>

'ያ ትውልድ' እሱ የማይናገረው፣ ሌላ ልናገር ቢል የሚናደድበት  የተደበቀ ሕመም አለበት....!!! (አዳም ረታ)

‘ያ ትውልድ’ እሱ የማይናገረው፣ ሌላ ልናገር ቢል የሚናደድበት  የተደበቀ ሕመም አለበት….!!!
አዳም ረታ

‘ምንም እንኳን በአሃዝ የተደገፈ መረጃ ባይኖረኝም፤ ካየሁት፣ ከሰማሁትና እኔም ራሴ ከኖርኩት ምሁራኖቻችን አንዳንድ መጠቀስ የሚገባው፣ የማንሸሸው በሽታ አለባቸው።
ሁሉን  በብድግ ብድግ ዘርዝረን ማጥናት ባንችልም፤ በቅርብ ታሪክ ያየናቸውን ተደጋጋሚ ገጠመኞቻችንን ብንጨምቃቸው መልስ ሊሆኑ የሚችሉ ወይም ወደ መልስ የሚጠጉ የተያያዙ መደምደሚያዎች እናገኛለን።
በነፃ አዕምሮ፤ የማዋረድ ዕቅድ ሳይኖረን ምሁራኑ እንደስልባቦት የለበሱትን የቋንቋና በዲግሪ የተሰፋ የክብር ስልባቦት ከላያቸው ላይ ብንገፍ ከስር ያልጠበቅናቸውን እነዚህን ደዌዎች እናገኛለን።
1/ እነዚህ ሰዎች እንደሚባለው የሚናገሩት ፍሬከርስኪ ቢሆንም ‘መሬት ጠብ አይልም’ ይባላል።
ለምን አይንጠባጠብ?
ለምን አይንዣረር?
ከዚህ አባባል ትምክህት ይቀዱና (‘የተማረ ይግደለኝ’ ምሳሌ ነው) እንደ ሁሉን አዋቂ ይሰራቸዋል። የሚሉት ካልገባህ፤ ወይ ‘መሃይም’ ወይ ‘ደደብ’ ወይ ‘ቂል’ ነህ። ከነዚህ ሶስቱ ካመለጥክ ታድለሃል።
‘የተማረ ይግደለኝ’ ሲባል ሰምቶ ተደሰተ እንጂ ‘ቀስ በሉ’ አላለም። ይሄ ሌላው ሕመሙ ነው።
2/የነዚህ ምሁራን አንዱ ተውህቦ፤ በሆነ ‘ትንታኔ’ በተባለ ነገር ራሳቸውን ማግለል መቻላቸውና ፍፁም ተጠያቂ የሚያደርጉት እዛ የተቀመጠ እነሱን ያልነካ (ያልነኩት)፣ ያልዳሰሰ (ያልዳሰሱት) በሽተኛ ሥርዓት እንዳለ ማውራታቸው ነው።
ይሄ የዘመናውያን ጥበብ ቢሆንም፣ በእነዚህ በኛ ልጆች ይበረታል። ይሄ የአተናተን ስልታቸው ወደ ድርጊታቸው፣ ወደሚኖሩበት ሃቅ ገብተው  በተቀናበረ ተጨባጭ መረጃ ራሳቸውን እንዲያጠኑ አላደረጋቸውም።
ይሄ የ’ትንታኔ’ ሰይፋቸው ግን ብዙ የሚያርፍበት ቦታ ስላልነበረ ታጥፎ ወደራሳቸው መጣ። እንዲህ ሆኖም ሌላ ያማርራሉ። ለምንድን  ነው በሳይንስ ካደጉ መረጃ ወይም ደረቅ እውነት የሚፈሩት? ይሄ ሁለተኛውም ሕመም ነው።
3/ የድሮውን ጊዜ ስርዓት በጠቅላላ በጨቋኝነቱ ቢያሙትም ራሳቸውን ግን ከዚህ ውሳኔ ያወጣሉ። ይሄ ማለት ድሮ ያገኙት ዲግሪ በሐይለስላሴም ሆነ በደርግ ጊዜ የበሉት፣ የጠጡት፣ የተከበሩበት፣ የጨቆኑበት ትክክል ነው።
ዞር ብለው የደርግንና የንጉሡን የትምህርት ስርዓት ቢሰድቡም ያኔ ያገኙት ዶክትሬት ግን ይሞካሻል። ይሄ ሶስተኛ ሕመም ነው።
መማርን በሚመለከት በአጠቃላይ የተማሩበትን ባዕድ ሀገር ማወደስ ደንባቸው ነው። ያን ሀገር ካወደሳችሁ እኔም ከወደዛ ተምሬ ስለመጣሁ አወድሱኝ ዓይነት ይመስላል።
4/ እውነት ካወራሁ የአባይን ወንዝ በፎቶግራፍ ከማየቴ በፊት ያየሁት የሚሲሲፒን ነው። የሰማሁት ዘፈን ደግሞ ጆኒ ካሽ Big River በ 1958 ሲያንጎራጉረው ነው። (አባይ ቢሞላ ቢሞላ/ መሻገሪያው ሌላ) አይደለም።
ታዲያ እሱ ሲያንጎራጉረው ስሰማው እዛ ሚሲሲፒ ወንዝ ዳር አሳ እየበላሁ፣ በሞተር ጀልባ እየተንሸራሸርኩ ፍቅር በፍቅር እየሆንኩ ያደግኩ መሰለኝ።
የስድሳ ስድስት ፖለቲከኞች ወይም ነን ባዮች የአባይን ወንዝ ጂኦ ፖለቲካ መሰረታዊነትና ወሳኝነት ተገንዝበው ፕሮግራማቸው ውስጥ ያላዋቀሩት ንቀውት ነው። ስለ ራስ ማወቅ አሳፍሮአቸው ነው። ከአዞ፣ ከዓሣ፣ ከደንገልና ከጎጃሜ ይልቅ የሚያምሩ ጀልባዎች የሚንሳፈፉበት ነጫጭ ባርኔጣ ያደረጉ ፈረንጆች የሚዝናኑበት ሚሲሲፒ አይበልጥም? እርስዎ አሁን ተነስተው አባይን ልገድብ ቢሉ ዋናው ግራ ተጋቢ ግብፅ ሳትሆን እኔና መሰሎቼ ነን።
በሌላ ምሳሌ ልምጣ። አንደኛ ደረጃ ስማር አደንቀው የነበረው የአሜሪካን ኮንፌዴሬቶች ዘፈን (Oh Susanna!) የተባለውን ነበር። ለምን? ብዬ ራሴን አልጠየቅኩም።
ለምን አልጠየቅኩም?
ደደብነት አይጠይቅም። ደደብነት መሰሎቹን ፈልጎ ይንጋጋል እንጂ ጥያቄ አይመልስም።
ዛሬ አሜሪካውያን ቢመጡ ወደው አይደለም። ገና በጅምሩ በ Oh Susanna ተነዝንዘው ነው። ዛሬ ዛሬ ደግሞ Oh Susanna ዘመኑ ቢያልፍበትም በ ሎስ ዴ ራዮ አሸሼ ገዳሜ ኦ ማካሪና ወይም ማካሬና ወይም ማካሬማ ወይም መከራማ (የሆነው ይሁን) እትዬ ዝኬ ብቅ ብላለች።
እነዚህ ልሂቃን ከልጅነታቸው ጀምሮ በራሳቸውና በ ‘ትላልቅ ሰዎች’  በተቀፈቀፈላቸው  ድንግዝግዝ ሕልም ታጅበው በተቀናበረ ሽሽት ይናጣሉ። ሽሽት ሕመም ነው። በራሱና በመሰሎቹ ለራሱ ግራ የሚያጋባ ቡድን አበጅቷል። የሚኮራበትም መለያ ስምም አውጥቷል
‘ያ ትውልድ’ ይባላል።
5/ ከአራተኛው ሕመም ጋር የተያያዘ ሌላ የተደበቀ (እሱ የማይናገረው፣ ሌላ ልናገር ቢል የሚናደድበት) ሕመም አለበት።
እነዚህ ሰዎች በተዘዋዋሪና (አነሳሱ) በቀጥታ (አጨራረሱ) ራሳቸውን ይጠላሉ። ጭቆና፣ ክፋት፣ ምቀኝነትና ጦርነት ጓዛቸውን ሰብስበው ኢትዮጵያ ውስጥ የገቡ አስመስለው በማማረር ይተነትናሉ ወይም ይናገራሉ።
የጃፓንን ነገር ያደንቁና ስለ ማንቹሪያ ዩኒት 713 እና ስለ ሳንኮ ሰኩሰን ሁሉን ወደ አመድ የመለወጥ ስትራቴጂ አያስታውሱም።
ቻይናን ያደንቁና እዛ ውስጥ ስለተሰራው ረገጣ፣ ጦርነትና ጭቆና አያወሱም።
አውሮፓን ይጠቅሱና ኦፔራ እየተዘመረና ሼክስፒር እየተተነተነ ነ 65 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የጨረሰውን ሁለተኛው የአለም ጦርነት አያይዘው አያስቡትም።
ሰላማዊ ነው እያሉ በሚያሞጋግሱት የዓለም ክፍል ምን ያህል ሚሊዮን ሕዝብ በጦርነትና ባለመግባባት እንዳለቀና በማለቅ ላይ እንዳለ አያነሱም። የሚያዩት የሀገራቸውን ገመና፣ የሚታያቸውም ይሄ ነው።
መረጃ የሚገባቸው ተበታትኖ ነው። በግድ ራሳቸው በፈጠሩት አገራቸውን ማጣጣያ የተመራረጠ መረጃ ተማርከው የዝቅተኝነት አቧራ ለብሰው ሁሉን ነገር ገለባብጠው ሊለውጡ ይፈልጋሉ። ሁለት አይነት ስሜት ያድርባቸዋል።
በመጀመርያ ሀገራቸውን ይጠላሉ። ‘መጥላት’ የሚለውን ቃል ግን አይጠቀሙም።
ሁለተኛ ራሳቸውን የመውደድ ስሜት ያድርባቸዋል። ምክኒያቱም አገራቸው መጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች፣ ይሄንንም የመረዳት ዕውቀት ያላቸውና እንደመንፈስ ያደረባቸው እነሱ ብቻ ናቸው።
እዚህ ላይ ሁሉ ነገር ይዘባረቃል። መዘባረቁን ግን ልብ አይሉም። በፈለጋቸው ጊዜ አቋማቸውን እዛና እዛ የሚያለዋውጣቸው ይሄ ነው።
አንዴ ‘ታላቋ ባለታሪክ ሀገራችን’ አንዴ ‘የተረገመች አገር’ ማለት ያበዛሉ።
ያልተማረው  በነሱ መረጃ ያልተበረዘው ገበሬና መሃይም ግን በሚያቀርቡት ማራኪ ስዕል ‘ልጆቼ የተማሩ ልጆቼ’  በተባሉ ቃላትና ‘በተማረ ይግደለኝ’ ስልት ማልሎ እነሱ ላዘጋጁለት ደብዛዛ ዓላማ በተለያየ መንገድ ይጠፋል። ከዚህ በኋላ የሚቀረው ነገሩ ሲበላሽ ማመሃኛ ሰበብ ፍለጋ ነው።
የሚያመሃኙት ግን በራሳቸው ቀሽምነት ሳይሆን  በሕዝቡ ድንቁርና፣ በአገሩ ምናምን እና እነሱ ስም በሚሰጡአቸው ተቀናቃኞች ላይ ነው።’
#የስንብት_ቀለማት
Filed in: Amharic