>
5:18 pm - Wednesday June 15, 4310

በጽሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተወልድ   የኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ የወሰን ዶሴዎች ፍለጋ… (ሄቨን ዮሀንስ)

በጽሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ኃብተወልድ የኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ የወሰን ዶሴዎች ፍለጋ…

ሄቨን ዮሀንስ

የታላቁን ሰው ሃሳብ… ስራ… በትዕግስት ታነቡት ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ! መልካም ንባብ:-
እንደ መግቢያ
ጸሐፌ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ  በደርግ ከተገደሉ የአጼ ኃይለስላሴ 60 ሹማምንት አንዱ ናቸው፡፡ መስከረም 10 ቀን 1967 አመተምህረት ለመርማሪ ኮሚሲዎን አንድ ጽሁፍ አቀረቡ፡፡ ጽሁፉን ያቀረቡት ለሀገራቸው የሰሩትን ውለታ የሚዘረዝር ቢሆንም፤ በጥቂት ገጾች የተጠረዘው ጽሁፋቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ2003 አመተምህረት በአማርኛና በእንግሊዘኛ አሳትሞት ነበር፡፡ መጽሃፈቸው  ለህዝብ፣ ሀገርና ለመንግስት የሚጠቀም ብዙ ጠቋሚ መረጃዎች አሉት፡፡

1. ከጂቡቲ ጋር …

”አፋምቦን በምን አዃኋን እንዳስመለስኩ…”ጸሐፌ አክሊሉ ሀብተወልድ መስከረም 10 ቀን 1967 ለመርማሪ ኮሚሲዎን ያቀረቡት ጽሁፍ – በአ.አ.ዩ ፕሬስ በታተመው የአክሊሉ ማስታወሻ መጸሀፍ  ውስጥ ያሰፈሩትን እንመልከት፡፡
አፋምቦ በኢትዮጵያና በፈረንሳይ ሱማሌ ጠረፍ አጠገብ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ስትራቴጂክ የሆነ ሥፋራ ነው፡፡ ለአውሣንና የፈረንሳይን ሱማሌ ተራራማ በመሆን ኮንትሮል የሚያደርግ ፤ውሃም ያለበት ባጣም ጠቃሚ ስፍራ ነው፡፡ ፈረንሳዮች ሁልጊዜ የጂቡቲ ግዛታቸውን ለማስፋፋት ወደ አውሳና ድሬደዋ  ነበር ዓይናቸውን የሚያዘነብሉት /በ1906 ፈረንሳይ ፣እንግሊዝና ጣልያን ኢትዮጵያን በዞን ለመከፋፈል ያደረጉትን ውል ማየት ይቻላል፡፡/
ከ1936 -1942 አመተ ምህረት ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በኋላም ሚኒስትር የነበሩት አክሊሉ ሀብተወልድ ከ1944 ውል በኃላ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ለቀው ሲሄዱ ፈረንሳይዎች አፋምቦን መያዛቸውን ከእንግሊዝ ይሰማሉ፡፡ ወዲያው የፈረንሳይን አምባሳደር ጠርተው ተቃውሟቸውን በመግለጽ በፍጥነት እንዲለቁ ይጠይቃሉ፡፡ የፈረንሳይ አምበሳደር  ”አገሩ የፈረንሳይ ስለሆነ አንለቅም” ብሎ ይመልስላቸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክሊሉም ከአጼ ኃይለስላሴ ጋርም ከመንግስትም ጋር  ተመካክረው በኃይል ለመውሰድ ይወስናሉ፡፡ በወቅቱ የጦር ሚኒስትሩ  ራስ አበበ ፤ጂቡቲ ከነበሩት ፈረንሳዮች ጋር ለመዋጋት የሚያበቃ እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡ የአክሊሉ ሀሳብ ጂቡቲንም ለመያዝ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምንም በኃይል ማድረግ አለመቻሉ ሲታወቅ በዲፕሎማሲ ብቻ የተቻለውን እንዲያደርጉ ይታዘዛሉ፡፡
አክሊሉ ሀብተወልድ አምባሳደሩን ጠርተው ” እናንተም የኛ ነው ስትሉ እኛም የኛ ነው ስንል፤የሚለየን በጅቡቲና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገው የጠረፍ ውል ነው፡፡ተውሉ ጋር የተያያዘ ካርታ ፣የሸራ ካርታ የሚባል አለ፡፡ ስለዚህ አሁኑኑ አንድ ስምምነት ፕሮቶኮል ፈርመን ዲሊሜቴሽን ለማድረግ እንስማማ፤ይህንንም ስናደረግ አፋምቦ በውነት የማን እንደሁ ይታወቃል፡፡ ”አሉት፡፡ የፈረንሳይ አምባሳደሩም በመንግስቱ ስም ”አሁን ጦርነት ላይ ነው ያለነው፤ይህንን ለማድረግ ጊዜም የለ አፋምቦን አንለቅም ” አላቸው፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክሊሉ ሀብተወልድ ” አገራችንን ይዛችሁ አንለቅም ፤አገሩ የማን እንደሁ ለመነጋገርና ስምምነት ለማድረግ አንድ ስምምነት እናድርግ ብንል እምቢ ታላችሁ፣የፈረንሳይ አምባሳደርነትህን ፐሪቪሌጅ ሁሉ አንስተናል፡፡ ይህንንም የምናደረግው በመጨረሻ በላቫል ሬዢም ጊዜ እናንተ የኢትዮጵያን ነጻነት አናውቅም ብላችሁ የጣልያንን ይዞታ አውቃችሁ ስለነበር ነው፡፡ እናንተም በጀርመን አራት ዓመት ስለቴዛችሁ ፤የፈረንሳይ ነጻነት አናውቅም ፡፡ ያቀረብኩትን  የውል ሀሳብ መንግስትህ ተቀብሎ ለመፈረም ፍቃደኛ  የሆነ ጊዜ ፤ስምምነቱ ስንፈርም አንድ መግለጫ እናወጣለን፤ይኸውም ኢትዮጵያንና ፈረንሳይ በኦፊሲል እንደ ነጻ አገርና መንግስት የሚተዋወቁበትን፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን እንደ ፕራይቬት ሰው ነው የምንመለከትህ” (የአክሊሉ ማስታወሻ ገጽ73) አሉት፡፡
የፈረንሳይ አምባሳደርንይህንን ካሉት በኋላ ማናቸውንም ልዩ መብቶች አነሱበት፡፡ ባንዲራ D.C አውቶሞቢሉ ላይ ማድረግ እንዲከለከል ለፖሊስ ነገሩ፡፡ የዲፕሎማቲክ ኢሚዩኒቲ መነሳቱን ለመንግስቱ አስታውቆ መልሱን ሲጠባበቅ መቆየቱን አክሊሉ ሀብተወልድ ጽፈዋል፡፡ከተወሰኑ ቀናት በኋላም የፈረንሳይ መንግስት (ዳጎል ) በኢትዮጵያ ሀሳብ ተስማምተው ውሉ እንዲፈረም አምባሳደሩን አዘዘ፡፡ በዚሁ አኳኋን ፕሮቶኮሉንም ሁለቱ መንግስታት የሚተዋወቁበትም አብሮ ተፈረመ፡፡
ያጼ ምኒልክ ውል መሠረት በማድረግ /የውሉ ዓመት በ1897 እ.ኤ.አ በፈረንሳይ ሱማሌና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ድንበር መጀመሪያ ካርታ ላይ በኋላም መሬት ላይ ምልክት ለማድግ በሁለቱም በኩል ኮሚሽን ተቋቋመ ፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የኮሚሽኑ የጸጥታ ኃላፊ ኮሎኔል ክፍሌ እርገቱና  አቶ አበበ ገብረጻድቅ ነበሩ፡፡
አክሊሉ ሀብተወልድ በሥራው ወቅት ያጋጠማቸውን ዘርዝረው ጽፈዋል፡፡ ” የካርታ ሥራ ምንም ፕሪሲዝን / Precision /የሌለው በጣም ግልጽነት የጎደለው ነበር፡፡ ”አገሩን ሳያየው እቤቱ ቁጭ ብሎ ወሰኑ በዚህ በዚህ ስፋራ ያልፋል እያለ ነው ያሰመረው የሚሉት አክሊሉ፤ቦታው ላይ ሲኬድ ፈረንሳይዎች ከብዙ ጊዜያት ጀምሮ የቦታውን ስም ሁሉ ለውጠውት መገኘቱን ያወሳሉ፡፡
ለእነሱ ጥቅም በሚሆን አኳኋን ፣የሐይቁን ስም ጭምር ሁሉ መለወጣቸውንና ምስክሮቹ ሁሉ ለእንሱ የሚያደሉ መሆናቸውን የተረዱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክሊሉ፤በዲፕሎማሲ እንጂ በውሉ መሰረት የደንቡን እንደማያገኙ ከተረዱ በኋላ ወደ ፓሪስ አመሩ፡፡
ፓሪስ በመሄድ ያገኙት ወዳጃቸው የነበረውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን መሊረኒ ማየርን ነበር፡፡ ሁሉን ነገር አስረዱት፡፡ ፈረንሳይና ኢትዮጵያ ከድሮ ጀምሮ ያለቸውን ወዳጅነት ፤በኢትዮጵያ ባቡር የፈረንሳይን ጥቅም፣የጂቡቲ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ በር መሆኗን ፣የፈረንሳይ ሊሴ መኖር፣ይህ ሁሉ እያለ ፈረንሳይ በአፋምቦ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር መጣላት ጥቅም እንዳልሆነ ገልጹላቸው፡፡
በሁለተኛው ቀን  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መሲ ቤዶ ጋር ተገናኝተው ተነጋገሩ፡፡ የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም  ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ መካለሉ እንዲደረግ መስማማታቸውን  አስታወቋቸው፡፡ በንግግሩም ጊዜ አቶ አበበ ገብረጻድቅ የሚያስፈልገውን ዶኩዩመንት ይዘው ከአክሊሉ ሀብተወልድ ጋር ፓሪስ ይገኙ ነበር፡፡
(በዚህ አኳኋን በፈረንሳይ ሱማሌና በኢትዮጵያ መካከል ውሉን ተከትሎ አፋምቦን ወደኛ አድርጎ የዴሊሜቴሽኑ ሥራ አለቀ(ዶክሜንቱን ማየት)፡፡ ያን ጊዜም ፤ፈረንሳይ ጋዜጦጭ የፈረንሳይ መንግስት ያደረገውን ክሪቲክ አድርገው ”የማይገባ አገር ለኢትዮጵያ ተሰጠ ፤ጃንሆይና አክሊሉ የፈረንሳይ ጠላት ናቸው… የሚል ዘመቻ መደረጉን አክሊሉ ሀብተውልድ ይነግሩናል፡፡ በፈረንሳይ ፓርላማም ጉዳዩ ተነስቶ ክርክር ተደርጎ እንደነበርና ይህም የታሪክ ሰነድ በፈረንሳይ ቤተመዛግብት እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡)

 

2  ከሱዳን ጋር ….

ጋምቤላን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ያደረግሁት ነጐሳሲዎን (1954 -55)
 በአጼ ምኒልክና በእንግሊዞች መካከል(የሱዳንና የኢትዮጵያን ድንበር በተለይ የሚወስነው) በ1902 እ.ኤ.አ የተፈረመው ውል የሚለው ጋምቤላ በእንግሊዞች እጅ ይቆያል፤ ይኸውም እንግሊዝ እሱዳን እስካለች ድረስ ነው የሚል ነበር፡፡
በ1954 ተጃንሆይ ጋር እንግሊዝን የጐበኘን ጊዜ ለሚስተር ኤደን ጉዳዩን አነሳሁበት ፣ ”ሱዳን በቅርብ ጊዜ ነጻ መሆኑ አይቀርም ፤ስለዚህ በውሉ መሠረት አሁኑኑ ጋምቤላን ብታስረክቡን ” በማለት ፡፡እነሱም ፤ ”የሱዳን ነጻነት ገና ነው፤ ሁለትና ሦስት ዓመት ቢያንስ ይወስዳል፡፡ በውሉ መሠረት ሱዳንን እስከምንለቅ መጠበቅ አለባችሁ” ብሎ፤አጥብቆ ተከራከረ፡፡ እኔም ” ሱዳን ነጻ መንግስት እስክትሆን ጠብቀን በኋላ ተነሱ ወንድሞቻችን ጋር ጋምቤላን አስረክቡን እያልን መጣላት አንፈልግም/እናንተ መቼም ይህ ነው ሥራችሁ፡፡/ ስለዚህ አሁኑኑ አስረክቡን ” ብዬ  አጥብቄ ጠየቅሁ፡፡ በመጨረሻም አንድ ፎርሙላ ላይ ስምምነት  አድርገን ተለያየን ፡፡ ይህም ሱዳን ነጻ ተመውጣቱ ከሦስት ወር በፊት ሁለቱ መንግስታቶች ተነጋግረው ጋምቤላን እንዲያስረክቡ፡፡
ከሦስትና አራት ወር በኋላ አዲስ አበባንና ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ማርሻል ቲቶ ስለመጡ፤ተሳቸውና ተጃንሆይ ጋር ለጉብኝት ምጽዋ እንገኝ ነበር፡፡በሬዲዎን ስንሰማ፤ታምስት ቀን በኋላ እንግሊዝ ለሱዳን ነጻነቷን የሚሰጥ መሆኑን ወሬው አተተ፡፡ ሁለትና ሦስት ዓመት የተባለው ውሸት ሆነ፡፡ እንግሊዝ ጋምቤላን ሳትለቅ ለሱዳን አስረክባ ልትሄድ መሆኑንና ፤ተሱዳንም መንግስት ጋር ኮንፍሊክት እንደሚሆን ግልጽ ነበር፡፡
 ጉዳዩ ለጃንሆይ አስረድቼ ፤ወዲያውኑ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ ኖቱን ሰጠሁት፡፡ የኖቱም ቃል የሚለው ፤ ”በውሉ መሠረት ጋምቤላን እንግሊዞች የሚይዙት  ሱዳንእስካሉ ድረስ ነው፡፡ አሁን እንግሊዞች በድንገት ሱዳንን ስለሚለቁ ፤በውሉና ተሱዳን ጋር በተስማማነው መሠረት ተሰኞ ጀምሮ / ተሁለት ቀን በኋላ / ኢትዮጵያ ጋምቤላን ይይዛል” የሚል ነበር፡፡ እሱም ፕሮቴስት አድርጎ ለመንግስቱ የኖቱን ቃል አስተላልፋለሁ አለ፡፡ ለሱዳን የውስጥ አስተዳደር ባለሥልጣኖችም አንድ ቴሌግራም በአቶ መለሰ አንዶም በኩል /ያን ጊዜ የኛ ሊኢዞን ኦፊሰር አሁን ካይሮ አምባሳደር / ላክሁ፡፡ይኸው የሚለው ፤ ለነጻነታችሁ ጥልቅና መልከም ምኞታችንንና ወደፊትም እንደወንድማማቾች አብረን እንድንሠራ ፤ጋምቤላ በኮሎኒአሊስቶች በኃይል ተይዞብን ስለነበር ተሰኞ ጀምሮ ኦኮፓይ ማድረጋችንን ፤ግን ይህንን ወዳጅነታችንን የማይነካና ሱዳንም ቆንሲልና ማናቸውም ቤትና ኢንስቶሌሽን ቢኖር ለጊዜው ለመቆየት መቻሉን የሚገልጽ ነበር፡፡ እነሱም በነጻነታቸው ለጊዜው በደስታ የተጥለቀለቁ ስለሆነ፤ተምስጋና ጋር በምናደርገውም መስማማታቸውን የሚገልጽ መልስ ሰጡ፡፡
 እንደተባለው ሰኞ ባቅራቢያው የሚገኝ የፖሊስ ኃይል ጋምቤላ ገብቶ የኢትዮጵያን ባንዲራ አውለበለበ ፤ አድሚኒስትሬሽኑን ያዘ፡፡ ምንም አክሲደንት አልደረሰ፡፡
ተሦስት ወር በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሚመራ የሱዳን ዴሊጌሽን ጋምቤላ ስላላቸው ኢንስቶሌሽን ለመነጋገር አዲስ አበባ መጡ፡፡ በንግግራችንም ጊዜ በቁጣ መልክ ፣” ለእንግሊዞች የፈቀዳችሁትን ጋምቤላን ለምን ለኛ ለአፍሪካኖች ትነፍጉናላችሁ ʔጋምቤላን መልሱልን ” በማለት ከሥረ ነገሩ መግባት ጀመሩ፡፡ እኔም ፣” እንግሊዞች ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካን በሚከፋፍሉበት ጊዜያት በኃይል የያዙብን ነው፡፡አሁን ኮሎኒ ሁሉ ነጻ ይውጣ ሲባል እናንተ ይህን እንዴት ትጠይቃላችሁʔ ይልቅስ በወንድማማች መንፈስ የምትወስዱትን ዕቃ ዘርዝር ብንነጋገር ይሻላል፤ስትመጡ በዚህ ብቻ መሆኑን የተለዋወጥነው ኖት ያስረዳል፡፡ ተዚያ በቀር ሌላ ጉዳይ ለመነጋገር የተስማማንበት ፕሮሲጀር አይፈቅድም ” አልኳቸው፡፡ እነሱም ተቆጥተው ስብሰባውን ጥለው ወጡ / ያን ጊዜ ተኔ ጋር ብላታ ዳዊት ፣ምክትል ሚኒስትር እንዳልካቸውና ዋና ዲሬክተሩ ነበሩ፡፡በዚህም እንዳልካቸው ደንግጦ ፤ምን ይሆን ብሎ ጠይቆ ነበር፡፡ ግድ የለም ፤አሁን እንስማማለን ስለው፣”እኔ መቸም ኤክስፒሪያንስ የርስዎን የለኝም ” ብሎ አደነቀ፡፡ ተወጡም በኋላ ለእንግሊዝ፣ለአሜሪካን አምባሳደሮች እየዞሩ ስሞታቸውን ያቀርቡ ጀመር፡፡ በኋላም እሱን (ሚኒስትሩን) ለብቻው ጠርቼ፤በረጀሙ አስረድቼው ፤ ተቁጣው ተመለሰ፡፡ አስፈካጊውን ስምምነት አደረግን ፡፡ ተዚያ በኋላ የጋምቤላ ጉዳይ በሱዳኖች ተነስቶም አያውቅም፡፡
 

3. ከኬኒያ፣ሱማሊያና ሱዳን ጋር….

ከውጭ ጉዳይ እንደገባሁ፤የኢትዮጵያ ወሰን ተሌሎች አገሮች ጋር በኢንተርናሽናል ውል መሠረት በትክክል መወሰን ዋና ጉዳይ አርጌ ነበር ያየሁት ፡፡ ይህም ወልወል በደረሰብን ኤክስፔሪያንስ ነው፡፡ ተዚያም በኋላ ያፋምቦ መጣ፡፡ ትንሽ መንግስት እንደመሆናችን መጠን የተከበብነው ፤ያን ጊዜ ፤ በነኛው በኮሎኒያሊስቶች ስለሆነ አጥራችንንን ደህና  አርጐ ማጠር አስፈላጊ ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ የወሰኑ ውል ፤ታጼ ምኒልክ ጋር / 1897 -1908 እ.አ.አ/ የተደረገ ቬግ የሆነ ፣ፕሪሲዥን የሌለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ተመወረሯ በፊት/1935/ ታንድ አገር ብቻ ነበር ወሰናችን የተከለለው ፡፡ ይኸውም ተእንግሊዝ ሱማሌ ጋር ነው፡፡ በዚሁ ምክንያት  ነው ተጐረቤት አገር ጋር በየጊዜው የፍሮንቲአር ኢንሲደንት የነበረን / ቤቪን፣ በኬኒያ በኩል ተናንተ ጋር ስላለው የድንበር ግጭት ፕሮቲስታሲዎን ያደረግንበት ወረቀት ይህን ቤት ይሞላል ብሎኝ ነበር/፡፡
ይህን ሁሉ ለጃንሆይ ታስረዳሁ በኋላ መጀመሪያ ጊዜ ሎንዶን ስሄድ /በ1946/ አንዱ ጉዳይ የተነጋገርሁበት ይህ ነበር፡፡/ተኔ ጋርም ጸሐፌ ትእዛዝ ተፈራወርቅ ነበሩ፡፡/ ዲሊሚቴሽን ለማድረግ የእንግሊዝ መንግስት ተስማምቶ ፣ይህንኑ ለመነጋገርና አንድ ፕሮቶኮል ለመፈራረም በቅርብ ጊዜ አንድ ዴሊጌሽን ወደ አዲስ አበባ እንደሚልክ አስታወቀ፡፡
የእንግሊዝ ዴሊጌሽንም ተመጣ በኋላ ፣ ውሉን መሠረት በማድረግ ካርታ ላይ መስመሩን ለማስመር ፣ አንድ ተእነሱና ተእኛ የተዋጣ ሚክስድ ኮሚሲዎን ተቋቋመ ፡፡ ሥራቸውንም ጀመሩ፡፡ ተእኛ በኩል እነ ኮሎኔል ክፍሉ፣አቶ አበበ ገብረጻዲቅና ሌሎችም ነበሩ፡፡ ብዙ ጊዜም ሥፍራውን እየሄዱ ይጎበኙ ነበር፡፡ በመጨረሻም የተስማሙበትን መስመር ለየመንግሥታቸው አቀርበው ተፈቀደ፡፡
ተዚህም በኋላ መሬቱ ላይ ዲሊሚቴሽን ተጀመረ፡፡ ብዙ ዓመትና ብዙ ገንዘብም ተፈጀ በኋላ ሥራው አለቀ፡፡ ተትንሽ አመት በኋላ ቀዳዱማ የሚባለው የውሃ ጉድጓድ ሕዝቡ ጠቃሚያችን ነው፤እንደ አድባርም የምንቆጥረው ነው ብሎ አቤት ስላለ ጉዳዩ እንዲታይ ተደረገ ፤በኮሚስዎን፡፡ የጉድጓዱ አከፋፈል የሚበልጠው ወደኛ እንዲሆን / ዘጠኝ ስፍራ ያለው  ጉድጓድ/፣ ለነሱ ደግሞ ሁለት ሥፍራ ያለ ጉድጓድ ነበር፡፡ሃሳቡ ፣ውሃ እናወጣለን በማለት የእኛም የነሱም ሕዝብ ወሰን እንዳያልፍ ኢንሲደንት እንዳይነሳ ነው፡፡በዚሁ ጉዳይ የሕዝብ ስሜት ስላለበት ቀዳዱማን እንዲመልሱ ለእንግሊዞች አስረደኋቸው፡፡ እነሱም ፣” የሚበቃ ውሃ ተኛ ይበልጥ አላችሁ ፤ግን ኢንሲስት ታድርጋላችሁ፤ በሱ ፋንታ የሰጠነውን የገር ክፍል መልሱና እኛም ቀዳዱመማን እንመልስ”ብለው ፤ጥያቄያችንን በጉድ ፌዝ ተቀበሉ፡፡ በዚሁ አኳኋን ጉዳዩ ተፈጽሞ የዚያን ክፍል እንደገና መሬቱ ላይ ምልክቶች እንዲደረግ ሆነ፡፡
ተዚያም ታመታት በኋላ ኬንያ ነጻ ስትወጣ ፣ድንበራችን ተከልሎ ስለቆዬ ፤ ተሷ ጋር በወዳጅነትና ወንድማማች መንፈስ እስታሁን እንኖራለን፡፡ ከፈረንሳይ ሱማሌ ጋር ያለን ወሰን እላይ በተባለው አኳኋን ስለተወሰነ፣ተእንግሊዝም ሱማሌ ጋር ያለው ተጦርነቱ በፊት አለቀ፡፡ ተኬንያም ጋር በዚሁ አኳኋን ሲያልቅ የሚቀረን ተጣልያን ሱማሌና ተሱዳን ጋር ያለው ድንበር ነው፡፡
ተጣልያን ሱማሌ ጋር ያለንን ለመወሰን፣ገና ሱማሌ በዩናይትድ ኔሽን ሞግዚትነትና በጣልያን አስተዳዳሪነት ባለች ጊዜ /ተ 1950 -1960/ የዩናይትድ ኔሽን ሪዞሊሽን እንደሚያዘውና በሱም መሠረት ለመወሰን ፣ ተጣልያኖች ጋር ብዙ ጉበዔ ተደርጐበታል፡፡ ብዙም ተደክሟል፡፡ ያን ጊዜ የኛን ዲሌጌሽን ፣ ስከወሰኑ ጉዳይ የሚነጋገረውን ፣የሚመራው አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ ነበር፡፡ ጉዳዩም የደረሰበትን ለዩናይትድ ኔሽን በየጊዜው እየቀረበ ሪዞሊሽን ያደረግበት ነበር፡፡  ያልተስማማንበትን ፣በሪዞሊሽኑ መሰረት ወደ አርቢትሬጅ ለመሄድ ፤ብዙ ታክቲክና ሳቦታጅ እያደረጉ ጉዳዩን ይጎትቱት ነበር/ ሁሉንም ለመረዳት ፕሮሲቬርባሉንና የዩናይትድ ኔሽንን ዶኩሜንት ማየት ያስፈልጋል ፡፡ ለዚሁ ሁሉ አቤቱታችንን ለዓለም ማህበር ማቅረብ አላቋረጥንም፡፡ ጉዳዩም ሳያልቅ ሱማሌ በ1960 ነጻ ወጣች ፡፡ጣልያኖች ጉዳዩን የሚጎትቱበትን አንድ ምክንያት ሱማሌዎችንም በመፍራት ነበር፡፡
ሱማሌ ነጻ ተወጣች በኋላ ወሰኑን ለመከለል በየጊዜው ፕሮፖዛል አቅርበንላቸው ነበር የነሱም መልስ ፣”ኡጋዴን የኛ ስለሆነ አንዋሰንም ነው፡፡ በሱዳን በኩል ያለውን ብዙ ጊዜ ተተነጋገርን በኋላ በመሠረቱ ስምምነት ላይ ደርሰናል/ ዶኩሜንቱን ማየት/ ፡፡
( አክሊሉ ማስታወሻ ገጽ 73- 80 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ 2003 አመተምህረት)
Filed in: Amharic