>

የዓድዋ ድል ታሪክ ትሰማ  እንደሆን ጫ ብለህ ስማ...!!! (ሔቨን ዮሐንስ)

የዓድዋ ድል ታሪክ ትሰማ  እንደሆን ጫ ብለህ ስማ…!!!

ሔቨን ዮሐንስ

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያም አልፎ የአለም ጥቁር ህዝቦች ድል ነው…!!!
አጤ ምኒልክ የኢጣሊያን ወረራ በመቃወም ወደ ዓድዋ ለመዝመት ሲያስቡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ ለመቀስቀስ ሁኔታው አስገድዷቸው ነበር። የሚከተለውን የክተት አዋጅ መስከረም 7 ቀን 1888 ዓ.ም አሳወጁ፡፡
‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ግን ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ለኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡ እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠረጥረውም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያስፈራራ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ አሁንም ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ዕርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም፡፡ ማርያምን!! ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታው ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡››
ልብ አድርጉ ከላይ የያወጀው አዋጅ የአገርና የህዝብ ፍቅር በጥልቅ ያስረዳል። የእምየን አሳቢነት ለህዝብ ለከብቱም የነበራቸው እይታ፤ ደግሞም ህዝብና መንግስት ምንም ቅራኔ እንዳልነበራቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የሆነው ሆኖ በዚህ ጥሪ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ ጦሩም አምባላጌ ደረሰ፡፡ ስለአምባላጌው ጦርነት #በርክሌይ ሲገልጽ:-
‹‹አምባላጌ በተለይም ቡታ በተባለው ቦታ ላይ በአንድ በኩል በጀግናው ራስ #አሉላና በራስ #መንገሻ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በራስ #መኮንንና በራስ #ሚካኤል የሚመራው ጦር የጠላትን ወገን እንዲሸሽ አደረጉት፤›› ይላል፡፡ ቀጥሎም
‹‹የኢጣሊያ ጦር በጀግንነት የተዋጋ ቢሆንም ሁኔታውን የሚቋቋመው አልሆነም፡፡ ከዚህ መዓት የተረፉት ኢጣሊያኖች አንዳሉት የአበሾች ቁጥር ከመጠን በላይ ብዙ ነው፡፡ ብዙ ይሞታል፤ ነገር ግን ሌላው ወደፊት ይገፋል፡፡ የምድሩም ተኩስ አይገታቸውም፡፡ ሁኔታው ከመሬት የሚፈሉ አስመሰላቸው፡፡ ጦሩ እየተኮሰ ይገድላቸዋል፡፡ ነገር ግን ቁጥራቸው እየበረከተ ይሄዳል፤›› ማለታቸውን አሥፍሯል፡፡
‹‹መድፈኞች ተኩሱን እንዳቆሙ በአየቅጣጫው የራስ አሉላ ጦር ፈጥኖ እየደረሰ ጨፈጨፈው፡፡ ጄኔራል #ቶዘሊም አምባለጌ ላይ ተገደለ፡፡ መቀሌም ከአርባ ቀን ጦርነት በኋላ ተያዘች፤›› በማለት #በርክሌይ ስለጦርነቱ ገጽታ ጽፏል፡፡ ምንም እንኳን ኢጣሊያውያን ሽንፈት ቢደርስባቸውም ታህሳስ 10 ቀን 1887 ዓ.ም የኢጣሊያ ፓርላማ ባደረገው ስብሰባ ለጦርነቱ መቀጠል ከፍተኛ በጀት መመደቡ ይታወሳል፡፡ ምፅዋ ወደብ የሚደርሰው መሣሪያ ወደ አዲግራት ለማድረስ 21 ሺሕ ግመል ያስፈልግ የነበረ ሲሆን፣ #አርሞንዲ ባደረገው ጥረት 8,200 ግመልና በቅሎ
ተገኝቶ እንዲጓጓዝ አደረገ፡፡ 38,000 የሚሆኑ ወታደሮች፣ 8,584 በቅሎዎችንና 100,000 በርሜሎች ከመርከብ ወርደዋል፡፡ ይህ ስንቅና ትጥቅ ለጊዜው ፋታ የሰጣቸው ቢመስልም፣ ጦርነቱ ቀጥሎ መቀሌ ሙሉ በሙሉ ጥር 4 ቀን 1888 ዓ.ም ከኢጣሊያውያን ፀዳች፡፡
የአፄ ምኒልክም ጦር አቅጣጫውን ወደ አዲግራት
በማድረግ ፋንታ ፊቱን ወደ ሰሜን ምዕራብ በማዞር ጥር 22 ቀን ከሐውዜን ጉዞውን ወደ ዓድዋ ቀጠለ፡፡

•የዓድዋ የጦር አሰላለፍ

እምየ ምኒልክ ኢጣሊያውያን ትግራይ ውስጥ ዘልቀው መግባታቸውን እንደተገነዘቡ ሕዝባቸውን ለዘመቻ እንዲንቀሳቀስ ወሰኑ፡፡ ዝናቡ በሚያቆምበት ማለትም መስከረም ወር ላይም ወደ ሰሜን የሚዘምቱ ስለሆነ የሸዋ ሰዎች እስከ ጥቅምት መጨረሻ እሳቸው እስከሚገኙበት ሥፍራ፣ ማለትም ከአዲስ አበባ 200 ኪሎ ሜትር ያህል ከምትርቀው #ወረኢሉ ድረስ እንዲመጡ አወጁ፡፡
የጎጃም፣ የደንቢያ፣ የቋራና የጎንደር ወታደሮችም #ጨጨሆ ላይ፤ የሰሜን፣ የወልቃይት-ጠገዴ #መቀሌ ላይ እንዲገናኙ ታዘዘ፡፡ የራስ #መኮንን ጦርም በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ከሐረር ተነስቶ አዲስ አበባ ደረሰ፡፡ የዓድዋ ጦርነት ዶ/ር ዓለሜ እሸቱ እንዳጠናቀሩት አፄ ምኒልክ የጦርነቱን ክተት አውጀው ከአዲስ አበባ የተነሱት ጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ነበር፡፡ ህዳር 28 ቀን 1888 ዓ.ም አምባላጌ ላይ፣ ታህሳስ 1888 ዓ.ም መቀሌ ላይ በተደረገው ዘመቻ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
ከዚያ በኋላ የፍልሚያው ሥፍራ ዓድዋ ላይ የነበረ ሲሆን፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ያዘመቱት ጦር ቁጥር ግን በልዩ ልዩ ጸሐፊዎች የተሰላው በተለያየ ቁጥር ነው፡፡ የኢንጂነር ካፑዚ ግምት — 85 ሺሕ ባለጠመንጃ ሲገመት ከዚህ ውስጥ:-
ራስ መኮንን (ሐረር) – 8 ሺሕ ጠመንጃ
ራስ ሚካኤል (ወሎ) – 8 ሺሕ ጠመንጃ
ራስ ተክለ ሃይማኖት (ጎጃም) – 5 ሺሕ ጠመንጃ
ራስ ወሌ — 5 ሺሕ ጠመንጃ
ራስ መንገሻ ዮሐንስ — 5 ሺሕ ጠመንጃ
ራስ መንገሻ አቲከም — 3 ሺሕ ጠመንጃ
ዋግ ሹም ጓንጉል — 20 ሺሕ ጠመንጃ
እቴጌ ጣይቱ — 4 ሺሕ ጠመንጃ (ከደጃዝማች ጣሰው ጭምር)
የአፄ ምኒልክ የክብር ዘበኛ ጦር 3 ሺሕ ጠመንጃ
በጅሮንድ ባልቻ — 3 ሺሕ ጠመንጃ
ሊቀመኳስ አባተ — 2 ሺሕ ጠመንጃ
ዕቃ ቤት፤ ጠጅ ቤት፣ ሥጋ ቤት — 15 ሺሕ ጠመንጃ
በአድዋ ጦርነት ላይ በኢትዮጵያ ወታደሮች ከተማረኩና ከተያዙ በኋላ ነፃነቱን አግኝቶ ኢጣሊያ የተመለሰው የጄኔራል #አልቤሮቶኒ ግምት ኢትዮጵያ ከ111 ሺሕ እስከ 122 ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሰለፈች ሲሆን ከዚህም ውስጥ:-
*ራስ መኮንን (ሐረር) ከ15 ሺሕ – 16 ሺሕ ጠመንጃዎች
* ራስ ሚካኤል (ወሎ) ከ14 ሺሕ – 15 ሺሕ ጠመንጃ
*ራስ ተክለሃይማኖት (ጎጃም) 5 ሺሕ – 6 ሺሕ ጠመንጃ
*ራስ ወሌ 6 ሺሕ ¬– 7 ሺሕ ጠመንጃ
*ራስ መንገሻ ዮሐንስ – 3 ሺሕ — 4 ሺሕ ጠመንጃ
*ራስ አሉላ 3 ሺሕ — 4 ሺሕ ጠመንጃ
*የአፄ ምኒልክ 33 ሺሕ — 38 ሺሕ ጠመንጃ
*እቴጌ ጣይቱ 5 ሺሕ — 6 ሺሕ ጠመንጃ
በወቅቱ ኢትዮጵያን ሊጎበኝ የመጣው ሩሲያዊው የካውንት #ሊኦንትየፍ ግምት 85 ሺሕ እግረኞች፣ 22,600 ፈረሰኞች፣ 42 መድፈኞች ሲሠለፉ ከእነዚህም ውስጥ:-
~ ራስ መኮንን 15 ሺሕ ጠመንጃዎችና 4 መድፎች
~ ራስ ሚካኤል 6 ሺሕ ጠመንጃዎችና 10 ፈረሰኞች
~ራስ ወሌ 10 ሺሕ ጠመንጃዎች
~ራስ መንገሻ አቲከም 6 ሺሕ ጠመንጃዎች
~ራስ መንገሻ ዮሐንስ 6 ሺሕ ጠመንጃዎችና 6 መድፎች
~ራስ አሉላ 3 ሺሕ ጠመንጃዎች፣
~አፄ ምኒልክ 30 ሺሕ ጠመንጃዎች፣ 12 ሺሕ ፈረሶችና 32 መድፎች
~እቴጌ ጣይቱ ሦስት ሺሕ ጠመንጃዎችና ስድስት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩ፡፡
አፄ ምኒልክ ዓድዋ ላይ ካሠለፏቸው ወታደሮች በተጨማሪ የራስ #ወልደ_ጊዮርጊስ ከስድስት እስከ ስምንት ሺህ፣ የራስ ተሰማ ናደው ከአራት እስከ አምስት ሺህ፣ የራስ ዳርጌ፣ ሦስት የደጃዝማች #ወልደፃድቅ ሦስት ሺህ፣ የደጃዝማች
#ልዑልሰገድ ሦስት ሺሕ፣ ወዘተ ግማሹ አዲስ አበባን
ሲጠብቁ ሌላው ኢጣሊያውያን በአፋር በኩል ያስገቡትን ጦር ለመግጠም በመዝመቱ ዓድዋ ላይ ሳይዋጉ መቅረታቸው፣ እንዲሁም ከአፋሮች ሌላ ኢጣሊያኖች በዘይላ በኩል ሶማሌዎችን አነሳስተው ኢትዮጵያን እንዲወጉ ለማድረግ የነበራቸው ዕቅድ፣ የእንግሊዝና የፈረንሳይ መንግሥት ሳይስማሙ በመቅረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ያም ሆነ ይህ በጦር መሣሪያውና የተሠላፊው ብዛት
በሚመለከት የተለያዩ ጸሐፊዎች የተለያየ አቆጣጠር
እንደነበራቸው ሁሉ፣ በአሠላለፉም ቢሆን ተለያይተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኢጣሊያውያን፣ እንግሊዛዊው አውጎስት #ዋይልድና ግራዝማች ዮሴፍ የተባሉት ጸሐፊዎች ያቀረቡት አሠላለፍ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
•የኢጣሊያ ጸሐፊዎች እንዳቀረቡት
አጤ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ‹‹ዓዲ ማሕላሽ›› በተባለው ሥፍራ ዓድዋ ከተማ አጠገብ ነበሩ፡፡ ራስ ወሌ ‹‹ማይ ደላዕታ›› ላይ በመሠለፍ የኋላ ደጀን ነበሩ፡፡ ራስ ሚካኤል ግንባር ቀደም በመሆን በሠናይ ጸባህና በእንዳ ሚካኤል መሀል ነበሩ፡፡ ፊታውራሪ ገበየሁ ከራ ሚካል በስተቀኝ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከ22 ወንዝ በስተግራ ከፊታውራሪ ገበየሁ በኋላ፣ ራስ መኮንን አዲ አቡን በስተሰሜን ዳዕሮ ተክሌ አጠገብ፣
ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ፣ ዋግ ሹም ጓንጉል
በገራዓና በማርያም ሸዊቶ አጠገብ ነበሩ፡፡
#ኦገስት_ዋይልድ የተባለው እንግሊዛዊ ጸሐፊ ደግሞ፣
አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በፍረሞና ኮረብታ ላይ፣
ንጉሥ ተክለሃይማኖት አፄ ምኒልክ ጦር ፊት ለፊት፣
ራስ መኮንን በዓድዋ አካባቢ፣
ራስ ሚካኤል ከሶሎዳ ኮረብታ በስተደቡብ፣
ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከሰሎዳ ኮረብታ በስተሰሜን፣
ራስ አሉላ በአዲ አቡን አካባቢ፣
ራስ ወሌ ከአድዋና ከራስ መኮንን ጦር ደቡብ ምዕራብ፣
ዋግሹም ጓንጉል – ከአድዋ (ከራስ መኮንን ጦር) ሰሜን ምዕራብ፣
ደጃዝማች በሽር ከራስ ወሌና ከዋግሹም ጓንጉል በስተኋላ ነበሩ በማለት መዝግቧል፡፡
ግራዝማች #ዮሴፍ መጋቢት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. #ለሞንድን_ቪደይሌት በጻፉት መሠረት ደግሞ፣
አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ከጦሩ በስተኋላ
ራስ ወሌ፣ ራስ መንገሻ አቲከም፣ ቱርክ ባሻ ታምሬ ከአፄ ምኒልክ ፊት ለፊት፣ ራስ መኮንን፣ ፊታውራሪ ተክሌ፣ ደጃች በሻህ በዓድዋ አካባቢ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት በአባ ገሪማ ኮረብታ አካባቢ፣
ራስ ሚካኤል፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ዋግ ሹም ጓንጉል፣ ደጃች ወልዴ በማርያም ሸዊቶ ሸለቆ አካባቢ ነበሩ፡፡
• የኢጣሊያ የጦር አሰላለፍ
በአድዋ ጦርነት 20 ሺህ ያህል የኢጣሊያ ጦር የተከማቸው #ሳውሪያ (ኢንቲጮ) ላይ ሲሆን፣ ይህም ከዓድዋ በስተምሥራቅ 16 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ሥፍራ ነው፡፡ የኢጣሊያ አሠላለፍ በአራት የተከፈለ ነበር፡፡ እርሱም፡-
*ጄኔራል ዳቦርሜዳ … የቀኝ ብርጌድ 3,500 ወታደሮችና -18 መድፎች
* ጄኔራል አልቤርቶኒ … የግራ ብርጌድ 8,300 ወታደሮችና 12 መድፎች
* ጄኔራል አሪሞንዲ … የመሀል ብርጌድ 2,900
ጠመንጃዎችና 12 መድፎች
* ጄኔራል ኤሌና … ተጠባባቂ (ሪዘርቭ) ብርጌድ 3,350 ወታደሮችና መድፎች ነበሩት፡፡
አፄ ምኒልክ ከነጦራቸው ዓድዋ ላይ የካቲት 7 ቀን 1888 ዓ.ም ኢጣሊያውያን ደግሞ ኢንቲጮ ላይ የካቲት 6 ቀን ከሠፈሩ በኋላ፣ የሁለቱ ወገን ሠራዊት ተፋጠው እስከ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ድረስ ቆዩ፡፡ እስከዚያ ዕለትም ሁለቱም የተፋጠጡ ወገኖች ሌላውን ሲሰልለው ሰነበቱ፡፡ በመጨረሻም ኢጣሊያውያን ‹‹ኢትዮጵያ ሠራዊት ገሚሱ ቀለብ ፍለጋ ወደ ሽሬና ወደ ተንቤን እንዲሁም ተከዜን ተሻግሮ ወደ ጸለምት ተበትኗል፡፡ ሌሎች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ አክሱም ጽዮን እሑድ የሚውለውን የጊዮርጊስ በዓል ለማስቀደስ ሄደዋል…›› የሚል መረጃ ስለደረሳቸው በዚሁ ዕለት ማለትም የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም እሑድ የጊዮርጊስ ዕለት በአጥቂነት የኢትዮጵያን ሠራዊት ለመውጋት ወሰኑ፡፡
የአፄ ምኒልክ ጸሐፊ ገብረ ሥላሴ እንደሚሉትም (ገጽ
262) ቀለብ ፍለጋ አክሱም ጽዮን ከሄዱት እሑድ ለጦርነቱ የተመለሱት ከሦስት እጅ ሁለት እጅ ነበሩ፡፡
#የዓድዋ_ጦርነት_በጆርጅ_ኤፍ_በርክሌይ_እይታ
ጆርጅ ኤፍ በርክሌይ የተባለ ጸሐፊ ‹‹የዓድዋ ዘመቻን
የምኒልክ አነሳስ›› በሚል ርዕስ ያሳተመው መጽሐፉ
በዳኛው ወልደ ሥላሴ ተተርጉሞ እንደምናነበው፡፡ … አጤ ምኒልክም ሆኑ የኢጣሊያው የጦር መሪ #ባራቲየሪ ቀድመው ለማጥቃት ሳይሽቀዳደም አንዱ የሌላው ጠላት ስንቅ እንዲያልቅ እየተመኘ ጦርነቱን ሳይጀመር በመቆየቱ፣ ሁለቱም ስንቃቸውን ወደ መጨረሱ ተቃርበው ነበረ፡፡ ድል በመምታት መበቀልን የፈለገው የሮማ ሕዝብ ውሎ ባደረ ቁጥር ተስፋ እየቆረጠ በመሄዱ #የባራቲየሪም ክብርና
ዝና ወደቀ፡፡ የካቲት 15 ቀን 1888 ዓ.ም በሚስጥር
#ባራቲየሪ ተሽሮ ጄኔራል #ባልዲሴራ የጦሩ አዛዥ እንዲሆን ተሾመ፡፡ ይሁንና ይኼው የጦር መሪ የካቲት 21 ቀን 1888 ዓ.ም በማይ ገበታ በኩል ወደ ማይ ማረት ለማፈግፈግ ወስኖ መንገድ ከጀመረ በኋላ፣ በዚሁ ምሽት አራቱን ጄኔራሎች ሰብስቦ ያለው ምግብ እስከ የካቲት 23 ቀን ወይም የካቲት 24 ቀን ድረስ ብቻ የሚያቆያቸው መሆኑን ካስረዳ በኋላ፣
ወደ ሰንአፌ ለመሸሽ ወይም አስፈላጊው ጥናትና ዝግጅት እንዲያደርጉ አማከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ጄኔራል #ዳቦር ሜዳ፤ የጄኔራል ባራቲየሪን ንግግር ከሰማ በኋላ መሸሹ የማይደረግ ነው ብሎ ስሜቱን ገልጾ ምክንያቱን ማስረዳት ጀመረ፡፡
አንደኛ የኢጣሊያን ሕዝብ ከምናሳፍር ሦስት ሺሕ ወታደር ቢሞትብን ይመረጣል፡፡ ሁለተኛ የወታደሩ ሞራል በጣም ይወድቃል፡፡ ሦስተኛ ጠላቶቻችን ከእኛ ፈጥነው ለመጓዝ ስለሚችሉ አሁንም በመሸሽ ላይ ሳለን ደርሰው ለራሳቸው ከሚያመቻቸውና ከመረጡት ቦታ ላይ አደጋ ሊጥሉብን ይችላሉ፡፡ ይህ ከሚሆን ወጥተን ማጥቃቱ ይሻላል ሲል አሳሰበ፡፡ ጄኔራል አልቤርቶኒም የጄኔራል ዳቦር ሜዳን ሐሳብ ደግፎ፣
‹‹የጠላት ጦር ምግብ ለመሰብሰብ የተበታተነ ከመሆኑም በላይ ብዙውም ወደ አገሩ በመመለስ ላይ ነው፤›› በማለት የሀበሻው ጦር ሠፈር በሁለት መሪዎች የተከፈለ ከመሆኑም በላይ ከ14 ሺህ ወይም ከ15 ሺህ ጦር በላይ እንደማይኖረው ገለጸ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሁኔታው አፄ ምኒልክም በጣም ተጨንቀዋል፡፡ የቀራቸው ለሦስት ወይም ለአራት ቀናት
የሚሆን ስንቅ ብቻ ነበር፡፡ ጠላት ከምሽጉ ወጥቶ ማጥቃት እንዲጀምር ብርቱ የሆነ ጸሎታቸው ነበር፡፡ ይህንንም ዕድል ለማግኘት #ለባሪያቲየሪ እንዲደርስ የሚያስወሩት ፕሮፓጋንዳ
‹‹በአጤ ምኒልክ የጦር ሠፈር ችግርና ረሃብ ጸንቶ ሠራዊቱ እየሸሸ በመሄድ ላይ በመሆኑ በዙሪያው የሚገኘው ሕዝብ ተነስቷል፤›› የሚል ነበር፡፡
አፄ ምኒልክ እንደተመኙትም የካቲት 22 ቀን 1888 ዓ.ም አመሻሽ 11፡00 ሰዓት ጄኔራል ባሪያቴሪ ወጥቶ ለማጥቃት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጠ፡፡ #የባሪያቴሪ ዓላማ በሦስት አቅጣጫ ሌሊቱን ሲጓዝ አድሮ
የጠላት ጦር ሳያውቅ በተራራው ገመገም ሥር ለመመሸግና የመከላከያ ቦታ ለመያዝ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ የጠላት ጦር ቢያጠቃ መልካም፣ ካልሆነም የሀበሻን ጦር ፍርኃት እንዲያድርበት በዙሪያው ለሚገኘው ሕዝብ ማሳየት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢጣሊያ ጦር ተንቀሳቅሶ የእነዚህን ተራራዎች ገመገም በሚይዝበት ጊዜ የሀበሻው ጦር
በርግጎ ወደኋላ ይመለሳል የሚል እምነትና ተስፋ ነበረው፡፡ ይህም ከሆነ ዓድዋን በሰላም (ያለችግር) ለመያዝ እንደሚችልም ገምቶ ነበር፡፡

•የጦሩ አሠላለፍም

ሀ. በቀኝ በኩል በጄኔራል ዳቦር ሜዳ የሚመራው የበላህን ተራራ አምባ፣ የበላህን ጎጥና በዙሪያው ያለውን ቦታ፣
ለ. በመካከል በጄኔራል ኦርሞንዲ የሚመራው የበላህን
ተራራ
ሐ. በግራ በኩል ‹‹በጄኔራል አልቤርቶኒ የሚመራው ኪዳነ ምሕረት ብለው የጠሯትና (ለዚች ተራራ የተሰጠው ስም በትክክል አልነበረም) ራይ የተባሉትን ተራራዎች እንዲዝ፣
መ. በጀኔራል ኤሌና የሚመራው ተጠባባቂው ጦር ረቢ
አርኧየኒ በተባለው ቦታ ሆኖ እንዲጠባበቅ፣
የቀኑ ትዕዛዝም ‹‹የካቲት 22 ቀን 1888 ቁጥር 87 ዛሬ ማታ ጦሩ በሦስት አቅጣጫ ወደ ዓድዋ በሚከተለው ሁኔታ ይቀንሳል፡፡
‹‹… የቀኙ ክፍል ጄኔራል ዳቦር ሜዳ 2ኛ እግረኛ ጦር
ብርጌድ የሞባይል (ተንቀሳቃሽ) ሻለቃ ጦር የ2ኛ ባትሪ
ብርጌድ አባሎች፣ የ5ኛ፣ የ6ኛ፣ የ7ኛ ከባድ መሣሪያ ጓድ፡፡ ‹‹…ግራው መስመር በጄኔራል አልቤርቶኒ (የሚመራ ሆኖ) አራት የአገሬው ተወላጅ ሻለቃ ጦር የአንደኛ ባትሪ ብርጌድ አባሎች፣ ከ1ኛ፣ ከ2ኛ፣ ከ3ኛ፣ ከ4ኛ ከባድ መሣሪያ ክፍልጋር፡፡ ተጠባባቂ ጄኔራል ኤሌና፣ 3ኛ እግረኛ ብርጌድ፣ 3ኛ የአገሬው ተወላጅ የአለቃ ጦር ሁለት የመትረየስና የከባድ መሣሪያ ጓድና አንድ ሻምበል መሐንዲሶች፡፡ ‹‹…ጄኔራል ዳቦር ሚዳ፣ በአርሞንዲና በአልቤርቶኒ የሚመራው ጦር ከሌሊቱ ሦስት ሰዓት ከቦታው እንዲንቀሳቀስ ሲታዘዝ ከአንድ ሰዓት በኋላ ደግሞ ተጠባባቂው ጦር የመካከለኛውን መሥመር ተከትሎ ይንቀሰቀሳል፡፡ ‹‹…የቀኙ ረድፍ በዛሃላ ጎጥ አድርጎ ጎልደም ጎጥን አልፎ
ወደረቢ አርእየኒ ጎጥ ይጓዛል፡፡ የመካከለኛው ተጠባባቂ ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንድብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንደብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ደግሞ ከሶሎዳ በአዲ ቸራይራ በኩል ወደ ኪዳነ ምሕረት ይጓጓል…›› የሚል ነበር፡፡
በዚህም ዓይነት ኢጣሊያኖች ብዛቱ 100 ሺህ
የሚሆን የጦር መሣሪያ ጦርና ጋሻ የያዘውን የሐበሻ
ሠራዊት ለመግጠም 17,700 ወታደርና 56 መድፎች
ጠምደው ተሰተሰናድተዋል፡፡
በዶ/ር እሸቴ ዓለሜ የተጠናቀረውን ልብ ይሏል) በአፄ ምኒልክ ግንባር የተሠለፈው ጦር በዶ/ር እሸቴ ዓለሜ
ጥንቅር አጤ ምኒልክ ከእነ ጦራቸው ዓድዋ መጋቢት 3 ቀን 1888 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ ኢጣሊያውያን #ኢንቲጮ ድረስ ሄደው ለመውጋት ያልፈለጉበት ምክንያት ቦታው ለአጥቂ ጦር የማያመች መሆኑን #ገብረ_ሥላሴ ለሞንድ ቬዳይሌት
በየካቲት 7 ቀን 1888 ዓ.ም ላይ ገልጸዋል፡፡ ከዚያም ጊዜ አንስቶ እስከ የካቲት 23 ቀን ቆይተዋል፡፡
እንኳን ለ125 የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ።

•ኢትዮጵያበክብርለዘላለምትኑር !!

•የጥቁርሕዝብኩራት

•ዓድዋ የኢትዮጵያ ድል ነው!

Filed in: Amharic