>

የካራማራ ጀግናው ሚስት እና ኮ/ል መንግስቱ  ኃ/ማርያም!!! (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

የካራማራ ጀግናው ሚስት እና ኮ/ል መንግስቱ  ኃ/ማርያም!!!

ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን

እንደመግቢያ

አንዳንድ ታሪኮች እያደር ይፈለቀቃሉ፤ እያደር ይደምቃሉ፤ እያደር ልብ ያሞቃሉ፤ እያደር ያሸበርቃሉ፣ እያደር ያስደንቃሉ።
ይህንን ታሪክ (ከታች የምታነቡትን) አምና አውግቻችሁ ነበር። የካራማራን ድል 42ኛ ዓመት በመዘከር ሰበብ ነበር ያወጋኋችሁ። በዚህ ዓመት ደግሞ ነፃነት” በተሰኘው የግጥምና የወግ ስብስብም ውስጥ አካትቼ ለሕትመት አብቅቼዋለሁ።
“ነፃነት” ለህትመት ካበቃ በኋላ፣ ከባለታሪኩ ልጆች መሃል አንደኛዋ፣ እዚሁ መንደር የፃፈችውን አነበብኩ። አንብቤ ስጨርስ ዐይኔ በአድናቆት ፈጠጠ። እና ተጨማሪ መረጃ መፈለግ ገባሁ። የምፈልገውንም አገኘሁ፦ ከካራማራ ዘማች ጓደኞቻቸው። ለዚህ ነው አንዳንድ ታሪኮች እያደር ይደምቃሉ፤ ይፈለቀቃሉ ያልኩት። እናም …ተጨማሪውን ታሪክ ላወጋችሁ ወደድኩ። ሆኖም …ታሪኩን የተሟላ ለማድረግ የእኔኑ ትዝታ ማስቀደም ግድ ነው።
እነሆ፦
ትዝ ይለኛል
ቤታቸው አሁን እኛ ከምንኖበት ቤት ፊት ለፊት ነበር። የእሳቸው ቤት የኋላ (የጓዳ) በር ከእኛ ቤት በር ትይዩ ነው። ቤታቸው ከእኛ ሰፈር (ግቢ) ጭርንቁስ ቤቶች የተሻለ የተባለው ነው። ባለ ሶስት ክፍል ቤት።
ትዝ ይለኛል።
አሁንም ድረስ ጭል ጭል የሚል ትዝታ አለኝ። ሁልጊዜ ጠዋት 12 ተኩል አካባቢ የመኪና ሞተር ሲንደቀደቅ ይሰማል። የእሳቸው ቮልስ ዋገን መኪና ነው። ሌላ /ጎረቤት/ ግቢ ውስጥ ነው መኪናውን የሚያሳድሩት። ብቻ ጠዋት ጠዋት ለ30 ደቂቃ ሲንደቀደቅ ይሰማል። ያኔ ሞተር አስተነስተው እሳቸው ቁርስ እየበሉ ነው ማለት ነው። የመኪናዋ ሞተር መንደቅደቅ ካቆመ ደግሞ ወደስራ ሄደዋል ማለት ነው። ያኔ “ተነሱ! ሻለቃ ሄዱ! ዳይ! ረፈደ ወደ ት/ቤት!” እንባላለን። በዚያ ወቅት በሰፈራችን/
በአካባቢያችን ያለች ብቸኛዋ መኪና የእሳቸው ሳትሆን አትቀርም።
ትዝ ይለኛል
ያኔ የአምስት ዓመት ልጅ ብሆንም፣ ጭል ጭል የሚል ስዕል አሁንም ድረስ ይታየኛል። ቀይ ናቸው። ረዥም፣ ሸንቃጣ። ወታደራዊ አለባበሳቸው የሚያምር። በቀበቶአቸው ላይ ባንጠለጠሉት የቆዳ ማቀፊያ ውስጥ ሽጉጣቸውን ሻጥ የሚያደርጉ ቆፍጣና። ቀጥ ብሎ የተተኮሰ ቅጠልያ ወታደራዊ ልብሳቸው ኮሌታ ላይ ከሩቅ የሚያበራ በአንበሳ ምስል የተቀረፀ ማዕረግ የሚሰኩ፤ አረማመዳቸው የሚያምር ከፍተኛ መኮንን ናቸው።
ትዝ ይለኛል
ሁልጊዜ አመሻሽ /ከቀኑ 11፡30 አካባቢ ቮልስዋገን መኪናቸው ስትንደቀደቅ ትሰማለች። ከስራ መጡ ማለት ነው። ወዲያው እሳቸው በኋላ በር በኩል ወደ ቤታቸው ይገባሉ። ይኼኔ የግቢአችን ወላጆች በሙሉ ልጆቻቸውን “መጡ! ተዘጋጁ” ይላሉ። በእኛ ግቢ ውስጥ 5 ደጃፍ/ቤተሰብ ነው ያለው። የአምስቱም ቤተሰብ ልጆች ከ30 ደቂቃ በኋላ ወደ እሳቸውጋ መሄድ አለበት፦ የተማረውን ለማጥናት።
ትዝ ይለኛል
ሁልጊዜ አመሻሽ ወታደራዊ ልብሳቸውን ቀይረው፣ የሳሎን ጠረጴዛቸው ትልቅ መፅሐፍ ዘርግተው እያነበቡ ነው የምናገኛቸው። እናም፣ እኛም ልጆቻቸውም ደብተራችንን ይዘን በጠረጴዛው ዙሪያ እንሰየማለን። ማውራት የለም። ማንኮሻኮሽ የለም። ደብተራችንን እንኳ የምንገልጠው በጣም በቀስታ፣ በጣም ተጠንቅቀንጠ ነበር። ካለ እሳቸው ፍቃድ፣ ካለ እሳቸው በቀር መንቀሳቀስ የሚፈቀድለት የለም። እሳቸውም የሚንቀሳቀሱት እኛ የቸገረንን፣ ወይም ያልገባንን ለማስረዳት ነው። ለጥናት አብረን ከተቀመጥን በኋላ ፀጥ ነው። ፀጥ ብሎ ማጥናት ብቻ። እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ።
ትዝ ይለኛል።
ከእኛጋ የነበራቸው ግንኙነት የራሱ ሕግ ነበረው። ቴሌቪዥን እንድናይ የሚፈቀድልን በቀን እና በሰዓት ተለይቶ ነበር። በግቢው ብቻ አይደለም በሰፈራችን የነበረው ቴሌቪዥን እሳቸው ቤት ነው። የአባባ ተስፋዬ እና /የዘነጋሁት ፕሮግራም/ ካልሆነ በቀር ቴሌቪዥን ማየት ለልጆቻቸው ጭምር/ አይፈቅድም። ቴሌቪዥን የሚከፈተው ልክ እኛ ጥናታችንን ጨርሰን ስንወጣ ነው። አስጠኚያችን /ሻለቃ/ራሳቸው የሆነ መፅሐፍ ሳይገልጡ መቀመጥ አይችሉም የተባለ ይመስላል። ትልልቅ መፅሐፍ ነበር የሚያነቡት። የኋላ ኋላ እንደሰማሁት /ወታደር ቢሆኑም/ የሕግ ምሁር ነበሩ።
ትዝ ይለኛል።
እነ ማዘር እየተጠራሩ የተንሾካሾኩበት ቀን ትዝ ይለኛል። ከመንሾካሾክ አልፈው በሐዘን የተከዙበት ቀን ትዝ ይለኛል።
“ሻለቃ ወደ ጦር ግንባር ሊሄዱ ነው” ሲሉ ትዝ ይለኛል።
ጊዜው 1969 ነው።
ያኔ ሻለቃ በቀለ ካሳ የቀበሌያችን /ፈረንሳይ ሌጋሲዮን ቀበሌ 11) ሊቀመንበር ነበሩ። የማይወዳቸው የቀበሌው ነዋሪ አልነበረም። ትሁት ናቸው። አዳማጭ ናቸው። ሰው የሚረዱ ናቸው። እሳቸው ሊቀመንበር በነበሩበት ወቅት የኢሕአፓ ወጣቶች እየታደኑ ነበር። በዚህ መኃል አዳኞች ወደእሳቸው ቢሮ መጡና ወጣቶችን ስጡን አሏቸው።
“አይሆንም!” አሉ ሻለቃ በቀለ ካሳ። “ዐይኔ እያየ የደኃ ልጅ አትወስዱም” አሉ።
“ዐይኔ እያየ የደኃ ልጅ ከሚገደል፣ እኔ ራሴ ጀግኖች የሚሰውበት ቦታ ሄጄ ብሞት ይሻላል!”
ብለውም አልቀረ ወደ ጦርሜዳ ላኩኝ ብለው አመለከቱ። በማመልከቻቸው መሠረት ተላኩ፦ ወደ ምስራቅ ጦር ግንባር።
ትዝ ይለኛል።
በዓመቱ፤ እኛ ግቢ ውስጥ ትልቅ “ሽብር” ተፈጠረ። ኡኡታ! ለቅሶ ነገሰ። ታይቶ የማይታወቅ ሐዘን ሆነ። የቀበሌው ነዋሪ ሁሉ “ደም” አነባ። ያ ሁሉ ሰው፣ እንዲያ እርር ድብን ሲል የነበረው በሻለቃ በቀለ ካሳ የመሰዋት መርዶ መሆኑ ትዝ ይለኛል። ሻለቃ በቀለ ካሳ ካራማራ ላይ ወደቁ።
ትዝ ይለኛል።
ከወራት በኋላ የቀበሌው ነዋሪ ስብሰባ ተጠርቶ እንደነበር። የግቢው እናቶች ወደ ቀበሌ መሄዳቸው ነግረውን ነበር። ሲመለሱ ግን የሁሉም ፊት ተለዋውጦ ነበር። በለቅሶ ቀልቶ ነበር። … እናም እንደገና በግቢአችን አዲስ ለቅሶ ሆነ። የሻለቃን ስም እንደ አዲስ እያነሱ አለቀሱ። ለካስ ቀበሌ ሄደው “ፊልም” አይተው ነው የመጡት። የካራማራ ጦርነትን የድል ፊልም። በዚያ ፊልም ውስጥ ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት ድል አድርጎ ባንዲራ ሲሰቅል ይታያል። ባንዲራውን የሚሰቅሉት ደግሞ እሳቸው ናቸው፦ ሻለቃ በቀለ ካሳ።
“አይ ባንዲራ አሰቃቀል! አይ አቋቋም! አይ ሰላምታ አሰጣጥ!” ትለኛለች እናቴ አሁንም ድረስ ስለ ሻለቃ በቀለ ድንገት ስናወጋ ያየችውን ፊልም እያስታወሰች።
“እንደው ሁሉም እይ! ሁሉም ወታደሮች! አይ ዠግና” ይላሉ ጎረቤታችን ወ/ሮ አረጋሽ ይመር።
መውጫ
የካራማራ ጦርነትና ድል በተነሳ ቁጥር እናቴ እና ጎረቤቶቿ ሁሌም ስለ ሻለቃ በቀለ ካሳ ያወሳሉ። ባለፈው ዓመት በካራማራ ድል ሰበብ “ታስታውሳለህ?” ስትል ጠየቀችኝ።
“ምኑን?”
“ሻለቃ በቀለ፤ ሁልጊዜ እሁድ ገላችሁን ያጥቧችሁ እንደነበር?”
“አ? ያጥቡን ነበር እንዴ?”
“ያውም ሰፈሩን ሕፃናት በሙሉ! እናንተም እኔ ልቅደም ትጣሉ ነበር! በኋላ ተራ አወጡላችሁ! አንድ ሳምንት አንተና እህትህ፣ በሚቀጥለው ሳምንት የአረጋሽ ልጆች፣ በሶስተኛው የወርቅነሽ ልጆች፣ በአራተኛው የፀሐይ ልጆች፣የራሳቸው ልጆች ቅድሚያ የመታጠብ ዕድል የሚያገኙት በአምስተኛው ሳምንት ነበረ” አለችኝ።
ገረመኝ።
ማሳረጊያ
ሻለቃ በቀለ ካሳ ከተሰዉ በኋላ ወራቶች በወራቶች ላይ እየተደራረቡ ነጎዱ። ባለቤታቸው እና ልጆቻቸው እየተፅናኑ ባለበት በአንደኛው ወር ወደቤታቸው መልዕክተኛ መጣ። እና የውጭውን በር አንኳኳ። ተከፈተለት።
የሚያምር ወታደራዊ ልብስ ያደረከ መኮንን ነው እንግዳው። በሩ እንደተከፈተለት ጠየቀ
“ወ/ሮ ፀሐይ የምሩ አሉ?”
“አሉ” አለው በሩን የከፈተለት ሰው ወደሳሎኑ በር እየጠቆመው።
እንግዳው መኮንን ወደሳሎኑ አመራ። የሻለቃ በቀለ ካሳ ባለቤት ወ/ሮ ፀሐይ ተሽቆጥቁጠው ተቀበሉት። መልዕክቱን ነገራቸው። በመጨረሻም “ተዘጋጅተው ይጠብቁኝ፤ ነገ መጥቼ እወስድዎታለሁ” አላቸው።
ነጋ።
በጠዋቱ ኡዋዝ ጂፕ መኪና መጣ። ወ/ሮ ፀሐይ አነስተኛ ሻንጣቸውን አንጠልጥለው ወጡ። መኮንኑ የመኪናውን በር ከፈተላቸው። ገቡ። የከፈተላቸውን በር ዘግቶ ተመለሰና የሾፌሩ ወንበር ላይ ተቀምጦ የመኪናውን ሞተር ቀሰቀሰ። እናም መረሸ። ወደ ጦርግንባር፤ ወደ ካራማራ።
እዚያ ….
የጀግናው ባለቤታቸው ሻለቃ በቀለ ካሳ አስከሬን ያረፈበት ምድር ላይ ተገኙ። ሲደርሱ፤ የሻለቃው ቀብር ላይ መቱን የተሰለፉ ወታደሮች ጠበቋቸው። በክብር ሰላምታ ተቀበሏቸው። “እናቴ እንደነገረችኝ፤ የተቀበረበት ቦታ ላይ ትንሽዬ ሐውልት አቁመውለት ነበር” ትላለች ልጃቸው ትዕግስት በቀለ።
ወ/ሮ ፀሐይ የምሩ፣ የባለቤታቸው አስከሬን ያረፈበት መቃብር ላይ ተደፍተው ስቅስቅ ብለው አለቀሱ። በስፍራው የነበሩ ወታደሮች /ዘማቾች/ አጀባቸው። አብረዋቸው አለቀሱ። ወዲያው ግን እንዲህ አሏቸው፦
“አያልቅሱ! ለጀግና አይለቀስም! ሞት ለጀግና ሰርጉ ነው! ይልቁስ ሊኮሩ ይገባዎታል፤ ለልጆችዎ አባታቸው አይበገሬ ጀግና እንደነበር፤ በአባታቸው ሊኮሩ እንደሚገባቸው ይንገሯቸው!”
እንዲህ አሏቸውና ለቅሶአቸውን አስቆሟቸው። በመጨረሻም ወደ አዲስአበባ ሸኟቸው።
የመጨረሻው መጨረሻ
አዲስአበባ።
እንደደረሱ ወደቤታቸው የሚመልሷቸው ነበር የመሰላቸው። ግን እንዳሰቡት አልሆነም። ወ/ሮ ፀሐይን ወደ ካራማራ የወሰዳቸው ሰው የመኪናውን አፍንጫ ወደ ቤተመንግስት አዞረው።
የቤተመንግስቱ ጥበቃዎች ቆፍጠን ያለ ሰላምታ ሰጥተው ወደውስጥ መሯቸው። ወ/ሮ ፀሐይን የያዘችው ኡዋዝ ጂኘ ለደቂቃዎች ግቢው ውስጥ ተጉዛ አንድ ሕንፃ አጠገብ ቆመች።
እዚያ በንቃት የሚጠባበቁ ወታደሮች የመኪናውን በር ከፍተው ወ/ሮ ፀሐይን በወታደራዊ ሰላምታ ተቀበሏቸው።እናም በአክብሮት እየመሩ ወደ አንድ አዳራሽ ወሰዷቸው። አዳራሹ ውስጥ በርካታ ቆፍጣና ወታደሮች አሉ። ወ/ሮ ፀሐይ ፊተኛው ወንበር ላይ እንዲቀመጡ ተደረገ። ፍፁም ፀጥታም ሆነ።
ከደቂቃዎች በኋላ…
ጥቂት ከፍተኛ መኮንኖች በሌላኛው በር ተግተልትለው ገቡ። ከመኮንኖቹ በኋላ የመጨረሻው የሀገሪቱ ቁንጮ ባለስልጣን፣ ጥቁሩ ግስላ፣ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ወደ አዳራሹ ገቡ።በአዳራሹ ውስጥ የታደመው ሰው ሁሉ ከተቀመጠበት ተነሳ። ኮ/ል መንግስቱ መንበራቸውን እንደያዙ፣ እየመሯቸው ከመጡ ከፍተኛ መኮንኖች አንዱ ወደ መነጋገሪያው ፖዲየም አመሩ። እናም የያዙትን ወረቀት ዘርግተው ማንበብ ጀመሩ፦ የሻለቃ በቀለ ካሳን የጦር ሜዳ ገድል።
.
መኮንኑ የሻለቃ በቀለን ገድል አንብበው ሲያበቁ ወደ ጥቁሩ ነበር ፊታቸውን ዞር አድርገው እንዲህ አለ፦
“…ይህ ጀግናችን ለፈፀመው ገድል የተዘጋጀውን ሽልማት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ለባለቤታቸው ያበረክቱልናል…”
ወ/ሮ ፀሐይ፣ ኩራት እየተሰማቸው፣ ግን ደግሞ እንባ እየተናነቃቸው ወደመድረኩ አመሩ። ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም፣ የወ/ሮ ፀሐይን እጅ ጠንከር አድርገው ጨብጠው ክንዳቸውን ከወዘወዙ በኋላ ሽልማቱን ሰጧቸው።
ወ/ሮ ፀሐይ ሽልማቱን ተቀብለው ሊመለሱ ሲሉ የመድረክ መሪው “ትዕዛዝ” ባሉበት እንዲቆዩ አደረጋቸው።
“ይቆዩ” አሉ መድረክ መሪው። እናም ንግግሩን ቀጠለ።
.
“….ሻለቃ በቀለ ካሳ አብዮታዊት ኢትዮጵያን ለመታደግ የፈፀመው ጀብዱ በታሪክ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ነው። ይህ ጀግና በህይወት ባለመኖሩ ከጎናችን ባይገኝም፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ እና መንግስታችን ውለታውን የሚዘነጉ አይደሉምና የማዕረግ ዕድገት እንዲሰጠው ተወስኗል። በዚህ መሰረት ሻለቃ በቀለ ካሳ የኮሎኔልነት ማዕረግ ተሰጥቶታል።…”
.
ወ/ሮ ፀሐይ የምሩ ከመንግስቱ ኃ/ማርያም እጅ የባለቤታቸውን የማዕረግ ዕድገት ተቀበሉ።
(ይህንን መረጃ የነገሩኝ የነገሩኝ ልጃቸው ትዕግስት በቀለ እና ከሻለቃ ጋር አብረው ዘምተው የነበሩ መኮንን ናቸው)
—- ስንብት
ክብር ለካራማራ /ሰማዕታት/ ጀግኖቻችን ሁሉ ይሁን!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
.
(የካቲት 26 ቀን 2013 ዓም የሚከበረውን የካራማራ ድል 43ኛ ዓመት ለመዘከር የተፃፈ)
Filed in: Amharic