>

ያልተዘመረላቸው  የየካቱት 12ቱ ጸረ ፋሽስቱ አርበኛ ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ  (አቻምየለህ ታምሩ)

ያልተዘመረላቸው  የየካቱት 12ቱ ጸረ ፋሽስቱ አርበኛ ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ 

አቻምየለህ ታምሩ

 

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በማርሻል ግራዚያኒ ላይ የተፈጸመው የቦንብ ጥቃትና የአርበኛነት ተጋድሎ  ሲነሳ  ቀድመው የሚታወሱት  የኤርትራ ተወላጆቹ  አብርሃ ደሞጭና  ሞገስ አስገዶም፤ ግፋ ካለም  የሐረሩ አማራ  ሲሞን አደፍርስ  ብቻ ናቸው። በተለይም በዘመነ ደርግ ሻዕብያና ጀብሀ የተባሉ ተገንጣዮችን ትርክት በፕሮፓጋንዳ ለመብለጥ ሲባል የአብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ስም የኤርትራ ተወላጆች ለኢትዮጵያዊነታቸው መስዕዋትነት የከፈሉ መሆናቸውን ለማሳየት እንደ አብነት እየተደጋገመ በየ መድረኩ ይወሳ ነበር። 
 
በደርግ ዘመን እንደዋዛ  የተጀመረው እነ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶምን  የካቲት 12 በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን ጥቃት የመሩና ያቀናበሩ የተደረጉበት ታሪክ በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን የግድያ ሙከራ ያመነጩ፣ መሩት፣ወዘተረፈ የሆኑበት መታሰቢያ  የታሪኩ ዋና ባለቤት የሆኑትን አርበኛ  ውለታ የሚያስረሳ ስለሆነ መስተካከል ይኖርበታል።   
 
በማርሻል ግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን ኦፕሬሽን የጠነሰሱት፣ ለዚህ ኦፕሬሽን የማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒ ኦፊሰር የነበረውን አብርሃ ደሞጭና  የግራዚያኒ አስተርጓሚ የነበረውን  ሞገስ አስገዶምን  የመለመሉት፤ ጥቃቱን እንዲፈጽሙ የተመለመሉት እነ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ጥቃቱን ከፈጸሙ በኋላ ለዋሉት ውለታ የሚገባቸውን ለመክፈል ያሳመኑትና ከአዲስ አበባ ወጠው ወደ ሱዳን የሚሄዱበትን እቅድም ያወጡት በወቅቱ  በነበራቸው ሥልጣን በጅሮንድ ኋላ ላይ  በደረሱበት ማዕረግ ደግሞ ደጃዝማች የነበሩት  ጀግናው አርበኛ ለጥ ይበሉ ገብሬ ናቸው። 
 
ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በመርሐ ቤቴ አውራጃ አፍቀራ አምባ ማናለሽ ቀበሌ በ1885 ዓ.ም.  የተወለዱ ሲሆን ከጥሊያን  ወረራ በፊት የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በጅሮንድ ነበሩ። 
 
በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን የግድያ ኦፕሬሽር የመሩት ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ የግድያ ሙከራውን ያቀናበሩት ጀኔቭ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በግራዚያኒ ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ ባስተላለፉላቸው ትዕዛዝ መሰረት ነው። ደርግ ግን ንጉሡንና ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬን ማውገዝ እንጅ በባለታሪክነት መጥቀስ ስለማይፈልግ አስራ ሰባት ዓመታት ሙሉ እነ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶምን ሲያስታውስ ሲከርም በግራዚያኒ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ትዕዛዝ የሰጡትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴንና ጥቃቱን ያስፈጸሙትን ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬን ስለውለታቸው አንድም ቀን  እንኳ ስማቸውን ጠርቶ በበጎ አስታውሷቸው አያውቅም። ከደርግ በኋላ የመጡት ፋሽስቶችም የቀጠሉት ደርግ በጀመረው መንገድ ነው። 
 
ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ በግራዚያኒ ላይ ለመፈጸም ያቀዱትን ጥቃት ለማድረስ በወዳጃቸው በሲሞን አደፍርስ አማካኝነት የመለመሏቸው አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በግራዚያኒ ላይ ቦንብ ለመጣል የታጩት በወቅቱ የግራዚያኒ የማይጠረጠሩ ታማኝ አገልጋዮችና ግራዚያኒን ከሚቀርቡ ጥቂት  የተማሩ ጥቁሮች መካከል ስለነበሩ ነው። 
 
ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን የግድያ ሙከራ ከመሩ በኋላ የእረኛ ልብስ ለብሰው ራሳቸውን በመቀየር ከአዲስ አበባ ስለወጡ ሳይገደሉ የቀሩና ቀሪውን የፋሽስት  የወረራ ዘመን ከነራስ አበበ  አረጋይ ጋር ሆነው በአርበኛነት ሲፋለሙ የቆዩ ከግራዚያኒ የግድያ ሙከራ ጋር ተያይዞ ስማቸው ከሚጠቀሱ  አርበኞች መካከል በሕይዎት የተረፉ ብቸኛው ሰው ናቸው። 
 
እኒህ በግራዚያኒ ላይ የተካሄደውን የግድያ ሙከራ  የመሩና ያቀናበሩት  አርበኛ  የሕይዎት ፍጻሜ የሆነው መንግሥቱ ንዋይና ግርማሜ ንዋይ የተባሉ የሰው ደም የተጠሙና የሰው ስጋ የተራቡ አውሬዎች በ1953 ዓ.ም. በካሄዱት የአርበኞች ፍጅት ነው። ከግራዚያኒና ከሙሶሎኒ ግድያ የተረፉት ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ለጥይበሉ ገብሬ «ለውጥ ለማምጣት ተነሳን» ባሉ  ባገራቸው ልጆች በአዛውንት እድሜ ላይ ሳሉ በማረፊያቸው ታኅሣሥ 7 ቀን 1953 ዓ.ም.  ያለ ፍርድ በግፍ ተረሸኑ። 
 
ዘላለማዊ ክብር የማይጠፋ ሥራ ሰርተው ላለፉ ለአይበገሬው ጀግና ለደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ!  
 
ምንጭ: 
– Campbell, I. (2017). The Addis Ababa Massacre: Italy’s National Shame. Oxford University Press; Page 243-248.
Filed in: Amharic