ጥቂት ቅኝት ስለ ቃኘውና አንዳንድ የታሪክ እውነታዎች!
አሰፋ ሀይሉ
በነገራችን ላይ ይህ በቅርቡ በዚህ የአብይ አህመድ ዘመነ መንግሥት (ወይም ከኢህአዴግ ወደ ብልጽግና በተደረገው የስምና የነውር ሽግግር ዘመን) በሐረሪ ክልልና በኦሮሚያ ክልል ይሁንታና ቸልተኝነት በሐረር ከተማ እንዲፈርስ የተደረገው የልዑል ራስ መኮንን ፈረስ – በህይወት እያለ መጠሪያ ስሙ ‹‹ቃኘው›› ነበር፡፡
የራስ መኮንን አኩሪ ሀገራዊ ተጋድሎና የዘመናዊ ፋናወጊነት ሥራ ለማስታወስ ሲባል – በ1951 በተባበሩት መንግሥታት ባንዲራ ሥር ወደ ኮሪያ የዘመተውና ከአሜሪካ 7ተኛው ብርጌድ ጋር አብሮ የተዋጋው የኢትዮጵያ ጀግና የኮሪያ ዘማች ሠራዊት መጠሪያም በልዑል ራስ መኮንን ፈረስ ስም ‹‹ቃኘው›› ተባለ፡፡ በመሆኑም ያ 122 ኢትዮጵያውያን በክብር ህይወታቸውን የሰዉለት፣ እና 536 ኢትዮጵያውያን ደግሞ ቆስለው ወደ ሀገራቸው የተመለሱለት፣ ያ ጀግና የኢትዮጵያውያን የኮርያ ዘማቾች ባታሊዮን፣ በዓለም ታሪክ መዝገቦች ሁሉ ላይ ‹‹ቃኘው ባታሊዮን›› (ቃኘው ሻለቃ) በሚል ስሙ ሲጠራ ይኖራል፡፡
ከዚያም በኋላ ደግሞ አሜሪካኖች በአስመራ ላይ በአፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ሁሉ እጅግ ግዙፉ የሆነውን የጦር ማዘዣ ጣቢያቸውን (ትልቁን ሚሊቴሪ ቤዝ) ሲያቋቁሙ ስሙን ‹‹ቃኘው ስቴሽን›› ብለው ነበር የሰየሙት፡፡ ያም በዓለም ታሪክ መዝገብ ሁሉ ላይ ሰፍሮ የምናገኘው ነው፡፡
ይህን በዓለም ሥሙ የተጠራ ታሪካዊ የልዑል ራስ መኮንን ፈረስ (ቃኘውን) ማን ይስራው? ልዑል ራስ መኮንን በዚያ ስሙ ዓለምን ባዳረሰ ፈረሳው በቃኘው ላይ ተቀምጠው ሲጋልቡ የሚያሳይ ‹‹ኤኩዌስትሪያን›› (የፈረስ) ኃውልት ለመሥራት ከጀርመን እስከ ኦስትሪያ፣ ከፈረንሳይ እስከ ጣሊያን ድረስ አሉ የተባሉ የዓለም ቅርጽ ሠሪ ጠቢባን ጥያቄያቸውን አቅርበው ነበር፡፡ ጃንሆይ የመረጡት ግን አንድን ሰው ብቻ ነው፡፡
እርሱም በብዙ የአፍሪካን የነጻነት ተጋድሎ በሚያወሱ እጅግ አስደናቂ የጥበብ ሥራዎቹ የተነሳ ‹‹የአፍሪካ የጥበብ ጀግና›› የሚል የክብር ሽልማትን የተቀበለው፣ እና የብዙ የአፍሪካ ነጻነት አባቶች የሚባሉትን የእነ ኔሬሬን፣ ካውንዳን፣ ንኩሩማህን፣ የግርማዊ ጃንሆይን እና የሌሎችንም ምስል በክብር ቤተመንግሥታቸው እየተጠራ (ኮሚሽን እየተደረገ) እና እጅግ ከፍተኛ ክፍያና ሽልማት እየተሰጠው ሲሠራ የኖረው፣ እና ምድር በሆነ ምክንያት ጠፍታ የሰው ልጅ ሥልጣኔ ከምድረ ገጽ ቢጠፋ እንኳ በጨረቃ ላይ መቀመጥ አለባቸው ተብሎ ምስላቸው በማይክሮ ፊልም ተገልብጦ በጨረቃ ላይ ከተቀበሩ 100 የዓለማችን ብርቅዬ የሰው ልጅ ድንቅ የአዕምሮ ፈጠራ ሥራዎች ውስጥ አንዱ የእርሱ የሆነው – የሀገራችን መኩሪያና የብዙ ዓለማቀፍ የክብር ሽልማቶች ባለቤት የሆነው – እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜይትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ነበረ፡፡
አፈወርቅ ተክሌ ይህን የልዑል ራስ መኮንንን ኃውልት ንድፍ ለመሥራት ጀርመንና ፈረንሳይ ድረስ ሄዶ የቢስማርክን፣ የሻርለማኝንና የደጎልን ኃውልቶች ተመልክቶ እንደመጣ – በፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሞ ለዓለም ከተሰራጨው ‹‹አፈወርቅ ተክሌ – ሕይወቱና ሥራዎቹ›› በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ከነልምምድ የእርሳስ ንድፎቹ ጭምር ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ሜይትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ይህን በዓለም ደረጃ የተደነቀበትን የልዑል ራስ መኮንን ኃውልት ሲሠራ – በሌሎችም የስቴይንድ ግላስ ሥራዎቹ እንደሚያደርገው – በሥሩ ረዳት አድርጎ የቀጠራቸው በርካታ የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜጎችም ተሳታፊ ነበሩ፡፡
ባለቅኔና ጸሐፊ ተውኔቱ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ በ1927 ዓመተ ምህረት በጻፉትና የአድዋን ጀግኖች በሚያነሳሱበት ታዋቂ መወድሳቸው ደጋግመው ስሙን የሚጠሩትን ራስ መኮንንን በአድዋ ደጋግሞ ስለሠራው ጀብዱ ድል ያደረገባቸውን ቦታዎች እየጠሩ እንዲህ እያሉ ያሞካሹታል፡-
«ይህ ራስ መኮንን ውብ ገበሬ ነው
አላጌ ላይ ዘርቶ መቀሌ ዐጨደው
ዐድዋ ከምሮ መረብ ላይ ወቃው፡፡
«ክብር ለመኮንን ሸመታ ረከሰ
ከዳጉሳው ይልቅ ጥሩ እህል ታፈሰ፡፡ »
— ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ (1927 ዓ. ም.)
የታሪክ ዝክሬን ከመጨረሴ በፊት አንድ እውነት ለታሪክ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ አስቀምጬ ላልፍ ወደድኩ፡፡ ይህን እውነት እኔ አልፈጠርኩትም፡፡ ተብሎ ያለቀና በተግባር ተፈትኖ የተረጋገጠ የታሪክ እውነት ነው፡፡ ለታሪክ ነው የምናገረው፡፡ ይህ እውነት ታሪክን ማጥፋት ያለመቻሉ እውነት ነው፡፡ ታሪክ ይሠራል እንጂ፣ ታሪክ አይጠፋም! እደግመዋለሁ፡፡ ታሪክ መሥራት እንጂ፣ ታሪክን ማጥፋት አይቻልም፡፡ ትናንትን ወደ ኋላ ተመልሰህ የሆነውን እንዳልሆነ ማድረግ የማይቻል ነው፡፡ ታሪክን በማጥፋት ታሪክ ለመሥራት የሞከሩ ሁሉ መና ሆነው ቀርተዋል፡፡ ታሪክን ሊያጠፉ የተነሱ ሁሉ ጠፍተዋል፡፡ ይህ የዓለማችን የተረጋገጠ እውነት ነው፡ የሰውን ልጅ ጥበብና አኩሪ ታሪክ በመደምሰስ – ተረስቶ የቀረ አንድም የዓለም ታሪክ የለም! ብዙዎች የማይገባቸው ይህ እውነት ነው፡፡
የሩሲያ ቦልሼቪክ አብዮተኞች የነገሥታቱን ሐውልት አፈራርሰው፣ ህይወታቸውን ጭምር አጥፍተው ሞክረውታል ታሪክ ማጥፋቱን፡፡ አልሆነላቸውም፡፡ ጭራሽ እንደማንኛውም የዓለም ንጉሥ ተረስቶ ሊቀር የነበረውን ዛር ኒኮላስንና ቤተሰቦቹን ዓለም አብልጦ እንዲያስታውሳቸው አደረጉ፡፡ ጭራሽ ቫቲካን ቅድስና ሁሉ ሰጥታቸዋለች ለንጉሣኑ፡፡
ከሩሲያ በተኮረጀው በራሳችን የ66ቱ አብዮት ማግስት የጃንሆይን ምስልና የአንበሳ ሀውልቶቻቸውን በማፈራረስ ብቻ ሳይሆን በህይወት ያሉ የሙዝየም አንበሶችን ጭምር በመግደል የጃንሆይን ታሪክ ለማጥፋት ተሞክሯል፡፡ ጃንሆይ የነኩትንና የሰየሙትን ሁሉ ነገር ስም በመቀየር ታሪክን ለማጥፋት የሞከረው ሁሉ ከሸፈ፡፡ ጭራሽ ከሆኑትም በላይ በዓለም ታሪክ፣ በሀገራቸውም የገዘፈ ታሪክ ይዘው ቀሩ፡፡ ታሪክን ማጥፋት አይሆንም፡፡ አይቻልም፡፡ ታሪክ ይሠራል እንጂ አይጠፍፋም፡፡
የአይሲስ የሐይማኖት አክራሪ ተዋጊዎች ከተሠራ ጀምሮ እስከዛሬ 2ሺ800 ዓመታት ሙሉ ተጠብቀው የኖሩትን በኒምሩድ የሚገኙትን የአሲርናሲፓል ጥንታዊ አዕማዶች በደማሚትና በቡልዶዘር ሲያፈራርሳቸው ዓለም ሁሉ ደንግጦ ይበልጥ እነርሱን የሚያጠፋበትን ፍጥነት አባባሱት እንጂ፣ ጭራሽ እነዚያን የጥበብ ሥራዎች ታዋቂ አደረጓቸው እንጂ፣ እንዳሰቡት ታሪክን ሊያጠፉ አልቻሉም፡፡
የታሊባን አክራሪ ጎረምሶችም በአፍጋኒስታን የዓለም ዕጹብ ድንቅ ቅርሶች የሆኑትንና ለ1ሺ500 ዓመታት በኖሩ ተከታታይ ትውልዶች ተጠብቀው የቆዩ የኢስትና ዌስት የቡድሃ አዕማዶችን በደማሚት ድምጥማጣቸውን ሲያጠፋ ዓለም ሁሉ ተባበረባቸው እንጂ፣ ታሪክን ከቶውኑ ሊያጠፉ አልቻሉም፡፡ ሂትለርን ታሪክን ሊያጠፋ ሃውልትና መጽሐፍ ሳይቀር ባደባባይ ያቃጥልና ያፈርስ ነበር፡፡ ባጭሩ ታሪክን ሊያጠፉ የሚነሱ ሁሉ፣ የራሳቸውን መጥፊያ ከማፋጠን ውጭ፣ እንደተመኙት ታሪክን አጥፍተው አያውቁም፡፡ እንደተባለው ታሪክን መሥራት እንጂ ማጥፋት አይቻልምና፣ አዲስ ታሪክ እንዲሠራ ምክንያት ይሆናሉ ታሪክ አጥፊዎች፡፡
አሁንም የጊዜያችን ቄሮ ተብዬዎችም ሆኑ የእነርሱን ስም እያስጠሩ በመንግሥት ይሁንታና ቸልተኝነት ታሪክን እናጠፋለን ብለው የተነሱት፣ የማይተካን ዕንቁ የጥበብ አሻራ በማፈራረስ ታላቅነትንና ብጽዕናን የተላበሱ መስሎ የሚሰማቸው የዘመናችን ነሆለሎችና ባለጊዜዎች – ይህ እውነት ሊገለጽላቸው ይገባል፡፡ ታሪክን ማጥፋት አ ይ ቻ ል ም ፡፡ አስራ ስድስት ነጥብ፡፡ ወተት ነጭ ነው፡፡ ወይም ከሰል ጥቁር ነው፡፡ ሲባል እንደማያከራክረው ሁሉ፡፡ በዓለም ሁሉ ተደጋግሞ ተፈትኖ የተረጋገጠ የታሪክ እውነት ነውና ይህም የሚያከራክር አይደለም፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜይትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥራው ምድር ብትጠፋ እንኳ እንዳይጠፋ ተብሎ በጨረቃና ስፔስ ላይ የተቀበረለት ሰው ነው፡፡ እርሱ የሠራውን የቃኘውን ፈረስ በማፈራረስ የእርሱን የጥበብ ከፍታ ታሪክ ልታጠፋው አትችልም፡፡ እጅግ የተከበሩ የብዙ የዓለም መንግሥታትን ሽልማት የተቀበሉትና ሀገራችንን ከጣሊያን (እና ያን አይተው እጃቸውን ከሰበሰቡ ከሌሎችም ቅኝ ገዢዎች ባርነት) የገላገሉን፣ ከባቡር እስከ ሥልክና አስፋልት ለሀገራችን ያመጡት፣ የለፉ፣ የወጡ፣ የወረዱት ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ – ዓለም ያወቃቸው፣ ሀገር የሞቃቸው፣ የዓለም የታሪክ መዝገብ ሥራቸውን በደማቁ የጻፈላቸው ታላቅ የኢትዮጵያ ክብር ናቸው፡፡ የእርሳቸውን የነሃስ ሃውልት ስላፈራረስክ፣ ስላጠፋህ – የእርሳቸውን ታሪክ አታጠፋውም፡፡
እንዲያውም አፈወርቅ ተክሌ እና ራስ መኮንን ታይቶ ወደማይታወቅ የክብር ከፍታ የሚወጡበት ጉዞ አሁን ይጀምራል፡፡ ታሪክ ይሠራል እንጂ አይጠፋም፡፡ ታሪክን ለማጥፋት የሻቱ ሁሉ ጠፍተዋል፡፡ እመኑኝ፡፡ እነዚህም ይጠፋሉ፡፡ ታሪካቸው ብቻ ይኖራል፡፡ እውነቱ ይኸው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በፍቅር ትኑር!
በተለይ የራስ መኮንንን! የእምዬ ምኒልክን! የእቴጌ ጣይቱን! የጎበናን! የባልቻን! የአሉላን! የመንገሻን! የስንቱን ባለታሪክ ስም ጠርተን እንዘልቀዋለን! የታሪክ ሀብታም ነን! የታሪካችን የታላቅነት ጉዞ አሁን ይጀምራል! የእነርሱን የጀግኖቻችንን ትንፋሽና ጥበብ ይስጠን!
የአድዋ ጀግኖቻችንን ልብና ልቦና ይስጠን!
ሌላ የምለው የለኝም!
አበቃሁ፡፡