የደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ…. የኛስ ነገር አፓርታይድን አያስከነዳም ትላላችሁ…???
አሰፋ ሀይሉ
* …እኛ እኮ እንዲህ በስቴዲየም ውስጥ በገመድና በብረት ምሰሶ ተሰምሮ ስላላየነው በአፓርታይድ ሥርዓት ውስጥ እየተገዛን ያለን መስሎ አይሰማንም እንጂ፣ እየኖርን ያለነው እኮ በብዙ መልኩ የደቡብ አፍሪካውን የአፓርታይድ ሥርዓት በሚያስከነዳ የለየለት መንግሥታዊ የዘር ክፍፍልና ሽንሸና አገዛዝ ውስጥ ነው…!
ይሄን ፎቶ ልብ ብለህ ተመልከተው፡፡ የደቡብ አፍሪካ አነስተኛ ስታዲየም ነው፡፡ የተመልካቾች መቀመጫ (ካታንጋ)፡፡ ልብ ብለህ እይ የተመልካቹን አቀማመጥ፡፡ ድንገት የሆነ አይደለም፡፡ ነጮቹ በአንድ በኩል፣ ጥቁሮቹ ደግሞ በሌላ በኩል ነው የተቀመጡት፡፡ በነጮቹና በጥቁሮቹ መቀመጫ መሐል ለመለያ የቆመላቸው ትልቅ የብረት ምሰሶና የገመድ አጥር አለ፡፡ ጥቁሮች የተሰመረላቸውን አጥር ዘለው ወደ ነጮቹ መቀመጫ ማለፍ አይችሉም፡፡ ነጮቹም እንደዚያው፡፡ ይህን ፎቶ ግራፍ ለዓለም ህዝብ መማሪያነት ሰንዶ ያስቀመጠው የተባበሩት መንግሥታት ቤተ መጻሕፍት ነው፡፡ ‹‹Conflict and Cooperation – Documents on Modern Global History›› በሚል መጽሐፍ ውስጥ ነው ያገኘሁት፡፡
በዓለም ሕዝብ የተወገዘው፣ እና ከአፍሪካ ምድር ተጠራርጎ እንዲጠፋ የተደረገው የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት እንዲህ ዓይነት ነበር፡፡ በሁሉም ስቴዲየሞች፡፡ በሁሉም መሥሪያ ቤቶች፡፡ በሁሉም ከተሞች፡፡ በሁሉም ገጠሮች፡፡ በሁሉም ሆቴሎችና ትምህርት ቤቶች፡፡ በህዝብ አገልግሎት መስጫዎች በሙሉ፡፡ የጥቁሮችና የነጮች መገኛ የተለየ ነው፡፡ ነጭ ወደ ጥቁር፣ ጥቁር ወደ ነጭ አይገባም፡፡ ያን ተላልፎ መገኘት ወንጀል ነው፡፡ ያስቀጣል፡፡
ጊዜ በሄደ ቁጥር የሰው ልጅ ከጥፋቱ መለስ ብሎ ለስለስ ወዳለው መንገድ ሲሄድ፣ ደቡብ አፍሪካውያኑ ግን የዘረኝነት አባዜው ይበልጥ እየጠናባቸው ነበር የሚሄዱት፡፡ በ1927 ላይ ነጭና ጥቁር ሴክስ ከፈጸሙ የሚቀጣ የወንጀል ህግ ደነገጉ፡፡ ቀጠሉና ደሞ በ1949 ላይ ነጭና ጥቁር ከተጋቡ የሚቀጣ የወንጀል ህግ አወጡ፡፡ በመጨረሻ በ1950 የህግ ማሻሻያ አድርገው ደቡብ አፍሪካውያን ነጭና ጥቁር ከጋብቻ ውጪ የድብቅ ፍቅር ሲያጣጥሙ ሲገኙ የሚቀጣ መሪር ህግ አወጡ፡፡
ይሄን ስል ትሬቨር ኖአህ ትዝ አለኝ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአሜሪካ ታዋቂ የቴሌቪዥን ቻናል ፖለቲካዊ ሽሙጦችንና ማህበራዊ ቀልዶችን በማቅረብ የሚታወቀው ሥኬታማ ደቡብ-አፍሪካዊ ኮሜዲያን – ትሬቨር ኖአህ – በደቡብ አፍሪካ ነጭና ጥቁር የግብረሥጋ ግንኙነት ማድረግም ሆነ መጋባት በተከለከለበት ዘመን – ከነጭና ከጥቁር የተወለደ ልጅ ነበር፡፡ እና የሕይወት ታሪኩን ያሳተመበትን መጽሐፍ ‹‹BORN A CRIME›› ብሎ ሰይሞታል፡፡ ‹‹ወንጀል ሆኖ የተወለደ›› ለማለት፡፡ እና በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ የዘር ልዩነት ሥርዓት በፍቅርም ከአንዱ ዘር ወደሌላው መሻገር ክልክል ነበር፡፡
ይህን ደቡብ አፍሪካውያንን የከፋፈለውን መንግሥታዊ የዘር ልዩነት ፖሊሲ ተቃውመው ነበር አነ ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ የተነሱት፡፡ ይህን የዘር ልዩነትና ሽንሸና ተቃውመው ነበር እነ ኔልሰን ማንዴላ የተነሱት፡፡ ይህን የዘር ሽንሸና ፖሊሲ ተቃውሞ ነበር የዓለም ህዝብ በደቡብ አፍሪካ መንግሥት ላይ ብዙ ተጽዕኖዎችን ያሳደረው፡፡ ዴዝሞንድ ቱቱ የደቡብ አፍሪካ ተራ ቄስ እያሉ ጀምሮ ይህን ዜጎችን ምርጫ የሚያሳጣውንና ‹‹እኔ በመደብኩልህ የዘር ከረጢት ብቻ ግባና ኑር›› የሚል አምባገነናዊ የዘረኝነት ሥርዓት ሲኮንኑት ነው የኖሩት፡፡ በኋላ ራሷን የቻለ አስተዳደር የነበራት የሌሶቶ መንፈሳዊ መሪ ሆኑ፡፡ እዚያም ፈጣሪ አንድ አድርጎ የሠራውን የሰው ልጅ በዘርና በቋንቋ፣ በመልክና በፀጉር የለየውን የአፓርታይድ የዘር ልዩነት ፖሊሲ አጥብቀው ይቃወሙ ነበር ዴዝሞንድ ቱቱ፡፡
በመጨረሻ የኬፕታውን አርክቢሾፕ ሆነው ተመረጡ፡፡ እና ሊቀጳጳስ ሆኑ፡፡ በ1984 ነው ይሄ የሆነው፡፡ በ1986 በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የዓለማቀፉ የኖቤል ሽልማት ድርጅት ዴዝሞንድ ቱቱ በሀገራቸው የሰፈነውን መንግሥታዊ የዜጎች የዘር ሽንሸና ፖሊሲ በአደባባይ በመፋለም ላሳዩት ታላቅ አርበኝነት የኖቤል ሽልማት ሸለማቸው፡፡ በድርጊቱ የተንጨረጨረው የደቡብ አፍሪካው የአፓርታይድ መንግሥት ግን አፍታም ሳይቆይ የዴዝሞንድ ቱቱን የኖቤል ሽልማት እንደማይቀበለው ለዓለም አወጀ፡፡ እነ ዴዝሞንድ ቱቱ ሁለነገራቸውን የሰጡለት ዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት ሲያበቃ፣ እና ኔልሰን ማንዴላና ፕሬዚደንት ዴ ክለርክ የጋራ ኖቤል ሊሸለሙ ዝግጅት ላይ እያሉ ነው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለዴዝሞንድ ቱቱ የኖቤል ሽልማት ዕውቅና የሰጠው፡፡ እንዲህ ይሉታል ዴዝሞንድ ቱቱ በ1996 እ.ኤ.አ. ላይ (በዚህ ወቅት በሀገራቸው የተቋቋመውን የሠላምና እርቅ ኮሚሽን ለመምራት ከመንፈሳዊ የጵጵስና አገልግሎታቸው ራሳቸውን ያገለሉበት ወቅት ነበር፣ እና ለዓለማቀፉ ሕብረተሰብ በላኩት መልዕክት ነበር እንዲህ ያሉት)፡-
‹‹እስከማውቀው ድረስ ያሻውን አድራጊ ፈጣሪ መሆን የሚችል አንድ ብቸኛ አካል – ሁሉን የፈጠረው፣ ሁሉን ቻዩ፣ አንድ ፈጣሪ አምላክ ብቻ ነው፡፡ ያ ዓለሙን የፈጠረ አምላክ ግን – ሰውን በግድ ገነትን መርጠህ ኑር ብሎ ላለማስገደድ ሲል – የፈጠራቸውና ከልቡ የሚያፈቅራቸው የሰው ልጆች ገሃነምን መርጠው ወደ እሣት ሲገቡ – ከልቡ እያዘነ ዝም ብሎ መመልከትን ነው የመረጠው፡፡ ይሄ የሚያሳየን ፈጣሪ አምላካችን ምን ያህል ለሰዎች ምርጫ፣ ለነፃነት፣ ሰዎች ወደፈለጉበትና ወዳሰኛቸው፣ ካሻቸው ጋር እንዲኖሩ ፈቅዶ ነጻነትን እንደሚሰጣቸው ነው! አሁን ግን የገጠመን ከእግዜሩም እንበልጣለን፣ ለዘለዓለሙ እኛ በሰፈርንልህ የዘር ከረጢት ገብተህ ኑር፣ ውልፍት እንዳትል፣ እኛ ያሰመርንልህን የዘር ሽንሸና አልቀበልም ካልክ፣ ዋጋህን እንሰጥሃለን የሚሉ፣ የፈጣሪን ስም እየጠሩ ግን ከፈጣሪ መንገድ በተቃራኒው የሚጓዙ፣ እና እኛንም በዚያ መንገድ እንድንጓዝ የሚያስገድዱን ሰዎች ናቸው…፡፡››
የሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱን ቁርጠኛ የፀረ ዘረኝነት ትግል ሲያዩ – የሀገራችንን ሕዝብ በዘርና በቋንቋ ሸንሽኖ አንተ ከዚህ አትለፍ፣ ያኛው ከዚያ አይለፍ እያለ – ዓለም ተጠይፎት አንቅሮ በጣለው የአፓርታይድ ፖሊሲ የሀገራችንን ሕዝብ እያስተዳደረ ያለውን የኢህአዴግ ወ ብልጽግና መንግሥት እየባረኩና እያገለገሉ እየኖሩ ያሉት የእኛዎቹ የሐይማኖት መሪዎች ግን ምን ይሰማቸው ይሆን? የተወሰነ ፀፀት ያድርባቸው ይሆን ግን?
አንዳንድ ገና ስማቸው አደባባይ ያልዋለ የፈጣሪን መንገድ የመረጡ ብርቱ የሐይማኖት አባቶች እንደሚኖሩ ሳይታለም የተፈታ ቢሆንም፣ የብዙዎቹ ለሥርዓቱ ያላቸው አድርባይነትም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለነፍሳቸው ሳይሆን ለሥጋቸው፣ ለሁሉን ቻዩ ፈጣሪ አምላክ ሳይሆን ለጉልበተኛ ባለጊዜ እያደገደጉ መኖርን ብቸኛው ግባቸው ያደረጉ መንፈሳውያን – እንዴት የአዕምሮ ሠላም አግኝተው መኖር እንደሚችሉ ይደንቀኛል፡፡ ከእነ ዴዝሞንድ ቱቱ ጋር ሳነጻጽራቸው፡፡ አትፍረድ ይፈረድብሃል ይላል መጽሐፉ፡፡ ብዙዎች የሀገራችን የሐይማኖት ሰዎች – በዚህ ወይም በዚያ በኩል – ጭራሽ ለዘር ሽንሸናና ክፍፍሉ ዋነኛ አውታር ሆነው ከሥርዓቱ ብሰው ሲያገለግሉ እያየን – ታሪክና ዘወትር ስሙን የሚጠሩት ፈጣሪ ይፍረዳቸው ብሎ ከመተው ውጭ ምን ይደረጋል፡፡
እኛ እኮ እንዲህ በስቴዲየም ውስጥ በገመድና በብረት ምሰሶ ተሰምሮ ስላላየነው በአፓርታይድ ሥርዓት ውስጥ እየተገዛን ያለን መስሎ አይሰማንም እንጂ፣ እየኖርን ያለነው እኮ በብዙ መልኩ የደቡብ አፍሪካውን የአፓርታይድ ሥርዓት በሚያስከነዳ የለየለት መንግሥታዊ የዘር ክፍፍልና ሽንሸና አገዛዝ ውስጥ ነው፡፡ አማራና ኦሮሞ፣ ከንባታና ሀዲያ፣ ሲዳማና ወላይታ፣ ትግሬና ጉራጌ፣ አደሬና አርጎባ፣ አፋርና ሱማሌ፣ ደንጣ ድባሞ ክችንችላና፣ ፀማይ በና ባኮ እያለ ዜጎችን በዘር እየሸነሸነ፣ ይሄ አካባቢ የዚህ ጎሳ ብቻ ነው፣ ያኛው ክልል የዚያኛው ብሔር ነው፣ እያለ ሀገርንና ዜጎችን በዘርና በቋንቋ ለያይቶ፣ ሸንሽኖ፣ ከፋፍሎ አልበቃ ባለው የአፓርታይድ ሥርዓት ሥር እየተዳደርን መሆኑን ያላወቀም ብዙ ሚሊዮን ሰው አለ በአሁኑ ሰዓት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ ጉድ ነው የምለው፡፡
እንኳን ጨዋው ሰው ይቅርና፣ ራሳቸውን በአዋቂነት ሥፍራ ያጩ ብዙዎች ራሳቸው – ላለፉት 30 ዓመታት እስካሁኑም ሰዓት ድረስ – የምንኖርበት የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሥርዓት – የለየለት አፓርታይዳዊ ሥርዓት መሆኑን ማስተዋል የተሳናቸው ሆነው መገኘታቸው እጅግ ይገርመኛል ሁልጊዜ፡፡ አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማምና ምን ይደረጋል? ለእነዚህ መሰሎቹ ኢትዮጵያውያን ጥቂት የዴዝሞንድ ቱቱን ጽሑፎች እንዲያነቡ፣ ጥቂት የዘር ልዩነት ነግሶባቸው የነበሩ ሀገሮች፣ እና ወደ ሀገራዊ የዜግነት ሥርዓት እንዴት እንደተሻገሩ ተመልክተው ለሀገራቸው መጪ ትውልድ አንድ የተሻለ አሻራ አኑረው እንዲያልፉ ምኞቴ ነው፡፡
አሁን በቅርቡ ባለጊዜነት በተሰማቸውና የመንግሥት ድጋፍ በተቸራቸው የጉጂ ኦሮሞዎች እጅ ከፍተኛ ስቃይና በሚሊዮን እስከሚቆጠር መፈናቀል የደረሰባቸው ጌዲዮዎች (ድሮ ‹‹ደራሳ›› ይባሉ የነበሩት)፣ በዚሁ የወያኔ-ኢህአዴግ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ – አንድ ወቅት ‹‹ጌዲዮ ያልሆነ ከክልላችን ይውጣ›› ብለው ብዙ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ ብዙ ሰው ፈጅተዋል፡፡ የአፓርታይዱ መንግሥታችንም ነገሩን ኋላ በዓይኑ የሥልጣን ጉዳይ ሲመጣበት እስኪገባበት ድረስ – ከጀርባ እያበረታታ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ለስቃይ አሳልፎ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ያን እውነት እስከ ቅርብ ጊዜ በአካባቢው የኖረ ማንም ሰው ሊመሰክረው ይችላል፡፡
እና ያኔ ‹‹ክልላችን የእኛ ብቻ›› ብለው በተነሱበት ወቅት፣ አንዱ የጌዴኦ ባለሥልጣን ‹‹ካሁን በኋላ አፍንጫ ሰልካካና ጸጉረ ዞማ የጌዲዮን ህዝብ አይገዛም!›› ያላትን ንግግሩን ይዤ ቀርቼያለሁ፡፡ ደቡብ አፍሪካውያኑ አፓርታይዳውያን – የዘር ማንነትን ለመለየት – የአፍንጫ ቁመትና የግንባር ወርድ፣ የፀጉር ዓይነትና የዓይን ቀለም፣ የቆዳ ቀለምና የሰውነት አቋም ጭምር ዘርዝረው መመሪያ አድርገው የተገበሩ መሆናቸውን ለሚያውቅ፣ የናዚዎችንና የፋሺስቶችን አካላዊ የዘር መለያ መስፈርቶችን የሚያውቅ – በእኛ የደረሰው ምን እንደሆነ አይስተውም፡፡ ሌላውን ለታሪክና ለፈጣሪ መተው ነው፡፡ ከሚሊዮን የሚበልጡ የጌዲዮ ተወላጅ ዜጎች ሲፈናቀሉ የደረሰላቸው በሥርዓቱ ተሰብከው አፍንጫ ሰልካካና ፀጉረ ዞማ እያሉ ደሙን ሲያፈሱት የኖሩት ወገናቸው ነው፡፡ ታሪክ ገና ብዙ ያሳየናል፡፡ ገና ብዙ የምንማረው አለ፡፡
በአንድ ወቅት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ዓመት ስማር ቆይቼ ክረምት ላይ ወደ ሐረር ከተማ ተመለስኩ፡፡ ብዙዎች የካምፓስ ጓደኞቼ በሐረር ጁንየር ት/ቤትና በአርበኞች (ቀኃሥ) ትምህርት ቤት ተሰባስበው – ለቀጣዩ ዓመት 11ኛና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የቱቶሪያል ትምህርት ድጋፍ ይሰጡ ነበር፡፡ በወቅቱ ትንሽ ማረፍ ስለፈለግኩ የቱቶሪያል ክላስ መስጠት አልፈለግኩም፡፡ ዘግይቼም ስለመጣሁ በመሐል መጀመር አልፈለግኩም፡፡ እና ቤቴ በተቀመጥኩበት አንድ ማስታወቂያ ሰማሁ፡፡ ወላጅ እናቴ ለብዙ ዓመታት በመምህርነት ባገለገለችበት ‹‹እስላም ት/ቤት››, ወይም ‹‹መድረሳ ጌይ›› በሚባለው የአደሬዎቹ ጥንታዊ ግንብ (ጀጎል) ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ውስጥ – የቱቶሪያል ክላስ ሊጀመር ስለሆነ ፈቃደኛ የሆነ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ይፈለጋል፡፡ የሚል፡፡ መቀመጥ ሰልችቶኛል፡፡ ትንሽ ትውልድን ባግዝም ምንም አይለኝም፡፡ ብዬ ሄጄ ለማስተማር ተመዘገብኩ፡፡
ከመምህራኑ አንዳንዶቹ እናቴ ያስተማረቻቸው፣ ወይም አባቴ በሀይስኩል ወይ በኤለመንተሪ ያስተማራቸው ነበሩ፡፡ እና ስቀላቀላቸው ደስ አላቸው፡፡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተምርልን አሉኝ፡፡ በደስታ እሺ ብዬ – ሁለቱን ቀን ለሰዋሰው ት/ት፣ ሶስቱን ቀን ደግሞ ለንግግር ሰጥቼ ከልጆቹ ጋር ተዋደን አንድ ሳምንት ዘለቅን፡፡ ቅዳሜና እሁድ አለፈ፡፡ በቀጣዩ ሰኞ ዕለት እያስተማርኩ ክፍሌ ተንኳኳ፡፡ አቤት ብዬ ብሄድ አዲስ የእንግሊዝኛ አስተማሪ ተመድቤ ነው እኮ – አንተ ምን እያስተማርክ ነው? ብሎ አዲሱ ልጅ ግራ ተጋብቶ ጠየቀኝ፡፡ እኔም እንግሊዝኛ እያስተማርኳቸው ነው አልኩት፡፡ ቆይ አጣርቼ ልምጣ ብሎ ሄዶ ከአስተባባሪው ልጅ ጋር ተመለሰ፡፡ እና አስተባባሪው አደሬ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በእፍረት ዓይኔን ማየት ተስኖት ወደ መሬት እያየ፣ ፀጉሩን በጣቶቹ እያፍተለተለ እንዲህ አለኝ፡-
‹‹አሴ በጣም ይቅርታ፣ እዚህ ማስተማር የሚችሉት ሳምቲ (የአደሬዎች የልማት ማህበር) የላካቸው ብቻ ናቸው ተባለና፣ .. አደሪኛ የሚችል ብቻ ያስተምር ስለተባለ..፣ እና በቃ አንተ እንድታቆም አሰብን… ፣ ቀደም ብለን መንገር ነበረብን፣.. ጥፋቱ የኛ ነው እኛም አላወቅንም ነበር… ሳምቲ የነገረን አሁን ነው…!..
እያለ ቀጠለ ልጁ የማስተባበያ መዓት፡፡ በሰዓቱ ምንም አላልኩም፡፡ ምን እንደምልም አላወቅኩም፡፡ የአራት ኪሎው ዩኒቨርሲቲ መምህር አጎቴ ለራሴ የገዛልኝንና በዩኒቨርሲቲ በጣም የጠቀመኝን፣ አንድ የእንግሊዝኛ ሪፈረንስ መጽሐፍ ፊት ለፊት ባለው ዴስክ ጠረጴዛ ላይ ዘርግቼ፣ ከእሱ ላይ እያስተማርኳቸው ነበር፡፡ ቀጥታ ሄጄ መጽሐፌን አጥፌ በረጋ አንደበት ያ የመጨረሻዬ ቀን እንደሆነና አዲስ ከእኔ የተሻለ፣ እንግሊዝኛን በዩኒቨርሲቲ ያጠና መምህር እንደመጣላቸው፣ እና መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማቸው ተመኝቼላቸው – ልጆቹ እንባ አቅርረው፣ እኔም ልቤ እንባ አቅርሮ ከጀጎሉ ትምህርት ቤት ወጥቼ ወደ ቤቴ ሄጄ እረፍቴን ማጣጣም ጀመርኩ፡፡ ይህ በሆነ በሳምንቱ በምኖርበት ግቢ በር አካባቢ የሰዎች ጫጫታ ሰማሁ፡፡ የብዙ ሰው ንግግር፡፡ ጫን ተደርጎ ተንኳኳ፡፡
ሄጄ ብከፍት የመድረሳ ትምህርት ቤት የዩኒቨርሲቲ በጎፈቃደኛ መምህራኑ ወዳጆቼ ተንጋግተው መጥተው በሩ ላይ ቆመዋል፡፡ ግቡ ከማለቴ በፊት፡- ምንድነው? ምን ተፈጠረ? ብዬ ጠየቅኩ፡፡ ይቅርታ ልንጠይቅህ ነው የመጣነው፡፡ አንተ አደሪኛ አትችልም ተብለህ ከትምህርት ቤቱ ስትሄድ ሁላችንም በጣም ስለተሰማን፣ ተሰብስበን ሳምቲ ሄደን አሳመንናቸው፣ እና ቀደም ብሎ የተመዘገብንበት መዝገብ ላይ ስምህ ስላልነበረ ነው እንጂ እናንተ ተመዝግቧል ካላችሁ ማስተማር ይችላል ስለተባልን ቤትህን አፈላልገን መጣን፣ እና በጣም ይቅርታ አድርግልን፣ ተማሪዎቹም እሱ ካላስተማረን አንማርም ብለዋል፣ ወዘተ ወዘተ ብዙ ማግባባቶች፣ ይቅርታዎችና ልመናዎች፡፡ መጀመሪያ እምቢ አልኩ፡፡ ግን ይህን ሁሉ ትህትናና የልብ መመለስ በምን አንጀቴ እችለዋለሁ? ተስማምቼ ልጆቹን ማስተማሬን ቀጠልኩ፡፡
አንድ የምናገረው ነገር፣ ያ ት/ቤት ጀጎል ውስጥ ያለ ት/ቤት ስለሆነ፣ በዘር ከተቆጠረ፣ ብዙዎቹ ተማሪዎች አደሬዎች ነበሩ፡፡ እናቴ ያስተማረችበትና እኔም አልፎ አልፎ በልጅነቴ በዝግ ወቅት ብቅ እያልኩ የተማርኩበት ት/ቤት ነበር፡፡ ስለ ዘር ግድ አልነበረኝም፡፡ ህዝባችንን በዘር ሸንሽኖ በህገመንግሥት አስቀምጦ ሀገሪቱን እያስተዳደረ ያለ መንግሥት እያለ ያን መንግሥት እቃወመዋለሁ እንጂ አብረውኝ ከሚኖሩ ወገኖቼ ጋር ለምን እጠላላለሁ? እስከማውቀውና እስከማምንበት ድረስ፣ ት/ቤት በዘር አይሸነሸንም፡፡ ዕውቀት ዘርን ተመርጦ አይሰጥም፡፡ ዕውቀትን ለማስተላለፍ ዘር አያስፈልግም፡፡ ለዝንተ ዓለም የማምንበትም፣ እነዚያ የዘመኔ ወጣቶች በተግባር ያሳዩኝም ይህንኑ የሰው ልጆች ወርቃማ መርህ ነው፡፡
በዚያች ክረምት ላስተምር በመነሳቴ፣ ብዙ ነገርን ተማርኩ፡፡ የሚገርም የዘመናዊነትን መንፈስ ተላብሰው፣ በሚገርም የሰውልጅ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ተመርተው፣ ያንን የክልሉን ዘረኛ አስተሳሰብ በጣጥሰው ትልቅ ሰውነታቸውን፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን፣ እና ወንድማማችነታችንን – በግቢዬ በር ላይ በትህትና ቆመው የመሰከሩልኝን እነዚያን (መጥቀስ ካስፈለገ የአደሬ ተወላጆች የሆኑ) የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና በጎ ፈቃደኛ መምህራን እስከዛሬም ሆነ – እስከ ምንጊዜም ድረስ – ፈጽሞ አልረሳቸውም፡፡
እነዚያ ልጆች – ተማሪዎቹም መምህራኑም – ዘረኝነትን እኛ ከተጸየፍነው፣ የዘር ልዩነትንና ሽንሸናን በመካከላችን የሚያነግሰውን መንግሥታዊ ሥርዓት እኛ በቃህ ካልነው፣ ተመልሰን ዘመናዊው ዓለም ወደሚመላለስበት ወደ ታላቁ የዕድገትና የዕውቀት ከፍታ ጎዳና እንደምንደርስና እንደምንመላለስ – በትንሿ ያሳዩኝ አስደናቂና ልባም ልጆች ናቸው፡፡ በሀገራችን ለነገሠው አፓርታይዳዊ የዘር ልዩነትን የሚያራምድ ሥርዓት እጅ ሰጥቼ ተስፋ እንዳልቆርጥ ያደረጉኝ፣ ሥርዓቱ በቅን ልቦች ብርቱ ጥረት መቀየር እንደሚችል፣ ትልቅ ማስረጃ የሰጡኝ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነዚያ የሀገሬ ልጆች ምንግዜም ከአዕምሮዬ አይጠፉም! ደግሜ ደጋግሜ አመሰግናቸዋለሁ፡፡
አንድ ቀን – ልክ እንደነዚያ የሐረር ተማሪዎችና መምህራን – ይሄን በሀገራችን የነገሠውንና እርስ በእርስ አለያይቶ እያባላን ያለውን፣ እገሌና እገሌ ብሎ በመካከላችን የዘር መስመር አስምሮ እያናከሰን ያለውን የዘረኝነት ሥርዓት – ወጊድ ከላያችን ብሎ በጋራ ሆ ብሎ የሚነሳ አንድ ነቄ ትውልድ፣ አንድ ዘመኑን የሚታደግ፣ አንድ ፍቅርን በኢትዮጵያዊት ምድራችን ሊዘራ የሚነሳ – አንድ ጀግና ትውልድ እንደሚፈጠር – አንዳችም ጥርጥር የለኝም! ፈጣሪ ያን ለማየት እንዲያበቃኝ፣ እንዲያበቃን በጽኑ እመኛለሁ!
ፈጣሪ አምላክ ከሁላችን ጋር ይሁን!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በፍቅር ትኑር!