የንግግር መክፈቻ ቃላት በእርግጥ ከድህረ ሶቬት ህብረት ማግስት ምን በብሄራዊ ጥቅማች ላይ አደጋ የሚደቅኑ እነማን ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥያቄ የሚያጭሩ ነበሩ።
ለኮንዶሊዛ ራይስ ብሄራዊ ጥቅምን ለማስከበር ከመትጋት በፊት ብሄራዊ አጀንዳ መቅረፅ እና ብሄራዊ ትልም ማስመር ይቀድማል። እነዚህን ሁነቶች በግልፅ የሚረዳ ዜጋ ደግሞ ለእነዚህ መሳካት ሌት ከቀን ከልዩነት ይልቅ በትብብር ለሀገሩ ጥቅም ይዋደቃል ነው ነገሩ።
መረጃ፣ቴክኖሎጂ እና እውቀት እና ጥበብን ማዳበር ደግሞ ለብሄራዊ ጥቅም መከበር ትልቅ መወጣጫ መሰላሎች ናቸው።የምጣኔ ሀብት የእድገት ምሰሶዎችን በግልፅ አስቀምጦ አካታች መተግበሪያ ስልቶችን ማንበር ሌላኛው ወሳኝ ምዕራፍ ነው።
የፖሊሲ ጉዳዮች መጀመሪያ መረቀቅ ያለባቸው በባለስልጣናት አልያም በካቢኔዎች ሳይሆን በሀሳብ አፍላቂዎች ፣ለሀገር ጥቅም ሟች በሆኑ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆን አለበት ነው ምክረ ሀሳባቸው። ኮንዶሊዛ ራይስ ያኔ ያሰሙት ንግግር ብሪታንያ ሰኔ 23 ቀን 2016 ከአውሮፓ ህብረት የመነጠል ውሳኔ ማግስት ዘ ኢኮኖሚስት ላተመው አንድ ርዕሰ ጉዳይ መነሻ ሆነዋል።
የአገር ብሄራዊ ጥቅም አደጋ ውስጥ የሚገባው ስልጣን በጓደኝነት ወይም ዲሞክራሲን መሰረት ሲያደርግ (the elite that failed .the economist 2016) ነው ይላል። አፍቃሪ ሪፐብሊካኗ እመቤት ኮንዶሊዛ ራይስ እንደሚሉት አምስት ነጥቦች ላይ ቅድሚያ ትኩረት ማድርግ ብሔራዊ ጥቅምን ለማሰጥበቅ እጅግ ወሳኝ የመሪዎች ሚና ነው። ዜጎች ደግሞ ለተቀመጡ ግቦች መሳካት የራሳቸውን ጠጠር ይጥላሉ።
ቀዳሚው ወታደራዊ አቅምን ማፈርጠም እና የደህንነት ተቋማት ብቃትን ማሳደግ፣ የምጣኔ ሀብት እድገትን አፋጣኝ ፖሊሲ ማውጣት እና መተግበር፣ ወዳጅ እና አጋር አገራትን ማብዛት እና ግንኙነትን በመርህ ላይ ማጠናከር፣ የምንጊዜ ጥላትን አካሄድ ማጤን እና በየጊዜው ፈጣን አፀፋ መውሰድ፣ብሄራዊ ጥቅምን የሚገዳደሩ መንግስታት ወደ በትረ ስልጣን ሲመጡም ከወደጅ አገራት ጋር በመሆን የፖሊሲያቸውን አንካሳነት በዓለም አደባባይ መሞገት የሚሉ ናቸው።
የኮንዶሊዛ ራይስን ሙሉ ንግግር ከዚህ በታች ባለው ማስፈንጠሪያ በመጫን ማንበብ ይቻላል።
ይቀጥላል….
ሸጋ ነገር እንዲገጥማችሁ፤ ሸጋ ሸጋውን ተመኙ!
Filed in: Amharic