ኢትዮጵያ እና 6ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ
በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
- እንደ መንደርደሪያ
ምርጫ ለአገራችን ኢትዮጵያ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ባህላዊ ምርጫ በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ሕዝቡ በየአካባቢው ኑሮውን፣ እምነቱንና ተስፋውን በሰላም ለመጠበቅ ተሰባስቦ የመምከር፣ የሀገር ሽማግሌዎችን የመምረጥና የመሰየም የቆየ ልማድ ነበረው፤ አለውም፡፡ የሚመረጡት ሽማግሌዎች የሚከተሏቸውና የሚያከብሯቸው ባህላዊ ሕጎች አሏቸው፡፡ ሸንጎ፣ ገዳ፣ ጐርዶና ሴራ፣ ጆንዶንጐ፣ ኮሞሩ እንደቅደም ተከተላቸው በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በጉራጌ፣ በአኝዋክና በሱርማ ሕዝቦች ዘንድ የሚታወቁ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓቶች ናቸው፡፡
ከባህላዊ የአስተዳደር ምርጫዎች በተጨማሪ እስካሁን ድረስ ዘልቀው የቆዩ የበጎ ፈቃድ ማኅበራት አሉ፡፡ ስማቸው ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ አብዛኞቹ የማኅበረሰብ የእርስ በርስ መረዳጃ ተቋማት ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ በምሳሌነት የሚጠቀሱት እቁብ፣ እድር፣ ሰንበቴ… ወዘተ ናቸው፡፡ የእቁብ ዳኞች፣ የእድር መሪዎችና የሰንበቴ ሙሴዎች የሚመረጡት ከማኅበሩ አባላት ውስጥ በማኅበርተኞቹ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነው፡፡ እነኚህ ማኅበራዊ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን የመምረጥና የመመረጥ የቆየ ልምድ የሚያመለክቱ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ ብለን መግለጽ እንችላለን፡፡
በዚህ የሐሳብ መንደርደሪያነትም፣ በቀጣይ ለ6ኛ ጊዜ ሊደረግ ዝግጅት እየተደረገበት ያለውን አጠቃላይ ምርጫ መሠረት በማድረግ ‘በሀገራችን፣ ኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ምን ይመስላል? ቀጣዩ ምርጫስ ምን ገጽታ ይኖረው ይሆን?’ በሚል አርእስት ጥቂት የመወያያ ሐሳቦችን ለማንሳት ነው፡፡
- ምርጫ በዘውዳዊ ሥርዓት
የዘውዳዊ ስርዓት በኢትዮጵያ ሰፍኖ የቆየው እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡ በዚህ ረዥም ዘመን በሀገራችን ውስጥ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚደረግ ምርጫ አይታወቅም፡፡ በዘውዳዊ ሥርዓት የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዘው በዘር ሐረግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በ1900ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት በዐፄ ምኒሊክ አማካይነት የሚኒስቴር አደረጃጀት ሲቋቋም ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ የተመረጡ ሰዎች በሓላፊነትና በአማካሪነት በንጉሠ ነገሥቱ አካባቢ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ በ1911 ዓ.ም. ከየጠቅላይ ግዛቱ የተመረጡ መሳፍንትና መኳንንት (ወይንም የእነርሱ ቤተሰብ አባላት) ንጉሠ ነገሥቱን በምክር እንዲረዱ በቤተመንግሥቱ ውስጥ ልዩ ቦታ ተሰጥቷቸው ሀገራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ወደ ሕዝቡ ከመድረሱ በፊት እንዲመክሩበት ይደረግ ነበር፡፡ ይህ አሠራር እስከ 1924 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በ1923 ዓ.ም. የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት ተዘጋጅቶ ተግባር ላይ ሲውል በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ ሁለት ምክር ቤት ፓርላማ ተቋቋመ፡፡ ምክር ቤቶቹ የሕግ መወሰኛና የሕግ መምሪያ በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ ሆኖም ሕዝቡ መማክርቱን (ማለትም የምክር ቤቶቹን አባላት) የመምረጥ መብት አልነበረውም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 መሠረት፤ ‘‘የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላትን ሕዝቡ ራሱ በቀጥታ መምረጥ እስከሚችል ድረስ እስከተወሰነ ዘመን ድረስ አማካሪዎቹ በመኳንንቶችና በሀገር ሽማግሌዎች ይመረጣሉ፡፡” ሕገ መንግሥቱ ይህን ቢደነግግም የምርጫው የበላይ አስተናባሪ ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው ነበሩ፡፡ ይህ የምርጫ ሥርዓት በጣሊያን ወረራ ሳቢያ ተስተጓጐለ እንጂ ከ1924 እስከ 1934 ዓ.ም. ድረስ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡
በ1935 ዓ.ም. ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሳይደረግ አዲስ አሰራር ሥራ ላይ ዋለ፡፡ በአዲሱ አሠራር መሠረት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላት በንጉሡ መመረጣቸው ቀርቶ ከየጠቅላይ ግዛቱ ወረዳዎች የተውጣጡ አምስት አምስት ተመራጮች በጠቅላይ ግዛት ደረጃ ተሰባስበው አምስት ተመራጮችን እንዲመርጡና ለምክር ቤት ውክልና ወደ አዲስ አበባ እንዲልኩ ይደረግ ጀመር፡፡ በዚህ መልክ ተመርጠው የተወከሉት የፓርላማ አባላት እስከ 1949 ድረስ ለ15 ዓመታት በአማካሪነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
በ1948 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ተደረገ፡፡ በ1948ቱ ሕገ መንግስት መሰረት ሕዝቡ ተወካዮቹን (እንደራሴዎቹን) ራሱ እንዲመርጥ ተፈቀደ፡፡ መራጮች ዕድሜአቸው 21 ዓመትና ከዚያ በላይ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የኖሩና በትውልድ ኢትዮጵያዊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
ተመራጮች ደግሞ ዕድሜያቸው 25 ዓመትና ከዚያ በላይ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የኖሩ፣ ዋጋው ከብር ሁለት ሺህ ያላነሰ ተንቀሳቃሽ ንብረት ወይንም ብር አንድ ሺህ የሚገመት የማይንቀሳቀስ ንብረት ያላቸው፣ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ፣ እዳ የሌለባቸውና በትውልድ ኢትዮጵያዊ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መምረጥም ሆነ መመረጥ ለሁለቱም ፆታዎች እኩል የተፈቀደ ነበር፡፡ በዚህ አግባብ የተመረጡት የየጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴዎች እስከ የካቲት 1966 አብዮት ድረስ አገልግለዋል፡፡ በእነዚህ 18 ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ በየአራት ዓመቱ አምስት ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡
- ምርጫ በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (1967 – 1979)
ከ1967 እስከ 1979 ዓ.ም. ድረስ በሀገራችን ምንም ምርጫ አልተካሄደም፡፡ በ1967 የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሥልጣን ሲይዝ የዘውዳዊው ሥርዓት ሕገ መንግሥት ታግዶ፣ ፓርላማው ተበትኖ፣ አስተዳደሩ በጊዜያዊነት ተሰየመ፡፡ በጥቅምት 1967 በፓርላማው ምትክ የመማክርት ጉባዔ ተቋቋመ፡፡ የጉባዔው አባላት 60 ሲሆኑ ከተለያዩ ወታደራዊ ክፍሎችና መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ነበሩ፡፡ የመማክርት ጉባዔ ስራ ላይ የነበረው እስከ 1978 መገባደጃ ድረስ ነበር፡፡ በ1979 ዓ.ም. የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ራሱን ወደ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ሕ.ዲ.ሪ.) ቀየረ፡፡ በአዋጅ ቁጥር 314/1979 አማካይነት ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ተቋቁሞ የኢ.ሕ.ዲ.ሪ. መንግሥት ተመሠረተ፡፡
- ምርጫ በኢሕዲሪ መንግሥት (1980 -1983)
ጥር 24 ቀን 1979 ዓ.ም. የኢ.ሕ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት ጸድቆ በዓመቱ መጨረሻ ብሔራዊ ሸንጎ በመባል የሚታወቅ ምክር ቤት ተቋቋመ፡፡ ሸንጎው 835 አባላት የነበሩት ሲሆን የሥራ ዘመኑ አምስት ዓመት ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሀገሪቱ በአስተዳደር አካባቢዎችና በራስ ገዝ አካባቢዎች ተከፋፍላ ተዋቀረች፡፡ የብሔራዊ ሸንጎው አወካከል በሕዝብ ቁጥርና በብሔረሰብ ላይ የተመሰረተ ነው ቢባልም አመራረጡ ድርጅታዊ በመሆኑ ተአማኒና ሕጋዊ አልነበረም፡፡
የሸንጎው አባላት (ወይንም የሕዝብ እንደራሴዎች) ምርጫ የጥር 1979ን ሕገ መንግሥት ተከትሎ በወጣው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ አዋጅ ቁጥር 23/1980 አማካይነት የተካሄደ ነበር፡፡ ምርጫው የሚከተሉትን አራት የምርጫ መሠረተ-ሐሳቦችን አካትቶ የያዘ ነበር፡፡
- ያለምንም አድልዖና ልዩነት (የብሔረሰብ፣ የጾታ፣ የዘር፣ የቀለም፣ የሃይማኖትና የሥራ ዓይነት) ሁሉም ዜጋ በምርጫ ይሳተፋል፣
- በየደረጃው ለሚካሄድ የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ እያንዳንዱ መራጭ አንድ ድምፅ ብቻ ይኖረዋል፤ እያንዳንዱም ድምፅ እኩል ዋጋ ይኖረዋል፣
- ምርጫው ቀጥተኛ ሆኖ በግምባር በመቅረብ አንድ ጊዜ ብቻ ይከናወናል፣
- ምርጫው ሚስጥራዊ የድምፅ አሰጣጥ ስርዓትን ይከተላል፡፡
ለብሔራዊ ሸንጎ የሚወዳደሩ እጩዎችና መራጮች በትውልድ ኢትዮጵያዊ፣ ከአእምሮ ሕመም ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠና በፍርድ ቤት ውሳኔ ቅጣት በመቀበል ላይ ያልሆኑ መሆን አለባቸው፡፡ በተጨማሪም የመራጮች ዕድሜ 18 ዓመትና ከዚያ በላይ፤ የተመራጮች ዕድሜ ደግሞ 21 ዓመትና ከዚያ በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ መራጮች የምርጫ ጣቢያው ኗሪ መሆናቸው ብቻ የግድ ሲሆን ተመራጮች ግን በሚመረጡበት አካባቢ ቢያንስ ለአምስት ዓመታት የኖሩ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የመምረጥና የመመረጥ መብት ለሁለቱም ጾታዎች እኩል ክፍት ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በ1979ኙ ሕገ መንግሥት መሰረት፤ ‘‘እጩዎችን መጠቆም የሚችሉት የኢሠፓ አባላት፣ ሕዝባዊ ድርጅቶችና ወታደራዊ ክፍሎች ብቻ ነበሩ፡፡ የሕዝባዊ ድርጅቶች አመራር አባሎችና የወታደራዊ ክፍሎች አመራሮች በኢሠፓ አመራር የተመሰረቱና የሚንቀሳቀሱ ስለሆኑ ዞሮ ዞሮ የእጩዎች ጥቆማ የሚደረገው በፓርቲው ብቻ ነበር፡፡” በመሆኑም የምርጫው ሂደት እንዳሳየው የኢ.ሕ.ዲ.ሪ. ምርጫ የአንድ ፓርቲ ድርጅታዊ አሠራር ተግባራዊ የሆነበት ነበር፡፡ እጩውን የሚጠቁመው የኢሠፓ አባል፣ በእጩነት የሚቀርቡት የኢሠፓ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት፣ አስመራጩ የኢሠፓ አባል፣ ተመራጩም የኢሠፓ አባል ነበር፡፡
- ምርጫ በሽግግር መንግሥት
ከኢ.ሕ.ዲ.ሪ. መውደቅ በኋላ ከግንቦት 24 እስከ ግንቦት 28/1983 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደው ‘‘የኢትዮጵያ ሰላማዊ የሽግግር ጉባዔ” አማካይነት የሽግግር መንግሥት ተመሰረተ፡፡ የሽግግር መንግሥቱ የሚመራው በቻርተር ሆኖ በእርሱ መሰረት የተወካዮች ምክር ቤትና የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቋቋሙ ተደረገ፡፡ የሽግግር መንግሥቱ የተወካዮች ምክር ቤት ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጡ 86 አባላት ነበሩት፡፡ በወቅቱ በቻርተሩ መሠረት የሚከተሉት አራት ዋና ዋና ተግባራት ተከናውነዋል፡-
- የብሔራዊ ክልሎችን መስተዳድር ምርጫ ለማመቻቸት አዋጅ ቁጥር 9/1984 ተዘጋጅቶ ወጥቷል፤
- የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 11/1984 ተዘጋጅቶ ወጥቷል፤
- በወረዳና በቀበሌ ደረጃ የጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚቴ አባላት ምርጫ ተከናውኗል፤
- የብሔራዊ ክልሎች የክልልና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ተካሂዷል፡፡
ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሚሽን በአዋጅ የተሰጠው ሓላፊነት የሽግግር ዘመኑን የክልልና የወረዳ ምክር ቤት አባላት ምርጫን ማስፈጸም ነበር፡፡ በአዋጅ ቁጥር 11/1984 መሠረት ለመራጮችና ለተመራጮች እንደ መስፈርት የተቀመጡት ሁኔታዎች ወቅታዊ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት ቀደም ካሉት መስፈርቶች የተወሰኑ ልዩነቶች ነበሩባቸው፡፡ ለምሳሌ መራጮች በዜግነት ኢትዮጵያዊ፣ ዕድሜያቸው 18ና ከዚያ በላይ፣ ከምርጫው እለት አስቀድሞ ከሁለት ዓመት በላይ የኖሩ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
በፖለቲካ ርምጃ ፍራቻ፣ በትጥቅ ትግል ሳቢያ፣ በሥራ ወይንም በትምህርት ከምርጫ ክልሉ ተለይተው የቆዩ ዜጎች በመራጭነት ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ ተመራጮችም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊ የሆኑ፣ የብሔራዊ ክልሉን ቋንቋ የሚያውቁ፣ ዕድሜያቸው 21 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ፣ በእጩነት በሚወዳደሩበት የምርጫ ጣቢያ ለአምስት ዓመት መደበኛ ኗሪ የነበሩ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ልክ እንደ መራጮች ሁሉ በፖለቲካ ርምጃ ፍራቻ፣ በትጥቅ ትግል ሳቢያ፣ በሥራ ወይንም በትምህርት ከምርጫ ክልሉ ተለይተው የቆዩና እጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡ ዜጎችም የኗሪነት ቅድመ-ሁኔታን እንዳሟሉ ተቆጥረው በተወዳዳሪነት ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ ሆኖም እጩ ተወዳዳሪዎች ለወረዳ ምክር ቤት የሚወዳደሩ ከሆነ የ50 ሰዎችን፣ ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ከሆነ የ350 ሰዎችን የድጋፍ ፊርማ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
- ምርጫ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ፌ.ዴ.ሪ.)
የምርጫ ኮሚሽን የተቋቋመበትን ተልዕኮ አከናውኖ ከፈረሰ በኋላ በ1985 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 64/1985 አማካይነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቋቋመ፡፡ ቦርዱ በግንቦት ወር 1986 የሕገ መንግስት ጉባዔ አባላትን ምርጫ አካሄደ፡፡ የሕገ መንግሥት ጉባዔ አባላት የተመረጡት የሕዝቡን ቁጥር መሰረት በማድረግ ለ100,000 ሰው አንድ ተወካይ እንዲኖር በማድረግ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሕዝቦች በጉባዔው የሚወከሉበት አግባብ መኖር ያለበት መሆኑ ስለታመነበት የተለየ ቀመር ተዘጋጅቶ በልዩ ውክልና እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡
በቁጥር አነስተኛ ሕዝብ ያላቸው ብሔረሰቦች የተባሉት በምርጫ ክልሉ ኗሪ ሆነው [ነገር ግን] የህዝባቸው ቁጥር ከምርጫ ክልሉ ጠቅላላ ሕዝብ ቁጥር [ጋር] ሲነጻጸር [ከግማሽ] በታች ሆኖ በማንኛውም የምርጫ ክልል ላይወከሉ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ናቸው፡፡ ስለሆነም ከ10,000 ሕዝብ በላይ ያላቸው ብሔረሰቦች አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው እንደሆኑ ተደርጐ በሕገ መንግስት ጉባዔው ልዩ ውክልና እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡
ይህ የልዩ ውክልና ምርጫ በተከታታይ በተደረጉ ሌሎች ምርጫዎችም ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ከዚህ ሌላ፣ የሕገ መንግሥት ጉባዔ አባላት የተመረጡት ቀደም ሲል በሽግግር ወቅት የክልልና የወረዳ ምክር ቤት አባላት በተመረጡበት አግባብ ሆኖ የድጋፍ ፊርማው ከ350 ወደ 500 ሰዎች ከፍ እንዲል ተደርጐ ነበር፡፡
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ1985 ዓ.ም ከተቋቋመ በኋላ በ1987 በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 102 መሠረት እውቅና ተሰጥቶታል፡፡ ከዚያ በኋላ በ1987፣ በ1992፣ በ1997 እና በ1999 ዓ.ም. የምርጫ ሕጉ ማሻሻያ ተደርጐበታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚከተሉት ሦስት ዓላማዎች አሉት፡፡
- አንደኛው ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ምርጫ በማካሄድ በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ ሲሆን፤
- ሁለተኛው ሕገ መንግሥቱንና በሕግ የተመሰረቱ ተቋማትን የሚያከብሩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች በእኩልነትና ያለአድልዖ የሚወዳደሩበት የምርጫ ሂደት መኖሩን ማረጋገጥ ነው፤
- ሦስተኛው ዜጎች በሕገ መንግስቱ በተጎናጸፉት የዴሞክራሲ በተለይም ደግሞ የመምረጥና የመመረጥ በነፃነትና በእኩልነት እንዲጠቀሙ ማድረግ ነው፡፡
ይቀጥላል…
ተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)፣ ‘የሕዝብ አስተያየት ጥናት’ ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ/ሪሰርቸር ሲሆኑ፣ እንዲሁም ‘የታሪክ ጥናትና የቅርስ አስተዳዳር’ ባለሙያ ናቸው፡፡
ዋቢ መጻሕፍት
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን 5ኛ ዙር አካባቢያዊ እና 6ኛ ዙር አገራዊ ምርጫ በተመለከተ የተካሄደ ‘የሕዝብ አስተያየት ጥናት’፣ ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት፣ ግንቦት፣ 2011 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የተወካዮች ምክር ቤት (1987) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት፣ ፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ አንደኛ ዓመት፣ ቁጥር 1፣ አዲስ አበባ፤
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (2003) የመራጮችና የሥነዜጋ ትምህርት ማሰልጠኛ ማኑዋል፣ አዲስ አበባ፤
Cowen, Michael and Liiasa Laakso (eds.) Multi-party Election in Africa. Oxford: James Curry, 2002.
Clapham, Christopher. Haile Selassie’s Government, London: Longman, 1969.
National Electoral Board, Election Officers Manual, Addis Ababa, 2000.