የተዘነጋው የአዲስ አበባ ራእይ….!!!
ክብሮም አሰፋ
ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካሉ ክፍለ ከተሞች በአንዱ ለስራ ጉዳይ ጎራ የማለት ዕድሉ ገጠመኝ። ቆይታዬን ባደረግኩበት ክፍለ-ከተማ ውስጥ የተለያዩ መጠን ያላቸው ባነሮች ባለጉዳይ እንዲያያቸው በሚያስችል መልኩ በር ላይ ተንጠልጠለው ይገኛሉ። በባነሮቹ ላይ ተልዕኮ፣ እሴት እና መርሆዎች ተብለው ተዘርዝረው ከተጻፉት ውስጥ ራዕይ ተብሎ የተገለጸው ትኩረቴን ሳበው። ራዕይ ተብሎ የተገለጸው ላይ ከተማዋ የቀረጸቺው የአስር ዓመት ጉዞ የሚገባደደው በዚህ ዓመት መሆኑን ያሳያል። በ2001 ዓ.ም በወጣው የአስር ዓመት ዕቅድ መሰረት፣ የከተማዋ ራዕይ የመዳረሻው ዓመት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 (በእኛው 2012) በማድረግ ተቋማቱ የሚሰጡት አገልግሎት መዳረሻ ጥግ ምን እንደሆነ ባነሩ ይነግረናል። ዳሩ ግን፣ ከተማዋ የአስር ዓመት ራዕዩዋን የረሳችው ነው የምትመስለው። ከተማዋ በያዝነው በጀት ዓመት ስለ አስር ዓመት ጉዞዋ በመገናኛ ብዙሃኗ አማካኝነት አጀንዳ አድርጋ ስታነሳው አይሰማም። ተቋማቱም ስላለፈው ጉዟቸው ሲመክሩም አልተሰማም። ሌሎች የመንግስት ተቋማት የመጪው አስር ዓመት ዕቅዳቸው ላይ ትኩረት ሰጥተው ሲወያዩ ያለፈውን አስር ዓመት ገምግመው እንደሆነ በሚድያው ሲናገሩ ይሰማል። ከዚህ አኳያ፣ የከተማ አስተዳደሩ በየጽ/ቤቱ አባሯ ጠጥተው የሚገኙ ባነሮች ላይ የተጻፈው ራዕዩን እንዲያስታውሰው ለማድረግ ያክል ዕቅዱ ሲዘጋጅ ተደርጎ የነበረው የመዋቅር ዝርጋታ፣ የሰው ኃይል ድልድል፣ ተቋማቱ ያወጡትን ራዕይ አሳኩት ወይስ ገና ናቸው? እና ለወደፊትስ ምን ቢሆን ይበጃል? የሚለውን ለመቃኘት እንሞክር።
የራዕዩ ጅማሬ
በ2001 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚመራቸው መንግስታዊ ተቋማት ላይ ስር ነቀል የሆነ የአሰራር ለውጥ ለማምጣት ሽር ጉድ ያለበት ዓመት ነበር። በወቅቱ ከንጉሱ ጌዜ ጀምሮ ሲንከባለል የመጣውን አሮጌውን መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ለመቀየር እንቅስቃሴዎች ታይተዋል። አሉ የተባሉ የውጭ አገር የአመራር መሳሪያዎች እንደ አገር እንዲጠኑ ተደርጎ የተሻለው ይተግበር ተብሎም ውሳኔ የተሰጠበት ወቅት ነበር። በግል የንግድ ተቋማት ላይ ተሞክሮ ውጤታማ እንደሆነ የተመሰከረለት የመሰረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥ ወይም ቢ.ፒ.አር. ልማዳዊ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ፍቱን መድሃኒት እንደሆነ ታምኖበት ለሰነዶች ዝግጅት፣ ለስልጠና እና ለውጭ አገር ተሞክሮ ተብሎ በርካታ ብሮች ፈስሰዋል። ጥናቱን ከየተቋማቱ የተመረጡ አካላት ከስራ ባህሪያቸው አኳያ በበላይ አመራር ቁጥጥር እየተደረገባቸው የስራ ፍሰቱን እንዲያጠኑ ተደርጓል። የስራ ክብደቱ እየተመዘነ፣ ቀድሞ በመመሪያ እና በቡድን የነበሩ ስራዎች በዋና እና ደጋፊ የስራ ሂደቶች ዳግም ተዋቅረዋል። ለስራ ሂደቶቹ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ብዛት እና የመደቡ ስያሜ በአጥኚዎቹ ቀርቦ በፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ እንዲጸድቁ ተደርጓል። በተጓዳኝም፣ አስተዳደሩ የሚፈልገውን ለውጥ እንዲያሳኩ በሚል የሰው ኃይሉን በአዳዲስ የዩንቨርስቲ ተመራቂዎች ለመሙላት ተነስቷል። ዳሩ ግን፣ ይህ አዲስ ምሩቅ ተማሪዎችን የማምጣቱ ነገር አንድም ነባሩ ሰራተኛ ስራየን አጣ ይሆን የሚል ስጋት ሲያስከትልበት፣ አዲስ ደም ለተባሉት የዩንቨርስቲ ተመራቂ ተማሪዎች ደግሞ አቀጣጠሩ ግልጽነት ስለጎደለው በተመራቂው ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል። የቅሬታው ምንጭ፣ አዲስ ሰራተኛ የመቅጠር ኃላፊነቱ የከተማዋ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ሳይሆን አራት ኪሎ የሚገኘው የኢህአዴግ ጽ/ቤት የመሆኑ ጉዳይ ነው። በወቅቱ፣ ኢህአዴግ በየዩንቨርስቲው ለየብሄራዊ ድርጅቶች ቢሮ ሰጥቷቸው የድርጅት ስራ ያሰራ ነበር። የድርጅቱ ካድሬዎች ዋነኛ ስራ አባላትን ማፍራት ሲሆን፣ አባላቱም እንደ ዩኒቨርስቲው ግሬድ(ውጤት) ይሰጣቸዋል። ድርጅታዊው ግሬድ ዩንቨርስቲው ከሚሰጠው ግሬድ በላይ የመቀጠር ዋስትና የሚሰጥ ነበር። ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ጊዚ ከማሳለፍ ይልቅ የየብሄራዊ ድርጅቱ በር ስር ፊት እያስገረፉ መዋል ዋነኛ ስራቸው አድርገውት ነበር። የዩንቨርስቲው ካድሬዎችም የተመራቂዎቹን የተጠቃለለ ድርጅታዊ ውጤት ወደ አራት ኪሎው የድርጅቱ ዋና ቢሮ ይልካሉ። የአራት ኪሎው አካልም ከተላከለት ዝርዝር ውስጥ የሚፈልገውን መርጦ በስልክ ጥሪ ያስተላልፍላቸዋል። ተማሪዎቹ ሲሰባሰቡም በመንግስት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ላይ የአስራ አምስት ቀን ስልጠና ይሰጣቸዋል። በስልጠና ባሳዩት አቋም መሰረትም ድርጅቱ በፌዴራል እና በከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ተቋማት ላይ ተመራቂዎቹን ይደለድላል። የተደለደለው ዝርዝርም ለሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር እና ለከተማው ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ይላካል። ሲቪል ሰርቪስ ለተቀጣሪ ሰራተኞቹ በማስታወቂያ ላላወጣበት የስድስት ወር የሙከራ ጊዜ የስራ ቅጥር ደብዳቢ አዘጋጅቶ ይበትናሉ። በዚህ መልክ ድርጅታዊ ተልዕኮ የተሰጣቸው አዳዲስ ሰራተኞች በመንግስታዊ ቢሮክራሲ ውስጥ በማስገባት አዲሱን መዋቅር ለማስተግበር ተሞክሯል። ይህ ህግን የጣሰ የስራ ቅጥር በድርጅት አመንጭነት እና በመንግስት ተባባሪነት በሰፊው ሲሰራበት የነበረ እውነታ ሲሆን፣ ይህ እውነታም በአገሪቱ ለትምህርት ስርዓት መውደቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።
ከላይ በተገለጸው አግባብ፣ በፌዴራል መንግስት እና በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ በተቀጠሩ አዳዲስ ሰራተኞች የተተገበረው የአደረጃጀት ለውጥ እንደ አገር ከተተገበረ አስር ዓመት አስቆጠረ። ጥናቱን ያከናወኑት አካላት ጥናቱን ሲያስተገብሩ በ2012 ዓ.ም ሁሉም ተቋማቱ መድረስ የሚገባቸውን ራዕይ አስቀምጠዋል። ራዕያቸውም በየቢሮው በባነር እንዲለጠፍ አድርገዋል። ሆኖም ግን፣ ባነሩ አባሯ ጠጥቶ በየተቋማቱ ይገኛል። በወቅቱ፣ ቀደም ብሎ የነበረውን መንግስታዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል መሰረታዊው የአሰራር ሂደት ለውጡ ጠቃሚ እንደነበር አያጠያይቅም። ተቋማት ስራ በመምራት ብቻ ያሳልፉ የነበረውን ጊዜ የስራ ፍሰቱን ማዕከል በማድረግ ወደ አንድ የስራ ቡድን በማምጣት የአገልግሎት አሰጣጡ ፍጥነት እንዲኖረው አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል። አንድን ስራ ለማስፈጸም ቢያንስ አራት እና ከዚያ በላይ የስራ ክፍሎችን ይነካ የነበረውን አሰራር ወደ አንድ በማምጣት ስራው እንዲያጥር መደረጉ ለተገልጋዩ መጠነኛ እፎይታን ፈጥሯል። ከዚህ አኳያ፣ የወቅቱ የስራ መዋቅሩን በሚገባ ከመፍጠር አኳያ የተሻለ እንደነበር መግለፅ ቢቻልም ስራን ከመመዘን እና የስራ ቅብብሎሽ ሪፖርቱን በማሳጠር ዘመኑ ከሚጠይቀው የዲጂታል ስርዓት ጋር ከማስተሳሰር አንፃር ውስንነት እንዳለበት ይገለጻል።
ጥናቱ ተግባራዊ ከሆነ አስር ዓመት ቢያስቆጥርም ሰራተኛው ስራን እንዴት እንደሚመዝን እና ውጤቱን እንዴት እንደሚመዝን ግንዛቤው የለውም። ይህ እውነታ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ሲቪል ሰርቪሱም የሚጋራው መሆኑ ደግሞ፣ ያለመረዳት ችግሩ ከምንጩ እንደሆነ ምክንያት ይሰጣል። በወቅቱ የተደረገው ጥናት ዋነኛ ትኩረቱ የመንግስትን ወጪ ለመቀነስ ያለመ ነበር። ይህም ሰራተኛውን ሁለገብ በማድረግ አንድ ሰራተኛ በርካታ ስራዎችን የመስራት አቅም እንዲኖረው ታስቦ የተተገበረ ቢሆንም፣ ስራውን የሚሰራው ሰራተኛ ግን በአንድ ዓይነት መልኩ የሚፈርጅ እና ለነባር ሰራተኞች ክብር የማይሰጥ ሆኗል። በሌላ አማርኛ ለዕውቀትና ክህሎት ዕውቅና አይሰጥም ነበር። ከዚህ በተጨማሪም፣ በወቅቱ ጥናቱ አስፈላጊ የነበረው በአገሪቱ የነበረውን የተመራቂ ቁጥር መጠን መጨመርን ለማስተንፈስ በርካታ የስራ መደቦች በዜሮ ዓመት የሚሰሩበት ሁኔታ መፈጠሩ በሰራተኛው መካከል መከባበር እንዳይኖር አድርጓል። መንግስት የመሰረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጡን ከውጭ አገር ተውሶ ሲያመጣው የአሰራር ፍሰቱን ማስተካከል ላይ የሚያተኩረውን አሰራር ብቻ መርጦ በማምጣት የሚያስችለውን መሳርያ አለማስተግበሩ ጥናቱ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል። ይህን ጎዶሎውን ለመሙላት በቡድን የሚያስመዝን አመለካከት፣ ክህሎት እና ግብኣት የሚባሉ ፖለቲካዊ ጫና የበዛባቸው የሰራተኛ መለኪያ ማምጣቱ ሰራተኛው በጅምላ እንዲጓዝ በማድረግ ጠንካራ ሰራተኞች ነጥረው እንዳይወጡ አድርጓል።
የመሰረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥ የሚያስፈልግበት ዋነኛ ምክንያት የተገልጋዩን እና የሰራተኛውን እርካታ ለመፍጠር ሲሆን እርካታው የሚመጣውም የስራ ሂደቶችን በማሳጠር፣ ድግግሞሽን በማስቀረት፣ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን በማሳደግ እንደሆነ ይታመናል። በስራው የረካ ሰራተኛ ተገልጋይን ያረካል ተብሎ ስለሚታመን ተቋማት ለሰራተኛ እርካታ እንዲጨነቁ ይመክራሉ። ነገር ግን፣ መንግስት ከለውጥ መርሆዎች ውስጥ የስራ ሂደቶችን በማሳጠርና የአሰራር ጥራትን በማሳደግ የተገልጋዩን እርካታ ለማምጣት ያደረገው ጥረት የተሳካ አልነበረም። በርካታ ስራዎች በአነስተኛ ሰራተኞች የሚሰሩበትን ሁኔታ ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ከክፍያ አንፃር አብሮ አለመካሄዱ ሰልጥነው የገቡ በርካታ ሰራተኞች በውስን ወራቶች ውስጥ እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል። የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኞች በሚያገኙት ገቢ ለመኖር አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። የቤት ኪራይ ወጪ ለመቀነስ በቡድን እየተከራዩ እና በጋራ እያበሰሉ ለመኖር ቢሞክሩም የከተማዋን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም አላስቻላቸውም። በውጤቱም ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ሰራተኞች ወደ ትውልድ ቀዬአቸው እንዲመለሱ አስገድዷቸዋል። የመሰረታዊ ሂደት ለውጡን ተከትሎ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ሰራተኞች የሚበረቱበት አሰራር አብሮ አለመታሰቡ የስራ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ሚና ፈጥሯል። አተገባበሩም ጎዶሎ እንዲሆን አድርጎታል። በመንግስት ተቋማት ውስጥ ሰራህም አልሰራህም የወር ደሞዝህን እንደማታጣ ስለሚታወቅ ሰራተኛው ወደ ስንፍና እንዲገባ አድርጓል። ሰራተኛው ስራውን አክብሮና ውጤታማ ሆኖ እንዲኖር በስራቸው ትጋት አርአያ የሚሆኑ ሰራተኞች በጥቅማጥቅም እንዲደጎሙ ማድረግ ባለመቻሉ የመሰረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጡ ውጤታማ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል። መንግስት ላለፉት አስር ዓመታት በዚህ መንገድ መሄዱ ከውስጥም ከውጭም እንዲናጥ አድርጎታል። የመናጡ ምስጢርም የመልካም አስተዳደር ጉድለትን አስከትሎ ህዝባዊ አመጽን አዋልዷል።
ራዕይ 2012
የመሰረታዊ የአሰራር ሂደት ለውጥ ትግበራን ተከትሎ በወቅቱ ከነበሩ ዋነኛ ስራዎች መካከል ተቋማት ከከተማዋ መሪ ዕቅድ የሚቀዳ የአስር ዓመት ራዕይ እንዲዘጋጁ ተደርጓል። ስለሆነም ተቋማት የአሰር ዓመት ዕቅዳቸውን ከማዘጋጀታቸው በተጓዳኝ በየመስሪያ ክፍላቸው የአስር ዓመት ራዕያቸውን፣ ተልዕኮአቸውን፣ ዓላማቸውን፣ እምነታቸውን እና ዕሴቶቻቸውን በደማቅ ቀለም በባነር እንዲጽፉ ተደርጎ ተገልጋዩ እንዲያውቀው ተደርጓል። ከተጠቀሱት መካከል በዋነኝነት የተቋሙ ራዕይ በጊዜ ገደብ ተቀምጦ በ2012 ዓ.ም የት መድረስ እንደሚፈልግ በግልጽ እንዲቀመጥ ተደርጓል። ይህ ባነር በየ መንግስታዊ ተቋሙ ተሰቅሎ ይገኛል። እርግጥ ነው፣ ይህ ራዕይ ለአስር ዓመት ተብሎ ቢወጣም ባጋጠመው የፖለቲካ ምስቅልቅል ምክንያት አመራሩ ስራውን ተረጋግቶ የመምራት ዕድል እንዳያገኝ ሰበብ ሆኗል። የያዘውን የረዘመ ራዕይ ከማሳካት ይልቅ እሳት የማጥፋት ዘመቻ ላይ ተጠምዶ የዋለባቸው ዓመታት ይልቃሉ። ብዙውን ጊዜ በአገሪቱ ለነበሩት የፖለቲካ ችግሮች ዋነኛ ተዋንያኖቹ እና መፍትሔ ፈላጊዎቹ አመራሮቹ በመሆናቸው ለራዕያቸው መሳካት ደንታ ሳይሰጣቸው በርካታ ዓመታትን አባክነዋል። በቦታው በርካታ አመራሮች ተፈራርቀውበታል። በርካታ ሰራተኞች ለቀዋል። እነዚህ የባከኑ ዓመታት ከተማዋ የያዘቺው የአስር ዓመት ዕቅድ እንዳይሳካ አድርጓል። ዛሬም መሪ የፖለቲካ ድርጅቱ ስላለና ዕቅዱን የመሳካት ግዴታ ስላለበት ጉዳዩን ለማንሳት አያግደንም። ለመነሻ ያክል፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያሉ አምስት ተቋማት በ2012 ዓ.ም ሊደርሱበት አስበውት የነበረውን ራዕይ እንመልከት። የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አስተዳደር በ2012 ዓ.ም ዘመናዊ አሠራር በመጠቀም ልማታዊ የመሬት አቅርቦት አስተዳደር ስርአትን ለማረጋገጥ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ተመሳሳይ ተቋማትን ሞዴል እንዳደረገ ሲነግረን፣ የከተማዋ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን በበኩሉ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋ እና የተቀናጀ የግንባታ ፍቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር አገልግሎትን በማሳለጥ በ2012 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማን በግንባታ(በህንጻ) ደረጃዋ የአፍሪካ ሞዴል ማድረግ መዳረሻው እንደሆነ ራዕዩ ይነግረናል። ከመሬት ወደ ማህበራዊ ዘርፉ ስንመጣ፣ የከተማዋ ጤና ተቋም በ2012 ዓ.ም የከተማዋ ነዋሪ በራሱ የሚያመርት፣ ጤናማና ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጥበት ከተማ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ የሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ በበኩሉ በ2012 ዓ.ም የስራ ስምሪት አገልግሎት የተስፋፋበት፣ የኢንዱስትሪ ሰላም የሰፈነበት እና የህብረተሰቡ ማህበራዊ ደህንነት የተረጋገጠበት ከተማን መፍጠር ራዕዩ ማድረጉን ይነግረናል። ሴቶችና ህጻናት ደግሞ በ2012 ዓ.ም የከተማ ሴቶች በሁሉም የልማት ዘርፎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሆኑበት፣ ፆታዊ ፍትሃዊነት የሰፈነበት የህጻናት መብትና ደህንነት የተከበረበት በጋራ ያደገ ማህበረሰብ ማየት እንደሆነ ገልጿል።
ከላይ ያየናቸው ዕቅዶች የወጡት ከአስር ዓመት በፊት ሲሆን ዘንድሮ ጊዜው ላይ ደርሰናል። በዚህ መሰረት፣ ከአስር ዓመት በፊት የወጣው ዕቅድ ዛሬ ላይ ገቢር ሆኗል ወይ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ራዕዩ የተጻፈው ሊተገበር ነውና አፈፃፀሙ ምን ይመስላል የሚለውን አንባቢያን የራሳቸውን ትዝብት ሊወስዱ ይችላሉ። የአዲስ አበባ መሬት አስተዳደር ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመሬት አቅርቦቱን ዘመናዊ ማድረግ ራዕዩ እንደሆነ የዛሬ አስር ዓመት ቢነግረንም፣ በተግባር ግን ከቴክኖሎጂ ጋር የማይተዋወቅ ሰራተኛን እናያለን። ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ አባሯ ጠጥቶ የተቀመጠ ማህደር የሚያገላብጡ ናቸው። የመሬት አሰጣጡም ግልጽነት የሚጎድለው እና ከልማዳዊ አሰራር ያልተላቀቀ ተቋም እንደሆነ ማንም ተገልጋይ የሚመሰክረው እውነታ ነው። የተገልጋይ ማህደራት ዲጂታላይዝድ ተደርገው አገልግሎቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቢታገዝ ችግሮች ይቀልሉ ነበር። ዛሬም ግን ስለ መሬት ወረራ የሚያወራ ተቋም ሆኗል። በተመሳሳይ፣ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ከተማዋን በግንባታ ደረጃዋ የአፍሪካ ሞዴል ማድረግ ነው ቢለንም እንኳን ለአፍሪካ ለክልል ከተሞች ሞዴል የምትሆን ማድረግ የተሳነው ተቋም ሲሆን ታይቷል።
ቀጣይ አስር ዓመትስ?
የከተማ አስተዳደሩ የአስር ዓመት ጉዞውን እንደሚገመግም ተስፋ አደርጋለሁ። የቀጣይ አስር ዓመት ዕቅዱንም እንደሚነግረን እንጠብቃለን። ያለፈው አመራር የሰራው ስራ የማይረባ ነው ብሎ ከመጣል፣ ቀደም ተብሎ የከተማዋን አደረጃጀት በሜትሮፖሊታን ደረጃ ለህዝብ ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል በሚል ተጠንቶ የተቀመጠውን ጥናት የማየት ዕድል ቢኖር ጠቃሚ ይሆናል። ሰራተኛን በስራው ልክ አለመመዘን፣ የተሻለ አፈጸጸም ያለው ሰራተኛ የተሻለ ተከፋይ የሚሆንበትን ስርዓት አለመከተል እንዲሁም አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አለመስጠትን የመሳሰሉት ችግሮች በቀጣይ አስር ዓመት ሊፈቱ ይገባል።