ነነዌ በዘመኗ ታላቅ ከተማ ነበረች፥ነገር ግን እግዚአብሔር የሌለበት ታላቅነት ከንቱ በመሆኑ፦”በሦስት ቀን ውስጥ ትጠፋለች፤”ተባለች።ምክንያቱም የከተማይቱ ኃጢአትና በደል ሰማይ ደርሶ ነበር።በከተማይቱ ከመቶ ሃያ ሺህ ሰዎች በላይ ይኖሩባት ነበርና ጥፋቱ ከመጣ ቀላል አልነበረም።የእግዚአብሔር ቸርነቱ ከቅጣቱ በፊት የንስሐን በር ሊከፍትላ ቸው ወደደ።የንስሐ መምህርና አባትም ነቢዩ ዮናስን መረጠላቸው።
ነቢዩ ዮናስ ግን፦”እኔ ንስሐ ባይገቡ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ነነዌ እንደምትጠፋ ለሕዝቡ ካስተማርኩ በኋላ እግዚአብሔር እንደ ልማዱ ራርቶ ቢተዋቸው ሐሰተኛ ነቢይ ልባል አይደለምን?” ብሎ በመርከብ ወደ ተርሴስ ኮበለለ።እንዲህም ማድረጉ በየዋህነቱ ነው፥ዮናስ ማለት ርግብ ማለት ነውና፥ርግብ ደግሞ የምትታወቀው በየዋህነቷ ነው።ማቴ፡፲፥፲፮።
“ኵሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ፤” እንዲል፦ዓለም በእግዚአብሔር የእጁ መዳፍ ላይ ናት፥ ባሕሩም የብሱም የእርሱ ነው፥ታዲያ ከእግዚአብሔር ፊት ወዴት ይሸሻል? “ከመንፈስህ ወዴት እሄዳለሁ? ከፊትህስ ወዴት እሸሻለሁ? ወደ ሰማይ ብወጣ አንተ በዚያ አለህ፥ወደ ጥልቁም ብወርድ አንተ በዚያ አለህ።እንደ ንስርም ክንፍን ብወስድ፥እስከ ባሕር መጨረ ሻም ብበርር በዚያ እጅህ ትመራኛለች፥ቀኝህም ታኖረኛለች።በእውነት ጨለማ ትሸፍነኛለች ብል፥ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ይሆናል።ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምምና፥ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና።” ይላል።መዝ፡፻፴፰፥፯-፲፫።
ነቢዩ ዮናስ የባሕር ላይ ጉዞው አልተሳካለትም፥የባሕሩም፥የየብሱም፥የአየሩም ጉዞ የሚሰምረው በእግዚአብሔር ቸርነት ነውና።ብርቱ ማዕበል ተነሥቶ መርከቧን አናወጣት፥ ልትሰበርም ቀረበች፥በሞያቸው፥በጥበባቸውና በሥራ ልምዳቸው ይመኩ የነበሩ መርከበኞ ችም ፈሩ።ጥበባቸው ስንፍና መሆኑን አውቀው (ፍጹምነት የሌለው መሆኑን ተረድተው)፥ ወደ አምላካቸው ጮኹ።፩ኛ፡ቆሮ፡፩፥፳።እንዲያም ሆኖ በተጥባበ ሥጋ መርከቢቱ እንድት ቀልላቸው የተሸከመችውን ጭነት ወደ ባሕር ጣሉት፥ነገር ግን አልሆነም።የሚያስፈልገው የመርከቧን ሸክም ማቅለል ሳይሆን የየራሳቸውን ሸክም ማቅለል ነበርና።ማቴ፡፲፩፥፳፰።
ይህ ሁሉ ሲሆን ዮናስ፦ወደ መርከቧ ውስጠኛ ክፍል ወደ ታች ወርዶ ተኝቶ ነበር። ይኸውም፦ከመከራው ይልቅ ጭንቀቱ ይበልጥ ስለሚጎዳ፥የዋህነቱን አይቶ እግዚአብ ሔር ከጭንቀት ሲሰውረው ነው።”በልባቸው የዋሃን ለሆኑ ሰዎች እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤”ይላልና።መዝ፡፴፫፥፲፰።ሰው ሰውኛውን በዮናስ ድርጊት የተገረመው የመርከቡ አለቃ ግን ቀሰቀሰውና ወደ አምላኩ እንዲጸልይ እሳሰበው።ተሳፋሪዎቹ ደግሞ ያ ሁሉ መከራ በማን ምክንያት እንደ መጣባቸው ለማወቅ ዕጣ ቢጣጣሉ፥ዕጣው በዮናስ ላይ ወደቀበት።
ነቢዩ ዮናስ በሰው ዘንድ ያልታወቀ ድካሙን ወደ ማስተባበል አልሄደም፥እኛ ብንሆን እንኳን የተሰወረውን በዐደባባይ የተገለጠውንም ቢሆን ዐይናችንን በጨው አጥበን ስናስተ ባብል ነው የምንገኘው።ዮናስ ግን በጠየቁት ጊዜ እያንዳንዱን ነገር ተናዘዘላቸው፥”ባሕሩ ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ?”ባሉትም ጊዜ፦”ወደ ባሕር ጣሉኝ፤”አላቸው።ሃይማኖት ያለው ሰው በራሱ ላይ ለመፍረድ አይቸገርም፥ሃይማኖት የጎደለው ሰው ግን፦በራሱ ድካም በሌላው ሰው ላይ ሲፈርድ ይኖራል።እንደ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል።
ተሳፋሪዎቹ በራሱ ከፈረደ ዘንዳ ብለው አልቸኮሉም፥ባይሳካላቸውም እርሱንም ጭምር ለማትረፍ ከወደብ ለመድረስ ታገሉ።በመጨረሻም፦”አቤቱ አንተ አንደ ወደድህ አድርገሃልና ስለዚህ ሰው ነፍስ አታጥፋን፥ንጹሕ ደምንም አታድርግብን፤”ብለው ወደ ባሕር ጣሉት፥ባሕሩም ከመናወጥ ጸጥ አለ።ልክ እንደዚህ ኃጢአታችንን ተናዝዘን ቀኖናችንን ስንፈጽም የታወከው ነገር ሁሉ ከረቂቅ አእምሮአችን ጀምሮ ጸጥ ይላል።የኅሊና እረፍት፥ የልቡና ሰላም እናገኛለን።ሀገርም ቤተ ክርስቲያንም ሰላም ያገኛሉ።እየዋሹ፥እየሰረቁ፥ እያመነዘሩና ደም እያፈሰሱ ጻድቅ ነኝ ማለት የትም አያደርስምና።
እግዚአብሔር ዮናስን የሚውጥ ታላቅ ዓሣ አዘጋጀ፥እርሱም የዓሣውን ሆድ እንደ ቤተ መቅደስ ተጠቅሞ፦ጸለየበት፥ሰገደበት።በዚያም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት ቆይቶ ከወደብ ላይ ተፋው።እግዚአብሔርም፦”ወደ ነነዌ ሂድ፥የነገርኩህን የመጀመሪያውን ስብከት ስበክላት፤”አለው።ዮናስም በየዋህነቱ ላይ ጥበብ ጨምሮበት ክርክሩን አቆመና ነነዌን ሰበካት።ሁሉም ሕዝብ በቃለ ስብከቱ አምነው ንስሐ በመግባት የሦስት ቀን ጾምና ጸሎት ዐወጁ።ነቢዩ ኢዩኤል፦”ጾምን ቀድሱ፥ምሕላውንም ዐውጁ፤”ያለውን ፈጽመው ተገኙ።ኢዩ፡፩፥፲፬።ንጉሡም ዐዋጁን በሰማ ጊዜ፦ከወርቅ ዙፋኑ ወረደ፥የወርቅ መጎናጸፊያ ውን አውልቆ ለገላ የማይመቸውን ማቅ ለበሰ፥አመድ ነስንሶ በዚያ ላይ ተኛ፥ሕዝቡም ሁሉ እንዲሁ አደረጉ።ጡት የሚጠቡ የ፵፥የ፹ ቀን ሕጻናት እንኳ ጡት ተከልክለው ሦስት መዓ ልትና ሦስት ሌሊት ጾሙ።ከሁሉም የሚደንቀው እንስሳቱ ጭምር በረት ተዘግቶባቸው አብረው ጾሙ።በጾም ጉዳይ ከነነዌ ሕጻናትና እንስሳት አንሰን እንዳንገኝ መጠንቀቅ አለብን።
እግዚአብሔርም የነነዌ ሰዎች ከክፉ መንገዳቸው ፈጽሞ መመለሳቸውን አይቶ ራራላቸው፥ምሕረትን ሰጣቸው፥ይቅርታን አደረገላቸው።እግዚአብሔር ለተነሣሕያን እንዲህ ነው።መዓቱ ወደ ምሕረት፥ቍጣው ወደ ትዕግሥት ተመለሰ።ዮናስም ይህንን አይቶ አዘነ፥ “ድሮም የፈራሁት ይኸንኑ ነበር፤” አለ፥”አሁንም አቤቱ! ከሕይወት ሞት ይሻለኛልና እባክ ህን ነፍሴን ከእኔ ውሰዳት፤”እያለም ጸለየ።ከከተማዪቱም ወጥቶ የከተማዪቱን መጨረሻ ለማየት በዚያ ዳስ ሠርቶ ተቀመጠ።እግዚአብሔርም ቅል አብቅሎ በጥላዋ እንድታሳር ፈው፥ከጭንቀትም እንድታድነው ካደረገ በኋላ መልሶ በምክንያት እንድትደርቅ አደረጋት። በዮናስም ዋዕየ ፀሐይ ስለጸናበትና ተስፋ ስለቆረጠም ለሁለተኛ ጊዜ፦”ከሕይወት ሞት ይሻለኛል፤”አለ።በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ፦”በውኑ ስለዚህች ቅል ታዝናለህን?”ብሎ ጠየቀው።እርሱም፦”እስከ ሞት ድረስ አዝኛለሁ፤”አለ።እግዚአብሔርም ፦”አንተ ትበቅል ዘንድ ላልደከምህባት፥ላላሳደግሃትም፥በአንዲት ሌሊት ለበቀለች፥በአንድ ሌሊት ለደረቀ ችው ቅል አዝነሃል።እኔስ ቀኛቸውን እና ግራቸውን የማይለዩ ከመቶ ሃያ ሺህ የሚበልጡ ሰዎችና ብዙ እንስሶች ላሉባት ለታላቂቱ ከተማ አላዝንምን?” አለው።
እግዚአብሔር ያዘነላቸው ስለ ኃጢአታቸው አዝነው በመገኘታቸውና ጾም ጸሎት በመያዛቸው ነው።እኛም ለንስሐ ስናዝን እንገኝ፥መምህራንን የሚያስደስታቸው ምእመናን ለንስሐ ሲበቁላቸው ነውና።ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦”መጀመሪያ በጻፍሁት መልእክት ባሳዝናችሁም እንኳ አያጸጽተኝም።ብጸጸትም እነሆ ያች መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳ ሳዘናችሁ አያለሁ።አሁን ግን እኔ ስለ እርሷ በብዙ ደስ ይለኛል።ደስታዬም ስለ አዘናችሁ አይደለም፥ንስሐ ልትገቡ ስለ አዘናችሁ እንጂ።ከእናንተ አንዱ እንኳ እንዳይጠፋ ስለ እግዚ አብሔር ብላችሁ አዝናችኋልና።ስለ እግዚአብሔር ተብሎ የሚደረግ ኀዘን የዘለዓለም ሕይ ወትን የሚያሰጥ ንስሐ ነው።ስለ ዓለም የሚደረግ ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል።”ያለው ለዚህ ነው።፪ኛ፡ቆሮ፡፯፥፰።
እንግዲህ ከነነዌ ምክንያተ ጾም አያሌ ነገሮችን ልንማር ይገባል።የእግዚአብሔር ርኅራኄ፥የነቢዩ የዮናስ የዋህነት እና የሕዝቡ ጸጸት ተገልጦበታልና።”የሰማይ አባታችሁ ርኅሩኅ እንደሆነ እናንተም ርኅሩኃን ሁኑ፤”በተባለው መሠረት ርኅሩኃን እንሁን።ሉቃ፡፮፥፴፮።
አንጨካከን፥አንተራረድ።ጭካኔ መግደል ብቻ አይደለም፥መዋሸትም፥መስረቅም፥ ዝሙት መፈጸምም፥ዘረኝነትም ወዘተ … ጨካኝነት ነው።ርኅራኄ የሚጀምረው ከራስ ነው፥አፈጻጸ ሙም ከኃጢአት መለየት፥ከበደል መራቅ ነው።ከዚህ በኋላ ለወገን የሚራራ ልቡና ይኖረ ናል።የዋህነትንም ከነቢዩ ከዮናስ እንማር፥እግዚአብሔር፦ከመንገድ የመለሰው፥በዓሣ አንበሪ ሆድ ውስጥም የጠበቀው የዋህነቱን አይቶ ነው።በዚህም “እኔ የዋህ በልቤም ትሁት ነኝና፤” ላለ፥፫ መዓልትና፥፫ ሌሊት በመቃብር ለቆየም ለክርስቶስ ምሳሌ ሆኖአል። ማቴ፡፲፩፥፳፱፤፲፪፥፵።እኛንም ዋጥ ስልቅጥ ያደረገችን ዓለም ከወደቡ እንድትተፋን ከእም ነት ጋር የዋህነትን ገንዘብ እናድርግ።ወደቧም በደሙ የተመሠረተች፥የሲኦል ደጆችም (የሲኦል ደጅ ጠባቂ አጋንንት) የማይችሏት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት።ማቴ፡፲፮፥፲፰። ከነነዌ ሰዎችም ስለ ኃጢአት መጸጸትን እንማር።”በደሉን የሚሰውር መንገዱ አይቃናም፥ የሚናዘዝና ራሱን የሚዘልፍ ግን ይወደዳል፤”ይላልና።ምሳ፡፳፰፥፲፫።የነነዌ ጾም የእግዚአብ ሔርን ቍጣ ወደ ትዕግሥት፥መዐቱንም ወደ ምሕረት የመለሰ በመሆኑ ወድደን፥ፈቅደን እንጾመዋለን።ነነዌ እኮ “የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ተነሥተው ይህችን ትውልድ ይፋረዱአ ታል፥በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፤” ተብሎላታል።ስለሆነም እምነቷ፥ንስሐዋና ጾሟ ይፋረዳል።ማቴ፡፲፪፥፵፩።የእግዚአብሔር ቸርነት፥የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፥ አሜን።