>

በእነ አቶ ስብሃት ነጋና አቶ ዓባይ ወልዱ የወንጀል ተሳትፎ ዙሪያ ሰፊ ክርክር ተደረገ (ታምሩ ጽጌ)

በእነ አቶ ስብሃት ነጋና አቶ ዓባይ ወልዱ የወንጀል ተሳትፎ ዙሪያ ሰፊ ክርክር ተደረገ

ታምሩ ጽጌ

ፍርድ ቤት ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ፈቀደ
 
አቶ ስብሃት ነጋ በግል ሐኪማቸው እንዲታከሙ ፍርድ ቤትን ጠየቁ!
 
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሙከራ፣ በአገር ክህደት፣ ከወሓትና ኦነግ ሽኔ ከተባሉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ወንጀሎች በመፈጸም ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት እነ አቶ ስብሃት ነጋና እነ አቶ ዓባይ ወልዱ (18 ተጠርጣሪዎች) የእያንዳንዳቸው የወንጀል ተሳትፎን በሚመለከት በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቡድንና የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ሰፊ ክርክር አደረጉ፡፡
ክርክሩ የተደረገው በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ መርማሪ ቡድኑ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በተሰጠው 14 የምርመራ ቀናት ውስጥ የሠራውን የምርመራ ግኝትና ቀሪ የምርመራ ሥራዎች ለፍርድ ቤቱ ከተናገረ በኋላ ነው፡፡
መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው 14 የምርመራ ቀናት ውስጥ የ113 የምስክሮችን ቃል መቐለ በሚገኘው የምርመራ ቡድን አማካይነት መቀበሉንና የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡ ቡድኑ በተጠርሪዎች ላይ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን ሰብስቦ የመለየት ሥራ እየሠራና የተለያዩ የመሠረተ ልማት ተቋማት አገልግሎት ሊያገኙት ይገባ በነበረው ጥቅም ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በባለሙያ አስለይቶ ማስመጣቱንም መርማሪ ቡድኑ አክሏል፡፡
ከተፈጸመው የወንጀል ስፋትና ውስብስብነት አኳያ ተጨማሪ የምስክሮችን ቃል መቀበልና ማስረጃ መሰብሰብ እንደሚቀረው፣ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የቴክኒክ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ እንደሚቀረው፣ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውን ማስረጃ መቀሌ በምርመራ ላይ ያለው ቡድን እያሰባሰበ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢወጡ የሰነድ ማስረጃዎች ሊያጠፉ፣ ሊያስጠፉ፣ ምስክሮችን ሊያስፈራሩና ሊደልሉ ስለሚችሉ እንዲሁም ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመገናኘት ተጨማሪ ወንጀል ሊፈጽሙ ስለሚችሉ ምርመራውን እስከሚያጠናቅቅ ድረስ የዋስትና መብታቸው እንዳይፈቀድላቸው ጠይቆ የሠራውን የምርመራ ሒደት ለፍርድ ቤቱ አሰምቶ አጠናቋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ የሠራውንና የቀረውን የምርመራ ሥራ ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ እንደጨረሰ በሦስት ጠበቆች የተወከሉት ተጠርጣሪዎች አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ፍርድ ቤቱ ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. መርማሪ ቡድኑ የእያንዳንዱን ተርጣሪ የወንጀል ተሳትፎ ለይቶ እንዲያቀርብ የተሰጠውን ትዕዛዝ ተግባራዊ አላደረገም፡፡ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በሥነ ሥርዓት ሕጉ እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌዎች ተጠርጣሪው ስለተጠረጠረበት የወንጀል ድርጊት በግልጽ ቋንቋ ሊነገረው እንደሚገባ ከመደንገጉ አንፃር፣ የደንበኞቻቸው የወንጀል ተሳትፎ እንኳን ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ይቅርና ባይታዘዝም መርማሪ ቡድኑ ሊነግራቸው ይገባ ነበር፡፡ መርማሪ ቡድኑ በጥቅል ስላቀረበው የትኛው ምርመራ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቀረው፣ የትኛው የምርመር ዓይነት እንደተጠናቀቀ ለመለየት በሚያስችል መልኩ ምርመራውን ስላልሠራ ለመከራከርም ሆነ ለደንበኞቻቸው የሕግ ድጋፍ ለመስጠት እንደተቸገሩ ጠበቆቹ ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ ሕርይቲ ምኅረተአብ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መሆናቸውን ጠቁመው እሳቸው ስለተጠረጠሩበት የወንጀል ተሳትፎ ምን እንደሆነና ምን እንደተገኘባቸው ከውንጀላ (Allegation) ባለፈ የተገለጸላቸው ነገር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ዋስትና ለመፍቀድም ሆነ ለመከልከል የሚችለው የትኛው ተጠርጣሪ በየትኛው የወንጀል ዓይነት እንደተሳተፈና ያደረገው ድርጊት ተለይቶ ሲቀርብለት እንጂ፣ በደፈና በቀረበ የምርመራ ሥራ ላይ ተመሥርቶ መሆን እንደሌለበት አክለዋል፡፡ አንዳንዶቹ ተጠርጣሪዎች የፖለቲካ ሥራ ኃላፊዎች እንደነበሩ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ድርጅቶች ይመሩ የነበሩ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት በዝርዝር ሳይቀርብ በጥርጣሬ ብቻ ዋስትና ሊከላከል እንደማይገባና የሕግ መሠረት እንደሌለውም አስረድተዋል፡፡
የምርመራ ቡድን ተደራጅቶ መቀሌ እንደተላከና እየመረመረ የምርመራ ውጤቱን እየላከ መሆኑን በሚመለከትም ተጠርጣሪዎቹ እንደተናገሩት፣ ምርመራው በትክክል እየተካሄደ መሆን አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ በየቀጠሮው የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ እየመለከተ ካልሆነ በስተቀር፣ መቆጣጠር እንደማይቻልና ምርመራውም ማለቂያ ጊዜ እንደማይኖረው ያላቸውን ሥጋት አስረድተዋል፡፡ የምርመራ መዝገቡ ቀርቦ፣ ምርመራው ሕግን በተከተለ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑንና አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ እያየ ትዕዛዝ የሚሰጥ ካልሆነ፣ ጠበቆቹ ተጨባጭ የሆነ ምላሽ ለመስጠት እንደሚቸገሩም ጠቁመዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ቀደም ባለው ችሎት ላይ ካቀረበው የምርመራ ሒደት የተለየ የምርመራ ሥራ ይዞ እንዳልቀረበም አክለዋል፡፡ ደንበኞቻቸው የተጠረጠሩበት በቂ ምክንያት ካልታወቀና ዝም ተብሎ የምርመራው ውጤት በጥቅሉ እየቀረበ ከቀጠለ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከጥፋተኝነት በፊት ለእስር እንደሚዳረጉና ይህ ደግሞ በየትኛውም የሕግ ሒደት ያልተፈቀደ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ዕልባት ሊሰጥበት እንደሚገባም ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድን መቐለ፣ ባለጉዳይ ደግሞ አዲስ አበባ ሆኖ ከቀጠለ፣ የጊዜ ቀጠሮው እስከ ክስ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ እውነተኛ የምርመራ ቡድን በመቀሌ ስለመቋቋሙም ጥርጣሬ እንዳላቸውም አክለዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ምስክሮቹ  ማን በማን ላይ እንደመሰከረና በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ የቀረውን ምስክር ማቅረብ እንዳለበት ተናግረው፣ የምርመራ ሒደቱ መቐለ ካለው የምርመራ ቡድን ምላሽ እየተጠበቀ የሚቀጥል ከሆነ ማለቂያ እንደማይኖረውም አስረድተዋል፡፡ ከጥቅምት  25 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የታሰሩ ተጠርጣሪዎች እንዳሉ ጠቁመው፣ በአዋጅ ቁጥር 562/2001 ድንጋጌ እንኳን ከአራት ወራት በላይ ጊዜ ቀጠሮ እንደማይፈቀድ በማስታወስ፣ ለመርማሪ ቡድኑ የተሰጠው ጊዜ በቂ መሆኑን በማንሳት ተከራክረዋል፡፡ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ ወ/ሮ ሕርይቲ ምህረተአብና አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ በጡረታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ‹‹ምክር ሰጥተዋል›› በሚል መጠርጠራቸውንና ለዚህም የሰነድና የቪዲዮ ማስረጃ እንዳለው መግለጹን ጠቁመው፣ ደንበኞቻቸው የሰጡትን ምክር ዓይነት ስለማያውቁት እንጂ፣ ተጠርጣሪዎቹ እንደ አንድ ግለሰብ የመሰላቸውን አስተያየት መስጠት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በዋስ ቢለቀቁ ምስክሮችን እንደሚያስፈራሩ፣ እንደሚደልሉ፣ ሰነድ እንደሚያሸሹና እንደሚያስጠፉ መርማሪ ቡድኑ ገልፆ ዋስትና መቃወሙን በሚመለከት ባቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ እንዳስረዱት፣ ከኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝና ካለው ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ መርማሪ ቡድኑ ያለውን ለመፈጸም እንደማይፈቅድና ፍርድ ቤቱም እንደሚገነዘበው ጠቁመው፣ ዋስትና ለማስከልከል በቂ ምክንያት እንዳልሆነም ተከራክረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ሌላው ያቀረቡት ክርክርና አቤቱታ ከመብት ጋር የተገናኘ ሲሆን፣ አቶ ስብሃት በከፍተኛ ሁኔታ መታመማቸውን ገልጸው፣ የግል ሐኪማቸው አዲስ ሕይወት ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ በመሆናቸውና በግል ሐኪማቸው የመታከምም መብት ስላላቸው ተፈቅዶላቸው እንዲታከሙ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡
አቶ ተክለወይኒ አሰፋ የተባሉት ተጠርጣሪ ደግሞ ባለቤታቸው እናታቸው አርፈው ሐዘን ላይ መሆናቸውን ተናግረው፣ ነገር ግን ከዕድር የተሰጣቸው 10,000 ብርና ከጡረታ የተቀበሉት 600 ብር እንደተወሰደባቸው፣ የግል ቤታቸው ካርታ እንደተወሰደባቸውና የተማሪ ልጃቸው የባንክ አካውንት ስለታገደ ችግር ላይ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡
ሌላዋ ተጠርጣሪ ወ/ሮ ሕርይቲ ምሕረተአብ ጡረታ ሲወጡ፣ በተቀመጠው ሕግ መሠረት መንግሥት የሰጣቸው ልዩ ጥቅም (Privilege) ማለትም የመንግሥት ቤት፣ ጠባቂዎች (Security) እንደነበር አስታውሰው፣ እሳቸው ከታሰሩ በኋላ ግን ጠባቂዎቻቸው መነሳታቸውንና ቤታቸውም መታሸጉን ገልጸዋል፡፡ ንብረቶቻቸውና ልብሶቻቸው ላይ ስለታሸገባቸው ልብሳቸውን እንኳን እንዲያወጡ እንዲፈቀድላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ቤቱም ተሰብሮ መዘረፉንም አሳውቀዋል፡፡ ‹‹በሕግ የተፈቀደና የመንግሥት ቤት እንዴት እንደዚህ ይደረጋል?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
አቶ ገብረመድኅን ተወልደ የተባሉት ተጠርጣሪ ደግሞ ተራ ግለሰብ መሆናቸውን ጠቁመው፣ የተጠረሩበት ወንጀል የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም መሆኑን ገልጸው፣ ተገቢ እንዳልሆነና ከፍተኛ ደረጃ ባላቸው አካላት (ግለሰቦች) እንጂ በእሳቸው  ሊሆን እንደማይችል ተናግረው፣ መርማሪው ማስረጃ ካለው ተሳትፏቸው ተለይቶ ፍርድ ቤቱ ሊመለከትላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ይህ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(4) እና በዓለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ድንጋጌም በአንቀጽ 9(4) ይህንኑ ስለሚያረጋግጥ ተግባራዊ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል፡፡ በአጠቃላይ የተሰጠው የምርመራ ጊዜ በቂ መሆኑን ጠቁመው፣ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው ጠበቆቹ ጠይቀዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ እንዳብራራው፣ የእያንዳንዱን ተጠርጣሪ የወንጀል ድርሻ በሚመለከት ጥር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡን አስታውሶ፣ የካቲት 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ያቀረበው ሪፖርት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የሠራውን ብቻ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዕለቱ ባቀረበው የምርመራ ውጤት የጠቀሰው የተፈጸመው ወንጀል አንድ ዓይነት መሆኑንና በቡድን የተፈጸመ በመሆኑ በጋራ የተደረገ የምርመራ ውጤት መሆኑንም አክሏል፡፡ የምርመራ ሒደትን በሚመለከትም ዋና የምርመራ ማዕከሉ አዲስ አበባ መሆኑን ጠቁሞ፣ በመቐለ ያለው የምርመራ ቡድን የሚሠራውን እየከታተለና የምርመራ ሒደቱንም በአግባቡ እየመራ ከመሆኑ አንፃር፣ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን አስቀርቦ መመልከት እንደሚችል በመግለጽ፣ የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ግን በግምት ያቀረቡት መከራከሪያ ሐሳብ ተገቢ አለመሆኑን ተናግሯል፡፡ የቴክኒክ ምርመራ ሥራንም ጎን ለጎን እየሠራ መሆኑንና በእያንዳንዱ ተቋም ላይ የተሠራውን የምርመራ ውጤት ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዙንም አስታውቋል፡፡ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ መርማሪዎችን በማሰማራት እየተሠራ መሆኑንም አክሏል፡፡ ወንጀሉ አገራዊ በመሆኑ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንና የተጠርጣሪ ጠበቆች አቅልለው ማየት እንደሌለባቸውም ተናግሯል፡፡
አቶ ተክለወይኒ ባለቤታቸው ከዕድር ስለተሰጣቸው የዕዝንና የጡረታ ገንዘብ በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ፣ በብርበራ ወቅት የተገኘና በኤግዚቢት መያዙን አስረድቷል፡፡ አቶ ገብረ መድኅንን በሚመለከትም፣ ፕሮግራም ይዘው ማን ምን እንደሚያደርግ ሲሠሩ እንደነበር፣ ወታደራዊ ተቋም ለመፍጠርና መከላከያን ለመመከት ሲያዋቅሩ እንደነበር ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
የአቶ ስብሃትን ሕክምና በሚመለከትም ፖሊስ በቂ የሕክምና ክሊኒኮችና ሪፈራል ሆስፒታል እንዳለው በማስረዳት፣ በግል ለማሳከም እሳቸው ከነበራቸው ከፍተኛ ኃላፊነት አኳያና ከፀጥታ አንፃር ጥቃት ሊደርስባቸው ስለሚችል እንደሚቸገር አስረድቷል፡፡ በአጠቃላይ የምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረውና ምርመራ እንዳልጨረሰ አስረድቶ፣ ምርመራውን ሲያጠናቅቅ ‹‹ዋስትና ይፈቅዳል ወይም አይፈቅድም?›› የሚለውን ማየት እንደሚቻል ገልጿል፡፡
አቶ ስብሃት በድጋሚ በጠበቆቻቸው እንደተከራከሩት፣ በግል ሐኪማቸው እንዲታከሙ የጠየቁት የእሳቸውን ሕመም የሚያውቁ ሐኪም አዲስ ሕይወት ሐኪም ቤት ዶ/ር እንዳሏቸውና በሕመማቸው ዙሪያም ስፔሻላይዝ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ሪፈራል ሐኪም ቤት ስላለ ብቻ ሁሉንም ዓይነት ሕመም የሚያክሙ ስፔሻሊስቶች አሉ ማለት እንዳልሆነ ተናግረው በሕግ የተፈቀደ መብት በመሆኑ በግል ሐኪማቸው እንዲታከሙ በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡
መርማሪ ቡድን በእነ አቶ ዓባይ ወልዱ (ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች) የምርመራ መዝገብና በእነ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሒም (ሁለት ተጠርጣሪዎች) የምርመራ መዝገብ ያቀረበውን የምርመራ ሪፖርት በእነ አቶ ስብሃት የምርመራ መዝገብ ካቀረበው የምርመራ ሪፖርት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አስረድቶ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ጠበቆቹ ባቀረቡት ክርክር፣ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ መርማሪ ቡድኑ ‹‹ተመሳሳይ ነው›› እያለ ማለፉ ተገቢ እንዳልሆነና ለመጠርጠርም በቂ ምክንያት ስለመኖሩ አለማስረዳቱን ተናግረው፣ ረዳኢ በርሄ (ዶ/ር) የዩኒቨርሲቲ መምህር እንደነበሩና ወደ ክልሉ ዋና ኦዲተር ጽሕፈት ቤት ተዛውረው የቁጥጥር ሥራ ይሠሩ እንደነበር በማስረዳት፣ አሁን መርማሪ ቡድኑ ካቀረበው የምርመራ መነሻ ጥርጣሬ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ለማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ የምርመራ ግኝቱን ገና እየለየ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ መግለጹንና ዋስትና እየተቃወመ ያለው ግምትን መሠረት አድርጎ መሆኑን አስረድተው፣ ይኼ ደግሞ የሕግ መሠረት የሌለው አካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጥርጣሬው በቡድን ከሆነና በዚያው የሚቀጥል ከሆነ የፖለቲካ ጉዳይ መሆኑን ተናግረው፣ ፍርድ ቤት ማየት ያለበት በሕገመንግሥቱ አንቀጽ (37) ፍትሕ ከማግኘት መብት አንፃር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በሕግ አግባብ የቀረበ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ ባለመሆኑ፣ የሕግ ዕገዛ ለማድረግ ስለሚቸገሩና ወንጀል በባህሪው ግላዊ በመሆኑ ደምድሞ ካቀረበ ዳኝነት የሚባል ነገር እንደሌለም ተናግረዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ በሰጠው ምላሽ እንዳስረዳው፣ የእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ሥራና የሥራ ተቋም የተለያየ ስለመሆኑ መጠቀሱን አስታውሶ በሰጠው ምላሽ፣ የእያንዳንዳቸው ተጠርጣሪዎች የሥራ ቦታና ሥራ የተለያየ ቦታ ቢሆንም የተጠረጠሩበትን ወንጀል የተፈጸመው ግን በቡድን መሆኑን ገልጿል፡፡ ይኼም ያቀረበውን የምርመራ ውጤት ሕግ የጣሰ እንደማያደርገው አክሏል፡፡ ወንጀሉ እንደ አገር አንድ ቢሆንም የፈጸሙት ተጠርጣሪዎችን ግን ብዙ መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ቃላቸውን እንዳይሰጡ ስለመከሯቸው አቶ ዓባይ ወልዱና ሌላ ሁለተኛ ተጠርጣሪ ቃላቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጠቁሞ፣ እንደ የሕግ ባለሙያ የሕግ ድጋፍ እያደረጉ ነው ማለት እንደማይቻልና ተገቢም እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
ጠበቆቹ መርማሪ ቡድኑ በእነሱ ላይ ያቀረበውን ወቀሳ መሳይ አቤቱታ ተቃውመው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ቃል መስጠት ወይም አለመስጠት መብት መሆኑን ተናግረው፣ መርማሪ ቡድኑ ምርመራ መጀመር ያለበት ከተጠርጣሪው ቃል ሳይሆን ከሌላ ማስረጃ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ትክክል ነው፡፡ ቃል መስጠትና አለመስጠት ምን ጥቅምና ጉዳት እንዳለው መክረናል፡፡ ይኼንን እራሱ ፖሊስ መናገር እንዳለበት ሕግ እንደሚያዘው አስታውሰው፣ ሌላ ወንጀል እንደተፈጸመ ተደርጎ ጠበቃን መወንጀል ተገቢ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተው፣ ተግሳጽ ሊሰጥና ሊታረም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ ዝም ማለት መብት መሆኑንና ቃላቸውን እንዳይሰጡ አልመክሯቸውም እንጂ ቢመክራቸው እንኳን ሕገወጥ ተግባር ወይም ምርመራ ማደናቀፍም እንዳልሆነም አክለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክርና አቤቱታ ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ አቶ ተክለወይኒ ባለቤታቸው ስለተወሰደባቸው ገንዘብ ያቀረቡት አቤቱታ በሚመለከት ገንዘቡ ተጣርቶ የግላቸው ከሆነ እንዲመለስላቸው፣ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት ወ/ሮ ሕርይቲ ቤታቸው ስለመታሸጉና ስለመዘረፉ ያቀረቡት አቤቱታን በሚመለከት፣ በጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት የሚታይ ባለመሆኑ እንዳልተቀበለው በመናገር ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችሉ፣ አቶ ስብሃት በግል ሐኪማቸው መታከም አለባቸው ወይም የለባቸውም የሚለውን በሚመለከት በቀጣይ ቀጠሮ ትዕዛዝ እንደሚሰጥበትና ጠበቆች የምርመራ መዝገቡ እንዲጣመር ያቀረቡትን ጥያቄን እንዳልተቀበለው በመንገር፣ መርማሪ ቡድኑ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት እንዳለው ገልጾ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዶ፣ ለየካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡››
Filed in: Amharic