እጅግ-አየሁ — የፍቅር አርበኛ፣ የትውልድ ልሣን፣ የነፍስ ባለቅኔ!
አሰፋ ሀይሉ
በእርሷ ጥበብ ውስጥ ብዙ ቁምነገሮችን ስላገኘሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ስሟን አነሳለሁ፡፡ አንስቼም ግን አልጠግባትም፡፡ በእርሷ ሥራዎች ውስጥ እጅግ ብዙ ቁምነገሮችን ስላየሁ፡፡ እውነትም ስምን መልዓክ ያወጣዋል፡፡ እጅግ አየሁ፡፡ እጅጋየሁ፡፡ ሽባባው፡፡ ጂጂ፡፡ የነፍስ አንጎራጓሪ፡፡ እንክርዳድ የሌላት፡፡ ልቅም ያለች፡፡ አንስተህ የማትጥላት፡፡ የፍቅር ፀሐይ፡፡ ናት ጂጂ፡፡ በሥራዎቿ፡፡ ብዬ ተነሳሁ ደሞ ዛሬ፡፡ ብዙዋን ጂጂን፡፡ ልሞሽራት፡፡ በጥበብ አምባ፡፡
ብዙ ሙዚቃዎች አሉ ባገሩ፡፡ በዓለሙም፡፡ ብዙዎቹ ግን፡፡ ጤዛ ናቸው፡፡ አላፊ፡፡ ያንድ ሰሞን ብቻ፡፡ ‹‹በደረጃ ሰንጠረዥ ተወዳጅነታቸውን ጠብቀው ለዚህን ያህል ሳምንት ቆዩ›› እየተባለ የሚዳነቅላቸው፡፡ ጉድ የሚባልላቸው፡፡ በወረት የሚደመጡ፡፡ በወረት የሚያከንፉ፡፡ የሳምንታት ሙዚቃዎች፡፡ ከዚያስ? ከዚያ፡፡ እንደ ሸንኮራ አገዳ ተመጠው ያልቃሉ፡፡ ያጣጣማቸው መልሶ አያነሳቸውም፡፡ የጂጂ ሙዚቃዎች ግን፡፡ ለሣምንታት አልተፈጠሩም፡፡ ለሣምንታት ደምቀው፡፡ በሣምንታት አይጠፉም፡፡ ይለያሉ፡፡
እንደ ጥቂት የዓለማችን አይረሴዎች፡፡ እንደ ታደሉት ዕጹብ-ድንቅ አንደበቶች፡፡ የጂጂም ሙዚቃ እንደነርሱ ነው፡፡ የእርሷ፡፡ በአንዱ ሙዚቃ ራሷ ፍቅርን እንደወከለችበት ቃል፡፡ እንደ እናት ጡት ወተት ነው፡፡ አንዴ አጣጥመኸው፡፡ አብሮህ የሚኖር፡፡ በሥሪትህ ውስጥ ያለ፡፡ ከትውልድ ትውልድ የሚቀጥል፡፡ እንደዚያ ነች፡፡ ብዙዋ፣ አይረሴዋ፣ አይጠገቤዋ፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው፡፡
መርጣ ነው የምትሞዝቀው፡፡ ጂጂ፡፡ ከሚከስም ህይወታችን ውስጥ፡፡ ከቶም የማይሞተውን፡፡ ፀሐይን ነው የምታንጎራጉረው፡፡ ውበትን ነው የምትዘፍነው፡፡ ሃቅን ነው የምትገልጠው፡፡ እምነትን ነው የምትኖረው፡፡ ናፍቆትን ነው የምታዜመው፡፡ ጥላቻን መሻገርን ነው የምትሰብከው፡፡ ዓለምን የሚያዳርስ ፍቅርን ነው የምትደርሰው፡፡ እኒህን የሰው ልጅ ወርቃማ አልፋና ኦሜጋዎች ነው፡፡ ስትሞዝቅ የኖረችው፡፡ ጂጂ፡፡ ለዚህ ነው፡፡ ‹‹የነፍስ አንጎራጓሪ›› የምላት፡፡ ጂጂዬ፡፡ የነፍስ አንጎራጓሪ ናት፡፡ ውስጥህ የምትቀር፡፡ በሙዚቃ ኃይል የምትታወጅ፡፡ ዘመንን የምትሻገር፡፡ የማትጥላት እውነት፡፡ የጠለቀች እምነት፡፡ ቦግ ብላ ያልጠፋች፡፡ ላይ-ላይታችንን የሠረገች፡፡ ወደ እማይሞተው የነፍሳችን ሥሪት ዘልቃ የገባች፡፡ አስተዋይ ዜመኛ ነች ጂጂ፡፡ ጂጂዋ ነፍስ ነገር፡፡
የጂጂ ሀቅ ይገርመኛል፡፡ መሆን እንዳለባት፡፡ ከራሷ ምድር፡፡ ከራሷ ሥር፡፡ ከራሷ ቤት፡፡ ከራሷ መንደር፡፡ ከራሷ ቀላል ቃላት ነው የምትበቅለው፡፡ የምትጠቀማቸው ቃላት ከጭንቀት ተምጠው የሚወለዱ አይደሉም፡፡ የዋዛ ናቸው፡፡ ልክ እንደምንኖረው፡፡ ልክ እንደሆንነው፡፡ ልክ እንደሆነችው፡፡ የጂጂ ሀቅ ከዚያ ይጀምራል፡፡
በእነዚያ ቀላላል ለዛዎች ግን ዘመን ተሻጋሪ እውነቶቿን ፈንጥቃ እንድታየው ታደርግሃለች፡፡ ስክን ብላ መስከን ያለበትን፣ ያልተገራውን፣ እውነት ትነግርሃለች፡፡ ሀቅ ቅለትን ይወልዳል፡፡ የጂጂ ሀቅ ቅለት ምን ያህል አስተውላ እንደምታየን ማሳያ ነው፡፡ ብዙ ምሁራን ተሰብስበው፣ በብዙ የጥናት ገጾች ሰንደው የማጨርሱትን ሀቅ ጂጂ እንደ ቀልድ ባልተራቀቁ ጥቂት ስንኞች ቁጭ ስታደርጋቸው አንዳንዴ እደነግጣለሁ፡፡ እንዴ! ጉድ እኮ ነች ጂጂ፡፡
ለምሳሌ ጂጂ በእናት የምትመስላትን ሀገር – ሀገራችንን ኢትዮጵያን – እግር ተወርች ጠፍንጎ አላላውስ ያላት ጥላቻ መሆኑን አስተውላ፣ ከማንም ቀድማ በቀላል ሀቀኛ ስንኞች ስታቀነቅንልህ ታገኛታለህ፡፡ እንደ ዋዛ ነው የምትነግርህ፡፡ መጀመሪያ ልብ አትለውም፡፡ ስትቆይ ነው የሚገዝፈው፡፡ ሀቋ፡፡ የምታንጎራጉረው ለአንድ ሰው ነው፡፡ የምታዜመው የራሷን፣ ከራሷ፣ ለራሷ ነው፡፡ ግን ደግሞ በአንድ ሰው ተወስኖ የሚቀር ብቻ አይደለም፡፡ ለሀገር ምድሩ ሁሉ ነው፡፡ ጂጂን አንዴ ‹‹ይገርማል›› በሚል ዜማዋ መሐል፣ እንደቀልድ መጠላላትን ኮንና ስትሰነኝ አገኘኋት፡፡ እንዲህ እያለች፡-
‹‹አመለኛ ፈረስ ልጓም ያላምጣል
ወደድኩህ ውደደኝ ጠላሁ ምን ያመጣል፡፡››
ይሄ አይገርምም ይሆናል፡፡ መልዕክቱ ግን ብርቱ ነው፡፡ ሁለታችንም በልባችን ያለንን ፍቅር በመካከላችን ማንገስ ስንችል፣ መጠላላታችን ለምን? ምንድነው የመጥላት ትርፉ? እያለች ነው የምትጠይቀው፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይሄንኑ ጥያቄዋን ከሁለት ወደ አራት ስንኞች ከፍ አድርጋ ጫን አድርጋ ስታዜመው ታገኛታለህ፡፡ ‹‹አባ ዓለም ለምኔ›› በሚለው ሙዚቃዋ ውስጥ ጂጂ እንዲህ የሚሉ ስንኞች ታዜማለች፡-
‹‹ምን ሊሰራልኝ ጥላቻ ሃሜት
ሃብት አይሆነኝም ቤት አልሰራበት፣
ልብ ያጨልማል ክፉ ነገር
ልቤን አብሩልኝ ስጡኝ ፍቅር፡፡››
አሁን ከጥያቄ አልፋ ስለ ራሷ ወደ መናገር ተሸጋገረች፡፡ ግን አሁንም ያንኑ ወርቃማ መልዕክቷን ነው ልታሳይህ የምትፈልገው፡፡ ጥላቻ ሀብት አይሆነንም፡፡ ቤት አንሠራበትም፡፡ ልባችንን ነው የሚያጨልመው፡፡ ክፉ ነው ጥላቻ፡፡ ፍቅር ይሻለናል፡፡ ልባችንን የሚያበራልን፡፡ ብላ ጫን ያለ እውነቷን በቀላል ቋንቋ፡፡ የጋራ እውነታችንን እንደ ግሏ እንጉርጉሮ፡፡ አድርጋ ታንቆረቁራለች፡፡ ትገርመኛለች፡፡
እዚህ ጋር ጥላቻ ልብን ያጨልማል፣ ፍቅር ልብን ያበራል ብላ አታቆምም፡፡ ደግሞ ፍቅርን በብርሃን መስላ – ዓለም ስትፈጠር ጀምራ፣ ዓለም እስክትጠፋ የሚዘልቁ የነፍሶቻችንን እውነቶች ትሰብክሃለች፡፡ ‹‹|ፀሐይ›› በሚለው በስፋት ባልተደመጠ አንድ አስደማሚ የሙዚቃ ሥራዋ ውስጥ – ብርሃንን በመውደድ ወክላ፣ ፍቅርን በጸሐይ ተርጉማ – ምኞቷን፣ ናፍቆቷን፣ ተስፋዋን.. እንዲህ እያለች ስታንጎራጉር አገኘኋት ጂጂን፡-
‹‹ማየት ናፈቀኝ ፀሐይ
አንቺን ወገኔ ላይ፣
ደመናውን ገልጠሽ ድመቂ
ብሪ ተሟሟቂ አንፀባርቂ
ያገሬ ፀሐይ ዓይኖቼን በተስፋሽ አንቂ፡፡››
ጂጂ ገና ተፈትታ ያላለቀች የሀገር ቅኔ ነች፡፡ ጂጂ ጥበብን ለፍቅር መስበኪያነት ያዋለች የፍቅር ገዳይ ነች፡፡ የማታረጅ የትውልድ ልሣን፡፡ ዘመን ተሻጋሪ የነፍስ አንጎጓሪ፡፡ ፍቅርን፡፡ ብርሃንን፡፡ እውነትን፡፡ ውበትን፡፡ ደግነትን፡፡ ይህ ሁሉ የማይሞት ነገራችን፡፡ በውስጣችን ያለው፡፡ አውጥተን ያልዘራነው፡፡ ያልተካፈልነው፡፡ በመሐላችን ያላነገስነው፡፡ ይህ ሁሉ ባርኮት፡፡ ይህ ሁሉ ሲሳይ፡፡ ይሁን ብለን ከፈቀድንለት፡፡ አብሮን ይኖራል፡፡
ግና አድምጠኝ ወገኔ፡፡ ያልዘሩት አይታጨድም፡፡ መጀመሪያ ፍቅርን እንዝራ፡፡ ልባችንን እንክፈት፡፡ ለፍቅር ቦታ እንስጥ፡፡ ፍቅርን እናኑር፡፡ እና በፍቅር እንኑር፡፡ ነው የምትለው፡፡ ባለቅኔዋ ጠይም ውቢት፡፡ ‹‹ሰም’ና ወርቅ›› በሚለው የሙዚቃ መድብሏ ውስጥ ጂጂ (እጅግ-አየሁ) እንዲህ እያለች ታዜማለች፡-
‹‹ውበት ባለችበት ውበት ትኖራለች
ፍቅርም ባለችበት ብርሃን ትኖራለች፣
ደግነት ባለበት ደግነት ይኖራል
ኑር ብለው ያኖሩት ካኖሩት ይገኛል፡፡››
ደግሞ ጂጂ መጥላትን በመውደድ እንተካ፣ ጥላቻ የትም አያደርሰንም እያለች ስትሰብክህ ራሷን ደብቃ አይደለም፡፡ ጂጂ ከሀቅ የተቀዳች የነፍስ ሀቅ አንጎራጓሪ ነች የምልበት አንዱ ምክንያትም ይኼ ነው፡፡ ጂጂ ሰው ላይ አመልካች ጣቷን ብትጠቁም፣ ሶስቱ ጣቶቿ መልሰው ወደ ራሷ እንደሚጠቁሙባት የምታውቅ ልባም ነች፡፡ ጠቢቡ ሠሎሞን ‹‹የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው›› እንደሚል፡፡ ጠቢብ ነፍሷ ራሷ ላይ ዓይኖቿን እንድትጥል የጥበብ ቀንዲሏን ያበራችላት አስተዋይ ወጣት ነች፡፡
እና እንደ ጲላጦስ እጆቿን ታጥባ ንጽህናዬን ልመስክርልህ አትልም፡፡ እኔ ጻድቅ፣ አንተ ኃጥዕ የሚል ‹‹ሂፖክሪሲ›› ጂጂ ጋር ሥፍራ የለውም፡፡ ልክ እንደ ወገኖቿ ሁሉ፣ እርሷም የኃጥያቱ ተካፋይ መሆኗን፣ ራሷን በመጥላቱ ኩነኔ ውስጥ ጨምራ ታሳይሃለች፡፡ ለምሳሌ ‹‹አባ ዓለም ለምኔ›› በሚለው ሥራዋ ውስጥ ራሷን እንዲህ ስታሳይህ ታገኛታለህ ጂጂዬ፡-
‹‹አባ ዓለም ለምኔ አባ ዓለም ለምኔ
ጀንበር ወጥታ አትገባም ሳልሠራ ኩነኔ፣
ሰው ወደደኩኝ እያልኩ ደሞ እጠላለሁ
ደሞ ይከፋኛል እደሰታለሁ…፡፡››
እንዴ! ይህች ሴት ለእኔ በእውነት ጥበብን የተሞላች፣ ጥበብን የምትሰብክ ሴት ብቻ አይደለችም፡፡ አንዳንዴ ልክ በብሉይ ዘመን ወደ ህዝባቸው ብቅ እያሉ ሊመጣ ያለውን እንደሚያስጠነቅቁ፣ የተሰበረውን የወገናቸውን ልብ ጠግነው መንፈሱን እንደሚያነሳሱ፣ ዘመን ተሻጋሪ እውነትን ለህዝባቸው እንደሚመሰክሩ፣ እንደ መንፈሳዊ ነብያት ሁሉ ትሆንብኛለች አንዳንድ ጊዜ ጂጂ፡፡
እውነት ምን ጊዜም እውነት ነው፡፡ እውነት አይቀየርም፡፡ ሀቅ አይታበልም፡፡ ጂጂም ደግማ ደግማ ያን ሁልጊዜ-ኗሪ እውነት ነው የምትናገረው፡፡ ዘመኗን ከጥላቻ ልትዋጅ፡፡ የዘመኗን ደዌ ልትፈውስ፡፡ የመለያየትን ግንብ በሙዚቃዋ ኃይል ልትንድ፡፡ ደግሞ – ሺህ ነቃፊዎች ቢሳሉባት፣ ረዣዥም ባለጊዜ እጆች ቢነቀንቁባት – ጂጂ – ከእውነቱ ውልፍት የለም፡፡ እንደ ሀቀኛ ካህን – እንደ እውነተኛ ነብይ – ያመነችበትን፣ የተገለጠላትን፣ አስተውላ የደረሰችበትን እውነት አደባባይ ወጥታ የምታውጅ የሙዚቃ ጀግና፣ የሀቅ መስካሪ፣ የነፍስ አንጎጓሪ ናት ጂጂ፡፡
‹‹እናት ኢትዮጵያ›› በሚል የሙዚቃ ሥራዋ ውስጥ – ደግማ ደጋግማ የነገረችንን ሀገራዊ እውነት፣ የመጨረሻው ከፍታ ላይ አድርሳ ታሳርገዋለች ወደ ኢትዮጵያ ሠማይ፣ ወደ ኢትዮጵያ ምድር፣ ልብ ላለው፣ ለሚሰማ፣ ለሚያይ፣ በጥበብ ለሚነካ ወገን ሁሉ በሚሰማ ተስረቅራቂ ልብ፡፡ እና ወኔ፡፡
ብዙ ያወቁ የረቀቁ የላቁ የምንላቸው አዋቂዎቻችን ያልደፈሩትን፣ ጥበቡ የራቃቸውን፣ ወኔ ያጡበትን ታላቅ እውነት ነው ጂጂ በ‹‹እናት ኢትዮጵያ›› ስንኞቿ – በትኩስ ለዛ፣ በማይበርድ ወኔ፣ በቀላልና ግልጽ ቋንቋ አደባባይ ወጥታ ላገር ለምድሩ የመሰከረችው፡፡ ያን የጂጂን እውነት፡፡ ብዙዎቻችን ሰምተነዋል፡፡ ግን የግድ ይለናል፡፡ ደግመን ደጋግመን ማድመጥ፡፡ የማይሞት እውነት ነውና፡፡ የጥበብ ንግሥቲቱ፡፡ እንዲህ ነው ያለችው፡-
‹‹ዘመን አመጣሽ የዘር በሽታ
መድኃኒት አለው የማታ ማታ፣
ሀገር በወገን እንዴት ይረታ
ፍቅር በነገር እንዴት ይፈታ፡፡
‹‹ዘር ሳይለያየን ወይ ሐይማኖት
ከጥንት በፍቅር የኖርንባት፣
እናት ኢትዮጵያ ውዲት ውዲቷ
በጎጆ አያልቅም ሙሽርነቷ፡፡
‹‹… እናት ራቁት እንዴት ልይሽ
ክብርሽ የት አለ አንድነትሽ፡፡››
እንዲህ በሁለት ገጽ አንስተህ አትጨርሳትም ጂጂን፡፡ ጂጂ ብዙ ነች፡፡ ብዙ የምታሳይ፡፡ አጥንተህ የማትጨርሳት፡፡ እንደ ሀገር የሰፋች፡፡ እንደ ወገን የበዛች፡፡ ብዙ፡፡ እንዲህ እላታለሁ ስሟን ሳሞካሸው፡፡ ጂጂያችን፡፡ እጅጋየሁ፡፡ በአንቺ፡፡ እጅግ-ብዙ-አየሁ፡፡ ስለ ጂጂ ሥራዎች በማስታወሻዬ ከትቤ ካኖርኳቸው ሶስት መወድሶች ይኼ የመጀመሪያው ነው፡፡ ሁለት ይቀሩኛል፡፡ አንድ ቀን፡፡ እግዜሩ ካለልኝ፡፡ ሁለቱን ማስታወሻዎቼን ደግሞ ይዤ ብቅ እል ይሆናል፡፡ የዚያ ሰው ይበለን፡፡
እስከዚያው፡፡ አንድ ሆና ብዙ፡፡ ብዙም ሆና ደግሞ፣ ራሷኑ አንድ፡፡ አንድ የማትተካ እጅግ-አየሁ ሽባባውን፡፡ አንድ ጂጂዬን፡፡ መሆን የተሳካላትን፡፡ ይህችን የዘመናችንን የፍቅር አርበኛ፣ የትውልዳችንን የጥበብ ልሣን፣ የነፍሳችንን ባለቅኔ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ በሥራዎቿ ሁሉ አብዝቶ ይባርካት፡፡ የጥበብ ሁሉ ምንጭ የሆነ የፍቅር አምላክ ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ በመግባት በመውጣታችን አይለየን፡፡
እናት ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም – በፍቅር ትኑር!