እውነትን መፍራት ወይም መጥላት – Alethophobia፤ ከመንግስት ወደ ማህበረሰብ እየተወረሰ ያለ ህመም
ያሬድ ሀይለማርያም
ስለ እራሳችን ወይም ስለ አገራችን ወይም ስለ ሃይማኖታችን ወይም ስለ ባህላችን ወይም ስለ ብሔራችን የሚነገሩ እውነቶችን የመቀበል አቅም ወይም ፍላጎት ማጣት በእንግሊዘኛው Alethophobia (The inability to accept unflattering facts about your nation, religion, culture, ethnic group, or yourself) የሚባለው የባህሪ መገለጫ ብዙን ጊዜ የፖለቲከኞች ወይም የመንግስት ኃላፊዎች ወይም የማህበረሰብ መሪዎች ህመም ብቻ ይመስለኝ ነበር። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ በዚህ የአስተሳሰብ ችግር የሚታወቁት እና ባህሪውም ጎልቶ የሚስተዋለው በንዲህ ያሉ ሰዎች ላይ ነበር። አሁን ደግሞ ያንን ችግር በማህበረሰብ ውስጥም ጭምር ስር እየሰደደ እና አንዳንዴም ጎልቶ ሲወጣ ይስተዋላል።
ነገሩ ይህ ባህሪ ጎልቶ የሚታየው ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ በራቀ ወይም እራሱን በዘር፣ በኃይማኖት፣ በቀለም ወይም በሌላ የማንነት መገለጫዎች ለይቶ እና በጎራ ፈርጆ በማንነት መስመሮች በታጠረ ማህበረሰብ ውስጥ ነው። ምክንያቱም ስለራስ የተሳሳተ ምልከታ ወይም የወል ማንነቶች የሚፈጠሩት ስለራሳችን ወይም ስለ ታቀፍንበት ክብ ካለን የማይለወጥ የማንነት ምልከታ ወይም ትርጓሜ ወይም fixed beliefs ነው። ያ የማይናወጥ ስለ እኛነታችን ወይም ስለ ቡድናችን ያለን እምነት ወይም ምልከታ ኃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ወይም ጎሳዊ ወይም ጽዎታዊ ወይም ሌሎች ውጫዊ የማንነት መሰረትን መነሻ ያደረገ ነው። ይህ አይነቱ በውስጣችን ያለው የማይናወጥ እውነት (fixed beliefs) ባብዛኛው ሳይንሳዊ እውቀትን መሰረት ያደረገ እውነት አይደለም። ስለዚህ ለምርምርም ሆነ ለፍተሻ ክፍት አይደለም። ከሳይንሳዊ እውቀት ጋር ይጋጫል። በእውቀት ከሚገኝ እውነት ይልቅም በስሜት በሚገኝ እምነት የታጨቀ (emotional baggage)።
ስለዚህ በዚህ መልኩ የተገነባ ስብዕናም ሆነ ማንነት እውቀትን እና እውነትን ይፈራል። ምርምርን ይሸሻል። እውቀትና እውነት ምንጫቸው ምርምር እና በማስረጃ የሚረጋገጡ ኩነቶች ናቸው። ስለዚህ በውስጣችን ያሉ እና አብረውን አድገው ያረጁ የማንነት ትርክቶችን ወይም እውነቶችን ለእውቀት እና ለእውነት ማጋለጠ ለብዙዎች ማንነትን የመካድ ያህል ትልቅ ፈተና ስለሚሆን ብዙዎች የሚመርጡት እውነትን መሸሽ ወይም መፍራት ወይም መካድ ነው። ስለአገራችን፣ ስለ ኃይማኖታችን፣ ስለ ብሔራችን ያሉን የማይናወጡ ምናባዊ ምልከታዎች እና መገለጫዎች ሁሌም የተነኩ ሲመስለን ነብር እንሆናለን።
ይሄን ሁሉ ያስቀባጠረኝ ሰሞኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ ከበርካታ ሰዎች፤ ምሁራንን ጨምሮ የተሰነዘሩት ምላሾች ናቸው። ድሮ ድሮ አምነስቲም ሆነ ሌሎች የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጸመ ስለሚሉት የመብት ጥሰት ጠንከር ያለ መግለጫ ሲያወጡ የሌባ ሻይ እንደጠጣ የቋጥ የባጡን ይለፈልፍ የነበረው የአገዛዝ ሥርዓቱ ነበር። ወያኔ ከምትታወቅበት ባህሪዋ አንዱ ይሄ የAlethophobia ችግር ነበር። አንድም ቀን ወያኔ መራሹ መንግስት በሰብአዊ መብት ድርጅቶች የሚደርስበትን ነቀፌታ በአግባቡ ፍሬ ጉዳዩ ላይ አተኩሮ መልስ ሲሰጥ ሰምቼም፤ አይቼም አላውቅም።
ኢሰመጉ መግለጫ ሲያወጣ የመንግስት ምላሽ ሁሌም የሚያስቅ እና የተለመደ ነበር። “እራሱን የሰብአዊ መብት ድርጅት ብሎ የሚጠራው፤ ኢሰመጉ” ብሎ ይጀምርና በመግለጫው ላይ የተፈጸሙት ጥሰቶች አንዳቸውንም ሳያስተባብል በኢሰመጉ እና በአመራሮቹ ላይ የስድብ ናዳውን አውርዶ እና ተራግሞ ኢትዮጵያ በሰብአዊ መብት እረገድ ተአምር ማስመዝገቧን በማሳሰቢያ መልክ ገልጾ ይዘጋ ነበር። አላማውም ግልጽ እና ግልጽ ነው። ኢሰመጉንም ሆነ ሌሎች በመብት ትግል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ማሸማቀቅ እና ማስፈራራት ነበር። ግና ማን ፈርቶ።
ዛሬ ያ እውነትን የመፍራት እና የመሸሽ ዛር ልበለው ህመም ከመንግስት ላይ ወርዶ ወደ ማህበረሰቡ ቀስ እያለ እየገባና ስር እየሰደደ ይመስላል። ለዚህም አምነስቲ ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል፤ አሁን ደግሞ በአክሱም ስለተፈጸሙት ጭፍጨፋዎች ያወጣው ዘገባ ይህን ባህሪያችንን ጸሃይ ላይ ያሰጣው ይመስለኛል። በአምነስቲ ዘገባ ላይ የሚቀርቡት ነቀፌታዎች ከሞላ ጎደል ሁለት ይዘት ያላቸው ናቸው።
1ኛ/ አምነስቲ ሁለቱም ዘገባዎች ላይ መረጃዎቹን ያገኘበትን መንገድ ሲያስቀምጥ በስልክ እና ከአገር ተሰደው ከወጡ ሰዎች በተገኘ ቃለ ምልልስ የሚል ነገር ስለገለጸ እንዴት ሥፍራው ላይ ሳይገኝ በስልክ የሰበሰበውን እና ከስደተኞች ያገኘውን መረጃ መሰረት አድርጎ እንዲህ ይደፍረናል የሚል ነው።
2ኛ/ ሌላው መቃወሚያ ደግሞ ትንሽ ነውርምና ሃሰት የተቀላቀለበት እና ባልተረጋገጠ መረጃ ላይ በመመስረት እነዚህን ሪፖርቶች የሠራውን የአምነስቲን የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ፤ አቶ ፍሰሐ ተክሌ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው።
እስከ አሁን ባየኋቸው ቅሬታዎች ውስጥ አንድም ሰው፤ መንግስትን ጨምሮ በመግለጫው ላይ የተጠቀሱት ክስተቶች ሃሰት ናቸው ብሎ በሌላ ማስረጃ የቀረበውን ሪፖርት ውድቅ ሲያደርግ አላየሁም። ግልጽ ለማድረግ ቦታ፣ ሰዓት እና ማንነት ተጠቅሶ አንድ ሰው እገሌ በተባለ አካል ተገድሏል የሚል ሪፖርት ሲቀርብ እሱን ውድቅ ማድረግ የሚቻለው አንድም ያ ሰው በህይወት ያለ መሆኑን በማስረጃ በማረጋገጥ አለያም ያ ሰው የሞተበት አኳኋን በተገለጸው መልኩ ሳይሆን በሌላ መሆኑን ማሳየት። በጥይት ተመቶ ሞተ የተባለው ሰው በኮቪድ ከሆነ የሞተው ያንን አሳይቶ የቀደመውን ሪፖርት በሌላ እውነት መጣል ይቻላል። ሃሰተኝነቱን ማጋለጥ ይቻላል። ያንን ማንም ሲያደርግ አላየሁም።
ኢሳያስ ሲነካ የሚያንዘረዝራቸው እና የኤርትራ ውለታ ያለባቸው ሰዎች ለምን የሻቢያ ጦር ስሙ ተነሳ በልው አምነስቲን እና ሪፖርት አቅራቢውን ሲራገሙ እና አቶ ፍሰሐን በሃሰት ሊወነጅሉት ሲሞክሩ ሳይ ከላይ የጠቀስኩት እውነትን የመፍራቱ በሽታ በሁለንተናችን መሰራጨቱን ነው የተረዳሁት። ሪፖርቱ ለኤርትራ ጦር ፈቃድ የሰጠው ዶ/ር አብይ ነው የሚል ወቀሳንም በዚህ ወገን ያስነሳል የሚል ስጋት ያላቸውም ሰዎች አይናቸውን በጨው አጥበው ከእውነታው ይልቅ አምነስቲን እና ፍሰሐን ሲረግሙ አይቻለሁ። ይህም ነውር ነው።
እስኪ እነዚህ ጥያቄዎች ላንሳና ጽሁፌን ልደምድም፤
1. ለመሆኑ ባለፉት ሃያ ምናምን አመታት አምነስቲ በኢትዮጵያ ላይ ያወጣቸው የነበሩ መግለጫዎች በምን መልኩ ተጠናቅረው ይወጡ እንደነበር ያውቃሉ? እኔ እስከማውቀው ላለፉት ሁለት አስርት አመታት የአምነስቲ መርማሪዎች ኢትዮጵያ ገብተው ምርመራ ማካሔድ አይፈቀድላቸውም ነበር። እንደውም የአሁን መንግስት መመስገን ካለበት በዚህ ጉዳይ መጠነኛ መሻሻሎችን ስላሳየ ሊመሰገን ይገባዋል። ባለፉት አሥርት አመታት አምነስቲም ሆነ ሌሎች አለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች ያወጡዋቸው የነበሩ መግለጫዎች መረጃ ይሰበሰብ የነበረው በስልክ እና ከአገር ተሰደው ሱዳን እና ኬኒያ ከገቡ ሰዎች ነው። ያኔ ወያኔን ለመታገል የአምነስቲን ሪፖርት መቶ ጊዜ እያባዘ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ሹሞችን ደጅ ይጠና የነበረ የመብት አቀንቃኝ ያኔ ያላነሳውን ጥያቄ ዛሬ አምነስቲ ለምን በጦርነቱ ውስጥ ሰንጥቆ አክሱም ገብቶ መረጃ አልሰበሰበም፤ በስልክ የሚገኝ መረጃ ውድቅ ነው ብሎ በአደባባይ ሲሟገት ሳይ አወይ የሰው ነገር ያስብላል። እኛ የማንፈልገውን እውነትን መፍራት ማለት ይሔ ነው።
2ኛ/ በትግራ ክልል ጦርነቱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ዶ/ር ዳንኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ቢያንስ ሁለት ትላልቅ መግለጫዎችን አውጥቷል። አንደኛው በማይካድራ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሌሎች አራት ከተሞች የደረሰውን የመብት ጥሰት እና የጉዳት መጠን የሚመለከት ነው። የማይካድራው መግለጫ በመንግስት እና በግል ሚዲያዎች ከሳምንት በላይ ሲራገብ ቆይቷል። የህውሃት የሃጢያት ልክ የታየበት ስለነበር ሁላችንም አለም እንዲያውቀው አድርገናል። እንደውም ዶ/ር ዳንኤል እና የኮሚሽኑ ሠራተኞች በየሚዲያው መግለጫም እንዲሰጡ እየተጋበዙ በማይካድራው ጭፍጨፋ ላይ ብዙ ተነግሯል። ሁለተኛው መግለጫ 108 ሴቶችን መደፈር ጨምሮ በርካታ ጥሰቶችን የያዘ ሲሆን የኤርትራ ሠራዊት የነበረውን ሚና በጨረፍታ ይነካል። ያንን ሪፖርት የመንግስትም ሆነ የግል ሚዲያዎች በቂ ሽፋን ሳይሰጡት እና ትኩረት ሳያገኝ አልፏል። እንግዲህ የምንፈልገው እውነት እንዲነገር እና የማንፈልገውን እውነት ደግሞ ማደባበስ ማለት ይሔ ነው።
3ኛ/ በአንድ አካባቢ ግጭት ወይም የመብት ጥሰት ሲፈጸም የተለያዩ መብት ተኮር ድርጅቶች ካላቸው አቅም፣ የማጣራት ችሎታ እና እውቀት እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ተነስተው ጉዳዩ ላይ ምርመራ ሊያካሂዱ እና መግለጫ ሊያወጡ ይችላሉ። መግለጫቸው ላይ የአሰራር ግድፈት፣ ድርጅቱ ነገሮችን ያየበት እና የመረመረበት ስልት እና የአትኩሮት አግጣጫዎች በሪፖርቱ ላይ ይንጸባረቃሉ። በዛ ሪፖርት ላይ በተካተቱት መረጃዎች ላይ ቅሬታ ያለው ወይም ይዘታቸውን እና መረጃዎቹን የተጠራጠረ ሰዎ ጉዳዩ በሌላ ገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ይጠይቃል ወይም አቅሙ ካለው እራሱ ያጣራል። እውነቱ ነጥሮ እንዲወጣ በማድረግም ያንን የተሳሳተ መረጃ ያወጣውን አካል ያሳጣል፣ እንዲታረም ያደርጋል፣ በሕግ መጠየቅ ካለበትም በአግባቡ ተጠያቂ ያደርገዋል። ከዚያ መለስ በሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱትን እውነታዎች እና ዝርዝር መረጃዎች ወደ ጎን ጥሎ ወይም በመግለጫው ለተካተቱ ፍሬ ሃሳቦች ጀርባውን ሰጥቶ የሪፖርት አሽጪውን ዘር እና ማንነት እየዘረዘረ እሱን የሚወቅጥ ከሆነ ሌላው እውነትን የመሸሽ ወይም የመፍራት ባህሪ መገለጫ ነው። ባጭሩ የህውሃትን ጫማ ማጥለቅ።
ለማጠቃለል ያህል፤ ሁሉም የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ንጹዎች አይደሉም። ልክ ሌሎች ድርጅቶችም ውስጥ ችግሮች እንዳሉ ሁሉ በሰብአዊ መብት ድርጅቶችም መካከል ይህ ችግር በግልጽ ይስተዋላል። በመሆኑም የመብት ድርጅቶችን አልፎ አልፎ ሌላ ተልዕኮ እንዳላቸው አድርጎ ማሰቡ ሙሉ በሙሉ ስህተት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን እኔ የምፈልገውን እውነት ሲናገርልኝ እና ሲጽፍልኝ አርማውን ግንባሬ ላይ መለጠፍ እስኪቀረኝ ድረስ መግለጫውን እውነት አድርጌ ተቀብዮ ለአለም እዩልኝ በደሌን ያልኩበትን ድርጅት እኔ የማልፈልገውን እውነት በተመሳሳይ የአሰራር ስልት ሲያወጣ አይንህን ላፈር ማለት እውነትን የመፍራት ወይም የመጥላት – Alethophobia በሽታ ነው እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም።
የአምነስቲ ኢንተርናችናል በአክሱም ላይ ያወጣው መግለጫ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት በቂ ምርመራ እንዲካሄድበት ያሳሰቡትን እና የአምነስቲንም ስጋር እንደሚጋሩ በመግለጫቸው ለገለጹት ለዶ/ር ዳንኤል በቀለ ያለኝን የቆየ አክብሮት በእጥፍ ከፍ አድርጌ እና ከመቀመጫዮም ብድግ ብዮ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። እንዲህ አይነት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን መኖሩ ብዙ ችግሮች ቢኖሩብንም “ለውጥማ አለ” ያስብላል። ለውጥማ የለም የምትሉ እራሳችሁን ፈትሹ።
እውነትን ከመፍራት – Alethophobia በሽታ ይፈውሰን።