>

"ብልፅግና የተጣለበትን የተስፋ ሸክም አራግፎ፣ ኢሕአዴግን መሥሎ፣ ከኢሕአዴግን በላይ ከፍቶ  ምርጫ 2013 ደጃፍ ላይ ቆሟል...!!!" (በፍቃዱ ኃይሉ)

“ብልፅግና የተጣለበትን የተስፋ ሸክም አራግፎ፣ ኢሕአዴግን መሥሎ፣ ከኢሕአዴግን በላይ ከፍቶ  ምርጫ 2013 ደጃፍ ላይ ቆሟል…!!!”
በፍቃዱ ኃይሉ

ኢትዮጵያ ከምርጫ 97 ወዲህ ውጤቱ በቅጡ ያልተገመተ ምርጫ ለማሰናዳት ሽርጉድ ላይ ነች። በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ይህ ምርጫ፣ ሶስት ወራት ተኩል ብቻ ቢቀሩትም ቅሉ፥ ፈፅሞ ሊሟሟቅ አልቻለም። በየዕለቱ ሲንቀሳቀሱ የሚታዩት እራሱ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ብቻ ናቸው። ሌላው ቀርቶ ገዢው ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲ እንኳን ይቀናቀኑኛል ያላቸውን ወደ ዘብጥያ ማውረድ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተደብቆ አወድሱኝ አሙቁልኝ ከማለት ያለፈ በአፈ ቀላጤዎቹ በኩል ፖሊሲውን የማስተንተን እንቅስቃሴ አላሳየም ።
የቀድሞው ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) የምርጫ 97ን ወላፈን ከቀመሰ ወዲህ «አውራ ፓርቲ ነኝ፤ አምሳያዎቼ ምሥራቅ እስያውያን ናቸው፤ ይህም ለልማታዊ መንግሥትነት በጅቶኛል» እያለ በብቸኛ ኃያልነት ይኖር ነበር። ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ምርጫዎችም ከአጋሮቹ ጋር በመተባበር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 99.6 በመቶ እና መቶ በመቶ ወንበሮች በመቆጣጠር ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ነበር። በገዛ አባላቱ ውስጣዊ ዐብዮት የገጠመው ይኸው ገዢው ፓርቲ መሥራች አባቱን ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) «በበቃኝ» አሰናብቶ ብልፅግና ፓርቲ ከሆነ ገና አንድ ዓመቱ ነው። የአንድ ዓመቱ ብልፅግና ፓርቲ ብልፅግና የተጣለበትን የተስፋ ሸክም አራግፎ፣ ኢሕአዴግን መሥሎ፣ ከኢሕአዴግን በላይ ከፍቶ  ምርጫ 2013 ደጃፍ ላይ ቆሟል። ሆኖም፣ መራጩም ተመራጩም ጉዳዩን ከቁብ ያልጣፉት ይመስል እጅግ መቀዛቀዝ ይታያል። የዚህ መጣጥፍ ወግም «ለምን?» የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መሞከር ነው።
ምርጫው አ-ይራዘም
ምርጫው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሰበብ ከመራዘሙ በፊት «ይራዘም/አይራዘም» የሚሉ ንትርኮች ነበሩ። «ይራዘም» የሚሉት ወቅቱ «የተሐድሶ ነው» ተብሎ ይታመን ስለነበር፣ አንደኛ፣ ተሐድሶው እስኪጠናቀቅና ምኅዳሩ እስኪሰፋ ወይም በፍትሓዊነት እስኪደላደል፣ ሁለተኛ፣ አማራጭ ፓርቲዎች ራሳቸውን መልሶ ማደራጀት እስኪችሉ እና ለውድድር መዘጋጂያ ጊዜ እስኪያገኙ ድረስ ነበር። በርግጥ ሦስተኛም ምክንያት አለ። ሰላም ይደፈርሳል፣ ግጭት ይቀሰቀሳል ብለው ፈርተው ምርጫው ይራዘም የሚሉም ነበሩ። በዚህ ረገድ ምርጫው በጊዜ እንዲካሔድ ያለውን ፍላጎት ቢያንስ በአደባባይ ደረጃ ደጋግሞ ሲገልጽ የነበረው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ (ወይም፣ ገዢ ፓርቲዎቹ ብልፅግና እና ሕወሓት) ነበሩ። «ይራዘም» ባዮች የሚያነሷቸው ሦስት ሁኔታዎችንም ይሁን፣ «አይራዘም» ባዮች እንዳይራዘም የፈለጉበትን ምክንያት ቀስ በቀስ እንመለስባቸዋለን።
በሌላ በኩል፣ እንዲያውም ቅቡልነት ባለው ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ስለሌለ አስቸኳይ ምርጫ (snap election) ይደረግ የሚሉም ጥቂቶች ነበሩ። ከነዚህም በተቃራኒ ደግሞ፣ ተሐድሶውም ይሁን ታዳሹ መንግሥት ያው በነበረው ስርዓት እና አሠራር የመጡ ስለሆኑ፣ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ነው መመሥረት ያለበት የሚሉም ነበሩ። እነዚህ ብዙኃን ስላልሆኑ እናልፋቸውና «ይራዘም» ያሉትም ይሁኑ «አይራዘም» ያሉት ባሰቡት እና በፈለጉት መንገድ ሳይሆን ባላሰቡት እና ባልፈለጉት መንገድ ምርጫው ቢያንስ ለአንድ ዓመት ከተራዘመ በኋላ ያለውን ሁኔታ እንገመግማለን።
የመራዘሙ ነገር፥ ለማን ጠቀመ?
የምርጫ 2012 መራዘም ላይ ይኼ ነው የሚባል ተቃውሞ አልነበረም። ሌላው ቀርቶ መራዘሙን «እምቢ» ብሎ የራሱን ክልላዊ ምርጫ ያዘጋጀው የያኔው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ኃላፊዎችም ቢሆኑ በኮቪድ 19 ምክንያት ምርጫው መራዘሙን አልተቃወሙም ነበር። ይልቁንም የሚራዘምበት መንገድ ላይ ሕወሓት «ጊዜያዊ ባላደራ መንግሥት» ይመሥረት የሚል፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) «ፖለቲካዊ መፍትሔ» ይፈለግለት የሚል፣ ኢዜማ «ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ» ይደረግ የሚል አቋም ቢያራምዱም፥ ብልፅግና ወይም መንግሥት ባለሙያዎች አማክሬ ደረስኩባቸው ካላቸው ሦስት አማራጮች መካከል «ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ» ማድረግ የሚለው ላይ ገፍቶበታል። እዚህ ድረስም ብዙዎች ከቅሬታ ጋርም ቢሆን ተሥማምተው ዘልቀው ነበር። ነገሩ ሁሉ የተገለባበጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የገዢው ቡድን ላይ ያለምንም ሥልጣን ገደብ እና ያለ ጊዜ ገደብ ምርጫው እንዲራዘም የወሰነ ዕለት ነው። አንዳንዶች የገዢው ፓርቲ ገዢነት «መስከረም ላይ ያበቃል» እስከማለት ደርሰዋል። ይህንን በአደባባይ የተናገሩት አካላት ዕጣ ፈንታ ባብዛኛው የሚታወቅ ነው።
ሕወሓት በትግራይ ክልል ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና የነሳውን ምርጫ አደረገ። ምርጫው በአንዳንዶች «በትግራይ ክልል ታሪክ ብዝኃነት የታየበት» ቢባልም ቅሉ ሕወሓት የርዕዮተ ዓለም ተቃርኖ የሌላቸውን ተቀናቃኞቹን ልክ እንደቀድሞው 99.8 በመቶ የመራጮችን ድምፅ በመሰብሰብ «አሸንፏቸዋል»። ምናልባት አገር ዐቀፉ ምርጫም ያኔ ቢካሔድ ኖሮ ብልፅግናም እንዲህ ባይጋነንም በጎላ ልዩነት ሊያሸንፍ ይችል ነበር ብሎ መገመት ይቻላል። የሆኖ ሆኖ ሕወሓት ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር በገባበት ፀብ ሰለባ ሆኖ ከስሟል። ሕወሓት የብልፅግና መንግሥት ከመስከረም ወዲያ ዕውቅና የለውም ባይ ነበር።
የምኅዳሩ ነገር…
የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ጠቅላይ ሚኒስትሩን «ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ የተከሰቱላት ምርጡ ነገር ናቸው» ብለው በሙገሳ ያንቆለጳጰሷቸው አንድ የፖለቲካ ተንታኝ፥ በቅርቡ ደግሞ «የፖለቲካ ምኅዳሩን እንዲያሰፉ፣ ብሔራዊ ሥምምነት እንዲያመጡ፣ እና ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር እንዲያቀላጥፉ የተጣለባቸውን አደራ ቀርጥፈው በልተዋል» ሲሉ በትችት አብጠልጥለዋቸዋል። የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን ማሳደግ፣ አፋኝ ሕጎችን መከለስ፣ እና ተቋማትን ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ለውጡ ሲጀምር ተስፋ የተጣለባቸው፣ «ምርጫው ይራዘም» ሲሉ የነበሩ አካላትም ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ሲሏቸው የነበሩ ነገሮች ነበሩ።
ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ በኋላ እመርታዎች አሉ፤ ነገር ግን ከእመርታዎቹ ይልቅ ወደኋላ መንሸራተቶቹ የበለጠ ብዙዎችን ያሳስባሉ። መንግሥት የሲቪል ማኅበራት ሕግጋቱን ቢከልስም፣ ሲቪል ማኅበራቱ ገና በሁለት እግራቸው አልቆሙም። ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ከካች አምና የተሻለ ቢሆንም፣ ዛሬም ጋዜጠኞች በእስር ቤት አሉ፣ ዛሬም ኢንተርኔት ነጋ ጠባ ይዘጋል፣ ዛሬም በሕዝብ በጀት የሚተዳደሩ ሚዲያዎች የገዢው ፓርቲ ልሣን ይመስላሉ። ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ከቀድሞው አልተለዩም። የፖለቲካ አመራሮች በሚያጠያይቅ ሁኔታ ታስረዋል፤ የፍርድ ቤት ትዕዛዞች በፖሊሶች ይገፈፋሉ። ብቸኛዎቹ አዎንታዊ ለውጥ ያሳዩ ተቋማት የምርጫው ደጋሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ናቸው። እነርሱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥርስ አልባ መሆናቸው እየተስተዋለ ይመስላል።
የመደራጀቱ ነገር…
ሌላኛው እና «ምርጫው ይራዘም» ባዮች ሲያነሱት የነበረው ጉዳይ አማራጭ ፓርቲዎች የመደራጀት ጊዜ አላገኘንም የሚል ነበር። ይሁንና የምርጫ ወረዳ መዋቅር መዘርጋት እና ፖሊሲ መቅረፅ ሥራ ላይ ተጠምዶ ከከረመው ከኢዜማ በስተቀር ብዙዎቹ ፓርቲዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ብሽሽቅ ተጠምደው ከርመዋል ማለት ይቻላል። ኦፌኮ ሌላኛው የተሻለ ሲዘጋጅ የነበረ ድርጅት ነበር ለማለት ቢያንስ ታዋቂውን አክቲቪስት እና የዛሬውን እስረኛ ጃዋር መሐመድን ማካተቱን እና በምሥራቅ ኦሮሚያ ከተሞች ትልልቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ማካሔዱን መጥቀስ ይቻላል። ከሌሎች ሁለት ሦስት የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ያደረገው ቅንጅት (ቅንጅት ለዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም) ብዙ ተስፋ ቢጣልበትም በአባላቱ አለመስማማት ባጭሩ ተቀጭቷል። ያደረጋቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎችም በገዢው ፓርቲ በጎሪጥ ሲታዩበት መክረማቸው አይዘነጋም፤ እንደምሳሌ በጅማ ከተማ የተፈጠረውን ግጭት መለስ ብሎ ማስታወስ ይቻላል።
ይባስ ብሎ የአርቲስት ሀጫሉ ግድያ ያስከተለው ነውጥ ውስጥ ተሳትፋችኋል በሚል ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባ እንዲሁም የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፕሬዚደንት እስክንድር ነጋን የመሳሰሉ ፖለቲከኞች ሲታሰሩ፣ ፍርሐት ነገሰ፤ የፖሊቲካ ማደራጀቱ ጉዳይም ላይ ውሃ ተከለሰ። ከዚህም በላይ በገዢው እና ሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አለመተማመን ነገሠ። በቅርቡ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ባደረጉት የበይነመረብ ዘመቻ ላይ ከ170 በላይ ተወዳዳሪ እጩ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎች ታስረዋል ብለዋል። የሆነው ሆኖ የምርጫ ጊዜ መራዘሙ ሰበብ ሆኖ ሲቀርብ የነበረው የመደራጀት ነገርም እንዲሁ ባክኗል።
የሰላሙ ነገር…
በ2010 ኢሕአዴግ በውጪያዊ ተቃውሞ እና በውስጣዊ ትግል ተንጦ «ተሐድሶ» ሲጀምር ኢትዮጵያውያንም ከዳር እስከ ዳር በተለያዩ ነውጦች እየታመሱ ነበር። በዚህም ሳቢያ ምርጫውን እንደ ጦርነት የፈሩት ሰዎች ነበሩ። በወል ግጭቶች በሚሊዮን ከመፈናቀል እስከ ዘግናኛ የአደባባይ የወል ፍርዶች ድረስ ይዘልቅ የነበረው ነውጥ፣ የኋላ ኋላ የፖለቲካ ግድያዎች፣ የበቀል አመፆች፣ የፀጥታ ኃይሎች ቸልታ ተጨማምሮበት አገሪቷን በመከራ እንድትታመስ አድርጓታል። ይህም አልበቃ ብሎ የትግራይ መሪዎች እና የኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የነበረው እሰጥ አገባ ወደ ለየለት ጦርነት ገብቶ የሰላም እጦቱ እያደር እየከፋ እንዲሔድ አድርጎታል።
ተጠናቋል ከተባለም በኋላ መጨረሻው ካልለየው የትግራይ ጦርነት ውጪ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለይም በመተከል፣ በደቡብ ክልል በኮንሶ፣ በሶማሊና አፋር ክልሎች ተጎራባች አካባቢዎች ደም አፋሳሽ ነውጦች አሉ። የተፈራው የሰላም መደፍረስ ሳይረጋጋ፣ ምርጫው ሰጋሩን እየጋለበ በር ላይ ደርሷል።
«ምርጫው ይራዘም» ይሉ የነበሩ አካላት ሲያነሷቸው የነበሩትን የሰላምና መረጋጋት ጉዳይ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን መስፋት ጉዳይ፣ የመደራጂያ ጊዜ የማግኘት ጉዳይ ሁሉም አልተሳኩም፤ በከፊል የተሳኩትም ቢሆን አዲስ በተፈጠሩት ተግዳሮቶች ተተብትበዋል። የፉክክር ዕድል ቢኖርም አብዛኛው የማሸነፍ ዕድል አሁንም የገዢው ፓርቲ ነው። አሁንም የምርጫ ፉክክሮች የበለጠ ቀውስ ሊያስከትሉ ይችላል የሚል ስጋት አለ። በተቃራኒው ደግሞ የአደባባይ ቅስቀሳዎች በዚህ የፖለቲካ ድባብ ሊካሔዱ ይችላሉ ወይ የሚልም ጥያቄ አለ። አሁንም «የፖለቲካ መሪዎቻችን ታስረው ስለምርጫ ማሰብ አንችልም» የሚሉ ሰዎች አሉ። አሁንም ብዙዎቹ አማራጭ ፓርቲዎች በቅጡ አልተሰናዱም።
በእነዚህ ነጥቦች ስንገመግመው ምርጫው እንደተጠበቀው እስከዛሬ ድረስ መሟሟቅ ያልቻለው፣ የዛሬ ሁለት ዓመት በብዙዎች የተሰነቀው ተስፋ ስለከሰመ ነው። የቀረ ተስፋ ካለ፣ ውጤቱን በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት የምናየው ነው፤ ከዚህ በኋላ ተስፋ ሊጣልበት የሚችለው የመነቃቂያ ጊዜ የቴሌቪዥን ክርክሮች ጊዜ ይሆናል።
Filed in: Amharic