>
5:21 pm - Saturday July 20, 2475

የአጤ ምኒልክን ስም እንዳታነሱት፤  ታላቅ ስሙን ታረክሱታላችሁ! (ጌታቸው ሽፈራው)

የአጤ ምኒልክን ስም እንዳታነሱት፤  ታላቅ ስሙን ታረክሱታላችሁ!

ጌታቸው ሽፈራው

* “አድዋን አወድሱ ምኒልክን አታንሱ!” ላላችሁ ላስባላችሁ….!!!
 
አጤ ምኒልክ ተቀናቃኙን ያከመ ሩህሩህ ሰው ነው። ለሀገር ጥቅም ሲል  ተፋልሞ አሸንፎት፣ የቆሰለን ባላንጣውን ያከመ  ሩህሩህን የዚህ ዘመን ጨካኝ ካድሬ ስሙን ቢያነሳው ያረክሰው እንደሆነ እንጅ አያከብረውም። ህፃናትና እናቶችን አስገድሎ በስካቨተር በሚቀብር፣ ንፁሃንን በማንነታቸው የሚያፈናቅል ካድሬ አጤ ምኒልክን ሊያከብረው አይችልም። ይህ የዘመናችን ጨካኝ ካድሬ የአጤ ምኒልክን ስም ሊያነሳ የሚያስችል ሞራል የለውም። እንዳያነሳው! አደራ በሉት!
ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የኢትዮጵያን ታላቅ መሰረት አስቀምጦ ያለፈ ጀግና ነው። ኃያል ነኝ ከሚል  የውጭ ጠለት ጋር ታግሎ ሀገሩን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ዘር እንዲኮራ፣ ለትግል ስንቅ እንዲይዝ ያደረገ ዓለም አንዴ ያገኘችው የክፍለ ዘመን ጀግና ነው። በዚህ ዘመን  ኢትዮጵያን እያዋረደ ያለ  ስግብግብ ካድሬ በየክልሉ የአጤ ምኒልክን ስም ቢያነሳ ክብር ይቀንስ ካልሆነ ቅንጣት ሊጨምርለት አይችልም።
አጤ  ምኒልክ ለኢትዮጵያ በርካታ ቴክኖሎጅን ያስተዋወቀ፣ በዚህ ወቅት ያሉትን ዋና ዋና  መንግስታዊ ተቋማት  ያቋቋመ ታላቅ መሪ ነው። ሰበብ ፈልጎ፣ ተቧድኖ  እነዚህን ተቋማት ሲዘርፍ የሚውል፣ ምኒልክ ለሀገር ያቋቋማቸውን ተቋማት በግሉ፣ በማንነቱ ለመጠቀም የሚሰራ፣ ለቴክኖሎጅና ለውጥ ነቀርሳ የሆነ ካድሬ ድግስ አድርጎ የአጤ ምኒልክን ስም ቢያነሳ ራሱን ያስተዋውቅበት ካልሆነ በስተቀር ለአጤ ምኒልክ ትንሽ ነገር አይጨምርለትም።
እነ ምኒልክ ከውጭ ኃይል ተከላክለው ባቆሟት ሀገር፣ እነ ምኒልክ ሀገር በማስከበራቸው ምክንያት ሀገር ተከብራ፣ ከተማዋ የአህጉር ዋና ከተማ እንድትሆን ሲያደርጉ፣ ልዩ ጥቅም፣ ግል ጥቅም እየጠየክ የታላቁን ዳግማዊ ምኒልክ ስም ብታነሳ ታሳንሰዋለህ። ምግባርህ አይመጥነውም። አላማህ ከእሱ ጋር አይደለም።
አጤ ምኒልክ ሌላውን ሕዝብ በመጥላት ማሕበራዊ ሚዲያ ያጀገነው አይደለም። ሚዲያ በሌለበት፣ ዓለም ብዙ በማትተዋወቅበት ዘመን ሳይቀር ዓለም ፈልጎ ያወቀው፣ ያከበረው ታላቅ ሰው ነው። የወራሪዎቹ ጥሊያን ሕዝብ “ቪቫ ምኒልክ” ያለው ጠላት ሳይቀር የወደደ፣ ያከበረው እድለኛ ትውልድ ብቻ አልፎ አልፎ ጣል የሚደረግለት መሪ ነው።  ዛሬ ማንም ጥላቻ ያናወዘው ስሙን ለማንሳት ቢፈራ “ጥሩ አድርገሃል እንዳታነሳው” ማለት አለብን። ከክፉ ስራው እስካልተመለሰ ድረስ የዚህ ዘመን ሸንሻኝ፣ በታኝ፣ ገዳይ፣ አስገዳይ፣ ጨካኝ፣ ድንቁርና ኩራቱ የሆነ  የእምዬ ምኒልክን ስም እንዳያነሳ። ቀጣዩ ትውልድ ስሙን ይፈልገዋል።
የዚህ ዘመን ቅራቅንቦ የታላቁን አጤ ምኒልክን ስም ቢያነሳ  ክብሩን ዝቅ ያደርገዋል እንጅ የሚጨምርለት ነገር አይኖርም! የአጤ ምኒልክን ስም እንደ ቅርስ እንፈልገዋለን። ስራችሁ ስሙን ለማንሳት የማይመጥነው እንዳታነሱት። የአጤ ምኒልክ ስም ለእናንተ ጥቃቅን የዳስ ፖለቲካ አይመጥንም። ግዙፍ ስሙን ጎትታችሁ እንዳታረክሱት። አትችሉትም። አታውቁትም።
አደራ አደራ አደራ
Filed in: Amharic