>

ትግራይ ለምን ተደራሽ አትደረግም? (በፍቃዱ ሀይሉ)

ትግራይ ለምን ተደራሽ አትደረግም?

በፍቃዱ ሀይሉ

ዛሬ የትግራዩ ጦርነት ከተጀመረ 95ኛ ቀኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ «የሕግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናቋል» ካሉ ደግሞ ሁለት ወር ገደማ ሆኗል። ሆኖም ክልሉ እስካሁን መንግስት እንደሚለዉ ሳይሆን ለዜጎች አንፃራዊ ነጻ እንቅስቃሴ፣ ለርዳታ ሠራተኞች፣ ለጋዜጠኞች እና ለሰብኣዊ መብቶች ጥሰት መርማሪዎች በሚፈለገዉ ደረጃ  ክፍት እንዳልሆነ ብዙዎች ይናገራሉ
የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት እና የርዳታ ሠራተኞች የሚያወጧቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ትግራይ ውስጥ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ አንዣንብቧል። ኢኮኖሚስቱ አማርትያ ሴን ‘ነጻነት እንደ ልማት’ በሚል ጽፈውት የኖቤል ሽልማት ያስገኘላቸው መጽሐፋቸው ላይ እንዳመላከቱት “ነጻ ሚዲያ ያለው አገር ሕዝቦች አይራቡም” ምክንያቱም፣ የአደጋው መጠን በጊዜ ይፋ ስለሚሆን የዕርዳታ ሠራተኞች በጊዜ ደርሰው ጉዳቱን መቀነስ የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም፣ መንግሥት ክልሉን ተደራሽ ለማድረግ የፈራባቸውን ምክንያቶች በማንሳት እየመጣ ካለው ቀውስ የከፋ መሆኑን መጠየቅ ነው።
ጦርነቱ አላለቀም?
ከተዋጊው የሕወሓት ቡድን ጋር ጫካ ውስጥ የተሸሸጉት ሙሉጌታ ገብረሕይወት ከዓለም የሰላም ፋውንዴሽኑ መሥራች አሌክስ ደ ዋል ጋር በመገናኛ ሬዲዮ የታገዘ ቆይታ አድርገው ነበር። ሙሉጌታ ሲናገሩ የነበረው በከፍተኛ ተስፋ የመቁረጥ ድምፅ ነበር። ያሉበትን ሁኔታ ሲገልጡም “ወዲያ ወዲህ የምንል ተራ የግለሰቦች ስብስብ ነን” ብለዋል። በርግጥ ከትግራይ ክልል አልፎ አልፎ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እዚህም እዚያም አልፎ አልፎ የሚፈነዱ የተኩስ ልውውጦች አሉ። ነገር ግን ይዘታቸው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሚመራው የፀጥታ ኃይል አይሆንም።
ታዳኞቹ ያመልጣሉ?
ሕወሓት የሰሜን ዕዝን ከማጥቃቱ ጋር ተያይዞ በከፍተኛ የአገር መክዳት፣ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በማናጋት፣ እና በሽብርተኝነት ወንጀሎች 369 ሰዎችን እየፈለገ እንደሆነ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ በቅርቡ አሳውቆ ነበር። ከነዚህ ውስጥ እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉት 124ቱ ብቻ ናቸው ተብሏል። የመንግሥት ስጋት የትግራይ ክልል ክፍት ከሆነ እነዚህ ታዳኞች ያመልጡኛል የሚል ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። ሆኖም ይህም ሕዝብ ላይ ካንዣበበው የረሃብ እልቂትና የገበያ መክሰም በዘላቂነት ከሚያስከትሉት አደጋ አንፃር ሲታይ ትግራይ ዝግ ሆና እንድትቆይ የሚያደርግ በቂ ሰበብ አይደለም።
የሚደበቅ ምሥጢር አለ?
በጦርነቱ የኤርትራ ወታደሮች መሳተፋቸው በሰፊዉ እየተነገረ ነው። ክልሉ ውስጥ ግዙፍ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ከፍተኛ ቁሳዊ ጉዳት፣ እንዲሁም ዝርፊያዎች እንደተፈፀሙ ተሰምቷል። በርግጥ ስለጉዳቶቹ መጠን የጠራ እና የነጠረ መረጃ ገና አልወጣም። ትግራይ ለዜጎች አንፃራዊ ነጻ እንቅስቃሴና ለብዙኃን መገናኛዎች ክፍት ቢሆንም የሚወጣው መረጃ ከዚህ የተለየ አይሆንም። ይልቁንም አሁን ያለው የተዛባ መረጃ ተፅዕኖ እና የሴራ ትንተናዎች ከሚፈጥሩት ዘላቂ አሻራ እና ሕዝባዊ መቃቃር የበለጠ አይሆንም። በዚህ ጊዜ የተፈፀሙ ወንጀሎች በሐቅ እና ዕቅር እንጂ በምሥጢር ሽሸጋ ማምለጥ አይቻልም። የቀድሞ የኢትዮጵያ ስርዓቶች (ዐፄያዊው ስርዓት እና ደርግ) ቸነፈሮችን በምሥጢር ለማፈን ያደረጉት ጥረት ካለመሳካቱም ባሻገር፣ ውድቀታቸውን በማፋጠን የታሪካቸው አሻራ ሁኖ ቀርቷል።
በትርክት ላለመበለጥ?
ዘመኑ የፖለቲካ ትርክት ውጊያ ከየትኛውም ውጊያ በተወሳሰበ መንገድ የሚካሔድበት እንደመሆኑ ትርክትን መቆጣጠር የበላይነት ማረጋገጥ ነው። ለዚህም ይመስላል መንግሥት ግጭት ኮሽ ያለባቸውን ቦታዎች በሙሉ የስልክ እና ኢንተርኔት ግንኙነቶችን በማቋራጥ በትርክት ለማሸነፍ የሚሞክረው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በትዊተር ገጻቸው ያሰፈሩት መልዕክትም በትርክት መበለጣቸውን እና በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲያግዟቸው እንደሚፈልጉ ያመላክታል። በክልሉም ቢሆን ጊዜያዊው አስተዳደር የቅቡልነት ቀውስ እንደገጠመው ካሉት መረጃዎች መገመት ይቻላል። ይህ የፖለቲካ ትርክትን ለመቆጣጠር ሲባል የሚደረግ የመረጃ እና ግንኙነት አፈና ሌሎች ማኅበራዊ ቀውሶችን ለማፈን እና የፀጥታ ኃይሎች የሚፈፅሙት ያልተመጣጠነ እርምጃ ያለተጠያቂነት ለማለፍ ይረዳል። ይህ ለተጋላጮቹ ማኅበረሰቦች ብቻ ሳይሆን ኃላፊነት ለሚሰማው መንግሥትም ቢሆን ተቀባይነት የለውም። ይልቁንም ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው አስተዳደር በመገንባት እውነተኛ ቅቡልነት መግዛት ይሻላል።
የክልሉ መዋቅር ፈርሷል?
በሕወሓት ሙሉ ቁጥጥር ሥር የነበረው የክልሉ አስተዳደራዊ መዋቅር ሕወሓት በመወገዱ ምክንያት ጊዜያዊ ቀውስ ውስጥ መግባቱ አይቀርም። ጊዜያዊ አስተዳደሩም ከሚገጥመው የፖለቲካዊ ቅቡልነት ፈተና አንፃር በቀላሉ መልሶ ማዋቀር እና ወደ ነባራዊ ሁኔታው መመለሱ ጊዜ ይወስዳል። ሆኖም አስተዳደራዊ መዋቅሩ መልሶ እስኪቋቋም ድረስ ክልሉን ከተደራሽነት መዝጋት መዋቅሩ መፍረሱ የፈጠረውን ችግር እንዲባባስ ከማድረግ የበለጠ ፋይዳ የለውም። የመዋቅሩ መፍረስ ወይም መዳከም ክልላዊ መስተዳድሩን ከፌዴራል መንግሥቱ እና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት በሚገኝ እገዛ መልሶ ማቋቋም አስፈላጊነትን ከፍ ያደርገዋል። ለዚህም ነው፣ የክልሉን ተደራሽነት ማረጋገጥ አስፈላጊ የሚሆነው።
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ወታደራዊ ግጭቶችን እና ውጤታቸውን ማቃለል አይደለም። ይልቁንም፣ የትግራይ ክልል በወታደራዊ ቁጥጥር ውስጥ በቆየ ቁጥር በአጭሩ ሊቀረፉ የሚችሉት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች እየጨመሩ እና እየተባባሱ መውጣት የማይቻልበት አዘቅት ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ ማሳሰብ ነው። ስለሆነም፣ የትግራይ ክልል በአስቸኳይ ለአንፃራዊ ነጻ እንቅስቃሴ፣ ለዕርዳታ ሠራተኞች፣ ለጋዜጠኞች እና ሰብኣዊ መብት ጥሰቶች መርማሪዎች ተደራሽ መደረጉ ለዘላቂ ሰላም እና ፍትሐዊ ስርዓት መስፈን አማራጭ የሌለው አማራጭ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል።
Filed in: Amharic