ታላቁ ንጉሥ፡ ንጉሥ ሚካኤል ንጉሠ ጽዮን ፡ ወወሎ ፡ ወትግሬ፡ ወጎንደር፡ ወጎጃም ሲታወሱ
አቻምየለህ ታምሩ
በየዕለቱ የሚከሰተቱ ተለዋዋጭ ነገሮች ስለታሪካቸውና ስራቸው ልንነግርላቸው የግድ የሚሉ ታላላቅ አባቶቻችንንና ስራዎቻቸውን ባቀድነው መልኩ እንዳናስታውስ አድርጎናል። እንደ አቅሚቲ ለረጅም ጊዜያት ለመዘከር ሳስባቸው ከኖርኋቸው አገር አውል ታላላቅ የኢትዮጵያ አባቶች መካከል ንጉሥ ሚካኤል ቀዳሚው ናቸው። ሆኖም ግን በአንዱ ላይ አንዱ እየተደራረበ ስለሳቸው በንባብ ያወቅሁትን ታሪካቸውን ለማውሳት ረጅም ጊዜ አልፏል።
የሆነው ሆኖ ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት ሲወጡ ሲወርዱ ኖረው ለአገር ከዋሉት ውለታ አኳያ በሚገባቸው ደረጃ ስማቸውና ስራቸው ባለመታወሱ ሲቆጩኝ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ አርበኛ ነገሥታት መካከል ንጉሥ ሚካኤል ግንባር ቀደሙ ናቸው። ንጉሥ ሚካኤል ለአገራቸው አሞራ የነበሩ፤ የአገር ፍቅር ስሜታቸው በጣም ከፍተኛ የነበረና በአስተዳደር ረገድም ቢሆን ታላቁ ዐፄ ምኒልክ ሳይቀር “አስተዳደርስ እንደ ራስ ሚካኤል ነው እንጂ [1]” ሲሉ የመሰከሩላቸው ታላቅ አስተዳዳሪ ነበሩ።
በፈረስን ስማቸው አባ ሻንቆ በመባል የሚታወቁት ንጉሥ ሚካኤል የልጅነት ስማቸው መሐመድ ሲሆን የተወለዱት ከአባታቸው ከይማሙ ዓሊ አባ ቡላ እና ከእናታቸው ከግንደ በረቷ ወይዘሮ ጌቴ ገባቤ ጥር 27 ቀን 1833 ዓ.ም. ወሎ ውስጥ ነው።[2] ንጉሥ ሚካኤል ራሳቸውም የተወለደቱበት ቀን ጥር 27 ቀን መሆኑን በግራኝ ፈርሶ ይኖር የነበረን ደሴ ከተማ ውስጥ የሚገኝ የመድኀኒያለም ቤተክርስቲያ አሳድሰው ሲጨርሱ ባስቀመጡት የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ገልጽዋል። በድንጋዩ ላይ ያስቀረጹት ጽሑፍ እንዲህ ይላል [የድንጋይ ላይ ጽሑፉ ከታች ተያይዟል [3]]፤
“ይህንን ቤተክርስቲያን ባጼ ልብነ ድንግል መንግሥት ግራኝ አጠፋው፤ ከዚያ ሲጀምር እስከ አጼ ምኒልክ ድረስ ነገሥታቱ 23፤ መሳፍንቱ 9 ናቸው። ዘመኑም ቢቆጠር 423 ዓመታት፡
ከ9 ወር 12 ቀን ሆነ፤ ከዚህ በኋላ እኔ ራስ ሚካኤል ባስጀመርሁ በሶስት ወራት ከ10 ቀን በእግዚያብሔር ፍቃድ ተፈጸመ። ለፈጣሪዬ ክብር ምስጋና ይግባው። ታቦቱም መድኀኒያለም ነው፤ እኔም የተወለድሁበት የጥር መድኀኒያለም ዕለት ነው፤ ልጄም እያሱ የጥር መድኀኒያለ ዕለት ተወለደ።
ሚያዚያ 30 ቀን 1905 ዓመተ ምሕርተት ተጻፈ”
ንጉሥ ሚካኤል ወሎ ውስጥ በግራኝ የፈረሱትን ታላቁን ደብር ርዕሰ አድባራት ወገዳማት ተድባበ ማርያም ጨምሩ በርካታ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲታደሱና ሕዝብ እንዲገለገልባቸው አድርገዋል።
ንጉሥ ሚካኤል ከክርስቲያንም ከእስላምም ቤተሰብ የሚወለዱ ሲሆን ከጎንደርና ወሎ የአማራ ቤተሰቦች የሚወለዱ የዐፄ ፋሲል ሰባተኛ ትውልድ ናቸው። የትውልዳቸው ሐረጋቸው እንዲህ ነው። ዐፄ ፋሲል ልዕልት ሰብለ ወንጌልን ይወልዳሉ፤ ልዕልት ሰብለ ወንጌል ደጃዝማች አኖሪዎስን ይወልዳሉ፤ ደጃዝማች አኖሪዎስ ደጃዝማች ወልደ አረጋይን ይወልዳሉ፤ ደጃዝማች ወልደ አረጋይ አማንን ይወልዳሉ፤ አማን ከወይዘሮ ነጭት ስኄንን ይወልዳሉ፤ ወይዘሮ ስኂን ደጃዝማች ሊበንን ይወልዳሉ፤ ደጃዝማች ሊበን ከዋድላ ደላንታዋ ከወይዘሮ ስንዱ ጎሹ ደጃዝማች አሊን ይወልዳሉ፤ ደጃዝማች አሊ ከግንደ በረቷ ወይዘሮ ጌቴ ንጉሥ ሚካኤልን ወለዱ። [4]
ንጉሥ ሚካኤል ግዛት የጀመሩት በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን በ1855 ዓ.ም. በወረሂመኖ በመሾም ነበር። በዐፄ ቴዎድሮስ ሥር ሆነ ለ6 ዓመታት በይማምነት ወረሂመኖን አስተዳድረዋል። ከዚያም በ1870 ዓ.ም. በዐፄ ዮሐንስ ክርስትና ተነስተው ስመ ጥምቀታቸው ሚካኤል እስኪባል ድረስ ለ9 ዓመታት በንጉሥ ምኒልክ ንጉሠ ሸዋ ሥር የባለቤታቸውን የወይዘሮ ባፈናን ልጅ ወይዘሮ ማናለብሽን አግብተው ይማሙ መሐመድ አሊ ሆነው ለ9 ዓመታት መረሂመኖን አስተዳድረዋል። [5]
ከዚያም ወሎን ጠቅልለው በመያዝ ንጉሥ እስከተባሉበት ግንቦት 23 ቀን 1906 ዓ.ም. ድረስ በዐፄ ዮሐንስና በዐፄ ምኒልክ ስር ለ35 ዓመታት ያህል በራስነት አስተዳድረዋል። [6] በነዚህ ዘመናት ውስጥ ኢትዮጵያ በውጭ ጠላት የተወረረችበትና ራስ ሚካኤል ቀድመው በመድረስ ያልተከላከሉት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣ ጥቃት የለም። በዐፄ ዮሐንስ ዘመን በተካሄዱት በጉንደት፣ በጉራዕ፣ በዶጋሊና በሰሐጢ ጦርነቶች ሁሉ ራስ ሚካኤል ቀድሞ ደራሽ በመሆን ኢትዮጵያን ወራሪዎች ጥቃት ተከላክለዋል። ዐፄ ዮሐንስ በወደቁበት የመተማ ጦርነትም ከዋና ዋና የጦር መሪዎች መካክል ራስ ሚካኤል ቀዳሚው ናቸው። በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመን በተካሄደው የአድዋ ጦርነትም ከዋና ዋና የአድዋ ጦርነት አዝማቾች መካከል ራስ ሚካኤል ቀዳሚው ናቸው።
ባጠቃላይ በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የንጉሥ ሚካኤልን ያህል የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በተደፈረ ቁጥር ቀድሞ በመድረስ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሲከላከል የኖረ ራስም ሆነ ንጉሥ የለም። በዐፄ ዮሐንስ ዘመን አምስት ጊዜ ማለትም በጉንደት፣ በጉራ፣ በሰሐጢ፣ በዶጋሊና በመተማ፤ በዐፄ ምኒልክ ዘመን ደግሞ አንድ ጊዜ ማለትም በአድዋ ዘምቶ በጠቅላላው ስድስት በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ በውጭ ወራሪዎችም የተቃጣውን ጥቃት ዘምቶ ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጋር በብዛት የተዋጋ ንጉሥ ወይም ንጉሠ ነገሥት የምናገኘው ንጉሥ ሚካኤልን ብቻ ነው። ለዚህም ነበር ንጉሥ ሚካኤል ኢትዮጵያ በውጭ ጠላቶቿ በተጠቃች ጊዜ ሁሉ ቀድመው የሚገኙ አገር ወዳድ አሞራ ነበሩ ያልሁት።
ንጉሥ ሚካኤል ንጉሠ ጽዮን ፡ ወወሎ ፡ ወትግሬ፡ ወጎንደር፡ ወጎጃም በሆኑ በአመታቸው በጉንደት፣ በጉራ፣ በሐጢና በዶጋሊ ጦርነቶች የተከላከሉትን ከመረብ ማዶ ያለውን የኢትዮጵያ ክፍል ማለትም የዛሬውን ኤርትራን የአንደኛው የአለም ጦርነት የፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅመው ጣሊያን በትሪፖሊው ጦርነት በተጠመደበት መረብን ተሻግረው ለመዝመት በ1907 ዓ.ም. የሚከተለውን አዋጅ አስነግረው ነበር[7]፤
“ከእንግዲህ ወዲህ የየሐንስን ምድር ባሕር ምድርን ከመሞቴ በፊት ማስመለስ አለብኝ። ሹማምንቶችና ወታደሮች ሆይ፤ ፈረሶቻችሁንና በቅሎዎቻችሁን ጫኑ፤ ቀልባቸውም፤ ስንቃችሁንም ሰንቁ፤”
የታቀደው ሳይሆን አንደኛው የአለም ጦርነት ተጠናቀቀ። ሆኖም ግን ይህ የንጉሥ ሚካኤል ህልም በአምቻቸው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በንጉሠ ነገሥቱና በጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሃብተ ወልድ ተጋድሎ እውን ቢሆንም ሕወሓት ባደረገው ተጋድሎ ኤርትራ ልትገነጠል ችላለች።
ንጉሥ ሚካኤል በሰገሌ ጦርነት ከተማረኩ በኋላ ጨቦ ውስጥ ደንዲ በተባለ ስፍራ በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ እጅ ታስረው ነበር። ደንዲ ላይ ሳሉ አንድ ዓመት ተኩል ከቆዩ በኋላ ቦታው ለጤናቸው ስላልተስማማቸው በንግሥት ዘውዲቱና በአልጋ ወራሽ ፈቃድ ወደ ሆለታ ከተማ እንዲዛወሩ ተደረገ። ሆለታ ስድስት ወር ያህል እንደተቀመጡ ጷግሜ 3 ቀን 1911 ዓ.ም. በ78 ዓመት ዕድሚያቸው ዐረፉ።
ሞታቸው አዲስ አበባ ላይ በተሰማ ጊዜ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪና ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ፣ እንዲሁም ራስ ካሳ ወደ ሆለታ ሄደው በዋጅቱ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስቀበሯቸው። ከዚያም በየካቲት 5 ቀን 1921 ዓ.ም. ዐፅማቸው ፈልሶ ወደ ወሎ ተወስዶ ከጣሊያን አገር ኢንጅነሮችን በማስመጣት እጹብ ድንቅ አድርገው ባሰሩት ተንታ ሚካኤል ተቀብሯል። [8]
ምንጮች፤
[1]. ጳውሎስ ኞኞ (2003)፥ አጤ ምኒልክ በአገር ውስጥ የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች፥ አስቴር ነጋ አሳታዊ ድርጅት፥ አዲስ አበባ፥ ገጽ 54.
[2]. ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (1998)፥ የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፤ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት፤ 1896-1922፥ አዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ፕሬስ፥ አዲስ አበባ፥ ገጽ 226.
[3] የድንጋይ ላይ ጽሑፉን ጨምሮ ከዚህ ጽሑፍ ጋር ያያዝኋቸውን ፎቶዎች ያገኘሁት ዶክተር ምስጋናው ታደሰ “Social and Political History of Wollo Province in Ethiopia: 1769-1916” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2019 ዓ.ም. በለዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ካቀረቡት የታሪክ ዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ወረቀት ነው።
[4]. ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (1998)፥ ገጽ 226.
[5]. ዝኒ ካማሁ፥ ገጽ 224.
[6]. ዝኒ ካማሁ
[7]. ጎበዜ ጣፈጠ(1988)፥ አባ ጤና ኢያሱ፥ ዩናይትድ ፕሪንተርስ፥ አዲስ አበባ፥ ገጽ 59.
[8]. ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (1998)፥ ገጽ 223-24.