>

የመስከረም  ላውንቸርና ሚሳይል...!!!  (ከብርሃነ መዋ)

የመስከረም  ላውንቸርና ሚሳይል…!!!

 ከብርሃነ መዋ 

መስከረም አበራ የምትጽፋቸው ጽሁፎች ሁሉ እንደ ሚሳይል ይዘታችው በሃይል የታመቀ ነው። በመሆኑም ያነጣጠሩት ኢላማ ላይ ሲፈነዱ እቧራ ያስነሳሉ። ጽሁፎችዋ በቋንቋ ችሎታዋ የተከሽኑ ብቻ ሳይሆን ቁም ነገርና የሚያስቆጥሩት ነጥብ አላችው። በፓርቲ ፖለቲካ ባለመጠለፏ አገርን ማእከል ያደረገ ሚዛናዊ ሃሳብ ለመሰንዝር ነጻነት እግኝታለች ብየ አምናለሁ። ለማንም ይሁን ለማን ለተጠቃ ወገን ሽንጧን ገትራ ድምጿን ጮክ አርጋ ትሟገታለች፣ ትተቻለች፣  የመፍትሄ ሃሳብም  ትሰነዝራለች፣ ሃሳቡን ስታምንበት ሃሳብ አቅራቢውን ትደግፋለች የደገፈችው ሲሳሳት ደግሞ ለመተችት የሚያስችል አቅም አላት። በይሉኝታ አትታፈንም።
ሰሞኑን የተኮሰችው ሚሳይል ግን በይዘቱ ለየት ያለ ነው። ሚሳይሉን ለመተኮስ የተጥቀመችበት ላውንችር  “የዘውግ ፖለቲካ ስረመስረቶች” ብላ በሰየመችው  መጽሃፍ ነው። መጽሃፉ የመምህርነት የሞያ ብቃቷን ያሳየችበት ነው። እንካስላንቲያ የሌለበት ምሁራዊ አቀራረብና ትምህርታዊ ይዘት ያለው ነው። መጽሃፉ ለህትምት ከመላኩ በፊት የማንበብ እድሉ አጋጥሞኝ ነበር። ለበዙ ሰዎች የዘውግን ፖለቲካ ስንተችም ይሁን ስንደግፍ በአብዛኛው በስሜትና ከተሞክሮ በመነሳት ሊሆን ይችላል። ግንዛቤን ለማዳበርና ሳይንሳዊ አረዳድ እንዲኖረን የሚያስችለን እውቀት በዚህ በመስከረም መጽሃፍ ውስጥ ታጭቋል።
ረዘም ያለ ጊዜ ወስዳ በርካታ መጽሃፍትን አጣቅሳና ጨምቃ ያቀረበችው በመሆኑ በዘውግ፣ በብሄር፣ በጎሳ፣ በዘር ላይ ያለንን ግንዛቤ ግልጽና የተሟላ ሆኖ እንድናገኝው በሚያስችል መልኩ የቀረበ መሆኑን ተገንዝቢያለሁ። በማንኛውም የድሜ ክልልና የስራመስክ ለተሰማራ ዜጋ ጠቃሚ መጽሃፍ ነው። አሁን አገራችን ባለው የፖለቲካ ውይይት በእውቀት ላይ የተመሰረተ የሃሳብ መለዋወጥ አቅም ይፈጥርልናል። የምናውቅና የሚመስሉንን ጉዳዮች ያረጋግጥልናል፣ የአረዳድ ክፍትቶች ካሉ ያሟላልናል።
ያሁኑ የመስክረም አበራ “የዘውግ ፖለቲካ ስረ መሰረቶች” የተሰኝው ላውንችር የሚተኩሰው ሚሳይል፣ ትችትንና ምስጋናን፣ብሶትንና  ወቀሳን፣ ምሬትና ሮሮን፣ ሳይሆን እውቀትና እውቀትን ብቻ ሊያፈነዳ የቀረበ ነው።
ዝምብሎ መጽሃፍ ተብሎ የሚታልፍ ሳይሆን የመማሪያ መጽሃፍ ተብሎ በወጣቱ በፖለቲከኛው ያሁኑ ያግሬ ጉዳይ ያስጨንቀኛል የሚል ሁሉ ዋጋ ሊሰጥው ይገባል ብየ ከልቤ አምናለሁ።
መስከረም ጣቶችሽ ይባረኩ።
Filed in: Amharic