>

125ኛው የድል በዓል:- ከአፍሪካ የድል በዓል የምታከብር ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ!!!  (ሳሚ ዮሴፍ)

125ኛው የድል በዓል 

ከአፍሪካ የድል በዓል የምታከብር ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ!!! 

ሳሚ ዮሴፍ


 

በአድዋ ጦርነት በሀገሪቱ ግዛቶች የተሰበሰቡ የበርካታ ብሔረሰብ ተወላጅ ሴቶች ጦርነቱን በተለያየ ግዳጅ ተሳትፈዋል፤ አስተዋጽኦዎቸውም ከስንቅ ዝግጅት ጀምሮ በውጊያ ቅስቀሳ ዘርፍ ስለነበር የአብዛኛዎቹ ተግባር ድርብ ነበር፤ በአድዋ ጦርነት የኢትዮጵያ ሴቶች በአዋጊነት ተሳትፈዋል፤ ጦር መርተው፣ መድፍ አስተኩሰው፣ ወታደር አዘው አዋግተዋል፤ ቀን በውጊያ ማታ ከስንቅ ዝግጅት ሳይነጠሉ ረጅሙን የውጊያ ወራት አሳልፈዋል።
ሴቶች ለአድዋ ጦርነት መዘጋጀት የጀመሩት ቀደም ብሎ ነበር፤ ከጣልያኖች ጋር ጦርነት የማይቀር መሆኑ ሲረጋገጥ ወደ ዘመቻው የሚጓጓዝ የሸክላ ምጣድ፣ አክንባሎ፣ ድስት በብዛት እንዲሠሩ ታዘዘ። ለስንቅ የሚሆነው ለዕለትም ሆነ ለመንገድ የሚሆን ደረቅ ምግብ ሲያዘጋጁ ከረሙ።
የሴቶች አገልግሎት የሚጀምረው ጉዞ የተጀመረ ዕለት ነው፤ ዘማቹ ከየቤቱ የተሰባሰበ ዕለት ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ መኳንንት ድረስ እንደየአቅሙ አብረው የሚጓዙት ሴቶች ቁጥር ቢለያይም አገልግሎታቸው ተመሳሳይ ነው።
ከመኳንንቱ ጋር የሚጓዙ ከሆነ ለአዛዦቹና ለሠራዊቱ የሚቀርበውን ግብር ለድርጎኛ የሚላከውን በየዋዜማው እያሰናዱ ለማግስቱ ያዘጋጃሉ። ሰፈር ሲደረግ ቀድሞ ብለው ደርሰው የያዙት ለግብር ያቀርባሉ፤ በቀረበው ሰዓትም ለማግስቱ የሚሆነውን ሲያዘጋጁ አድረው ጠዋት ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ። ወጥቤቶቹም ተራ ገብተው በየድንኳናቸው ሢሠሩ ያድራሉ በማግስቱ ጉዞ ሲሆን ‘አፍላል’ በሚባል እንደ ገንቦ ያለ የወጥ መያዣ አንግተው በበቅሎ ተቀምጠው ሲገሰግሱ ይውላሉ። ቀድመው በመድረስ የያዙትና አሙቀውና አስተካክለው ለቀዳሚ ግብረኞች ያቀርባሉ።
ቀዳሚዎቹ እስኪበሉ በበቅሎ የሚጫነው ትልቁን ብረት ድስት ጥደው ወንዶቹ ተሸክመውት የሚጓዙትን የተመተረውን ስጋ ተረክበው ለሠራዊቱ የሚሆነውን ወጥ ሰርተው ለግብር ያደርሳሉ፤ ለሠራዊቱ በሙሉ ግብሩን ያቀርባሉ።
ጠላ ቤቶቹም በገንቦ የያዙትን ድፍድፍ አዘጋጅተው ጠጅ ቤቶቹም በቀንድ የያዙትን የደረቀውን ማር አልሰው የላላውን አወፍረው ያዘጋጃሉ፤ ሠራዊቱ በልቶ እስኪጨርስ ተረኞቹ እንጀራቸውን መጋገር ወጣቸውን መሥራት ይቀጥላሉ።
በአድዋ ጦርነት ሴቶች በዘማችነትም ተሳትፈዋል፤ በታሪክ መዝገብ ተደጋግሞ ስማቸው የተጠቀሰው እቴጌ ጣይቱ ቢሆኑም በርካታ ሴቶች የአድዋን ጦርነት መካፈላቸው ተጽፏል። በዚያን ጊዜ ራሳቸውን ችለው የሚዘምቱ ከባላባቶችና ከአጃቢዎቻቸው ጋርም አጃቢ ሆነው የሚጓዙም አሉ። በተለይ በዚያን ጊዜ የቤተሰብ ፍቅር የፀና ነበርና ከባለቤቴ አልነጠልም ከወንድሜ አልለይም እያሉ የሚዘምቱ አያሌ ሴቶች ነበሩ። በጦር አዝማችነት የሚታወቁት እቴጌ ጣይቱ በዚያ ጊዜ በስራቸው የሚታዘዙ 3000 የሚሆኑ ተዋጊዎችና 4 መድፈኞች እንደነበሯቸው”በርክሌይ” ጽፏል። በመቀሌውና በአድዋው ጦርነት አብረዋቸው ከነበሩት ሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን አዋግተዋል፤ በተለይም ጄነራል አልበርቶኒ ድል ከሆነበት እንዳ ኪዳነ ምህረት አካባቢ የሠሩትን ሥራ ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ወልደአረጋይ እንዲህ ሲሉ ጽፈውላቸዋል።
“በዚህም ጊዜ እቴጌ አይነ እርግብዎን ገልጠው ጥቁር ጥላ አስይዘው በእግርዎ ሲሄዱ ነበር፤ ሴት ወይዛዝሩና የንጉሠ ነገሥቱም ልጅ ወ/ሮ ዘውዲቱ ከደንገጡሮቹም ተከትሎዎት ነበር። የኋላው ሰልፍ እንደመወዝወዝ ሲል ባዩት ጊዜ ተናገሩ። “አይዞህ አንተ ምን ሆነሃል ድሉ የኛ ነው በለው” አሉት፤ ሰውም እቴጌን ባየ ጊዜ ሴት ሲያጠና ወንድ መሸሽ አይሆንለትምና ፀጥ አለ፤ እቴጌም ነፍጠኞችቻቸውን በግራ በቀኝ አሰልፈዉ በዚያን ቀን የሴቶችን ባህሪ ትተው እንደተመረጠ የጦር አርበኛ ሆነው ዋሉ፤ የእቴጌም መድፈኞች እቴጌ በቆሙበት በስተቀኝ መልሰው መልሰው መድፍ ቢተኩሱ በመካከል የመጣውን የጣልያን ሰልፍ አስለቀቁት። ንግሥቲቱ እቴጌ ጣይቱ የመጀመሪያው ጣልያን ድል ከሆነበት ሜዳ ላይ ቆመው የተከተሏቸውን ሰዎች ወንዱን በእርኮት ሴቱ በገንቦ ውሃ ያዙ ብለው አዘዙ፤ ለተጠማውና ለቆሰለው ውሃ ሲያጠጡ ዋሉ እንኳን የኢትዮጵያ ሰው የጣልያን ቁስለኛ እንኳ ከዚያ ስፍራ የተገኘ እቴጌ ካዘዙት ውሃ አልቀረበትም። ዘጠኝም ሰዓት በሆነ ጊዜ የአጼ ምኒልክ ሠራዊት ቁስለኛውንና የማረከውን ጣልያናዊ እየያዘ ይመለስ ጀመር፤ አጼ ምኒልክ ግን ከጦርነቱ ገና አልተመለሱም ነበር፤ እቴጌም ሠራዊቱ ብዙ ብዙ እየሆነ መመለሱን ባዩ ጊዜ “ንጉሡ ሳይመለሱ የት ትሄዳላችሁ የቆሰለውን ሰው እኔ ካለሁበት አሳርፉት እናንተም ተመለሱ” ብለው ተናገሩ።
የእቴጌም እህት ወ/ሮ አዛለች ከሰልፉ አብራ የነበረችው ሰው እየማረከ ሲመለስ ባየች ጊዜ ተናገረች፤ “አድዋ ቤት አለህ ጠጅህን ጮማህን ትተህ ወዴት ትመጣለህ” እያለች ለፈፈች የምኒልክ ደግነት እንኳን ወንዱን ሴቱን መነኩሴውን አጀገነው በአድዋ ጦርነት እቴጌ ጣይቱንና አብረው የነበሩትን ሴቶች ማጋነንና ማድነቅ ይገባናል ብዙ ብዙ ሲሰሩ ውለዋልና”
በአድዋ ጦርነት የተሳተፉ ሴቶች ታሪካቸው ባለመመዝገቡ እንጂ ምድር ቀውጢ በምትሆንበት በጦርነት ገብተው ጀግንነት የፈፀሙ ብዙ ናቸው። ለዚህም የጊደን ገብሬ እህት ታላቅ ጀብዱ ከፈፀሙት ሴቶች እንደምሳሌ ልትጠቀስ ትችላለች፤ ስሟን አላወቅነውም ግን የላስታና የዋግ ጦር የአንድ ክፍል መሪ እህት መሆኗ ተጽፎልናል፤ ይህቺ ወይዘሮ ከወንድሜ አልለይም ብላ ከደጃዝማች ጓንጉል ጦር ጋር ከዘመተው ወንድሟ ጊደን ገብሬ ጋር ዘመተች፤ በአላጌው ጦርነት ወቅት ወንድሟ ገደል እየቧጠጠ በሚዋጋበት ወቅት አብራው ሆና ጥይት በቀሚሷ እየታቀፈች ስታቀብለው ነበር፤ ታላቅ የጀግንነት ሥራ ሲፈጽም ጊደን ገብሬ ተሰዋ፤ እህቱም አጠገቡ ሞታ ተገኘች።
የሴቶች ተሳትፎ በዚህ አያበቃም ስሜትን በሚኮረኩሩ ልብን በድፍረት በሚሞሉ ዜማዎችና ግጥሞች እየቀሰቀሱ ያበረታታሉ፤ የፈራውን በግጥም እየዘለፉ ያበረታቱታል….
ፈሪ ሰው አልወድም፤ ያልገደለ አልወድም
አብሬው ስተኛ፤ ይመስለኛል ወንድም
ምነዋ ብኮራ፤ ምነው ቢጀንነኝ
ተጋዳይ አጋዳይ፤ ያገኘው እኔ ነኝ
ቀና ብለህ ተኩስ ወርች ነው ብልቱ
እዚህ ሆኜ ታየኝ እኔ እንኳን ሴቲቱ…..
በማለት ፈሪውን እየነቀፉ ጀግናውን ያሞግሳሉ።
የእናቶቻችን የአድዋ ጉዞ ይሄን ይመስል ነበር።
ክብር ለእናቶቻችን!!!
*    *      *
   
Filed in: Amharic