>
5:21 pm - Sunday July 20, 7332

ምርጫ...የክህደት ወጥመድ እንዳይሆን። (ዐቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ፤)

ምርጫ…

       የክህደት ወጥመድ እንዳይሆን።

ዐቢይ ኢትዮጵያዊ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ፤

        ከታሪክ ትምህርት እንደተገነዘብነው ሕዝባዊ  ምርጫ በዕውነት ጥበቃ ክንድ ውስጥ ለመሆኑ፣ዋና ዋስትናው የሕግ የበላይነት መኖሩን ማረጋገጥ ብቻ ነው።ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ትክክለኛ ሕገ መንግስት ሳይሆን በሕዝብ የፀደቀ የሕዝብ ሕግ(ሕገ ሕዝብ)ወሳኝ ነው፤በ አሁኑ ጊዜ ሕገ ሕዝብ እንደሌለን ቢታወቅም።ህገ ሕዝብ እንዳይኖረን ባለፉት አርባ ስድስት ዓመታት በደም ሲያጨማልቁን እና ስንቶቹን ኢትዮጵያውያንን በግድያ ቀጥፈው ያሳጡንና ዛሬም ድረስ የሚገድሉን እና የሚያጋድሉን ቀንደኛ የኢትዮጵያ፣የሥጋ ትሎችን እዩዋቸው እስኪ፤ አጠገባች ሁም አሉ።የእነርሱ ሴራ ባይኖር ፓርላማው ከሕገ ሕዝቡ ሕገ መንግሥትንና ህግጋትን ለመቅረፅ፣ፖሊሲዎችን ለመንደፍና ዝርዝር ደንቦችን ያለ ሕገ ሕዝብ የአንቀፅ ተቃርኖ ለማውጣት አያስቸግረውም ነበር  ። ሕገ፡ሕዝብ ሳይኖር ምርጫን ማሰብ፣የህግ የበላይነት ሳይኖር ያለዋስትና ያለሕግ ከለላ፣የሕዝብን ሥልጣን ለመንግሥት ወይም ግለሰቦች እንደመስጠት ነው፤ያለደረሰኝ ዕቃ እንደመሸጥ፤ኣሊያም ያለውል ወይም  ያለስምምነት እና  ያለፊርማ የሥራ ኮንትራትን በወጥመድ ውስጥ እንደመጀመር ነው።ሕዝባዊ ሐቁ፤ሕገ መንግስትማ ለተቀጣሪው ለመንግስት የሚጥቅመው መራጃ ሲሆን፣ለሕዝቡ ግን በሕግ የሚረገጥበት፤መንግስትም የሚጠላውንም የሕብረተሰብ ክፍል እንደፈለገው የሚያደርግበት ለመሆኑ ዛሬም ድረስ በብሌናችን በ አደባባይ እንደምናየው ነው። ምርጫ፣(ያለ ስሌት ወይስ…)የሚመረጠውን ነገር ለይቶ መምረጥ ማለት  ቢሆንም፤መራጮችም ሆኑ ተመራጮች ከሌሉ ግን፣ምርጫው  ሕዝብን የሚያሳዽ የክህደት ወጥመድ ይሆናል።
እነሆ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሕግን የበላይነት ለማስፈን ለዘመናት እየታገለ በነፍስ ወከፍ የተወራረሰውን ነብስ፣ ሽልንግ በማትሞላ የተባረከችም ሆነ ያልተባረከች ዕድሜ፤ የሚተካላትን ትውልድ ለመዝራት፣በሰላምና በደስታ እየኖረ ሕይወቱን ሊጠቀምባትና ሊኖርባት ይታገላል። ይህ የህልውና ትግል ከግለሰብ አልፎ፤ቤተሰብን ተሻግሮ እና ሕብረተሰብ ውስጥ አድጎ አገርን እያስጠራ ይኖራል፤ጥሪውም  የሰብዓዊነታችንን ማንነት ወደ ዓለም አቀፋዊ የዕውቅና ደረጃ በከፍታ ለማድረስ ነው፤ኢትዮጵያዊነትን።
ከዚህ የታሪክ ሐቅ አንፃር ነው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሰብዓዊነታቸው ያሳለፉት የኑሮ ደረጃ ከፍታ በደስታ እና በመከራ የነበር። ተብሎ ለማጠቃለል ካልሆነ በቀር፣መረራውን፥መከራን የሚመርጥ የቱ ነው ጤናማ ያልሆነ ሰው ብቻ ነው፣ለምን ቢባል መምረጥ  ስለሚሳነው። ያለበለዚያማ ጤነኛ የሆነ ሰው ሁሉ ተሳስቶ ካልሆነ በቀር፣ አሊያም ሆን ብለው ጥቅም ፈላጊዎች፣መቼም ገንዘብ የተጫነች አህያ የማትከፍተው ዋሻ የለምና ከደስታ ይልቅ መከራን እንዲመርጥ አይሻም።የመከራን ቅርፅ ተንኮለኛው በተለያዩ ገፅታዎች አሽሞንሙኖ በመሸፋፈን ወይም አባብሎ በማጉረስ፣ አሊያም በጉልበት በማጋት የግድ እንዲመርጡ ይደረግ ይሆን እንጂ ፍላጎቱ አይሆንም። ለምን ቢባል የሰው ልጅ ሀሳቡ አይቆምምና ሰውን ሰው ያደረገው አዕምሮው ስለሆነ፣ ፍላጎቱ ያድጋል።ይህ በቋንቋ የሚነገረው አስተሳሰቡ ደግሞ ሁሌም የሚቀርቡለትን ሁሉ አማርጦ ያደርጋል፤እናም ምርጫን አይተወውም፤የዕለት ተዕለት ፍላጎቱም ያለምርጫ አይኖርም።
አንድን ነገር ለመምረጥ ደግሞ ብዙ መንገዶች ቢኖሩ እና ሌላ ክዚህ ጋር የማይገናኝ ነገር ለመምረጥ ሌሎች መንገዶች ቢኖሩ፣ሁለቱን አንድ ላይ መምረጥ ባይቻል፣ ከሁለቱ አንዱን ለመምረጥ[ሀ እና ለ]መንገዶች አሉ ማለት ነው።ይህን ቀላል ቀመር የማያውቅ መ+ደ+መ+ር ገብቶኛል ብሎ [ሀ + ለ]ነው፣እኔ አሻግራችኋለው  ስለተባለ በለበጣ ከተናገረው ጋር እንደቀልድ ጉዞ መጀመሩ ያጠያይቃል፤እናም ክፉነት ባይሆንም ላንዳፍታ ቆም ብሎ ቀመሩን ማሰቡ በጎ የስሌት ማስተዋል ነው የሚያሰኘው።
ለበጎ ማስተዋል ሠለጠኑ የምንላቸውን ሀገሮች ከማንሳታችን በፊት ግለሰቦችን በጥንቃቄ ብንመረምራቸው በአብዛኛው አንዱ ከሌላው ልምድ የተማረው፣አሊያም የገለበጠው ዕውቀት መሆኑን እንገነዘባለን፤እንጂ በተፈጥሮ የሚገኝ ፀጋ ወይ በልጅነት ይታያል አሊያም በስተእርጅና ይጀምራል፤ ከእነዚህ የተፈጥሮ ሕግጋት ውጭ አይሆኑም፣ቤትሆቭን እና ሞዛርትን ይመለከቷል፤አንዱ ተምሮ፣ሌላው በተፈጥሮ የነበራቸው የሙዚቃ ዕውቀት ነው።
ወደ ተነሳንበት ርዕሰ፡ጉዳይ ስንመጣ የአገራችንን ጉዳይ አስመልክቶ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ መንግሥት ለማቋቋም በመዘጋጀት ላይ ትገኛለች፤ በቀላል አቀራረብ ኖሮ የማያውቀውን የሕዝብ መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና ትላለች።ለዚህ መልካም ተግባር ሰዎች በአንድ ልብ ሆነው ሲነሱ ርኩሳን መናፍስት ደግሞ ዝም ብለው አይመለከቱም፤በሰዎች ልብ ሰርፀው ርኩስ ተግባር እንዲፈጸም ያደርጋሉ።ዜጎች ግን ይሰበሰቡና እነዚያ እና እነዚህን ሰዎች በሰውነታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው ካላቸው ዕውቀትና የዕድሜ ተመክሮ አንፃር በመንግሥትነት ያገለግሉኛል በለው በኮንትራት ቀጥረው ለተወሰኑ ዓመታት ያሰሩላቸው ዘንድ በግልፅ ጨረታ አወዳድረው ይመርጧቸዋል፤ይህ ነው ቀላሉ ዕውነታ።ዳሩ ግን በመንግስትነት በሚከፈቱ ቀዳዳዎች ነገሮች እየተደራረቡ በጊዜ ውስጥ ሲደራረቡ በሌሎች ተቀጥላዎች በላይ በላዩ ላይ ሲደማመሩ ነው የሚወሳሰበው።ለምሳሌ ሶስት የተለያዩ ነገሮች ከተደመሩ ውጤት አይኖራቸውም፤ቢያንስ ሁለቱ በአሃዝ መገለጽ አለባቸው ሦስተኛውን ለማግኘት፣ 
125098052_3731122983567318_6868060100735916836_o.jpg
ሁለቱም አሃዞች ካልሆኑ ግን መደመሩ በስብስብ ስሌት መሠረት ለመፍታት ሕዝብ የሚችለው አይሆንም ለመረዳትም፣እንደሴካ እና ኮንከር ስላልሆነ[ሀ + ለ ]መ፣ ተራ የድምር ጨዋታ ባለመሆኑ።
በቀላል የአገላለፅ በምሳሌ ሳስቀምጠው፤ጫማ ሊገዛ የፈለገ ግለሰብ የጫማውን ዋጋ ሃያ አምስት ብር ብቻ መሆኑን አውቆ ሃያ አምስት ብር ብቻ ነው ብሎ ከወሰነ ግምቱ በመሳሳቱ ውድቅ ፖለቲከኛ ያደርገዋል።በእጁ ገብቶ እስከተጫመው ድረስ የአርባ አምስት ብር ድምር ዋጋ ካወጣ፤ ዋጋው ይሄ ነው ብሎ መናገር ይቻለውም።ወደ ኋላ የቀረ ስሌት ነው ማለት ነው፤እናም ድብቅ መኖሩን ማወቅ አለበት።እኛ ሰዎችን ስንመርጥ በጣም በጥንቃቄ መምረጥ አለብን፤መጠንቀቅ አደጋን ይቀንስ እንደሆነ እንጂ እንደማያስቀረው ብናውቅም።እንዲሁም ያልተማሩት መስዋትነት ነው እያሉ ቀስ በቀስ በሚጨመር ዋጋ እንደማያስከፍሉን ቢያንስ እርግ ጠኞች መሆን ስለሚኖርብን ነው።ለዚህም ከሁሉም ችግር መፍቻዎች ይበልጥ ለመፍትሄነት የሚረዳን ብስል ግልፅነት ብቻ ነው፤ዕውነትም ነጻ ታወጣለችና።
የተንኮለኞች የመጀመሪያ ማፈሪያ  ርምጃቸው ግልፅነት ብቻ ነው፤የሚነገረውና የሚባለው የፈለገውንም ያህል መስዋዕትነት  ቢያስከፍሉንም፣ ግልፅ ከመሆናቸውም በፊት ሆነ በኋላ እንዲታወቁ ከተደረገ፤ስለዕውነተኛነታቸው ምስክርነትም አያስፈልጋቸውም።ዛሬ ስንት ጉዳዮችን ማወቅ ሲገባን እና የዜግነት መብታችን መሆኑ እየታወቀ ተከልክለናል፤ምርጫ እነርሱን ወይም እኛን አይመለከተንም የሚባል ጉዳይ አይደለም።ሕዝብ በግልፅ ጨረታ በኅላፊነት ቅን ሰዎችን ለሕዝባዊ ኃላፊነት አወዳድሮ ለመቀጠር ይፈልጋል፤ይህን ሕዝባዊ ቃልኪዳን የመግባት መንፈስ ጥቅመኞች ግን ሊሾሙና በሕዝብ ላይ ክንዳቸውን ለማሳየት በአጎብጓቢዎቻቸው ሴራ ሊደባብቁት ስለሚፈልጉ፣ሥሙን ፖለቲካ ብለውታል።
እኛ ግልፅነትን ለሕሊናችን ንጽህና መመሪያችን ያደረግን ሰዎች ግን፣ሕዝብን ሌት ተቀን በመንግሥትነት እናገለግላለን ያሉትን ሰዎች ቀድሞ ሕዝብ ይወቃቸው እንላለን።ማሕበራዊ ሕይወታቸውን፣ሁለገብ የአዕምሮ ችሎታቸውን፣ ዕውቀታቸውን፣ የአስተዳደር ልምዳቸውን፣ታማኝነታቸውንና ዓላማቸውን አቅርበው የሕዝብ ታዛዥ ለመሆን አሁን ያመለክቱትንም  ከወዲሁ በአደባባይ ካልተቆጣጠሩት፣ ምርጫውን በስሌት ቅርፅ ይሰጡትና  ድምፁን ለማጭበርበር የምርጫ ሥልጣኑን ይቆጣጠሩታል።ለነገሩ ዕምርጫ ትርጉሙ የሚመረጠውን ነገር ለይቶ ለመምረጥ ማወዳደር ማለት አይደለምን።ካለበለዚያ ምርጫውም ሆነ ተመራጮች ከሌሉ ግን፣ምርጫው የክህደት ወጥመድ ይሆናል፤እስከዛሬም የሚሊዮን ሰዎች ያስገበረን ይኼው ሞላጫ የምርጫ ሂደት ነው።
ስለዚህም ምርጫው በግልፅ እንዲኖር እና ተመራጮችም በሕጉ መሠረት በሕዝብ እንዲመረጡ ሁኔታዎች ከተመቻቹ፣ምርጫ የነፃነትን ጎዳና ይከፍታልና፣በፍፁም የክህደት ወጥመድ አይሆንም።

Filed in: Amharic