>

የጭቆና ትርክት መነሻውም መድረሻውም የበታችነት ስሜት ነው...!!! (ቤተልሄም ብሩ)

የጭቆና ትርክት መነሻውም መድረሻውም የበታችነት ስሜት ነው…!!!

ቤተልሄም ብሩ

 

* ባቡሩ ሠገረ፣ ስልኩም ተናገረ፣ 
ምኒልክ መልአክ ነው ልቤ ጠረጠር!!!
 

አድዋ  125

“የጭቆና ትርክት መነሻውም መድረሻውም የበታችነት ስሜት ነው፤ ምኒልክ ጠል ብሔርተኞች የበታችነት ስሜታቸውን ወደጎን ትተው በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሚና እንደነበራቸው ማሰብ ቢጀምሩ፤ ለትውልድም ቢያስተምሩ ሀገርን የማሳደግ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ” የታሪክ ምሁር
አጤ ምኒልክ ለቡድን ጥቅም ሳይሆን ለሀገር አንድነት የተጉ፤ ብሔርተኝነትን ሳይሆን ሰብዓዊነትን ያስቀደሙ፤ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች መብት መከበር እና ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ልዕልና ከአዕምሮ የማይጠፋ ታሪክ የሠሩ መሪ ናቸው፡፡
ጥበብ በተሞላዉ አስተዋይነት እና ብልህነት ኢትዮጵያን መርተው ለስኬት በማብቃት ድንቅ መሪ መሆናቸውን በተግባር አስመስክረዋል፡፡ የነጭ የበላይነትን ሲያቀነቅኑ ለነበሩትም የጥቁር ሕዝቦችን ትክክለኛ ማንነት በማሳየት የተመጻደቁ ቀኝ ገዢዎችን አንገት አስደፍተዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ያላትን ቀርጽ እንድትይዝ ያደረጉት አጤ ምኒልክ በድንቅ የመሪነት ጥበባቸው፣ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸው፣ አርቆ አሳቢነታቸው እና ርኅሩኅነታቸው በዓለም የታሪክ ማሕደር በደማቅ ተጽፏል፡፡
አጤ ምኒልክ ሲታወሱ ኢትዮጵያን የማዘመን እሳቤያቸው አብሮ ይነሳል፡፡ ምንም እንኳን እሳቤው ከአፄ አምደጽዮን ጀምሮ የተጠነሰሰ ቢሆንም የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሀንዲሱ አጤ ምኒልክ መሆናቸውን የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህሩ ገንዘብ አታላይ አስረድተዋል፡፡
አጤ ምኒልክ ጥንታዊ የደብዳቤ መላላኪያ ዘዴን በዘመናዊ ፖስታ ቀይረዋል፣ የቴሌፎንና የቴሌግራፍ አገልግሎትን በማስጀመርም በፍጥነት አስፋፍተዋል፤ የባቡር ሐዲድ እንዲዘረጋም አድርገዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ መነጋገር የተጀመረው፣ ኤሌክትሪክ የተገጠመው፣ የውኃ ቧንቧ የተዘረጋው፣ ሲኒማ ቤት፣ ፎቶ ቤትና ማተሚያ ቤት የተከፈቱት በአጤ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡
አጤ ምኒልክ በኢትዮጵያ አዉቶሞቢል አስገብተው ማሽከርከርን አስተምረዋል፤ ብስክሌት መዘወር ተምረው ለንግሥት ጣይቱም ያስተማሩ፣ ዘመናዊ ሆቴል በመሥራት በሆቴል መመገብ ነዉር አለመሆኑን ያስገነዘቡ መሪ ናቸው፡፡
አጤ ምኒልክ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ዘርግተው ሚኒስትሮችን በመሾም የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር ያደረጉ ዘመናዊ መሪ ናቸው፡፡ መንግሥታቸውን ያዋቀሩትም ከሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተውጣጡ ሚኒስትሮች እንደሆነ የታሪክ መምህሩ አስታውሰዋል፡፡ እነ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ ባልቻ አባነብሶ፣ ጎበና ዳጫ እና ሌሎችንም ለሀገረ መንግሥት ግንባታ እና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር ከፍተኛ ሚና ከነበራቸው ሚኒስትሮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
አጤ ምኒልክ በሀገር ለመጣባቸው ድርድር የማያውቁ ቆራጥ፣ ሀገር ወዳድ፣ ጎበዝ የፖለቲካ ሰው እንደነበሩም ታሪክ ይነግረናል፡፡ የሀገራቸውን ዳር ድምበር ለማጽናት የጦር ሜዳ ፊታውራሪ ሆነው የኢትዮጵያ አርበኞችን በማስተባበር ተዋግተዋል፡፡
 በተለይ ከአጤ ምኒልክ የንግሥና ዘመን ታሪክ ውስጥ ጎልቶ በሚነሳው ዓድዋ ጦርነት ንጉሡ የክተት አዋጅ ባሰሙ ጊዜ ሴቶች፣ ሽማግሌዎች፣ አካል ጉዳተኞችና ሌሎችም ሳይቀሩ በወኔ የተነሱት አንድም ለሀገራቸው ያላቸውን ቆራጥ አቋም ያሳያል፤ በሌላ በኩል አጤ ምኒልክ በሀገራዊ አንድነት ላይ ሠርተው እንደነበር ማሳያ መሆኑን የታሪክ መምህሩ አንስተዋል፡፡
ሕዝብን አንድ ለማድረግ የሰሜኑን ከደቡብ፣ የምሥራቁን ከምዕራብ በጸና ጋብቻ ያስተሳስሩ እንደነበርም አብራርተዋል፡፡ ይህ ውጤታማ እንዳደረጋቸው የተናገሩት መምህር ገንዘብ ‹‹አጤ ምኒልክ እስከዛሬ ሀገር የመምራት ዕድል ቢኖራቸው ኖሮ ኢትዮጵያ ከስልጣኔና ከእድገት ማማ እንደምትደርስ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል›› በማለት ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን የዓለም ሕዝብ ስለ አጤ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የስኬት አብነት ብዙ ቢመሰክርም ኢትዮጵያን የማዳከም ሕልም የነበራቸው ሀገራት ግን የማጠልሸት ሀሳብ ጠንስሰው ብዙ ጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ አንድነት ለመናድ አቅደውም ሠርተዋል፡፡ እሳቤውን በሀገር ውስጥ ያሉ ቡድኖች ተቀብለው ተግብረውታል፡፡
የአጤ ምኒልክ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በኃይልና በመደፍጠጥ የተመሠረተ መሆኑን፤ አንዳንዶችም በቀኝ ግዛት የተያዙ በማስመሰል በተሳሳተ መንገድ ለትውልዱ ማስተማራቸውን አንስተዋል፡፡ እነዚህ አካላት ለአጤ ምኒልክ ብሔር በመስጠት የብሔር ጭቆናን እንደ ሀሳብ መሸጫ መሳሪያ ተጠቅመዋል፡፡ በተለይም አማራን ከኦሮሞ ለማጣላት ሀውልት በማቆም የአማራውን ስነልቦና ለማዳከም የተለያዩ አጀንዳዎችን ፈጥረው ተግባራዊ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም እስካሁን ድረስ ማፈናቀል፣ መግደል፣ ንብረት ማውደምና በማንነቱ ማሸማቀቅ እንደፈጸሙ ተናግረዋል፡፡ አጤ ምኒልክ ትውልዳቸው አንጎለላ ሲሆን ከኦሮሞ ልጆች ጋር እየተጫወቱ ነው ያደጉት፡፡
ከመቅደላ አምልጠው ወደ ሸዋ ሲያቀኑ ደብረዘይት (ቢሾፍቱ) አካባቢ የሸዋ ኦሮሞዎች ተቀብለዋቸው እንደነበር የጳውሎስ ኞኞ መጽሐፍን አጣቅሰው ተናግረዋል፡፡ በንግሥናቸውም ጊዜ ያስተባበሯቸው አብረዋቸው ያደጉት እንደ ጎበና ዳጫ አይነት ኦሮሞ ጓደኞቻቸው እንደሆኑ አንስተዋል፡፡
ጎበና ደግሞ የቱለማ ኦሮሞ መሪ የነበሩት የዳጨ ልጅ ናቸው፡፡ የምኒልክን ግዛት ያመቻቹ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን ጨምሮ ሌሎች ኦሮሞዎች በታሪክ ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ ደግሞም ከአጤ ምኒልክ ጋር ለሀገር አንድነት የሠሩ ናቸው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ ሀሰተኛ ትርክቱ በትህነግ መዋቅር ጭምር ይደገፍ ስለነበር ትውልዱ ታሪኩን በትክክል እንዲረዳ ከማድረግ ይልቅ ዘውጌ አስተሳሰብ እንዲጎለብት እድል ሰጥቷል፡፡
የትምህርት ሥርዓቱ መሠረታዊ ክፍተት እንዳለበትም አንስተዋል፡፡ ትርክቱን ለማስተካከል በትኩረት መሥራት እንደሚገባ የመከሩት የታሪክ መምህሩ ለዚህም ትክክለኛውን የታሪክ ሰነድ ለሕዝብ ማድረስ፣ ጥናታዊ ጹሑፎችን በተለያዩ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ማዘጋጀት፣ በበየነ መረብ እና የሕትመት ጹሑፎች ማከማቻ ማዕከላት ማዘጋጀት፣ በተሳሳቱ ትርክቶች ላይ ግልጽ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡
እንደ አቶ ገንዘብ ማብራሪያ መገናኛ ብዙኀን ድርጅቶች ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ተከታታይ ሸፋን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትክክለኛውን ታሪክ እየተረዳ እንዲሄድ የሚጋብዝ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
በተለይ ምኒልክ ጠል ብሔርተኞች የተሳሳተ ትርክትን የሙጥኝ ከማለት ይልቅ አጤ ምኒልክ ምን አይነት ስብዕና እና መስተጋብር እንደነበራቸው መረዳት ይገባል ብለዋል፡፡ “ከጣልያን ጋር በነበረ የነጻነት ተጋድሎ የአድዋ ተራሮች በኦሮሞ ፈረሰኞችም ተንቀጥቅጠዋል፡፡ ይሕንን ታላላቅ ጸሐፍትም ጽፈውታል፡፡
 የኦሮሞ አባቶች ሀገርን በመጠበቅ፣ ወገን፣ ሕዝብን የማትረፍ ሚናቸው ትልቅ ነበር፤ በሀገረ መንግሥት ግንባታም ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ማሰብ ተገቢ ነው” በማለት ንጉሡን የኦሮሞ ጠላት አድርጎ የመያዝ አባዜን መተው እንደሚገባ መክረዋል፡፡
“የጭቆና ትርክት መነሻውም መጨረሻውም የበታችነት ስሜት ነው፤ ምኒልክ ጠል ብሔርተኞች የበታችነት ስሜታቸውን ወደጎን ትተው በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሚና እንደነበራቸው ማሰብ ቢጀምሩ፤ ለትውልድም ቢያስተምሩ ሀገርን የማሳደግ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ” በማለት መክረዋል፡፡
ምንጭ:- (አብመድ )
Filed in: Amharic