>
5:13 pm - Monday April 18, 1735

ኢትዮጵያ አትፈርስም ብሎ ነገር....!!!

ኢትዮጵያ አትፈርስም ብሎ ነገር….!!!


*…   “አገሮች ያለፌደራሊዝም ዴሞክራሲያዊ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን አገሮች ያለ ዴሞክራሲ ፌደራላዊ ሊሆኑ አይችሉም” ወደሚለው ብሉይ አስተሳሰብ ይወስደናል። ከዚህም ተነስተን ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ የፌደራል አስተዳደር ካልሔደች ‘ትበተናለች’ የሚለው ስጋትም እየጨመረ እንጅ እየቀነሰ የሚሔድ አይሆንም የሚል መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን…!
 
ቅዳሜ ነሐሴ 10፣ 1983 የወጣው የ‹ኒውዮርክ ታይምስ› ጋዜጣ እህት የነበረው ‹ኢንተርናሽናል ሔራልድ ትሪቡን› የተሰኘው ጋዜጣ በወቅቱ የመንግሥት ለውጥ ላይ ስለነበረችው ኢትዮጵያ አንድ አነጋጋሪ ጽሑፍ ይዞ ወጥቶ ነበር። በወቅቱ የ‹ካርኒጌ ኢንዶውመንት› ሠራተኛ የነበሩት ፓውሊን ቤከር እና ጀምስ ክላድ ‘But Where Is Ethnic Fragmentation to Stop?’ በሚል ርእስ በጻፉት ጽሑፍ “በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን (self-determination) ጥያቄ አገሪቱን ወደ መበታተን ሊመራት ይችላል። ይህም አካሄድ 2,000 በላይ ጎሳዎች (tribes) ያሉበትን የአፍሪካ አህጉር ወደ ድሃና ጥቃቅን አገርነት የመቀየር መጥፎ ምሳሌ ሊሆን ይችላል” በማለት ስጋታቸውን የገለጹበት ነበር።
ጸሐፊዎቹ “እንግዲህ የኢትዮጵያ መበታተን የማይቀር ከሆነ ከኀይል ይልቅ በሰላማዊ መንገድ መሆን አለበት” በማለት የአሜሪካ መንግሥትን ጣልቃ መግባት ይጠይቃሉ። ይህ ከሆነ ከ21 ዓመታት በኋላ መስከረም 12፣ 2005 በወጣው የ‹ኒውዮርክ ታይምስ› ጋዜጣ ላይ የጅኦ ፖለቲካ ሊቃውንት የሆኑት ፍራንክ ጃኮብስና ፓራግ ካሃን ‘The New World’ በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ ቀጣዮቹ አዳዲስ የዓለም አገሮች እነማን እንደሆኑ ጥናታዊ ግምታቸውን ሲያስቀምጡ፤ “ኢትዮጵያ አሁን ካላት ቁመና የሚጨምርም የሚቀንስም ነገር በቅርቡ አይኖርም” በማለት ሌሎች ዐሥር ግምቶቻቸውን ያስቀምጣሉ። ይህ በብዙዎች ዘንድ ያለ ስሜት ነው። ኢትዮጵያ ትበታተናለች ብለው የሚሰጉ በአንድ በኩል፤ አይ ምንም አዲስ ነገር አይፈጠርም ብለው የሚያስቡ በሌላ በኩል ሆነው ጥያቄው የአገሪቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሁሉ እንደጥላ የሚከተል ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ሌሎች ሲያስሉ የሚያስነጥሳት ኢትዮጵያ
አሁን አሁን በሌላ አገሮች የሚከናወኑ ክስተቶች ለኢትዮጵያ ሁኔታ ምን አስተዋጽዖ/ተጽዕኖ ይኖራቸዋል? ብሎ መጠየቅ የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ስትገነጠል የኢትዮጵያ ውስጥም ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸው ቡድኖች ድርጊቱን እንደ ጥሩ ምሳሌ በመውሰድ ሲያወድሱት ታይቷል። በሌላ በኩል ስኮትላንድ ከታላቋ ብሪታኒያ ማኅበር ጋር ለመቆየት ስትወስን “መገንጠል አይጠቅም” የሚሉ ኀይሎች ድርጊቱን ሲያወድሱት ታይቷል። ሩሲያ የክሪሚያ ግዛትን ከዩክሬን “ቀምታ” ስትወስድም ሆነ በቅርቡ ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ስትወስን ከሁለቱም ወገኖች የደስታና የተቃውሞ ድምጽ ይሰማ ነበር። ይሄም በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚነፍስ የአዲስ አገር መመሥረት የፖለቲካ ነፋስ፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምኅዳር ሳይነፍስበት እንደማያልፍ ጥሩ አመላካች ነው።
ከዚህ የኢትዮጵያ ዐውድ ባለፈ ግን ሆናቴው በፖለቲካ ምሁራን ዘንድ “ዓለም ወደ አራትና አምስት መቶ ጥቃቅን አገርነት (microstates) ብትቀየር ይሻላል ወይስ በውህደት ወደ አርባና ሐምሳ አህጉር መሰል ግዙፍ አገራትነት (Giant states) ብትቀየር ይሻላል?” የሚለውን የቆየ የጂኦ ፖለቲካ ምሁራን ጥያቄ ደጋግሞ የሚያነቃቃ ነው። የኢትዮጵያውን ጥያቄ ከዚህ የጅኦ ፖለቲካዊ ጥያቄ ለየት የሚያደርገው “አገሪቱ አሁን ባላት ቁመና ትቀጥል” የሚለውም ሆነ፣ “የለም የራሴን አገር እመሠርታለሁ” የሚለው ቡድን በዋናነት ዘውግን መሠረት ያደረገና ለስሜታዊነት የቀረቡ መፍትሔዎችን ማቅረባቸው ነው።
ሦስትዮሽ የፌደራሊዝም ግንዛቤ
አገሮች ራሳቸውን በፌደራላዊ ቅርፅ ማደራጀታቸውን የተለያዩ አካላት በተለያየ ዐይን ማየታቸው የተለመደ ነው። የፌደራል የአስተዳደር መዋቅር በተገበሩ አገሮች ልኂቃን መካከል መዋቅሩ በቅርብና በሩቅ ጊዜያት ሊያመጣ የሚችለውን ተስፋና ፈተና እየመዘዙ መከራከሩም በብዙዎቹ የዓለም የፌደራል አገሮች የተለመደ ነው። ኢትዮጵያም ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት በሕገ መንግሥት ደረጃ የፌደራል አስተዳደር አዋቅራ “ወደ ፊት እየገሰገስኩ ነው” ብትልም በብዙዎች ዘንድ ይህ አወቃቀር ላይ ጥያቄ ሲነሳበት ይስተዋላል። በመሠረታዊነት አሁን ባለው የኢትዮጵያ የፌደራል ሥርዓት ላይ ከተለያዩ አካላት የሚነሱትን ጥያቄዎች/ውዳሴዎች/ትችቶች ወደ ሦስት መሠረታዊ ግንዛቤዎች ማምጣት ይቻላል።
የመጀመሪያው ሥልጣን ላይ ባለው መንግሥት እና ደጋፊዎቹ አማካኝነት የሚሰጠው አስተያየት ነው። መንግሥት እና ደጋፊዎቹ የፌደራል ሥርዓት አገሪቱን ከብተና ስጋት በማትረፍ ወደ ታላቅነት የምታደርገውን ግስጋሴ የፈጠረ ነው በማለት አሁን ላለው የፌደራል ሥርዓት ሙገሳ ሲሰጥ ማየት የተለመደ ነበር። ኢሕአዴግ ይህን ሲል እንደ ቀድሞዋ ሶቪዮት ኅብረት፣ ዩጎዝላቪያ፣ ሱዳንና ፓኪስታን ያሉ አገሮች የፌደራል ሥርዓት ዘርግተው ለምን ወደ መበታተን እና መከፈል እንደሄዱ መናገር አይፈልግም።
በኹለተኝነት የምናገኝው ግንዛቤ ደግሞ የፌደራል ሥርዓቱ አገሪቱን ወደማትመለስበት ማጥ ውስት እየከተታት ነው፤ አገሪቱንም በመበታተን ቋፍ ላይ አስቀምጧታል የሚል ሲሆን፤ የዚህ ግንዛቤ አቀንቃኞች ፌደራሊዝም ለዩጎዝላቪያና ለሶቪዮት ኅብረትም አልበጃት ከሚል መነሻ አሃዳዊ የመንግሥት አስተዳደርን ይሰብካሉ። እንደ ኢሕአዴግ ሁሉ የዚህ ግንዛቤ አቀንቃኞችም ከምሥራቅ ቲሞር እስከ ኤርትራ ያሉ አገራት በአሃዳዊ አስተዳደር ሥር ሆነው ወደ መገንጠል እንዳመሩ አያብራሩም።
በሦስተኝነት የምናገኝው ግንዛቤ በውስጡ ኹለት መሠረታዊ ቡድኖችን የያዘ ነው። የመጀመሪያው የፌደራል አወቃቀሩን እንደ መርሕ የሚቀበል ነግር ግን የፌደራል አወቃቀሩ በዋናነት ዘውግን መሠረት ያደረገ መሆኑን የሚቃወም ሲሆን፤ ኹለተኛው ደግሞ የፌደራል አወቃቀሩን እንደ መርሕ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ነገር ግን ፌደራሊዝም ያለ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የውሸት ፌደራሊዝም ነው በሚል እሳቤ ለፌደራል ሥርዓቱ የዴሞክራሲ መኖር ወሳኝ መሆኑን የሚገልጽ ግንዛቤ ነው።
እንግዲህ የኢትዮጵያ የመበታተን ጉዳይ በነዚህ ሦስት/አራት ቡድኖች ፍላጎት እና ግንዛቤ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። አንዱ የአንዱን እምነትና ዕውቀት ባለመቀበል በራሱ መሥመር ሲጓዝ የሌላውን እውነት መካዱ የማይቀር ነው። የልኂቃን እንዲህ ባለ መሠረታዊ ጉዳይ ላይ ያለመስማማት ደግሞ የአገሪቱን ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ሰዎች እውነታ አላቸው የሚያስብል ነው።
ምሥራቅ አፍሪካዊ አዲስ አገር
ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚለው ስጋት በሌላ አገላለጽ (ሰሜን) ምሥራቃዊ አፍሪካ አዲስ ሉዓላዊት አገር ይኖረዋል ወደሚለው መደምደሚያ የሚያደርስ ሐሳብ ነው። ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር ከ1990 ጀምሮ ባለፉት 28 ዓመታት ውስጥ 34 አዳዲስ አገራት ሉዓላዊ ነጻነታቸውን አውጀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የተቀላቀሉ ሲሆን፤ ከነዚህ 34 አገሮች መካከል 25 የሚሆኑት ከቀድሞዎ ሶቪዮት ኅብረትና ዮጎስላቪያ መበታተን ጋር ተያይዞ በምሥራቅ አውሮፓ፣ ባልካን እና መካከለኛው ኤሲያ አካባቢ የተፈጠሩ ናቸው። ቀሪዎቹ 9 አገሮች በተለያዮ የዓለማችን ክፍሎች የተፈጠሩ ሲሆን ከእነዚህ 9 አገሮች መካከል ኹለቱ በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው። ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን። ኹለቱም አዳዲስ የአፍሪካ አገሮች በ(ሰሜን) ምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙና ኢትዮጵያን የሚያጎራብቱ ሲሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ የራሳቸውን አዲስ አገር ለመመሥረት ለሚታገሉ ኀይሎችም እንደ ምሳሌ ሆነው የሚታዩ ናቸው። (ሰሜን) ምሥራቅ አፍሪካ እንደተለመደው ለአህጉሪቱ አዲስ አገር ይጨምርላት ይሆን? የሚለው ጥያቄ ለመመለስ አስቸጋሪ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጥናቶች መደረጋቸው ግን አልቀረም።
ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ዓለም ላይ ያሉ ትልልቅ የሚዲያ ተቋማት “ቀጣዮቹ የዓለም አዳዲስ ሉዓላዊ አገሮች እነማን ሊሆኑ ይችላሉ?” በሚል ርዕስ ባለፉት አምስት ዓመታት የዘረዘሯቸውን ግምቶች ተመልክቼ፤ አምስቱን ማለትም 1. ‹ኒውዮርክ ታይምስ› ጋዜጣ ሴፕቴምበር፣ 2012፣ 2. ‹ሊስትቨረስ ዶትኮም› ኖቬምበር፣ 2015፣ 3. ‹ዘ ኢንዲፔንደንት› ጋዜጣ ጁላይ፣ 2014፣ 4. ‹ፖሊሲ ሚዲያ› (Mic) ኦገስት 2013 እና 5. ‹ወርልድ አትላስ› አፕሪል፣ 2013 በመምረጥ “አዲስ ምሥራቅ አፍሪካዊ አገር በይፋ አህጉሩን ይቀላቀል ይሆን?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሞክሬ ከአምስቱ ተቋማት ሦስቱ “ሶማሊላንድ አዲሷ አፍሪካዊት አገር ሆና መታወቋ የማይቀር ነው” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተውኛል።
እንግዲህ በሰሜን ኤርትራ፣ በምዕራብ ደቡብ ሱዳን፣ በምሥራቅ ሶማሊላንድ ኢትዮጵያን ከበው በቅርብ ጊዜያት የተመሠረቱ አገሮች ናቸው ማለት ነው። ይህም ምሥራቅ አፍሪካ እንደ ምሥራቅ አውሮፓ ሁሉ ለዚህ ዓይነት አዲስ አገራት ፈጠራ የተመቸ መሆኑን የሳያል። ይህም በአካባቢው ያሉ አገሮች ላይ ተዛማች ተጽዕኖ (Domino Effect) ማሳደሩ አይቀርም። የኢትዮጵያ ትፈርሳለች ስጋትም ይህ አካባቢያዊ ተጽዕኖም ያለበት ነው።
ፌደራሊዝም ያለ ዴሞክራሲ
ብዙዎች አሁን ያለውን የኢትዮጵያ የፌደራል አወቃቀር እውነታነቱን ይጠራጠራሉ። አንዳንዶች “አስገንጣይ ፌደራሊዝም” (Secessionist Federalism) እያሉ የሚጠሩት ይህ አወቃቀር በዋናነት የሚቀርብበት ትችት አገሪቱን ለብተና እያዘጋጃት ነው የሚል ነው። በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የመገንጠል መብት ‘እያዩም ምን ታስቦ ነው ይህ የሆነው?’ የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ለገዥው መንግሥት ስስ ልብ አላቸው ከሚባሉት ምሁራን አንዱ የሆኑትና በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ልማትና ትምህርት ኢንስቲቲውት ፕሬዘደንት የሆኑት ዶ/ር ገላውዲዮስ አርአያ ‘Ethiopia is to Big too Fail’ ባሉት ጽሑፋቸው እና “ኢትዮጵያ ከተዋቀረችበት የረጅም ጊዜ ታሪካዊና ባሕላዊ መሠረት አኳያ የመበታተን ስጋት የለባትም” ካሉ በኋላ፤ “ነገር ግን ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል ከተፈለገ በሕገ መንግሥት ደረጃ የተቀመጠው የመገንጠል መብት ከሕገ መንግሥቱ እንዲወጣ ያስፈልጋል” ይላሉ። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ “መብቱ በሕገ መንግሥት ተቀባይነት አገኘም አላገኝም ሰዎች ጥያቄ ካላቸው የሚያስቆማቸው አካል ሊኖር አይችልም” የሚሉ ወገኖችን እናገኛለን።
ስጋቱ ኖረም፣ አልኖረም ግን አንድ መሠረታዊ ነጥብ ላይ መስማማት የሚቻል ይመስላል። የኢትዮጵያ የፌደራል አወቃቀር አገሪቱን እንዲሁ ማስቀጠል የሚኖርበት ከሆነ ዴሞክራሲ ባለበት ብቻ መሆኑ። “ፌደራሊዝም በምን ሁኔታ ነው አገራትን የሚበታትነውና የሚያዋህደው?” ብለው የሚጠይቁት የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ማሂንድራ ላዎቲ “የተሳኩና ያልተሳኩ ተሞክሮዎችን በማየት ሒደቱን በሚገባ መረዳት እንችላለን” ይላሉ። ይኸውም “ፌደራሊዝም በዴሞክራሲያዊ አገሮች አንድነትን ሲያመጣ፣ በኢ-ዴሞክራሲያዊ አገሮች ደግሞ ብተናን ነው ያመጣው” የሚል መደምደሚያ ላይ ይደርሳሉ። አያይዘውም የፖለቲካ ምኅዳር የጠበበት አገር ውስጥ ተራማጅ ሐሳቦች ወደፊት ገፍተው መውጣት ስለማይችሉ የዘውግ ጥያቄዎችን ከማጉላት አልፎ የመገንጠል ዘርን ሊዘራ እንደሚችል ይገልጻሉ።
ይህም ሐሳብ “አገሮች ያለፌደራሊዝም ዴሞክራሲያዊ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ነገር ግን አገሮች ያለ ዴሞክራሲ ፌደራላዊ ሊሆኑ አይችሉም” ወደሚለው ብሉይ አስተሳሰብ ይወስደናል። ከዚህም ተነስተን ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ የፌደራል አስተዳደር ካልሔደች ‘ትበተናለች’ የሚለው ስጋትም እየጨመረ እንጅ እየቀነሰ የሚሔድ አይሆንም የሚል መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን። በሌላ አነጋገር የምሥራቅና መካከለኛው አውሮፓ ጥናት ሊቅ የሆኑት ጅም ሶሮካ እንደሚሉት “የአንድ አገር የፌደራል ሥርዓት በእግሩ የሚቆመው በሕግ የበላይነት [እና ዴሞክራሲ] ላይ እንጅ በኀይልና ጭቆና አይደለም። […] ከታሪክ እንደምንማረውም ያልተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳር የፌደራል ሥርዓት የዘረጉ አገሮችን ለብተና ይዳርጋቸዋል።”
ምንጭ :- ሐዋርያ ጋዜጣ
Filed in: Amharic