>

የፖለቲካ ድርጅቶች ሩጫ...!!! (ሄቨን ዮሀንስ)

የፖለቲካ ድርጅቶች ሩጫ…!!!

ሄቨን ዮሀንስ

ፖለቲከኞች እስካሁን የነበረውን የወያኔ ፕሮፓጋንዳ እና መንገድ መከተል የለባቸውም፡፡ ህውሃትንም ከዚህ በሓላ ለማስለቀሻ መጠቀም አያስፈልግም የተሻለ ነገር ሰርተው መገኘት አለባቸው፡፡ ትናንት ህውሃት ሰብአዊነት፣ እኩልነትና ነፃነት እያለች በአንፃሩ ደግሞ ግፍን ስሰራ በገሃድ ታይታለች፡፡ እኩልነትን፣ ነጻነትን እና ፍትህን ማስተጋባት ያለበት ማነው? ከላይ ሆኖ የታችኞቹን ነፃ ናችሁ ማለትን ምን አመጣው? የእኩልነት ውዝግብ የተበደሉት በበዳዮቻቸው ላይ የሚመሰጥሩበት ለምን ሆነ? አንድ ድሃ እኩልነቱንና ነፃነቱን እየተናገረ በማን መበለጡን ለማወቅ ይቸገራል፡፡ ምናልባት ድሆች በሎሌነታቸው እየፈነጠዙ ስለአስቸገርን ጌቶች ለእኩልነት ሰገዱ ማለት ይሆን?… ነገር ግን ድሆች ጥንትም ሆነ ዛሬ እርስ በእርሳችን ነፃና እኩል ነን፡፡ እንዲሁም ድሆች ከጌቶቻቸው ጋር እኩልና ነፃ ሆነው አያውቁም፡፡
የሌለ ሁኔታ የአለውን ሁኔታ ያድበዘብዝ ዘንድ እኝህ ቃላት በአለም ላይ ተናኙ ፍትህ እኩልነት ወዘተ… ጌቶች እነሱ መውረድ የማይችሉትንና የማይፈልጉትን በቁልቁለት የተከበበ የሕይወት/የኑሮ/ ተራራ አምባ ሞጭጨው ይዘው የድሆችን ልብ በዳገት ለማፍሰስ ከኛ ጋር እኩል ናቸው እያሉ ይመሰቅላሉ፡፡ አይ ህውሃቶች የድሃ እርግማን ጭምር ነው ትቢያ ያደረጋቸው፡፡ ከእነሱ የማይማር ፖለቲከኛ ካለ  እሱ ያሳዝናል፡፡
ድሃ ራሱን በራሱ እኩልና ነፃ አደርጎ ለመኖር የጌቶችን በቅንጦት የተጨማለቀ የህይወት አምባ አርዕያነት አይፈልግም፡፡ ላዩ በረዶ ነው፡፡ ስንፍናን፣ ነፈዝነትን፣ የበላይነትን… ከሆነ በቀር የሥራ መንፈስና ዋጋ የሌለበትን ተራራ ድሆች አንፈልግላቸውም። ስለዚህ ፖለቲከኞቻችን ጠቢብ ሊሆኑ ይገባል፡፡
ፓለቲከኞቻችን መሻሻል ከፈለጉ በድርጅቶቻቸውና በሕዝብ መካከል ልዩነቶች መኖራቸውን ይወቁት፡፡ የድርጅቶች የስልጣን ሽኩቻ ለሕዝብ ሰላማዊ አስተሳሰብና ኑሮ የመንፈስ ውጋት መሆኑን ይወቁት፡፡ ማንኛውም የድርጅት አባል በሕዝብ የመምረጥ መብት ውስጥ አይግባ- እሱ ድርጅቱን መምረጡ ይብቃው፡፡ ስለዚህም በተቀናቃኞች ፖለቲካ ያልተደራጀው ህዝብ አስተዳዳሪዎች በፈቃዱ ይመርጥ ዘንድ መብቱን ለቀቅ ያድርጉለት፡፡
ይህን የምለው መጭው ምርጫ ስለሆነ ከወዲሁ መገፋፋት እያየን ነው። አንዳንዶችማ ይባስ ብለው እገሌ ከተነካ አገር ትፈርሳለችም የሚሉ አልጠፉም፤ ማስፈራሪያና ዛቻ ለህውሃትም አልጠቀምም። ከመገፋፋት ይልቅ የህዝቡን ስሜት ማወቅ ላይ ትኩረት እንዲያርጉ ለማሳሰብ ወደድሁ፡፡ ይህ ካልሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ሩጫ ደጋፊ ለማግኘት እንጂ አባል ለመመልመል አይሆንም፡፡ ይህ ከሆነ ለሕዝብ መቆምና በሕዝብ ስም መቆም ይለያያሉ ወዘተ… ሁሉም ሆኖ የመጨረሻው መዳረሻ የጌቶች አምባ መሸርሸር /ማፍጋትና ማብቃት/ የድሆች መደላደል /ማደግና መመንደግ/ መሆኑ አይቀርም፡፡ እናም እኩልነት ያኔም ይታወሳል  ግና ከዛሬው በተለየ በተገለበጠ አኳኋን ይሆናል፡፡ ለአባቱ ባለጋራ ጥብቅና የቆመ ነገረ ፈጅ ተሟግቶ አያሸንፍም፡፡ ገባር ምሁሮችን ተልካሻ የጦር አለቆች ለአገርና ለወገን መሆን አይችሉም፡፡ ስለዚህም በለስ የሰጠው ተዋጊም ሆነ አዋጊ ሁሉ ለአገር ጠባቂነት መመደብ የለበትም፡፡ የገባር ምሁራን አስፈላጊነት ለአሸሙር፣ ለዘለፋ፣ ለቅስቀሳና ለተሸናፊነት አርአያነት ብቻ ነው፡፡
Filed in: Amharic