“ለእነዚህ ንጹሃንና ምስኪኖች ርህራሄ ይኖራችሁ ይሆን…?!?
ጋዜጠኛ ፍስሐ ተገኝ
የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ አቅም ወይም ፍላጎት የሌለው መንግስት መንግስት ከመባል ይልቅ የህግ ከለላ ያለው ወንበዴ ቢባል ይሻላል!!!”
በ1976-77 ዓ.ም ከቀድሞው ላስታ አውራጃ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በግዳጅ ተወስደው እንዲሰፍሩ ከተደረጉት ላስቴዎች መካከል እኔና እናቴ እንገኝበታለን፡፡ በወቅቱ በነበሩት የገበሬ ማህበራት አማካኝነት ከየአካባቢው ቤተሰቦች እንዲመረጡ ከተደረገ በኋላ እኛም ወደ ሌላ ቦታ ተወስደው እንዲሰፍሩ ከተወሰነባቸው መካከል በመሆናችን እኔ፣ እናቴና እኛን ለመሸኘት በሚል የእናቴ ወንድም አጎቴ ሆነን ከገጠሯ ‘ብርግነት’ ‘ሰማይ ቀበሌ’ ጎጥ ተነስተን ጉዟችንን ወደ ሙጃ ከተማ አደረግን፡፡
ወደ ሙጃ ስንሄድ ከብርግነት እስከ ሙጃ ድረስ በእግር ከሁለት ሰአት በላይ ስለሚወስድ አጎቴ እኔን እሽኮኮ አድርጎ ያንን ተራራና ሸለቆ ወጥተንና ወርደን ሙጃ ደረስን፡፡
ሙጃ ስንደርስ አሁን ‘ሶስት ጎዳና’ የሚባለው አካባቢ ከተለያዩ የአካባቢያችን ጎጦች የመጣው የሕዝብ ማዕበል ጎዳናውን ሞልቶት ስለነበር የአቧራው ጢስ ላይ የህብረተሰቡ ዋይታና ለቅሶ ተጨምሮበት በቅርበት ያለ ሰውን እንኳን ማየት ያስቸግር ነበር፡፡ ሙጃ ላይ ከተሰባሰብን በኋላ ያ ሁሉ ወዴት እንኳን እንደሚወሰድና የትኛው ምድር ላይ እንደሚያርፍ የማያውቅ ሕዝብ ጋር ሆነን በወታደሮች ታጅበን ሙጃን ለቀን በእግር ወደ ኩልመስክ ጉዞ ጀመርን፡፡ አጎቴ ከእኔና ከእናቴ ጋር መሄድ ስለማይችል ከእህቱ ጋር ተላቅሰው፣ እኔንም እቅፍ አድርጎ እያለቀሰ ተሰነባብቶን ሄደና ተለያየን፡፡
እናቴ አልፎ አልፎ እኔን እያዘለች፣ መንገዱና ጸሃዩ ሲያደክማት ደግሞ አውርዳኝ እጄን ይዛ አብሬያት ከጎኗ እየተራመድኩ ከአካባቢያችን ሕዝብ ጋር ኩልመስክ ደረስን፡፡ ኩልመስክ ስንደርስ በርካታ የጭነት መኪናዎች ተሰልፈው ቆመው ወደነበሩበት አቅጣጫ በወታደሮቹ መሪነት ከሄድን በኋላ ስማችን እየተጠራ ወደ የምንሄድባቸው አካባቢዎች ወደተዘጋጁት የጭነት መኪኖች ሄደን እኔና እናቴ ወደ ወለጋ የሚሄደው የጭነት መኪና ላይ ተሳፈርን፡፡ በግዜው ግን ወዴት እንደሚወስዱን እንኳን ምንም መረጃ የለንም ነበር፡፡ መንገድ ላይ የሚሞተው የሞተበት መንገድ አቅራቢያ ያለ ዱር ውስጥ እየተቀበረ፣ የተረፍነው ደግሞ ህመማችንና የመንገዱን ስቃይ እየቻልን ከቀናት ፈታኝ ጉዞ በኋላ እንደምንም ወለጋ ደረስን፡፡ እኔና እናቴ የነበርንበት የጭነት መኪናን የሞላነውና በሌሎች በርካታ የጭነት መኪኖች ተጭነው አብረውን ወለጋ የገቡ ወገኖቻችን ቄለም የሚባለው ስፍራ ልዩ ስሙ ‘ቄጦ’ የሚባል አካባቢ ስንደርስ ሰው ይቅርና እንስሳ እንኳን የማይታይበት እልም ያለ ስፍራ ላይ በኬሻ የተበጃጀ ግዜያዊ የመጠለያ ጣቢያ ተዘርግፈን ኑሯችንን በዛው አደረግን፡፡
ጊዜያዊ የሰፈራ ጣቢያው ውስጥ የነበረው ህይወት እጅግ በጣም አስቸጋሪና ፈታኝ በመሆኑ እጅግ የከፋ ቀን በአንድ ቀን ብቻ እስከ 150 ሰው ያህል ህይወቱን በበሽታ፣ ብርሃብና በድካም አጥቶ በጅምላ የሚቀበርበት ቦታ ነበር፡፡
አቅም የነበራቸው ወጣቶችና ጎልማሶች ቦታውና የኑሮው ሁኔታ እጅግ በጣም አስቀያሚ መሆኑን በመረዳታቸው ከሰፈራ ጣቢያው ለማምለጥ ሲሞክሩ ጣቢያውን በሚጠብቁት ታጣቂዎች፣ እነሱን ካለፉ ደግሞ በየጫካው በተሰገሰጉ ሽፍቶች በጥይት እየተለቀሙ የጅብ ‘ራትና የአሞራ ምግብ ሆነዋል፡፡ ያንን ሁሉ መሰናክል አልፈው ወደየመጡበት ቀዬ የተመለሱ አንዳንድ ሰዎችን በቅርቡ አግኝቼ ሳናግራቸው ሁሉም በአንድነት የሚሉት ነገር ቢኖር “በህይወታችን ትክክለኛውን ውሳኔ የወሰንበት ቀን” የሚል ነው፡፡ እንዲህ እንዲያስቡ ያደረጋቸው እዛው በቀሩ ወዳጆቻቸውና ወገኖቻቸው ላይ በየግዜው እየደረሰ ያለውን ግፍና ሰቆቃ ስለሚያውቁ ነው፡፡
በሰፈራ ጣቢያው የተፈጠረው ተላላፊ በሽታና አስቀያሚ የኑሮ ሁኔታም ወገናችንን መግደሉን አላቆመም ነበር፡፡ በየእለቱ የሰውን ልጅ በጅምላ የመቅበሩ ሂደት እየቀጠለ ሄዶ የእኔም እናት እዛው ሰፈራ ጣቢያ ውስጥ ከዚህ አለም በሞት በመለየቷ የቄለሟ ቄጦ የምትባል ስፍራ መሬት እናቴን ጨምራ በጅምላ መቅበሯን ቀጠለች፡፡
ወደማናውቀው ስፍራ ተወስደን ህይወታችንን እንዲህ እየመራን እያለን ከጎናቸው እናት ወይም አባት የሌላቸው ህፃናትን ከሌላው የሰፈራ ጣቢያው ነዋሪ ለየት በማድረግ እዛው በአቅራቢያው ለልጆች ብቻ የሚሆን ሌላ በኬሻ የተሰራ መጠለያ ውስጥ አስቀምጦ ህፃናትን የሚረከብ ግለሰብም ሆነ በጎ አድራጎት ድርጅት እስኪመጣ ልጆችን በትኩረት መርዳት በማስፈለጉ እናቴን ያጣሁት እኔም ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት ወደተቀመጡበት መጠለያ ገባሁና እጣ ፈንታዬን መጠበቅ ቀጠልክ፡፡ እድለኛ ነበርኩና እኔና ሌሎች ወደ 50 የምንጠጋ ህፃናት የወለጋዋ ቄለምንና እናቴ የተቀበርችባት ቄጦን ለቀን ሌላ ጉዞ ጀመርን፡፡ እኔ የተወሰድኩት በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን ወደሚያሳድገው የሐረር ኤስ. ኦ. ኤስ የህፃናት መንደር ነበር፡፡
እንደኔ እድለኛ ሳይሆኑ ቀርተው የእኔ እጣ ያልደረሳቸውና እዛው ወለጋ ቄለም ውስጥ የቀሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የነበራቸው ብቸኛ አማራጭ ወዴት እየተወሰዱ እንደሆነ እንኳን ሳያውቁት ያረፉበት ጫካና ባዶ ቦታን የመኖሪያ ስፍራ አይነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግና ያሉበትን ስፍራ የህይወታቸው ቀጣይ እድሜን የሚመሩበት አካባቢ ለማድረግ የሚችሉትን አድርገው ኑሯቸውን እዛው መመስረት ነበር፡፡ ያ እንኳን ለኑሮ ይቅርና በአካባቢው እንኳን የሚያልፍ ሰው የማይገኝበት ቦታን መንደር መስርተው፣ ልጆችና የልጅ ልጆችን እያዩ ኑሯቸውን ቀጠሉ፡፡ ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው ከዛ አካባቢ ውጪ የሚያውቁት ሌላ አለም የለም፡፡ ወላጆቻቸውና አያቶቻቸውም ቢሆኑ ህይወታቸውን በስፍራው በማቅናታቸውና ባዶ የነበረን ቦታ ወደ የሰው ልጅ መኖሪያነት በመቀየር ኑሮና ሁኔታዎች አስገድደው ያስጀመሯቸው ህይወትን አምነው ተቀብለው ባረፉበት ቀዬ ለኑሯቸው የሚሆን መኖሪያ ስፍራን መስርተው መኖር ቀጠሉ፡፡
እነዚህ ስንት መከራና ችግርን አልፈው ህይወትን እየመሩ ያሉ ወገኖች ግን ህወሓትና ኦነግ የሚባሉ ጉደኞች በዘሩት አማራና ኢትዮጵያዊነትን የሚጠላ፣ ዘርን መሰረት ያደረገና የሰውን ልጅ የፖለቲካ መቆመሪያ ያደረገ ፖለቲካዊ መዋቅር ምክንያት እጅግ አስቃቂና ዘግናኝ ወንጀሎች እየተሰሩባቸው ነው፡፡
ሰላማዊ ሰውን መግደል፣ ማፈናቀልና ማሳደድ፣ ንብረቶቻቸውን ማውደም ጀግንነት የሚመስላቸው ፖለቲከኞች፣ ጠባብ ብሄርተኞች፣ ቅልብ ምሁራንና በስልጣናቸው እስካልተመጣባቸው ድረስ የሌላው ሰው ነፍስና ህልውና ግድ የማይሰጣቸው ባለስልጣናትና አመራሮች እነዚህ ምስኪን ወገኖቻችንን መቆመሪያ አድርገዋቸዋል፡፡
ስንቱን ግፍና መከራ አልፈው ካቀኑት የአገራቸው መሬት እንደ ወራሪ እየታዩና የመወያያ አጀንዳ ብቻ ተደርገው እየተቆጠሩ እንዲፈናቀሉና ተሰደው ሌላ ጫካ ውስጥ እንዲገቡ ተገደዋል፡፡ የማንም አረመኔ ፖለቲካዊ ህልም ማሳኪያ ለመሆን ተብሎ ወገኖቻችን ከራሳቸው መሬት ላይ የሚፈናቀሉበትና የሚገደሉበት ሁኔታ ማብቃት አለበት፡፡ የሃገራቸው መሬት ነው! የራሳቸው መሬት ነው! ጫካን መንጥረው ነፍስ ዘርተውበት ህይወታቸውን እየመሩበት ያሉበት፣ ልጅና የልጅ ልጆቻቸውን ያዩበት የሃገራቸውና የራሳቸው መሬት ነው! ለእነዚህ ንጹሃንና ምስኪኖች ደህንነት አቅም የሌለው መንግስት መንግስት ከመባል ይልቅ የህግ ከለላ ያለው ወንበዴ ቢባል ይሻላል፡፡
በተለይ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና በሐረር፣ በድሬ ዳዋ፣ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች በየግዜው እየተተገበሩ ያሉት ፖለቲካዊና ተያያዥ እንቅስቃሴዎች አማራን እንደጠላት የሚፈርጁና በሃገሩ እንዲሸማቀቅ የሚያደርጉ ሻጥር የሞላባቸው ተግባራት በቀጥታም ሆነ ኢ-ቀጥታዊ በሆነ መንገድ የህግና የመንግስት ከለላ ያላቸው፣ በደህንነትና የጸጥታ አስከባሪዎች አድሏዊ አሰራር የሚደገፉ ናቸው፡፡
ይሄ ግፍ እስከመቼ ነው የሚቀጥለው? መቼስ ነው የሚያበቃው?
[ከላይ ያያያዝኩት ፎቶ ወለጋ ክፍለሃገር ቄለም ቄጦ ውስጥ እያለን የተሞላ ቅፅ ነው]