>

ብርቱካን ሚደቅሳ የብልጽግናዋ መርጋ በቃና..!! (ስንታየሁ ቸኮል የህሊና እስረኛ)

ብርቱካን ሚደቅሳ የብልጽግናዋ መርጋ በቃና..!!

ስንታየሁ ቸኮል የህሊና እስረኛ

ይችን ፁሑፍ የማዘጋጀው እስሩን ከኩላሊት ህመሜ ጋር እየታገልኩ ነው፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በግፍ ታስረውበት ከነበረው የሴቶች እስር ቤት ጀርባ ወይም በቅርቡ አቶ እንዳርጋቸው ፅጌ በመፅሐፋቸው ካስጎበኙን ግቢ ማለትም ትንሿ ወህኒ ቤት ውስጥ እገኛለሁ፡፡ በግፍ እስር ቤት የምንገኝ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ልባችን የህዝብ ጉያ ውስጥ ነው፡፡ ስጋችንን እንጂ መንፈሳችን አምባገነኖች አላሰሩትም፡፡ በርግጥ ቢችሉ ኖሮ መንፈሳችንንም ከማሰር አይቆጠቡም ነበር፡፡ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው፡፡ እኛም ‹ነፃነት ወይም ሞት› እንታገላለን!


ሀገራችን ኢትዮጵያ በየዘመኑ የሚወድቁላት፣ በሃቀኝነት የሚደሙላት ልጆች አታጣም፡፡ የሚያጠቋት እንዳሉ ሁሉ የሚወዷት አጥታ አታፍርም፡፡ የአድዋ ልጆች የሰማዕታት ልጆች የአርበኞች ልጆች ትላንትም ነበሩ ዛሬም አሉ፡፡ ለሀገራቸው አንድነት ሉአላዊነት ግዛት በሁሉም ተፈትነው እነዳለፉት ሁሉ ይህ ትውልድ የእነሱን ምሳሌ ይዞ መነሳቱ ታላቅ መመረጥ ነው፡፡ እድለኝነት ነው፡፡ በዘንድሮው የአድዋ የድል በዓል የታየው ድባባም ይኸው ነው፡፡ ልባችን በደስታ፤ ነጋችን በተስፋ የተሞላ አድርጎታልና ይበል ማለት እወዳለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ የድሉ ቀዳሚ ባለቤቶችን እምዬ ምኒልክን እና ብርሐን ዘ ኢትዮጵያ እቴጌ ጣይቱን ገለል አድርገው ‹የአድዋው ዘማች እኔ ነኝ› የማለት ያህል ቢውተረተሩም ሕዝብ በተለየ ድምቀት አክብሮታል፡፡ ወላጆች ሕፃናት ልጆቻቸውንም ጭምር እሽኮኮ ብለው በመውሰድ ታሪክ ሲያስተምሩ ውለዋል፡፡ የነገስታቱ ምስሎች የታተሙባቸው አልባሳት በሰፊው ተለብሰው እንደዋሉ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ከገዥው ፓርቲ የፕሮፖጋንዳ ጋጋታ ጋር አዳብለው አሳይተውናል፡፡

መቼም ስለ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስናነሳ ስለ በርካታ ሰዎች መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በተቋሙ የሓላፊነት ቅብብሎሽ ውስጥ ያየናቸው ክስተቶች ሁሉ ታሪኮቻችን ናቸውና፡፡ ታሪካችንን ማገላበጥም ያስፈልጋል፡፡
አምስት ጊዜ የይስሙላ ምርጫዎች ተደርገዋል፡፡ ገዥው ፓርቲ አውራ ተዋኒ ሆኖ የተሳተፈባቸው እነኝህ ምርጫዎች ትንንሽ ንጉሶችን እየቀቡ ቤተ መንግሥት አስገብተዋል፡፡ በተለይም ከ1997ቱ ምርጫ ውጭ የያሉት አራቱ በሂደትም በውጤትም ተገማችና ከንቱ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የሕወሓትን የህዳጣን መንግሥት ከማደስ ውጭ ሚና አልነበራቸውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ዋነኛው መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡
ከ1987 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. ከቀድሞው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ከማል በድሪ እስከ የእንስሳት ሀኪሙ ፕ/ር መርጋ በቃና የተለያዩ የገዥው ፓርቲ ካድሬዎች ቦርዱን በሓላፊነት መርተዋል፡፡ በአቶ በረከት ስምዖን የካድሬነት መመሪያና ስልጠና አለፍ ሲልም ቀጭን ትዕዛዝና ሌሎች የሕወሓት ሓላፊዎች በፈለጉት መልኩ ሲመሩት መቆየታቸው በሂደቱ ያልፉ ሰዎች የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ለምሳሌ ከማል በድሪ ሰብሳቢ ቢሆኑም ከፍተኛ ሚና ያላቸው ተዋንያን ግን ከስር የነበሩ ካድሬዎች ነበሩ፡፡
ከ1987 – እስከ 1996 ድረስ አስፋ ብሩ የተባሉ የጽ/ቤት ኃላፊ በሂደቱ ላይ ሲቆዩ እሳቸውን ተክተው ከገዢው ፓርቲ የተላኩት አቶ ተስፋዬ መንገሻ የፖለቲካ ጉዳዮችን እና የዕለት ተዕለት ሥራዎችን ሲያከናውኑ አቶ ወንድሙ ጎላጎል የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጉዳይ በመከታተልና እንከን እየፈለጉ ፓርቲዎችን ልማጨናገፍ ሰርተዋል፡፡ ምርጫ 97 በሂደቱና በውጤቱ እንዲሰናከልም ይህ አይነቱ ሂደት ታላቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ እነሆ ዛሬም በተመሳሳይ የታሪክ አዙሪት ውስጥ እየገባን ነው፡፡
አምስቱን ምርጫዎች ገዥው ፓርቲ በጡንቻው የራሱ መጠቀሚያ ሲያደርግ ዋነኛው አስፈፃሚ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡
ፕ/ር መርጋ በቃና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ሲመደቡ በድርጅቱ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ለመንግሥታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዲህ አሉ፡-
. . . የአቅም ግንባታ ስልጠና በፍፁም አልነበረም፡፡ የቁሳቁስ ስልጠናም አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰራተኞች በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት አልነበራቸውም፡፡ የቦርዱ ባለሙያ የሚባል ጭራሽ አንድም አልነበረም፡፡ ስነ ዜጋ ትምህርት እና የህዝብ ግንኙነት የተማረ ሰው አልነበረም፡፡ የፖለቲካ ዘርፍ የለም፡፡ የተቀናጀ የእውቀት ሥራ የሚመራ አልነበረም፡፡ ‹የክልል› ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በጭራሽ አልነበሩም፡፡ ምርጫው ላይ ሳይሆን ሎጀስቲክስ ላይ ብቻ ነበር ርብርቡ ሲደረግ የቆየው. . .
መርጋ በቃና በዚህ ንግግራቸው የ1987፣ የ1992 እና ታሪካዊው የ1997 ምርጫዎች የጨበጣ እንደነበሩ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ተቋሙ የባለሙያዎች እና የአደረጃጀቶች ድርቅ እንዲመታው የተደረገውም ትክክለኛ ሥራ እንዳይሠራ ነው፡፡ ትክክለኛ ሥራ ከሠራ እውነተኛ ሥራ ከሠራ ተቃዋሚዎች አሸንፈው ቤተ መንግሥት ይገባሉ፡፡ ስለዚህ ቦርዱን ለይስሙላ አቋቁሞ ገዥው ፓርቲ እንዲቆጣጠረው ነበር የተፈለገው፡፡ ሆኗልም፡፡ መርጋ በቃናም ሥልጣን ሲረከቡ ያነሷቸውን ችግሮች ደግመዋቸዋል፡፡ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳም ከመርጋ በቃና የሚለዩት የቦርዱን አሠራሮች በኮምፒዩተር የታገዙ በማድረግ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መርጋ የኢቲቪ ስቱዲዮ ድረስ ሄደው መግለጫ ይሰጡ ነበር፤ እሳቸው ደግሞ በቦርዱ የፌስቡክ ገፅ ገብተው ባሉበት መግለጫ ይሰጣሉ፡፡
ወ/ሪት ብርቱካንን የማውቃቸው የቅንጅት አመራር በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ በቅርበት ያወቅኳቸው ደግሞ አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ በ2001 ዓ.ም. ከተመሰረተ ወዲህ ነው፡፡ አንጋፋው ፖለቲከኛና ምሁር ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ስለ ብርቱካን ሲናገሩ ‹‹እኔ በእሷ ተስፋ አለኝ፡፡ ጎበዝ ጠንካራ እህታችን ናት፡፡ እድል ሊሰጣት ይገባል›› ይሉ ነበር፡፡ እውነት ነው ብርቱካን ከምርጫ 97 በኋላ ትግሉ አምጦ የወለዳቻ ሴት መሪ ከመሆናቸውም በላይ በወቅቱ ብቸኛ የቅንጅት ወራሽ ፓርቲ በማቋቋም የወቅቱን ፍርሃት የመለስ ዜናዊ ቅንብር ሰላማዊ የትግል መንገድ ሲታወስ ሲደንቀን ይኖራል፡፡
ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ከፓርቲው ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ ምክንያታቸውን በግልፅ ባላውቅም በውሳኔያቸው አክብሮት ነበረኝ፡፡ በተለይ ህፃን ልጃቸውን ጥለው፣ አዛውንት እናታቸውን አስቀምጠው ለጀመሩት ህዝባዊ ትግል ‹ቃሌን አላጥፍም› በማለት ለከፈሉት ውድ ዋጋ እክብሮቷ ያለቀ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ብርቱካን የመካዕክት አለቃ አይደሉምና የትላንቱን ለታሪክ ትተን ዛሬ ባሉበት ሓላፊነትና ቦታ እየገመገምን ድክመታቸውን መናገር አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ መድበለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ የሃሳብ ሜዳውን በሰላማዊ ትችት መግለፅ የሚጠበቅ በመሆኑ ምልከታየን አጋራለሁ፡፡
ወደ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት ሲመጡ በበርካታ ወገኖች ዘንድ ተስፋ የተጣለባቸው ከተረኞች ጋር ተደምረው እንዲደምሩን አልነበረም፡፡ የስርዓቱ ሥልጣን አስጠባቂ የሆነውን ምርጫ ቦርድ ከተለጣፊነት መንጥቀው ያወጡታል በሚል ተስፋ ነበር፡፡ በፕ/ር መርጋ በቃና ጫማ ውስጥ ብርቱካን ‹በቃና›ን ማግኘት ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ብርቱካን በእልልታ የተቀበላቸውን የአዲስ አበባ ኗሪ ሊያሳዝኑት ባልተገባ ነበር፡፡ ያለፉት የቦርዱ ሓላፊዎች ጠንካራ ተቃዋሚዎችን በማፈራረስ ሥርዓቱን እንዳስቀጠሉት ሁሉ ብርቱካን ሚደቅሳም ያንኑ ደጋሚ ሆነዋል፡፡ የመጀመሪያው ዱላቸው ደግሞ ፓርቲያችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ላይ አርፏል፡፡ አዋጅ ጥሰው በእስር ቤት ያለን ተጠርጣሪዎች በምርጫ እንዳንሳተፍ አድርገዋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ በርካታ ጉድፎችን ከመናገራቸውም በላይ ተጠሪነታቸው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይልቅ ለሚንስትሮች ምክር ቤት የተዘዋወረ በሚመስል መልኩ የፖለቲካ ተለጣፊነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በቅርቡ በሰጡት መግለጫም ሦስት መሰረታዊ ስህተቶችን አንስተዋል፡፡ እነርሱም፡-
 ‹‹በደቡብ ኢትዮጵያ ዳውሮ ታስረው የነበሩ ሰዎች ከእስር ተፈተው ወደ ምርጫ እንዲገቡ ሲደረግ ሌሎቹ ላይ ለምን በር ተዘጋ›› ለሚለው ጥያቄ መልስ አልነበራቸውም፡፡ በአዋጁ መሰረት በእስር ቤት ያለን ተጠርጣሪዎች የመወዳደር መብታችን ለምን እንደተከለከለ አላብራሩም፡፡
 ‹‹በሕግ ጥላ ስር ያሉ ሰዎች በዕጩነት ቢቀርቡ ነገ ጧት ወጥቼ ለምርጫ ልቀስቅስ ይላሉ›› የሚል አመክንዮ በመግለጫቸው ሲያነሱ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ ፈፅሞ የተሳሳተ ነው፡፡ በእስር ላይ ያለን ሰዎች ወጥተን እንቀስቅስ የሚል ጥያቄ ሳይሆን በዕጩነት እንመዝገብ ነው ያልነው፡፡ ይህ ደግሞ በአዋጅ በተደነገገው መሰረት ግልፅ የሆነ መብታችን ነው፡፡ በእስር ላይ ያሉ ዕጩዎች እንዴት መቀስቀስ እንዳለባቸው አዋጁ ያስቀመጣቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ይኸውም አንደኛ ባሉበት እስር ቤት ሆነው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ መስጠት የሚችሉ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በራሪ ወረቀቶችን ማዘጋጀትና ማሰራጨት ነው፡፡ ይህም ከወህኒ ቤት ሳይወጡ ሊያደርጉት የሚችሉት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሰጡት ማብራሪያ የለም፡፡
 ‹‹በተመረጡበት አካባቢ በፌዴራልም ሆነ በ‹ክልል› ምክር ቤት ቢያሸንፉ ነገ ጧት ከእስር ባይወጡ የመረጣቸውን ሕዝብ ማደናገር ይሆናል›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ‹‹የታሰሩ ሰዎች በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ሳያገኙ በተመረጡበት አካባቢ በድጋሜ ምርጫ ነው የምናደርገው ወይስ በእነርሱ ቦታ ሌላ ልንተካ ነው?›› የሚል መጠይቃዊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እነዚህ መልሶች በሕግ አግባብ ሲታዩ ሚዛን አይደፉም፡፡ አመክንዮዋቸውም ውሃ አይቋጥርም፡፡ አንደበታቸውን ስንሰማው ነገሩ የተገላቢጦሽ ይሆናል፡፡ በእስር ቤት ያሉ ወገኖች የዕጩነት ጥያቄን በተመለከተ በአዋጅ 1162/2011 በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ተጠርጣሪዎች የጥፋተኝነት ውሳኔ ሳይሰጣቸው መምረጥና መመረጥ ይችላሉ፡፡ ይህንን አዋጅ ቦርዱ ሊያስታውሰው አልፈለገም፡፡ በተመረጥንበት አካባቢ በፌዴራልም ሆነ በአዲስ አበባ ምክር ቤት ብናሸንም ቦታው ክፍት ሆኖ ይጠብቀናል እንጂ የሚፈጠር ችግር አልነበረም፡፡ እኛ አራት ሰዎች በምርጫው ውስጥ ብንሳተፍ የምናሸንፈው እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ድርጅት ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብም የሚመርጠን እንደድርጅት እንጂ እንደ ግለሰብ አይደለም፡፡ በመሆኑም የሚፈጠር ችግር የለም፡፡ ብርቱካን ሚደቅሳ ግን ይህንን ሊያብራሩ አልፈለጉም፡፡
በጥቅሉ በምርጫ እንዳንሳተፍ የተከለከልነው በሕግ አግባብ አይደለም፡፡ በቀጥተኛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ በንግግራቸው እኛ ላይ እንደሚፈረድብን እርግጠኛ ሆነዋል፡፡ ፍርድ እንደሚሰጠን ከወዲሁ ደምድመዋል፡፡ ይህ ከምን የመጣ እንደሆነ አናውቅም፡፡ የቅርብ መንግሥታዊ መረጃ ሊኖራቸው እንደሚችል ግን እንገምታለን፡፡
በዓለም ተሞክሮ ሰዎች እስር ቤት ውስጥ ሆነው በምርጫ የተወዳደሩበት ታሪክ አለ፡፡ ለአብነትም የእስራኤል የፓርላማ አባላት ይጠቀሳሉ፡፡ በሩሲያም ተመሳሳይ ተሞክሮ አለ፡፡ ታዲያ በኢትዮጵያስ በምን መስፈርት ነው አዋጅ ሊጣስ የሚችለው? ይህ የአምባገነኖች ፍርደ ገምድል ውሳኔ ነው፡፡ ሕዝብ ሊያጤነው ይገባል፡፡ ብርቱካን ሚደቅሳ እስረኞች በእዚያው ይቆያሉ ከሚለው አማራጭ በተጨማሪ ይፈታሉ ብለውም ማሰብ ነበረባቸው፡፡
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ተለጣፊ ሆነዋል የምንለው በምክንያት ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዋና ዋናዎቹን በተጨማሪነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
አንደኛ ባልደራስ ፓርቲ ሆኖ ሲመሰረት ማሟላት የሚገባውን መስፈርቶች በቀዳሚነት አሟልቶ የቀረበ ቢሆንም ሕጋዊ የምዝገባ ሰነዱን ለመቀበል ምርጫ ቦርድ ጠሞበት ቆይቷል፡፡ በብዙ መሰናክሎች ነው የተቀበለው፡፡ በአንፃሩ እራሱን ብልፅግና ፓርቲ በማለት የስም ለውጥ ያደረገው ኢህአዴግ ጠቅላላ ጉባኤ ሳያደርግና የጉባኤውን ሪፖርት ሳያቀርብ ህጋዊ መሰረት እንዲኖረው የተደረገበት መንገድ የቦርዱን ጥገኝነት ያሳየ ነው፡፡
የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ድልድል በአዲስ አበባና ድሬድዋ ከዋናው የጊዜ ሰሌዳ ውጪ በማውጣት የክልል ም/ቤቱን ሰኔ 5 መደበኛውን ግንቦት 28 የተደረገበት አንድምታ ለምን ሰፊ ፖለቲካዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ስርዓቱ ትርፍ መታወቂያዎች በገፋ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሲያድል መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን ይህን ውንብድና በተግባር ስናጋልጥ መቆየታችን አይዘነጋም፡፡ በኦሮሚያ ግንቦት 28 መርጫው ሲጠናቀቅ በገፍ ካርድ የወሰዱ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት እና የሁለተኛ ዙር ምርጫ ለማድረግ የታለመ ቢሆንም ከምኞት የዘለለ መወራጨት እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ የአዲስ አበባን ህዝብ ቁጥር ሊያስለወጥ ቀርቶ ሊገዳደር የሚችል ፋይል በፈለጉት መጠን አይሳካም፡፡ በአዲስ አበበ ባልደራስ 23 ለ 0 እንደሚያሸንፍ አልጠራጠርም፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡
Filed in: Amharic