>
5:28 pm - Monday October 10, 9194

ከዓቢይ ፆም እስከ እንጦጦ ንግሥ.... !!! (ፕ/ር ሥርግው ሀብለሥላሴ)

ከዓቢይ ፆም እስከ እንጦጦ ንግሥ…. !!!

ፕ/ር ሥርግው ሀብለሥላሴ

— እምዬ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ አጼ ዮሐንስ እና ደርቡሽ
ንጉሥ ምኒልክ የንጉሠ ነገሥትነትን ማዕረግ ላለመጠቀም ከአጼ ዮሐንስ ጋር በገባው ስምምነት መሠረት ከተወ ዐሥር ዓመታት አለፉ፡፡ ዐሥራ አንደኛው ሊጀምር ዳድቶታል፡፡ በዚህ ዐሠርት ዓመት ውለታውን እንዳከበረ ነው፡፡ ዮሐንስ ና ሲሉት ፈጥኖ ይሄዳል፡፡ ይኸን አድርግ ሲሊት በሚገባ ያደርጋል፡፡ ያን አምጣ ሲሉት የተፈለገውን ያቀርባል፡፡ በዚህ ዓይነት የግል የሙዚቃ መሣሪያም አልቀረውም፡፡ ለምሳሌ ‹‹እርጎ›› የተባለውን የአያቱን የሣህለ ሥላሴ በገና ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ እርሱ እጅ ደርሷል፡፡ አፄ ዮሐንስ ሸዋን ለመያዝ የመጣ ጊዜ ያንን በገና ያያል፡፡ እና በትውስት ይወስዳል፡፡ ግን የመመለሱ ነገር ዘገየ፡፡
የፈላስፋው የዲዎጋን ነገር ተመልሶ መጣ፡፡ እርሱ በክረምት ከአንድ ባለጸጋ ሰው ብርድ ልብስ ይዋሳል፡፡ ክረምቱ ቢያልፍም ግን ብርድ ልብሱን አልመለሰም፡፡ ስለዚህ ባለጸጋው ዴዎጋን ዘንድ ይሄድና ብርድ ልብሱን እንዲመልስለት ይጠይቀዋል፡፡ ዴዎጋንም ‹‹እንግዲህ በወጣሁ ቁጥር እየመጣህ አትጨቅጭቀኝ፣ ሰጥተኸኝም እንደሆነ አንጡራ ገንዘቤ ነው፣ አውሰኸኝም እንደሆነ ገና እፈልገዋለሁ፡፡›› ብሎ አለው ይባላል፡፡ እንደው ዝም ጭጭ ሲሆን ጊዜ ንጉሥ ምኒልክ እንዲህ ብሎ መልዕክት ወደ አፄ ዮሐንስ ላከ፡-
«ዓቢይ ፆም ገባ ሥንቅ እንኳ አልሸምቼ
እንዴት አደርጋለሁ ከርጎ ተለይቼ፡፡»
በጾም ወራት የፀሎት ሠላምታ መደርደር የተለመደ ነበርና ለዚያ ስለ አስፈለገው ነበር በገናውን የፈለገው፡፡ መልዕክቱ ሲደርሰው አፄ ዮሐንስ እንደ ዲዮጋን ድርቅ አላለም፡፡ በገናውን መልሷል፡፡
ጥቂት ቆይቶ ደርቡሽ ጎንደርን በማቃጠሉ አፄ ዮሐንስ ተቆጥቶ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ደርቡሽን ወግቶ እንዲያባርር ያዘዋል፡፡ ተክለ ሃይማኖት እንደ ታዘዘው ዘመተ፡፡ ነገር ግን በዚህ ዘመቻ በለስ አልቀናውም፡፡ እርሱና ጳጳሱ አቡነ ሉቃስ በጭንቅ ሲያመልጡ ከሠራዊቱ ስምንት ሺህ ያህል ተማረከ፡፡ ከእነዚህ መካከል ወንድ ልጁና ሁለት ሴት ልጆቹ ነበሩበት፡፡ አንዷ ሴት ልጁ ምንትዋብ ትባላለች፡፡ ተካርቱም ለአባቷ በግጥም እንዲህ ብላ መልዕክት ላከች፡-
«አባቴ ባለ ዘውድ ወንድሞቼ ራስ
ባሌ ፊታውራሪ ቀድሞ ሚተኩስ
እኔንም ወሰደኝ የደርቡሽ ንጉሥ፡፡
ምናልባት ምናልባት እንደኔ እማትቀሩ
ድመት በልታ ሞተች ብላችሁ ንገሩ፡፡»
የጎጃምም ሕዝብ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ልጆቻችንንና ባሎቻችንን አስፈጃቸው እያለ ያማው ነበረና እሱም በበኩሉ ለዚህ ወቀሳ እንዲህ ሲል በግጥም መለሰ፡-
«ባሌን ጥሎ መጣ – ልጄን ጥሎ መጣ – ይለኛል ባላገር
ለምንትዋብ አዳል ያልሆነውን አገር፡፡»
እንዲህ ዓይነት አሳዛኝ እልቂት ከተካሔደ በኋላ ንጉሥ ምኒልክ ወደ ጎንደር አልፎ ደርቡሽን እንዲወጋ ይታዘዛል፡፡ ምኒልክም እንደ ታዘዘው ሠራዊቱን ይዞ ወደ ጎንደር ያመራል፡፡ ደርቡሽ የምኒልክን መምጣት ሲሰማ ወደ ኋላ አፈገፈገ፡፡
ምኒልክ ደምቢያ ሲደርስ የእግዝእትነ ማርያም ፅላት በደርቡሽ ወረራ ምክንያት ተወስዳ ከአንድ ገጠር ቤተ ክርስትያን መኖሯን ሰማና ሰው ልኮ አስመጣት፡፡ ያቺ ጽላት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይፀልይባት የነበረችና በአፄ ሱስንዮስም ዘመነ መንግሥት (1597 – 1624 ዓም) እጨጌ አብርሃም ለደብረ ሊባኖስ ጉልት ለመለመን ወደ ደንቀዝ ሲሔድ ይዟት የሄደችና እዚያው አዘዞ ለደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ማረፊያ በአፄ ፋሲል ዘመን ስለተሰጠ እየተገለገሉባት ቆይታለች፡፡ በደርቡሽ ወረራ እንዳትጠፋ ከአዘዞ ወደ ደምቢያ ተወስዳ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለምኒልክ የተነገረለት ንግርት ነበር፡፡ በተክለ ጻዲቅ መኩሪያ መጽሐፍም ላይ ይገኛል፡፡ ቀደም ብለንም ገልጸነዋል፡፡ ያ ንግርት ምንድነው? ያቺን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጽላት ሲያገኝ እንደሚነግሥ አንድ መነኩሴ ነግሮት ነበረ፡፡ ያቺ ጽላት የምትፈለገው መሆኗን ካረጋገጠ በኋላ ነው ምኒልክ ‹‹ንግርቴ ደረሰ፣ መፈጸሚያው ተቃርቧል›› ብሎ ከደምቢያ መለስ አለ፡፡
አምባ ጫራ ላይ ሁሉም ነገሥታት ይሰፍሩበታል፡፡ ምኒልክም አምባ ጫራ ላይ ሰፍሮ ሳለ፣ እንዲህ የሚል ዘፈን ወጥቶ ሲዘፈንለት ቆየ፡-
«ሳብበት
ሰውም የለበት
አምባ ጫራ ላይ ጉብ በልበት፡፡»
ከዚያ ምኒልክ ወደ ጎጃም ተሻግሮ ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖር ጋር የወደፊት እቅድ አወጡ፡፡ ይኸውም ምንድነው? አፄ ዮሐንስ ደርቡሽን በአንዱ አቅጣጫ ያጠቃ እንደሆነ፣ ሌላው እንዲረዳ ነበረ፡፡ ምኒልክ ይህን አድርጎ ወደ ከተማው እንጦጦ ተመለሰና ለመጀመሪያ ጊዜ የዓመት ግብር ለአጼ ዮሐንስ ሳይልቅ ቀረ፡፡ ከንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር የመከረውን አፄ ዮሐንስ ሰምቷል፡፡ ግብርም እንዳልከፈለ ያውቃል፡፡ ግን ከምኒልክ ጋር የሚላላከው ሠላማዊ ነገር ብቻ ነበረ፡፡ ይህም ማለት አርዓያ ሥላሴ በ1880 ዓም ስለሞተ ሚስቱን ወይዘሮ ዘውዲቱን ከሥጦታ ጋር እንደሚልካት የሚጠቁም ነበር፡፡ እንዳለውም ከብዙ መንጋ ከብት ጋር ላካት ወደ ምኒልክ፡፡ የዚያን ጊዜ ከብት በሸዋ እያለቀ ነበርና ትልቅ ዋጋ ያለው ገጸ በረከት እንደሆነ ነበር የተቆጠረው፡፡
ከዚያ ዮሐንስ ጦሩን ይዞ ወደ ሸዋ ጉዞ ጀመረ፡፡ በመካከሉ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከአፄ ዮሐንስ ታርቆ ምኒልክ ብቻውን ቀርቷል፡፡ ምንም እንኳን ምኒልክ ንግርቱ መድረሱን ቢያውቅም በገሃድ ጦርነት ለመግጠም አልፈለገም፡፡ ስለዚህ አጎቱን ራስ ዳርጌን አንዲያስማማው ወድ አፄ ዮሐንስ ላከ፡፡ ግን የዳርጌ መልዕክት ሰሚ ጆሮን አላገኘም፡፡ በዚህ መሐል ምኒልክን ሸሽቶ ያፈገፈገው ደርቡሽ ተመልሶ እንደ ገና የጎንደርን አብያተ ክርስትያናት ስላቃጠለ፣ በዚህ አፄ ዮሐንስ ተቆጥሩ ፊቱን ድንገት ወደ መተማ አዞረ፡፡ ለምኒልክ ትልቅ እፎይታ ነበረ፡፡ ከዚያ ጦርነት አፄ ዮሐንስ በሕይወት አልተመለሰም፡፡ ቀደም ሲል የወሎው ሁሴን ጅብሪል ሀብተ ትንቢት የኘበረው ሰው እንዲህ ብሎ ነበረ፡-
«በመተማ በኩል የምትጨሰው ጭስ
እጅግም አትሆነው ላፄ ዮሐንስ
የዮሐንስ በቅሎ ብረኪ ብረኪ
መተማ ላይ ወርደሽ እንዳትማረኪ፡፡»
ይህን የሼህ ሁሴን ትንቢት ጉዳይ አፈወርቅ ገብረየሱስ በጻፉት መጽሐፍም ውስጥ በዝርዝር ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡፡ አፈወርቅ የጎጃም ሴቶችን እርግማንም አብሮ ጨምሮበታል፡፡ ለማንኛውም እንደተባለውም አፄ ዮሐንስ መተማ ላይ ተሰየፈ፡፡ በእንዲህ ዓይነት አሟሟት ሕይወቱ የተቀጨ ሦስተኛው ንጉሥ ሆነ፡፡ ከዚህ በፊት በዛጉዬ መንግሥት ዜና ጴጥሮስ፣ በዐሥራ ስድስተኛው ምእት ዓመት ደግሞ አፄ ገላውዴዎስ (1533 – 1551 ዓም) በተመሳሳይ ሞት ሕይወታቸው አልፏል፡፡
የአፄ ዮሐንስን ሞት ምኒልክ ቶሎ ይሰማል፡፡ በአሟሟቱ አዝኖ ሐዘን እንደተቀመጠም በአፈወርቅ መጽሐፍ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ወዲያው እንጦጦ ከተማው ላይ ንጉሠ ነገሥት መሆኑን ዐወጀ፡፡ ለሥርዓተ ንግሡ ዝግጅት ሲደረግ ሁለት ጳጳሳት ምኒልክን ለመቀባት ፉክክር ገጠሙ፡፡ አንደኛው አጼ ዮሐንስ ያስመጣቸው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ ሁለተኛው ግን በምኒልክ ዘንድ የበዛ ሞገስ ያላቸው አቡነ ማቴዎስ ነበሩ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ዮሐንስ ከግብጽ ካስመጣቸው አራት ጳጳሳት አንዱ ነበሩ፡፡ ጉዳዩ እንጦጦ ላይ ተፈታ፡፡ የምኒልክ ምርጫ ከሸዋ ሀገረ ስብከት የመጡትን አቡነ ማቴዎስ ነበረ፡፡ እዚህ ላይ ምኒልክ እስክንድርን ለመሆን ፈለገ – የጎርድዮኑን ቋጠሮ ፈታው እየተባለ ጉድ አሰኘ፡፡ ማቴዎስ እንዲቀቡት አድርጎ ሊቀ ጵጵስናውን ሲጠቀልሉ፣ አቡነ ጴጥሮስ በሰሜን ኢትዮጵያ በተራ ጳጳስነት ክህነት እየሰጡ እንዲቆዩ ሆነ፡፡ አፄ ምኒልክ ጉዳዩን ለእስክንድርያው ፓትሪያርክ በጽሑፍ አስታወቀ፡፡ ፓትርያርኩ አልተቃወመም፡፡
የምኒልክ የንግሥ ቀን ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓም እንዲሆን ተወስኖ በዚያ ቀን በእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስትያን ብዙ መኳንንትና ሕዝብ በተሰበሰበበት በአቡነ ማቴዎስ እጅ ተባርኮ ዘውድ ጫነ፡፡ ይኸውም ሦስተኛውና የመጨረሻው ንግሥ ነበር፡፡ ዘውድ ጭኖ ከአደባባይ ሲወጣ አዝማሪው እንዲህ የሚል ግጥም አሰማ፡-
«ቤተ ክርስትያን ገብቶ ጸሎቱ በልክ
ዳዊት ደግሞ ወጣ አፄ ምኒልክ፡፡»
አሁንም ያው አዝማሪ ደግሞ የምኒልክ የዐሥር ዓመቱ ትዕግሥትና ብልሃት ዋጋ እንዳለው ለማመልከት እንዲህ አለ፡-
«አንበሳው ግሥላው ተሰፍቶ በልክ
ቢተዋ አማረበት አፄ ምኒልክ፡፡»
ሌላው አዝማሪ ምኒልክ ባላጋራዎቹን አንድ በአንድ እያደረገ በመጨረሻ አጼውን ያለ ጦርነት በትዕግሥት ብቻ ማሸነፉን ለመግለጽ እንዲህ አለ፡-
«እንታገል ይላል ጉልበቱን ያመነ
መጣል እንዳንተ ነው እያመነመነ፡፡»
ምኒልክ ለበዓሉ ክብር በዚያን ቀን ለመኳንንት፣ ለካህናትና ለሕዝብ ታላቅ ግብር አገባ፡፡ ስለዚህ ግብር ከዘግጅቱ አንስቶ እንዴት እንደ ተፈጸመ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ በምኒልክ የዘመን ታሪክ በዝርዝር ገልጾልን እናገኛለን፡፡ ከዚህ በኋላ ለምኒልክ በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ዕውቅና ተሰጣቸው፡፡ ብዙ ሹመት ሰጡ፡፡ ምኒልክ በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫ ብዙ ደከሙ፡፡ ብዙ ሀገርም አቀኑ፡፡ ገና የአድዋ ድል ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል፡፡ የክፉ ቀን መከራም፡፡ በክፍለ ዘመኑ ማብቂያ ምኒልክ የተሟላችና አንድነቷን የጠበቀች – እንደ አንድ ቤተሰብ ሊቆጠር የሚችል ሀገርንና ህዝብን ይዘው ነው 20ኛው ክፍለ ዘመንን የተቀላቀሉት፡፡
ለዛሬ እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡
ለህዝበ ክርስትያን የተባረከ ጾመ አብይ እንዲሆን ተመኘሁ፡፡
የፈጣሪ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን!
መልካም ጊዜ፡፡
*     *     *
የበዛ ምስጋና ለዶ/ር ፕ/ር ሥርግው ሀብለሥላሴ በመንፈስ ይድረሳቸው፡፡ ለደራሲው ነፍስ የኢትዮጵያ አምላክ በገነተ አፀዱ የበዛ እረፍትን ይስጥልን፡፡ «ኢትዮጵያ ታበጽዕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር»፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
Filed in: Amharic