>
5:13 pm - Saturday April 18, 2443

የኢትዮ ቴሌኮም  ሽያጭ ጥቅምና ጉዳት ጉዳይ - ሙያዊ ቅኝት (ሳመንጉሥ ጥላሁን)

ኢትዮ ቴሌኮም  ሽያጭ ጥቅምና ጉዳት ጉዳይ

ሙያዊ ቅኝት

ሳመንጉሥ ጥላሁን


አፄ ምኒሊክና የመጀመሪያው የስልክ ግንኙነት

ኢትዮጵያ፣በ1886ዓ.ም፣በታላቁ ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት፣  የመጀመሪያውን የ477 ኪ.ሜ የስልክ መሥመር ዘርግታ፣“ጤና ይስጥልኝ  ዐዲስ!! ጤና ይስጥልኝ ሐረር!!” ካስባለች፣126 ዓመታት ተቆጠሩ። አፄ ምኒሊክ፣ሀገሪቷን ያስተዳድሩ በነበሩበት ዘመን ያስገቧቸውን፣ዘመናዊ አሠራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ብዛት ስናይ፣አፄ ምኒሊክ፣“የሥልጣኔ ማግኔት ነበሩ!!” ለማለት እንችላለን።

 አፄ ኃይለሥላሴና የቴሌኮሙኒኬሽን እድገት ኹኔታ

የቴሌፎን ቴክኖሎጂ ወደ ኢትጵያ የገባው፣በ1886 ዓ.ም በምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ የምኒሊክን ፈለግ የተከተሉት አፄ ኃይለሥላሴም፣ኢትዮጵያን፣በኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ እድገት እንድታሳይ፣ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ከ1903 ዓ.ም ጀምሮ፣በተቋም ደረጃ፣የፖስታ፣ የቴሌግራፍና ቴሌፎን ሚኒስቴር (ፖቴቴ) እየተባለ ይጠራ የነበረውን፣የቴሌኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤት፣በ1945 ዓ.ም፣በአዋጅ፣“የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት፣   የቴሌኮሙኒኬሽን ቦርድ (IBTE)” ወደሚል  አዲስ ስም በመቀየር፣ኹለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣የሀገሪቱን የቴሌኮሙኒኬሽን አቅም በእጥፍ በማሳደግ፣በዐዲስ አበባ ብቻ፣ሦስት ሺህ የስልክ ጥሪዎችን  የሚያስተናግዱ የአውቶማቲክ  ማዞሪያዎች በመትከል፣ሥራ ላይ ለማዋል ችለዋል። ይኽ ፈጣን እድገት ሊመዘገብ የቻለው፣የመጀመሪያውን የምሥረታ ዓመት፣የቴክኒክ ባለሞያዎችን እንዲኹም ብቃት ያለው የሥራ አመራርን ሊሰጡ የሚችሉ ባለሞያዎችን  ለማፍራት የሚያስችሉ፣ተመጣጣኝ ሥልጠናዎች በመሰጠታቸው ነበር።

የደርግ መንግሥትና የቴሌኮሙኒኬሽን ማናጅመንት

የደርግ መንግሥት፣የተቋሙን ስም፣ኹለት ጊዜ የቀያየረ ቢኾንም፣በዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመን፣ ደረጃ በደረጃ ይካኼድ የነበረውን፣የቴሌኮሙኒኬሽን እድገት ለማስቀጠል የሚያስችለውን ቢሮክራሲያዊ አሠራር፣አላፈረሰም። የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን (ኢ.ቴ.ኮ) ፣ሀገሪቷ ባፈራቻቸው፣ከፍተኛ ብቃት  ባላቸው ባለሞያዎች፣ኢንጅነሮችና ማናጀሮች  እንዲመራ አድርጓል። በደርግ ዘመን፣ ልክ እንደ ኢ.ቴ.ኮ ኹሉ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፣ንግድ ባንክ ፣ ንግድ መርከብ፣መድን ድርጅት፣መብራት ኃይል፣አውራ ጎዳና እንዲኹም በዐሥር ዘርፍ ተከፍለው የነበሩ የኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽኖች ይመሩ የነበሩት፣የሞያ ነፃነታቸው በተከበረላቸው፣የማናጅመንት አካላት ነበር። ደርግ፣ምንም ዓይነት የምዕራባውያን የፋይናንስ ብድርም ኾነ እርዳታን የማያገኝ መንግሥት የነበረ ቢኾንም፣ወሳኝ የኾኑትን የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ተቋማት፣አንፃራዊ በኾነ መልኩ ከፖለቲካ ነፃ በማድረጉ፣የሀገሪቷን ከፖለቲካ ውጪ የኾነውን አስተዳደራዊ አቅሟን፣አሟጦ ለመጠቀም አስችሎታል። ይኽ እርምጃው፣በኢንዱስትሪውም ኾነ አገልግሎት ሰጪ ተቋሟት ላይ፣በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ይፈጠሩ  የነበሩ ችግሮችን፣በሀገር ውስጥ አቅም ለማካካስ እንዲያስችለው፣ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎለታል። 

የወያኔ ኢሕአዴግ መንግሥትና የቴሌኮሙኒኬሽን ማናጅመንት

ደርግን ተክቶ ሥልጣን ላይ የወጣው፣የወያኔ ኢሕአዴግ መንግሥት፣በአንፃሩ፣የመጀመሪያ ሥራው ያደረገው፣በደርግ ዘመን፣የሞያ ነፃነት የነበራቸውን መንግሥታዊ ተቋማትን በማፈራረስ፣ድርጅቶቹን የሚመሩትን ቢሮክራቶች፣መበታተን ነበር። ለዚኽም ጥሩ ምሳሌ የሚኾነው፣በአንድ ሌሊትና በአንድ ፊርማ፣ዐሥሩን የኢንዱስትሪ ዘርፎች ይመሩ የነበሩትን ኮርፖሬሽኖች አፍርሶ፣ከፍተኛ ባለሞያዎችን  መበተኑ ነበር። በኮንስትራክሽን ዘርፉም፣የኢትዮጵያ ሕንፃ ኮንስትራክሽንን፡፡ ከኢንዱስትሪውም ወጣ ብለን ብናይ፣ባለሞያ ጠሉ ኢሕአዴግ፣የዐዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ   መምህራንን፣ከሥራ ለማባረር የወሰደውን   ተመሳሳይ እርምጃ ማስታወስ እንችላለን።

ከመፈራረስ የተረፉትንም የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽንና የኢትዮጵያ አየር መንገድን  የመሳሰሉ፣ የሀገሪቱ ትልልቅ ተቋማት ከፍተኛ የማናጅመንት አመራር ቦታዎችን  እንዲኹ፣የብሔር ፖለቲካን ለሚያራምዱ እንደነ አቶ ስዬ አብርሃና ዶ/ር አብዱልመጂድ ሁሴንን ለመሳሰሉ ሹማምንቶች በማስተላለፍ፣የሀገሪቱን ዋና ዋና ተቋማት የሥራ አመራር፣ቀድሞ ከነበሩበት፣ ከፖለቲካ ነፃ ሞያዊ አስተዳደር ወደ ፖለቲካዊ ቅኝት ያለው አስተዳደር እንዲያሽቆለቁሉ አደረጉ። 

ከደርግ በተለየ፣ወያኔ ኢሕአዲግ፣ የምዕራባውያንን ድጋፍና አዎንታ  ያልተለየው መንግሥት ስለነበር፣የወርልድ ባንክንና የአይ.ኤም.ኤፍን እንዲኹም የምዕራባውያን ሀገራትን ብድርና እርጥባን፣በቀላሉ ያገኝ ነበር። ይኽ የውጪ ብድርና የገንዘብ እርዳታ፣ከፖለቲካ ነፃ የነበረውን ቢሮክራሲ በማፈራረሱ ምክንያት፣እየተከሰተ የነበረውን፣ዘለቄታዊ  ገጽታ ያለው የኢኮኖሚክና ማህበራዊ  አደጋ  ማየት እንዲሳነው ወይም  እያወቀም ቢኾን፣ከቁብ እንዳይቆጥረው አድርጎታል። ይኽ፣የወያኔ ኢሕአዲግ ባለሞያ ጠል እርምጃው፣እጥፍ ድርብ ችግሮችን እየወለደ፣ለ30 ዓመታት ሲንከባለል ቆይቶ፣በአኹኑ ሰዓት፣እንደ የኢትዮጵያ መብራት ኃይልና የኢትዮጵያ መንገድ ባለሥልጣንን የመሳሰሉ የመንግሥት ተቋማትን፣ወደ 600 መቶ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ እዳ  ባለቤት አድርጓቸዋል።

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን፣በወያኔ ኢሕአዲግ መንግሥት  መስተዳደር ከጀመረበት ከ1983 ጀምሮ፣የተጓዘበትን መንገድ ስንዳስስ፣የእነ ዶ/ር አብዱልመጂድ ሁሴን  የኮርፖሬሽኑን የከፍተኛ አመራር ቦታ  ሹመት ተከትሎ፣ቀስ በቀስ፣አጠቃላይ ማናጅመንቱን፣በተለያዩ የብሔር የፖለቲካ ሹመኞች በመለወጡ፣መሥሪያ ቤቱ፣ለከፍተኛ የአሠራር ችግሮችና እንቅፋቶች  እንዲጋለጥ መደረጉን፣እንገነዘባለን። የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ፣እንደሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ከአጠቃላዩ ሕዝብ የቀን ተቀን እይታ ውጪ፣እንዲኹም ከሌሎች ሀገራት የቴሌኮሙኒኬሽን  እድገትና አጠቃቀም አንፃራዊ እይታ ውጪ ሊኾን ስለማይችል፣ወያኔ ኢሕአዲግ፣ውሎ አድሮም ቢኾን፣መሥሪያ ቤቱ ላይ ያንሰራፋውን፣ለሥራና እድገት ማነቆ የኾነውን፣ፖለቲካዊ ገጽታ ያለውን ማናጅመንት ለመቀየር፣እንዲያስብበት አስገድዶታል።

በዚኽም መሠረት፣ከፍተኛውን የማናጅመንት የሥራ ቦታ፣በ1995 ዓ.ም፣ከዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጡ መምህራን፣እንዲያዝ  አድርጓል። ዐዲሶቹ የማናጅመንት አባላት፣በቴሌኮም ኢንዱስትሪው የነበራቸው ልምድ አነስተኛ በመኾኑ፣ከነባር ኢንጅነሮችና ኤክስፐርቶች ጋር፣ አንዳንድ አለመግባባቶችና ቅራኔ ቢፈጥሩም፣እነዚኽ መምህራን፣የራሳቸው የኾነ፣የለውጥ ዕቅድ የነበራቸው ነበሩ። የቴሌኮም መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት ባሻገር፣በተለይ የሀገሪቱን የቴሌኮም አቅም ለማሳደግ፣ወሳኝ የኾነውን የሰው ኃይል ለማፍራት፣ፈጣንና ተግባራዊ ሥራዎችን ለማከናወንም ችለውም ነበር።  ለዚኽም፣እንደ ምሳሌ ሊወሰድ የሚችለው፣የቴሌኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት(ICTIT) እየተባለ ይጠራ የነበረውን፣ለማቋቋም ያደረጉት ተግባራዊ ጥረት ነው። ከፍተኛ  ልምድ ያላቸውን፣የኤም አይቲ ዶክቶራል ዲግሪ ተመራቂ  ኢትዮጵያውያዊ  መምህራንን ያካተተው ይኽ ተቋም፣ኢንፎርሜሽን ሳይንስ፣ቴሌኮም ኢንጂነሪንግና ቴሌኮም ማናጅመንትን የመሳሰሉ ዲፓርትመንቶችን በመክፈት፣በማስተርስ ዲግሪ ደረጃ፣ለወጣት ተተኪ የተቋሙ ሠራተኞች እንዲኹም ከተቋሙ ውጪ ላሉ፣በቴሌኮም ዘርፍ  ሞያ ለመቀጠል ለሚፈልጉ፣ብሩህ አእምሮ ላላቸው ተወዳዳሪ ተማሪዎች፣በክፍያና በስኮላርሺፕ መልክ፣የትምህርት እድል እንዲያገኙ ያደረጉት ተግባራዊ ሥራ፣የሚጠቀስ ነው። ይኹንና፣ የወያኔ ኢሕአዴግ መንግሥት፣ከፖለቲካ ነፃ የኾነ፣በፕሮፌሽናሎች  የሚመራ፣ቢሮክራሲን አጥብቆ የመጥላት አባዜው የሚለቀው ስላልነበረ፣እነዚኽ ከዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡ የማናጅመንት አመራሮች፣ሦስት ዓመት  እንኳን ሳይሞላቸው፣በሙስና  እንዲከሰሱ አድርጎ፣  ወደ ወኽኒ ቤት አወረዳቸው። የእነርሱን ወደ ወይኽኒ ቤት መውረድ ተከትሎም፣የሃገሪቷን  የቴሌኮም ዘርፍ የሰው ኃይል አቅም ለማሳደግ እንዲረዳ ያቋቋሙትንም ኢንስቲትዩት ዘጋው። አጠቃላይ የማናጅመንት ቦታውን፣በአውራ ካድሬዎች መልሶ እንዲያዝ አደረገ።

በፋይበር  ብሮድባንድ ኢንተርኔት ኮኔክሽን ለማግኘት የተደረገው ስምምነት

እነዚያ ካድሬ ማናጀሮች፣ሥልጣናቸውን እንደተረከቡ፣ከ800 ሜጋ ባይት የማይበልጠውን፣ በዋናነት ከሳተላይት ሊንክ  ይገኝ የነበረውን፣የሀገሪቷን የኢንተርኔት አቅም  ለማሳደግ፣ የ47ሚሊዮን ዶላር  ስምምነት፣ለምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያውን  ኢንተርናሽናል ሰብማሪን የብሮድባንድ ኬብል ከዘረጋው፣ከሲኮም (SEACOM) ኩባንያ ጋር ተፈራረሙ። በስምምነቱም፣  ሲኮም፣ለገበያ ካቀረበው 2.3 ቴራ ባይት ኢንተርናሽናል ብሮድባንድ  ሊንክ ላይ፣0.25% ማለትም 2.5 ጊጋ ባይት  ኢንተርኔት ኮኔክሽን፣ጅቡቲ ወደብ ላይ እንዲቀጥል ተደረገ።  ስምምነቱን ተከትሎ፣“የኢ.ቴ.ኮ ማናጅመንት፣የሀገሪቷን የኢንተርኔት አቅም፣ከሦስት እጥፍ በላይ አሳደገ!” የሚለው ዜና፣በመንግሥት የሜዲያ አውታሮች ተሰራጨ።  የመንግሥት ልሣን የኾነው አዲስ ዘመን ጋዜጣም፣የኢ.ቴ.ኮ  ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩትን ግለሰብ  በመጥቀስ፣ ስምምነቱ፣ከኹለት ዓመት በላይ ድርድር ተደርጎበት የተፈረመ መኾኑን  በመግለጽ፣  አንባብያንን አስደመሙ። የሚገርመው ነገር ቢኖር፣ሲኮም (SEACOM)፣ 2.3 ቴራ ባይት  ሰብማሪን ኬብል፣ሕንድ ውቅያኖስ ላይ ዘርግቶ፣በዓለም የመጨረሻው የብሮድባንድ ኢንተርኔት መዳረሻ ለኾኑት፣ለምሥራቅና ደቡም አፍሪካ ሀገራት፣የፈጣን ኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ  የፈጀበት ጊዜ፣ሦስት ዓመት ብቻ መኾኑ ነበር። የሲኮም ኢንቨስተሮች፣ከ75% በላይ የሚኾኑት፣ አፍሪካውያን የነበሩ ሲኾን፣አጠቃላይ ኢንቨስትመንቱም፣750 ሚሊዮን ዶላር አይበልጥብም ነበር።  

ነገር ግን፣ከላይ የተጠቀሰው  ኢ.ቴ.ኮ፣ከሲኮም፣2.5 ጊጋ ባይት ኢንተርኔት ባንድዊድዝ   ለመግዛት የከፈለው 47 ሚሊዮን ዶላር፣ሲኮም(SEACOM) ሲቋቋም  አክሲዮን ቢገዛበት ኖሮ፣  ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ከ100 ጊጋ ባይት  ወይም 0.1 ቴራ ባይት   ሊደርስ የሚችል፣  ኢንተርናሽናል  ኮኔክሽን ልታገኝበት ትችል ነበር። ልብ ልንለው የሚገባው፣አኹንም፣ከ15 ዓመት በኋላም ቢኾን እንኳን፣የኢንተርናሽናል ኮኔክሽን አቅማችን፣100 ጊጋ ባይት  አለመድረሱን ነው። ሀገር፣የካድሬዎች መጫወቻ ስትደረግ የሚደርሰው አደጋ፣ይኼንን ይመስላል። ኬንያ፣እ.ኤ.አ ማርች 2020 ላይ፣ ሞምባሳ ላይ ካገናኘችው፣ባለ12 ቴባ ሰብማሪን ኬብል በተጨማሪ፣ESSAT, SECOM, ESSAY ከተሰኙ ሰብማሪን ኬብሎች ጋር፣ኮኔክሽን ያላት ሲኾን፣የኬንያ መንግሥት፣ESSAY  ሰብማሪን ኬብል ላይ፣35%  የአክሲዮን ድርሻ አለው።

ከቻይናው የመሠረተልማት ካምፓኒ ዚቲኢ(ZTE) ጋር የተደረገው ስምምነት

ኢ.ቴ.ኮ፣በካድሬዎች ደካማ  አመራር ሥር በወደቀበት በዚያን ወቅት፣የአፍሪካን ገበያ ለመቆጣጠር አቅዳ ትንቀሳቀስ የነበረችው ቻይና፣ለወያኔ መንግሥት፣የብድር ስምምነት እንዲዋዋልና ዚቲኢ(ZTE) በተሰኘው መንግሥታዊ የቴሌኮም የመሠረተልማት ካምፓኒዋ አማካኝነት፣በመላው ሀገሪቱ  የቴሌኮም መሠረተልማትን ለመዘርጋት  የሚያስችል፣የ1.5 ቢሊዮን ዶላር፣የቬንደር ፋይናንሲንግ ስምምነት እንዲደረግ፣እድል የሰጠችው። በዚኽ፣ በተደረሰው ስምምነት መሠረት፣የቴሌኮም መሠረተልማቱ፣የ2ጂን እና 3ጂን ቴክኖሎጂ ሊያስተናግድ በሚችል ኹኔታ፣የፕሮጀክት ሥራው፣በተለያዩ ደረጃዎች የቴሌኮም ማስፋፊያ ፕሮጀክት 1-2 (TEP 1-2) ተከፋፍሎ ነው ዝርጋታው የተከናወነው። የኔትወርክ መሠረተልማቱ ዝርጋታ እንዳለቀ፣በወያኔ ካድሬና ወታደሮች የተሞላው የሥራ አመራር፣ይኽ የተዘረጋውን ከፍተኛ የኔትወርክ አቅም ሊጠቀም የሚችል ደንበኛ ለማፍራት  የሚያስችል፣ የማርኬቲንግ ስትራተጂ ሊነድፉ የሚችሉ ስላልነበሩ፣ወያኔ፣ለኹለት ዓመት የሚቆይ የማናጅመንት ኮንትራት፣ከ30 ሚሊዮን ዩሮ በላይ በማውጣት፣ለፍራንስ ቴሌኮም (France Telecom)  ለመስጠት ተገደደ።

 ከፍራንስ ቴሌኮም ጋር የተደረገው የማናጅመንት ስምምነት

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን (ኢ.ቴ.ኮ) የሚለውን ስም፣ወደ ኢትዮ ቴሌኮም በመቀየር ሥራውን የጀመረው፣የፍራንስ ቴሌኮም ማናጅመንት፣በመላው ሀገሪቷ የተዘረጋውን፣ የመሠረተልማት  አቅም ለመጠቀም የሚያስችል ስትራተጂ በመንደፍ፣የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚውን፣በተለይም የሞባይል ስልክ ተጠቃሚውን ቁጥር፣ከ4ት ወደ 7፣ከ7 ወደ  14፣ከ14 ወደ 23  ሚሊዮን፣በኹለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ፣እንዲያድግ አድርገውታል። በዚኽ በኹለት ዓመት ተኩል፣የፍራንስ ቴሌኮም ማናጅመንት ዘመን፣ብዙ የአገልግሎት ዓይነቶች፣በስፋት የተዋወቁና የዋጋ ቅነሳና ማሻሻያዎች እንዲተገበሩ እንዲኹም በርካሽ ዋጋ የሚገዙ የስልክ ቀፎዎች  ለደንበኞች እንዲቀርቡ በመደረጉ፣በሀገሪቱ የነበረው የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ቁጥር፣በከፍተኛ ኹኔታ ሊጨምር ችሏል። እዚኽ ላይ፣የፈረንሣይ ማናጅመንት፣አንጻራዊ የሥራ ነፃነት የነበረው እንደመኾኑ፣የአገልግሎት ዘርፉን በተለይም የተገልጋዮችን ቁጥር በመጨመር ረገድ እንዲኹም የተገልጋዮችን እንክብካቤ (Customer Care) በማሳደግ፣ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ቢያስችለውም፣በእውቀት ሽግግር በኩል፣ሊሠራው ከሚገባው በታች ነበር – የሠራው።  ይኽም የኾነበት ዋናው ምክንያት፣ሥራውን በቅልጥፍና ሊሠሩና የማናጅመንት ክህሎታቸውን ሊያሳድጉ የሚችሉ፣በርከት ያሉ ንቁ ባለሞያዎች፣ከፍራንስ ቴሌኮም  ማናጅመንት ባለሞያዎች ጋር፣ጎን ለጎን  ኾነው እንዲሠሩ፣ዕድል ስላልተሰጣቸው ነበር።

የኢንተርኔት በገጠር ከተሞች መስፋፋትና ሕዝባዊ አመጽ

ወያኔ፣የፍራንስ ቴሌኮም ማናጅመንትን ካሰናበተ በኋላ፣ተመልሶ፣የከፍተኛ የሥራ አመራሩን፣ ወደነበረበት፣ካድሬዎችና ወታደሮች ወደተሰገሰጉበት አስተዳደር እንዲመለስ ቢያደርግም፣ወያኔ እንዳሰበው፣ኹኔታዎች ሊኾኑለት አልቻሉም። የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚውን ቁጥር ማደግ ተከትሎ፣በተለይም በገጠሪቷ ኢትዮጵያ፣የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚው ቁጥር እየበዛ በመምጣቱ፣ከ2008ዓ.ም ጀምሮ፣በመላው ሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን ፖለቲካዊ ይዘት ያለው አመጽ ለማቀጣጠል፣ዋነኛ መሣሪያ ኾኖ አገለገለ። ወያኔ፣ሕዝባዊ አመጹ ሲበረታበት፣ኢንተርኔቱን፣ ከ6ት ወር በላይ እስከመዝጋት ቢደርስም፣የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ግፊት እያየለ በመምጣቱና  የኢንተርኔት ፌስቡክ አብዮቱን መቋቋም ባለመቻሉ፣በ2010 ዓ.ም ለተደረገው የሥልጣን ሽግሽግ፣በር ከፍቷል።

የኦዴፓ መራሹ ብልጽግናና የኢትዮ ቴሌኮም ሽያጭ  ኹኔታ

በወያኔ ኢሕአዴግ እግር ሥር የተተካው ኦዴፓ ኢሕአዴግ፣የአኹኑ ብልጽግና፣ገና ወንበሩን ከመያዙ ሳምንት ሳይሞላው፣የቴሌኮም ዘርፉን፣ለውጪ ኢንቨስተሮች  ሽያጭ እንደሚያቀርብ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ማስታወቁ፣ብዙዎቻችንን፣ግራ ያጋባና ያስደነገጠ ጉዳይ ነበር። ይኽ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስታወቂያ፣ከውጪ ኃይሎች በተደረገ ግፊትና ምንአልባትም  ከወያኔ እጅ ላይ፣የሥልጣን ሽግግሩን ለማሳካት እንዲረዱ፣ለውጪ ኃይሎች እጅ መንሻ ቃል የተገባበት ጉዳይ እንደኾነ ይገመታል።  ይኽን ግምት የሚያጠናክርልን ነገር ቢኖር፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣እ.ኤ.አ በ2018ቱ የዳቮስ የኢኮኖሚክ ፎረም ላይ ተጋብዘው፣ንግግር ባደረጉበት ወቅት፣የቴሌኮሙን ሴክተር፣ለውጪ ኢንቨስተሮች ገበያ ማቅረባቸውን ሲገልጹ፣ከሌሎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጠቀሷቸው በርካታ ጉዳዮች በተለየ፣ከዓለም አቀፉ ግሎባሊስት ኢኮኖሚክ ኤሊት ታዳሚ  የተቸራቸውን ጭብጨባ ስንመለከት፣ የቴሌኮም ሽያጩ ጉዳይ የውጪ ኃይሎች ግፊትና ተፅእኖ ሥር እየተከናወነ ያለ መኾኑን እንረዳለን። ዐዲሱ ተረኛ ኦዴፓ-ኢሕአዴግ  የቴሌኮም ሴክተሩን ሽያጭ በአሁኑ ጊዜ ዋነኛ ጉዳዩ አድርጎ የሽያጭ ኺደቱን አማካሪ አድርጎ ከቀጠራቸው ከዓለም ባንክ እንዲኹም ከኢንተርናሽናል ፋይናንሻል ኮርፖሬሽንና ሌሎች የግሎባሊስቱ ማኅበረሰብ ጉዳይ አስፈጻሚ ድርጅቶችና አካላት ጋር በመኾን የሽያጩን ኺደት እያጣደፈው ይገኛል።  ይኽ፣ያልበሰለ ጊዜያዊ ኢኮኖሚያዊ እንዲኹም ፖለቲካዊ ጥቅምን ብቻ ያማተረ ችኩል የመንግሥት እርምጃ፣ የሀገሪቷን  ዘለቄታዊ የኢኮኖሚክ ሉዓላዊነት አሳልፎ የመስጠት፣የመጀመሪያው ምዕራፍ  ተደግጎ ሊቆጠር ይችላል።  ይኽን ሀቅ ለመረዳት፣ ከሽያጩ ሊገኝ የሚችለውን ጊዜያዊ ጥቅምና ዘለቄታዊ ጉዳት ስናጤን፣የምናገኘው እውነታ እንደሚከተለው ነው።

 ጊዜያዊ ጥቅም

መንግሥት፣ኢትዮ ቴሌኮምን፣በከፊልም ኾነ በሙሉ በመሸጥ፣በነስትራትፎር የተገመተለትን፣ ከ 15 እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ግምት ግማሽ ዋጋ ቢያወጣለት፣ከ28 ቢሊዮን ዶላር በላይ  እዳ የተጫነውን የሀገሪቷን የ110 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚ(GDP)፣ለጊዜው ከ5% እስከ 10% ሊያሳድግ ይችላል። ይኽን ጊዜያዊ እድገትና የውጪ ምንዛሬ ፍሰት ተጠቅሞ፣መንግሥት፣ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ገጽታውን እንዲገነባ፣ሊረዳው  ይችላል። በሌላ በኩል፣የቴሌኮም ሴክተሩን በሚቆጣጠሩት የውጪ ኢንቨስተሮች፣ዐዳዲስ አገልግሎቶች በፍጥነት ሲተዋወቁ፣ተገልጋዩን ኅብረተሰብ፣ለጊዜውም ቢኾን፣ሊያስደስተው ይችላል። ይኽ፣መንግሥት፣በችኩልነትና በውጪ ተጽእኖ ሥር እያካኼደው ያለው፣የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ ሽያጭ፣ሊያስገኝ የሚችለው ውጤት ቢኖር፣ልክ ወያኔ የቢራ  ፋብሪካዎቹን በቢሊዮን ዶላር በመሸጥ፣አግኝቶት የነበረውን ዓይነት ጊዜያዊ ትርፍ ማግኘት ብቻ ነው። ውሎ አድሮ፣“የማልጠግብ መስሎኝ በሬዬን አረድኩት!!” የሚለውን የአበው ብሂል፣እንድናስታውስ መኾናችን  አይቀርም።  

ዘለቄታዊ ጉዳቱ

    መንግሥት፣የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅሙ ይዳከማል። ለምሳሌ ብንወስድ፣በአኹኑ ሰዓት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣16ሺ ቋሚ  ሠራተኞች  ያሉትና ከ20ሺ ላላነሱ የኮንትራት ሠራተኞችና፣248 ዋና አከፋፋዮች 1348 ተቀባይ አከፋፋዮች እንዲሁም ከ247ሺ በላይ ቸርቻሪዎች የሥራ ዕድልን የፈጠረ ነው። ለውጪ ባለሃብቶች ፕራይቬታይዝድ ሲደረግ፣እንዲኽ ያለ፣ ሰፊ ቅጥርና የሥራ እድል፣ የመፈጠሩ ጉዳይ የማይታሰብ ነው። የውጪ ኢንቨስተሮች፣ዋናው የኢንቨስትመንት ዓላማቸው፣ትርፍ ነው። በመኾኑም፣በጥቂት ሠራተኛ፣ ብዙ ሥራን በማሠራት፣ትርፋማነታቸውን ማረጋገጥ ብቻ ነው – ዓላማቸው።  በ2011ዓ.ም፣ከፍራንስ ቴሌኮም ጋር የተደረገው የማናጅመንት ውልን ተከትሎ፣ከ3ሺ በላይ ሠራተኞች የተቀነሱበትን ማስታወስ፣በቂ ነው። የኢትዮ ቴሌኮም በሙሉ ወይም  በከፊል መሸጥ፣በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞችን፣የሥራ ዕድል እንደሚያሳጣ ይታወቃል።  ምክንያቱም፣ኢትዮ ቴሌኮም፣ግማሽ የቢዝነስ አቅሙን ሸጦ፣ አኹን የያዘውን 16ሺ ሠራተኛ መሸከም የሚያስችል፣አቅም አይኖረውም። ላድርግም ቢል፣ ተወዳዳሪ መሆን ያቅተዋል፡፡ በመኾኑም፣የሚጠብቀው ዕድል፣ለቀጣይ ሽያጭ እራሱን ማመቻቸት ብቻ ይኾናል።

  የመንግሥትን የኢኮኖሚክ አቅም ምንጭ በማድረቅ፣የንግሥትን አቅምን ያዳክማል። በመንግሥት አቅም ሊሠሩ የሚችሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች፣እንደ ሕዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችን (state sponsored) የማካኼድ ዕድላቸው ይመናመናል።  በመኾኑም፣ ፖለቲካው ከውጪ በመጣው ከበርቴ ግሩፕ የመጠለፍና ከሕግና ደንብ ይልቅ፣ለቢዝነስ ኢንተረስት ግሩፕ የመቆም ወይም የመገዛት ዕድሉ፣እየሰፋ ይኼዳል። የ”political market place” የሚባለው ዓይነት መንግሥታዊ አስተዳደር እንዲሰፍን፣በር ይከፍታል።

          መንግሥትና ኅብረተሰቡ፣በማኅበራዊና ብሔራዊ ጥሪ አማካኝነት የሚያገኙትን፣የገንዘብና ያገልግሎት ድጋፍ ያጣሉ ። ለምሳሌ፣ባለፈው ዓመት 2012 ዓ.ም ብቻ፣ኢትዮ ቴሌኮም፣ ለኮሮና ወረርሽኝ ያደረገውን የ772 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ጨምሮ፣ከ1.15 ቢሊዮን ብር የሚደርስ፣ለመንግሥትና ለኅብረተሰቡ ድጋፍ ሰጥቷል። የዐዲስ አበባው ቀላል ባቡር ፕሮጀክትም የተገነባው፣ከቴሌኮም ሴክተሩ በተገኘ ትርፍ ጭምር መኾኑንም፣ማስታወስ ይቻላል።

          የቴሌኮም ሴክተሩን የሚቀራመቱት የውጪ ኩባንያዎች የገንዘብ አቅም፣ ከፍተኛ ስለሚኾን፣የሀገር ውስጥ ባለሃብቶችና ባለሞያዎች ተደራጅተው፣በቴሌኮም ዘርፍ ሊሳተፉ የሚችሉበትን ዕድል  ይዘጋል። በአፍሪካ ሀገራት ያለውን ልምድ እንደምናየው፣ተወዳዳሪ ሊመጣ የሚችለው፣በቀጥታ ከውጪ ኩባንያዎች ብቻ ይኾናል። ለምሳሌ፣የአፍሪካን ከ40 በላይ የኾኑ የቴሌኮም ኦፐሬተሮች ቢዝነስ ብንቃኝ፣በከፊል በመንግሥት የአክሲዮን  ድርሻ ከታየዙት ኦፐሬተሮች በስተቀር፣በአፍሪካውያን ባለሃብቶች፣ሙሉ በሙሉ የተያዙት ኦፐሬተሮች፣ከአንድና ሁለት የዘለሉ አይደሉም። በዚኽ ረገድ፣በናይጄሪያዊው ማይክ  አዴኑጋ (Mike Adenuga) ባለቤትነት የተያዘው፣45 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት  “ግሎ ሞባይል (glo mobile)” ፣ለናይጄሪያውያን ኩራት ነው።

          ኢትዮጵያ፣ይብዛም ይነስ፣እስካኹን፣በራስዋ ልጆች እውቀት የምትተማመን ሀገር የነበረች መኾኗ፣የሚታወቅ ነው።  አኹን፣እራሱን ለማሸጋገር እየተንደረደረ ያለው፣ኦዴፓ መራሹ የብልጽግና መንግሥት፣በኢትዮጵያውያን ባለሞያዎችና የቢዝነስ ሰዎች እንዲኹም ባለሃብቶች፣እምነት በማጣት፣ሊወስድ የተዘጋጀውና እየወሰደ ባለው ትልልቅ የመንግሥት ኩባንያዎችን ለውጪ ባለሃብቶች የመሸጥ ችኩል እርምጃ፣የሀገሪቷን የኢኮኖሚክ ሉአላዊነት፣ቀስ በቀስ አሳልፎ የመስጠት ጉዞውን፣ሀ ብሎ ጀመረው ማለት ነው። እንደ ኬንያዊው  ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ  እንዲኹም ጆሸዋ ኦፔንጋ፣በአፍሪካ ደረጃ የታወቁ፣የአፍሪካ የፖለቲካና የኢኮኖሚ  ልሂቃን አስተያት፣አፍሪካ በአኹኑ ሰዓት፣ በአውሮጳውያንና በቻይናውያን የኢኮኖሚክ ቅኝ ግዛት ውስጥ ያለች አህጉር  ናት ። በአፍሪካ፣በየሃገራቱ የሚገኙ መሠረታዊ  የባንኪንግ፣የኢንሹራንስ፣የማእድን፣የቴሌኮምን የመሳሰሉት ኢንዱስትሪዎች፣በአውሮጳውያን  ባለሀብቶች የተያዙ ናቸው። የአፍሪካ ኢኮኖሚ፣በአጭሩ፣በአውሮፓውያንና በቻይናውያን እጅ ውስጥ የወደቀ ነው።  ፈረንሣይ ብቻዋን፣ ወደ 15 ሚጠጉ  ቤኒን ፣ ቡርኪናፋሶ ፣ ጊኒቢሳኦ ፣ አይቮሪኮስት ፣ ማሊ ፣ ኒጀር ፣ ሴኔጋል ፣ ቶጎ ፣ መካከላኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ካሜሩን፣ጋቦን፣ኢኳቶሪያል ጊኒ እንዲኹም ኮንጎ የምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ የቀድሞ ፈረንሣይ ቅኝ ሃገራትን ኢኮኖሚ ተቆጣጥራለች ። እነዚኽ ሀገራት የሚጠቀሙት ገንዘብ፣የፈረንሣይ ፍራንክ ሲኾን፣የብሔራዊ ሪዘርቭ ገንዘባቸውን 85% የሚያስቀምጡት፣ፓሪስ በሚገኘው በፈረንሣይ ሴንትራል ባንክ ሥር ብቻ ነው። ገንዘብ መበደር ሲፈልጉ እንኳን፣የራሳቸውን ገንዘብ፣በወለድ ነው – የሚበደሩት።  እንደ ዶ/ር ኤሪካና ቺሆምቦሬ፣የቀድሞ በአሜሪካን ኒውዮርክ የአፍሪካ አንድነት አምባሳደር  መረጃ ከኾነ፣ከምዕራብ አፍሪካ ብቻ፣ወደ 500 ቢሊዮን ዶለር የሚጠጋ  ሀብት፣በየዓመቱ፣ወደ ፈረንሣይ ባንኮች፣ፈሰስ ይደረጋል። በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት፣በአኹኑ ጊዜ፣ከፈረንሣይ የኢኮኖሚክ ቅኝ ግዛት ለመላቀቅ፣በምዕራብ አፍሪካ የጋራ ኢኮኖሚክ ማኅበር  (ECOWAS) በኩል፣ከፍተኛ ትግል እያደረጉ ይገኛል። ኢኮ (eco) የተሰኘ የጋራ ገንዘብና   ነጻ የጋራ ገበያ ለማቋቋም  የሚያስችላቸውን ስምምነትም ተፈራርመው፣ወደተግባር እየገቡ ነው።  የእነዚኽን የአፍሪካ ሀገራት ልምድ ስናይ፣ምንም እንኳን በአኹኑ ሰዓት፣ኢትዮጵያ ያለችበት የፖለቲካና የኢኮኖሚክ ኹኔታ፣ከብድርና ከእርዳታ አዙሪት አላስወጣ ብሎ ቢይዛትም። ለኢትዮጵያ ሀገራችን ዘለቄታዊ እድገት የምናስብ ከኾነ፣የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን አቅም ማሳደግ፣ አማራጭ የሌለው  አቅጣጫ መኾኑን እንረዳለን። ይኽን ለማድረግ ደግሞ፣መንግሥት፣ ትልቁን ሚና መጫወት የሚያስችለውን፣በእጁ የያዛቸውን ትልልቅ ኩባንያዎች፣ለውጪ ባለሀብቶች ከማዘዋወሩ በፊት፣ወደ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች እጅ ሊገቡ የሚችሉበትን መንገድ፣መቀየስ ይጠበቅበታል። በኢትዮጵያ ያሉ የግል ባንኮች የተቋቋሙት፣ቀደም ሲል፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ይሠሩ በነበሩ፣ልምድ ባላቸው ባለሞያዎች አማካኝነት ነበር።  ይኽ ዕድል፣መንግሥት፣ለባንክ ባለሞያዎች ከዚኽ ቀደም እንደሰጠው ኹሉ፣በኢትዮ ቴሌኮምም ኾነ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይሠሩ የነበሩ ነባር ባለሞያዎች፣የየሴክተራቸውን  የግል ኩባንያ እንዲያቋቁሙ፣ዕድሉን መንግሥት ሊያመቻች ይገባል። ይኽን በማድረግ፣ ወደፊት ሊመጡ ከሚችሉ የውጪ ኩባንያዎች ጋር፣ተፎካካሪ የሚያደርጋቸውን የማናጅመንት እና የካፒታል አቅም ሊገነባላቸው ይችላል።  የኤየርላይንስም ኾነ የቴሌኮም ቢዝነስ፣ዋናው አቅም የሚጠይቀው ማናጅመንት ነው። ለረጅም ጊዜ ፖለቲካውን ከሚመሩት አምባገነኖች የሚመነጩ፣እንጭጭ አስተሳሰቦችና ተጽዕኖዎች፣ነፃ የነበሩና ያልተበረዙ የማናጅመንት አመራር  የነበሯቸው፣እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ  ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች፣ለረጅም ዐሥርት ዓመታት፣በዓለም ደረጃ  ያሳዩት ተወዳዳሪ የኾነ የማናጅመንት ብቃት፣በሌሎች እንደ ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ለመድገም፣የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ችግር ካልኾነ በስተቀር፣የእውቀት ችግር እንደማያግዳቸው፣ለመረዳት እንችላለን። የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣የአፍሪካ ሀገራት ሕዝቦች ኩራት እና አርአያ አድርገው የሚመለከቱት ኩባንያ መኾኑንም፣ማስታወስ አለብን። የኢትዮጵያን አየር መንገድ፣አሳልፎ ለአውሮፓውያን ወይም ለቻይና ወይም ለዐረብ  ሀገራት ባለሐብቶች መሸጥ፣የአፍሪካውያንንም ቅስም የሚሰብር እንደኾነ፣ልናውቅ ይገባል።  በመኾኑም፣መንግሥት፣ልክ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣በየሴክተሩ፣ትልልቅ አገር በቀል ኾነው፣አገር ዘለል፣በተለይ በአፍሪካን ሰፊ ገበያ ላይ ሊያተኩሩ የሚችሉ  ኩባንያዎችን እንዲያቋቁሙ፣መሥራት ይጠበቅበታል። ነገር ግን፣አኹን፣“ሀገሪቷን እያሻገርኩ ነው!!” የሚለው መንግሥት፣ጊዜያዊ የፖለቲካልና ኢኮኖሚክ ጥቅምና ትርፍን በማስላት፣ኢትዮ ቴሌኮምን በመሸጥ የጀመረውን ጉዞ፣ ወደ ባንኮቹና ኢንሹራንሶቹ፣ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ማሪታይም ትራንዚት፣ወደ ምድር ባቡር እና የስኳር ኮርፖሬሽን ከቀጠለ፣እንደ አያያዙም ከኾነ፣የሚቀጥል ይመስላል። ኢትዮጵያ፣እንደ አፍሪካውያን መንግሥታት፣ያላትን ኹሉ ሸጣ፣ባዶ እጇን የምታጨበጭብበት ጊዜ፣እሩቅ አይኾንም። ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የመጣውን፣ኢትዮጵያውያን እንኮራበት የነበረውን፣በራስ የመተማመንና በራስ አቅም የማደግ መንፈሳችንን፣ሰባብሮ የሚጥልም ይሆናል። አኹን፣የአፍሪካ ሀገራት ለመመለስ ሚታገሉለትን  የኢኮኖሚክ ነፃነት፣በገዛ እጃችን፣አሳልፈን ለውጪ ባለሀብቶች  በማስረከብ፣የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ፣በኢኮኖሚክ ባርነት ውስጥ፣የሚከተው ይኾናል።

 በምርጫ የሚያሸንፍ መንግሥት፣ሊያያቸው የሚገባቸው አማራጮች

  1. የአምስት ዓመት እቅድ ወስዶ፣የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ከነባርም ኾነ ዐዳዲስ ባለሞያዎች ጋር ኾነው፣የኢትዮ ቴሌኮምን የተለያዩ ሴክተር ሥራዎችን፣በአውትሶርሲንግበመስጠት፣ የቴሌኮም ሴክተሩን ሥራ፣ልምድ እንዲያገኙበት እንዲኹም የገንዘብ አቅማቸውንም እንዲያደረጁ ማገዝ። ለምሳሌ፣የቴሌኮም መሠረተልማቱን የጥገና ሥራ፣የፋይበር ኬብል ዝርጋታ ሥራን ለሀገር ውጥ ባለሞያዎችና ባለሀብቶች ጥምረት ለሚፈጠሩ ኩባንያዎች፣አውትሶርስ ማድረግ። እዚኽ ላይ፣ የቻይናን ምሳሌ ብንመለከት፣አኹን፣የዓለምን የቴሌኮምና የኦንላይን ንግድ እየተቆጣጠሩ የመጡት፣እንደ ሁዋዌና አሊባባ ያሉት፣ጠንካራ የዓለማችን የቴክኖሎጂ ካምፓኒዎች፣አኹን የደረሱበት ለመድረስ፣የቻይና መንግሥት ያደረገላቸው አስተዋፅኦ፣ እጅግ ወሳኝ ነበር።  በቻይና መንግሥት ድጋፍ እየተደረገላቸው የተቋቋሙ፣የግል  የቢዝነስ ተቋማት  ያፈሯቸው የቻይና ኢንተርፕሬነር ቢሊየነሮች፣እ.ኤ.አ በ2020፣የሀብት መጠናቸው፣ ከ4.3 ትሪሊየን የዘለለ ኾኗል። ይኽም፣የአፍሪካን 3.3 ትሪሊየን አጠቃላይ ኢኮኖሚ፣በትሪሊየን ዶላር የሚበልጥ ነው። የቻይና ፈጣን እድገት የተመዘገበው፣መንግሥትና ኢንተርፕሬነሮችዋ በጋራ፣ለአንድ ዓላማ፣’ቻይና’ን በጥምረጥ፣በመሥራታቸው ነው። ለእኛም ሀገር ኢንተርፕሬነሮችና ባለሀብቶች፣የኢትዮጵያን ዕድገት ዓላማው ያደረገ የመንግሥት ድጋፍ፣ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ መንግሥትና የኢትዮጵያ ኢንተርፕሬነሮችና ባለሀብቶች፣የጋራ ዓላማቸው ለኾነችው ‘ኢትዮጵያ’፣በፍጹም ታማኝነትና  ሀገር ወዳድነት፣በጥምረት ሊሠሩ የሚችሉበትን፣ለዘመናት የሚዘልቅ ስትራተጂካዊ አሠራር መቀመር ይጠበቅበታል። 
  2. የቴሌኮም መሠረተልማት ግንባታ ፈቃድን፣ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፣ከመንግሥት ጋር ኾነው እንዲገነቡ ማድረግ። ለምሳሌ፣ኢትዮጵያ፣የራሷ ኢንተርናሽናል ሰብማሪን ኬብልየምትዘረጋበትን ዕድል፣ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች እንዲገቡበት ማገዝ፣ማበረታታትና መርዳት።
  3. ዲያስፖራውን፣አዋጪነቱ በማያጠራጥረው በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሳተፍ በመጋበዝ፣ መንግሥት፣የቴሌኮም ሴክተሩን፣ወደ ግል ይዞታ በማዘዋወር ያገኛል ተብሎ የሚታሰበውን የውጪ ምንዛሪ፣በቀላሉ እንዲያገኝ ማድረግ። በውጪ፣በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በሀገራቸው ኢኮኖሚክ ዕድገት፣ቀጥታ ተሳታፊ እንዲኾኑ ማድረጉ፣ኢትዮጵያን፣ከዲያስፖራው ሊገኝ የሚችሉ በርካታ ተዛማጅ ጥቅሞችን ማግኘት እንድትጀምር፣ማድረግ ያስችላታል። በሌላ በኩል፣የዲያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ዕድል ይከፈታል፤ ብሎም፣በዜግነታቸው ማግኘት የሚገባቸውን፣የሞራልም ኾነ የኢኮኖሚክ ጥቅም እንዲያገኙ፣ ማድረግ ያስችላል።
  4. በአብዛኛው፣ ከ70% በላይ፣በወጣትነት ዕድሜ ላይ ባሉ ሠራተኞች የተሞላውን፣የኢትዮቴሌኮም ሠራተኛ፣ከ5 እስከ 10 ከመቶ የሚደርስ፣የኩባንያቸውን የኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ድርሻ እንዲገዙ ወይም በስጦታ እንዲያገኙ በማድረግ፣መጪው ትውልድ፣ተስፋው የለመለመ፣ ሀገር ወዳድ፣በቴሌኮም ዘርፍ፣ከሀገር ውስጥ አልፎ ድንበር ተሻግሮ፣ትጉኽ ተወዳዳሪ ሠራተኛ እንዲኾን ማድረግ  ይቻላል።
  5. ኢትዮጵያ በአኹኑ ሰዓት፣አንድ ሦስተኛው ኢኮኖሚዋ(GDP)፣ብድር መኾኑ የታወቀ ኾኗል። እንደዚያም ኾኖ፣ሀገራችን  ጠንካራ የፖለቲካ አመራር ካገኘች፣ከዚህ ብድር አባዜ፣እጅግ በጣም አጭር በኾነ  ጊዜ ውስጥ  የምትወጣበት ዕድል፣ለመፍጠር ትችላለች። ይኽንንም ለማድረግ የምትችለው፣የራስዋን የሰው ኃይልና የኢኮኖሚክ አቅም በማሳደግ ላይ፣አተኩራ በመሥራት ብቻ ነው። በውጪ ኢንቨስትመንት ላይ፣ጥገኛ የኾነን የኢኮኖሚክ ዕድገት የምንመኝ ከኾነ፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ፣መላው ኢኮኖሚያችንን፣ፖለቲካውንም ጨምሮ፣ለውጪ ኃይሎች አስረክበን፣ቁጭ እንላለን። አባቶቻችን፣በደማቸው ያቆዩልንን፣የእምቢ ባይነት በራስ የመተማመን ብሔራዊ ሀብት እናጣለን።
  6. በመንግሥት እጅ የሚገኙትን ኢትዮ ቴሌኮምንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ፣ ሌሎችንም ትልልቅ ድርጅቶች የማናጅመንት ሥራ፣ከፖለቲካ ሹመትና  አጉዋጉል ጣልቃ ገብነት ተፅእኖ ነፃ በማውጣት፣ለቦታው ተመጣጣኝ አቅምና ልምድ ባላቸው ባለሞያዎች እንዲመሩ ማድረግ። ይኽን በማድረግ፣የተቋማቱን ዕድገትና ትርፋማነት በማረጋገጥ፣  የሀገሪቷን ኢኮኖሚና  ቢሮክራሲ፣ጠንካራ መሠረት ላይ እንዲወድቅ ማድረግ ይቻላል። ዐዲሱም ትውልድ፣በእነዚኽ ተቋማት ውስጥ፣በተገቢው መንገድ፣ሙያዊ ብቃቱን የሚያሳድግበትንና ልምድ የሚቀስምበትን ዕድል፣ማመቻቸት ይገባል። የግል ሴክተሩም፣አግባብና ሙያዊ ብቃት  ባለው ማናጅመንት ከሚመሩ፣ትልልቅ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በሚወጡ፣ከፍተኛ ልምድ በሚኖራቸው ባለሞያዎች፣አቅሙን ሊያጎለብትና የሥራ መስኩን፣ሊያስፋፋ ይችላል።

ምንጭ ፦ ባልደራስ ጋዜታ 1ኛ ዓመት ቁጥር 05 ጥር 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

Filed in: Amharic