በትግራይ ክልል ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ 108 የመደፈር ጥቃቶች ለጤና ተቋማት ሪፓርት ተደርገዋል!
ኮሚሽኑ በመቀለ ከሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ ባገኘው መረጃ መሠረት፤ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በመቀለ ሆስፒታል 52፣ በአይደር ሆስፒታል 27፣ በአዲግራት ሆስፒታል 22፣ በውቅሮ ሆስፒታል 7 በአጠቃላይ 108 የመደፈር ጥቃቶች ለጤና ተቋማት ሪፖርት ተደርገዋል።
“የጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎች ወንጀሉን ለማሳወቅና የሕክምና እርዳታ ለማግኘት የሚሄዱባቸው እንደ ፖሊስ ጣቢያ እና ጤና ጣቢያ ያሉ ተቋማት በአንዳንድ አካባቢዎች ፈርሰው በመቆየታቸው፤ ሪፖርት የተደረጉ ጥቃቶች ቁጥር ትክክለኛውን የጉዳት መጠንና ስፋት እንደማያመላክት እና የጾታዊ ጥቃት መጠኑ ከዚህ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል” በማለትም የደረሰው ጥቃት ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
በክልሉ የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ የሕክምና እርዳታ ፈላጊዎች በምሽት ወደ ጤና ተቋማት እንዳይሄዱ እንቅፋት እንደሆነም ኮሚሽኑ የጤና ባለሙያዎችን ጠቅሶ ግልጿል።
ጉዳት የደረሰባቸው ሕጻናት
ኮሚሽኑ እንዳለው በጦርነቱ ሳቢያ የአዕምሮ መረበሽ የገጠማቸው ሕጻናትን አግኝቷል።
በአይደር ሆስፒታል የሕፃናት ተኝቶ መታከሚያ ክፍል በመታከም ላይ ከነበሩት 20 ከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀት እና ድንጋጤ ታካሚ ሕፃናት መካከል 16ቱ በጦርነት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው እንደሆኑ ኢሰመኮ ገልጿል።
በሆስፒታሉ በመታከም ላይ ከነበሩ ሕፃናት መካከል እጃቸውን እና አይናቸውን ያጡ፣ በጭንቅላት፣ በሆድ እና በአጥንታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የትግራይ ክልልን ጤና ቢሮ ጠቅሶ “ጦርነቱን ተከትሎ በየገጠሩ ያሉ የጤና ተቋማት አገልግሎት በማቆማቸው ምክንያት እና መቀለን ጨምሮ ህክምና ለማግኘት ወደሚቻልባቸው ከተሞች ለመጓጓዝ የትራንስፖርት እጥረት በመኖሩ የተጎዱ ሰዎች ሕይወት እያለፈ እና ከባድ የአካል ጉዳት እየደረሰ ነው” ብሏል።
ከአይደር ሆስፒታል በተገኘው መረጃ መሠረት፤ በተለይ በሕፃናት ላይ ለደረሱት ጉዳቶች አንዱ ምክንያት በመሬት ውስጥ የተቀበሩ እና በሜዳ ላይ የተጣሉ ፈንጂዎች የሚያስከትሉት አደጋ ነው።
በተለያየ እድሜ ላይ የሚገኙ ሕጻናትን ያነጋገረው ኢሰመኮ ባገኘው መረጃ መሠረት፤ ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ እንዲሁም በተባራሪ ጥይት ጉዳት የደረሰባቸውም እንዳሉ ገልጿል።
በተባራሪ ጥይት ተመትተው ከሞቱ ሕጻናት መካከል ለአራት ቀናት በፅኑ ህሙማን ክፍል ሲረዳ ቆይቶ ሕይወቱ ያለፈ የአራት ዓመት ልጅ አንዱ ነው።
“በሴቶች እና በሕፃናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትን በተመለከተ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማረጋገጥ ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች ተገቢውን እርዳታ መስጠት ያስፈልጋል” ብሏል ኮሚሽኑ በመግለጫው።
የጸጥታ ጉዳይ
የክልሉ መደበኛ የፖሊስ አባላት ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ባለመግባታቸውና ለጸጥታ ጥበቃ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ባለመሟላታቸው በክልሉ ዘረፋና ጾታዊ ጥቃትን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎች በከፍተኛ መጠን እንደጨመሩ የኮሚሽኑ መግለጫ ይጠቁማል።
“በክልሉ የሚገኙት የፌደራል ጸጥታ ኃይሎች ቁጥር በክልሉ ከሚያስፈልገው የደኅንነት ጥበቃ ፍላጎት አንጻር ሲታይ ውስን መሆኑ የሕግ ማስከበር እና ደኅንነትን የማረጋገጥ ሥራውን ፈታኝ አድርጎታል” በማለትም ያክላል።
በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ውጊያ ባለመቆሙ መደበኛ የእለት ከእለት እንቅስቃሴዎች እንደተገደቡና የመሰረታዊ ፍላጎት ሸቀጦች በአግባቡ እንደማይዘዋወሩም ተገልጿል።
በተያያዥም የክልሉ የቀድሞ አስተዳደር መዋቅር መፍረሱን ተከትሎ በ10 ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ እስረኞች በሙሉ ከእስር እደወጡና የእስረኞችን መረጃዎች የያዙ ሰነዶች እንደወደሙ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጠቅሶ ኢሰመኮ ገልጿል።
“በተለይ ከባድ ወንጀል ፈጻሚዎችን መልሶ የመሰብሰብና በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራውን እጅግ አዳጋች እንዳደረገው” ኮሚሽኑ አክሏል።
አገልግሎት ሰጪ ተቋሞች
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ከሚሽን በተለይም የጤና አገልግሎት ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
አብዛኞቹ አምቡላንሶች በክልሉ የጤና ቢሮ ሥር እንዳልሆኑና አምቡላንስ ባለመኖሩ ምክንያት አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ለመስጠት ባለመቻሉ ሕይወት እንደሚጠፋም አክሏል።
“በክልሉ የጤና አገልግሎትን ለመመለስ አስቸጋሪ የሆነው በተለይ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ በምሥራቅ ትግራይ እና በማዕከላዊ ትግራይ የሚገኙ የተወሰኑ ጤና ተቋማት በግዜያዊ አስተዳደሩ ሥር ባለመሆናቸውና በባለቤትነት ችግር የተነሳ ደመወዝ፣ መድኃኒት እና የሰው ኃይልን በአግባቡ ማቅረብ ባለመቻሉ ነው” ይላል የኮሚሽኑ መግለጫ።
መቀለ እና አዲ ጉደም የሚገኙ የጤና ተቋሟት በአንጻራዊነት የተሻለ ሁኔታ ላይ ቢገኙም፤ በተለይ በአድዋ፣ በአክሱም እና በሽረ የጤና ተቋሞች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች የጤና ባለሙያዎችም ለአስቸኳይ እርዳታ እንደተጋለጡ፣ እንደተፈናቀሉ እንዲሁም ደመወዝ ወይም ገንዘባቸውን ከባንክ ለማንቀሳቀስ ባለመቻላቸው መሠረታዊ አቅርቦት እንዳጡ መግለጫው ይጠቁማል።
ስደተኞች እና ተፈናቃዮች
በትግራይ ክልል ከሚገኙ አራት የስደተኛ ካምፖች ውስጥ ሁለቱ ሽመልባ እና ሕፃፅ ይገኙ የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደተበተኑና ካምፖች እንደወደሙ ኢሰመኮ ጠቁሟል።
ከጦርነቱ ቀደም ብሎ ሽመልባ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ የነበሩ 8500 የሚጠጉ ኤርትራዊያን ስደተኞች የነበሩ ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ በግምት 5000 የሚሆኑት ወደ ሽራሮ እና ሽሬ ከተሞች መበታተናቸው ቀሪዎቹ 3500 በፍቃዳቸውም ሆነ ያለፍቃዳቸው ወደተለያየ ስፍራ መጓዛቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በሕፃፅ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ በግምት ወደ 13000 የሚጠጉ ስደተኞች የነበሩ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 8000 የሚሆኑት በሽሬ እና ሽራሮ ከተሞች መበታተናቸውና “አብዛኛዎቹ ስደተኞች መጠለያ እና መሠረታዊ አቅርቦቶችን ለማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ እንደሚገኙ ኮሚሽኑ ያገኛቸው መረጃዎች ያሳያሉ” ሲልም አክሏል።
ስምንት የተፈናቃዮች መጠለያ ትምህርት ቤቶችን ተዘዋውሮ ባገኘው መረጃ መሠረት እየቀረበ የሚገኘው መሠረታዊ አገልግሎት አነስተኛ እንደሆነ ኮሚሽኑ አስታውቋል።