>

የዓድዋ ጦርነትና የስለላ ሚና (ሀ ነው ፊደሌ)

የዓድዋ ጦርነትና የስለላ ሚና

ሀ ነው ፊደሌ

የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን ሊያስገብር ሲያስብ ብዙ ወጪ ሳያወጣና ብዙ ወታደሮቹን ለጦርነቱ ሳይገብር ለመጨረስ ነበር ያሰበው። ይህንንም እንዲያስብ ያደረገው በወቅቱ የነበረውን የአገራችንን ሁኔታ ጠንቅቆ በመገንዘቡ ነበር።
ለዚህም በተመራማሪነትና በሚሲዮናዊነት ያሰማራቸው ሰላዮቹ ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ ስለቀጠለው ሽኩቻና አለመግባባት በሰሜን በኩል በ”ሚሲዮናዊነት” ካባ ከተሸፈነው  ጁሴፔ ሳፔቶ ከተሰኘ ሰላይና ከሌሎች በአካባቢው ከሚገኙ “ሚሲዮናዊያን” መረጃን ሲያገኝ በመሐልና ደቡብ ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ኩማይሳና ጭፍሮቹ እንዲሁም ከነቼኪ እጅግ ብዙ መረጃን ሰብስቦ ነበር።
ኢጣሊያ መጀመሪያ አሰብን ቀጥሎም ምፅዋን በእጁ ካደረገ በኋላ፤ በስመ አገር ጎብኚና ተመራማሪ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መረጃ አቀባይ በሁሉም አቅጣጫ ስላሰማራ የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ “ከእኔ ወዲያ አዋቂ ላሳር …” እንዲል አድርጎት ነበር።
የጎጃም መስፍን ለነበሩት ለንጉሥ ተ/ሃይማኖት “ድልድይ ይሰራልዎታል” ተብሎ ከኢጣሊያ መንግሥት የተላከላቸው ሳሊምቤኒ የተሰኘው መሃንዲስ ከድልድይ ሥራው ባሻገር ለንጉሡ የቅርብ አማካሪያቸው ሆኖ ነበር። ንጉሥ ተ/ሃይማኖት ከዮሐንስ፣ ከምኒልክና ከሌሎች መሣፍንት ጋር ስለነበራቸው ጠብም ሆነ ወዳጅነት የመረጃ ምንጩ ሳሊምቤኒ ነበር።
ከንጉሥ ተ/ሃይማኖት ባሻገር የአጼ ዮሐንስ ቤተመንግሥትም በብዙ የታወቁ የኢጣሊያ “መልዕክተኞች” ተጎብኝቷል። ከእነዚህ መካከል የውጫሌ ውል ዋና ተዋናይ የነበረው ፔዮትር አንቶኔሊ አንዱ ሲሆን ከእሱ በተጨማሪም ቢያንኪ፣ ኔሪኪኒንና ትራቬርሲ ዋነኞቹ ነበሩ። ታዲያ ለእነዚህ መልዕክተኞች ስለ አጼ ዮሐንስ የዉስጥና የውጭ ፖለቲካ ያስጠናቸው የነበረው የንጉሡ መሐንዲስ የነበረው ጃኮሞ ናሬቲ ነበር።
ናሬቲ ከአጼ ዮሐንስ ጋር ከመገናኘቱ በፊት ከርታታ አናጢ ነበር። ንጉሡን ካገኘ በጏላ ግን ተሹሞ ተሸልሞ የቤተመንግሥቱ የአናጢዎችና ግንበኞች የበላይ ሹም ሆኖ በክብር ተቀምጦ ነበር። ነገር ግን በጥቁር ንጉሥ መታዘዝ ውርደት ነው ብሎ ያሰበው ናሬቲ የኢጣሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሲይዝ ሥልጣን ይሰጠኛል ብሎ በማሰቡ ያገኘውን መረጃ ሁሉ ለኢጣሊያ መንግሥት ሰላዮች ዘክዝኮ ይነግራቸው ነበር። ይህም ኢትዮጵያ በውስጧ የተረጋጋችና የተዳከመች ሀገር ናት እንዲሉ ያሳመናቸው ይመስላል።
ዳግማዊ ምኒልክና አንቶኔሊ…እንዴት ተገናኙ?
ኢጣሊያኖች የአሰብንና የምፅዋን ወደብ ከያዙ በኋላ ለአጤ ዮሐንስ አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች የሚገዙ ነጋዴዎች በኢጣሊያኖች በጣም በመጠራጠራቸውና በዓይነ ቁራኛ በመጠበቃቸው ምጽዋ ውስጥ ብዙ ችግር ይደርስባቸው ነበር። እስጢፋኖስ የተባለ ነጋዴ ከሃያ ሺ ጠገራ ብር በላይ የሚያወጡ ለዮሐንስ የተገዙ ዕቃዎችን ይዞ በምፅዋ ወደ መቀሌ ማለፍ ስለፈራ በዘይላ አድርጎ ወደ አዲስ አበባ ደረሰ፡፡ ይህንን የሚያዉቀዉ አንቶኔሊ እስጢፋኖስ ወደ ትግራይ ከመሻገሩ በፊት አስያዘዉና ለዮሐንስ የገዛቸውን እቃዎች በሙሉ ለሱ እንዲሸጥለት አስገደደው።
አጤ ዮሐንስንና ንጉሥ ምኒልክን ይበልጥ ለማቀያየምና ለማቆራረጥ አልሞና አቅዶ የነበረዉ አንቶኔሊ የአጤ ዮሐንስን ዕቃዎች በሙሉ ከኢጣሊያ ንጉስ የተላከ ገፀ በረከት በማስመሰል ለምኒልክና ለጣይቱ ሰጠ። በዚህም ግንኙነታቸዉ እየዳበረ በመምጣቱ ምኒሊክ በአንቶኔሊ ላይ እምነት አሳደሩ፡፡ ይህ እምነታቸዉ  በመጨረሻ ወደ ውጫሌው ውል ላይ አደረሳቸው።
አጤ ምኒልክ አንቶኔሊ የተጠቀመባቸውን ያህል የመሳሪያ ስጦታ እንዲያስመጣላቸው አድርገው ከተጠቀሙበት በኋላ ለክብራቸውና ላገራቸው ነፃነት ሲሉ የውጫሌን ውል ለመሰረዝ ወሰኑ።
ከውሉ መሰረዝ በኋላ አንቶኔሊ ወደ አገሩ ቢመለስም በአዲስ አበባ ብዙ የኢጣሊያ መንግሥት ወኪሎች ቀርተው ነበር። ከነዚህም ዉስጥ  አንደኛው ኮፑቺ የተባለው ወኪል ሲሆን ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ የኖረና የምኒልክን ሠራዊት ጥንካሬ በየጊዜው የሚገመግምና ምኒልክ ከሌሎች መሳፍንት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በመከታተል ብዙ ዘገባ የሚያስተላልፍ ነበር።
ከዚህም ባሻገር ‹‹ለእርቅና ለስምምነት የሚሆኑ ሃሳቦችን አምጥተናል›› በማለት እ.ኤ.አ በ1893 የገቡት ኮሎኔል ፒያኖና ዶክተር ትራቪርሲ ዋና ተልዕኮአቸው የምኒልክን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ለይቶ ማወቅ ነበር።
ኢጣሊያኖች ከምኒልክ ባሻገር ሌሎች መሳፍንቶችንና መኳንቶቻቸዉን የሚሰልሉና መረጃ የሚያቀብሉ ወኪሎች ነበሯቸዉ፡፡ በሐረር ፌልተርን፤ በወሎና በአውሳ አውራጃ ፔርሲኮና ረዳቱ የነበረው አብዱራህማን ቤን ዮሱፍ የተባለን ኢትዮጵያዊ፤ እንዲሁም በጎጃም ሳሊምቤኒን እና ሌሎችንም አሰማርተዉ መረጃ ሲሰበስቡ ነበር፡፡

የጥቁር ህዝብ ኩራት

ዓድዋ 125

የኢትዮጵያውያን ድል

Filed in: Amharic