>

ፈተና የበዛበት የጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ‘የሰላም እና የይቅርታ’ መንገድ… (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

ፈተና የበዛበት የጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ‘የሰላም እና የይቅርታ’ መንገድ…

(ክፍል- ፩)

 

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


‘‘Power based on Love is a thousand times more Effective and Permanent than Power derived from Fear’’

‘‘ከፍርሃት ከሚመነጭ አምባ ገነንነትና ጥላቻ ከሠለጠነበት ኃይል/ሥልጣን ይልቅ ከፍቅር የሚመነጭ ሥልጣን ውጤታማና ዘላቂ ነው፤’’

(የህንድ የነጻነት አባት፣ ማኅተመ ጋንዲ)

 

 

  • ምክንያተ-ጽሕፈት

 

የዛሬው ጽሑፌን በአንድ የአስተውሎት ትዝብቴ መነሻነት ለመጀመር ወድድኹ፡፡ ከዚህ ጽሑፍ ጋር ተዛንቀው የቀረቡት፣ የምትመለከቷቸው የፍቅርና የይቅርታ መልእክትን ያዘሉ ምስሎች ይህን ጽሑፍ ለማዋለድ ዐቢይ ምክንያት ኾነዋል፡፡ ጥቅሶቹ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ ሰሞን ካደረጓቸው ንግግሮቻቸው መካከል የተወሰዱ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ እነዚህን ፍቅርንና ይቅርታን (ዕርቀ-ሰላምን) የሚሰብኩ ጥቅሶችን መሠረት አድርጌ ጥቂት ትዝብት አዘል ቁም ነገሮችን በማንሳት ወደጽሑፌ ዐቢይ ቁምነገር ላምራ፡፡

ከጥቂት ወራቶች በፊት የምሠራበት መስሪያ ቤት ከአንድ የፌዴራል ተቋም ጋር በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት ዙሪያ የሕዝብ አስተያየት ጥናት/Public Opinion Survey/Research ለማድረግ፣ የሐረሪ ሕዝብ ክልልን ጥናት ለማስተባበርና ለመሥራት ‘‘የፍቅር/የመቻቻል ከተማ’’ በመባል በምትጠራው እና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድ/ት (ዩኔስኮ)፣ ‘‘ዓለም አቀፍ የሰላም ከተማ’’ ተብላ በተሰየመችው በታሪካዊቷና በጥንታዊቷ የሐረር ከተማ የሁለት ሳምንት ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡

በሐረሪ ክልል ቆይታዬ በኢፊዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ የሚደረገውን ጥናት ግብአት የሚሆኑ ዓይነታዊ መረጃዎች/Qualitative Data’s ለማግኘት የሚደረገውን የቁልፍ መረጃ ሰጪ ቃለ-መጠይቅ/Key Informants Interview- KII እና የአትኩሮት ቡድን ውይይት/Focus Group Discussion- FGD ለመምራትና ለማስተባበር በአንድ ረፋድ ማለዳ ላይ በሐረሪ ሕዝብ ክልል ፍትሕ ቢሮ ተገኝቼ ነበር፡፡

በቀጠሮዬ ሰዓት ወደሐረሪ ሕዝብ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሳመራ በመስሪያ ቤቱ አጥር ዙሪያ የተለጠፉት ጥቅሶች ቀልቤን ሳቡትና ለአፍታ ያህል ቆሜ ጥቅሶቹን ማንበብ ጀመርኩ፡፡ የሐረሪ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሰፊውንና በረጅሙ አጥሩን- የጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ የእነ ማርቲን ሉተርን እና የኔልሰን ማንዴላን- ይቅርታን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን በሚሰብኩ ጥቅሶች ሞልቶታል፡፡ እንደው ለመሆኑ እነዚህ የሐረሪ ክልልን ፍትሕ ቢሮ አጥር ያስዋቡ ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ጥቅሶች በእውን በክልሉም ሆነ በተቀሩ የሀገራችን ክልሎች በተግባር እየተተረጎሙ ይሆን ብለን ብንጠይቅ ግን ምላሹ አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡

የሺሕ ዘመናትን አስደናቂ የታሪክ ውርስንና ቅርሶችን፣ ገናና ሥልጣኔን በተሸከመችው፣ ከየመን እስከ ሳውዲ ዐረቢያና ቱርክ፣ ከአፍሪካ ጫፍ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ- የሰው ልጆችን ኹለተናዊ መስተጋብር በፍቅርና በሰላም ያተመች፤ ከታላላቅ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖት ሊቃውንትን እና መምህራንን እስከ አውሮፓዊው/ፈረንሳዊው ባለቅኔና ገጣሚ አርተር ራምቦን በፍቅር ተቀብላ ያሰተናገደች የሰላም ከተማ ሐረር!!

ያች ጥንታዊትና ታሪካዊት ከተማ ዛሬ ያ ዓለምን ያስደነቀ የፍቅር ጉልበቷና የሰላም ውበቷ ከድቷት፣ ደምቃና ፈክታ እንዳትታይ በብሔር/በዘውጌ ፖለቲካው የተነሣ፣ ‘‘እኛ እና እናንተ’’ እኮ በሚል ትርክት የመለያየት፣ የመከፋፈል ቅርቃር ውስጥ ወድቃለች፡፡ እናም ሐረር/የሐረሪ ክልል የፍቅር፣ የሰላም ትንሣኤዋን በብርቱ የምትናፍቅ ከተማ ሆናለች!!

ይህን ትዝብቴን የሚጠናክርልኝ አንድ ሌላ ገጠመኜን ልጨምር፡፡ በሐረሪ ክልል ለሌላ የመስክ ሥራ በነበረኝ ቆይታዬ ካነጋገርኳቸው ወጣቶች መካከል አንድ በሃያዎቹ መጨረሻ የምትገኝ ወጣት ሴት በሐረሪ ክልል ስላለው እውነታ እንዲህ ስትል ነበር ብሶቷን የገለጸችልኝ፡፡

ይኸውልህ ለምሳሌ እኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ልቦና ትምህርት ዘርፍ ከተመርቅኩ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ፡፡ ግን ተወልጄ ባደግኩበት ሐረር ሥራ ለማግኘት ብሔሬ ምክንያት ሆኖ ይኸው አለሥራ ቁጭ ብያለኹ፡፡ የሚገርምህ ነገር ወላጅ አባቴ ሶማሊያ ሀገራችንን በወረረችበት ጊዜ ‘የእናት ሀገር ጥሪን’ ተቀብሎ፣ በነጻነቷና በልዑላዊነቷ ተክብራ የኖረች ሀገሬን እንዴት ጠላት፣ እብሪተኛ ወራሪ ይደፍራታል?! ብሎ ከሸዋ ድረስ ገሥግሦ መጥቶ ነው – በኢትዮጵዊነት ዜግነቱ የሐረር ከተማ ኗሪ ለመሆን የበቃው፡፡

አባቴ ወራሪውን የሶማሊያን ጦር ከሌሎች ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ጋር ሆኖ ሽንፈቱን እንዲከናነብ አድርገው አባረሩት፡፡ አባቴ ከድሉ በኋላም ቀብሪዳሃር ካገኛት ኢትዮጵያዊ ከእናቴ ጋር ተጋብተው እኔ ተወልደኩ፡፡ ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ሕይወቱን ሊሰጥላት ቆርጦ ወደ ከሸዋ ወደምሥራቅ የመጣው አባቴና ጓደኞቹ ትናንትና በጅግጅጋ፣ በደጋሐቡር፣ በቀብሪዳሃር፣ በሐረርና በካራማራ ተራሮች ለእናት ምድራቸው፣ ኢትዮጵያ አንድነትና ልዑላዊነት ያፈሰሱት ደማቸው፣ የከሰከሱት አጥንታቸው ዛሬ እንደከንቱ ነገር እየተቆጠረ ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡

የእኔ አባትም ሆነ ሌሎች ጀግኖች ለኢትዮጵያ ሀገራቸው ያፈሰሱት ደማቸው ከቁጥር፣ ከውለታ ሳይገባ ብሔራቸው እየተፈተሸ፣ ደማቸው እየተጣራ ‘‘መጤና ሰፋሪ’’ የሚባሉበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ወንድሜ ‘‘ሐረር አንተ ትብስ እኔ ትብስ ተባብለው የሚኖርባት ከተማ ናት፤’’ የሚለው ብሂል ዛሬ ተረት እየሆነ ነው፡፡ ‘‘ሐረር የመቻቻል ሳይሆን የመቻል ከተማ ሆናለች፤’’ በብሔርንና በሃይማኖትህ ምክንያት የሚደርስብህን መገፋት ችለህና ታግሰህ መኖር እስከፈቀድክ ድረስ የምትኖርባት ከተማ ሆናለች፡፡

እኔ ራሴን ለዚህች ከተማ ‘‘ቱሪስት ነኝ ወይስ ኗሪ’’ እያልኩ መጠየቅ ከጀመርኩ ሰነባብቻለሁ፡፡ ለመኖር፣ ለሥራም ሆነ መብትህን ለመጠየቅ የብሔር ማንነትህ እንጂ ኢትዮጵዊነትህ ሁለተኛ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትህ ወይም ዜግነትህ ዋጋ ቢስ ሆኗል፡፡ አባቴና የአባቴ ጓደኞች በምሥራቅ ግንባር፣ በካራማራ ተራራ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የከፈሉት መሥዋዕትነትም ዛሬ ትርጉሙ ሌላ ሆኗል፡፡

የዚህች ኢትዮጵያዊት ወገናችን ብሶትና ሮሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚጋሩት እውነታ እየሆነ እንደመጣ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በሐረር ከተማ የጥቂት ቀናት ቆይታዬ እንዳስተዋልኩት በርግጥም ሐረር- ያ የድሮ ኢትዮጵያዊ የአንድነት ክቡር መንፈሷ ተዳክሟል፤ የፍቅር ውበቷ ደብዛዟል፣ የሰላም አየር ደፍርሷል፡፡ ከከተማዋ መግቢያ በር አንስቶ እስከ ትላላቅ ተቋማቶቿ ድረስ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ይቅርታን በሚሰብኩ ጥቅሶችና አባባሎች የደመቀችው ሐረር በተግባር ግን ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጽንፈኝንትና አክራሪነት በብርቱ እየተፈታተናት ያለች ከተማ ሆናለች፡፡

ይህ አሳዛኝ እውነታ ደግሞ በሀገራችን በሚገኙ ሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ የሚንጸባረቅ መሆኑ እንደ ሀገር፣ እንደ ሕዝብ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ እየገባን እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ ለአብነትም ለውጡን ተከትሎ ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመት ውስጥ በሀገራችን የተከሠቱትና እየተባባሱ የሔዱት ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ጽንፈኝነትና አክራሪነት፣ ጥላቻዎችና ግድያዎች ብዙዎቻችን ሥጋት ውስጥ ጥለውናል፡፡ በዚህ ሂደትም የነገ የኢትዮጵያችን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ እየሆነ ነው፡፡ በሐረሪ ክልል የገጠመኝን ታሪክ መሠረት ያደረኩበትን የመጀመሪያ ክፍል ጽሑፌን በዚሁ ልቋጨውና በቀጣይ ብርቱ ፈተና ስለገጠመው ስለ ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‘የፍቅር እና የዕርቀ-ሰላም’ መንገድ ዙሪያ ለመመለስ እሞክራለኹ፡፡

 

ይቀጥላል…

ሰላም!!

Filed in: Amharic