>
5:18 pm - Monday June 15, 3265

በማቴሪያል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ፈርቀዳጅ የሆነችው ኢትዮጵያዊት እንስት ተመራማሪ፦ ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ 

በማቴሪያል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ፈርቀዳጅ የሆነችው ኢትዮጵያዊት እንስት ተመራማሪ፦ ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ

ፕሮፌሰር ሶስና ኃይሌ እ.ኢ.አ በ 1958 ከአዲስ አባባ የተገኘች ኢትዮጵያዊት ሳይንቲስት ናት፡፡ በ1967 በሃገሪቱ የመንግስት ለውጥ መምጣት ተከትሎ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ አሜሪካ ለመሰደድ የተገደደችው ፐሮፌሰር ሶስና አብዛኛውን የህይወት ጊዜዋንም በዚህ አንድታሳልፍ ሆናለች፡፡ ፐሮፌሰር ሶስና ከቤተሰቦቿ ጋር አብራ በመሆን የልጅነት ጊዜዋን በሚኒሶታ ሃገረ ግዛት ገጠራማ አካባቢ ካደረገች በኋላ በ1986 የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት በማቴሪያል ሳይንስና በኢንጂነሪንግ ማግኘት የቻለች ሲሆን፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ማሳካት ችላለች፡፡
ፐሮፌሰር ሶስና በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት የፒችዲ ትምህርቷን ለመማር እንዲያስችላት የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካገኘችበት የማሳቹሴትስ የቴክኒሎጂ ኢኒስቲትዩት ያቀናች ሲሆን፤ በዚህም እንዲሁ በምትወደው የማቴሪያል ሳይንስና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ መመረቅ ችላለች፡፡ ፐሮፌሰር ሶስና ከዚህ የተሳካ የትምህርት ጉዞዋ በኋላ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ካገኘችበት የካልቴክ ፋካልቲ ከማምራቷ በፊት ሲያትል በሚገኘው የዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት የሰራች ሲሆን በዚህ የሶስት ዓመት ቆይታዋም ሀገሯን የሚያኮራና አፍሪካንም የሚያስጠራ ትልልቅ የምርምር ስራዎችን ለመስራት በቅታለች፡፡
ፐሮፌሰር ሶስና ድምራቸው ከ150 በላይ የሆነ የጥናትና ምርምር ፅሁፎችን በግል እና ከሌሎች ምሁራን ጋር በጋራ በመቀናጀት ሰርታ ለህትመት አብቅታለች፡፡ በስሟ የተመዘገቡላት ፓተንቶችም ቢሆን አስራ አምስትን ተሻግረዋል፡፡
ከነዚህ የህትመት እና ምርምር ውጤቶች ውስጥ ብዙሃኑ በጠጣር የአዮን ቁስ እና መሳሪያዎች ላይ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚያጠነጥኑት የፕሮፌሰር ሶስና ስራዎች መካከል ደግሞ ከዓመታት በፊት የሰሩት አዲስ ዓይነት የፊውል ሴል ከሌሎች ፈጠራዎቿ ይጠቀሳል፡፡ በወቅቱ ሶስና ኬሚካሎችን ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል በመቀየር ለመኪኖች፣ ሃይል ማመንጫዎች እንዲሁም ሌሎች ሃይልን ለሚጠይቁ ተግባራት ንፁህ የሃይል ምንጭ በመሆን እንዲያገለግለ፤ በማሰብ የፊውል ሴሎችን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽል ቁስን ለመስራት አልማ ተነሳች፡፡ ይህ ሃሳቧም በአይነቱ አዲስ የሆነ የኃይል ማመንጫን ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንስ የሚችል የሱፐርፕሮቶኒክ ቅንብር መስራትን ያጠቃልላል፡፡ ሆኖም ይህ ሃሳቧን ተቀብለው የአሰራር ስርዓታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ አዲስ ከመቀየር የታቀቡት የፊውል ሴል አምራቾች የራሷን ቤተ-ሙከራ ተጠቅማ በዓለም የመጀመሪያውን ጠጣር የአሲድ ፊውል ሴል ቁስ አካል እንድትፈበርክ ምክንያት ሆኗት፡፡ ኋላ ላይ ይህን አዲስ ፈጠራዋን የቀድሞ ተማሪዎቿ በንግድ ሰርቶ ማሳያነት የተጠቀመበት ሲሆን ለተመራሪዋም በአረንጓዴ የሃይል ልማት ዘርፍ ዕውቅናን እንድትሸምትበት አስችሏታል፡፡
ፕሮፌሰር ሶስና በአሁኑ ሰዓት ጠጣር ፊውል ሴሎችን በተለይም ለከባቢ ተስማሚ የሃይል ምንጭ መሆን በሚችሉት ላይ አተኩሮ የሚሰራን የምርምር ቡድን በሃላፊነት በመምራት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ረገድ ይህ ቡድን የተለያዩ ስኬቶችን በማስመዝገብ ላይ ሲገኝ ከቅርብ ስኬቶቹ መካከልም ውሃና ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን በቴርሞ ኬሚካል ሂደት አማካኝነት በመጠቀም የፀሐይን ኃይል ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ሌላ ምዕራፍን የከፈተ ነበር፡፡ በፕሮፌሰር ሃና እና ቡድኗ እየተሰራባቸው ካሉት ስራዎች ውስጥ ፕሩቶንን አስተላላፊ ጠጣር አሲድ እና ፐሮቭስካይት ኤሌክትሮይቶች፣ የኤሌክትሮን እና ኦክስጅን ድብልቅን አስተላላፊ ፍሎሪት እና ፐሮቭስካይት እንዲሁም ኢ-ስቶይኪዮሜትሪክ ኦክሳይዶችን ማበልፀግ ይገኝበታል፡፡
ይህች ኢትዮጵያዊት እንቁ ተመራማሪ በትልቁ ስሟን ከሚያስጠሩ ስራዎቿ አንዱ ከሆነው የፊውል ሴል ፈጠራዋ በተጨማሪ በሴራሚክ ሳይንስ፣ በኤሌክትሮኬሚካል እና በፋንክሽናል ሶሊድ (electrochemical and functional solids) የደረገቻቸው ምርምሮች እና ያሳተመቻቸው ፅሁፎች በተሰማራችበት የሳይንስ ዘርፍ ከሚኖረው አበርክቶት ባለፈ ለብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን እና ሴት ተመራማሪዎች የሚኖረው ጠንካራ መልእክት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ፐሮፌሰር ሶስና ለሰራቸው ስራና ላበረከተችው የምርምር ውጤት እውቅና የሚሆን ሽልማቶችን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያገኘች ሲሆን ከእንዚህ ውስጥም በ1989 በማቴሪያል ሳይንስ ባደረገችው ሰፊ ምርምር ያገኘችው የሃርዲ አዋርድ፣ በ2002 በፊውል ሴል ፈጠራዋ ያገኘችው የኬሚካል ፖይነር አዋርድ እንዲሁም በ2004 በሴራሚክ ሳይንስ ምርምሯ ያገኘቸው የዓለም አቀፍ የሴራሚክ ፕራይዝ በጥቂቱ የሚጠቀሱ የእውቅና ሽልማቶቿ ናቸው፡፡
ምንጭ፡ ቴክ-ሳይንስ ቅፅ 15 @Technology & Innovation Institute
Filed in: Amharic