>

በ‹‹ሰባራ ወንበር›› እና በ‹‹የፉክክር ቤት›› መካከል ላይ.. .!!!  (በድሉዋቅጅራ) .

በ‹‹ሰባራ ወንበር›› እና በ‹‹የፉክክር ቤት›› መካከል ላይ.. .!!!
 (በድሉዋቅጅራ)
.

.


ከአመት በፊት ‹‹ዴስትኒይ ኢትዮጵያ›› የተባለ ድርጅት የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን ሰብስቦ፣ ሀገራችን በወቅቱ የምትገኝበትን ሁኔታ መሰረት አድርጎ የወደፊት እጣ ፋንታዋን የሚያመላክት ውይይት አድርጎ ነበር፡፡ በውይይቱ መጨረሻ የተደረሰባቸው ሴናሪዎዎች አራት ናቸው፤
.
1. ‹‹ሰባራ ወንበር›› (ለመልካም አስተዳደር ፍላጎት ያለው ግን ተግባራዊ ያልሆነ መንግስት)፣ 2. ‹‹አጼ በጉልበቱ›› (አንባገነን መንግስት)፤
3. ‹‹የፉክክር ቤት›› (ክልሎች ተጠናክረው እርስ በርስ የሚፈታተሹበትና የፌደራል መንግስቱ  የደከመበት)፣
4. ‹‹ንጋት›› (በትክክለኛው መንገድ ላይ የምትገኝ ወደ ዲሞክራሲ የምትጓዝ ሀገር)፡፡
.
በስብሰባው የተሳተፉት የፖለቲካ መሪዎች ሀገራችንን ወደ ‹‹ንጋት›› ለማድረስ ተስማምተው (አጨብጭበው) ተለያዩ፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘው የተስማሙበትን ለህዝባቸው በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት አሳዩ፡፡  . . . ዛሬ ከአንድ አመት በኋላ ሀገራችን በ‹‹ሰባራ ወንበር›› እና ‹‹የፉክክር ቤት›› መካከል ትገኛለች፡፡ አብዛኞቹ የፖለቲካ መሪዎች እንኳን መስማማታቸውን መወያየታቸውን ረስተውታል፡፡
.
አንዳንዶች ‹‹ወደ ፈላጭ ቆራጭ የአምባገነንነት ስርአት እየሄድን ነው›› ይላሉ፤ አይደለም፡፡  የአምባገነንነት ዋናው መገለጫ፣ የመንግስት እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ማለት፣ ዜጎችን አስሮም ይሁን ገድሎ የተናገረውን (ፍላጎቱን) ለመተግበር ያለው ቁርጠኝነት፣ በስልጣኑ ከመጡበት የትኛውንም ሰብአዊ መብት ከዜጎች ላይ ለመግፈፍ ወደኋላ አለማለቱ፣ . .  የመሳሰሉት ናቸው፡፡ አንባገነን መንግስታት ጠንካራ ሰራዊትና የስለላ ድርጅቶች አሏቸው፡፡ ጽዋው ሞልቶ ህዝብ እስኪገነፍል ድረስ ያለ እነሱ ታጣቂ፣ ያለ እነሱ ገዳይ አይኖርም፤ ኮሽ አይልም፡፡
.
አሁን ያለው መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን አያሟላም፡፡ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ታጣቂዎችና ገዳዮች የሌሉበት የሀገሪቱ ክፍል የለም ማለት ይቻላል፡፡ የተናገረውን የማስፈጸም አቅሙ ዜሮ የሚባል ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በፌደራልና በክልል ያሉ ባለስልጣናትና ፖሊሶች ግጭትና ግድያን ሪፖርት ከማድረግ ዘለው፣ ሊቆጣጠሩት አልቻሉም፡፡ ይህ ከመለመዱ የተነሳ ባለስልጣናቱና የጸጥታ አስከባሪው ህግን ማስከበርን የማይመለከታቸው ጉዳይ አድርገው ቆጥረውታል፡፡ ህጻናትና እናቶች በግፍ በተገደሉበት ቀን ጠዋት ተነስተው ስራ ይገባሉ፤ ስብሰባ ይሰበሰባሉ፤ የመሰረት ድንጋይ ያኖራሉ፤ የምረቃ ሪቫን ይቆርጣሉ፡፡ . . . ይህ ዋናው ‹‹የሰባራ ወንበር›› ሴናሪዎ ባህርይ ነው፤ የማስፈጸም አቅም ማጣት (ይህ ደግሞ ካለመቻል ወይም ካለመፈለግ ሊመነጭ ይችላል)፡፡
.
መንግስት አንድን ህገወጥ ተግባር መቆጣጠር ባልቻለ ቁጥር የህግ አፍራሾቹ ጉልበት እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ በአንጻሩ መንግስት እየደከመ፣ እየደከመ እንደማያስቀምጥ ሰባራ ወንበር ይሆናል፡፡ አንድ ቀን ጉልበቱ ዝሎ ልቀመጥ ሲል ነው ወንበሩ እንደተሰበረ የሚያውቀው፤ይዞት ሲወድቅ፡፡ ዛሬ ወደዚያ እየገሰገስን ነው፡፡
.
የፌደራል መንግስት የማስፈጸም አቅም ማነስ የክልሎችን አቅም ያጎለብታል፤ የፌደራሉን መንግስት ስራ እየሸራረፉ መውሰድ ይጀምራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ‹‹የፉክክር ቤት›› ሴናሪዮ የሚወስድ መንገድ ነው፡፡ ዛሬ ክልሎች በአስተዳደር ወሰናቸው ከሚፈጸመው ግድያና ግፍ በላይ በተጎጂ ክልሎች ጥቃቱ እንዲቆም የሚቀርበው ጥያቄ የቃላት አመራረጥና አቀራረብ ያስቆጣቸዋል፡፡ የፌደራሉ መንግስት በየክልሉ የሚፈጸሙትን ግድያዎችና ህገወጥ ተግባራት ሙሉ በሙሉ ማስቆም ባለመቻሉ፣ ክልሎች ጡንቻቸውን አጠንክረው እራሳቸውን ለመከላከል እየተጣደፉ ነው፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ‹‹የፉክክር ቤት›› ሴናሪዮ ዋና መገለጫ፡፡ . . .  በነገራችን ላይ እነዚህ ሁለት ሴናሪዮዋች ከአንባገነንነት በላይ ሀገር አፍራሾች ናቸው፡፡ መሪን በማስወገድ አንባገነንነትን መታደግ ይቻላል፡፡ ሁለቱ ግን ጦሳቸው ሀገርን እስከማፍረስ ይደርሳል፡፡
.
እንግዲህ ዛሬ ምርጫ የምንመዘገበው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነው፡፡ በዚህ ሰላም ጠፍቶ፣ ግድያና መፈናቀል አዘቦታዊ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ውጤቱ በተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሁሉ ተቀባይነት ያለው ሰላማዊ ምርጫ የማድረግ እድላችን ጠባብ ነው፡፡ ከምርጫው ወደ ‹‹ንጋት›› ሊያራምድ የሚችል ፋይዳ ያለው ነገር እናገኝ ዘንድ፣ የፌደራሉ መንግስት ከክልል አመራሮች ጋር በወጥነት ተቀናጅቶ ግድያን ማስቆምንና ህግን ማስከበርን ተቀዳሚ ተግባሩ ማድረግ አለበት፡፡
Filed in: Amharic