>

ስለ ተጋሩ እጮሃለሁ...!!! (በፍቃዱ ኃይሉ)

ስለ ተጋሩ እጮሃለሁ…!!!

በፍቃዱ ኃይሉ

“ሀገር ማለት ሰው ነው”፣ ያሉህን ተቀበል
ሰው በሞተ ቁጥር፣ “ሀገሬ ሞተች” በል!
(በላይ በቀለ ወያ)
የትግራዩ ጦርነት ከተጀመረ አራት ወራት ከግማሽ አለፈው። ስለ ቅድመ ጦርነቱ ሁኔታ፣ ስለጦርነቱ ጀማሪ፣ ስለ ድኅረ ጦርነቱ ቀውስ ተጠያቂ ማንነት ብዙ አካራካሪ መረጃዎች ተነግረዋል፣ እየተነገሩም ነው። ጦርነቱ በተካሔደበት ሜዳ፣ ትግራይ ክልል ውስጥ የፍዳው ገፈት ቀማሽ ስለሆኑት ብዙኃን እና በምኑም የሌሉበት የትግራይ ተወላጆች (ብዙኃን ተጋሩ) ግን በበቂ ሁኔታ አልተነገረም። የድረሱላቸው ጩኸት በበቂ አልተጮኸም።
ኢትዮጵያውያን በታሪካችን ደግመን ደጋግመን ከምንሠራቸው ስህተቶች ውስጥ ለገዢዎች ጥቅም መስዋዕት ይሆን ዘንድ እንደ ሕዝብ የሚያስተሳስሩንን ድልድዮች ሰብረን አጥር ካቆምን በኋላ መልሰን መፀፀታችን አንዱና ዋነኛው ነው። ዛሬም በሥልጣን ድልድል እና ርስት ጉዳዮች የብዕር ሥም የተሸፈነው የገዢዎች ጭካኔ የተሞላበት ሽኩቻ የዜጎቻችንን እልቂት፣ መታረዝና መዋረድ አስከትሏል። ይህ ግፍና መከራ ከዓመት ዓመት አፈር ለሚገፉ ገበሬዎቻችን ምንም ሳያተርፍ ማለፉ አይቀርም። ከዘመናት በኋላ መለስ ብለን ስንመለከተው “ለዚህ ነው ከወገኖቼ የተቆራረጥኩት” ብለን ለምንፀፀትበት የዝሆኖች ፀብ ሰበብ አስባብ ከመታለላችን በፊት ስለሳሩም አሳር እንናገርለት።
ዘገባዎቹ ምን ይላሉ?
ላለፉት ዓመታት በየዓመቱ የሚደረገው የጉዞ አደዋ ዘንድሮ ከተጀመረ በኋላ ተቋርጧል። ከጉዞው አዘጋጆች መካከል ያሬድ ሹመቴ መንገዱ የደኅንነት ሥጋት ስላለበት ይቅርባችሁ ተብለን ነው ያቋረጥነው ብሎ ለሚዲያ ተናግሯል። ምናልባትም ጥበቃ ሊያገኙ የሚችሉ እነዚህ ከተሜዎች መንገዱ አደጋ ነው ተብለው ከመጓዝ የቀሩበት አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች አሉ። ዛሬ በትግራይ ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ ማደር፣ ምርትን መሰብሰብ ብርቅ ሆኗል። ትግራይ ከመላው ኢትዮጵያ እና ዓለም ግንኙነቷ ተገደቧል። እኛ የተጋሩን ብሶት አንሰማም፤ ተጋሩ የእኛን ጩኸት አይሰሙም። የንፁኃን ጭፍጨፋ፣ ፆታ ተኮር ጥቃቶች፣ መታረዝና መሰደድ ብዙኃን ተጋሩ የቀመሱት ፍዳ ነው። ከዚህም አልፎ ግን በበደል ላይ በደል የሚሆነው የደረሰባቸውን መከራ የሚክደውም ቁጥሩ ያን ያህል መሆኑ ነው።
አንዲት እናት የወለደችው ልጅ ወንጀል ሠርቶ ቢገኝ የእናትነት ፍቅሯን ለልጇ እንድትነፍግ መጠበቅ ፍትሐዊ አይደለም። ልጇ ለፍርድ መቅረብ አለበት፤ እናት ግን በልጇ ወንጀል ለስቃይ የምትዳረግበት ምንም ዕዳ የለባትም፤ ይህንንም አይቶ ዝም ማለት ከወዳጅ አይጠበቅም። ሕወሓት እና የትግራይ ሕዝብ የመሐል አገር ሰው በቀላሉ የማይረዳው ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል። ብዙኃን የትግራይ ቤተሰቦች በሕወሓት ትግል ወቅት የቤተሰብ አባል ገብረዋል። ሕወሓት በሥልጣን ሽኩቻው የአጥፍቶ ጠፊ መጥፎ ስሌት ሠርቷል። የትግራይ ሕዝብ ለዚህ የሕወሓት ጥፋት መክፈል የለበትም። አሁን እየሆነ ያለው ግን ይኸው ነው።
ይህንን ጽሑፍ ያዘጋጀሁት በኔ ሚዛን ተዓማኒ ናቸው ብዬ ከማስባቸው የብዙኃን መገናኛ እና የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ዘገባዎች ላይ በመመሥረት ነው። በጽሑፉ በጦርነቱ ወቅት ሕወሓትና የሕወሓት ወገንተኛ የሆኑ አካላት ያደረሱትን ጉዳትና ጭፍጨፋ አልዳሰስኩም፤ ብዙኃን ተጋሩ ላይ የደረሱ ጥቃቶችን ስዘረዝር ሕወሓት በመከላከያው እና ሌሎችም ንፁኃን ላይ ያደረሰውን ጉዳት ከመካድም፣ ከመዘንጋትም ተነስቼ እንዳልሆነ አንባብያንን ማሳሰብ እወዳለሁ። መነሻዬ በፖለቲከኞች ጥፋት ሰለባ ስለሆኑ ንፁኃን ተጋሩ ድምፅ የመሆን ፍላጎት ነው።
፩) የንፁኃን ጭፍጨፋ
የጦርነት ፍትሐዊ የለውም ይባላል። ነገር ግን ጦርነትም ሕግ አለው። ጦርነቱ ውስጥ በቀጥታ የማይሳተፉ ሲቪሎች በሙሉ የመጠበቅ መብት አላቸው። ንፁኃንን ያጠቁ ተዋጊዎች ሁሉ የእከሌ የእከሌ ሳይባሉ በጦር ወንጀል መጠየቅ አለባቸው። በትግራይ ጦርነት የተፈፀሙ የንፁኃን ጭፍጨፋዎች ሁሉ በመረጃ እጥረት እና ክልሉ ገና ለሁሉም ሰው ተደራሽ ባለመሆኑ ይፋ አልሆኑም ነገር ግን ይህን ሁሉ መሰናከል አልፈው የወጡ ብዙ የጭፍጨፋ መረጃዎች አሉ። የአክሱሙ የንፁኃን ጭፍጨፋ አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የምር ሊወሰድ ይገባል” ያሉት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የ25 ገጽ ሪፖርት ላይ 41 የዓይን ምሥክሮችን እና ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎችን፣ እንዲሁም 20 በጉዳዩ ላይ ዕውቀት ያላቸውን የተለያዩ ሰዎችን በማነጋገር አክሱም ውስጥ የንፁኃን ጭፍጨፋ ተፈፅሟል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።
አምነስቲ የንፁኃን ጭፍጨፋው የተፈፀመው ሕዳር 19 እና 20 ቀን በኤርትራውያን ወታደሮች ለበቀል ነበር ብሏል፤ ከዚያ አስቀድሞ በከተማው ያሉ ጥቂት የትግራይ ሚሊሺያ አባላትና ዱላ እና ድንጋይ የያዙ የከተማው ወጣቶች ጥቃት ለመሰንዘር ሞክረው ነበር። ለዚህ በቀል የተነሳሱት የኤርትራ ወታደሮች በመንገድ ላይ ያገኟቸውን ወጣቶች በዘፈቀደ ተኩሰው ገድለዋል፣ ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ ወንዶችን ለይተው በዘፈቀደ ረሽነዋል። በዚህ ጭፍጨፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን እንደተገደሉ ሂዩማን ራይትስ ዎችም ከአምነስቲ ተከትሎ ባወጣውና በአጫጭር ቪዲዮዎች በታጀበረው ሪፖርቱ ተናግሯል።
በአክሱሙ ጭፍጨፋ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች በስፋት መሳተፋቸውን የአምነስቲም የሂዩማን ራይትስ ዎችም ምስክሮች የወታደሮቹን መለዮ፣ የቋንቋ ለዛቸውን፣ የመኪናቸውን ታርጋ፣ እና ፕላስቲክ ሰንደል ጫማዎቻቸውን በማጣቀስ ተናግረዋል። አንድ የዓይን ምስክር ለሂዩማን ራይትስ ዎች የኤርትራ ወታደሮች ያደረጉትን የኢትዮጵያዊዎቹ ባለማስቆማቸው የተሰማውን ሲገልጽ ባጭሩ “ያማል” ነበር ያለው። የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የሻዕቢያና የሕወሓት ጦርነት ነው ይባላል። የኤርትራ ወታደሮች በበቀል ስሜት ብዙ ጉዳት ማድረሳቸውም ከዚህ የመነጨ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ሰለባዎቹ ንፁኃን ናቸው።
ኢሰመኮም የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ባወጣው የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ሪፖርት ላይ በእረኝነት ላይ የነበረ የ12 ዓመት ሕፃን ሳይቀር በፍንዳታ እግሩን አጥቷል። ኢሰመኮ በሆስፒታሎች ጉብኝቱ የ3፣ የ5 እና የ7 ዓመት ሕፃናት ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክቷል። ሌላው ቀርቶ አቦይ ስብሓት ነጋ በመያዛቸው የደስታ ጥይት ሲተኩሱ የነበሩ ወታደሮች ተባራሪ ጥይት መቀሌ ከተማ ላይ የ4 ዓመት ሕፃን ገሏል። እነዚህ ሪፖርቶች ከተሠሩባቸው ጥቂት ቦታዎች የተገኙ ታሪኮች ናቸው፤ የጉዳቱ መጠን ከዚህም የሰፋ ሊሆን ይችላል።
እስካሁን የተቀጠፉ ንፁኃንን ነፍስ መታደግ አንችልም፤ ነገር ግን ይህ ታሪክ እንዳይደገም ስለፍትሕ ብለን መጮህ እንችላለን።
፪) ፆታ ተኮር ጥቃቶች
ሰሞኑን አንዲት ወዳጄ አንድ ቪዲዮ ላከችልኝና ተመለከትኩት። በእውነቱ ቪዲዮውን ካየሁት በኋላ ለሰዓታት ያክል ከአእምሮዬ ማውጣት ተስኖኝ ከባድ ውስጣዊ ስቃይ ሲሰማኝ ነው የቆየሁት። የሰው ልጆች ምን ያህል አውሬያዊ ፀባይ ሊያንፀባርቁ እንደሚችሉም ነው የተረዳሁት። ቪዲዮው የተቀረፀው ትግራይ አንዱ ሆስፒታል ውስጥ ነው። ከሴትየዋ ብልት ውስጥ ሐኪሞቹ ሁለት ፍሬ ሚስማሮችና የተጠቀለለ ላስቲክ ሲያወጡ ይታያል። ተግባሩ በልቦለድ ፊልም ላይ እንኳን ብንመለከተው ሰብአዊ የሆነ ሰው እንዲህ ዓይነት ነገር አይፈፅምም ብለን የምናልፈው ይሆን ነበር።
ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ በሁለት ወራት ብቻ መቀሌ ውስጥ 52፣ አዲግራት ውስጥ 22፣ ውቅሮ ውስጥ 7 እና አይደር 27 ሴቶች በድምሩ 108 ሴቶች መደፈራቸውን ከጤና ተቋማትና የክልሉ የጤና ቢሮ ማረጋገጥ መቻሉን ዘግቧል። ይሄ እንግዲህ በነዚህ ከተሞች ብቻ፣ ሆስፒታል የሔዱ ሴት ተጠቂዎች ቁጥር ነው፤ በደላቸውን አፍነውና ውጠው የተቀመጡትን ቤታቸው ይቁጠራቸው።
ጉዳዩ ግን የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ሳይቀሩ ያመኑት ነበር። አንድ የሠራዊቱ አባል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተላለፈ ለሠራዊቱ አባላት ባደረጉት አንድ ንግግራቸው “እንዴት በመቀሌ ክፍለ ከተማ ሴት ይደፈራል?” ሲሉ ይጠይቃሉ። “በውጊያ ጊዜ ቢሆን ምንም ማኔጄብል አይደለም ኤክስፔክትድም ነው።… ፖሊስ በተመለሰ፣ ፌዴራል ፖሊስ ባለበት፣ ይህ ሁሉ የሰው ኃይል ባለበት ማታ ሪፖርት ተደረገ፤ በሁለተኛው ቀን ደግሞ ተደገመ” በማለት ጉዳዩ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሯል በተባለበት ጊዜ እንኳን ከቁጥጥር ውጭ መውጣቱን ተናግረዋል። ያውም መቀሌ ከተማ ውጊያው ያልበረታባት ከተማ ነበረች። ውጊያው በበረታባቸው ከተማዎች ደግሞ ችግሩ የተባባሰ እንደሚሆን መገመት አይቸግርም።
በየካቲት ወር፣ ኧርባን ሴንተር የተባለ አዳራሽ ውስጥ በተዘጋጀ አንድ ሴሚናር ላይ ምክሆን አፈወርቅ የተባሉ ተመራማሪ በግጭቶች ወቅት ሴቶችና ሕፃናት ድርብ የጥቃት ተጋላጮች መሆናቸው በመረጃ አስደግፈው አስረድተዋል። በሴሚናሩ ላይ ሴታዊት የተሰኘችው የግብረሰናይ ድርጅት ከሚዲያዎች አሰባስባ ባቀረበችው መረጃ ላይ ትግራይ በጦርነቱ ምክንያት ተዘግታ በሰነበተችበት ጊዜ ወታደሮች የተለያዩ ቁሳቁሶችን በወሲብ እንደመነዘሩ፣ በወታደሮች ተገደው በቤተሰባቸው አባል መደፈር የተፈፀመባቸው ሴቶች እንደነበሩና ከምገልሽ ወይም ከምደፍርሽ ምረጪ የተባሉ ሴቶች እንዳሉ ምንጯን ጠቅሳ ሴታዊት ለታዳሚዎች አቅርባለች።
እነዚህን አሰቃቂ ታሪኮች ሰምተን ዝም ልንል አይገባም፤ አሁንም ስለፍትሕ መጮህ አለብን።
፫) መታረዝ፣ ስደትና መፈናቀል
ወትሮም በድርቅ፣ እንዲሁም በወቅታዊው የአንበጣ ወረርሽኝ ለርሃብ ተጋላጭ የሆኑ የትግራይ ገበሬዎች የቀረውን መኸራቸውን በጦርነቱ ምክንያት መሰብሰብ አልቻሉም ነበር። አልፎ ተርፎም ማሳቸው የወደመባቸው ገበሬዎች አሉ። የወር ደሞዝተኞች ሥራቸው ተቋርጧል፣ ባንኮችና ንግድ ቤቶች ተዘግተዋል። በጦርነቱ ወቅት በርካታ የንብረት ዘረፋዎች እንደተከሰቱ በርካታ መረጃዎች ያሳያሉ። የትራንስፖርት አገልግሎት የለም። በነዚህ ሁኔታዎች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 4.5. ሚሊዮን መድረሱን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርን ጨምሮ የዓለም ዐቀፍ ተቋማትም ጭምር አሳውቀዋል።
ሂዩማኒቴሪያን ሪስፖንስ የሚያሳትመው ዓመታዊው ሪፖርት በየካቲት ወር መጨረሻ ይፋ ሆኖ ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ከሚያስፈልጋቸው 4.5 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 3.5 ሚሊዮኖቹ ጋር በአለመረጋጋቱ ሳቢያ ወይ በከፊል አልያም ሙሉ ለሙሉ መድረስ አስቸጋሪ ነው።
ጉድ ኔበርስ ኢትዮጵያ ባሰናዳው ጥናት ላይ ደግሞ በትግራይ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ 500 ሺሕ ሰዎች ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶችና በቤተ እምነቶች ተጠልለው ይገኛሉ። እነዚህ ሁሉ ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ምግብና መጠጥን ጨምሮ መሠረታዊ የጤና ጥበቃ አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶቹ ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ ቤት ንብረታቸው ወድሟል አልያም ተዘርፏል። ከነዚህ ውጪ ወደ ሱዳን በመሰደድ የተጠለሉ 61 ሺሕ ገደማ ሰዎች አሉ።
እነዚህ ወገኖቻችን በረሃብና መታረዝ እንዳያልቁ፣ ወደ ቀያቸው በሙሉ የደኅንነት ዋስትና እንዲመለሱ መቀነቴ አደናቀፈኝ ሳይሉ መጮህ ያስፈልጋል። የሰብአዊ ዕርዳታ ሠራተኞች ጥበቃም እገዛም ተደርጎላቸው ለመድረስ የሚቸግሩ ቦታዎች ላይ ሁሉ እንዲደርሱና ተጨማሪ ነፍሶችን ከመቀጠፍ እንዲታደጉ በጩኸታችን ጫና ማድረግ የሞራል ግዴታ አለብን።
፬) ጥቃትን መካድ
ጥንታዊው ግሪካዊው የትራጄዲ ደራሲ ኤሺለስ “በጦርነት፣ ቀዳሚዋ ሟች እውነት ናት” ብሎ ጽፎ ነበር። እውነትም ነው ተጠቂዎችን ወግኖ ለመቆም እንኳን እስኪቸግር ድረስ የተዛቡ መረጃዎች ምኅዳሩን ሞልተውታል። ከወዲያ ወዲህ የሚያወናብዱ እና የሚያደናግሩ መረጃዎች አሉ። ለዚህም ነው ለሰብአዊ ጉዳዮች የአጥቂው ማንነት ላይ ክርክሮች ኖሩም አልኖሩ ተጠቂዎቹን ድጋፍ አለመንፈግ የሚኖርብን።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የአማራ እና የወልቃይት ተወላጆች የተጠቁበትን የማይካድራውን ጭፍጨፋ ከኢሰመኮ አስቀድሞ የዘገበ ወገንተኝነቱን ለሰብኣዊ መብቶች ብቻ ያደረገ ድርጅት ነው። የአምነስቲ ተማራማሪዎች ሰው እንደመሆናቸው ስህተት ሊሠሩባቸው የሚችሉበት ዕድል ያለ ቢሆንም ቅሉ የአክሱም ጭፍጨፋን ሪፖርት ሲያወጡ ግን ብዙ ያልተገቡ ትችቶች ተሰንዝረውባቸዋል። ትችቶቹ ጥቃቶቹን ከመካድ የሚመነጩ ናቸው። የኤርትራው የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ሪፖርቱን “የለየለት ውሸት” ብለውታል።
መንግሥታዊው የኢትዮጵያን ሔራልድ እንግሊዝኛ ዕለታዊ ጋዜጣ የካቲት 30፣ 2013 እትሙ የፊት ገጽ ላይ “የአክሱም ጭፍጨፋ አልተከሰተም፣ በማስረጃም አልተደገፈም” በማለት ዩኤስኤይድ የተባለ የአሜሪካ ግብረሰናይ ድርጅትን ዋቢ አድርጎ ያሰራጨው ዘገባ በዩኤስኤይድ በራሱ የሐሰተኛ እንደሆነ ተነግሯል። ነገር ግን እነዚህን የሐሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎች እውነት መስሏቸው ያስተጋቡ ብዙዎች ናቸው። እንዲህ ያሉ ጭካኔ የተሞላባቸው ነገሮችን የሚፈፅሙ አካላት ባሉበት ሁኔታ፣ የተፈፀመውን የሚክዱ ሰዎች ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ይሆናል።
አልጄዚራ ቴሌቪዥን ትግራይ መግባት በተፈቀደለት ባጭር ጊዜ ውስጥ ሽፋን የሰጠው ዜና ሞናሊዛ አብርሃ የተባለች ወጣት ተጠቂን ታሪክ በመተረክ ይጀምራል። ሞናሊዛ ሊደፍሯት ሙከራ ካደረጉ የኤርትራ ወታዶሮች ልታመልጥ ስትሞክር በጥይት እንደተመታች ትናገራለች። በጥይት የተመታው እጇና እግሯ በሐኪሞች እንዲቆረጡ ተወስኖ ተቆርጠዋል። ይህ ልብ የሚሰብር ዜና በወጣ በማግስቱ የማኅበራዊ ሚዲያ ሰዎች ሞናሊዛ እንዳለችው ሲቪል ሳትሆን የልዩ ኃይል አባል እንደሆነች ተናግረው የአንዲት ታጣቂ ፎቶ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያዘዋውሩ ዋሉ። ሆኖም ኢትዮጵያ ቼክ የተሰኘው ሐቅ አረጋጋጭ እውነቱን አጣርቶ ፎቶዋ የሚዘዋወረው ታጣቂ ለምለም የምትባል ሌላ ሴት እንደሆነች አሳይቷል። ሞናሊዛ የደረሰባት ጥቃት ሳያንስ ዋሽታለች ተብሎ ክህደት ደርሶባታል። የሚያሳዝነው ያንን የሐሰተኛ ምስል ሲያዘዋውሩ ከነበሩ ሰዎች መካከል የኢትዮጵያ ቼክን የተጣራ መረጃ ጠቅሶ “ያልኩትን አረጋገጠልኝ” ብሎ ውሸቱን በውሸት ለመደገፍ የሞከረ ሰው አይቻለሁ።
የሞናሊዛ አብርሃ ታሪክ ግልጽ ማሳያ ሆኖ አነሳሁት እንጂ እስካሁንም በቅጡ ያልተጠናቀቀ ጦርነት ባለበት ክልል ውስጥ ደረሱ የሚባሉ ቀውሶችን ሁሉ መካድ ያለፉት አራት ወራት የፖለቲካ ተዋስዖዋችን አካል ነበር። ክህደቱን የሚፈፅሙት የመንግሥት ሰዎች እና ወዳጆቻቸው ብቻ አለመሆናቸው ደግሞ ነገሩን የበለጠ ውስብስብ ያደርገዋል። የሕወሓት ታሪክ እና ተግባር ቁጣ የቀሰቀሰባቸው ሰዎች በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ከክልሉ ሾልከው የሚወጡ ለጆሮ የሚከብዱ ስቃይና መከራዎችን በማስተባበል ላይ ተመሥርተዋል። የሕወሓት ደጋፊዎች የሐሰተኛ መረጃዎችን ያሰራጩባቸው ጊዜያት አሉ፤ ሆኖም ያለምንም ማስረጃ ደረሱ የተባሉ ጉዳቶችን ሁሉ መካድ አልፎ ተርፎም ያፈጠጡ እውነቶችን መደፍጠጥ ዜጎች ለዜጎች ሊያኖሩ የሚገባቸው ታሪክ አይደለም።
በትዊተር የመንግሥት ደጋፊዎች ያስተባበሩት እና “መንስዔው ሕወሓት ነው” በሚል መሪ ቃል በየካቲት ወር የተካሔደው ዘመቻ የዓለም ዐቀፉን ማኅበረሰብ ቀልብ ለመግዛት የተደረገ ማስተባበያ ዘመቻ ነበር። ዘመቻው ከቀድሞው “ንፁኃን ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም” ከሚለው ድፍን ያለ ክህደት ለደረሰው ጉዳት መነሻው ሕወሓት ነው ወደ ማለት ያደላ ነበር። ይህ በራሱ ንፁኃን ተጎጂ መሆናቸውን ፍንጭ ይሰጣል።
በርካታ ሴቶች ተደፍረዋል ሲባል፣ ‘በትግራይ ቀድሞም እንዲህ ዓይነት ሴት የመድፈር ባሕል ነበር’ የሚሉ እና ‘ሕወሓት ታስረው የነበሩ ወንጀለኞችን ፈትቶ በመሸሹ እነርሱ የፈፀሙት ነው’ የሚሉ ማስተባበያ ክህደቶች ተደጋግመው ይሰሙ ነበር። እነዚህ ዓይነት ሰበብ አስባቦችን መደርደር የጥቃት ሰለባዎች ድርብ ጥቃት እንዲሰማቸው የሚያደርግ በበደል ላይ በደል ነው። ይህ ሁሉ ደግሞ እየተደረገ ያለው ትግራይ በመረጃ ጨለማ ውስጥ በተዘፈቀችባቸው ያለፉት ወራት በመሆኑ ራሳቸውን እንኳን እንዳይከላከሉ፤ በደላቸውን በራሳቸው አፍ እንዳይናገሩ ተደርገዋል። ለዚህ ነው ጩኸታችን የሚያስፈልጋቸው።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ ነች። ግጭቶች ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ እየፈነዱ ነው። አንዱ የሌላውን ሕመም ካላዳመጠ፣ ሌላው ላንዱ ካልጮኸ የጋራ ዕጣ ፈንታችን ከመቼውም ጊዜ በባሰ አደጋ ላይ መውደቁ ነው። ወገኖቻችንን ከጥቃት ማስጣል ቢያቅተን እንኳን፣ ሰምተን እንዳልሰማን፣ አይተን እንዳላየን በዝምታ ልናልፍ አይገባም። እንጩህላቸው!
(ይህ ጽሑፍ ዛሬ የወጣው 124ኛው ፍትሕ መጽሔት – Feteh Magazine እትም ላይ ታትሟል።)
Filed in: Amharic