>

ኢትዮጵያ የአባይ ስጦታ ኪሮስ ነጋ (አዲስ አበባ)

ኢትዮጵያ የአባይ ስጦታ

ኪሮስ ነጋ (አዲስ አበባ)


በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ተጠቃሚ የሆኑ ብዙ ሀገሮችን በኢኮኖሚ በማኅበራዊና በአንዳንዶቹ ሀገሮች ደግሞ በፖለቲካውም  ሲደጋገፉ ይታያል፡፡ በአንዳንዶቹ ሀገሮች ባህል ደግሞ አንድ ውኃ የሚጠጡ ሕዝቦች፣ በአንድ ተሻጋሪ ውኃ በለሙ ሰብሎች  የሚመገቡ እና ፈጣሪ በውኃ ያስተሳሰራቸው ሕዝቦች ስለሆኑ ሲደጋገፉ ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ በሱዳን እና በግብጽ መካከል እየተካሄደ ያለውን መስመሩን ካለፈ ስስትና ስግብግብነት የመነጨ እሰጥ አገባ ስንመለከት እጅግ አሳዛኝ እና አሳሳቢ የሆነ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደሆነ እንታዘባለን፡፡ አባይ ግብጽና ሱዳንን ለዘመናት ያለማንም ተቀናቃኝ ሲጠቀሙበት እንደነበር ዓለም ሁሉ የሚያውቀው ሃቅ ነው፡፡ ለዕውቀት እንዲሆነን የውኃውን 86.4% የምታዋጣው ሀገር ኢትዮጵያ ነች፡፡ ከዚህ ውኃ የረባ ጥቅም የማታገኘው ደግሞ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያ ማንንም ከሳ አታውቅም፡፡ ዕድገቷ በፈቀደላት መጠን በውስጥ ባሏት ወንዞች ብቻ ስትጠቀም ኖራለች፡፡ ዛሬ ደግሞ የሕዝቧ ቁጥር እየበዛ፣ የፍላጎት መጠኑም እያደገ ሲሄድ ውኃዋን መጠቀም እንደሚገባት አምና በዚያ አቅጣጫ ጥረቷን ቀጥላለች፡፡ መንግሥታት ሕዝባቸው ለዕድገት የሚያደርገውን መነሳሳት በመደገፍና በማስተባበር ውጤታማ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለማንም ድጋፍ በራስ ተነሳሽነት ከልሂቅ እስከደቂቅ ተነሳስቶ የኅዳሴ ግድብን በመገንባት 40% የነበረውን ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነት ወደ 80% ለማሳደግ ሀገራችን አቅዳ እየሠራችበት ነው፡፡ ይህ ግድብ ሲገነባ የኢትዮጵያን ሕዝብ ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀይረው ይታመናል፡፡ ግድቡ የሚይዘው ውኃ ግብጽ የናስር ኃይቅ በክረምት ሲሞላባት በአሸዋ ላይ ያለምንም ጥቅም የምታፈሰውን ውኃ አያህልም፤ ወይም ግብጾች የጎልፍ መጫወቻ ሜዳዎቻቸውን የሚያጠጡበትን ውኃ አያህልም፡፡ ግን ግብጽ ለምንድነው በጠረጴዛ ዙሪያ የሚፈታን ጉዳይ እያመሰቃቀለችው ያለችው?

  1. የግብጽ መሪዎች ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጋር ሆነው ከዓለም አቀፉ ህግ ውጭ ኢትዮጵያን የገዛ ውኃዋን ከመጠቀም ማስቆም ይችላሉ?
  2. ውኃው ሱዳንን አቋርጦ የሚሄድና በየጊዜው በውኃ እየተጥለቀለቀች መቸገሯ እየታወቀ፣ እንደ አጋጣሚ ውኃው ካነሰ ግብጽ ውኃውን ትቀማናለች ብለው ፈርተው ይሆን? ለመሆኑ ኢትዮጵያ በሱዳን ሕዝብ ትጨክናለች ብለው አስበውስ ይሆን?
  3. ግብጽ ስንት ግድብ ሠርታ እስክትጨርስ እና ስንት ትሪሊዮን ሊትር ውኃ ተጠቅማ የመስኖ ልማት ሠርታ እስክትጨርስ ነው ኢትዮጵያና ሱዳን እየተራቡ የሚጠብቋት?
  4. ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ድንበር በጋራ በውይይት እንከልለዋለን በሚል ተስማምተው በየጊዜው ይወያያሉ ተብሏል፡፡ የሱዳን መሬት የሆኑት ሃላይብና ሻላቲን ዛሬ በማን እጅ ነው ያሉት? መሞት ካስፈለገ 30 ከተሞች በውኃ የተጥለቀለቁባትና  ከ500,000 በላይ ሱዳናዊያን የተፈናቀሉባት ዛሬ ግብጻውያን የኛ ሆኗል የሚሉትን የራሳቸውን ግዛት ማስመለስ አይቀልም ነበር? 
  5. ኢትዮጵያ ውስጥ  ድርቅ ከተከሰተ የዝናብ እጥረት አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ  ወደ ሱዳን እና ወደ ግብጽ የሚሄድ ውኃ ከየት ይመጣል? 
  6. በግድቡ መገንባት ምክንያት ግብጽ ወደጦርነት ብታስገባን ከዚያ በኋላ በውኃ ላይ ውይይት ይኖራል? ወደግብጽና ሱዳን የሚፈስ ውኃስ ይኖራል? ከፈሰሰስ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውል ንጹሕ ውኃ ይገኛል? ሸርና ተንኮል ከተፈለገ ይህን ወንዝ በተለያዩ ነገሮች መበከልስ ያስቸግር ይሆን?
  7. ማንኛውም ሀገር በግዛቱ የሚገኙ ድምበር የማያቋጡ ወንዞችን እንደፈለገው መጠቀም እንደሚችል ዓለም አቀፉ የውኃ ህግ ይደነግጋል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ክፋት ብትፈልግና ሞራላዊ ልዕልናዋ ቢያሽቆለቁል የአባይን መጋቢ ወንዞች በመከተር አባይ ከኢትዮጵያ ውጪ እንዳይፈስ አቅም እንዳይኖረውና በርሱ ምክንያት የሚንቦገቦገው እሳት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቆም ማድረግ ቀላል አይደለም? 
  8. ለመሆኑ ግብጽ ሆነች ሱዳን ለሽዎች ዓመታት በአባይ ወንዝ እንደፈለጉ ሲጠቀሙ፣ በመሸጥም በመለወጥም የልባቸውን ሲያደርሱና አስዋንን ጨምሮ በርካታ ግድቦችን በየሀገራቸው ሲገነቡ የኢትዮጵያን ፈቃድና ይሁንታ ጠይቀው ነበርን? ኢትዮጵያ ታዲያ በገዛ ውኃዋ ቢያንስ አንድ ግድብ ብትሠራና ከድህነት ለመውጣት ብትሞክር ማንን ይጎዳል? ነው ተራ ምቀኝነት ይሆን? “ኢትዮጵያ ካደገች እንዳሻን የምንጠቀምበት አባይ ፍሰቱ ሊቀንስ ይችላል” ብለው ሰግተውስ ይሆን እንዲህ በሰው መብት እየገቡ በረት በጥባጭ ኮርማ ሊሆኑ የቻሉት?
  9. በኢትዮጵያ ቦታ ግብጽና ሱዳን ቢሆኑ ኖሮ ምን ሊፈጠር ይችል ይሆን? ለመሆኑ አንዲት ኩባያ ውኃ ይልኩላት ይሆን? አሁን እነሱ እንደሚያደርጉት ለዓለም ብትጮህስ አድማጭ ታገኝ ይሆን?
  10. የግብጽን ጀብደኝነት በመሪዎቿ ዕብሪታዊ ንግግር መረዳት እንችላለን፡፡ ለምሣሌ ሰሞኑን አል ሲሲ “ለግብጽ ከተመደበው የአባይ ውኃ አንዲት ጠብታ ኢትዮጵያ ከተጠቀመች ወይ ወደ ግድቡ ካስገባች ቀይ መስመር እንዳለፈች ቆጥረን አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ዝተዋል፡፡ ይህ ማንን ይጠቅማል? ትብብርንና የወዳጅነት መንፈስን የሚያደበዝዝ ይህን መሰል ንግግር ከመናገር መቆጠብ ይበልጥ የሚጠቅመው ማንን ነው? ይህ ዓይነቱ ዛቻ ሌሎች የተፋሰሱ ሀገሮችንስ አያስበረግግም ወይ? ግብጽ ኢትዮጵያን እንዲህ ለማስፈራራት ያበቃት ምን ይሆን? “ከሳሽ የተከሳሽን መልስ ቢያውቅ ከቤቱ ባልወጣ” ይባላል፡፡ መናገር ቀላል ነው፤ የተናገሩትን መተግበር ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ የውኃን ፍሰት መቆጣጠር የሚቻለው ደግሞ በጥበብና ውል ባለው ድርድር እንጂ በሚሳይልና በጠበንጃ ጩኸት እንዳልሆነ መገንዘብ ብልኅነት ነው፡፡

 እስኪ ከላይ በጠቀስኳቸው መወያያ ርዕሶች ላይ አሁን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አየተፈጠረ ያለውን አዳዲስ አስተሳሰቦች መሠረት አድርገን እንመልከታቸው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለተፋሰሱ ሀገራትና ለዓለም ሕዝብ በተደጋጋሚ በግልጽ ለማስረዳት እንደሞከሩት የአባይን ግድብ የሚገድበው ሀገሪቷ ለዕድገቷ መሠረት ከሆኑት አንዱ የሆነውን የመብራት ኃይል የመጠቀም እና በዝቅተኛ ደረጃ የሚኖረውን ሕዝብ ኑሮ ለማሻሻል ነው፡፡ እንጂ ግብጽንና ሱዳንን ውኃ ለመከልከል አይደለም፤ የመከልከል ፍላጎትም ሆነ ዕቅድ ደግሞ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከኅሊና ፍርድና ከሞራል አኳያም ብቻ ሣይሆን ኢትዮጵያም ሆነች ሕዝቧ ከዓለም አቀፍ ህግጋት ውጪ ሊሆኑ አይችልምና፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥትና ሕዝብ ባላቸው የወል ተነሳሽነት ግድቡን ከማንም ብድር ሳይጠይቁ መገንባት ጀምረዋል፡፡ ይህም ጅምር እንደሚጠናቀቅ ምንም ጥርጥር የለንም፡፡ እዚህ ላይ ኢትዮጵያ ይህንን ግድብ ስትገድብ የዓለም አቀፉን ህግ አክብራ እንደምትገነባ ለሁሉም ማሳወቅ ግዴታ ባይኖርባትም ለትብብር እና ለግልጽነት ስትል በየጊዜው አሳውቃለች፡፡ በዚህ መመስገን ሲገባት እንዲያውም ግንባታው ቆሞ እንወያይ ወይም አለፍ ሲሉ ደግሞ ግድቡ እኛ ሳናውቅ እንዳይገነባ፤ ይህ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ውኃው እንዳይሞላ፤ ቆየት ብለው ደግሞ ቴክኒካል ችግር አለበት … ወዘተ. ይሉናል፡፡ አሁን ደግሞ በጦርነት ለማስፈራራት መሞከር ጀምረዋል፡፡ ለነገሩ የሚፈራ የለም እንጅ እነዚህ አካሄዶች የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት “የኛ ነው” ከሚለው አስተሳሰብ እየወጣ “የኔ ነው” ወደሚለው እየገፋው ሄዷል፡ ስለሆነም በቀጣይ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን ህግ በማክበር የታችኛዎቹን ተፋሰስ አገሮች በማይጎዳ ሁኔታ ግድቧን ገንብታ ታጠናቅቃለች፡፡

የአባይ ውኃ ሱዳንን አቋርጦ ነው ወደ ግብጽ የሚደርሰው፡፡ ግብጽ ያንን ሁሉ ግድብና የመስኖ ልማት እየሠራች ያለችው በሱዳን አልፎ በሚሄደው ውኃ ነው፡፡ ከተለያዩ መረጃዎች እንዳረጋገጥኩት በኢትዮጵያ የክረምት ወራት የሚዘንበው ዝናብ ከወትሮው ከጨመረ  ሱዳን ለዘመናት በውኃ ስትጥለቀለቅ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህንን ብዛት ያላቸው የሱዳን ምሁራን ሲያረጋግጡት ነበር፡፡ ታዲያ አሁን ከአሥር ዓመት በኋላ ምን የሚሉት ችግር ተፈጠረ? ቀደም ባሉት ዓመታት ሱዳናውያን  ለኢትዮጵያውያን “ግድቡ ለኛም ጥቅም ስለሆነ ተጋግዘን እንገድበው” ሲሉ አልነበረም? በዓለም እንደዚህ ያለ ተለዋዋጭ ባሕርይ ያላቸው መሪዎች ያሉባቸው ሀገራት ታይተው አያውቁም፡፡ በተባራሪ ወሬ እንደሚሰማው ግብጽ ለአልቡርሃንና ለሳቸው ጓደኞች ደጋግማ ወደሀገሯ እየጠራች “ኢትዮጵያን በኦፊሴል ከተቃወማችሁ ይህንን ያህል ዶላር፤ ግጭት ከፈጠራችሁ ተጨማሪ ይህንን ያህል ዶላር ፤ የመሬት ወረራ ካደረጋችሁ እና ይህንን ማድረጋችሁ በግብጽ ባለሙያዎች ከተረጋገጠ የሱዳን ሕዝብ እንዳይጠራጠር ታንኮች የነብስ ወከፍ ጠብመንጃዎች እና አስፈላጊ ከሆነ ሌላም ድጋፍ ይጨመርላችኋል” ስለሚባሉና በተጨማሪም “ድንገት የሱዳን ሕዝብ ከተጠራጠረ ወይም በሥልጣናችሁ ላይ ችግር ከተፈጠረ ግብጽ ድጋፍ እንደምታደርግ፣ ነገር ግን ሕዝቡ ካሸነፋችሁ ግብጽ መጥታችሁ ለመኖር የሚያስችላችሁ የመኖሪያ ፈቃድ እንደሚሰጣችሁ፣ ካልፈለጋችሁ አሁን የምንሰጣችሁን ገንዘብ እናንተ ወደምትፈልጉት ሀገር ልናሸጋግርላችሁ እንችላለን” በሚል ስምምነት አንደኛውንና ሁለተኛውን ክፍያ የተቀበሉ መሆናቸው በውስጥ ዐዋቂዎች የሚነገር ሲሆን አሁን ለሦስተኛው ክፍያ እየሠሩ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ለዚህም አል ሲሲ ሱዳን ድረስ መጥተው ቼኩን እንደሚያስረክቧቸው፣ ለይምሰል ግን “የጋራ ስምምነት እንፈራረማለን” በማለት የሤራ ስምምነታቸውን ተግባራዊ እንዳደረጉ ይነገራል፡፡ ነገር ግን የሱዳን ሕዝብ ኤርፖርት ድረስ በመሄድ ተቃውሟቸውን በማሰማት ለሁለት ቀን የመጡትን አል ሲሲ በግማሽ ቀን እንዲሸሹ አድርገዋቸዋል፡፡ ይህ የሕዝቡ ከመንግሥት በልጦ መገኘት ሱዳንና ኢትዮጵያ ያላቸውን ነባር ሰላማዊና ወንድም-እህታዊ ግንኙነት ያሳያል፡፡ የሚያሳዝነው አሁን ለሱዳን ባለሥልጣናት የተከፈላቸው ትንሽ የገንዘብ መጠን በግብጽ እና በሌሎች ሀገሮች ያስቀመጠችላቸው ጉቦ ጠቀም ያለ ቢሆን ጓጉተው ነው ይባል ነበር፤ ነገር ግን  ለማይረባ ገንዘብ  ብለው የሱዳንን ሕዝብ በማይመለከተው  ጉዳይ ለሌላው ሀገር ሲባል  በቅጥር ነፍሰ ገዳይነት ለማሰለፍ ቋምጠዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አልቡርሃን  የመሬት አቀማመጡን ግብጽ እኔ ከላይ ልሁን ሱዳን ደግሞ አሁን ግብጽ አለችበት አገር ቦታ እታች ትሁን ቢሏቸው  እምቢ እንደማይሉ አልጠራጠርም፡፡ ገንዘብ የማይሠራው የለም፡፡ ለዚህም ነው “ገንዘብ የተሸከመች አህያ የማትደረምሰው ግምብ የለም” የሚባለው፡፡

የአባይን ውኃ ግብጽ ለዘመናት በብቸኝነት ስትጠቀምበት እንዳልነበረ ሁሉ አሁን የግድቡን ግንባታ አቁመን ቁጭ ብለን እንድንወያይ ትፈልጋለች፡፡ እኔ የሚገርመኝ የኢትዮጵያ የትግስቷ ብዛት ነው፡፡ ይጠና ተባለና የግብጽ ባለሙያዎች ባሉበት በጋራ በተመረጡ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ተጠንቶ ግድቡ ከጉዳት ይልቅ ጥቅም ነው ያለው ሲባል ግብጽ አልቀበልም አለች፡፡ በተፋሰሱ ሀገሮች ውይይቶች ለመስማማት አልቻለችም፤ አንዴ አሜሪካ አንዴ አፍሪካ በማለት ውኃ የማይቋጥር ምክንያት እየደረደረች ጊዜ ትገዛለች፡፡ መልሳ ደግሞ ሊታሰብ የማይቻል እና መፍትሔ የማያመጣ አስገዳጅ ውል ኢትዮጵያ ትፈርም ትላለች፡፡ በማን ውኃ ነው ኢትዮጵያ ግዴታ ውስጥ የምትገባው? 86.4% ውኃ የምታበረክተው ሀገር ብቻየን ልጠቀምበት ከሚል ገብጋባ አቋም ውጪ ምንም ዓይነት የውኃ አስተዋፅዖ ከማታደርግ ሀገር ጋር ወደ ስምምነት ለመድረስ በቀናነት ጊዜዋንና ገንዘቧን ስታወጣ ከረመች፡፡ ለቀጣይ ዓመታት  በአካባቢው ዝናብ እንዳይቋረጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎች በየዓመቱ ኢትዮጵያ ትተክላለች፡፡ ግብጽና ሱዳን ግን እንዲያው ምን እንርዳ እንኳን አይሉም፡፡ ግብጽ ክፍተኛ የሆነ የከርሰ ምድር ውኃ ካላቸው ሀገሮች አንዷ ነች፡፡ ከዚህም በላይ ከግምሽ በላይ የሆነው የግብጽ መሬት ከሜዲትራንያንና ከቀይ ባህር ጋር የተያያዘ ስለሆነ ባሕሩን አጣርቶ ለመጠቀም የሚያስችል አቅም አላት፡፡ ታዲያ ግብጽ በምን ሂሣብ ነው ውኃ ልጠማ ነው የምትለው? ነገሩ “ሳታመካኝ ብላኝ” እንደተባለው የአህያና የጅብ ታሪክ ነው፡፡

በሌላ በኩል .ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ድንበር ጊዜ ወስደን በጋራ በስምምነት እንካለለዋለን በሚል ተስማምተው በየጊዜው ይወያያሉ፡፡ ይህ ማለት አባይ የጋራችን ነው ለማለት ነው፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው መለስተኛ ግጭት አጋጣሚውን ተጠቅማ ሱዳን በአሁኑ ጊዜ የድንበር አካባቢ መሬቱን ወርራ “የኔ ብቻ ነው” በማለት በአካባቢው የነበሩትን ኢትዮጵያውያን በማፈናቀልና በመዝረፍ እንዲሁም በመግደል ይቅር የማያስብል ክህደት ፈጽማለች፡፡ ለመሆኑ የሱዳን መሬት የሆኑት ሃላይብና ሻላቲን ዛሬ በማን እጅ ነው ያሉት? እነዚያን ማስመለስ አይቀድምም?  

ሌላው ወደስምምነት እንዲገባ የሚፈለገው ድርቅ ሲሆን ኢትዮጵያ የግድቡን ውኃ ትልቀቅ የሚል የሞኝ ጥያቄ ነው፡፡ በመሠረቱ  ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ ከተከሰተ የዝናብ እጥረት አለ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ  ወደ ሱዳን እና ወደ ግብጽ የሚሄድ ውኃ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ነው፤ ከየት ይመጣል? ነው ወይስ ህልም ተፈርቶ እንዲሉ ለዚህ ሲባል ግድብ መሥራቱ ይቁም ማለታቸው ነው?

ለማጠቃለል ያህል ቀደም ሲል እንደገለጽኩት በግድቡ መገንባት ምክንያት ግብጽ ሱዳንን በመላክ ወይም ከጀርባ በመደገፍ ከኢትዮጵያ ጋር ወደጦርነት ብታስገባን ከዚያ በኋላ በውኃ ላይ ውይይት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ወደግብጽና ሱዳን የሚፈስ ውኃም ይኖራል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ አንድ ነገር ከደፈረሰ ብዙ መዘዝ አለው፡፡ ስለዚህ የሚያዋጣው ከራስ ወዳድነትና ከስግብግበነት ተቆጥቦ የውኃ ባለይዞታዎችንም መብትም አክብሮ አባይን በጋራ መጠቀም ነው፡፡ ገንዘብ ወይም ጉልበትና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት አለኝ በሚል ከንቱ ዕብሪትና ትምክህት በሰው ሀገር መብት ጥልቅ እያሉ መፈትፈት የኋላ ኋላ የሚያስከትለው ጣጣ አለና ከወዲሁ መጠንቀቁ አይከፋም፡፡ ኢትዮጵያም መብቷንና ጥቅሟን ለማንም አሳልፋ የማትሰጥና ቁርጥ ቀን ሲመጣ ከየቀያቸው ግር ብለው የሚወጡ ሣተና ልጆች እንዳሏት ከታሪክ ጭምር መማር ተገቢ ነው፡፡

Filed in: Amharic