>

የእስረኞች የርሀብ አድማ ከህግ አንጻር...?!? (የህግ ባለሙያና ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ)

የእስረኞች የርሀብ አድማ ከህግ አንጻር…?!?

የህግ ባለሙያና ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳ


 

*  የፖለቲካ ግለት ለመጨመር የሚደረግ አድማ ተቀባይነት የለውም
· መንግስት በአንድ እስረኛ ጤንነትና ህይወት ላይ ሃላፊነት አለበት
· በረሃብ አድማ ምክንያት ክስን ማቋረጥ የህግ ድጋፍ የለውም

*    ብዙ ጊዜ እስረኞች የረሃብ አድማ አደረጉ ሲባል ይሰማል፡፡ ከሰሞኑም እነ አቶ ጃዋር መሃመድ የረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው ተነግሯል፡፡ ለመሆኑ የረሃብ አድማ በእስር ቤት ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል? የረሃብ አድማ ለእስረኞች ምን ይፈይድላቸዋል? መንግስት በረሃብ አድማ ወቅት ምን ሃላፊነት አለበት? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የህግ ባለሙያና ጠበቃ ወንድሙ ኢብሳን በዚህ ዙሪያ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡

በፍ/ቤት ጉዳዩን የሚከታተል የህግ ታራሚ የረሃብ አድማ ሲያደርግ የሃገሪቱ ህጎች በምን አግባብ ያስተናግዱታል?
ማንኛውም የህግ ታራሚ ወይም በህግ ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ያለን ሰው ህግ የሚያየው ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ነው፡፡ ሚዛናዊነት ማለትም ጉዳዩ ዋስትና የሚያሰጥ ሆኖ ያለ አግባብ ከተከለከለ፣ በቀጠሮ ላይ ያለ እስረኛ ከሆነና የሚደርስበት ህግን የጣሰ አያያዝ ካለ ወይም በከሳሹ አካል ቀጠሮ ያለ አግባብም ሲጓተት… እነዚህ ነገሮች እንዲስተካከሉ በሚል እስረኛው የምግብ አድማ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የራሱን የእስር ቤት የውስጥ ጉዳይ ትቶ ወጪ ባለ ጉዳይ አድማ ማድረግ ነገሩ በሚዛኑ እንዲታይ አያደርግም። አንድ ታሳሪ ለሌላ ታሳሪ ምስክር ይሆናል እንጂ ለሱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ለመሆን የሚያደርገው የረሃብ አድማ የህግ ድጋፍ የለውም። በሚዛን ሊታይ የሚችልም አይሆንም። እስረኞች በእስር ቤት ባጋጠማቸው የአያያዝ ጉዳይ፣ አያያዞች ይስተካከል ብለው ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መንግስት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ሲፈልጉ የረሃብ አድማዎች ሊደረጉ ይችላሉ። አንዳንዱ ግን ለረሃብ አድማ ምክንያት የሚያደርጉት ከህግ የሚጣረስ  አቻቻይ ሁኔታዎችን የማይፈጥር ይሆናል፡፡
ለምሳሌ?
እስረኛ ሆኖ ውጪ በሚደረጉ ነገሮች ላይ ለሚነሳ ጥያቄ አድማ ማድረግ ተቀባይነት የለውም፡፡ በውጭ ያለን የፖለቲካ ግለት ለመጨመር የሚደረግ አድማ ተቀባይነት የለውም፡፡ እንዲህ ያለው አድማ በአስገዳጅ ሁኔታ እንዲፈርስ ወይም እንዲቀር ነው የሚደረገው፡፡ የረሃብ አድማ የተደረገው በእስር ቤት ውስጥ ያለን አያያዝ አስታኮ ካልሆነና በውጭ ሌሎች ችግሮችን ለመቀስቀስ የተደረገ ከሆነ እንዲቀር ነው የሚደረገው፡፡ በእስር ቤት አያያዝና በፍትህ ሂደት ላይ ባለ ቅሬታ የሚደረግ አድማ በመንግስትም በአለማቀፍ ሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም ትኩረት ይሰጠዋል። መንግስት ምላሽ እንዲሰጥም ይገደዳል፡፡ በዚህ መሃል ግን መንግስት የረሃብ አድማ ለሚያደርጉ ሰዎች ተገቢውን የጤና ክትትል የማድረግ ግዴታ አለበት፡፡ ምክንያቱም እስረኛ በማንኛውም መልኩ ራሱን ማጥፋት አይችልም፡፡ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ የሚያደርግ ሰው በህግ ይጠየቃል፡፡
የረሃብ አድማውም ራስን የማጥፋት አዝማሚያ ካለው የረሃብ አድማ አድራጊው ተገቢው ህክምና ተሰጥቶት በህግ ተጠያቂ ሊደረግ ይችላል፡፡ እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ከውጭ ያለው ፖሊሲ ይስተካከል ተብሎ የሚደረግ አድማ፣ እስረኛውን ከመጉዳት ባሻገር የህግም ሆነ የመርህ ድጋፍ የለውም፡፡
አድማው እንዲቀር ወይም እንዲፈርስ የሚደረግባቸው የህግ አግባቦች ምንድን ናቸው?
በመንግስት እጅ ባለ እስረኛ ላይ ለሚደርሰው ሁሉ መንግስት ሃላፊነት ወይም ተጠያቂነት አለበት፡፡ በምግብ አድማም ቢሞት መንግስት ሃላፊነቱን አልተወጣም ነው የሚባለው፤ ስለዚህ ተጠያቂ ይሆናል። በህክምና እጦት ከሞተም መንግስት መጠየቁ አይቀርም። ስለዚህ መንግስት ራሱን ከተጠያቂነት ለማዳን በአድማ አድራጊው ላይ አስገዳጅ ሁኔታዎችን ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ ህክምና እንዲያገኙ ያስገድዳል፡፡ ሃኪሙን መምረጥ የሚችለው ደግሞ መንግስት እንጂ እስረኛው አይደለም፡፡
ሃኪሙንም ሆነ  ሆስፒታሉን እኛ ነን መምረጥ ያለብን ሲባል ይሰማል፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡ እስረኛው የሚመርጣቸው ሃኪሞች ከእስረኛው ጋር ተመሳጥረው ራሱን ለማጥፋት በሚያደርገው ጥረት ቢያግዙትስ? በመንግስት ላይ ሆን ብለው ጉዳት ለማድረግ እስረኛው ለፈለገው አላማ ተባባሪ በመሆን ሰዎቹ ላይ ጉዳት ቢያደርሱስ? መንግስት በአንድ እስረኛ ጤንነትና ህይወት ላይ ሃላፊነት አለበት። ስለዚህ መታከም ያለባቸው እነሱ በመረጡት ሳይሆን መንግስት በመረጠው ብቻ ነው መሆን ያለበት፡፡ መንግስት አድማው እንዲፈርስ ከሚያደርግባቸው ጥረቶች አንዱ፣ አድማ አድራጊዎቹን በሃገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች በኩል ማስጠየቅ ነው፡፡
በዚህ አይነት መንገድ ከህግ ማምለጥ እንደማይቻል በሽማግሌዎች በኩል ማስረዳትና የሚጠየቁበት ጉዳይ ከፖለቲካ የፀዳ መሆኑን መንግስት ማረጋገጥ አለበት፡፡ ከዚህ ባለፈ ለእስረኛ ስለትና ራስን የማጥፊያ መንገዶች ይዞ መገኘት እንደማይፈቀድ ሁሉ፣ በረሃብ ራስን ለማጥፋት የሚደረግ ሙከራም ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ ራሱ በመረጣቸው ሃኪሞች ተገቢውን ህክምና እንዲከታተሉ ማድረግ አለበት። እኔ ለምሳሌ ለፕ/ር መረራ ጉዲናና በቀለ ገርባ ጠበቃ በነበርኩበት ጊዜ ፕ/ር መረራ የረሃብ አድማን አይደግፉም ነበር፤ በደንብ ነው የሚመገቡት፡፡ ምክንያቱም መንግስት እሳቸውን ሲያስር የህግ እስረኛ ብሎ ነው፤ እሳቸው ግን የፖለቲካ እስረኛ ነኝ ብለው ነው የሚያምኑት፡፡
አንድ ሰው የፖለቲካ እስረኛ ነኝ ካለ፣ ታዲያ ማንን ለመጉዳት ብሎ ነው የረሃብ አድማ የሚያደርገው? መንግስትንማ በዚህ ሊጎዳ ሳይሆን ምናልባት ሊጠቅም ነው የሚችለው፡፡ ገና ዲሞክራሲ ባልዳበረበት ሃገር እንዲህ አይነት አድማ ብዙም አይጠቅምም፡፡
አንድ እስረኛ የረሃብ አድማ የማድረግ መብቱ በህግ የተደገፈ ነው?
የረሃብ አድማ ሲያደርግ ደረጃ አለው። አንደኛ ምክንያቱ ግልጽ መሆን አለበት። አያያዜ ይስተካከል ብሎ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ሰውየው እስሬ የፖለቲካ ነው ብሎ ካመነ የረሃብ አድማ ያደርጋል፤ ነገር ግን ይሄን ከማድረጉ በፊት በግልጽ በፅሁፍ ከእነ ምክንያቱ ለመንግስት ወይም ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አለበት። ምክንያቱም የረሃብ አድማው ከአቅም በላይ ሆኖ ለህይወት የሚያሰጋ ከሆነ፣ መንግስት የዚያን ሰው ህይወት የመጠበቅ ግዴታ ስላለበት አድማው እንዳይካሄድ ይሞክራል፤ ከተካሄደም የህክምና ክትትል እንዲደረግ ሃኪሞች ይመድባል፡፡ በስሜት ተነሳስቶ ማድረግ ግን ህግ አይደግፈውም። መንግስትም አይቀበለውም፡፡ ራስን የማጥፋት ሙከራ በህግ ተቀባይነት የለውም፡፡ ለሌሎች እስረኞች በር ከፋች ስለሚሆን አይፈቀድም፡፡
በዚህ የረሃብ አድማ መሃል የጤና እክል ወይም ሞት ቢያጋጥም የመንግስት ሃላፊነት ምንድን ነው?
አንደኛው አድማው በስሜት ሳይሆን በግልጽ እስረኛው እያደረገ ስለመሆኑ መንግስት ማረጋገጥ አለበት፡፡ ካረጋገጠ በኋላም የጤና እክል እንዳያጋጥም የህክምና ባለሙያ ይመድባል፡፡ ይሄ ህክምና እየተደረገለት ህይወቱ ካለፈ ግን እንደ ተፈጥሮ ሞት ይቆጠራል፡፡ ዋናው በረሃብ እንዳይሞት መንግስት በህክምና የተቻለውን ሁሉ ማድረግ አለበት፡፡ ቫይታሚኖች፣ ውሃ፣ መድሃኒት መስጠት ከህክምናዎቹ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ነገር ግን የራሱ ጉዳይ ቢርበው ብሎ ዝም ካለ ግን መንግስት ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡
አንድ በቀጠሮ ላይ ያለ ተጠርጣሪ የረሃብ አድማ ላይ ሆኖ አቅሙ ቢዳከምና ፍ/ቤት መቅረብ ባይችል ምን ይደረጋል?
ፍ/ቤት በመርህ ደረጃ በህግ የሚጠይቃቸው ሰዎች በጤንነት ላይ ያሉ ሰዎችን ነው፡፡ የእነዚህ ሰዎች ጤንነት ከተጓደለ ፍ/ቤቱ የአያያዛቸውን ጉዳይ በተመለከተ ለመንግስት ማሳሰቢያ ይሰጣል። ከዚያ ባለፈ ሰዎቹ አቅማቸው ከተዳከመ የግድ በቃሬዛ ወደ ፍ/ቤት ይምጡ አይልም፡፡ እንደነ ሆስኒ ሙባረክ ሆን ብለው አልመጣም ካሉ ግን በቃሬዛም ቢሆን ፍ/ቤት እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡
በዚያው ልክ አውቆ በፖለቲካ አላማ ፍ/ቤት ለማወክ፣ ብይን እንዳይሰጥ፣ ምስክር እንዳይሰጥ፣ ቃል ላለመስጠት ሆን ብሎ ጉዳዩን ለማጓተት በሚደረግ ጥረት ላይ ግን ልክ እንደ ሆስኒ ሙባረክ በቃሬዛም ቢሆን ወደ ፍ/ቤት እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ በዚህ አድማ ምክንያት ግን ክስ ማቋረጥ፣ ክስ ማሳነስ የህግ ድጋፍ የለውም፤ ምክንያቱም ለሌሎች መጥፎ አርአያ ይሆናልና፡፡

Filed in: Amharic