በፀጥታው ምክር ቤት ክርክር ሊደረግበት ቀጠሮ የተያዘለት የትግራይ ክልል ጉዳይ ወዴት ሊያመራ ይችላል?
ዮሐንስ አንበርብር
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤትን ለአንድ ወር ለመምራት የሊቀመንበርነት ወንበሩን እ.ኤ.አ. ማርች 1 ቀን 2021 የተረከበችው አሜሪካ፣ በሊቀመንበርነት በምትቆይባቸው 30 ቀናት ቅድሚያ እንደምተሰጣቸው ከገለጸቻቸው ጉዳዮች አንዱ የትግራይ ክልል ሰብዓዊ ሁኔታን ይመለከታል።
ይህንን ፍላጎቷን ለመፈጸም ተቀራራቢ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚከተሉ የአሜሪካ ወዳጅ አገሮችን በማስተባበር አጀንዳው እንዲነሳ ያደረገች ሲሆን፣ በዚህ ሳምንት ረቡዕ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በምክር ቤቱ ቋሚ አባል አገሮች ክርክር ሊደረግበት ቀጠሮ ተይዟል።
የአሜሪካ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘ የክልሉ ነዋሪዎች በከፍተኛ የምግብና የሕክምና አቅርቦት ችግር ውስጥ እንደወደቁ፣ እንዲሁም የሲቪሎችን ግድያ ጨምሮ ፆታዊ ጥቃት እንደ ተፈጸመባቸው አስታውቋል። ችግሩ ዕልባት እንዲያገኝ መደረግ አለባቸው ተብለው በአሜሪካ መንግሥት መግለጫ ከተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የተራድኦ ድርጅቶች ያለ ገደብ በትግራይ ክልል እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ አንዱ ሲሆን፣ በአካባቢው ተሰማርተዋል የተባሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ከክልሉ በፍጥነት እንዲወጡ ማድረግ ሌሎቹ ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአሜሪካ መንግሥት መግለጫ ወዲያውኑ ምለሽ የሰጠ ሲሆን፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ በተለይም የአማራ ልዩ ኃይል በትግራይ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንዲሰማራ መደረጉን በተመለከተ ያስተላለፈችው መልዕክት ተገቢነት የሌለው፣ በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር እንደ መሆኗ የውስጥ ችግሮቿን በራሷና በመረጠችው መንገድ እንደምትፈታ የገለጸው መግለጫው፣ ይህ የማንኛውም ሉዓላዊ አገር ሥልጣን ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትን ሉዓላዊነት የሚጥስ የውጭ ኃይል ጣልቃ ገብነት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ብሏል። የኤርትራ ወታደሮችን ጉዳይ በተመለከተ ግን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ለተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወዳጅ አገሮች እንዲያግዙት ግብዣ ማድረግ የሚችል ቢሆንም፣ ለኤርትራም ሆነ ለሌላ አገር ድጋፍ እንዲያደርጉ አለመጋበዙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ሰሞኑን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮችና በክልሉ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ ግብረ ኃይል ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ የተራድኦ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ መፈቀዱንና ተፈጽመዋል የተባሉ ሰብዓዊ ጥሰቶችን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የውጭ ተቋማት ትብብርን በማከል እንደሚያከናውን አስታውቀዋል።
የተራድኦ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ያለ ገደብ እንዲንቀሳቀሱ ቢፈቀድም፣ እነዚህ ተቋማት በእንቅስቃሴያቸው ወቅት ለሚገጥማቸው ማንኛውም አደጋ ኃላፊነቱን ራሳቸው እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።
እነዚህ ተግባራት በኢትዮጵያ በኩል ከተወሰዱ በኋላ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒዮ ብሊንከን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር ባለፈው ረቡዕ የተወያዩ ሲሆን የተወሰዱትን ዕርምጃዎችም እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አሜሪካ ጉዳዩ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲታይ የጀመረችው እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን፣ ባለፈው ሐሙስ በአየርላንድ መንግሥት አቅራቢነት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።
ለዚህ ውይይት መነሻ እንዲሆንም የተመድ የአስቸኳይ ዕርዳታ አስተባባሪ ማርክ ሎኮክ፣ በትግራይ ክልል አለ ያሉትን የሰብዓዊ ዕርዳታ ቀውስ የተመለከተ ሪፖርት አቅርበዋል።
ባቀረቡት ሪፖርትም በክልሉ 4.5 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው የገለጹ ሲሆን፣ በገጠራማ አካባቢዎች ዕርዳታ ማድረስ ባለመቻሉ ሁኔታው አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።
በክልሉ ከነበሩ 205 የሕክምና ተቋማት ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት 22 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊው፣ የመጠጥ ውኃና የንፅህና መጓደል ወርሽኝ ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
የተራድኦ ተቋማት ዕርዳታ ለማቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ከሰሞኑ መሻሻል ቢስተዋልም፣ በቂ ባለመሆኑ የበለጠ ሊሠራ እንደሚገባ ተናግረዋል። የዕርዳታ ፍላጎቱም በገለልተኛ አካል በቋሚነት እየተጠና አቅርቦቱ ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌትም ለፀጥታው ምክር ቤት በክልሉ አሉ ያሉዋቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተመለከተ ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን፣ ፆታዊ ጥቃትንና ግድያን ጨምሮ አሰቃቂ ጥሰቶች መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
የተፈጸመው ጥሰት ዓለም አቀፍ ወንጀል የሆኑትን በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልና የጦር ወንጀሎችን ሊያቋቋሙ ይችላሉ ተብሎ እንደሚገመት አስረድተዋል።
ለእነዚህ የሰብዓዊ ጥሰቶችም በሁሉም አካላት ማለትም በመከላከያ ሠራዊቱ፣ በአማራ ክልል ኃይል፣ በኤርትራ ወታደሮችና በሕወሓት ጦር እንደተፈጸሙ ተናግረዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት በዚህ መሠረት መነሻ ውይይት ካደረገ በኋላ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት ለመምከር ለመጪው ሳምንት ረቡዕ ቀጠሮ ይዟል። በመጪው ሳምንት የሚደረገውን ውይይት ተከትሎም በኢትዮጵያ ላይ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚችል ይጠበቃል።
ውሳኔው ወዴት ሊያመራ ይችላል?
በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ የሰብዓዊ ሁኔታን በተመለከተ በአሜሪካ መሪነት በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ለምክክር የሚቀርበው አጀንዳ፣ ከላይ በተመድ የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪና በተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አማካይነት በአስረጂነት የቀረቡት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚቀርብ እንደሆነ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች የተላለፈ መረጃ ያመለክታል።
ሁሉም ሚሲዮኖች የተላለፈላቸውን መረጃ መሠረት አድርገው ተልዕኳቸውን እንዲወጡ በተለይም በምዕራብ አውሮፓ፣ በቻይና፣ በሩሲያ፣ በፈረንሣይና በአሜሪካ የተመደቡ አምባሳደሮች በዚሁ ጉዳይ ላይ በተለየ መንገድ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መታዘዛቸው ታውቋል።
በዚህ መሠረት ባለፈው ሳምንት በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ዓለማየው ተገኑ፣ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ተሾመ ቶጋ፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ፍፁም አረጋ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ያደረጋቸውን ማሻሻያዎችና በውጭና በአገር ውስጥ ገለልተኛ የሰብዓዊ ተቋማት በጋራ ምርመራ እንዲደረግ መወሰኑንም አስረድተዋል።
ይህ ቢሆንም የአሜሪካ አቋምን ማለዘብ አልተቻለም። አሜሪካ በዋናነት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ቀነ ገደብ እንዳስቀመጠች የሚያመለክቱ መረጃዎች ወጥተዋል።
በመሆኑም ጉዳዩ በፀጥታው ምክር ቤት የመታየቱ ጉዳይ አይቀሬ ሆኗል። የፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ሲመለከትም ማጠንጠኛ ይሆናሉ ተብለው ከላይ የተገለጹት፣ ከምግብ ዕርዳታ አቅርቦት ጋር ተያይዞ ተፈጽመዋል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ናቸው።
ይህንን መሠረት በማድረግም የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 2417 ተብሎ የሚታወቀውን የተመድ ‹‹ሪዞሊዩሽን›› በመጠቀም፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ተጠያቂነት እንዲወድቅበት ግፊት ሊደረግ እንደሚችል ከኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ምንጭች የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ይህ የተመድ የውሳኔ ሐሳብ እ.ኤ.አ. በ2018 በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን፣ ሰላማዊ ነዋሪዎች በግጭት ምክንያት ምግብና ሌሎች ሰብዓዊ ፍላጎቶቻቸው እንዳይስተጓጎሉ አገሮች ትኩረት እንዲሰጡ የሚያስገድድ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ግጭትን ምክንያት አድርጎ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ክልከላ በሚፈጽሙ አካላት ላይ ቅጣት ለመጣል የተለመ ነው።
ይህ የዕርዳታ አቅርቦት ክልከላ ሆን ተብሎ ጉዳት ለማድረስ የሚፈጸም ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ የተቀመጠ ድንጋጌ ነው። የፀጥታው ምክር ቤት በውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 2417 መሠረት ድምዳሜ የሚሰጥ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ላይ ሊወሰኑ የሚችሉት በትግራይ ከልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ሳያስተጓጎል ለማቅረብ የሚያግዙ ሰላም አስከባሪዎች እንዲሰማሩ የመወሰን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ፈጽመዋል በሚላቸው ግለሰቦች ወይም አካላት ላይ ማዕቀብ መጣል እንደሚሆን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ካላቸው አባል አገሮች አምባሳደሮች ጋር ባለፈው ዓርብ ውይይት ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኰንን፣ መንግሥት በትግራይ ያለውን ሁኔታ ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት አስረድተዋል።
ከዚሁ ጋር አያይዘውም በአሜሪካ መንግሥት የተያዘው አቋም ያለውን ሁኔታ ከግንዛቤ ያላስገባ ፖለቲካዊ ጥረት እንደሆነ ገልጸው፣ የፀጥታው ምክር ቤትን በመጠቀም በኢትዮጵያ የውጭ ጦር እንዲሰማራ ማድረግ ፈጽሞ እንደማይቻልና ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ተፈጽሞ እንደማያውቅ ገልጸዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ ምንጮች ሩሲያን ጨምሮ፣ ቻይና ህንድና ሌሎች አገሮች በፀጥታው ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ጎን ይቆማሉ ብለው የሚጠብቁ መሆኑን ገልጸው፣ አሜሪካ በዋናነት የያዘችው ዲፕሎማሲያዊ ጫና መፍጠር ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል።