>
5:13 pm - Monday April 19, 8309

የጉዞ ማስታወሻ፡ ትግራይ ላይ በአካል ተገኝቼ ካየሁትና ከሰማሁት...!!! (በአማን ነጸረ)

የጉዞ ማስታወሻ፡ ትግራይ ላይ በአካል ተገኝቼ ካየሁትና ከሰማሁት…!!!

በአማን ነጸረ


እይታዬ በሥራ አጋጣሚ በቆየሁባቸው ቀናት በመቐለ፣ በምሥራቃዊና ማዕከላዊ ዞን ማለትም ከመቐለ እስከ ሽረ ባሉ ከተማና ገጠሮች በእግረ መንገድ ባስተዋልኳቸው ነባራዊ ሁኔታዎች የተወሰነ ነው፡፡ በቆይታዬ ዐይንና ጆሮዬን ተጠቅሜያለሁ፡፡ ሰማሁ፤ አየሁ፡፡ ያየሁትና የሰማሁትን፡- እንቅስቃሴ፣ በጎ አድራጎት፣ ኤርትራ፣ ዘረፋ፣ ሚዲያ፣ ሰሜን ዕዝ፣ የሽግግር አስተዳደሩ፣ ሕወሓት፣ ኑሮ፣ አብያተ ክርስቲናትና ምዕመናን በሚሉ አርእስት በስሱ እናገራለሁ፡፡ የምናገረው ባየሁትና በሰማሁት ቦታና ድርጊት ልክ ነው፡፡
ሰሜን ዕዝ
የሰሜን ዕዝን በትግራይ ልዩ ኃይል መጠቃት የሚያስተባብል ነዋሪ አልገጠመኝም፡፡ ለጥቃቱ ብዙ መላ ምትና ሰበብ ተነግሮኛል፤ በሕግ የተቃኘው ሕሊናዬ ግን መላ ምቱንና የፖለቲካ ትንተናውን በትዕግሥት ቢያዳምጥም ድርጊቱን በሕጋዊነት ለመቀበል እሺ አላለኝም፡፡ የሰሜን ዕዝ ጥቃት በደል ነው፣ ጥቃቱ የተከፈተበት ቦታና አጋጣሚም በክልሉ ሕዝብ ላይ ለደረሰው ጉዳት አንደኛው ዐቢይ መነሾ ነው የሚለውን ሐሳብ የሚያቀልልኝ መረጃ አላገኘሁም፡፡ የግፉዓኑን ወታደሮችን አስከሬን ከየተቋማቱና ከየማሳው ተለቅሞ በአንድ ቦታ በቅጡ የማሳረፍ ተግባርም እንዳልተከናወነ ታዝቤ አዝኛለሁ፡፡ ባላሰቡበት የወደቁት ግፉዓን በክብር ሊያርፉ ይገባል!
የትግራይ ልዩ ኃይል
ልዩ ኃይሉም ሆነ አመራሩ ባገኘኋቸው የትግራይ ነዋሪዎች ሁሉ ምጽአቱ የሚናፈቅና የሚጠበቅ ነው፡፡ ሕወሓትን የሚተች ይኖራል፤ የማይደግፍ ግን አልገጠመኝም፡፡ የድርጅቱ ተቀባይነት ለመቶ ፐርሰንት የቀረበ ነው፡፡ ልዩ ኃይሉ ከአምስት ኃይሎች ጋራ ተዋግቶ በሕይወት መኖሩ እንደሚያስደንቃቸው የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም፡፡
እንቅስቃሴ
መቐለን ጨምሮ ባየኋቸው ከተሞች እንቅስቃሴ አለ፡፡ መቐለ ለ‹‹ኖርማል››ነት የቀረበ እንቅስቃሴ ሲኖራት ሽሬና ውቅሮ ይከተሏታል፡፡ አዲግራትና አክሱም ከሰቀቀናቸው አልተመለሱም – በተለይ አክሱም፡፡ ኤርፖርቱ በመጎዳቱ፣ የቱሪዝም ፍሰት በመቀነሱ፣ በርካታ ፈላስያንን በማስጠለሏ፣ የኤርትራ ታጣቂዎች ፍጅትና ተደጋጋሚ ጉብኝት ያስደነገጣት አክሱም በትካዜ እንደ ተሸፈነች ናት፤ አድዋም እንዲሁ፡፡
እውነት ነው! የቁጥር መለያየት ይኖር እንደሆነ እንጂ አክሱም ላይ በንጹሓን ላይ ፍጅት ደርሷል፡፡ የኤርትራ ታጣቂዎች አሁንም በአካባቢው ወጣ ገባ ይላሉ፤ እኔም የደረስኩ እለት እነርሱንም በእነርሱ መኖር የሚሰቀቀውን ግፉዕ ሕዝብም በዐይኔ አይቻለሁ፡፡ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ሕንፃና አፀድ ላይ ግን የደረሰ ጉዳት የለም፤ ፍጅቱም ከዐፀደ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ነው – አንዲት መበለት እንደ ነገሩኝ፡፡
የቤተ ክርስቲያኑን ዙሪያ ገብና ውስጡን ለምዕመኑ በብቸኝነት በተከፈተው የምሥራቅ በር ገብቼ አይቻለሁ፤ ወደ ውስጥ ዘልቄ ተሳልሜያለሁ፤ የደረሰ ጉዳት የለም፡፡ መበለቷ እንደ ነገሩኝ ‹‹የከተማ ሰው ግን አልቋል!›› ከመቐለ ወደየትኛውም አካባቢ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አለ፡፡ መቐለ ላይ የነዳጅ እጥረት እንደሚፈራው አይደለም፤ የነዳጅ አቅርቦት አለ፡፡ በየትኛውም አቅጣጫ ፍትሻው ጥብቅና ተደጋጋሚ ነው! የሕዝብ ትራንስፖርት፣ ባጃጆች፣ የጀበና ቡና የትግራይን በሕይወት መኖር ለመናገር ትር ትር ይላሉ፤ ይውተረተራሉ፡፡ ከአምስት በላይ የዋና ዋና አገናኝ አስፓልት መንገዶች ለጦር ስትራቴጂ ሲባል በትግራይ ልዩ ኃይል፣ እንዲሁም በጀት ድብደባ ጉዳት ቢደርስባቸው ለጊዜው ተመልሰው ተሞልተዋል፤ ትራንስፖርት አልተቋረጠም፡፡ መቐለ ላይ ንግድ ባንክን ጨምሮ በርካታ የግል ባንኮች ሥራ ጀምረዋል፡፡ አዲግራት፣ አክሱምና ሽሬ ንግድ ባንክ ተከፍቷል፡፡ ወረፋው ግን በሁሉም ሥፍራ አሰልቺ ነው፤ ገንዘብ የሚያወጣ እንጂ የሚያስገባ ባለመኖሩ የገንዘብ እጥረት አለ፡፡ ኤ.ቲ.ኤም ማሽን ሙሉ ሉሙ አይሠራም፤ ከመቐለ ውጭ ያለው ከሞላ ጎደል ያየሁት ሁሉ ተዘርፏል፡፡ የሮማናት አደባባይ እንደ ወትሮው ሁሉ አዳዲስና ነባር መጻሕፍት ተዘርግተው ይሸጡበታል፡፡ በእዚያ ድባብ ውስጥ ሆነው መጽሐፍ የሚያነቡ ሰዎች ምንኛ ጽኑዓን/ት ናቸው!
በጎ አድራጎት
የትግራይ ትልቁ የበጎ አድራጎት ድርጅት ራሱ ሕዝቡ ነው፡፡ በሰቆቃው ጊዜ፡ ውሃ፣ መብራት፣ ስልክ በተቋረጠበት ወራት የነበረው የእርስ በርስ መተሳሰብና መረዳዳት ከሁሉም አንደበት ይስሰማል፤ ሲሰሙት አንጀት ይበላል፤ ደግሞም ያስደንቃል፡፡ ያ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በአሁኑ ጊዜ ለቁጥር የሚያታክቱ የእርዳታ ድርጅቶች መቐለ ገብተዋል ሳይሆን ጎርፈዋል! በገቢር ወደ ገጠር እየወጡ ሲንቀሳቀሱ ያየኋቸው ግን፡- የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ ሳማሪታን፣ ዩኒሴፍ፣ ድንበር የለሽ ሐኪሞች፣ የጀርመን፣ የዴንማርክ፣ የአይሪሽ የእርዳታ ድርጅቶች ናቸው፡፡ በተለይ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና ድንበር የለሽ ሐኪሞች በተደጋጋሚ በገቢር ያየኋቸው ናቸው፡፡ የተቀሩት ብዙኃኑ መቐለ ላይ በየሆቴሉና ጀበና ቡናው በተሽከርሪዎቻቸው ግንባር የድርጅት አርማቸውን ቀስረው ከዓዲ ሐውሲ እስከ ሮማናት የሚያውደለድሉ፣ በየሆቴሉ ሰገነት ሲጃራ እያቦነኑ ምናልባትም ሐሳዊ ሪፖርት ሲጽፉ የሚውሉ ሆነውብኛል፡፡ በጀታቸውን በአስዳደር ወጪ እያፈሰሱ በምስኪናን ስም እንዳይነግዱ የሚከታተል አካል እንደሚኖር ተስፋ አለኝ፡፡ የፌደራሉ መንግሥት በየትናንሽ ከተሞች እርዳታ ሲያከፋፍል ተመልክቻለሁ፤ እርዳታው የገጠሩን ክፍል በስፋት መሸፈኑን ግን አላረጋግጥም፡፡ ከተማ ላይ ያለው ሰው ደጋግሞ እንደሚወስድ ተነግሮኛልና ለገጠሩ ሰው መዳረሱ ላይ በቂ ክትትል ማድረግን ይጠይቃል፡፡ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ትጋትና ንቃት ምስጋናም ድጋፍም የሚገባው ነው፡፡
 
የሽግግሩ አስተዳደር
የትግራይ የሽግግር አስተዳደር ሥራውን በመጠኑ ይሠራል፡፡ መዋቅሬን 70 በመቶ ዘርግቻለሁ ማለቱ ግን የማይታመን ነው፤ እውነት አይመስለኝም፡፡ በመቐለ ያሉት ቢሮዎች ጭል ጭል ይላሉ፡፡ ግማሽ ቀን ይሠራሉ፤ ከዚያቸውም ሩቧን ለስብሰባ ይሠዋሉ፡፡ ቢሮዎቹ ለሥራ ምቹ አልተደረጉም፣ ከፌደራል መንግሥት ቃል የተገቡ የቢሮ ቁሳቁሶች፣ ተሸከርካሪዎች፣ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ እየቀረበ እንዳልሆነ ሰምቻለሁ፤ በቦታው ተገኝቼም አረጋግጫለሁ፡፡ ደሞዝ ብቻ ነው የሚገባላቸው፡፡ ሲቪል ሰርቪሱን ወደ ሥራ ለመመለስ በሁሉም አካል ጥረት ቢደረግ መልካም ነው፡፡ መቐለ ላይ የፀጥታ መዋቅሩን ከፌደራል ፖሊስ ጋራ በመተባበር ለማቋቋም ብርቱ ጥረት እየተደረገ መሆኑንና ፖሊሶችም ሪፖርት እያደረጉ መሆኑን ታዝቤያለሁ፡፡ ፍርድ ቤት ግን እየገቡ ፈርመው ከመውጣት ውጪ ሥራ አልተጀመረም፤ ሬጅስትራር አዲስ ፋይል መክፈት አልጀመረም፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ከፊል ወድመት ደርሶበታል፡፡ የትግራይ ልዩ ኃይል የሚኒሻና ፖለስ መዋቅሩንም አካትቶ ለጦርነት መጠቀሙ የፀጥታ መዋቅሩን ዳግም ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት፣ የከተማ ወንበዴዎችን መቆጣጠሩን፣ የተቋማትን ጥበቃ አክብዶታል፡፡ በየፕሮጀክት ሳይቱ የነበሩ የአካባቢ ሚሊሻዎች ወይ በረሀ ገብተዋል፤ ወይ መሣሪያ አውርደዋል፡፡ ይህም የንብረት ጥበቃውንና የየጎጥ ፀጥታውን ሙሉ ለሙሉ ወደ ፈሪሃ አግዚአብሔር አዙሮታል፡፡ ደግነቱ ተራ ሽፍታ አለመኖሩ! የአሠራር ጉድለት በ‹‹ፀረ-መኸተ/መከላከል/››ነት መፈረጁን የሚያሳዩ ባነሮች፣ የሕወሓት ዓመታዊ በዓላት መፈክሮች፣ አርማዎች፣ ወይን መጽሔት፣ በየቢሮው አሉ፤ የሕወሓት ሃርድ ዌር በቦታው ነው፤ በሽግግር አስተዳደሩ አልተነካም፡፡ የትግራይ ክልል የፕሬዝዳንት ቢሮ የእንግዳ መቀበያ ላይ የቀድሞዎቹ ፕሬዝዳንቶች የአለቃ ፀጋይና የአቶ ገብሩ ዐሥራት ፎቶ ግራፍ ብቻ አለ፡፡ እነ አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ከጦርነቱ በፊት ለሽምግልና ተልከው የተፈተሹበትን ጥብቅ የሕንፃ መግቢያ ዛሬ ከውጭ ብቻ አንድ ጊዜ ተፈትሾ እንደ ዘበት መግባት ይቻላል፡፡ የሽግግሩ ፕሬዝዳንት እንደ ልብ ባይገኙም የእርሳቸው ቢሮ የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴና ግብዓት አለበት፡፡ የሽግግሩ ፕሬዝዳንት በሚኖሩ ጊዜ በበራቸው ላይ በፌደራል ፖሊስ ኮማንዶዎች የሚካሄድ ተጨማሪ ፍተሻ አለ፡፡ ቢሮው ለሁሉም ባለጉዳይ ክፍት መሆኑን አይቼ አረጋግጫለሁ፤ ክፍት የመሆኑን ህል መፍትሔ መስጠተቱን ግን አላረጋግጥም፡፡ የመቐለ የጽዳት አገልግሎት ጥሩ የሚንቀሳቀስ የሕዝብ አገልጋይ ነው፤ አጽጂዎቹ ክብር ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እንደ መንገድ ባለሥልጣን፣ መብራት ኃይል፣ ቴሌ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ የፌደራል የመሰረተ ልማት ተቋማት የመልሶ ጥገና የማድረግና የደረሰ ጉዳትን የመለየት ሥራ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ የሽግግር መንግሥቱና ኮማንድ ፖስቱ ለዚህ የሚሰጡት ድጋፍ በካድሬ አነጋገር ‹‹አበረታች›› የሚባል ነው፡፡ የሽግግር አስተዳደሩን ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ብሎ ለመጥራት ገና ረዥም ርቀት ይቀራል፡፡ በውስጡ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ችግር ለመቅረፍ የሚጥሩ ቅን ሰዎች ከፌደራሉ መንግሥት በኩል ቃል በሚገባው ልክ ድጋፍ ሳያገኙ፣ ከመፍቀርያነ ሕወሓት በኩል እንደ ባንዳ እየታዩ እንኳ ባለቻቸው አቅም የሕዝባቸውን ሸክም ለማቅለል የሚያደርጉት ጥረት ራሴን በእነርሱ ጫማ አድርጌ እንዳዝንላቸው አድርጎኛል::
መከላከያና ፌደራል ፖሊስ
ሕዝቡ ከመከላከያና ከፌደራል ፖሊስ ጋራ ያለው ግንኙነት መጥፎ የሚባል አይደለም፡፡ የትግራይ ልዩ ኃልንም መከላከያውንም ‹‹የኛ›› የሚሉ ሰዎች ገጥመውኛል፡፡ ሁለቱ እንደ ሕዝብ ፀር አይታዩም፡፡ ‹ሕወሓት መንገድ ላይ ጠብቆ ሰው ገደለ፣ መከላከያ ወጣቶችን እንዲህ አደረገ፣ … › የሚሉ ነጠላ ድርጊት ገላጭ ተጨባጭ ማስረጃዎችን አይቻለሁ፡፡ ቢሆንም ማስረጃዎቹ መሬት ላይ ያለውን ሰፊና ተጨባጭ ሀቅ ወካይ አልሆኑልኝም፡፡ ነጠላ ክስተቶች ናቸው፤ ዘለዕለታዊ ዘወትራዊ ድርጊቶች አይደሉም፡፡ እንደ አንድ ግዙፍ ሸማች ኃይል መከላከያና ፖሊስ የከተማው የአገልግሎት ዘርፍ ወደ ሥራ እንዲመለስ ድርሻ እንዳላቸው ታዝቤያለሁ፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያለመዛነፍ ይተገበራል፡፡ ፍተሻዎች ጥብቅ ናቸው፤ መታወቂያም የግድ ነው፡፡ ስልክ ስለመበርበር ግን ይወራል እንጂ አልገጠመኝም፡፡ የመደፈር ሪፖርት በሚመለከት መረጃ የማገኝበት ዕድልና አጋጣሚ ስላልነበረኝ ምንም ማለት አልችልም፡፡ የፌደራልና የመከላከያን የብሔር ተዋጽኦ ከገጽታቸውና ከቋንቋ ዘያቸው በመነሣት ሚዛናዊ ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ከማዕከል የተላኩ የትግራይ ተወላጅ የፌደራል ፖሊስ አባላት ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ በብዛት አሉ፡፡ ትግርኛ የሚናገር የመከላከያ ሠራዊት አባል አክሱምና መቐለ መግቢያ ላይ መሶቦ የሚባል አካባቢ አጋጥሞኛል፡፡ ‹የአንድ ብሔር ተወላጆችን ብቻ መርጦና አደራጅቶ መከላከያን ማጥቃት ጸያፍ ነው› ለሚል መከራከሪያዬ ‹አዲግራት አካባቢ የትግራይ ልዩ ኃልን በወጋው መከላከያ ውስጥ የተጋሩ ወታደሮች ቁጥርና ተሳትፎ ከምታስበው በላይ ነው› የሚል ማስተባበያተሰጥቶኛል፡፡
የኤርትራ ታጣቂዎች
እጅግ ጸያፍና ኢሰብአዊ እንዲሁም አውዳሚ ድርጊት በሰውና በንብረት ላይ እያሳደሩ ያሉት የኤርትራ ታጣቂዎች ናቸው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የገባውን የኤርትራን ታጣቂ በሁለንተናዊ መገለጫው ሠራዊት ለማለት ይከብዳል፡፡ ሲቪሎችን በጭካኔ ይገድላል፣ ይዘርፋል፣ በየቦታው ድንበር እየገፋ ባንዲራ ይሰቅላል፡፡ ምሥራቅና ማዕከላዊ ትግራይ በከፊል በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ ዘመን በነበረ ኋላቀር የወረራና ዘረፋ መልክ ባለው ጨካኝ ታጣቂ እጅ ውስጥ ነው ያለው፡፡ እዚያ ያልተሰማ እንጂ ያልተፈጸመ የለም! የኤርትራ ታጣቂዎች (አሁንም ታጣቂ ነው የምለው፤ በፍጹም ‹‹ፕሮፌሽናል›› ወታደሮች አይደሉም፤ የደህና ሽፍታ መመዘኛም አያሟሉም!) ዘረፋ ግለሰብን፣ ባለሀብትን፣ የክልሉ መንግሥት የልማት ድርጅቶችን፣ የፌደራል መንግሥት ተቋማትን ከመቐለ ዙሪያ እስከ አክሱም ሸፍኗል፡፡ በዐይኔ ያየኋቸው ውቅሮ፣ አዲ ግራት፣ አድዋ የታጣቂዎቹ ብርቱ የክፋት ክንድ አርፎባቸዋል፡፡ አዲ ግራት ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ ፋርማሲዩቲካል፣ ጎዳ ብርጭቆ፣ ሳባ አብነ በረድ፣ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ የኤርትራ ታጣቂ የክፋት በትር ካረፈባቸው ታላላቅ ኢንደስትሪዎች ውስጥ ናቸው፡፡ ይህ ኹሉ ግፍ የተፈጸመው የትግራይ ልዩ ኃይል ተመትቶ የተጠቀሱትን ከተሞች ከለቀቀ ከቀናት በኋላ ነው፡፡ የፌደራል ኃይላት ንብረት ከመወሰዱ በፊት ከደረሱ ወይም ተነግሯቸው ቅኝት ካደረጉ ዘረፋው ጋብ ይላል፤ ተዘርፎ በመሄድ ያለ ንብረትን ግን ሲያስቆሙ እንዳልታዬ ብሶተኞች ደጋግመው ነግረውናል፡፡ ዘረፋው ከአጥር የሽቦ ገመድ እሰከ ክሬሸርና የኢንዱስትሪ መሣሪያዎች የደረሰና እንደ መካኒክ፣ ሹፌር፣ ኤሌክትሪሺያን የመሳሰሉ ሙያተኞች የሚታገዝ፣ ፕሮፌሽናል ባልሆነ ታጣቂ የሚካሄድ በቀል-ወለድ ‹‹ፕሮሽናል›› ዘረፋ ነው፡፡ የኤርትራ ታጣቂዎች መግባትን እስካሁን የሚጠራጠር ካለ መጽሐፍ መትቼ፡ ስመ እግዚአብሔር ጠርቼ ማረጋገጥ የምችል ምስክር ነኝ! በደንብ አሉ! የዘረፋ መንገዳቸውን ከከተማ ወደገጠሩ ሕዝብ እያዞሩ ነውና እንደ ሀገር የበለጠ ከማፈራችን በፊት በአመራር ደረጃ ቢቻል እንዲወጡ፣ ካልተቻለም ‹‹ሠራዊት›› ለመሆን እንዲሞክሩ መልእክት ቢደርሳቸው መልካም ነው! ስለ ኤርትራ ታጣቂዎች መግባት አናውቅም የሚል ምላሽ ከእንግዲህ ቢሰጥ ሕዝብን መሸንገል ነው! ብሔራዊ ክብር ላይ ቸልተኛ መሆን ነው፤ ሕወሓት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጸያፍ ድርጊት ብሔራዊ ክብርን ቸል እስከ ማለት ሊያደርስ የሚችልን እልህ ሊያነግሥ አይገባም! ዐይኔን ነው የማምነው! እዚህ ላይ ስለ ሀገሬ ክብር ‹የታዬ ሁሉ አይነገርም› ብዬ ያለፍኩትም መኖሩ አይዘንጋብኝ!
ሚዲያና መረጃ
ኢንተርኔት አልተከፈተም፡፡ መቐለ ላይ የሚታዩ ሚዲያዎች በቅደም ተከተል፡- ትግራይ ሚዲያ ሐውስ፣ የኤርትራ ተቃዋሚዎች የሚመሯቸው አሰና ቴሌቪዥንና ኤሪሳት፣ መረጃ ቴሌቪዥን (በተለይ ኢትዮ 360 የሚባለው) ናቸው፡፡ እነዚህን ጣቢያዎች ላለማጣት አብዛኛው ተመልካች ዲሹን ወደ ኢትዮ ሳት አላዞረም፡፡ ትልልቅ ሆቴሎች ግን ኢትዮ ሳትንም ናይልን ሳትንም አቀናጅተዋል፡፡ እዚያ ሳለሁ አንድም የክልሉን ቅኝት ለመረዳት፡ አንዳንዴም በአማራጭ እጦት እነዚህን ሚዲያዎች እከታተል ነበረ፡፡ ክፋቱ፡- ያገኘሁት ሰው ሁሉ ራሴ በጆሮዬ ማታ የሰማሁትን ወሬ ልክ ራሱ እንዳየና እንደሰማ አድርጎ ቃል በቃል ያወራልኛል፡፡ የመረጃ ክፍተቱና ውጥረቱ የስሚ ስሚ መረጃንና የረከቦት ዙሪያ ፖለቲካዊ ሐተታን አበረታትቷል፡፡ ከነዋሪዎች የሚገኙትን መረጃዎች እንደ ወረደ ከመውሰድ ይልቅ ከሚከታተሏቸው ሚዲያዎችና ለሚሰጡት መረጃ ወይም ድርጊት ካላቸውን አካላዊ ቅርበት አንጻር መገምገም ይመረጣል፡፡ ታዳጊ ሕፃናት ፖለቲካዊ ቃናና ውጥረት ያለበትን ሚዲያ በተመስጦ ሲሰሙ ሳይ ይጨንቀኛል፡፡ ያለ ልማዴ የኢቲቪዎቹ ‹‹አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች›› ይናፍቁኛል፡፡ ጥቅል የሚዲያዎቹ ይዘት ‹ትግራይን ከብሶት የመውለድ› ሆኖ ይስሰማኛል፡፡ ስሜቱ በከተሜው ዘንድ የመጋባት ምልክት አለው፡፡ የሚዲያዎቹ ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው! ያን ዕድል ከፖለቲካዊና ወታደራዊ አጀንዳ ባሻገር በመጠኑ የሞራል ይዘት ጨምረው ውንብድና እንደማይገባ፣ እርስ መረዳዳቱ እንዲቀጥል፣ ሲቪል አስተዳደሩ በመጠኑ ወደ አገልግሎት እንዲመለስ ቢሠሩ መልካም ነው፡፡ ማኅበራዊውንና ኢኮኖሚያዊውን ዘርፍ በዘዴ ማገዝንና ያለውንም በሕይወት ማቆየትን የዘነጉት ይመስለኛል፤ ቋንቋቸው ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ምከታን ወይም የውትድርና ጥሪን ብቻ ማዕከል ያደርጋል፡፡ ትግራይ ላይ ‹‹ሕግ ማስከበር›› የሚለው ቃል (በሕዝቡ) እጅግ የሚጠላና የሚያስቀይም አነጋገር ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ‹ከሕግ ማስከበሩ ጋራ በተያያዘ የሞተ ሲቪል የለም› የሚል ይዘት ያለው የጠ/ሚ/ር ዐቢይ የፓርላማ ንግግርም ብዙኃንን ያሳዘነና በእርግጥም እውነትነት የሌለው አነጋገር ነው፡፡ የማዕከላዊው መንግሥት ሚዲያዎች ዘገባ የሕዝቡን ሕማም አለማንፀባረቁ ተቀባይነታቸውን ጎድቶታል፤ በተቃውሞ ድምጸት የተቃኘ አድማጭ ተመልካች ፈጥሯል፡፡ የግራ ቀኙ ‹መገናኛ ብዙኃን› በእርግጥም መገናኛ ሳይሆን ‹መለያያ ብዙኃን› መሆናቸውን በትግራይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይናገራል፡፡ ከጦርነት ዐውዱ ባሻገር በነዋሪው ሕዝብ ላይ የደረሰውን ሰቆቃ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አልተረዳልንም የሚል ሰፊ ቅያሜና የባይተዋርነት ስሜት አለ፡፡ ለዚህም የአገር ውስጡ ሚዲያ በስፋት ይከሰሳል፡፡ የሚያሳዝነው 42 አማሮች ወለጋ አካባቢ መገደላቸውን የሰማሁ ሰዎቹ ከተፈጁ ከሦስት ቀናት በኋላ ከመቐለ አዲስ አበባ ከገባሁ ገብቼ ነው፡፡ የአንዳችን ሞትና ስቃይ ለሌላችን በዚህ መጠን አለመሰማቱ ገረመኝ፤ አሳዘነኝም!
ኑሮ
በሚነገረው ልክ ስለ ኑሮ ውድነትና ነዳጅ እጥረት አልመስማቴ ደንቆኛል፡፡ ሽሮ ከ80-120 ብር ተመግቤ አማርሬያለሁ፡፡ እነሱ ግን አመስጋኝ ናቸው፤ አያማርሩም፡፡ የምግብ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እጥረት አላየሁም፡፡ ትግራይ ለእንግዳ ፈገግታዋን አልነፈግችም- ዛሬም! በዲጂታሉ ሚዲያ የገነነውን ጥላቻ እዚያ አላገኘሁትም፤ ከረዥም ጨዋታና መላመድ በኋላ በብሽሽቅ ጊዜ ከሳቅ ጋራ ብልጭ ማለቱ ባይቀርም፡፡ አርሶ አደሩ አልፎ አልፎ ያርሳል፡፡ የኤርትራ ታጣቂዎች በሚበረክቱበት አካባቢ ግን አንድም የከብት ዘረፋ በመፍራት፣ አንድም ራሱን አርሶ አደሩንም የዘረፉትን ንብረት የማሸከም ፍላጎት በመኖሩ የእርሻው ሥራው ቀጣይነት ያስፈራል፡፡ ምንም ዓይነት እርዳታ ቢቀርብ እርሻውን ስለማይተካ አርሶ አደሩ ከእርሻው እንዳይዘነጋና መሬት ጦም እንዳያድር በሁሉም ወገን ቅስቀሳና ድጋፍ ያስፈልጋል፡፡ ትምህርት ካለመጀመሩም በላይ የመምህራን ደሞዝ ለወራት አልተከፈለም፡፡ የገንዘብ አቅርቦት እጥረት አሁንም አለ፡፡ ባንኮች ያልተከፈቱባቸው የወረዳ ከተሞች በርካታ ናቸው፤ በተለይም የግል ባንኮች፡፡ የፀጥታው ሁኔታ ላይ ሕዝቡ ያለው እምነት አናሳ ነው፤ ስጋቱ አልተገፈፈም፡፡
ቤተ ክርስቲያን
ያ ሁሉ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሚርመሰመስባት መቐለ አንድ የኢኦተቤክ ተራድኦ ተሸከርካሬ አለማየቴ የማይደበቅ ኃፍረት አምጥቶብኛል፡፡ የካቶሊካውያንን ንቁ እንቅስቃሴ ሳይ ደግሞ ቅናትም ሞክሮኛል፡፡ ምዕመኑ ወደየ ቤተ ክርስቲያኑ በነግሕ ይገሠግሣል፡፡ ዘወትር ካህናት ምሕላ ያደርሳሉ፡፡ ሴቶች ከሕፃን እስከ መበለታት ድረስ በባዶ እግር ክብ ሠርተው ምሕለላ የሚባለውን ሥርዓት በየአጥቢያቸው ያደርሳሉ፡፡ በጣም ያረጁት መካከል ላይ ይንበረክኩና ጎንበስ ቀና ይላሉ፣ የቻለው ዑደት ያደርጋል፣ የእመቤታችንንና የጌታን ስም ሲጠሩ ከመስማት በቀር ትርጓሜውን በማላውቀው አራኅራኂና ቀስ ያለ የትግርኛ ምት ዜማ ያለው መዝሙር በማውጣት ደረትና ጭናቸውን እየመቱ ይዞራሉ፣ በመካከሉ ይቆሙና አግዚኦታ ያደርሳሉ፣ እንደገና ዑደት ያደርሳሉ፡፡ ዜማው፣ ዑደቱ፣ ገጽታቸው ዕንባዬን ከቁጥጥር ውጭ እንዳፈስ ታግሎኛል፡፡ መቐለ ላይ አራት አጥቢያዎችን ተሳልሜያለሁ፡፡ በሁሉም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አልተቋረጠም፡፡ የአብነት ጉባኤያት አልተፈቱም፤ ሕዝቡም ለተማሪዎች እጁን አላጠፈም፡፡ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ዓዲ ሐቂ ካምፓስ ስር በቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሚሰጠው የግቢ ጉባኤ እየተካሄደ እንደሆነ በምልከታ አረጋግጫለሁ፡፡ ነጋሽ ከተማ አቅራቢያ ከአል-ነጃሺ መስጊድ ጋራ አብሮ የተጎዳውን አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን ከሩቅ አይቸዋለሁ፡፡ ጣራው ፈርሶ ይታያል፤ አልተጠገነም፡፡ ያሳፍራል! ቤተ ክርስቲያን እስካሁን በዚህ ጉዳይ ምንም አላለችም! የደንጎላት ማርያም እልቂት ትክክል ነው! እውነት ነው! ያሳዝናል! አሁንም ቤተ ክርስቲያን ምንም አላለችም! በአክሱም ከተማና እዚያው አክሱም ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የደረሰው እልቂት እውነት ነው! አሁንም እረኛው ስለ በጎቹ አልተናገረም! ‹‹የክረምት ውሃ ጥምና የእናት በደል አይታወቅም›› ይባላል፤ ቤተ ክርስቲያን ትግራይ ስላሉት ልጆቿ በለሆሳስ እንኳ አለመናገሯ ያሳፍራል፤ ያስጨንቃል፡፡ ምዕመኑ ግን ማዕተቡን አልፈታም! በማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን እነ ዲ/ን ዶ/ር ቢኒያም ቀርበው መተንፈሳቸው ሕማሙን እንዳስገሠለት በሲቃ የሚናገር ሰው አዲግራት ላይ ገጥሞኛል፡፡ ‹በዚህ አጋጣሚ የተረዳሁት የክህነት አገልግሎት እረኝነት ሳይሆን መተዳደሪያ ፕሮፌሽን መሆኑን ነው› የሚል አቋም የያዘ ሰውም ገጥሞኛል፡፡
ከእይታዬ የተረዳሁትና የተመኘሁት ሰላም ትርጓሜው ሲያጡት ብቻ የሚገለጥ ትልቅ ጸጋና በረከት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጦርነት አያሌ ጀግኖች አሏት፡፡ የሰላም ጀግኖቿ ግን በምናስብና በምንመኘው ልክ አይመስለኝም፡፡ ጀግንነትን ከማሸነፍና መሸነፍ ከፍ አድርጎ የሚተረጕም፣ በቀቢፀ ተስፋ የተዋጡ እናቶች፣ ትምህርት ቤት በመግቢያቸው ጊዜ ያለ አበሳቸው የሚባዝኑ ሕፃናት፣ እምቅ አቅማቸውን በየጀበና ቡናው ስር እየተንጓለሉ የሚያሳልፉ ወጣቶች፣ በሬው ጠምዶ ለማረስ የሚሳቀቁ አባ ወራዎች፣ … እንዳይኖሩ ሲባል እልሁን ሠውቶ የሰላምን በር የሚከፍት እርሱ ጀግና ነው፤ ደግሞ ብፁዕ! ትግራይ ላይ ያየሁት ሰቆቃ አልፎ በሰላም እንድንገናኝ ምኞቴን የለጥኩላቸውን ወዳጆቼን ይህ ቀን አልፎ ዳግም እንደማያቸው ተስፋ አለኝ፡፡
ጸሎታ ለማርያም ወሥዕለታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ ይዕቀባ እመዐተ ወልዳ!
Filed in: Amharic