>

* የጣልያን ስነ ልቦና ከዓድዋ ጦርነት በፊት እንዴት ነበር?  (ሁነኛው መብራቱ)

የጣልያን ስነ ልቦና ከዓድዋ ጦርነት በፊት እንዴት ነበር? 

ሁነኛው መብራቱ

ጣልያኖች እንደ ወራሪ ኃይል ወደ አፍሪካ ለመስፋፋት ሲወጥኑና ከኢትዮጵያም ጦር ሲማዘዙ በሀገራቸው የነበረው ማኅበራዊ ሥነ-ልቦናዊ ሁኔታ የተዛነቀ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡
ከጥንታዊው የሮማ ስልጣኔና ጥንካሬ በተቃራኒ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት ጣሊያኖች እንደ ሀገር እንኳን ለመቆም ቸግሯቸው ነበር፡፡ ጥንት ከነበሩበት የዓለም ልዕለ ኃያልነት ወርደው ወደ የበይ ተመልካችነት ደረጃ አቆልቁለው ራሳቸውን አገኙት፡፡ ይህን ነባራዊ ሁኔታ ላለመቀበልና ግፋም ሲል ለመቀየር የነበራቸው የዘመኑ ዘዴ ከሀገር ውጪ ግዛት ማስፋፋትና መያዝ ነበርና ቅኝ ለመግዛት ሩጫ ገቡ፡፡ ኢትዮጵያን መውረራቸው ውስጥ ውስጡን ሲታይ ጣሊያኖች ከጎረቤቶቻችን አናንስም ከሚል
ሀገራዊ (ማኅበረሰባዊ) የበታችነትን ሥነ-ልቦና ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡
ጣሊያኖች ለራሳቸው የነበራቸው ከእውነታው የራቀ ግምት የተለየ ሚና እንዳላቸው አድርገው እንዲቆጥሩ ሳያድረጋቸው አልቀረም፡፡ “ኋላ ቀርን ሕዝብ እናሰልጥናለን” ብለው ለወረራና መስፋፋታቸው ትክክለኝነት ምክንያት ሲያቀርቡ ሀገራችን ኢትዮጵያ በወቅቱ እነሱ ይጠቅሱ እንደነበረው እጅግም “ኋላ የቀረች” ሀገር አልነበረችም፡፡ በሌላ ወገን በዓለም አቀፍ ውል በማሰር ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር የሞከሩት የብልጣብልጥነት መንገድ አልሰራ ሲል፤ እልፍም ሲል ንጉሡ ውሉን ውድቅ ሲያደርጉት፤ ምኒልክ እንደመሪ ኢትዮጵያዊ እንደ ሕዝብ ንቆኛል ብለው እንዲያስቡ አደረጋቸው፡፡ ለዚህም ጦር መማዘዝን እንደ መፍትሔ ቆጥረው ወረራውን ጀመሩ።
ከዓድዋው ጦርነት ቀደሞ አጤ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በእንግሊዞች፤ አጤ ዮሐንስ በደርቡሾች መተማ ላይ መረታታቸው ለኢጣሊያ ቀጣይ ወረራ የተመቸና የኢትዮጵያ ህዝብ “ገብር” -ቢሉት የሚቀበል አቅሙ ያልደረጀ “ኋላ ቀር” አድርገው ቆጠሩት፡፡ በአንጻሩ ጣሊያን ከጎኗ ያሉ ትንንሽ ግዛቶችን በማሸነፍ ሀገራዊ አንድነቷን ያወጀችበት ወቅት ስለነበር ኢትዮጵያን ለመዉረር ተጨማሪ የማን ያሸንፈኛል ሥነልቦና ሰጥቷቸው ነበር፡፡
በጥቅሉ በጦርነቱ በፊት የነበረው የጣሊያን ሥነ ልቦና ኋላ ቀር ህዝብ ድል አይመታንም። አሸንፈን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛታችን ስር እናደርጋለን የሚል ትዕቢት ነበር።
የማይነካ ንብ ነክተው ድባቅ ተመቱና እንዲህ ተገጠመባቸው እንጂ…
ባመጣው መጨፎ
ባመጣው እርሳስ 
ተፈጠመ ጣሊያን
ዓድዋ ድረስ! 
የጥቁር ህዝብ ኩራት
ዓድዋ 125
የኢትዮጵያውያን ድል
Filed in: Amharic