ዝክረ ኮ/ል ሳህሌ ደጋጎ…!!!
[በወሰንሰገድ ገ/ኪዳን]
እንደ መግቢያ
በ1923 ዓም
ወለጋ፣ ነጆ።
በባላምባራስ ደጋጎ አለቤ እና በወ/ሮ ደጊቱ ፈይሳ ቤት ታላቅ ደስታ ሆነ፦ ወንድ ልጅ ተወለደ። እልልታ ቀለጠ።
ነጆ ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ፣ በአንዲት መንደር የተወለደው ይህ ሕፃን፣ በምድረ ኢትዮጵያ ስሙ የገነነ፣ ዝነኛ እና ታላቅ የሙዚቃ ሰው ይሆናል ብሎ የገመተ አልነበረም።
እንደማንኛውም ሕፃን በወለጋ ነጆ ምድር እየቦረቀ አደገ። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ወደ ነቀምት ተላከ፦ ት/ቤት ገባ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ወደ አዲስአበባ አቀና። እናም ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ዘለቀ።
፩
ሳህሌ ደጋጎ።
እንደማንኛውም እንደዘመኑ ተማሪዎች እውቀት የተጠማ ነው። ንቁ ነው። ጎረምሳ ነው። በዚያ የጉርምስና ዕድሜው የሚያያቸው ወታደሮች ትኩረቱን ሳቡት። ሸንቃጦች ናቸው። አለባበሳቸው ያምራል። እነሱን መሆን አማረው። በውትድርና ፍቅር ተለከፈ። እናም ሄደ፦ ወደ ክቡር ዘበኛ ክ/ጦር። ተቀጠረ። በ19 ዓመቱ፦ በ1942 ዓም።
፪
የተቀጠረው በተራ ወታደርነት ነው። ስልጠና ወሰደ። ለውትድርና ፍቅር ስለነበረው ስልጠናው አልከበደውም። ከስልጠና በኋላ ክ/ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ውስጥ ተመደበ። እግረኛ ባንድ ውስጥ።
የእግረኛ ባንዱ አሰልጣኝ ፈረንሳዊ ነው። ሙሴ ኒኮ ይባላል። ክላርኔት የተባለ የሙዚቃ መሳርያ ሰጠው። በሚገባ አሰለጠነው። ሳህሌ ጎበዝ ነው፤ ክላርኔትን ተራቀቀባት። ቀጠለ። አኮርዲዮንን፣ አልቶ ሳክስን፣ ፒያኖን ተካነባቸው። ድንቅ የሙዚቃ ባለሙያ ወጣው።
በውትድርናውም እንደዚያው ነው። ጥንቁቅ ነው። ስነ ስርዓት አክባሪ ነው። በዚህም የተነሳ በአንድ ጊዜ ከተራ ወታደርነት ተንደርድሮ የሃምሳ አለቅነት ማዕረግ ተቀዳጀ።
፫
“ጠቅል ራዲዮ ጣቢያ”
በ1950ዎቹ መጀመሪያ ነው የተቋቋመው። ወታደራዊ ሬዲዮ ጣቢያ ነው። ሙዚቀኞች ለሕዝብ በቀጥታ ሙዚቃቸውን የሚያቀርቡበት ጣቢያም ነበር፦ በወቅቱ።
ይህ ጣቢያ በተቋቋመ ጊዜ በአኮርዲዮን ጥዑም ዜማ ለጣቢያው አድማጮች ሲያንቆሩ ከነበሩት የሙዚቃ ሰዎች መካከል የመጀመሪያው ነበር፦ ሣህሌ ደጋጎ።
ከዚያም፣ ከእነ ሻለቃ ግርማ ይህደጎ፣ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ እና ከሻለቃ ባሻ ገብረዓብ ጋር የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራን ደመቀባት።
፬
ከዚህ በኋላ “አንቱ” እያልን ነው ታሪኩን ምንተርከው። በስራዎቻቸው በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መንገስ የ
ከቻሉ ጎምቱ የሙዚቃ ባለሙያዎች ተርታ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸውና።
ብዙዎቻችን ኮ/ል ሳህሌን የምናውቃቸው በሙዚቃ ሰውነታቸው ብቻ ነው። እሳቸው ግን “ሁለገብ የጥበብ ሰው” ነበሩ። የሕይወት ታሪካቸው እንደሚዘክረው አጫጭር እና ረዣዥም ድራማዎችም ይደርሱ ነበር። ከሁሉ በላይ ግን የሚጎላው ሙዚቃ አቀናባሪነታቸው ነው። እንዲያም ሆኖ እጅግ በጣም ብዙ የግጥምና የዜማ ድርሰቶችን አበርክተዋል።
ለአብነት ያህል፦
ጥላሁን ገሠሠ ከተጫወታቸው ሙዚቃዎች ውስጥ “ስቆ መኖር”፣ “እውነት ማሪኝ” የሚሉትን ግጥሞች የኮሎኔል ሳህሌ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው። “ዋይ ዋይ ሲሉ”፣ “ውሸት ለመናገር”፣ “ልብሽን ለአፈር ሰው”፣ “ኮቱሜ”፣ የሚሉትን ዘፈኖች ደግሞ ግጥምና ዜማዎች ሰርተዋል።
የድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ “አይወጣኝም ክፉ ነገር”፣ “ፍላጎቴ”፣ “ምን ነበር”፣ “ምንድነው ትዝታህ”፣ … የተሰኙትን ዘፈኖች አቀናብረዋል። “ከንቱ ሥጋ” “አታሳየኝ ጭንቁን”፣ “የፍቅር ወጋገን”፣ “ቃልኪዳን”፣ “በብር አይጋዛም”፣ “ፍቅርህ ቀሰቀሰኝ”፣ ወዘተ የተሰኙትን ዜማና ግጥሞች አበርክተዋል።
ከመሐሙድ አሕሙድ፣ ለተፈራ ካሳ፣ ከመንበረ በየነ ከውብሻው ስለሺ እና ስማቸውን ያልጠቀስናቸው አንቱ የተባሉ ድምፃውያን ጀርባ ሕዋው አሻራቸውን ያሳረፉ ድንቅ ባለሙያ ነበሩ፦ ኮል ሳህሌ።
፭
ኮ/ል ሳህሌ ከላዬ ለጠቀስናቸው እና ለሌሎች ብዙ ሙዚቀኞች ከ500 በላይ ሙዚቃ አቀናብረዋል። እጅግ ብዙ ግጥምና ዜማ ፅፈዋል። ይህም ብቻ አይደለም፤ ከ100 በላይ የኦሮምኛ ዜማና ግጥምም አበርክተዋል፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ዘመን አይሽሬ አሻራ ያሳረፉ ጎምቱ ባለሙያ ናቸው/ነበሩ፦ ኮ/ሳህሌ ደጋጎ።
እኚህ ታላቅ እና ጎምቱ የሙዚቃ ባለሙያ ባደረባቸው ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በ79 ዓመታቸው ነው። የዛሬ 11 ዓም ልክ በዛሬው ዕለት። መጋቢት አምስት ቀን 2002 ዓም።
እነሆ እኛም የታላቁን የሙዚቃ ሰው 11ኛ ሙት ዓመት እንዲህ ዘከርነው።
ነፍስ ይማር!