>

ጦርነቱ ተጠናቋል ከተባለ፣ የመንግስት ትኩረት ምን ላይ ሊሆን ይገባል ? ( አበጋዝ ወንድሙ)

ጦርነቱ ተጠናቋል ከተባለ፣ የመንግስት ትኩረት ምን ላይ ሊሆን ይገባል ?

   አበጋዝ ወንድሙ


አሳዛኙና ሃላፊነት የጎደለው፣ ሃገርን አደጋ ላይ ጥሎ የነበረውና አክሳሪው የህወሃት ቁንጮ አመራር በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው አስነዋሪ የሀገር ክህደት ተግባር አራተኛ ወሩ አለፈ። በዚህ ቡድን የተካሄደውን ሃገራዊ ክህደት ለመቀልበስና በክልሉም ህግና ስርዓትን ለማስከበር የፌደራል መንግስቱ የከፈተው ጦርነትም እንዲሁ አራት ወራትን አስቆጥሯል።

መንግስት በመሰረቱ ጦርነቱ ካለቀ ሶስት ወራትን አስቆጥሯል ቢልም ግን አሁንም ድረስ በክልሉ ከፍተኛ ቀውስና የሰላም እጦት እንዳለ ፣ ትናንሽም ቢሆኑ ወታደራዊ ግጭቶች መኖራቸው ይታወቃል።

የጦርነት አስከፊ ገጽታው በሁለት ወገን ባሉ ተፋላሚዎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ብቻ ሳይሆን በዋናነት ተጠቃሽ የሚሆነው በከፋ መልኩ ሰላማዊ ህዝቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ነው። በትግራይ ክልልም  የሆነው ውስንም ቢሆን የእስካሁን አይን ምስክሮች ዘገባም እንደሚያትተው  ከዚህ የተለየ አይደለም።

 መንግስት በወሰደው በከባድ መሳሪያ፣ በአየርና በእግረኛ ወታደር የታጀበ መልሶ ማጥቃት ዘመቻ፣ ምንም ያህል ጥንቃቄ ቢደረግ በሰላማዊ ዜጎች በንብረትና ሌሎችም ላይ ጉዳት ማድረሱ ሊካድ የማይቻል ሃቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የህወሃት ልዩ ሃይል ራሱን ለመከላከልም ሆነ ጥቃት ሲጸናበት ሲሸሽ፣ የመንገድ፣ የመብራትና የቴሌኮምኒኬሽን ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱና፣ሊጠቅሙኝ ይችላሉ ብሎ የሚገምታቸውን መድሀኒቶችና የመሳሰሉትን መዝረፉ የሚያጠያይቅ አይደለም። 

ጦርነቱ ከተጀመረ ከዛሬ አራት ወር በፊትና አሁንም በውጭ የሚገኘው (ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም) ንቁ የህወሃት ካድሬዎችና ደጋፊዎች ስብስብ፣ አመራሩ የወሰደውን የክህደት ተግባር ወደ ጎን ብሎ መንግስትን በማጥላላትና፣ በዘላቂነት ህዝብ ለህዝብ ሊያቃቅር በሚችል ፕሮፓጋንዳ ላይ፣ (ውጤቱ ሀገር አፍራሽ የሆነ እንቅስቃሴ)  እንደተጠመደ የሚታወቅ ነው። ምናልባትም የሀገር ክህደት የፈጸመው የህወሃት ቁንጮ ቡድን ደጋፊዎች ይሄንን ማድረጋቸው የሚጠበቅ ሊሆን ይችላል  

ሆኖም ሀገር ወዳድ ነን የሚሉ ኢትዮጵያውያን ይሄንን ነውረኛ የህወሃት ቁንጮ ደጋፊዎች አካሄድ ለመከላከል ወይንም ለማምከን  በሚያደርጉት ጥረት፣ ሰላማዊው የትግራይ ህዝብ ላይ በጦርነቱ ምክንያት እየደረሰ ያለውን ሞት፣ ስደትና ከቀዬ መፈናቀል፣ የዘነጋ በሚመስል መልኩ ፣መንግስት ላይ ችግሩን አስመልክቶ እንዲታደጋቸው ማድረግ ያለባቸውን አስፈላጊ ግፊት በበቂ ደረጃ እያደረጉት ያለ አይመስለኝም።

ግጭቱ በተጀመረ  በመጀመሪያው ወራት፣ መንግስት የህወሃት አመራር ካድሬዎችና ደጋፊ ፈረንጆች፣ በነሱም ፕሮፓጋንዳ የተወናበዱ ጋዜጠኞች በየእለቱ የሚያሰራጩት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እምብዛም ያሳሰበው እይመስልም ነበር። 

  ሆኖም አሜሪካና የአውሮፓ ሀገሮች በመጀመሪያ ላይ የነበራቸውን አቋም ለውጠው ጫና ማድረግ በመጀመራቸው ግራ በመጋባት ወደ መከላከል የገባና፣ ከዋናውና ከመደበኛ ተግባሩ በተወሰነ ደረጃ የተዘናጋ ይመስላል። 

ካድሬዎቹና የረጅም ጊዜ ደጋፊ የነበሩት ፈረንጆች ለምን በዚህ ተግባር ተሰማሩ የሚለው ግልጽ ቢሆንም፣ የአውሮፓ ህብረትና የአሜሪካ የአቋም ለውጥ ለምን ተከሰተ ለሚለው በርካታ መላ ምቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛ፡ አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር፣ ኢትዮጵያ አንዱን ወሳኝ የፖለቲካ ችግር መፍታትና ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃል የሚፈጠረው ወዳጅነት አካባቢው ላይ ሊኖር የሚችለው ተጽዕኖ፣ ሁለተኛ፡ ከዚህ ተያይዞ ኢትዮጵያ በቻይና አፍሪካ ፖሊሲ ላይ ሁነኛ ስፍራ ስላላት የቻይና በአካባቢው ሊኖረው የሚችለውን ተጽዕኖ ለመግታት፡ ሶስተኛ…  ወዘተ እያሉ መዘርዘር ይቻላል።

ዋናው ቁም ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት ተጠሪነቱም ሆነ ሃላፊነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑና፣ ሃያላኑን ለማሳመን የሚደረገውም ጥረት አውቆ የተኛን… ነገር ስለሆነ ትኩረቱን አፍጥጦ ያለው ችግርን መቅረፍ ላይ መሆን ይኖርበታል።

ይሄን በማድረግም ነው ህዝብን መታደግ የሚቻለውና የሐሰት ፕሮፓጋንዳን ማምከን የሚቻለው።

በኔ ግምት መንግስት ከዚህ በታች ባሉ አምስት አንኳር ጉዳዮች ዙሪያ ካተኮረና አመርቂ እርምጃዎችንም  ከወሰደ ክልሉን ወደ ተረጋጋና መልሶ ግንባታ ማሻገር ይቻላል የሚል እምነት አለኝ

በዝቅተኛ እርከን ስላሉ አስተዳደራዊ መዋቅሮች

መንግስት በተደጋጋሚ እንደገለጸው ለተፈጸመው ሃገራዊ ክህደት ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን ቁንጮ አመራሮች ስምና ፎተግራፍ አውጥቶ ፍለጋ ላይ እንዳለና፣ በርካቶውችንም በቁጥጥር ማዋሉን አስታውቋል።

ሆኖም ይሄ ውንጀላና ፍረጃ ብዙሃኑን የድርጅቱ አባላት እንደማይመለከትም ጭምር በየጊዜው በመናገሩ፣ በቀጥታ በክህደት ወንጀል ተባባሪነት ከሚጠየቁት ውጭ፣ ከቀበሌ እስከ ወረዳና ከዚያም በላይ የነበሩ የክልሉ አመራሮች፣ በክልሉ ሰላምን ለማስፈንና በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት መደረግ ባለበት ሂደት፣ የመፍትሄው አካል አድርጎ መውሰድና ማሰራት ይኖርበታል።

ይሄን አለማድረግ፣ ከሰላሳ አመታት በላይ ተገንብቶ የነበረውን የክልሉን አስተዳደራዊ መዋቅር ከዜሮ እንደመጀመር ስለሚሆንና ነገሮችን የበለጠ ስለሚያወሳስብ ፣ በየእርከኑ ያሉ አመራሮችንም፣ሳይወዱ በግድ ወደ ተቃውሞና ችግር ፈጠራ ስለሚገፉ፣ በክልሉ መስፈን ያለበትን ሰላምና መልሶ ግንባታውን በእጅጉ ሊያጓትት ስለሚችል በቅጡ ሊታሰብበት ይገባል። መለወጥም እንኳ ካስፈለገ ከህዝብ ጋር እየመከሩ በሂደት ሊከናወን የሚቻል በመሆኑ አስፈላጊ ጥንቃቄ ያሻዋል።

ሰላም ማስፈንና መልሶ ግንባታ በሚመለከት

በውጭ ያለው አሉታዊ ፕሮፓጋንዳ እንደተጠበቀ ሆኖ ፣አሁን ላይ ሆነን መጠየቅ ያለብን ዋነኛ ጉዳይ መንግስት በጦርነቱ አማካይነት የተመሳቀለውን የብዙሃን ዜጎቹን ህይወት ለማስተካከል ምን እርምጃ እየወሰደ ነው? ባቅሙ በቂ የገንዘብ የሰው ሃይልና ቁሳቁስ እያቀረበ ይገኛል ወይ? የወደሙ የትምህርትና የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ምን ጥረት እያደረገ ነው?… ወዘተ አቅሙ ውሱን ከሆነስ ከተባበሩት መንግሥታት ሌሎች ሀገሮችና የእርዳታ ድርጅቶች ስለህዝቡ ተቆርቋሪነት በሚያወሩት መጠን የእርዳታ እጃቸውን እንዲዘረጉ ወትውቷል ወይ? ካላደረጉስ እንዲያደርጉ ምን አይነት ግፊት እየተደረገ ነው ወይንም ለማድረግ ታስቧል? ወዘተ በዋነኛነት መጠየቅ ያለባቸውና በውጭ የሚደረገውን ፕሮፓጋንዳ ለማምከን ከመሞከር በላይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ይመስሉኛል። 

 

በእህቶቻችን ላይ ስለደረሰው ልዩ ጥቃት 

 

በክልሉ ባሉ እህቶቻችን ላይ ተደረገ የተባለውን የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የፌደራል መንግስቱ የሴቶች ምኒስቴር መከሰቱን ያረጋገጡት ሀቅ በመሆኑ፣ መንግስት አጣዳፊና ጠንካራ ክትትል አድርጎ ወንጀለኞችን በመያዝና ለፍርድ በማቅረብ አስተማሪ የሆን ቅጣት እንዲያገኙ ሊያደርግ ይገባል።

ለዚህ የከፋ ወንጀል ለተጋለጡት እህቶቻችንም አስፈላጊውን ህክምናና ወደ መደበኛ ኑሮአቸው ተመልሰው እንዲኖሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ከመንግስት ይጠበቃል። እነዚህና መስል ድርጊቶች ናቸው ለዘላቂ ሰላምና መልሶ ግንባታ እገዛ ሊያደርጉ የሚችሉት።

በትግራይ ክልል ስላሉ የኤርትራ ወታደሮች

በበርካታ መንግሥታት እንዲሁም ዜና አውታሮች እምነት (አንዳንድ የመንግስት ሹሞችም እየተሽኮረሙም ቢሆን ያመኑት!) የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ውስጥ መኖርና በጦርነቱ መካፈልን በሚመለከት ለምንና፣ እንዴት የሚለውን መንግስት በግዴታ በግልጽነት ለኢትዮጵያ ህዝብ መመለስ ያለበት ጉዳይ ነው። 

በአሁኑ ሰዓት ግን አጣዳፊው ጉዳይ፣ ጦርነቱ በመሰረቱ ተጠናቋል ከተባለ ከሶስት ወር በዃላ በትግራይ ክልል ውስጥ መገኘታቸው ተቀባይነት የሌለው በመሆኑና፣ በክልሉ ነዋሪ ህዝብም ላይ ትልቅ ቅሬታን ያሳደረ ጉዳይ እንደመሆኑ ሙሉ በሙሉ ወጥተው ወደ ድንበራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በክልል ውስጥ በነበሩበት ወቅት የፈጸሙት ህገወጥ ግድያ ወንጀልና ዘረፋ ካለም ተጣርቶ የሚመለከታቸው ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያስፈልጋል። 

ሰላማዊ ሰዎች ላይ  ህገወጥና ጅምላ ግድያን በሚመለከት 

በተለያየ ጊዜ ሰላማዊ ዜጎች በጅምላ እንደተገደሉ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች የተገለጸ ጉዳይ ነው። በማይካድራ የተገደሉትን ንጹሃን ዜጎች አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሺን አምነስቲን ኢንተርናሽናልና ፣ሂውማን ራይትስ ዋች ጥናት አካሂደው ዝርዝር መግለጫ ያወጡበት ጉዳይ ነው። መንግስትም ክትትል አድርጎ በድርጊቱ የጠረጠራቸውን ሰዎች ለፍርድ ማቅረቡ ይታወቃል

ትግራይ ውስጥ አንዳንድ ስፍራዎችና በተለይ በአክሱም ሰላማዊ ህዝብ ላይ የጅምላ ግድያዎች ተካሂደዋል የሚሉ ክሶች በዓለም መገናኛ ብዙሃንና በአምነስቲ ኢንተርናሽናልም ጭምር  ሲቀርቡ ከርመዋል። መንግስት የማይካድራውን የጅምላ ግድያ በራሱና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት፣ በሂውማን ራይትስ ዋችና በአምነስቲ እንዲመረመሩ እንዳመቻቸ ሁሉ፣ እነዚህ የተባሉ ስፍራዎችም በነዚህም ሆነ ሌላ ተጨማሪ አካላት አካቶ  ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ ይኖርበታል።

ከዚህ አንጻር በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በጋራ ትግራይ ውስጥ ተካሄደ ስለተባሉት ግድያዎች ለማጣራት መስማማታቸው ትልቅ ጅምር ነው።

የምርመራውም ውጤት ምንም ሆነ ምንም የማስታወቅ ሃላፊነት የመንግስት ሲሆን፣ ዕውን ሆነው በተገኙ ወቅት ደግሞ ከባድ ወንጀል ነውና ማንም ያድርገው ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል። ይሄን ማድረግም መንግሥት ህግ የማስከበሩን ሥራ በቅጡ እየሰራ ለመሆኑ በቂ ማስረጃ ስለሚሆንም የህዝብን ይሁንታ የሚያገኝበት ተግባርም ነው።

በኔ እምነት እነኚህ ከላይ የዘረዘርኳቸው አምስት ነጥቦች ላይ መንግስት ካተኮረ የትግራይ ክልል ላይ የሚገኘውን ችግር በቶሎ ቀርፎ ሕዝቡን አስተባብሮ ወደ ሰላማዊ ኑሮና ወደ ልማት መሄድ ይችላል።

ከዚያም አልፎ፡ በአሁን ወቅት በየአካባቢው አልፈው አልፈው የሚፈነዱን ግጭቶችንና ችግሮችንም በተመሳሳይ መንገድና አካሄድ ሊፈታ ቢሰማራ ህግን የማስከበር ግዴታውን የሚወጣበትና የህዝብን አመኔታ የሚያገኝበትን በር ይከፍትለታል  የሚል እምነት አለኝ።

Filed in: Amharic