>
5:21 pm - Thursday July 21, 0355

ግብፅና ሱዳን ህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ከፈጠሩት ጥምረት ጀርባ ያለ ደባ (ዮሐንስ አንበርብር)

ግብፅና ሱዳን ህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ከፈጠሩት ጥምረት ጀርባ ያለ ደባ

ዮሐንስ አንበርብር

ባለፈው ሳምንት ወደ ሱዳን የተጓዙት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በካርቱም በነበራቸው ቆይታ በዋናነት ከሱዳን የሽግግር መንግሥት ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር አዛዥ ሌተና ጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር በሁለቱ አገሮች የጋራ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ላይ በመምከር፣ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ስለማድረጋቸው የሱዳን መንግሥት የዜና አውታሮች ዘግበዋል።
ባደረጉት ስምምነትም ለግብፅና ለሱዳን ወቅታዊ የፖለቲካ አንድነት ምክንያት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የሱዳን ፖለቲካዊ ሽግግር ይገኝበታል።
የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር በሕዝባዊ አመፅ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የተፈጠረውን የሽግግር መንግሥት እየመሩ የሚገኙት የሱዳን ጦር ከፍተኛ አመራሮች አብዱልፈታህ አል ቡርሃንና ምክትላቸው የሱዳን ጦር ልዩ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ሌተና ጄነራል መሐመድ ሃማዲት ዳጋሎ፣ ከዚህ ቀድም ያልነበረ ጥብቅ ቁርኝት ከግብፅና ከሌሎች የባህረ ሰላጤው ዓረብ አገሮች ጋር መሥርተዋል።
ሁለቱ የሱዳን ጦር አመራሮችና የወቅቱ የሽግግር መንግሥት ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቃነመናብርት ቢሆኑም፣ የውጭ ግንኙነትና የዕለት ተዕለት መንግሥታዊ ተግባራት በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ለሚመራው የአገሪቱ ሥራ አስፈጻሚ መንግሥት የተተዉ ናቸው።
ነገር ግን የሽግግር መንግሥቱ ከተመሠረተ ወዲህ ዋነኛ የሚባሉት የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ሥራዎች እየተከናወኑ የሚገኙት በሁለቱ የጦር አመራሮች ሲሆን፣ አንዳንድ መሠረታዊ የሚባሉ የውጭ ስምምነቶች (ከእስራኤል ጋር ዕርቅ ማውረድን ጨምሮ) የተፈጸሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳያውቁ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከግብፅ መንግሥት ጋር የተፈጠረው አዲሱ ወዳጅነትም በእነዚሁ የጦር አመራሮች የተመሠረተ ሲሆን፣ የሱዳን የውጭ ግንኙነት በእነዚህ አመራሮች መዘወር ከጀመረ አንስቶም ሱዳን በህዳሴ ግድቡ ላይ የነበራት ለዘብተኛ አቋምና ከግድቡ ከፍተኛ ጥቅም ተቋዳሽ እንደምትሆን በይፋ ስትገልጽ የነበረው አቋም ተቀይሯል።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን የጠበቀና በዕውቅ የውጭ ኩባንያ የሚከናወን በመሆኑ የመደርመስ አደጋ ይኖረዋል የሚል ሥጋት እንደሌላቸው፣ የግድቡ ግንባታ ከግብፅ አስዋን ግድብ በሚበልጥ የግንባታ ጥራት የሚከናወን እንደሆነ በይፋ ለመገናኛ ብዙኃን ሲያስረዱ የነበሩ ባለሥልጣናቷ ዛሬ የአቋም ለውጥ አድርገዋል።
በምትኩም የህዳሴ ግድቡ የደኅንነት ደረጃ እንደሚያሠጋቸውና የውኃ ሙሌቱን በተመለከተ ሦስቱም አገሮች የሚስማሙበት አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ ከተከናወነ፣ የ20 ሚሊዮን ሕዝብ ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ማስተጋባት ጀምረዋል።
በቅርቡ ወደ ሱዳን ያመሩት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ሰፊ ጊዜ ያሳለፉት ከሉዓላዊ ምክር ቤቱ ዋና ሊቀመንበር ሌተና ጀነራል አል ቡርሃንና ከምክትላቸው ሌተና ጄነራል ዳጋሎ ጋር ነበር።
ከሁለቱ የሱዳን ጦር መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ትልቅ ትኩረት የነበረው ጉዳይ በእንጥልጥል ላይ የሚገኙት የታላቁ የህዳሴ ግድብ ልዩነቶች ለመፍታት ያስችላል በተባለ አዲስ የድርደር አማራጭ ላይ የጋራ አቋም መያዝ እንደነበር፣ ፕሬዚዳንት አልሲሲና ሌተና ጄነራል አል ቡርሃን በሰጡት የጋራ መግለጫ ገልጸዋል።
አዲሱ የድርድር አማራጭ በሱዳን መንግሥት በኩል የቀረበና የግብፅን ሙሉ ድጋፍ ያገኘው፣ አራት ዓለም አቀፍ አባላት የሚኖሩትና አራትዮሽ አደራዳሪዎችን በመሰየም ውዝግቡን ለመፍታት አዲስ ውይይት መጀመር እንደሆነም ተገልጿል።
አራትዮሽ አደራዳሪዎች እንዲሆኑ በግብፅና ሱዳን ፍላጎት የተሰየሙትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአሜሪካ መንግሥትና የአፍሪካ ኅብረት ናቸው።
ሌላው በሁለቱ አገሮች ውይይት ተደርጎ ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ በህዳሴ ግድቡ ሙሌትና አስተዳደር ላይ ስምምነት ሳይደረስ፣ ኢትዮጵያ የሁለተኛ ዓመት የውኃ ሙሌት በዘንድሮው የክረምት ወቅት እንዳታካሂድ ማድረግ ነው። የተቀረው ጉዳይ የሱዳን መንግሥት የፖለቲካ ሽግግርን ማገዝ ሲሆን፣ በዚህ ውስጥ የሱዳንን ግዛትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ትብብር ማድረግ በሚል ርዕስ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ እንዲካተት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን በተመለከተ የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ያለቸውን ልዩነት ለመፍታት፣ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ከተጀመረው መንገድ ውጪ እንደማይሄድ በይፋ አስታውቋል።
ሰኞ የካቲት 29 ቀን ወደ ኬንያ ያመሩት የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ አፍሪካን በመወከል በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት የወቅቱ አባል ከሆነችው ኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተገናኝተው ይህንኑ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም በግልጽ ማስረዳታቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በሳምንቱ መጀመርያ ላይ ወደ ኬንያ ከማቅናታቸው አስቀድሞ፣ የህዳሴ ግድቡን አጀንዳ ከተረከቡት የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቺሴኬዲ የተላከ የልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ ተቀብለው አነጋግረው ነበር።
ልዩ መልዕክተኛው ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጋር የተገናኙት የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የህዳሴ ግድቡ ድርድር የሚቀጥልበት ሁኔታን አስመልክቶ የላኩትን መልዕክት ለማድረስና በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር እንደሆነ፣ ሪፖርተር ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ለመረዳት ችሏል።
ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ሰሞኑን ለኬንያው አቻቸው የገለጹትን የኢትዮጵያ አቋም ነበር ለዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ልዑክም ያረጋገጡት። የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ያሉ ልዩነቶችን ኢትዮጵያ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የሚጠቅም መፍትሔ ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ ስለመሆኗ የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፣ ወደዚህ ለመድረስ የሚያስችለው መንገድ ‹‹አፍሪካዊ መፍትሔ ለአፍሪካዊ ችግር›› የሚለው መርህ እንደሆነ ገልጸውላቸዋል።
በዚህ መንገድ ልዩነቶችን ለመፍታት ኢትዮጵያ ምንጊዜም ዝግጁ እንደሆነችበትም አስምረውበታል፡፡
ግብፅና ሱዳን ከፈጠሩት ጥምረት ጀርባ ምን አለ?
የህዳሴ ግድቡ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተሉ አንድ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ በግብፅና ሱዳን መካከል የተፈጠረው አዲስ ጥምረት በህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ላይ ያለውን የሦስቱ አገሮች አለመግባባት ለመፍታት ያለመ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።
ግድቡን የተመለከተ ድርድር በአሜሪካም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት ተሞክሮ መቀራረብ የተቻለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያን የወደፊት የዓባይ ውኃ የመጠቀም መብት ለመገደብ ትልቅ ፍላጎት በግብፅ በኩል በመያዙ መቋጫ መፍትሔ አልተገኘለትም ብለዋል።
በግብፅ በኩል የተያዘው አቋም የህዳሴ ግድቡ ዕውን መሆን ኢትዮጵያን ባለችበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢም ሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና ትልቅ ፖለቲካዊ ጉልበት እንድታገኝ ያስችላታል የሚል ሥጋት እንደሆነ የገለጹት ባለሙያው፣ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያለውን ልዩነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ በላይ ባለው የዓባይ ውኃ ተፋሰስ ላይ ሌላ ተጨማሪ መሠረተ ልማት እንዳታከናውን የሚገድብ አንቀጽ ስምምነት ውስጥ እንዲገባ ፅኑ አቋም የያዘችውም፣ ሆን ብላ ስምምነት እንዳይደረስ ያደረገችው እንደሆነ ይገልጻሉ።
በቅርቡ የግብፅ ፕሬዚዳንት በሱዳን ባደረጉት ጉብኝት ወቅት በአራትዮሽ አደራዳሪዎች አዲስ ድርድር እንዲጀመር አቋም እንደያዙ ቢገለጽም፣ በጉብኝቱ ወቅት ዋና የውይይት አጀንዳ የነበረው ኢትዮጵያ በመጪው ክረምት የውኃ ሙሌት እንዳታካሂድ ማድረግ የሚችሉበትን መንገድ ለመቀየስ እንደሆነ ገልጸዋል።
የግብፅ ፕሬዚዳንት በሱዳን ያደረጉትን ቆይታ አጠናቀው በተመለሱ ማግሥት በሱዳን መንግሥት በኩል አዲስ ዝግጅት መጀመሩን የገለጹት ተደራዳሪው፣ የዝግጅቱ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ በመጪው ክረምት የውኃ ሙሌት ብታካሂድ ሱዳን ላይ ማወቅ የሚቻልበትን መንገድ የመንደፍ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከዚህ የግብፅ ፍላጎት ጋር ስምም ሆኖ አሁን ላይ አዲስ የተከሰተው ፖለቲካዊ ጉዳይ፣ የአውሮፓ አገሮችና አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካና በአጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴን በተመለከተ የያዙት አዲስ አቋም እንደሆነ ይናገራሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት የፖለቲካ መንገድ የተባበረች ኢትዮጵያን የመፍጠር ህልም መሆኑ ሥጋት ውስጥ ሳይጥላቸው እንዳልቀረ የሚናገሩት ምንጮች፣ የሥጋቱ መሠረት የፖለቲካ ልዩነት ተከስቶ ሳይሆን መፃኢ የፖለቲካ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ነው ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል።
ይህንንም ሲያስረዱ ኃያላኖቹ አገሮች የወደፊት የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በአንድ አገር ላይ ለመፈጸም የሚያስችላቸውን ቀዳዳ ዘውትር አስበው እንደሚንቀሳቀሱ፣ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለመፈጸም በሚፈልጉበት ወቅት ተግዳሮት ቢገጥማቸው ወደ መንግሥት ለውጥ መሄድ የሚችሉበት ክፍተት መኖሩን ያረጋግጣሉ ብለዋል።
የተባበረ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ለውጥ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች መግቢያ መንገድ የማይሰጥ በመሆኑ ይህ ከመፈጠሩ በፊት ኃያላኖቹ እንደሚንቀሳቀሱ የገለጹት ምንጮች፣ የህዳሴ ግድቡ አጀንዳ ከኃያላኑ ፍላጎት ጋር የሰመረውም እዚህ ነጥብ ላይ እንደሆነ ያስረዳሉ።
ይህንን የውጭ ኃይሎች ትብብር መናድ የሚቻለው የጠበቀ የውስጥ ፖለቲካዊ አንድነት በመመሥረት፣ ወይም ይህ እንዳይፈጠር ኃያላኑ የሚያደርጉትን ጫና በመቀበል እንደሆነ ገልጸው ሁለቱንም የማድረግ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ አስረድተዋል።
የጠበቀ የውስጥ ፖለቲካዊ አንድነት በመመሥረት መቋቋም ለኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል ስንቅ እንደሆነ ጠቁመው፣ ይህንን ተግባራዊ በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ጫናዎችና ማዕቀቦች የሚኖሩ ቢሆንም ዘላቂነት እንደማይኖራቸው ገልጸዋል።
በግብፅና በሱዳን በኩል የተፈጠረው ጥምረትም ይህንን የምዕራባዊያን ፍላጎት የማስፈጸም አሻጥር እንደሆነ፣ ይህንንም ለመፈጸም የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደማይኖር፣ ይህንን በሚያደርጉበት ወቅትም እንደ ተመድ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ድጋፍ እንደሚያገኙ አክለዋል።
Filed in: Amharic