>
5:26 pm - Saturday September 15, 2300

የግራኝ አህመድ ወረራ....!!! (ከአያሌው ፈንቴ)*

የግራኝ አህመድ ወረራ….!!!

(ከአያሌው ፈንቴ)*

«አሁን የገጠመን ፈተና ከ500 ዓመት በፊት ከገጠመን የከፋ ነው…!!!»
          — ብ/ጄኔራል አሣምነው ጽጌ 

አህመድ ኢብራሂም ኤል ቃዚ ኦጋዴን ውስጥ በምትገኝ ሆባት በምትባል መንደር በአባቱ “መለሳይ” በእናቱ “ሐርላስ” ከተባሉ የሶማሌ ጎሳዎች በ1498 ዓ.ም የተወለደ የጦር መሪ ነበር።
በግራኝ ወረራ ዋዜማ የኦቶማን ቱርክ የዘመኑ የአካባቢው ኃያል መንግሥት ነበረች፡፡ ግዛቷ እስከ ምሥራቅ አውሮፓ፣ ሰሜንና ምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም የአረቡን ዓለም በሙሉ የሚያጠቃልል ሲሆን፣ የቱርክ የንግድና የጦር መርከቦች የሜድትራንያንንና የሕንድ ውቅያኖስን ይቆጣጠሩ ነበር።
ኦቶማን ቱርክ አገሮችን የወረረችበት ዋና ምክንያቶቿ (1ኛ) ግዛት በማስፋፋት የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመመዝበርና (2ኛ) የእስልምና ሀይማኖትን ለማስፋፋት ነበር። በወቅቱም ከአካባቢው አገሮች ሁሉ በቱርክ እጅ ያልወደቀች ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች።
ደዋሮ (ሐረር) ውስጥ የነበሩ ኃያል የእስላም መሪዎች አቅም ሲያንሳቸው ለኢትዮጵያ ነገሥታት ታማኝ ሆነው በመገበር ሰላም ይፈጥሩ ነበር። በዚህ ሁኔታ ለብዙ ዘመን ሲኖሩ የቱርክ መሣሪያና ወታደራዊ እርዳታ በገፍ ይመጣላቸው ጀመር። በዚህ ወቅት ነው አህመድ ኢብራሂም (ግራኝ) የተነሳው።
ግራኝ በተነሳበት ወቅት ደገልሀን የተባለ ለንጉሥ ልብነ ድንግል የገበረ የጦር መሪ የፈጠጋርን (አርሲ) አውራጃ ያስቸግር የነበረውን በግራኝ አህመድ የሚመራውን የእስላም ጦር በማሸነፍ እስከ ሆባት አባሮት ነበር። ሆኖም ሆባት ላይ ሲደርስ የስንቅና የትጥቅ እጥረት ስለደረሰበት፣ የግራኝ አህመድ ጦር መልሶ አባረረው። በዚህም ግራኝ በ1517 ዓ.ም. በንጉሱ በልብነ ድንግል ጦር ላይ የመጀመሪያውን ድል አገኘ። ይህም ለግራኝ ተጨማሪ የመሣሪያና የወታደር እርዳታ ከቱርክ መንግሥት አስገኘለት።
በ1521 ዓ.ም. የካቲት ወር ማለቂያ ላይ የግራኝ ጦር በስውር ተጉዞ ሞጆ ወንዝ አካባቢ ከምትገኝ ባደቄ ከምትባል ሥፍራ ላይ ከንጉሡ ጦር ጋር ገጥሞ በመሸነፉ ሸሽቶ ዝቋላ ተራራ አጠገብ መሸገ። ነገር ግን የንጉሡ የጦር መሪዎች ግራኝን ተከታትለው ሊደመስሱት ሲችሉ ይህን ባለማድረጋቸው፣ ግራኝ ሲጠብቃቸው የነበሩ ሁለት መቶ (200) የቱርክ ወታደሮች እስኪደርሱለት ጊዜ ሰጡት።
የአገሬው ነዋሪዎች የነበሩት ሜያዎች ግራኝን ሊወጉት ሞክረው ነበር፡፡ 300 ቀስተኞችን ጨረሰባቸውና አፈገፈጉ። በዚያው ሳምንት እዚያው ዝቋላ አካባቢ “ሽምብራ ኩሬ” የተባለችውን ቀበሌ ለጦር ምሽግ ግራኝ መርጦ ያዘ። የጠበቃቸውም የቱርክ 200 ነፍጠኞች ደረሱለት። መጋቢት 3 ቀን 1521 ዓ.ም. የሽምብራ ኩሬ ጦርነት ተደረገ። ከዚያን በፊት በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ የጠመንጃ ጦርነት ታዬ። ይህ ለንጉሡ ወታደሮች ፍፁም አዲስ የሆነ የጦር መሣሪያ ለግራኝ ድል አስገኘለት። በጦርነቱ 12,000 ክርስቲያን ወታደሮችና 6,000 የእስላም ወታደሮች እንደሞቱ፣ በዕለቱ ከግራኝ ጋር አብሮ የነበረ አብድልቃድር የተባለ የአረብ ፀሀፊ ዘግቧል።
በአካባቢው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ። ወንዶች አንገታቸው በሰይፍ ተቆረጠ። ሴቶችና ሕፃናት ወደ አረብ አገር (የመን) ለባርነት ተላኩ። ከብቶች ወደ ሶማሊያ አገር ተነዱ። ጠንክሮ ለመመለስ ግራኝ በምርኮ ያገኘውን ይዞ ወደ ሐረር ተመለሰ። በሐምሌ ወር 1521 ዓ.ም. እንደገና ተመልሶ ደዋሮን (ሐረርን) ወረረ። ቀጥሎም ባሊን (ባሌን) ወረረ። በባሌ የነበሩና የኖሩ ገዳማት ሀብታቸውና ወርቃቸው ተዘርፎ ተቃጠሉ። ከባሊ (ባሌ) ገዳማት በተገኘው ብቻ ሰባት (7) መድፎችንና ለሠራዊቱ የሚያስፈልገውን ስንቅና ጠመንጃዎችን ገዛ። ባሌ ውስጥ በግራኝ የወደሙ ገዳማት እስከዛሬ አልተተኩም።
በጥር ወር 1522 ዓ.ም. ግራኝ ጦሩን በይፋት በኩል አዝምቶ አንጾኪያ ላይ ታላቅ ጦርነት ተደረገ። የኢትዮጵያ ወታደሮች አይተውት በማያውቁት በመድፍ ጥይት ተደበደቡ። የደረጀችው የአንጾኪያ ቤተክርስቲያን በወርቅና በብር የተሰሩ ንዋዬ ቅድሳት በግራኝ ከሶማሊያ ያመጣቸው ወታደሮች ከተመዘበረ በኋላ እሳት ተለቀቀባት። ግራኝ በወረራ በያዛቸው በደዋሮ (ሐረር) እና በፈጠጋር (አርሲ) አውራጃዎች የራሱን ሰዎች በመሾም ሥልጣኑን አደላድሎ በአዋሽና በዝቋላ መካከል በሚገኘው በሜያዎች አገር ሰፈረ። በአካባቢው በመዘዋወርም ብዙ ክርስቲያኖችን በሰይፍ እያስፈራራ አሰለመ።
ሐምሌ 9 ቀን 1523 ዓ.ም. ግራኝ በ 1200 ዓ.ም. የተመሠረተውን የታላቁን የደብረ ሊባኖስ ገዳም ንብረት ካስመዘበረ በኋላ፣ ከነመነኮሳቱ አቃጠለው። ንጉሡ ልብነ ድንግል ግራኝን መቋቋም ስላቃታቸው በሽሽት ወደ ቤተአማራ ተጓዙ። የግራኝ ዋና እቅድ ንጉሡን በመግደል ወይም ቢቻል ይዞ በማስለም ኢትዮጵያን በአጠቃላይ ለማስለም ነበር። ዱካቸውን ተከትሎ አንጎት (ራያ) ላይ ደረሰባቸው። ብርቱ መከላከል አድርገው ለጊዜውም ቢሆን ግራኝን ማቆም ተቻለ።
እዚያው አንጎት ውስጥ ግራኝ ንጉሡን ደርሶባቸው፣ ንጉሡ ሲያመልጡ ሚናስ የተባለው የንጉሱ የመጨረሻ ልጅና ወይዛዝርት በምርኮ ግራኝ እጅ ገቡ። ሁሉም የመንን ሲያስተዳድር ለነበረው የቱርክ ፓሻ በባርነት ተላኩ። አልሰልምም ያለውን የአንጎትን (የራያን) አማራ ሕዝብ ግራኝ በገፍ ጨረሰ።
ቀጥሎም ግራኝ ወደ ጣና ሐይቅ በመሄድ፣ በሐይቁ ደሴት ውስጥ የሚገኘውንና በ1200ዓ.ም. የተሠራውን ገዳም ሊያቃጥል ሲል፣ መነኮሳቱ ገዳሙን ከቃጠሎ ለማዳን ባደረጉት ሥምምነት የገዳሙን ንብረት በጀልባ እየጫኑ አስረከቡ። 150 ሰዎችን ለመጫን የተሠራ ጀልባ 3 ጊዜ ተመላልሶ አጋዘ። ከንብረቱ ውስጥ የወርቅ መስቀሎች፣ ማጠኛዎች፣ ፅዋዎችና የከበሩ ዕቃዎች ይገኙበታል።
ግራኝ ይዞታውን ለማጠናከር ከባሕር ዳር እንደገና ወደ ደቡብ ምዕራብ በመምጣት የጦር ሠፈሩን እንደገና ወደ ዝዋይ አዛወረ። የአገሬው ኑዋሪዎች የሆኑትን የንጉሡን ታማኝ ዜጎች (የሜያ ሕዝብ) ከጠራረገ በኋላ፣ መጀመሪያ ደዋሮን፣ ቀጥሎም ባሌን እንደገና ወረረ። ግማሽ ቀን በፈጀው በዚህ በባሌ ጦርነት አዝማች አዳሉና ልጁ ዘመንክርም በታላቅ ጀግንነት ተዋግተው ከ3,000 የክርስቲያን ወታደሮች ጋር ወድቀዋል።
በ1524 ዓ.ም. ምሥራቅ፣ ደቡብና መካከለኛ የኢትዮጵያ ግዛቶች በግራኝ ጦር ተደብድበዋል። በዚህ ዘመን ያልተወረሩ ግዛቶች ዳሞት (ጎጃም) እና ሌቃ (ምሥራቅ ወለጋ))፣ ቢዛም፣ ቄለም (ምዕራብ ወለጋ))፣ ሰሜን ቤጌምድር፣ ትግሬና ባሕር ምድር (ኤርትራ) ስለነበሩ እነዚህን ግዛቶች ለመውረር እንዲችል በመጋቢት 1525 ዓ.ም. ግራኝ ሠራዊቱን ደብረ ብርሀን ላይ አከማቸ። በአጼ ዘርዐ ያዕቆብ በተሠሩ ገዳማት ምትክ መስጊዶች ተሠሩ፣ በግዳጅ የሰለመ ሠለመ፣ ያልሰለመ የአካባቢው አማራ በግራኝ ሠይፍ አንገቱ ተቀላ፣ ያመለጠውም ጫካ ገባ።
በ1525 ዓ.ም. መጨረሻ ግራኝ በጎንደር ዘልቆ ደምቢያንና አካባቢውን ከወረረ በኋላ በእንደርታ ላይ አልፎ ተምቤንን ወጋ። በሹም አጋሜ የተመራው ጦር ተምቤን ላይ ብርቱ መከላከል ቢያደርግም ግራኝን ማቆም ግን አልቻለም። በዕለቱ ጦርነትም 10,000 የአጋሜ ወታደሮች አልቀዋል።
በዚሁ ዕለት አጼ ልብነድንግል አክሱም ገብተው ጦር ለማሰባሰብ ሞክረው ነበር፣ ነገር ግን ግራኝ ስለደረሰባቸው ወደ ወልቃይት ጠገዴ ሸሽተው አመለጡ። ግራኝም የአክሱምን ደብሮች ከነቀሳውስቱ አቃጠለ። ቀጥሎም ሠራዬንና ቤጌምድርን ወረረ።
በ1531 ዓ.ም ለረጅም ዘመን ሲጠበቅ የነበረው 1,000 ነፍጥ፣ 1,000 የፈንጂ ጦር፣ 4 ከባድ መድፎችና በድምሩ 535 ወታደሮችን የያዘው በክርስቶፎር ደጋማ የሚመራው የፖርቱጋሎች የጦር ዕርዳታ በባሕረ ነጋሽ ይሥሐቅ መንገድ መሪነት ደብረ ዳሞ ደረሰ (ዝርዝሩን ለማወቅ “የፖርቱጋሎች ጀግንነት” የተባለውን መፅሐፍ ይመልከቱ)።
ጳጉሜ 3 ቀን 1532 ዓ.ም. አጼ ልብነ ድንግል ተሸሽገው ከኖሩበት በደብረ ዳሞ ደብር ሞቱ። ልጃቸው ገላውዲዎስ ነገሠ። ሚያዝያ 9 ቀን 1534 ዓ.ም. እንጣሎ አጠገብ በተደረገው ጦርነት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ግራኝ በጥይት ቆስሎ ተሸንፎ ሸሸ። እና ዞብል በምትባል የደንከል በርሀ መንደር ገብቶ ጦሩን ማጠናከር ጀመረ።
ግራኝ በደንከል በርሃ መሽጎ ጦሩን እያደረጀ፣ ከአለቆቹ ከቱርክ ገዥዎች ጋር በመላላክ በእጁ ያስገባው የክርስቲያን አገር ከእጁ ሊወጣ ስለሆነ ተጨማሪ ወታደርና መሣሪያ ባስቸኳይ እንዲደርስለት ገጸ በረከት ጨምሮ ላከ። ከቱርክ መንግሥትም 900 ምርጥ ነፍጠኞችን ያካተተ 2,000 ወታደሮችና 10 መድፎች ተላኩለት። በተጨማሪም ንጉሡን ሊረዱ ለመጡት ለፖርቱጋሎቹ ምንም ዓይነት እርዳታ እንዳይደርስ የቱርክ መርከቦች ምፅዋንና አካባቢውን አጥረው ያዙ።
ምንም እንኳን የሰውና የመሣሪያ እርዳታ ባይደርስለትም ክርስቶፎር ደጋማ ከግራኝ ጋር ለመዋጋት ቆረጠ። መስከረም 2 ቀን 1535 ዓ.ም. ዋግ ላይ በተደረገው ውጊያ ኢትዮጵያውያንና ፖርቱጋሎች ብዙ ዕልቂት ደርሶባቸው ተሸነፉ። ክርስቶፎር ደጋማንም ግራኝ አንገቱን ቆርጦ ገደለው። ከፖርቱጋሎች ከ535 ወታደሮች ውስጥ 150 ብቻ ነው የተረፉት። ግራኝም በድል አድራጊነት ኑሮውን ለመቀጠል ተመልሶ ወደ ደምቢያ ሄደ።
አሸናፊነቱ በያቅጣጫው በግራኝ በኩል አጋድሎ ባለበት፣ ሸዋ ውስጥ ከግራኝ የጦር አለቆች ጋር ሲዋጋ የቆየው አጼ ገላውዲዎስ የግራኝን ከበባ ጥሶ ወደ ሰሜን በመምጣት ከተረፉት የፖርቱጋል ወታደሮች ጋር ተገናኝቶ በጋራ ስለሚያደርጉት ጦርነት ተማክረው ዕቅድ አወጡ።
በመጨረሻም በየካቲት ወር 1535 ዓ.ም. ገላውዲዎስ 9,000 ወታደሮችን ይዞ፣ ግራኝ ደግሞ 15,000 ወታደሮችን አሰልፎ የንጉሡ ጦር እዚያው የመሸገበት ደምቢያ ወረዳ ድረስ በመሄድ ለሳምንት ያህል ተፋጥጠው ቆዩ። ረቡዕ የካቲት 28 ቀን 1535 ዓ.ም. ሲነጋጋ፣ ዘንተራ በር ከተባለው ሥፍራ ጦርነቱ ተጀምሮ ከብዙ ዕልቂት በኋላ የግራኝ ጦር ተሸነፈ። ግራኝም ተገደለ። ከግራኝ ጦር ውስጥ በህይወት ተርፈው ያመለጡ ሚስቱ ድል ወንበራና 40 የቱርክ ወታደሮች ብቻ ነበሩ።
የግራኝ ወረራ ውጤት፡- 
ሀ) የኦቶማን ቱርክ በኢትዮጵያ ላይ የመስፋፋት ዕቅድ ከግራኝ ጋር ዘንተራ በር (ደምቢያ) ላይ አብሮ ሞተ።
ለ) በዚህ ጦርነት የሌሎች ነገዶች መስዋዕትነት ባይናቅም በባሊ፣ በፈጠጋር፣ በቤተ አማራ፣ በቤጌምድርና በዳሞት በብዛት የረገፈው የአማራ ሕዝብ ነው።
ሐ) ጦርነቱ የተካሄደው በራሷ በኢትዮጵያ ሀብት ነበር። በዚህ ጦርነት ምክንያት የኢትዮጵያ ሀብትና ንብረት የቱርክንና የየመንን ባለሥልጣናት እስከ ተራው ወታደር ድረስ አክብሯል። የኮንስታንቲኖፕል ቤተ መንግሥት ዕቃዎች በወርቅ የተሠሩ እስከመሆን ደርሰዋል።
መ) ምንም እንኳን አጼ ገላውዲዎስ በግራኝ ላይ ድል ቢቀዳጅም፣ በአካባቢው ግራኝ የሾማቸውን መሪዎች ለመምታትና አካባቢውን ለመቆጣጠር የረጅም ጊዜ ሥራ ሆነበት። አፄ ገላውዲዎስ ከግራኝ የእህት ልጅ ከኑር ዓሊ ጋር ሲዋጋ ሞተ። በዚህ ወቅት አገሪቱ በጦርነት የደቀቀች በመሆኗ “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ሆነና ለጋሎች (ኦሮሞዎች) ወረራ የተጋለጠች ሆነች።
አጠቃላይ ጽሑፉ 4 ክፍሎች ነበሩት፡፡ ይህ የመጀመሪያው ክፍል ነው፡፡ ልክ እንደዚህኛው ሁሉ ቀሪው እያንዳንዱ ክፍልም ራሱን የቻለ የምርምር ሥራ ነው፡፡ እንደ ሁኔታው አይተን ወደፊት እናቀርበዋለን፡፡ እስከዚያ ያገኘው በደራሲው ስም ፈልጎ ያንብበው፡፡
ለዚህ ታሪካዊ የምርምር ጽሑፍ አቅራቢ፣ ለአያሌው ፈንቴ፣ ልባዊ ምስጋናዬን አቅርቤ ተሰናበትኩ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
_________________________________________
*ምንጭ (ከምስጋና ጋር)፡- ከላይ የቀረበው ታሪክ ሙሉ በሙሉ የተወሰደው ከአያሌው ፈንቴ የጥናት ጽሑፍ፣ ክፍል 1 ላይ ነው፡፡
ምስሎቹ (ከምስጋና ጋር)፡- (ከላይ በስተግራ) በግራኝ ወረራ ወቅት እስከ ቀይ ባህር የኦቶማን ቱርክን ግዛት አስፋፋ በሚል በቱርኮች ታሪክ ታላቁ የሚል መጠሪያ የተሰጠው የቱርኩ አፄ ሱልጣን ሱሌማን፤ (ከላይ በስተቀኝ) በግራኝ ወረራ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የፖርቹጋል የጦር መሪ ክሪስቶቮ ደ ጋማ፤ (ከታች) በሞቃዲሾ ሶማሊያ የሚገኝ የአህመድ ጉሬይ (ግራኝ) የግድግዳ ላይ ሐውልት/ቅርጽ (ሙራል ሪሊፍ)፡፡
Filed in: Amharic