>

እጅግ ስሜታዉ፤ ተጠራጣሪ፤ ጠንቃቃና ጨካኝ እንደሆኑ ስለሚነገርላቸው የደርጉ. ሊቀመንበር ህይወት በወፍ በረር ቅኝት...!!! (አንተነህ ዘ ሠላም)

እጅግ ስሜታዉ፤ ተጠራጣሪ፤ ጠንቃቃና ጨካኝ እንደሆኑ ስለሚነገርላቸው የደርጉ. ሊቀመንበር ህይወት በወፍ በረር ቅኝት…!!!
(አንተነህ ዘ ሠላም)

የየሐገራትን የሐገር ምስረታ ታሪካቸው እንደበጋ ሠማይ የጠራ፣ የነፃ ሳይሆን በጥቁርና በነጭ ቀለሞች ድብልቅ የቀለመ ዥንጉርጉር እንደነበር ለመናገር የታሪክ ሳይንቲስት መሆን አያስፈልግም። ሀገራትን የሚዘውሩት የመንግስት መሪዎች ሰው እንደመሆናቸው መጠን በሰውኛ ተፈጥሮዎዐቸው የሚያጠፉትም፣ የሚያለሙትም ነገር መኖሩ ይታወቃልና ነው። ይሄንንም አስቀድሞ ማወቅና መረዳት ከፍርደ ገምድልነትን ያቅባል አስባለው። ሰው ይሳሳታል፣ ያጠፋል፣ ያፋልሳል። ፍፅምናን ላልተጎናፀፈው ሰው፤ ይሄ ሰውኛ ተፈጥሮው ሊያስደንቅን አይገባም። የአብዛኛዎኛችን ስህተትም የሚጀምረው ይሄን ባህሪ ካለመረዳት የሚመነጭ ይመስለኛል።
ኢትዮጵያም እንደሀገር ፀንታ በመንግስት ጥላ ስር ከተጠለለች አያሌ ዘመናት እንዳስቆጠረች በዘርፉ ጥናታቸውን ያሰፈሩ ምሁራን ይገልፃሉ። ሁሉም መሪዎች በሚባል ደረጃ ልማትም ከውነዋል፣ ጥፋትም ሰርተዋል። ይሄ የማይታበል የታሪክ ሐቅ ነው።
የሀገራችንን ረጅሙን የመንግስት በትረ ስልጣን ጨብጦ ከነበረው ዘውዳዊ ስርዓት ሌሎች ሀገራት ላይ እንደተስተዋለው በብዙ ደም መፋሰስና እልቂት ሳይሆን በተቃራኒው በጥቂት ደም ብቻ ወታደራዊ መንግስት ዙፋኑን ተቆናጦ የነበረ ቢሆንም ከኮርቻው ማግስት ግን በተከሰተው ዕርስ በዕርስ መጠፋፋት ሀገራችን በደም ዝናብ እንድትታጠብ አስገድዷታል። ከዘመነ መሳፍንት በኋላ ዳግም የሀገር ውድቀት ሆኖ በታሪክ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል። ለ17 ዓመታት የእናቶች እንባ በእጅጉ የደማበት፣ ወላጆች ጧሪ ቀባሪ ያጡበት፣ ሕፃናት ተንከባካቢያና አሳዳጊ እናት አባት ብርቅ የሆነባቸው ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። በተለይ ደግሞ የሀገር አቅኚ ትንታግ ወጣት ምሁራን የሞቱት ሞተው፣ የቀሩት ደግሞ ከሀገር ሸሽተው የተደዱበትም ነበር። ለአንድ ደሃ ሀገር ይሄ ትልቅ ክስረት ሆኖ ቢያልፍም በተለይ የአሁኑ ትውልድ የተማረበት አይመስለኝም። እርስ በርስ ጎጥ፣ በጎሳ፣ በብሄር ተቧድነው ደግመኛ የደም ባህር ለመፍጠር የሚወተረተሩ የተማሩ ደናቁርቶችን አለን አለን እያሉ ነው።
ታሪካችን አስቀያሚ ነበር። አዎ ታሪካችን አስቀያሚ ነበር። ግን ዋናው ነጥብ ከዚህ ከተበላሸው የጋራ ታሪካችን የቱን ጥለን፣ የቱን መውሰድ አለብን የሚለው ነው። ሁሉም አስያስፈልግም ብሎ ጠቅልሎ መጣል የእኛነታችንን፣ የማንነታችን ስሪት ነቅሎ መጣል በመሆኑ ከታነፀው ላይ የማያስፈለወጉትን ሳንካዎች ከርክሞ ማስተካከል ይበጃል ባይ ነኝ። ወደ ተነሳውበት ልመለስና።
የወቅቱ ወታደራዊ መንግስት ርእሰ ብሔር የነበሩት መንግስቱ ኃ/ማርያም ከስልጣን ወርደው ወደ ዚምቧቤ ካቀኑ በኋላ ከተፃፉላቸው ጥቂት መጻሕፍት መካከል የጋዜጠኛ ገነት አየለ አንበሴ ይጠቀሳል።
በጥገኝነት ከተሸሸጉበት ዙምቧቤ መንግስቱ ኃ/ማርያምንም ለማግኘትና ለማናገር ብሎም በወቅቱ ስለነበረው የታሪክ ጭቅጭቅንና ውዝግብን ለማጥራት እንዲሁ በቀላሉ የተገኘ በለስ ሳይሆን በብዙ ድካምና ጥረት የተገኘ ዕድል ነው። ጋዜጠኛዋ እንደምትናገረው የይለፍ መንገዱን አግኝታ ወደ ዙምቧቤ ሐራሬ ካቀናች በኋላ እንኳን መንግስቱ ጋር ለመቅረብ እንዲሁ በቀላሉ የሚሆን ነገር አልነበረም።
በ1991 ዓ/ም በመጀመሪያ ዙር ጉዞዋ በአካል ሳታገኛቸው 15 ቀናት ሙሉ ተጉላልታ ጥያቄና መልሱን በመልክተኛ አድርጋ ቢሆንም በመጨረሻ አግኝታቸው ወደ መኖሪያ ቤቷ ፓሪስ ተመልሳለች። በ1994 ዓ/ም ደግሞ በድጋሚ በማቅናት ለ8 ሰአታት የፈጀውን ቃለ ምልልስ አድርጋ በሁለት ቅፅ፣ በአንድ መጻሕፍ ለማሳተም ችላለች።
ጋዜጠኛዋ ሳትሰለች፣ ሳትፈራ እንደውም እየሞገተች፣ የተከራከረች በርካታ ጥያቄዎችን ለማንሳት ሞክራለች። በዚህ አጋጣሚ ለታሪክ ተጨንቃና አስባ በመጻሕፍት መልክ ስለሰነደችልን ክብርና ምስጋና ይገባታል። እናም ሌተና ኮሎኔል መንግስቱም የተነሳላቸውን ጥያቄዎች አንዳንዴ በጩኸትና በቁጣ እጆቻቸውን ሁሉ እያወራጩ ሲመልሱ፣ ሌሎቹን በሳቅና ፈገግታ፣ የተቀሩትንም በኖርማል መንገድ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ።
ያልተነሳላቸው ጥያቄ የለም ለማለት ባይቻልም በጣም አስፈላጊና አንገብጋቢ ጥያቄዎች ተሰንዝረዋል። አንዳንዴ ቀጥተኛ ለሆኑት ጥያቄዎች በቀጥታ ምላሽ ሲሰጡ፣ አንዳንዴ ደግሞ መጥራት አለባቸው ብለው ላመኑበት ጉዳዮች ወደ ኋላ ተጉዘው ታሪካዊ ዳራውን በማውሳት ወደ መልሱ ያቀናሉ፣ ፕሬዝዳንቱ። ከመለሷቸው መልሶች ብዙዎቹን አልተስማሙባቸው ወይም አጣጥለዋቸዋል ማለት ይቻላል። “እውነት አይደለም! ሐሰት ነው!” ሲሉ ይነበባሉ። በተለይ ስለ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃነመስቀል ረዳና ሀይሌ ፊዳ ግድያ ዙሪያ ሽምጥጥ አደርገው በመካድ እጃቸውን ሲታጠቡ ይታያሉ። “የመንግስት እጅ የለበትም! እኔ ምንም አላውቅም ይሄን የሚያውቀው እገሌ ነው! አሁን ካንቺ መስማቴ ነው” ይላሉ። የአንድ ሀገር መሪ ነብረው ጥቃቅኑን እንኳ ይቅር እነዚህን ዐብይና ትልልቅ ጉዳዮች እንደማያውቁ ሆነው ሲናገሩ መስማት ለሰሚው በተለይ ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው ሕመሙና ሀዘኑ ከባድ እንደሚሆን ግልፅ ነው። እናም ከላይ የተጠቀሱትን ሰዎች ቃለ ምልልሱን ማሳጠር ተገቢነቱ ስላልታየኝ እንደወረደ በቀጣይ እከትበዋለው። በማያያዝም ሌሎች ፀሃፍት በዛው ርዕሰ ጉዳይ ምን እንዳሉ ይዤ እቀርባለው።
ብቻ ግን ምንም አሉ ምን ሙሉ ግንዛቤ እንዲኖራቹህ መጻሕፉን እንድታነቡት በመጋበዝ ነገር ግን ከተነሱት ጥያቄና መልሶች ውስጥ ዋና ዋና እና አንኳሮቹን እንደሚከተለው በማሳጠር ለማቅረብ ጥረት ተደርጓል።
ትውልድና ቤተሰብ
ከፋሺሽት ጣልያን ወረራ ማግስት ግንቦት 19 ቀን 1933 ዓ/ም አዲስ አበባ ጊዮርጊስ አጠገብ 3ተኛ ፖሊስ ጣቢያ በሚገኝበት አካባቢ ፕ/ት መንግስቱ ኃ/ማርያም እንደተወለዱ ይናገራሉ። አባታቸው የሸዋ ኦሮሞ ሲሆኑ በእናታቸው ወገን ደግሞ ከሰሜን ሸዋ ይመዘዛሉ። አባታቸው ወታደር ነበሩ።
ሰውነት/ባህሪ
“መንግስቱ ሲናደዱ በጣም ተቆጪ ሆነው ማመዛዘን የሚባል ነገር ፈፅሞ አይታይባቸውም እናም ለውሳኔ ይቸኩላሉ። በፀጥታ ሰውን ማድመጥና ማስታወሻ መያዝ ይቀናቸዋል። ያደመጡትን ደግሞ ነጥቡን ሳይስቱ የማስታወስ ችሎታ የታደሉ ናቸው። የምግብ ወስፋታቸው ብዙም አይደለም። ለኮፍ፣ ለኮፍ ማድረገ ያዘወትራሉ። በስልጣናቸው ለሚመጣባቸው ሰው ምህረት የለሽ ጨካኝ ይሆናሉ። ማንንም አይምሩም። ቆቅ! ሲበዛ ተጠራጣሪና ጠንቃቃ ስለሆኑ ነገር በሩቁ ይሸታቸዋል” ብለው የሚያወቋቸው ሰዎች ይናገሩላቸዋል።
አብዮቱ ሲፈነዳ
መንግስቱ ዘውዳዊው ስርዓት ተገርስሶ ለወጥ በእጅጉ ናፋቂ እንደነበሩ ይገልፃሉ። በሕዝቡ የለት ተለት እሮሮ እንደሚንገበገቡ በአንፃሩ ደግሞ ጭቁኑን ሕብረተሰብ እንደ መዥገር ተጣብቀው የሚመጡትን የመኳንንትና የመሳፍንት ዘሮች እንደሚያበሳጯቸው ያወሳሉ። የአብዮቱን ሂደት በሶስት ምዕራፍ ይከፍሉታል። የአንደኛና የሁለተኛው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቆ በሶስተኛው ምዕራፍ ላይ ከሻለቃነት ማዕረግ በታች ያላቸውን ሰራዊት ከየጦር ሰፈራቸው ተመርጠው አዲስ አበባ 4ተኛ ክ/ጦር ተሰባስበው በከፍተኛ ትግል ደርግን እንዳቋቋሙ ያትታሉ።
 የጃንሆይ እስርና ሞት
ደርግ እንደተቋቋመ ባለፈው ስርዓት በዝባዥና አቆርቋዥ የነበሩትን ባለስልጣናት አንድ ባንድ ተለቅመው ወህይኑ ወረዱ። በመጨረሻም ንጉሱም ታሰሩ። በእርግጥ ንጉሱ ግዞት ላይ እንዳሉ ሕይወታቸው በማለፉ እስካሁን ድረስ ግድያ ስለመሆኑ ጥርጣሬና ክስ አለ። “ጃንሆይ አብዮቱን ለማደናቀፍ ስጋት አልነበሩም። በተደጋጋሚ ይታመሙና አርጅተው እንደነበር” በመግለፅ ሞታቸው ተፈጥሮዋዊ እንደሆነ መንግስቱ ይሞግታሉ።
የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎች
ደርግ ያሰራቸውን የአፄ ኃ/ስላሴ ባለስልጣናት በተለምዶ ስልሳዎቹ በመባል የሚታወቁትን እና ጀነራል አማን ሚካዔል ጨምሮ ያለችሎትና ዳኛ ረሸኗቸው። ቢሆንም ጋዜጠኛዋ ያነጋገረቻው የቀድሞ የደርግ መኮንኖች ሁሉም በሚባል ደረጃ ሁነቱ እንደሚፀፅታቸው እና መሆን ያልነበረበት ድርጊት እንደነበር ተናዘዋል። በእርግጥ ሌ/ኮ መንግስቱም ድርጊቱ ስህተት እንደነበርና ማንም ሰው ሊያስደስት የሚችል ነገር እንዳልነበረ ቢገልፁም የትኛውም አባል ሊጠየቅ፣ ሊከሰስ እንደማይገባ ግን ያሰምሩበታል። ም/ክ ወቅቱ የለውጥ አየር የሚነፍስበት ጊዜ ስለነበር ሁሉም አባል ስለፍትህ በእልህና በቁጭት እሳት የሚተፉበት በዚህም የደርጉ ህልውና አደጋ ውስጥ ነበር ይላሉ።
ቀይ ሽብር
“ስለቀይ ሽብር ሁሉም ሰው ያወራል ግን ስለነጭ ሽብር ምንም ድምፅ የለም። ከቀይ ሽብር በፊት ነጭ ሽብር ነው መጤን የሚገባው” ብለው ይጠይቃሉ። “የተማሪዎችን ንቅናቄ ተከትሎ ጊዜው ብዙ ፓርቲዎች እንዲወለዱ አስቻላቸው። ከዚህ ውስጥ ኢሕአፓ አንዷ ነች። ደርግ ለተራማጅ ፓርቲዎች ጥሪ በማድረጉ ቡዙዎቹ ጎረፉ። ይሄም ኢሕአፓን አላስደሰታትም። ም/ክ ኢሕአፓ ቤዟን አሲምባ ትግራይ ሆኖ የትጥቅ ትግልን ብቸኛ አማራጯ አድርጋ የምትከተል ስለነበረች ነው። የሰራዊት ስልጠና እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ደግሞ በሻቢያ በኩል ከአረቡ ክፍል ዘርግታለች። በምልሹ ደግሞ ለሻቢያ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን በማለት የመገንጠል አማራጭ አስቀምጣ ነበር” ይላሉ ፕ/ቱ።
በዚህም ምክንያት ስለኢሕአፓ የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ በማድረግ እርቃኗን እንዳስቀሯትም ያክላሉ። በዚህ ብስጭት እሳቸውን የመግደል ሙከራ እንዳደረጉባቸውና መትረፋቸውም በትዓምር እንደነበር ያስታውሳሉ። ከዚያ ቀጥሎ የሌሎችን ፓርቲ አባላትን መግደል በመጀመሯ ነጭ ሽብርን አወጀች። “የዜጎችን ደህንነትና የሀገር ሕልውናን ለማስጠበቅ ቀይ ሽብር ነጭ ሽብርን እንዲቀለብስ ነው የታወጀው” ሲሉ ያብራራሉ።
 የጦሩ መሸነፍ
ከአብዮቱ ማግስት ጀምሮ ሀገራችን በብዙ ጦርነት አውድ የተፈተነችበት ጊዜ ነበር። በውስጥ የኢሕአፓ የከተማ ትጥቅ ትግል፣ የኤርትራ ገንጣዮች፤ በውጪ ደግሞ የሱማሌ ወረራ አብዮቱንና ሰራዊቱን ትንፋሽ ያሳጡበትና ፋታ የነሱበት ጊዜ ነበር። የጦርነቶቹ መራዘም ሰራዊቱ ላይ መሰላቸት ሲያመጣ፤ የጦር መሳሪያና ቀለብ እጥረት ደግሞ የስነ ልቦና ውድቀት አስከተለ፤ የአመራሩ መዝረክረክና የሰፋ እንኳ ባይሆንም ሙሰኝነቱ ሲታከልበት ለውድቀቱ የራሳቸውን ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል ብለው ቃላቸውን ይሰጣሉ። በምስራቅ ግንባር በሶማሌ ወራሪዎች ላይ ድል ቀንቶን ነበረ፤ በዚያው ሞራል ተገንጣዮች ላይ በወሰድናቸው ጥቃቶች አድክመናቸው የነበር ቢሆንም የኛ ዐብይ ስህተት የሚመስለኝ ጨርሰን ሳናጠፋቸው በቀጥታ ወደ ኢኮኖሚ ግንባታ ፊታችንን በማዞራችን ሻዕቢያ እንዲያንሰራራ በር ከፍቶለታል ብለው ያምናሉ።
በመቀጠል ውስጣችን የተሰገሰጉት ሰላዮች ቁልፍ መረጃዎችን በማውጣት እና የጦር ጀነራሎች በገንዘብ መገዛት፣ የጦሩ አርስ በርስ ያለመናበብና ቅንጅት መጥፋት ሞታችንን አፋጥኖታል ብለው ይጨምራሉ።
መፈንቅለ መንግስቱ
ፕ/ት መንግስቱ ለጉብኝት ወደ ምስራቅ ጀርመን ባቀኑበት ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ/ም የተሞከረው የጦር የጀነራሎቹ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ምንም ውጤት ሳያመጣ ሊከሽፍ ችላል። ጠንሳሾቹ “መንግስቱ በጦር እንጂ በስምምነት አያምንም። ለዕርቅ መች በሩን ከፍቶ ያውቃል። እኛ በድርድርና በዕርቅ ነገሩን እንፍታው” ብለው የተወሰኑ የጦር መኮንኖችን ወደ ራሳቸው ሳቡ። በሽኝቱ ፕሮግራም ላይ ጠንሻቹ ባለመገኘታቸው ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገቡ አደረጋቸው። ያለ መከላከያ ሚኒስቴሩ ዕውቅና በመከላከያ ሚኒስቴር ቅጥር ስብሰባቸውን በማድረጋቸው ደግሞ መፈንቅለ መንግስቱን እርግጥ አደረገው። ከዛ በአስቸኳይ ከበባ ተደርጎ ኩዴታው ሊከሽፍ ችሎ ጥቂት ጀነራሎች ወዲያው ራሳቸውን ሲያጠፉ ጥቂት ደግሞ ለመሰወር ችለዋል። ብዙሃኑ ባለበት ተማርኳል። ፕ/ቱ ከሄዱበት አገር ሲመለሱ የጦር ወንጀለኞች ችሎት ተቋቁመው ጥፋተኛ ሆነው የተገኙትን እንዲረሸኑ አድርገዋል።
ከሐገር ፈረጠጡ ወይስ…
“በሰሜኑ ክፍል ከሻቢያ ጋር ያደረግነው ጦርነት እንደምንሸነፍ ቀድሜ የተረዳሁት ምፅዋን የለቀቅ ቀን ነው” ይላሉ ፕ/ት መንግስቱ። ምክንያቱም ለጦሩ የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ማቀበያና ማድረሻ መንገድ በመዘጋቱ ነው። ቀጥሎ የአሰብ ወደብን ተነጠቁ። እና ሁሉም ነገር እያበቃለት በሚመስልበት ሰአት የዩኒቨርሲቲ ተማርዮችን ብላቴ ማሰልጠን ጀምረው ነበር። እናም 70 ሚሊዮን የሚያወጣ ጦር መሳሪያ ግዢ ከቻይና በዱቤ ፈፅሞው ስለነበር ተማሪዎቹን ሊጎበኙ ባቀኑበት ብላቴ ሳያርፉ በድብቅ ወደ ኬንያ ሄዱ። “እኔ ከቻይና የሚመጣውን መሳሪያ በሞባሳ ወደብ የሚገባበትን መንገድ ላመቻች እንጂ ሀገር ትቼ አልሄድኩም። ገና እግሬ ከመውጣቴ ወንበሬን ነጠቁኝ” ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ “አይ በዕለቱ ዕለት ባለቤታቸው ወ/ሮ ውባንቺ ወደ ዙምቧቤ በማቅናታቸው ቀድሞ ለመውጣት የታሰበበት እንጂ ፕ/ቱ እንደሚሉት አይደለም” የሚሉ አሉ።
ሆነም ቀረ ፕ/ቱ መንግስቱ ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት ከመሯት በኋላ ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ/ም የበትረ ስልጣናቸው መጨረሻ ነበር።
ቸር ጊዜ!
Filed in: Amharic